በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በፈጠርሁት ለዘላለም ደስ ይበላችሁ’

‘በፈጠርሁት ለዘላለም ደስ ይበላችሁ’

ምዕራፍ ሃያ ስድስት

‘በፈጠርሁት ለዘላለም ደስ ይበላችሁ’

ኢሳይያስ 65:​1-25

1. ሐዋርያው ጴጥሮስ የትኞቹን አጽናኝ ቃላት ጽፏል? ምን ጥያቄስ ይነሳል?

 መከራና ግፍ የሚያከትምበት ዘመን ይመጣ ይሆን? ሐዋርያው ጴጥሮስ ከ1, 900 ዓመታት በፊት የሚከተሉትን አጽናኝ ቃላት ጽፎ ነበር:- “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ [አምላክ በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት] እንጠብቃለን።” (2 ጴጥሮስ 3:13) ባለፉት ብዙ መቶ ዘመናት ጴጥሮስም ሆነ ሌሎች በርካታ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ሕገ ወጥነት፣ ጭቆናና ዓመፅ የሚወገዱበትንና በምትኩ ጽድቅ የሚሰፍንበትን ይህን ታላቅ ቀን በጉጉት ሲጠባበቁ ኖረዋል። ይህ ተስፋ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

2. ስለ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” የተናገረው ነቢይ ማን ነው? ከብዙ ዘመናት በፊት የተነገረው ይህ ትንቢት ምን ፍጻሜዎች አሉት?

2 አዎን፣ እርግጠኞች መሆን እንችላለን! ጴጥሮስ ስለ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” የተናገረው ሐሳብ አዲስ ነገር አልነበረም። ወደ 800 የሚጠጉ ዓመታት ቀደም ብሎ ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ተመሳሳይ ቃል ተናግሮ ነበር። ይህ ቀደም ሲል የተነገረው ቃል በ537 ከዘአበ አይሁዳውያን ከባቢሎን ግዞት ተላቅቀው ወደ ትውልድ አገራቸው በተመለሱበት ጊዜ በተወሰነ ደረጃ ፍጻሜውን አግኝቷል። ይሁን እንጂ የኢሳይያስ ትንቢት በዘመናችን ታላቅ ፍጻሜውን በማግኘት ላይ ሲሆን አምላክ በቅርቡ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ይበልጥ አስደሳች በሆነ መንገድ የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን። በእርግጥም በኢሳይያስ በኩል የተነገረው እጅግ የሚያስደስት ትንቢት አምላክ ለሚወዱት ሰዎች ያዘጋጃቸውን በረከቶች በተመለከተ ጥሩ ፍንጭ ይሰጠናል።

ይሖዋ እጁን ወደ “ዓመፀኛ ሕዝብ” ዘረጋ

3. የ⁠ኢሳይያስ መጽሐፍ 65ኛ ምዕራፍ ለየትኛው ጥያቄ መልስ ይሰጠናል?

3 ኢሳይያስ በባቢሎን በግዞት የሚኖሩትን አይሁዳውያን ወክሎ ያቀረበው ትንቢታዊ ጸሎት በ⁠ኢሳይያስ 63:​15–64:​12 ላይ ሰፍሮ እንደሚገኝ አስታውስ። ኢሳይያስ በግልጽ እንደተናገረው ብዙዎቹ አይሁዳውያን ይሖዋን በሙሉ ነፍሳቸው ባያመልኩትም ንስሐ የገቡና ወደ አምላካቸው የተመለሱ የተወሰኑ አይሁዳውያን ነበሩ። ይሖዋ ንስሐ ለገቡት ቀሪዎች ሲል ሕዝቡን ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ይመልሰው ይሆን? የ⁠ኢሳይያስ መጽሐፍ 65⁠ኛ ምዕራፍ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ታማኝ ለሆኑት ጥቂት ሰዎች የመዳን ተስፋ ቃል ከመናገሩ በፊት እምነት የለሽ የሆኑት በርካታ አይሁዳውያን የሚጠብቃቸውን ፍርድ ገለጸ።

4. (ሀ) ዓመፀኛ በሆኑት ሕዝቦቹ ፋንታ ይሖዋን የሚፈልጉት እነማን ናቸው? (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ ኢሳይያስ 65:​1, 2ን የተጠቀመበት እንዴት ነው?

4 ይሖዋ በዓመፅ ድርጊታቸው የገፉትን ሕዝቦቹን ቢታገሳቸውም እንኳ እነሱን ለጠላቶቻቸው አሳልፎ በመስጠት ለሌሎች ሞገሱን የሚያሳይበት ጊዜ ይመጣል። ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል እንዲህ አለ:- “ላልጠየቁኝ ተገለጥሁ፣ ላልፈለጉኝም ተገኘሁ፤ በስሜም ያልተጠራውን [“ስሜን ላልጠራ፣” አ.መ.ት ] ሕዝብ:- እነሆኝ፣ እነሆኝ አልሁት።” (ኢሳይያስ 65:1) ይህ የይሖዋን የቃል ኪዳን ሕዝብ አስመልክቶ የተሰጠ አሳዛኝ መግለጫ ሲሆን ከአሕዛብ የተውጣጡ ሰዎች ወደ ይሖዋ ሲመጡ ዓመፀኛ የሆነው የይሁዳ ሕዝብ ግን በብሔር ደረጃ ወደ ይሖዋ ለመመለስ አሻፈረኝ እንደሚል ያሳያል። አምላክ ውሎ አድሮ ቀደም ሲል የማይታወቅን አዲስ ሕዝብ እንደሚመርጥ የተነበየው ኢሳይያስ ብቻ አይደለም። (ሆሴዕ 1:​10፤ 2:​23) ሐዋርያው ጳውሎስ ከአሕዛብ የተውጣጡ ሰዎች፣ ሥጋዊ አይሁዳውያን ለመቀበል አሻፈረኝ ያሉትን “ከእምነት የሆነ ጽድቅ” እንደሚያገኙ ለማስረዳት ኢሳይያስ 65:​1, 2ንሰፕቱጀንት ላይ ጠቅሶ ጽፏል።​—⁠ሮሜ 9:​30፤ 10:​20, 21

5, 6. (ሀ) ይሖዋ ምን ልባዊ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል? ሆኖም ሕዝቡ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ከይሁዳ ጋር ከነበረው ግንኙነት ምን ልንማር እንችላለን?

5 ይሖዋ ሕዝቡ መከራ እንዲደርስባቸው የሚፈቅድበትን ምክንያት እንዲህ ሲል ገለጸ:- “መልካም ባልሆነው መንገድ፣ አሳባቸውን እየተከተሉ፣ ወደሚሄዱ ወደ ዓመፀኛ ሕዝብ ቀኑን ሁሉ እጆቼን ዘረጋሁ።” (ኢሳይያስ 65:2) እጆችን መዘርጋት ግብዣን ወይም ልመናን ያመለክታል። ይሖዋ እጆቹን የዘረጋው ለአጭር ጊዜ ሳይሆን ቀኑን ሙሉ ነው። ይሁዳ ወደ እሱ እንድትመለስ ከልብ የመነጨ ፍላጎት አለው። ይሁንና ይህ ዓመፀኛ ሕዝብ ወደ ይሖዋ ለመመለስ ፈቃደኛ ሆኖ አልተገኘም።

6 ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት አንድ እጅግ አስደሳች የሆነ እውነታ እንድንገነዘብ ያደርጉናል! ይሖዋ በቀላሉ የሚቀረብ አምላክ በመሆኑ ወደ እሱ እንድንቀርብ ይፈልጋል። (ያዕቆብ 4:​8) በተጨማሪም እነዚህ ቃላት ይሖዋ ትሑት መሆኑን ይጠቁሙናል። (መዝሙር 113:​5, 6) የሕዝቡ ግትርነት ‘እጅግ እንዲያዝን’ ቢያደርገውም እጁን ዘርግቶ ወደ እሱ እንዲመለሱ ሲማጸናቸው ቆይቷል። (መዝሙር 78:​40, 41) ለጠላቶቻቸው አሳልፎ የሚሰጣቸው ለብዙ ዘመናት ሲማጸናቸው ከኖረ በኋላ ነው። በዚያን ጊዜም እንኳ ቢሆን በመካከላቸው ያሉትን ትሑት ግለሰቦች ለመቀበል ፈቃደኛ ነው።

7, 8. ዓመፀኛ የሆኑት የይሖዋ ሕዝቦች አምላክን ያስቆጡት በምን መንገዶች ነው?

7 ዓመፀኛ የሆኑት አይሁዳውያን ወራዳ በሆነው ምግባራቸው ይሖዋን በተደጋጋሚ ጊዜያት አስቆጥተውታል። ይሖዋ ጸያፍ ድርጊቶቻቸውን እንዲህ ሲል ገለጸ:- “ይህ ሕዝብ ዘወትር [“በፊቴ፣” አ.መ.ት ] የሚያስቈጡኝ ናቸው፤ እነርሱ በአትክልት ውስጥ የሚሠዉ በጡብም ላይ የሚያጥኑ፣ በመቃብርም መካከል የሚቀመጡ፣ በስውርም ስፍራ የሚያድሩ፣ የእሪያ ሥጋም የሚበሉ ናቸው። የረከሰው መረቅ በዕቃቸው ውስጥ አለ። እነርሱም:- ለራስህ ቁም፣ እኔ ከአንተ ይልቅ ቅዱስ ነኝና ወደ እኔ አትቅረብ ይላሉ፤ እነዚህ በአፍንጫዬ ዘንድ ጢስ ቀኑንም ሁሉ የምትነድድ እሳት ናቸው።” (ኢሳይያስ 65:3-5) እነዚህ ጻድቅ መስለው የሚታዩ ሰዎች ይሖዋን ‘በፊቱ’ ያስቆጡት ሲሆን ይህም አጉል ድፍረትንና ንቀትን ሊያመለክት ይችላል። ጸያፍ የሆኑ ድርጊቶቻቸውን ለመደበቅ ምንም ያደረጉት ጥረት የለም። እጅግ ሊከበርና ሊፈራ በሚገባው አምላክ ፊት ኃጢአት መፈጸም ትልቅ ጥፋት አይደለምን?

8 እነዚህ ራሳቸውን የሚያመጻድቁ ኃጢአተኞች ሌሎች አይሁዳውያንን ‘ከእናንተ ይበልጥ ቅዱስ ስለሆንን አትቅረቡን’ ይሉ ነበር። እንዴት ያለ ግብዝነት ነው! እነዚህ ‘ጻድቅ ነን ባዮች’ የአምላክን ሕግ በመጻረር ለሐሰት አማልክት መሥዋዕት ያቀርቡ የነበረ ከመሆኑም በላይ ዕጣን ያጥኑ ነበር። (ዘጸአት 20:​2-6) በመቃብር መካከል የሚቀመጡ ሲሆን ይህ ደግሞ በሙሴ ሕግ መሠረት የሚያረክስ ነበር። (ዘኍልቁ 19:​14-16) ከዚህም በተጨማሪ ርኩስ የሆነውን የእሪያ ሥጋ ይበላሉ። a (ዘሌዋውያን 11:​7) ሆኖም እንዲህ ያሉትን ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በመፈጸማቸው ከሌሎቹ አይሁዶች ይበልጥ ቅዱስ እንደሆኑ አድርገው ያስቡ የነበረ ሲሆን ሌሎች ሰዎች ከእነርሱ ጋር በመቀራረብ ብቻ ይቀደሱ ወይም ይነጹ ይመስል አጠገባቸው እንዳይደርሱ ይከለክሏቸው ነበር። ይሁንና “ለእሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ” [NW ] እንዲቀርብለት የሚፈልገው ይሖዋ ያለው አመለካከት ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው!​—⁠ዘዳግም 4:​24

9. ይሖዋ ራሳቸውን የሚያመጻድቁትን ኃጢአተኞች የተመለከታቸው እንዴት ነው?

9 ይሖዋ እነዚህን ራሳቸውን የሚያመጻድቁ ሰዎች ቅዱስ አድርጎ አልተመለከታቸውም። ከዚህ ይልቅ “እነዚህ በአፍንጫዬ ዘንድ ጢስ” ናቸው ብሏል። ‘አፍንጫ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ቃል ብዙውን ጊዜ በምሳሌያዊ ሁኔታ ቁጣን ለማመልከት ይሠራበታል። ጢስም ቢሆን የሚነድደውን የይሖዋ ቁጣ ለማመልከት ይጠቀሳል። (ዘዳግም 29:​20) ሕዝቡ ይፈጽሙት የነበረው ጸያፍ የጣዖት አምልኮ የይሖዋን የሚነድድ ቁጣ ቀስቅሷል።

10. ይሖዋ ኃጢአት የፈጸሙትን አይሁዳውያን መልሶ ዋጋቸውን የሚከፍላቸው እንዴት ነው?

10 በይሖዋ የፍትሕ ሥርዓት መሠረት እያወቁ እንዲህ ያለውን ኃጢአት ይፈጽሙ የነበሩት ሰዎች ከቅጣት ሊያመልጡ አይችሉም። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጻፈ:- “እነሆ፣ በፊቴ ተጽፎአል:- ኃጢአታችሁንና የአባቶቻችሁን ኃጢአት በአንድ ላይ ወደ ብብታቸው [“እቅፋቸው፣” NW ] ፍዳ አድርጌ እመልሳለሁ እንጂ ዝም አልልም፣ ይላል እግዚአብሔር፤ በተራሮችም ላይ ስላጠኑ፣ በኮረብቶችም ላይ ስለ ሰደቡኝ፣ ስለዚህ አስቀድመው የሠሩትን ሥራቸውን በብብታቸው [“በእቅፋቸው፣” NW ] እሰፍራለሁ።” (ኢሳይያስ 65:6, 7) አይሁዳውያን በሐሰት አምልኮ በመካፈል ይሖዋን ሰድበዋል። የእውነተኛው አምላክ አምልኮ በዙሪያቸው ካሉት አሕዛብ አምልኮ ምንም የማይሻል መስሎ እንዲታይ አድርገዋል። ይሖዋ የጣዖት አምልኮንና መናፍስታዊ ድርጊቶችን ጨምሮ የፈጸሟቸውን ‘ኃጢአቶች’ ፍዳ አድርጎ “ወደ እቅፋቸው” ይመልሰዋል። እዚህ ላይ የገባው ‘እቅፍ’ የሚለው ቃል አንድን ነገር ለመቀበል ከላይ የለበሱትን ልብስ ወደ ላይ አጥፎ መያዝን የሚያመለክት ሲሆን ይህም እያዞሩ የሚሸጡ ነጋዴዎች የተሰፈረን ምርት ሊከቱበት የሚችል ከረጢት ሆኖ ያገለግላል። (ሉቃስ 6:​38) ለከሃዲዎቹ አይሁዳውያን መልእክቱ ግልጽ ነበር። ይሖዋ ‘ፍዳቸውን’ ወይም ቅጣታቸውን ሰፍሮ ይሰጣቸዋል። የፍትሕ አምላክ እንደመሆኑ መጠን ተገቢውን ቅጣት ሳይሰጥ አያልፍም። (መዝሙር 79:​12፤ ኤርምያስ 32:​18) ይሖዋ የማይለወጥ በመሆኑ እሱ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይም ተገቢውን ቅጣት እንደሚያስፈጽም እርግጠኞች መሆን እንችላለን።​—⁠ሚልክያስ 3:​6

‘ስለ ባሪያዎቼ ስል’

11. ይሖዋ ታማኝ ቀሪዎችን እንደሚያድን ያመለከተው እንዴት ነው?

11 ይሖዋ በሕዝቡ መካከል ላሉት ታማኝ አገልጋዮቹ ምሕረት ያሳይ ይሆን? ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ወይን በዘለላው በተገኘች ጊዜ:- በረከት በእርስዋ ላይ አለና አታጥፉት እንደሚባለው፣ ሁሉን እንዳላጠፋ ስለ ባሪያዎቼ እንዲሁ አደርጋለሁ። ከያዕቆብም ዘርን ከይሁዳም ተራሮቼን የሚወርሰውን አወጣለሁ፤ እኔም የመረጥኋቸው ይወርሱአታል፣ ባሪያዎቼም በዚያ ይኖራሉ።” (ኢሳይያስ 65:8, 9) ይሖዋ ሕዝቡን ከወይን ዘለላ ጋር በማመሳሰል በቀላሉ ሊረዱት የሚችሉትን ምሳሌ ተጠቅሟል። ወይን በምድሪቱ እንደ ልብ የሚገኝ ፍሬ ሲሆን ከዚህ ፍሬ የሚገኘው ወይን ጠጅ ለሰው ልጆች ጠቃሚ ነው። (መዝሙር 104:​15) እዚህ ላይ ከተጠቀሰው የወይን ዘለላ መካከል ጥሩ የሆነው ከፊሉ ብቻ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ አንዱ ዘለላ ጥሩ ሆኖ የተቀሩት ዘለላዎች ያልበሰሉ ወይም የበሰበሱ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚያም ሆነ በዚህ የወይኑ ገበሬ ጥሩውን የወይን ፍሬ እንደማያጠፋው የታወቀ ነው። በዚህ መንገድ ይሖዋ ብሔሩን ሙሉ በሙሉ እንደማያጠፋ ከዚህ ይልቅ ታማኝ ቀሪዎችን ከጥፋት እንደሚያተርፍ ለሕዝቡ ማረጋገጫ ሰጥቷል። ሞገሱን የሚያሳያቸው እነዚህ ቀሪዎች ‘ተራሮቹን’ ማለትም ይሖዋ የራሱ አድርጎ የገለጸውን ኮረብታማውን የይሁዳ ምድርና ኢየሩሳሌምን እንደሚወርሱ ገልጿል።

12. ታማኞቹ ቀሪዎች ምን በረከቶች ይጠብቋቸዋል?

12 እነዚህ ታማኝ ቀሪዎች ምን በረከቶች ይጠብቋቸዋል? ይሖዋ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ሳሮንም የበጎች ማሰማርያ፣ የአኮርም ሸለቆ የላሞች መመሰግያ ለፈለጉኝ ሕዝቤ ይሆናል።” (ኢሳይያስ 65:10) የከብት መንጎች በብዙዎቹ አይሁዳውያን ኑሮ ውስጥ ትልቅ ድርሻ የነበራቸው በመሆኑ በሰላም ዘመን ለግጦሽ የሚሆን መሬት እንደ ልብ መኖሩ ብልጽግና ያስገኛል። ይሖዋ ሰላምንና ብልጽግናን ለማመልከት ሲል በሁለት የተለያዩ የምድር ጽንፎች የሚገኙ ቦታዎችን ጠቅሷል። በምዕራብ በኩል በሜዲትራኒያን የባሕር ዳርቻ በውበቱና በልምላሜው የሚታወቀው የሳሮን ሜዳ ተንጣልሎ ይገኛል። የአኮር ሸለቆ ደግሞ በአገሪቱ ሰሜናዊ ምሥራቅ ዳርቻ ይገኛል። (ኢያሱ 15:​7) አይሁዳውያን ወደ ግዞት በሚወሰዱበት ጊዜ እንደተቀረው የምድሪቱ ክፍል ሁሉ እነዚህ ቦታዎችም ባድማ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ አይሁዳውያን ቀሪዎች ከግዞት ሲመለሱ እነዚህ ቦታዎች ውብ የከብቶች ማሰማሪያ እንደሚሆኑ ይሖዋ ቃል ገብቷል።​—⁠ኢሳይያስ 35:​2፤ ሆሴዕ 2:​15

‘እድል በተባለ ጣዖት’ መታመን

13, 14. የአምላክ ሕዝቦች ይሖዋን እንደተዉ የሚያሳዩ ምን ልማዶችን ይፈጽሙ ነበር? በዚህስ ሳቢያ ምን ይደርስባቸዋል?

13 በመቀጠል የኢሳይያስ ትንቢት ይሖዋን በመተው ፊታቸውን ወደ ጣዖት አምልኮ ያዞሩትንና ለመመለስ አሻፈረኝ ያሉትን ሰዎች በማስመልከት እንዲህ ይላል:- “እናንተን ግን እግዚአብሔርን የተዋችሁትን፣ ቅዱሱንም ተራራዬን የረሳችሁትን፣ ጉድ [“ዕጣ ፈንታ፣” አ.መ.ት ] ለተባለ ጣዖትም ማዕድ ያዘጋጃችሁትን፣ እድል ለተባለ ጣዖትም የወይን ጠጅ [“ድብልቅ የወይን ጠጅ፣” አ.መ.ት ] ለመጠጥ ቁርባን የቀዳችሁትን።” (ኢሳይያስ 65:11) ወደ ኃጢአት ድርጊት የተመለሱት አይሁዳውያን ‘ዕጣ ፈንታ በተባለ ጣዖትና እድል በተባለ ጣዖት’ ፊት ማዕድና መጠጥ በማቅረብ በአረማውያን የጣዖት አምልኮ ልማዶች ተሸንፈው ወድቀዋል። b በእነዚህ አማልክት በመታመን ጥበብ የጎደለው ድርጊት የሚፈጽም ሰው ምን ይገጥመዋል?

14 ይሖዋ የሚከተለውን ቀጥተኛ የሆነ ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው:- “እድላችሁን ለሰይፍ አደርገዋለሁ፣ ሁላችሁም ለመታረድ ትጐነበሳላችሁ፤ በፊቴም ክፉ ነገርን አደረጋችሁ፣ ያልወደድሁትንም መረጣችሁ እንጂ በጠራሁ ጊዜ አልመለሳችሁልኝምና፣ በተናገርሁም ጊዜ አልሰማችሁኝምና።” (ኢሳይያስ 65:12) ይሖዋ በዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ ላይ የእድል አምላክን ለማመልከት የገባውን ያንኑ ቃል በመጠቀም ይህን የሐሰት አምላክ የሚያመልኩ ሰዎችን ‘እድላቸውን ለሰይፍ እንደሚያደርገው’ ማለትም እንደሚያጠፋቸው ገልጿል። ይሖዋ እነዚህ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ በነቢያቱ በኩል በተደጋጋሚ ቢያሳስባቸውም ማሳሰቢያውን ችላ ብለው በግትርነት እያወቁ በይሖዋ ፊት ክፉ የሆነውን ነገር መሥራት መርጠዋል። ይህም ለአምላክ ያላቸውን ከፍተኛ ንቀት የሚያሳይ ነው! አምላክ አስቀድሞ በሰጠው ማስጠንቀቂያ መሠረት ይሖዋ በ607 ከዘአበ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን እንዲያጠፉ በሚፈቅድበት ጊዜ ሕዝቡ ታላቅ እልቂት ይደርስበታል። በዚያን ጊዜ ‘እድል የተባለው ጣዖት’ በይሁዳና በኢየሩሳሌም የሚገኙ ቀናተኛ አምላኪዎቹን ሊታደጋቸው አይችልም።​—⁠2 ዜና መዋዕል 36:​17

15. በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች በ⁠ኢሳይያስ 65:​11, 12 ላይ የሚገኘውን ማስጠንቀቂያ በተግባር ላይ የሚያውሉት እንዴት ነው?

15 በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች በ⁠ኢሳይያስ 65:​11, 12 ላይ የሚገኘውን ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ ያደርጋሉ። ጥሩ ገድ እንዲገጥመን ሊያደርግ የሚችል ከሰው በላይ የሆነ ኃይል እንዳለ አድርገው አያምኑም። ‘እድል የተባለውን ጣዖት’ ለማስደሰት ሲሉ ቁሳዊ ንብረታቸውን አያፈስሱም። በመሆኑም ከማንኛውም ዓይነት ቁማር ይርቃሉ። ይሖዋ እነዚህን ሰዎች አስመልክቶ “እድላችሁን ለሰይፍ አደርገዋለሁ” ሲል የተናገረ በመሆኑ ለዚህ ጣዖት ያደሩ ሰዎች በመጨረሻ ሁሉንም ነገር እንደሚያጡ እርግጠኞች ናቸው።

“እነሆ፣ ባሪያዎቼ ደስ ይላቸዋል”

16. ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን የሚባርከው በምን መንገዶች ነው? እሱን የተዉ ሰዎችስ ምን ይደርስባቸዋል?

16 ትንቢቱ ይሖዋን የተዉትን ሰዎች በመውቀስ አምላክን ከልብ በመነጨ መንፈስ የሚያመልኩና በግብዝነት የሚያመልኩ ሰዎች የሚገጥማቸውን ዕጣ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- እነሆ፣ ባሪያዎቼ ይበላሉ እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ እነሆ፣ ባሪያዎቼ ይጠጣሉ እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤ እነሆ፣ ባሪያዎቼ ደስ ይላቸዋል እናንተ ግን ታፍራላችሁ፤ እነሆ፣ ባሪያዎቼ ከልባቸው ደስታ የተነሣ ይዘምራሉ፣ እናንተ ግን ከልባችሁ ኀዘን የተነሣ ትጮኻላችሁ፣ መንፈሳችሁም ስለ ተሰበረ ወዮ ትላላችሁ።” (ኢሳይያስ 65:13, 14) ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ይባርካል። ልባቸው በሐሴት ተሞልቶ ይዘምራሉ። እዚህ ላይ የተጠቀሱት መብል፣ መጠጥና ደስታ ይሖዋ አምላኪዎቹ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች አትረፍርፎ እንደሚሰጣቸው የሚያመለክቱ ቃላት ናቸው። በአንጻሩ ደግሞ ይሖዋን ለመተው የመረጡ ሰዎች በመንፈሳዊ ይራባሉ እንዲሁም ይጠማሉ። የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች አያገኙም። በሚደርስባቸው መከራና ችግር ምክንያት ይጮኻሉ እንዲሁም ወዮ ይላሉ።

17. በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች በደስታ የሚዘምሩበት በቂ ምክንያት አላቸው የምንለው ለምንድን ነው?

17 ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት በዛሬው ጊዜ ያሉ አምላክን እናገለግላለን የሚሉ ሰዎች የሚገኙበትን መንፈሳዊ ሁኔታ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። በሚልዮን የሚቆጠሩት የሕዝበ ክርስትና ተከታዮች መንፈሳቸው የተሰበረ ሲሆን የይሖዋ አምላኪዎች ግን በደስታ ይዘምራሉ። የሚደሰቱትም እንዲሁ አለምክንያት አይደለም። በመንፈሳዊ በሚገባ እየተመገቡ ነው። ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎችና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አማካኝነት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርብላቸዋል። በእርግጥም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት የሚያንጹ እውነቶችና አጽናኝ ተስፋዎች ‘ልባችንን በደስታ’ ያስፈነድቁታል!

18. ከይሖዋ የራቁ ሰዎች ትተውት የሚያልፉት ነገር ምንድን ነው? ስማቸው በእርግማን መጠቀሱ ምን ነገርን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል?

18 ይሖዋ በመቀጠል እሱን የተዉትን ሰዎች እንዲህ አለ:- “ስማችሁንም ለተመረጡት ሕዝቤ እርግማን አድርጋችሁ ትተዋላችሁ፣ ጌታ እግዚአብሔርም ይገድላችኋል፣ ባሪያዎቹንም በሌላ ስም ይጠራቸዋል። እንዲሁም በምድር ላይ የተባረከ በእውነት አምላክ ይባረካል፣ በምድርም ላይ የማለ በእውነት አምላክ ይምላል፤ የቀድሞው ጭንቀት ተረስቶአልና፣ ከዓይኔም ተሰውሮአልና።” (ኢሳይያስ 65:15, 16) ይሖዋን የተዉት ሰዎች ትተውት የሚያልፉት ነገር ቢኖር በእርግማን ወቅት ብቻ የሚነሳውን ስማቸውን ይሆናል። በሌላ አነጋገር ሰዎች ‘የገባሁትን ቃል ባጥፍ በእነዚያ ከሃዲዎች ላይ የደረሰው ቅጣት በእኔም ላይ ይድረስ’ ይላሉ እንደ ማለት ነው። አልፎ ተርፎም ስማቸው ልክ እንደ ሰዶምና ገሞራ አምላክ በክፉዎች ላይ ለሚወስደው የቅጣት እርምጃ ተምሳሌት ሆኖ ያገለግላል ማለትም ሊሆን ይችላል።

19. የአምላክ አገልጋዮች በሌላ ስም መጠራታቸው ምን ያመለክታል? በእውነት አምላክ ላይ ሙሉ እምነታቸውን የሚጥሉትስ ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

19 የአምላክ አገልጋዮች የሚገጥማቸው ዕጣ ግን ከዚህ ፍጹም የተለየ ነው! በሌላ ስም ይጠራሉ። ይህም ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ የሚያገኙትን በረከትና ክብር ያመለክታል። የሌላ የማንኛውንም የሐሰት አምላክ በረከት አይሹም ወይም በድን በሆነ ጣዖት አይምሉም። ከዚህ ይልቅ ራሳቸውን የሚባርኩት ወይም መሐላ የሚገቡት በእውነት አምላክ ይሆናል። ይሖዋ ቃሉን የሚጠብቅ አምላክ መሆኑን በተግባር ያሳየ በመሆኑ የምድሪቱ ነዋሪዎች በእሱ ላይ ሙሉ በሙሉ የሚተማመኑበት በቂ ምክንያት አላቸው። c በትውልድ አገራቸው ከስጋት ነፃ ሆነው ስለሚኖሩ የቀድሞውን መከራና ችግር ወዲያውኑ ይረሱታል።

“አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እየፈጠርኩ ነው”

20. ይሖዋ ‘አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርን’ አስመልክቶ የገባው ቃል በ537 ከዘአበ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

20 ይሖዋ በመቀጠል ከባቢሎን ግዞት የሚመለሱትን ንስሐ የገቡ ቀሪዎች መልሶ እንደሚያቋቁም የገባውን ቃል ይበልጥ ግልጽ አደረገ። በኢሳይያስ በኩል እንዲህ ሲል ተናገረ:- “እነሆ፣ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና [“እየፈጠርኩ ነው፣” NW ]፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም።” (ኢሳይያስ 65:17) ይሖዋ ሕዝቡን መልሶ እንደሚያቋቁም የተናገረው ቃል መፈጸሙ የማይቀር በመሆኑ ወደፊት የሚሆነውን ነገር ልክ እየተፈጸመ እንዳለ አድርጎ ተናግሯል። ይህ ትንቢት በ537 ከዘአበ የአይሁድ ቀሪዎች ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሱ ጊዜ የመጀመሪያ ፍጻሜውን አግኝቷል። በዚያን ጊዜ ‘በአዲስ ሰማይ’ የተወከለው ማን ነው? ኢየሩሳሌምን ማዕከል ያደረገውና በሊቀ ካህናቱ ኢያሱ ይታገዝ የነበረው የዘሩባቤል መስተዳድር ነው። ከግዞት የተመለሱት አይሁዳውያን ቀሪዎች “አዲስ ምድር” ሆነዋል። ይህም ለዚህ መስተዳድር ራሱን ያስገዛውንና ንጹሑን አምልኮ በምድሪቱ ላይ መልሶ ለማቋቋም የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደረገውን ንጹሕ ኅብረተሰብ ያመለክታል። (ዕዝራ 5:​1, 2) ይህ ተሃድሶ የፈጠረው ደስታ ቀደም ሲል የደረሰባቸውን መከራም ሆነ ችግር እንዲረሱና እንዳያስቡት አድርጓቸዋል።​—⁠መዝሙር 126:​1, 2

21. በ1914 እውን የሆነው አዲስ ሰማይ ምንድን ነው?

21 ይሁን እንጂ ጴጥሮስ የኢሳይያስን ትንቢት መልሶ በማስተጋባት ወደፊት ሌላ ፍጻሜ እንደሚያገኝ ማመልከቱን አስታውስ። ሐዋርያው እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።” (2 ጴጥሮስ 3:13) በ1914 ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የኖረው አዲስ ሰማይ እውን ሆነ። በዚያ ዓመት የተወለደው መሲሐዊው መንግሥት ከሰማይ ሆኖ የሚገዛ ሲሆን ይሖዋ በምድር ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቶታል። (መዝሙር 2:​6-8) አዲሱ ሰማይ በክርስቶስና በ144, 000 ተባባሪ ገዥዎቹ የሚተዳደረው ይህ ንጉሣዊ መንግሥት ነው።​—⁠ራእይ 14:​1

22. የአዲሱ ምድር አባላት የሚሆኑት እነማን ናቸው? ሰዎች የአዲሱ ምድር መሠረት ለመሆን በአሁኑ ጊዜም እንኳ እየተዘጋጁ ያሉት እንዴት ነው?

22 አዲሱ ምድርስ? በጥንት ዘመን ከተፈጸመው ሁኔታ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ለአዲሱ ሰማያዊ መንግሥት አገዛዝ ራሳቸውን በፈቃደኝነት የሚያስገዙ ሰዎች የአዲሱ ምድር አባላት ይሆናሉ። በአሁኑ ጊዜም እንኳ በሚልዮን የሚቆጠሩ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ለዚህ መንግሥት ራሳቸውን በማስገዛት ላይ ከመሆናቸውም በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን የዚህ መንግሥት ሕጎች ለመከተል በመጣር ላይ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከሁሉም ብሔራት፣ ቋንቋዎችና ዘሮች የተውጣጡ ሲሆን በመግዛት ላይ ያለውን ንጉሡን ኢየሱስ ክርስቶስን በአንድነት እያገለገሉ ነው። (ሚክያስ 4:​1-4) በአሁኑ ጊዜ ያለው ክፉ ሥርዓት ከጠፋ በኋላ እነዚህ ሰዎች ውሎ አድሮ የአዲሱ ምድር ማለትም የአምላክን መንግሥት ምድራዊ ግዛት የሚሞላው ፈሪሃ አምላክ ያለው ዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ መሠረት ይሆናሉ።​—⁠ማቴዎስ 25:​34

23. በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ‘አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርን’ አስመልክቶ ምን የተጠቀሰ ነገር አለ? ይህ ትንቢት ፍጻሜውን የሚያገኘውስ እንዴት ነው?

23 የራእይ መጽሐፍ ይህ ሥርዓት የሚጠፋበትን በቅርቡ የሚመጣውን የይሖዋ ቀን አስመልክቶ ሐዋርያው ዮሐንስ ያየውን ራእይ ይገልጻል። ከዚያ በኋላ ሰይጣን ወደ ጥልቁ ይጣላል። (ራእይ 19:​11–20:​3) ዮሐንስ ይህን መግለጫ ከሰጠ በኋላ የኢሳይያስን ትንቢታዊ ቃላት መልሶ በማስተጋባት “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ” ሲል ጻፈ። በዚህ ታላቅ ራእይ ዘገባ ላይ ቀጥለው የተጠቀሱት ቁጥሮች ይሖዋ አምላክ በዚህ ምድር ላይ ያሉትን ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ የሚለውጥበትና የሚያሻሽልበት ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራሉ። (ራእይ 21:​1, 3-5) ኢሳይያስ ስለ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” የገለጸው ተስፋ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ አስደሳች በሆነ መንገድ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ በግልጽ መረዳት ይቻላል። በሰማይ በተመሰለው አዲስ መስተዳድር ሥር የሚኖረው አዲስ ምድራዊ ኅብረተሰብ በመንፈሳዊ ሁኔታም ሆነ ቃል በቃል ገነትን ይወርሳል። ይሖዋ “የቀደሙትም [በሽታ፣ መከራና በሰው ልጆች ላይ የሚደርሱ ሌሎች ችግሮች] አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም” ሲል የገባው ቃል እጅግ የሚያጽናና ነው። በአዲሱ ዓለም ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ብዙዎችን የሚያሳስቧቸውንና የሚያስጨንቋቸውን ነገሮች እያብሰለሰልን በሐዘን አንዋጥም።

24. ይሖዋ ኢየሩሳሌም ቀድሞ ወደነበረችበት ሁኔታ መመለሷ የሚያስደስተው ለምንድን ነው? በዚያች ከተማ ጎዳናዎች ላይ ዳግመኛ የማይሰማውስ ነገር ምንድን ነው?

24 የኢሳይያስ ትንቢት በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሤት አድርጉ፤ እነሆ፣ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፣ ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁና። እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤት አደርጋለሁ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፤ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ አይሰማባትም።” (ኢሳይያስ 65:18, 19) ወደ ትውልድ አገራቸው በመመለሳቸው የሚደሰቱት አይሁዳውያን ብቻ አይደሉም። አምላክም ኢየሩሳሌምን በምድር ላይ ዳግመኛ የእውነተኛ አምልኮ ማዕከል እንድትሆን በማድረግ የሚያስውባት በመሆኑ እጅግ ይደሰታል። በርከት ካሉ አሥርተ ዓመታት ቀደም ብሎ በዚያች ከተማ በደረሰው ጥፋት ሳቢያ በጎዳናዎቿ ላይ የተሰማው ዓይነት የልቅሶ ድምፅ ዳግመኛ አይሰማም።

25, 26. (ሀ) በዘመናችን ይሖዋ ኢየሩሳሌምን “ለሐሤት” የሚፈጥረው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ አዲሲቷን ኢየሩሳሌም የሚጠቀምባት እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ እንድንደሰት የሚያደርጉን ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

25 በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ኢየሩሳሌምን “ለሐሤት” ይፈጥራል። እንዴት? ቀደም ሲል እንዳየነው በ1914 እውን የሆነው አዲስ ሰማይ በመጨረሻ በሰማያዊው መንግሥት የሚገዙ 144, 000 ተባባሪ ገዥዎች ይኖሩታል። እነዚህ ገዥዎች በትንቢት “አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” ተብለው ተገልጸዋል። (ራእይ 21:​2) አምላክ “እነሆ፣ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፣ ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁ” ሲል የተናገረው አዲሲቷን ኢየሩሳሌም በማስመልከት ነው። አምላክ አዲሲቷን ኢየሩሳሌም መሣሪያ አድርጎ በመጠቀም ታዛዥ በሆኑ የሰው ልጆች ላይ የተትረፈረፉ በረከቶች ያፈስሳል። ይሖዋ ‘የልባችንን መሻት’ የሚሰጠን በመሆኑ የልቅሶም ሆነ የዋይታ ድምፅ ዳግመኛ አይሰማም።​—⁠መዝሙር 37:​3, 4

26 በእርግጥም በዛሬው ጊዜ ሐሴት የምናደርግበት በቂ ምክንያት አለን! በቅርቡ ይሖዋ ተቃዋሚዎቹን ሁሉ በማጥፋት ታላቅ ስሙ እንዲቀደስ ያደርጋል። (መዝሙር 83:​17, 18) ከዚያ በኋላ አዲሱ ሰማይ ምድርን ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራል። እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች አምላክ እየፈጠረ ባለው ነገር ለዘላለም እንድንደሰት የሚያደርጉ እንዴት ያሉ ግሩም ምክንያቶች ናቸው!

አስተማማኝ የሆነ ተስፋ

27. ኢሳይያስ ወደ ትውልድ አገራቸው የሚመለሱት አይሁዶች የሚያገኙትን ደህንነት የገለጸው እንዴት ነው?

27 በትንቢቱ የመጀመሪያ ፍጻሜ መሠረት በአዲሱ ሰማይ አገዛዝ ሥር የሚኖሩት ከግዞት የተመለሱ አይሁዶች ሕይወት ምን መልክ ይኖረዋል? ይሖዋ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “ከዚያም ወዲያ ጥቂት ዘመን ብቻ የሚኖር ሕፃን፣ ወይም ዕድሜውን ያልፈጸመ ሽማግሌ አይገኝም፤ ጎልማሳው የመቶ ዓመት ሆኖት ይሞታልና፣ ኃጢአተኛውም የመቶ ዓመት ሆኖት የተረገመ ይሆናልና።” (ኢሳይያስ 65:20) ከግዞት የሚመለሱት አይሁዳውያን ቀድሞ ወደነበረችበት ሁኔታ በምትመለሰው የትውልድ አገራቸው የሚያገኙትን ደህንነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ግሩም መግለጫ ነው! አራስ ልጅ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሕይወቱ አይቀጭም። በዕድሜ የገፋውም ሰው ቢሆን ሙሉ የሕይወት ዘመኑን ሳያገባድድ በአጭር አይቀጭም። d ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት ወደ ይሁዳ የሚመለሱትን አይሁዳውያን ምንኛ የሚያጽናኑ ናቸው! ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ምንም ዓይነት አስጊ ሁኔታ ስለማይገጥማቸው ጠላቶቻችን ልጆቻችንን ይነጥቁናል ወይም ጎልማሶቹን ይፈጁብናል ብለው የሚጨነቁበት ምክንያት አይኖርም።

28. ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት በአዲሱ ዓለም በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚኖር ያስገነዝቡናል?

28 ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት በቅርቡ በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ስለሚኖረው ሕይወት ምን ያስገነዝቡናል? በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር እያንዳንዱ ልጅ አስተማማኝ ተስፋ ይጠብቀዋል። በተጨማሪም ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው በጉልምስና ዕድሜው በሞት አይቀጭም። ከዚህ ይልቅ ታዛዥ የሰው ልጆች ከስጋት ነፃ የሆነ፣ የተረጋጋና አስደሳች ሕይወት ይኖራሉ። በአምላክ ላይ የሚያምፁ ሰዎችስ ምን ይገጥማቸዋል? እንዲህ ያሉ ሰዎች የመኖር መብት ይነፈጋሉ። በአምላክ ላይ የሚያምፅ ኃጢአተኛ “የመቶ ዓመት ሆኖት ይሞታል።” ይህ ሰው ማብቂያ የሌለው ሕይወት ማግኘት ይችል የነበረ ከመሆኑ አንጻር ሲታይ “ገና ሕፃን” [NW ] ሳለ በሞት እንደተቀጨ ተደርጎ ይቆጠራል።

29. (ሀ) ታዛዥ የሆኑት የአምላክ ሕዝቦች የይሁዳ ምድር ቀድሞ ወደነበረችበት ሁኔታ ስትመለስ ምን አስደሳች ነገሮች ያገኛሉ? (ለ) ዛፍ ረጅም ዕድሜን ለማመልከት ተስማሚ ምሳሌ የሆነው ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

29 ይሖዋ ቀድሞ ወደነበረችበት ሁኔታ በምትመለሰው የይሁዳ ምድር የሚኖረውን ሁኔታ እንዲህ ሲል መዘርዘሩን ቀጠለ:- “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፣ ሌላም እንዲበላው አይተከሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፣ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና።” (ኢሳይያስ 65:21, 22) ታዛዥ የሆኑት የአምላክ ሕዝቦች ቤትም ሆነ ወይን አልባ ወደሆነውና ባድማ ሆኖ ወደቆየው የይሁዳ ምድር ከተመለሱ በኋላ ራሳቸው በሠሩት ቤት መኖርና ራሳቸው የተከሉትን ወይን መብላት መቻላቸው ከፍተኛ እርካታ ያስገኝላቸዋል። አምላክ የእጃቸውን ሥራ የሚባርከው ከመሆኑም በላይ በድካማቸው ፍሬ መደሰት የሚችሉበትን እንደ ዛፍ ያለ ረጅም ዕድሜ ይሰጣቸዋል። e

30. በዛሬው ጊዜ የይሖዋ አገልጋዮች በምን አስደሳች ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ? በአዲሱ ዓለም ውስጥስ ምን አስደሳች ሁኔታ ይጠብቃቸዋል?

30 ይህ ትንቢት በእኛም ዘመን ፍጻሜውን አግኝቷል። የይሖዋ ሕዝቦች በ1919 ከመንፈሳዊ ግዞት ነፃ በመውጣት ‘ምድራቸውን’ ወይም ሥራቸውንና አምልኳቸውን የሚያከናውኑበትን መስክ ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ጥረት ማድረግ ጀመሩ። ጉባኤዎችን ከማቋቋማቸውም በላይ መንፈሳዊ ፍሬ አፍርተዋል። በመሆኑም የይሖዋ ሕዝቦች በአሁኑ ጊዜም እንኳ መንፈሳዊ ገነትና አምላክ የሚሰጠውን ሰላም አግኝተዋል። ይህ ሰላም በምድራዊቷ ገነት ውስጥም እንደሚኖር እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋ ታዛዥ ልብና እጅ ያላቸውን አምላኪዎቹን በመጠቀም በአዲሱ ዓለም ውስጥ ምን ሊያከናውን እንደሚችል ከወዲሁ ለመገመት አዳጋች ነው። የራስህን ቤት ሠርተህ መኖር መቻል ምንኛ የሚያስደስት ነገር ነው! በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ወቅት እርካታ የሚሰጥ ሥራ እንደ ልብ ይገኛል። የእጃችሁ ሥራ ዘወትር “መልካም” [NW ] ሲሆን ማየት ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል! (መክብብ 3:​13) በእጃችን ሥራ በሚገባ ለመደሰት በቂ ጊዜ እናገኝ ይሆን? እንዴታ! ታማኝ ሰዎች የሚያገኙት ማብቂያ የሌለው ሕይወት “እንደ ዛፍ ዕድሜ” በሺህ ብሎም ከዚያ በሚበልጡ ዓመታት የሚቆጠር ይሆናል!

31, 32. (ሀ) ከግዞት የሚመለሱት አይሁዳውያን ምን በረከቶች ያገኛሉ? (ለ) በአዲሱ ዓለም ታማኝ ሰዎች ምን ተስፋ ይጠብቃቸዋል?

31 ይሖዋ ከግዞት የሚመለሱት አይሁዳውያን የሚያገኟቸውን ተጨማሪ በረከቶች እንዲህ ሲል ገለጸ:- “እነርሱ ከነልጆቻቸው የእግዚአብሔር ብሩካን ዘር ናቸውና በከንቱ አይደክሙም ለጥፋትም አይወልዱም።” (ኢሳይያስ 65:23) ወደ ትውልድ አገራቸው የሚመለሱትን አይሁዳውያን ይሖዋ ስለሚባርካቸው በከንቱ አይደክሙም። የሚወልዷቸው ልጆችም በለጋ ዕድሜያቸው አይቀጩም። ግዞተኞቹ አይሁዳውያን ቀድሞ ወደነበሩበት ሁኔታ በሚመለሱበት ጊዜ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ልጆቻቸውም የይሖዋን በረከቶች ያገኛሉ። አምላክ ሕዝቡ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ከፍተኛ ፍላጎት ያለው በመሆኑ እንዲህ ሲል ቃል ገባ:- “እንዲህም ይሆናል፤ ሳይጠሩ እመልስላቸዋለሁ፣ ገናም ሲናገሩ እሰማለሁ።”​—ኢሳይያስ 65:24

32 ይሖዋ እነዚህን ተስፋዎች በቅርቡ በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የሚፈጽማቸው እንዴት ነው? ይህ ጊዜው ሲደርስ የምናየው ይሆናል። ይሖዋ ይህን በተመለከተ ዝርዝር መግለጫ አልሰጠንም። ይሁንና በዚያን ጊዜ ታማኝ ሰዎች ‘በከንቱ እንደማይደክሙ’ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አርማጌዶንን በሕይወት የሚያልፉ እጅግ ብዙ ሰዎችና የሚወልዷቸው ልጆች አስደሳች የሆነ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ይጠብቃቸዋል። ትንሣኤ የሚያገኙና አምላክ ካወጣቸው መስፈርቶች ጋር ተስማምተው ለመኖር የሚመርጡ ሰዎችም በአዲሱ ዓለም ውስጥ ደስታ ያገኛሉ። ይሖዋ ልመናቸውን በመስማት ፈጣን ምላሽ የሚሰጣቸው ከመሆኑም በላይ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች አስቀድሞ በማወቅ ያሟላላቸዋል። በእርግጥም ይሖዋ እጁን ከፍቶ ‘ሕይወት ላለው ሁሉ መልካም ነገርን ያጠግባል።’​—⁠መዝሙር 145:​16

33. አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው ሲመለሱ እንስሳት ሰላማውያን የሚሆኑት በምን መንገድ ነው?

33 በዚያን ጊዜ የሚሰፍነው ሰላምና ደህንነት ምን ያህል ስፋት ይኖረዋል? ይሖዋ ይህን የኢሳይያስ ትንቢት ክፍል እንዲህ ሲል ደመደመ:- “ተኩላና ጠቦት በአንድነት ይሰማራሉ፣ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል፣ የእባብም መብል ትቢያ ይሆናል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ አይጐዱም፣ አያጠፉምም፣ ይላል እግዚአብሔር።” (ኢሳይያስ 65:25) ታማኞቹ አይሁዳውያን ቀሪዎች ወደ ትውልድ አገራቸው ሲመለሱ በይሖዋ ጥበቃ ሥር ይሆናሉ። አንበሳ በአይሁዳውያኑም ሆነ በቤት እንስሶቻቸው ላይ ጉዳት የማያደርስ በመሆኑ እንደ በሬ ገለባ የሚበላ ያህል ይሆናል። ይህ የተስፋ ቃል “ይላል እግዚአብሔር” በሚሉት ቃላት የተደመደመ በመሆኑ እጅግ አስተማማኝ ነው። ይሖዋ የተናገረው ቃል መቼም ቢሆን መሬት ጠብ አይልም!​—⁠ኢሳይያስ 55:​10, 11

34. ይሖዋ የተናገረው ቃል በዛሬው ጊዜም ሆነ በአዲሱ ዓለም ውስጥ አስደሳች በሆነ መንገድ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው?

34 የይሖዋ ቃል በዛሬው ጊዜ ባሉ እውነተኛ አምላኪዎች ላይ እጅግ አስደሳች በሆነ መንገድ ፍጻሜውን እያገኘ ነው። ከ1919 አንስቶ አምላክ ሕዝቡ ያለበትን መንፈሳዊ ምድር ወደ መንፈሳዊ ገነትነት በመለወጥ ባርኮታል። ወደዚህ መንፈሳዊ ገነት በመምጣት ላይ ያሉት ሰዎች በሕይወታቸው ላይ በጣም አስደናቂ የሆነ ለውጥ ያደርጋሉ። (ኤፌሶን 4:​22-24) በአንድ ወቅት የአውሬነት ጠባይ የነበራቸውና ምናልባትም ሌሎች ሰዎችን አላግባብ መጠቀሚያ ያደረጉ ወይም በሰዎች ላይ ግፍ ሲፈጽሙ የኖሩ ግለሰቦች በአምላክ መንፈስ እርዳታ ራሳቸውን በመግራት የነበሯቸውን አላስፈላጊ ባሕርያት ማስወገድ ችለዋል። በውጤቱም እንደነሱው ካሉ አማኞች ጋር ሰላምና የአምልኮ አንድነት ሊያገኙ ችለዋል። በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ እያገኟቸው ያሉት በረከቶች ሰዎች ብቻ ሳይሆን እንስሳትም ሰላማውያን በሚሆኑበት በምድራዊው ገነት ውስጥም ይትረፈረፋሉ። አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ መጀመሪያ ላይ ለሰው ልጅ ሰጥቶት የነበረው የሚከተለው ተልዕኮ በአግባቡ ፍጻሜውን ያገኛል:- “[ምድርን] ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።”​—⁠ዘፍጥረት 1:28

35. ‘ለዘላለም የምንደሰትበት’ በቂ ምክንያት አለን የምንለው ለምንድን ነው?

35 ይሖዋ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” እፈጥራለሁ ሲል ለገባው ቃል ምንኛ አመስጋኞች ነን! ይህ ቃል በ537 ከዘአበ ፍጻሜውን ያገኘ ከመሆኑም በላይ በዛሬውም ጊዜ እየተፈጸመ ነው። ይሖዋ የሰጠው ተስፋ በእነዚህ ሁለት የተለያዩ ጊዜያት ፍጻሜውን ማግኘቱ ታዛዥ የሆኑ የሰው ዘሮች ወደፊት የሚጠብቃቸውን ታላቅ ጊዜ የሚጠቁም ነው። ይሖዋ እርሱን ለሚወዱት ሰዎች ምን ነገር እንዳዘጋጀላቸው በኢሳይያስ ትንቢት በኩል ትንሽ ፍንጭ ሰጥቶናል። በእርግጥም ‘በፈጠርሁት ለዘላለም ደስ ይበላችሁ’ የሚሉትን የይሖዋ ቃላት ተግባራዊ የምናደርግበት በቂ ምክንያት አለን!​—⁠ኢሳይያስ 65:​18

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ብዙዎች እነዚህ ኃጢአተኞች በመቃብር ሥፍራዎች ይቀመጡ የነበረው ከሙታን ጋር ለመገናኘት ሲሉ እንደነበረ ያምናሉ። የእሪያ ሥጋ መብላታቸው ደግሞ ከጣዖት አምልኮ ጋር ዝምድና ሊኖረው ይችላል።

b የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ የሆነው ጄሮም (በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ የተወለደ) ይህን ጥቅስ አስመልክቶ አስተያየት ሲሰጥ ጣዖት አምላኪዎች በዓመቱ የመጨረሻ ወር የመጨረሻ ቀን ላይ የሚያከናውኑትን አንድ ጥንታዊ ልማድ ጠቅሷል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ያለፈው አሊያም መጪው ዓመት የብልጽግና ዘመን ይሆንላቸው ዘንድ መልካም ዕድል እንዲገጥማቸው በመመኘት በተለያዩ ምግቦች የተሞላ ማዕድና ጣፋጭ የሆነ ድብልቅ ወይን ጠጅ የያዘ ጽዋ ያቀርባሉ።”

c በዕብራይስጡ የማሶሬቲክ ጽሑፍ ላይ ኢሳይያስ 65:​16 ይሖዋ “የአሜን አምላክ” እንደሆነ ይገልጻል። “አሜን” ማለት “ይሁን” ወይም “የሚያስተማምን” ማለት ሲሆን ይህም አንድ ነገር እውነተኛ እንደሆነ ወይም ፍጻሜውን ማግኘቱ እንደማይቀር የሚያረጋግጥ ዋስትና ነው። ይሖዋ ቃል የገባውን ሁሉ በመፈጸም የሚናገረው ነገር እውነት እንደሆነ ያሳያል።

d አዲሱ መደበኛ ትርጉም ኢሳይያስ 65:​20ን እንዲህ ሲል ተርጉሞታል:- “ከእንግዲህም በዚያ፣ ለጥቂት ጊዜ ብቻ በሕይወት የሚኖር ሕፃን፣ ወይም ዕድሜ ያልጠገበ አረጋዊ አይኖርም፤ አንድ መቶ ዓመት የሞላው ሰው ቢሞት፣ በአጭር እንደ ተቀጨ ይቈጠራል።”

e ዛፎች በምድር ላይ ረጅም ዘመን ከሚኖሩ ሕያዋን ነገሮች መካከል የሚጠቀሱ በመሆኑ ረጅም ዕድሜን ለማመልከት ተስማሚ ምሳሌ ናቸው። ለምሳሌ ያህል የወይራ ዛፍ በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት ፍሬ የሚያፈራ ሲሆን እስከ አንድ ሺህ ዓመት ድረስ ሊኖር ይችላል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 389 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ በእጃችን ሥራ የምንደሰትበት በቂ ጊዜ ይኖረናል