በሐዘን ለተደቆሱ ግዞተኞች የተላከ ተስፋ ሰጭ መልእክት
ምዕራፍ አሥራ ስድስት
በሐዘን ለተደቆሱ ግዞተኞች የተላከ ተስፋ ሰጭ መልእክት
1. አይሁዳውያን ግዞተኞች በባቢሎን የነበሩበትን ሁኔታ ግለጽ።
ጊዜው በይሁዳ ታሪክ በጣም አስከፊ የሆነ ጨለማ ያጠላበት ዘመን ነው። የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝቦች ከትውልድ አገራቸው ተፈናቅለው በባቢሎን በግዞት እየተንገላቱ ነው። እርግጥ ነው፣ የዕለት ተዕለት ጉዳዮቻቸውን ለማከናወን የሚያስችል መጠነኛ የሆነ ነፃነት ነበራቸው። (ኤርምያስ 29:4-7) አንዳንዶቹ ከፍተኛ ሙያዎችን የመማር ወይም በንግድ ሥራ የመሰማራት አጋጣሚ አግኝተዋል። a (ነህምያ 3:8, 31, 32) ያም ሆኖ የባቢሎን ኑሮ ለአይሁዳውያን ግዞተኞች ቀላል አልነበረም። በአካላዊም ሆነ በመንፈሳዊ ባርነት ሥር ወድቀው ነበር። እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ሊወድቁ የቻሉት እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
2, 3. አይሁዳውያን ግዞተኞች መሆናቸው ለይሖዋ በሚያቀርቡት አምልኮ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው እንዴት ነው?
2 የባቢሎን ሠራዊት በ607 ከዘአበ ኢየሩሳሌምን ባወደመ ጊዜ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ጥፋት ከማድረሱም በተጨማሪ እውነተኛውን አምልኮ አናግቷል። የይሖዋን ቤተ መቅደስ ከመዝረፉና ከማጥፋቱም በላይ የሌዊን ነገድ አባላት በመማረክና አንዳንዶቹንም በመግደል የክህነት አገልግሎቱን አስተጓጉሏል። የአምልኮ ቤት፣ መሠዊያና የተደራጀ የክህነት አገልግሎት ሳይኖር አይሁዶች ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት ለእውነተኛው አምላክ መሥዋዕት ማቅረብ የሚችሉበት ሁኔታ አልነበረም።
3 ያም ሆኖ ታማኝ አይሁዳውያን የግዝረትን ልማድ በመፈጸምና ሁኔታቸው በፈቀደላቸው መጠን ሕጉን ተግባራዊ በማድረግ ሃይማኖታዊ መለያቸው ተጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ ይችሉ ነበር። ለምሳሌ ያህል ከተከለከሉ ምግቦች መራቅና የሰንበትን ሕግ መጠበቅ ይችሉ ነበር። ሆኖም ባቢሎናውያን አይሁዶች ይከተሉት የነበረውን ሃይማኖታዊ ሥርዓት እንደ ሞኝነት ይቆጥሩት ስለነበረ አይሁዳውያኑ ሕጉን መጠበቃቸው የጠላቶቻቸው ማፌዢያና ማላገጫ ያደርጋቸው ነበር። መዝሙራዊው የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት ግዞተኞቹ ምን ያህል ልባቸው ተሰብሮ እንደነበረ ያሳያሉ:- “በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን፤ ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን። በአኻያ ዛፎችዋ ላይ መሰንቆቻችንን ሰቀልን። የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን፣ የወሰዱንም:- የጽዮንን ዝማሬ ዘምሩልን አሉን።”—መዝሙር 137:1-3
4. አይሁዳውያን ሌሎች ብሔራት ነፃ ሊያወጡን ይችላሉ ብለው ተስፋ ማድረግ የሌለባቸው ለምንድን ነው? ሆኖም ከማን እርዳታ ሊያገኙ ይችላሉ?
4 እንግዲያው አይሁዳውያን ግዞተኞች ማጽናኛ ሊያገኙ የሚችሉት ከማን ነው? ሊያድናቸው የሚችለውስ ማን ነው? በዙሪያቸው ያሉት ብሔራት እንደማይሆኑ የታወቀ ነው! እነዚህ ብሔራት የባቢሎንን ሠራዊት ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል ያልነበራቸው ከመሆኑም በላይ ብዙዎቹ የአይሁዳውያን ጠላቶች ነበሩ። ይህ ማለት ግን ምንም ተስፋ አልነበራቸውም ማለት አይደለም። ነፃ ሕዝብ በነበሩበት ጊዜ ያመፁበት አምላካቸው በደግነት ተገፋፍቶ በግዞት ያሉ ቢሆንም እንኳ ብሩህ ተስፋ እንዲታያቸው የሚያደርግ ጥሪ አቅርቦላቸዋል።
“ወደ ውኃ ኑ”
5. “ወደ ውኃ ኑ” የሚሉት ቃላት ምን ትርጉም አላቸው?
5 ይሖዋ በኢሳይያስ አማካኝነት በባቢሎን በግዞት ላሉት አይሁዳውያን በትንቢት እንዲህ ሲል ተናገረ:- “እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፣ ወደ ውኃ ኑ፣ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፤ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ።” (ኢሳይያስ 55:1) እነዚህ ቃላት በርከት ያሉ ተምሳሌታዊ አነጋገሮችን የያዙ ናቸው። ለምሳሌ ያህል “ወደ ውኃ ኑ” የሚለውን ጥሪ ተመልከት። ያለ ውኃ መኖር አይቻልም። ለሕይወታችን በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ውኃ ካላገኘን ከአንድ ሳምንት በላይ መቆየት አንችልም። በመሆኑም ይሖዋ መልእክቱ በአይሁዳውያን ግዞተኞች ላይ የሚያስከትለውን ውጤት ለመግለጽ ቃሉን በውኃ መመሰሉ ተገቢ ነው። ሞቃታማ በሆነ ቀን ጥም እንደሚቆርጥ ቀዝቃዛ ውኃ መልእክቱ መንፈሳቸውን ያነቃቃዋል። የእውነትና የጽድቅ ጥማቸውን በማርካት ከተጫናቸው የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲላቀቁና ከግዞት ነፃ እንወጣለን በሚል ብሩህ ተስፋ እንዲሞሉ ያደርጋቸዋል። ያም ሆኖ ግዞተኞቹ አይሁዳውያን ይህን ጥቅም ማግኘት እንዲችሉ የአምላክን መልእክት መጠጣት ማለትም ለቃሉ ጆሯቸውን መስጠትና የታዘዙትን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
6. አይሁዳውያን “የወይን ጠጅና ወተት” በመግዛት ሊጠቀሙ የሚችሉት እንዴት ነው?
6 በተጨማሪም ይሖዋ “የወይን ጠጅና ወተት” አቅርቧል። ወተት ሰውነትን ያጠነክራል እንዲሁም ሕፃናት እንዲያድጉ አስተዋጽኦ ያደርጋል። የይሖዋ ቃልም እንደዚሁ ሕዝቡን በመንፈሳዊ የሚያጠነክር ከመሆኑም ሌላ ከእርሱ ጋር ያላቸውን ዝምድና ማጎልበት እንዲችሉ ይረዳቸዋል። ስለ ወይንስ ምን ለማለት ይቻላል? ወይን ብዙውን ጊዜ የሚጠጣው በድግስና በበዓላት ወቅት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወይን ከብልጽግናና ከደስታ ጋር ተያይዞ ተገልጿል። (መዝሙር 104:15) ይሖዋ ሕዝቡ ‘ወይን ጠጅ እንዲገዙ’ ማበረታታቱ በሙሉ ልባቸው ወደ እውነተኛው አምልኮ ከተመለሱ ‘ፈጽሞ ደስ እንደሚላቸው’ የሚያረጋግጥ ነው።—ዘዳግም 16:15፤ መዝሙር 19:8፤ ምሳሌ 10:22
7. ይሖዋ ለግዞተኞቹ አይሁዳውያን ርኅራኄ ማሳየቱ የሚያስደንቅ የሆነው ለምንድን ነው? ይህስ ስለ እሱ ምን ያስተምረናል?
7 ይሖዋ በግዞት ላሉት አይሁዶች እንዲህ ያለ መንፈሳዊ ግብዣ ማቅረቡ እጅግ መሐሪ መሆኑን የሚያሳይ ነው። አይሁዳውያን በራሳቸው ስሜትና ፍላጎት የሚነዱ እንዲሁም ዓመፀኞች እንደነበሩ ስናስብ ደግሞ የይሖዋ ርኅራኄ እጅግ አስደናቂ መሆኑን እንገነዘባለን። ይሖዋ እንዲህ ያለ ርኅራኄ ያሳያቸው ሞገሱን ማግኘት የሚገባቸው ሰዎች ሆነው አይደለም። ይሁንና መዝሙራዊው ዳዊት ብዙ መቶ ዘመናት አስቀድሞ እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር:- “እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፣ ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩም የበዛ ነው። እርሱ ሁልጊዜ በደልን አይከታተልም፤ ለዘላለምም አይቈጣም።” (መዝሙር 103:8, 9 አ.መ.ት ) ይሖዋ ሕዝቡን እርግፍ አድርጎ አልተዋቸውም። ከዚህ ይልቅ ዕርቅ ለመፍጠር ቀዳሚውን እርምጃ ወስዷል። በእርግጥም “ፍቅራዊ ደግነት በማሳየት የሚደሰት [NW ]” አምላክ ነው።—ሚክያስ 7:18
ማዳን በማይችሉ ሰዎች መታመን
8. ብዙዎቹ አይሁዶች እምነታቸውን የጣሉት በማን ላይ ነው? የትኛውንስ ማስጠንቀቂያ ችላ ብለዋል?
8 ይሁንና ብዙዎቹ አይሁዳውያን መዳን ለማግኘት ሙሉ በሙሉ እምነታቸውን በይሖዋ ላይ አልጣሉም ነበር። ለምሳሌ ያህል ኢየሩሳሌም ከመውደቋ በፊት ገዥዎቿ ከኃያላን ብሔራት እርዳታ ለማግኘት በመሞከር ከግብጽና ከባቢሎን ጋር ያመነዘሩ ያህል ሆነው ነበር። (ሕዝቅኤል 16:26-29፤ 23:14) ኤርምያስ “በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው” ሲል ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ተገቢ ነበር። (ኤርምያስ 17:5) ይሁንና የአምላክ ሕዝቦች ያደረጉት ይህንኑ ነው!
9. ብዙዎቹ አይሁዳውያን ‘ገንዘባቸውን እንጀራ ላይደለ ነገር እንደመዘኑ’ ተደርጎ ሊቆጠር የሚችለው እንዴት ነው?
9 አሁን በአንድ ወቅት እምነታቸውን ጥለውባት የነበረችው ብሔር ራሷ ባሪያ አድርጋቸዋለች። ከዚህ ስህተታቸው ተምረው ይሆን? ይሖዋ እንዲህ ሲል መጠየቁ ብዙዎቹ ከደረሰባቸው ሁኔታ ትምህርት እንዳላገኙ የሚጠቁም ነው:- “ገንዘብን እንጀራ ላይደለ፣ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ?” (ኢሳይያስ 55:2ሀ) ግዞተኞቹ አይሁዳውያን በይሖዋ ላይ እምነት መጣል ሲገባቸው በሌላ ከታመኑ ‘ገንዘባቸውን እንጀራ ላይደለ ነገር እንደመዘኑ’ የሚቆጠር ነው። የባቢሎን ፖሊሲ ግዞተኞቿ ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ የማይፈቅድ በመሆኑ ከባቢሎን ነፃ የመውጣት ተስፋ አይኖራቸውም። እንደ እውነቱ ከሆነ በቅኝ አገዛዝ ፖሊሲዋ የምትታወቀው፣ ትርፍ ለማጋበስ የምትሯሯጠውና በሐሰት ሃይማኖት የተሞላችው ባቢሎን ለግዞተኞቹ አይሁዳውያን የምትፈይድላቸው ምንም ነገር አይኖርም።
10. (ሀ) ይሖዋ ግዞተኞቹ አይሁዳውያን ቃሉን ከሰሙት በእጅጉ የሚክሳቸው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ከዳዊት ጋር የገባው ቃል ኪዳን ምንድን ነው?
10 ይሖዋ ሕዝቡን እንዲህ ሲል ተማጸነ:- “አድምጡኝ፣ በረከትንም ብሉ፣ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው። ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔም ቅረቡ፤ ስሙ ሰውነታችሁም በሕይወት ትኖራለች፤ የታመነችይቱን የዳዊትን ምሕረት፣ የዘላለምን ቃል ኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ።” (ኢሳይያስ 55:2ለ, 3) በመንፈሳዊ ምግብ እጥረት የሚሰቃዩት እነዚህ ሰዎች ብቸኛ ተስፋቸው በኢሳይያስ በኩል በትንቢት እያነጋገራቸው ያለው ይሖዋ ነው። ይሖዋ ቃሉን ከሰሙ ‘ሰውነታቸው በሕይወት እንደሚኖር’ የተናገረ በመሆኑ ሕይወታቸው የተመካው የአምላክን መልእክት በማዳመጥ ላይ ነው። ይሁንና ይሖዋ ከሚታዘዙት ሰዎች ጋር የሚገባው ‘የዘላለም ቃል ኪዳን’ ምንድን ነው? ይህ ቃል ኪዳን ይሖዋ ‘ለዳዊት ያሳየውን ፍቅራዊ ደግነት’ የሚያመለክት ነው። ብዙ መቶ ዘመናት ቀደም ብሎ ይሖዋ “ዙፋንህም ለዘላለም ይጸናል” ሲል ለዳዊት ቃል ገብቶለት ነበር። (2 ሳሙኤል 7:16) በመሆኑም እዚህ ላይ የተጠቀሰው ‘የዘላለም ቃል ኪዳን’ ከአገዛዝ ጋር የተያያዘ ነው።
ዘላለማዊ በሆነ መንግሥት ላይ ጸንቶ የሚኖር ወራሽ
11. በባቢሎን የሚኖሩት ግዞተኞች አምላክ ለዳዊት የገባው ቃል ፍጻሜውን እንደማያገኝ ሆኖ ሊሰማቸው የሚችለው ለምንድን ነው?
11 እርግጥ ነው፣ አይሁዳውያን ግዞተኞች በዳዊት ዘር የሚመራ አገዛዝ ይቋቋማል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ሆኖባቸው ሊሆን ይችላል። አገራቸውን ብሎም ብሔራዊ ሕልውናቸውን አጥተዋል! ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይለወጣል። ይሖዋ ከዳዊት ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አልዘነጋም። ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ ሊሆን የማይችል ነገር መስሎ ቢታይም እንኳ አምላክ በዳዊት ዘር አማካኝነት ዘላለማዊ መንግሥት ለማቋቋም ያወጣው ዓላማ ዳር ይደርሳል። ይሁንና ይህ የሚሆነው እንዴትና መቼ ነው? በ537 ከዘአበ ይሖዋ ሕዝቡን ከባቢሎን ግዞት ነፃ በማውጣት ወደ ትውልድ አገራቸው መለሳቸው። በዚያን ጊዜ ዘላለማዊ መንግሥት ተቋቁሟልን? አልተቋቋመም፤ አይሁዳውያን በሌላ አረማዊ አገዛዝ ማለትም በሜዶ ፋርስ መንግሥት ተገዝተዋል። አሕዛብ የሚገዙበት ‘የተወሰነው ዘመን’ ገና አላበቃም ነበር። (ሉቃስ 21:24) በእስራኤል የተሾመ ንጉሥ ስላልነበረ ይሖዋ ለዳዊት የገባው ቃል ፍጻሜውን ሳያገኝ ብዙ መቶ ዘመናት አለፉ።
12. ይሖዋ ከዳዊት ጋር የገባውን የመንግሥት ቃል ኪዳን ለመፈጸም ምን እርምጃ ወሰደ?
12 እስራኤል ከባቢሎን ግዞት ነፃ ከወጣች ከ500 የሚበልጡ ዓመታት ካለፉ በኋላ ይሖዋ የፍጥረት ሥራው መጀመሪያ የሆነውን የበኩር ልጁን ክብራማ ሰማያዊ ሕይወት ማርያም ወደምትባል አይሁዳዊት ድንግል ማኅፀን በማዛወር የመንግሥቱን ቃል ኪዳን ለመፈጸም የሚያስችል ትልቅ እርምጃ ወሰደ። (ቆላስይስ 1:15-17) የይሖዋ መልአክ ይህን ለማርያም ባስታወቃት ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር:- “እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፣ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” (ሉቃስ 1:32, 33) ስለዚህ ኢየሱስ ከንጉሣዊው የዳዊት የዘር ሐረግ የተወለደ በመሆኑ የንግሥና ሥልጣን መውረስ ችሏል። ንጉሥ ሆኖ ዙፋን ላይ ከተቀመጠ በኋላ ‘ለዘላለም’ ይገዛል። (ኢሳይያስ 9:7፤ ዳንኤል 7:14) በዚህ መንገድ ይሖዋ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ዘላለማዊ ወራሽ እንደሚያስነሳ የገባው ቃል ፍጻሜውን የሚያገኝበት ሁኔታ ተመቻቸ።
‘ለወገኖች አዛዥ’
13. ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅትም ሆነ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ “ለአሕዛብ ምስክር” የሆነው እንዴት ነው?
13 በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጠው ይህ ንጉሥ ምን ያከናውናል? ይሖዋ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “እነሆ፣ ለአሕዛብ ምስክር፣ ለወገኖችም አለቃና [“መሪ፣” አ.መ.ት ] አዛዥ እንዲሆን ሰጥቼዋለሁ።” (ኢሳይያስ 55:4) ኢየሱስ ካደገ በኋላ የይሖዋ ምድራዊ ወኪል ማለትም ለአሕዛብ የአምላክ ምስክር ሆኖ አገልግሏል። ኢየሱስ ሰው ሆኖ በኖረበት ዘመን አገልግሎቱ ያተኮረው ‘የጠፉትን የእስራኤል ቤት በጎች’ በመፈለጉ ሥራ ላይ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ከጥቂት ጊዜ በፊት ተከታዮቹን “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 10:5, 6፤ 15:24፤ 28:19, 20) በመሆኑም ውሎ አድሮ የመንግሥቱ መልእክት አይሁዳውያን ላልሆኑ ሰዎች መነገር የጀመረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ ይሖዋ ከዳዊት ጋር የገባው ቃል ኪዳን ፍጻሜ ተካፋዮች ሆነዋል። (ሥራ 13:46) በዚህ መንገድ ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳና ወደ ሰማይ ካረገ በኋላም ‘ለአሕዛብ የይሖዋ ምስክር’ ሆኖ ማገልገሉን ቀጥሏል።
14, 15. (ሀ) ኢየሱስ “መሪና አዛዥ” መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የኢየሱስ ተከታዮች ምን ተስፋ አግኝተዋል?
14 በተጨማሪም ኢየሱስ “መሪና አዛዥ” እንደሚሆን ተነግሯል። በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ከዚህ ትንቢታዊ መግለጫ ጋር በሚስማማ መንገድ የራስነት ሥልጣኑ የሚያስከትልበትን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የተቀበለ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ወደ እሱ በመሳብ፣ የእውነትን ቃል በማስተማርና አመራሩን የሚከተሉ ሁሉ የሚያገኟቸውን ጥቅሞች በመግለጽ በሁሉም ዘርፍ ግንባር ቀደም ሆኖ አገልግሏል። (ማቴዎስ 4:24፤ 7:28, 29፤ 11:5) ደቀ መዛሙርቱን ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው የስብከት ዘመቻ በሚገባ በማዘጋጀት ውጤታማ በሆነ መንገድ አሠልጥኗቸዋል። (ሉቃስ 10:1-12፤ ሥራ 1:8፤ ቆላስይስ 1:23) ኢየሱስ በሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የጣለው መሠረት ከተለያዩ ዘሮች የተውጣጡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አባላትን ያቀፈ አንድነት ያለው ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ እንዲቋቋም አስችሏል! እንዲህ ያለ ታላቅ ሥራ ማከናወን የሚችለው እውነተኛ “መሪና አዛዥ” ብቻ ነው። b
15 በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ሥር የተሰባሰቡት ሰዎች በአምላክ ቅዱስ መንፈስ የተቀቡ ሲሆን በሰማያዊው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር ተባባሪ ገዥዎች የመሆን ተስፋ አግኝተዋል። (ራእይ 14:1) ይሁን እንጂ የኢሳይያስ ትንቢት ከጥንቱ የክርስትና ዘመን ባሻገር ያለውንም ሁኔታ ይዳስሳል። ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ 1914 ድረስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት እንዳልጀመረ ማስረጃዎቹ ያመለክታሉ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በምድር ባሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ላይ የተፈጠረው ሁኔታ በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በግዞት የነበሩት አይሁዳውያን ገጥሟቸው ከነበረው ሁኔታ ጋር በብዙ መልኩ ይመሳሰላል። እንዲያውም የኢሳይያስ ትንቢት የላቀ ፍጻሜውን ያገኘው በእነዚህ ክርስቲያኖች ላይ ነው።
ዘመናዊ ግዞትና ነፃነት
16. በ1914 ኢየሱስ በዙፋኑ ላይ ሲቀመጥ ምን መከራ ተከሰተ?
16 ኢየሱስ በ1914 ንጉሥ ሆኖ በዙፋን ላይ ሲቀመጥ በዓለም ላይ ከዚያ በፊት ታይቶ የማያውቅ መከራ ተከስቷል። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ ሲነግሥ ሰይጣንንና ሌሎቹን ክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታት ከሰማይ አባርሯል። ሰይጣን እንቅስቃሴው በምድር ብቻ እንዲወሰን ሲደረግ በምድር ላይ በቀሩት ቅዱሳን ማለትም በቅቡዓን ቀሪዎች ላይ ጦርነት ከፈተ። (ራእይ 12:7-12, 17) በቅቡዓኑ ላይ የተከፈተው ይህ ውጊያ በ1918 በከፍተኛ ሁኔታ በመፋፋሙ የስብከቱ ሥራ የተዳፈነ ያህል ሆኖ የነበረ ሲሆን በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚሠሩ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር አባላትም በመንግሥት ላይ ዓመፅ ለማነሳሳት ሞክራችኋል በሚል ክስ ተወንጅለው ታሠሩ። በዚህ መንገድ ዘመናዊዎቹ የይሖዋ አገልጋዮች በጥንት ዘመን ቃል በቃል በግዞት ተይዘው ከነበሩት አይሁዳውያን ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ በመንፈሳዊ ግዞተኞች ሆኑ። በዚህም ሳቢያ ለከፍተኛ ነቀፋና ትችት ተጋልጠው ነበር።
17. ቅቡዓን ቀሪዎቹ ገጥሟቸው የነበረው ሁኔታ በ1919 የተለወጠው እንዴት ነው? በዚያን ጊዜ የተጠናከሩትስ እንዴት ነው?
17 ይሁን እንጂ የአምላክ ቅቡዓን አገልጋዮች በመንፈሳዊ ግዞት የቆዩት ለረጅም ጊዜ አልነበረም። ታስረው የነበሩት ወንድሞች መጋቢት 26, 1919 የተፈቱ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ደግሞ ተመሥርቶባቸው ከነበረው ክስ ሙሉ በሙሉ ነፃ ሆኑ። ይሖዋ ነፃ በወጡት ሕዝቦቹ ላይ ቅዱስ መንፈሱን በማፍሰስ ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ሥራ አበረታቸው። ‘የሕይወትን ውኃ በነፃ እንዲወስዱ’ የቀረበላቸውን ጥሪ በደስታ ተቀበሉ። (ራእይ 22:17) ‘የወይን ጠጅና ወተት ያለ ገንዘብና ያለ ዋጋ’ ከመግዛታቸውም በላይ ብዙም ሳይቆይ የተገኘውንና ቅቡዓን ቀሪዎቹ ፈጽሞ ያልጠበቁትን እጅግ አስደናቂ የሆነ እድገት ለማስተናገድ የሚያስችል መንፈሳዊ ጥንካሬ አግኝተዋል።
እጅግ ብዙ ሰዎች ወደ አምላክ ቅቡዓን ይሮጣሉ
18. ኢየሱስ ክርስቶስን የሚከተሉት ሁለት ቡድኖች የትኞቹ ናቸው? በአሁኑ ጊዜስ ምን ሆነዋል?
18 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሁለት ዓይነት ተስፋ አላቸው። በመጀመሪያ 144, 000 ቁጥር ያላቸው ‘የታናሹ መንጋ’ ማለትም ‘የእግዚአብሔር እስራኤል’ አባላት የሆኑ ከአይሁድና ከአሕዛብ የተውጣጡ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የተሰባሰቡ ሲሆን እነዚህ ክርስቲያኖች በሰማያዊው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር የመግዛት ተስፋ አላቸው። (ሉቃስ 12:32፤ ገላትያ 6:16፤ ራእይ 14:1) በመጨረሻዎቹ ቀናት ደግሞ ‘የሌሎች በጎች’ አባላት የሆኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ብቅ ብለዋል። እነዚህ ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው። አስቀድሞ የተወሰነ ቁጥር የሌላቸው እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ታላቁ መከራ ከመምጣቱ በፊት ከታናሹ መንጋ ጎን ተሰልፈው የሚያገለግሉ ሲሆን እነዚህ ሁለት ቡድኖች ‘በአንድ እረኛ’ የሚመራ ‘አንድ መንጋ’ ሆነዋል።—ራእይ 7:9, 10፤ ዮሐንስ 10:16
19. የአምላክ እስራኤል አባላት መጀመሪያ ላይ ላላወቁት “ሕዝብ” ያቀረቡት ጥሪ ምን ዓይነት ምላሽ አግኝቷል?
19 በኢሳይያስ ትንቢት ላይ የሚገኙት የሚከተሉት ቃላት እጅግ ብዙ ሰዎች እንደሚሰበሰቡ የሚያመለክቱ ናቸው:- “እነሆ፣ የማታውቀውን ሕዝብ ትጠራለህ፣ የእስራኤልም ቅዱስ አክብሮሃልና ስለ አምላክህ ስለ እግዚአብሔር የማያውቁህ ሕዝብ ወደ አንተ ይሮጣሉ።” (ኢሳይያስ 55:5) መጀመሪያ ላይ ቅቡዓን ቀሪዎች ከመንፈሳዊ ግዞት ነፃ ከወጡ በኋላ በነበሩት ዓመታት አንድን ትልቅ “ሕዝብ” ወደ ይሖዋ አምልኮ በመጥራት ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ አልተገነዘቡም ነበር። ይሁን እንጂ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ሰማያዊ ተስፋ የሌላቸው ብዙ ቅን ሰዎች ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር መሰብሰብና ከቅቡዓኑ በማይለይ የቅንዓት መንፈስ ይሖዋን ማገልገል ጀመሩ። ወደ ይሖዋ አምልኮ የተሰባሰቡት እነዚህ አዳዲስ ሰዎች የአምላክ ሕዝቦች ያሉበትን ክብራማ ሁኔታ ከማስተዋላቸውም በላይ ይሖዋ በመካከላቸው እንዳለ ተገንዝበዋል። (ዘካርያስ 8:23) በ1930ዎቹ ዓመታት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ቁጥራቸው እያደገ የመጣውን የዚህ ቡድን አባላት ትክክለኛ ማንነት አስተዋሉ። ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ የመሰብሰብ ሥራ ከፊታቸው እንደሚጠብቃቸው ተረዱ። እጅግ ብዙ ሰዎች ከአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብ ጋር ለመጎዳኘት እየተጣደፉ ነበር። ለዚህም በቂ ምክንያት አላቸው።
20. (ሀ) በዘመናችን ‘ይሖዋን መፈለግ’ አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህንንስ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ወደ እሱ ለሚመለሱ ሰዎች ምን ያደርግላቸዋል?
20 በኢሳይያስ ዘመን የሚከተለው ጥሪ ቀርቦ ነበር:- “እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፣ ቀርቦም ሳለ ጥሩት።” (ኢሳይያስ 55:6) በዘመናችን እነዚህ ቃላት ለአምላክ እስራኤልም ሆነ ቁጥራቸው እያደገ ለመጣው እጅግ ብዙ ሰዎች ተስማሚ ናቸው። ይሖዋ በረከቱን የሚያፈስሰው ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ አይደለም። ከዚህም በተጨማሪ ይህ ጥሪ የሚቀርበው ለዘላለም አይደለም። በመሆኑም የአምላክን ሞገስ ለማግኘት መጣር ያለብን ዛሬ ነው። ይሖዋ ፍርዱን ለማስፈጸም የወሰነው ጊዜ ከደረሰ በኋላ እንዲህ ያለውን አጋጣሚ ማግኘት አይቻልም። በመሆኑም ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ተናገረ:- “ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፣ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ።”—ኢሳይያስ 55:7
21. የእስራኤል ሕዝብ የቀድሞ አባቶቻቸው የገቡትን ቃል ሳይጠብቁ የቀሩት እንዴት ነው?
21 “ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ” የሚለው ሐረግ እነዚህ ንስሐ መግባት ያለባቸው ሰዎች ቀደም ሲል ከአምላክ ጋር ዝምድና እንደነበራቸው ያመለክታል። ይህ አገላለጽ በዚህ የኢሳይያስ ትንቢት ላይ የተጠቀሱት ብዙዎቹ ነገሮች በባቢሎን በግዞት በነበሩት አይሁዶች ላይ የመጀመሪያ ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ እንድናስታውስ ያደርገናል። ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት የቀድሞ አባቶቻቸው “እግዚአብሔርን ትተን ሌሎች አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ” ብለው በመግለጽ ይሖዋን ለመታዘዝ ያላቸውን ቁርጥ አቋም አስታውቀው ነበር። (ኢያሱ 24:16) ይሁን እንጂ አናደርገውም ያሉትን ነገር ደጋግመው እንደፈጸሙ ታሪክ ይመሠክራል! የአምላክ ሕዝቦች በባቢሎን ለግዞት የተዳረጉት እምነት ስለጎደላቸው ነው።
22. ይሖዋ አሳቡና መንገዱ ከሰው አሳብና መንገድ ከፍ ያለ እንደሆነ የተናገረው ለምንድን ነው?
22 ንስሐ ከገቡ ምን ሁኔታ ይገጥማቸዋል? ይሖዋ ‘በብዙ ይቅር እንደሚላቸው’ በኢሳይያስ በኩል ቃል ገብቷል። አክሎም እንዲህ አለ:- “አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና፣ ይላል እግዚአብሔር። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው።” (ኢሳይያስ 55:8, 9) ይሖዋ ፍጹም ከመሆኑም በላይ አሳቦቹም ሆኑ መንገዶቹ እጅግ ከፍ ያሉ ናቸው። ሌላው ቀርቶ ምሕረቱ እንኳ እጅግ ከፍ ያለ ከመሆኑ የተነሳ ፈጽሞ ልንደርስበት አንችልም። ለምሳሌ ያህል ለአንድ ሰው ይቅርታ በምናደርግበት ጊዜ ይቅር የምንለው እንደ እኛው ኃጢአተኛ የሆነን ሰው ነው። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ እኛው ራሳችን ሌላ ሰው በድለን ይቅርታ እንደምንጠይቅ እናውቃለን። (ማቴዎስ 6:12) ይሁን እንጂ ይሖዋ ይቅር መባል የማያስፈልገው ቢሆንም እንኳ ‘በብዙ ይቅር ይላል’! በእርግጥም ፍቅራዊ ደግነቱ እጅግ ታላቅ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ በምሕረቱ የሰማይን መስኮቶች በመክፈት በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ በሚመለሱት ሰዎች ላይ በረከቱን ያፈስሳል።—ሚልክያስ 3:10
ወደ ይሖዋ የሚመለሱ ሰዎች የሚያገኟቸው በረከቶች
23. ይሖዋ ቃሉ በእርግጠኝነት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?
23 ይሖዋ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል:- “ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፣ ምድርን እንደሚያረካት፣ ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት፣ ዘርንም ለሚዘራ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፣ ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም።” (ኢሳይያስ 55:10, 11) ይሖዋ የተናገረው ሁሉ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ጥርጥር የለውም። ዝናብና በረዶ ከሰማይ ወርደው ምድርን በማርካትና ፍሬ እንድታፈራ በማድረግ ተልዕኳቸውን እንደሚፈጽሙ ሁሉ ከይሖዋ አፍ የወጣ ቃልም ፍጹም አስተማማኝ ነው። ቃል የገባውን ነገር ያላንዳች ጥርጥር ይፈጽመዋል።—ዘኍልቁ 23:19
24, 25. ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል ያስተላለፈውን መልእክት ተቀብለው ተግባራዊ የሚያደርጉ አይሁዳውያን ግዞተኞች ምን በረከቶች ይጠብቋቸዋል?
24 በመሆኑም አይሁዳውያን በኢሳይያስ በኩል በትንቢት የተነገሩትን ቃላት ተግባራዊ ካደረጉ ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት እንደሚያድናቸው የተረጋገጠ ነው። ይህም ከፍተኛ ደስታ ያስገኝላቸዋል። ይሖዋ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “እናንተም በደስታ ትወጣላችሁ በሰላምም ትሸኛላችሁ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በፊታችሁ እልልታ ያደርጋሉ፣ የሜዳም ዛፎች ሁሉ ያጨበጭባሉ። በእሾህም ፋንታ ጥድ በኩርንችትም ፋንታ ባርሰነት ይበቅላል፤ ለእግዚአብሔርም መታሰቢያና ለዘላለምም የማይጠፋ ምልክት ይሆናል።”—ኢሳይያስ 55:12, 13
25 በእርግጥም አይሁዳውያን ግዞተኞች በ537 ከዘአበ በታላቅ ደስታ ከባቢሎን ምድር ወጥተዋል። (መዝሙር 126:1, 2) ኢየሩሳሌም በርከት ላሉ አሥርተ ዓመታት ባድማ ሆና በመቆየቷ እሾህና ኩርንችት ወርሷት ነበር። ይሁን እንጂ አሁን ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱት የአምላክ ሕዝቦች መልሰው ውበት ሊያላብሷት ይችላሉ። በእሾህና በኩርንችት ፋንታ እንደ ጥድና ባርሰነት ያሉ ረጃጅም ዛፎች ይበቅላሉ። ሕዝቡ ‘በእልልታ’ ሲያገለግሉት የይሖዋ በረከት በግልጽ ጎልቶ ይታያል። ምድሪቱ ራሷ ሐሴት ያደረገች ያህል ይሆናል።
26. በዘመናችን የአምላክ ሕዝቦች ምን በረከት አግኝተዋል?
26 በ1919 በምድር ላይ ያሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከመንፈሳዊ ግዞት ነፃ ወጥተዋል። (ኢሳይያስ 66:8) በአሁኑ ጊዜ የሌሎች በጎች አባላት ከሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች ጋር በአንድነት ሆነው አምላክን በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ በደስታ እያገለገሉት ነው። ከማንኛውም ባቢሎናዊ ተጽዕኖ በመላቀቅ የአምላክን ሞገስ አግኝተዋል። ይህም ለይሖዋ “መታሰቢያ” ሆኗል። መንፈሳዊ ብልጽግናቸው ስሙን የሚያስከብር ከመሆኑም በላይ እውነተኛ ትንቢት የሚናገር አምላክ መሆኑን በሚገባ ይመሰክራል። ይሖዋ ያደረገላቸው ነገር አምላክነቱን በግልጽ የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ ቃሉን እንደሚጠብቅና ንስሐ ለሚገቡ ሰዎች ምሕረት እንደሚያደርግ የሚያረጋግጥ ጥሩ ማስረጃ ነው። ‘የወይን ጠጅና ወተት ያለ ገንዘብና ያለ ዋጋ መግዛታቸውን’ የሚቀጥሉ ሰዎች ሁሉ ይሖዋን ለዘላለም በማገልገል እንዲደሰቱ ምኞታችን ነው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በጥንቶቹ የባቢሎን የንግድ ሥራ መዝገቦች ላይ በርካታ የአይሁዳውያን ስሞች ተገኝተዋል።
b ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በበላይነት መቆጣጠሩን ቀጥሏል። (ራእይ 14:14-16) በአሁኑ ጊዜ ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች ኢየሱስን የጉባኤው ራስ አድርገው ያዩታል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ደግሞ ኢየሱስ በአርማጌዶን በአምላክ ጠላቶች ላይ የሚከፈተውን ወሳኝ የሆነ ውጊያ በመምራት ለየት ባለ መንገድ “መሪና አዛዥ” ሆኖ እርምጃ ይወስዳል።—ራእይ 19:19-21
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 234 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመንፈሳዊ የተጠሙ አይሁዳውያን ‘ውኃው ወዳለበት እንዲመጡ’ እና ‘የወይን ጠጅና ወተት እንዲገዙ’ ግብዣ ቀርቦላቸዋል
[በገጽ 239 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ለወገኖች “መሪና አዛዥ” መሆኑን አስመስክሯል
[በገጽ 244, 245 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
‘ክፉ ሰው መንገዱን ይተው’