ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ይሰማሃል?
የዓለማችን ሁኔታ ምን የሚሆን ይመስልሃል?
-
ባለበት የሚቀጥል?
-
እየተባባሰ የሚሄድ?
-
ወይስ እየተሻሻለ የሚሄድ?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“እሱም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:3, 4 አዲስ ዓለም ትርጉም
ይህን ማወቅህ ለአንተ ምን ጥቅም አለው?
ትርጉም ያለውና አርኪ ሥራ ይኖርሃል።—ኢሳይያስ 65:21-23
ከሕመምና ከመከራ ነፃ የሆነ ሕይወት ይኖርሃል።—ኢሳይያስ 25:8፤ 33:24
ከቤተሰብህና ከወዳጆችህ ጋር ለዘላለም በደስታ ትኖራለህ።—መዝሙር 37:11, 29
መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው ነገር ላይ እምነት መጣል እንችላለን?
አዎ፣ ቢያንስ ሁለት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፦
-
አምላክ የገባውን ቃል የመፈጸም ችሎታ አለው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ሁሉን ቻይ” ተብሎ የተጠራው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም እሱ ገደብ የለሽ ኃይል አለው። (ራእይ 15:3) በመሆኑም ዓለማችንን እንደሚለውጥ የገባውን ቃል መፈጸም ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “በአምላክ ዘንድ . . . ሁሉ ነገር ይቻላል።”—ማቴዎስ 19:26
-
አምላክ የገባውን ቃል ለመፈጸም ፍላጎቱ አለው። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን ለማስነሳት ‘ይናፍቃል።’—ኢዮብ 14:14, 15
በተጨማሪም የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ የታመሙትን እንደፈወሰ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? ሰዎችን የመርዳት ፍላጎት ስላለው ነው። (ማርቆስ 1:40, 41) ኢየሱስ ችግር ላይ የወደቁትን የመርዳት ልባዊ ፍላጎት ያለው መሆኑ የአባቱን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ እንዳንጸባረቀ ያሳያል።—ዮሐንስ 5:19
በመሆኑም ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ የወደፊቱ ጊዜ አስደሳች እንዲሆንልን የሚፈልጉ መሆናቸውን እርግጠኞች መሆን እንችላለን! —መዝሙር 72:12-14፤ 145:16፤ 2 ጴጥሮስ 3:9
ምን ይመስልሃል?
አምላክ ዓለማችን የተሻለች እንድትሆን የሚያደርገው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ ማቴዎስ 6:9, 10 እና ዳንኤል 2:44 ላይ ይገኛል።