ለአምላክ ሕዝብ የተሰጠ ማጽናኛ
ምዕራፍ አሥራ ሁለት
ለአምላክ ሕዝብ የተሰጠ ማጽናኛ
1. ኢየሩሳሌምና ነዋሪዎቿ ምን ዓይነት የጨለማ ጊዜ ይጠብቃቸዋል? ሆኖም ምን ተስፋ ተሰጥቷቸዋል?
የይሁዳ ሕዝብ በባቢሎን ተማርኮ ለሰባ ዓመታት በግዞት ይኖራል። ይህ ደግሞ የአንድ ሰው አማካይ ዕድሜ ነው። (መዝሙር 90:10፤ ኤርምያስ 25:11፤ 29:10) ወደ ባቢሎን ተማርከው ከሚወሰዱት እስራኤላውያን መካከል አብዛኞቹ እዚያው አርጅተው ይሞታሉ። ጠላቶቻቸው ሲያላግጡባቸውና ሲሳለቁባቸው ምን ያህል በኀፍረት እንደሚሸማቀቁ አስበው። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ስሙን ያኖረባት ከተማ ለረጅም ዘመን ባድማ ሆና ስትቆይ በአምላካቸው ስም ላይ የሚደርሰውን ከፍተኛ ነቀፋ አስብ። (ነህምያ 1:9፤ መዝሙር 132:13፤ 137:1-3) ሰሎሞን ለይሖዋ አገልግሎት እንዲወሰን ባደረገበት ወቅት በአምላክ ክብር ተሞልቶ የነበረው እጅግ ተወዳጅ የሆነው ቤተ መቅደስም ይጠፋል። (2 ዜና መዋዕል 7:1-3) በእርግጥም ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ጊዜ እጅግ ተስፋ አስቆራጭ ነው! ይሁን እንጂ ይሖዋ ወደ ትውልድ አገራቸው የሚመለሱበት ጊዜ እንደሚመጣ በኢሳይያስ በኩል ተንብዮአል። (ኢሳይያስ 43:14፤ 44:26-28) በኢሳይያስ መጽሐፍ 51ኛ ምዕራፍ ውስጥ ይህን አጽናኝና ተስፋ ሰጪ መልእክት የሚያጠናክሩ ተጨማሪ ትንቢቶች ተጠቅሰው እናገኛለን።
2. (ሀ) ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል የሚያጽናና መልእክት የላከው ለእነማን ነው? (ለ) ታማኝ አይሁዳውያን ‘ጽድቅን የሚከተሉት’ እንዴት ነው?
2 ይሖዋ ልባቸውን ወደ እሱ ላዘነበሉ አይሁዳውያን እንዲህ ሲል ተናገረ:- “እናንተ ጽድቅን የምትከተሉ እግዚአብሔርንም የምትሹ፣ ስሙኝ።” (ኢሳይያስ 51:1ሀ) “ጽድቅን የምትከተሉ” የሚለው አገላለጽ ድርጊትን ያመለክታል። ‘ጽድቅን የሚከተሉ’ ሰዎች የአምላክ ሕዝብ መሆናቸውን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም ያሳያሉ። ጻድቅ ሆነው ለመገኘትና ከአምላክ ፈቃድ ጋር ተስማምተው ለመኖር ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። (መዝሙር 34:15፤ ምሳሌ 21:21) ብቸኛው የጽድቅ ምንጭ ይሖዋ መሆኑን በማመን ‘ይሖዋን ይሻሉ።’ (መዝሙር 11:7፤ 145:17) ይህን የሚያደርጉት ይሖዋን ሳያውቁ ቀርተው ወይም ወደ እሱ እንዴት መጸለይ እንደሚቻል ጠፍቷቸው አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋን በማምለክ፣ ወደ እሱ በመጸለይና በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው አመራሩን ለማግኘት በመጣር ይበልጥ ወደ እሱ ለመቅረብ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ።
3, 4. (ሀ) አይሁዳውያን ተቆርጠው የወጡበት “ዐለት” ማን ነው? ተቆፍረው የወጡበት ‘ጉድጓድስ’ ማንን ያመለክታል? (ለ) አይሁዳውያን ቅድመ አያቶቻቸውን መለስ ብለው ማስታወሳቸው ማጽናኛ የሚሰጣቸው ለምንድን ነው?
3 ይሁን እንጂ ከልባቸው ጽድቅን የሚከተሉት አይሁዳውያን በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በቁጥር በጣም ጥቂት በመሆናቸው ድፍረት ሊያጡና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል። ስለሆነም ይሖዋ የድንጋይ ካባን እንደ ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም የሚከተለውን ማበረታቻ ሰጣቸው:- “ከእርሱ የተቈረጣችሁበትን ድንጋይ [“ዐለት፣” አ.መ.ት ] ከእርሱም የተቈፈራችሁበትን ጉድጓድ ተመልከቱ። ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፣ ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሳራ ተመልከቱ፤ አንድ ብቻውን በሆነ ጊዜ ጠራሁት፣ ባረክሁትም አበዛሁትም።” (ኢሳይያስ 51:1ለ, 2) አይሁዳውያን ተቆርጠው የወጡበት “ዐለት” እስራኤላውያን እጅግ ይኮሩበት የነበረውና በታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ ከሚሰጣቸው ሰዎች አንዱ የሆነው አብርሃም ነው። (ማቴዎስ 3:9፤ ዮሐንስ 8:33, 39) የእስራኤል ሕዝብ ቅድመ አያት ነው። “ጉድጓድ” የተባለችው ሳራ ስትሆን የእስራኤላውያን አባት የሆነው ይስሐቅ የወጣው ከሳራ ማኅፀን ነው።
4 አብርሃምና ሳራ ልጅ ያልነበራቸው ከመሆኑም በላይ ዘር ማፍራት የሚችሉበት ዕድሜ አልፎ ነበር። ሆኖም ይሖዋ አብርሃምን እንደሚባርከውና ‘እንደሚያበዛው’ ቃል ገብቶለት ነበር። (ዘፍጥረት 17:1-6, 15-17) አብርሃምና ሳራ በመለኮታዊ ኃይል አማካኝነት በስተርጅናቸው ዘር ማፍራት የቻሉ ሲሆን የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብም የተገኘው ከዚህ ልጅ ነው። በዚህ መንገድ ይሖዋ ይህን አንድ ሰው በሰማይ እንዳሉ ከዋክብት ሊቆጠር የማይችል ታላቅ ሕዝብ አባት አደረገው። (ዘፍጥረት 15:5፤ ሥራ 7:5) እንግዲያው ይሖዋ አብርሃምን ከሩቅ አገር ወስዶ ታላቅ ሕዝብ ሊያደርገው ከቻለ ታማኝ አይሁዳውያን ቀሪዎችን ከባቢሎን የባርነት ቀንበር አላቅቆ ወደ ትውልድ አገራቸው በመመለስ ዳግመኛ ታላቅ ሕዝብ ለማድረግ የገባውን ቃል መፈጸም እንደማይሳነው ጥርጥር የለውም። አምላክ ለአብርሃም የገባው ቃል እንደተፈጸመ ሁሉ በግዞት ለሚኖሩት አይሁዶች የገባው ቃልም መፈጸሙ አይቀርም።
5. (ሀ) አብርሃምና ሳራ ማንን ይወክላሉ? አብራራ። (ለ) በትንቢቱ የመጨረሻ ፍጻሜ መሠረት ‘ከዐለቱ’ የወጣው ሕዝብ የትኛው ነው?
5 በኢሳይያስ 51:1, 2 ላይ በምሳሌያዊ ሁኔታ የተገለጸው ድንጋይ የማውጣት ሥራ ሌላም ትርጉም አለው። ዘዳግም 32:18 [አ.መ.ት ] የእስራኤል አባት የሆነውንና እስራኤልን ‘የወለደውን’ ይሖዋን “ዐለት” ብሎ ይጠራዋል። እዚህ ላይ ይሖዋ እስራኤልን መውለዱን ለመግለጽ የገባው የዕብራይስጥ ግስ ኢሳይያስ 51:2 ላይ ሳራ እስራኤልን እንደወለደች ለመግለጽ ከተጠቀሰው የዕብራይስጥ ግስ ጋር ተመሳሳይ ነው። በመሆኑም አብርሃም በትንቢታዊ ሁኔታ ታላቁን አብርሃም ማለትም ይሖዋን ይወክላል። የአብርሃም ሚስት ሳራ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክ ሚስት ወይም ሴት ተደርጋ የተገለጸችውን መንፈሳዊ ፍጥረታት ያቀፈችውን የይሖዋን ሰማያዊት ድርጅት ትወክላለች። (ዘፍጥረት 3:15፤ ራእይ 12:1, 5) በኢሳይያስ ትንቢት ላይ በተገለጹት በእነዚህ ቃላት የመጨረሻ ፍጻሜ መሠረት ‘ከዐለቱ’ የወጣው ሕዝብ ‘የእግዚአብሔር እስራኤል’ ማለትም በ33 እዘአ የተቋቋመው በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ጉባኤ ነው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቀደም ባሉት ምዕራፎች ላይ እንደተገለጸው ይህ ሕዝብ በ1918 በባቢሎን ቀንበር ሥር ወድቆ የነበረ ቢሆንም በ1919 ቀድሞ የነበረውን መንፈሳዊ ብልጽግና መልሶ አግኝቷል።—ገላትያ 3:26-29፤ 4:28፤ 6:16
6. (ሀ) የይሁዳ ምድር ምን ይደርስባታል? ወደ ቀድሞ ሁኔታዋ የምትመለሰውስ እንዴት ነው? (ለ) ኢሳይያስ 51:3 ዘመናዊ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
6 ይሖዋ ለጽዮን ወይም ለኢየሩሳሌም ማጽናኛ የሰጠው ሕዝቡን እንደሚያበዛ ቃል በመግባት ብቻ አልነበረም። ትንቢቱ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርም ጽዮንን ያጽናናል፤ በእርስዋም ባድማ የሆነውን ሁሉ ያጽናናል፣ ምድረ በዳዋንም እንደ ዔድን በረሀዋንም እንደ እግዚአብሔር ገነት ያደርጋል፤ ደስታና ተድላ ምስጋናና የዝማሬ ድምፅ ይገኝበታል።” (ኢሳይያስ 51:3) የይሁዳ ምድር ባድማ ሆና በምትቆይባቸው 70 ዓመታት ወደ ምድረ በዳነት ተለውጣ እንደ እሾህና ቁጥቋጦ ያሉ የበረሃ ዕጽዋት ይወርሷታል። (ኢሳይያስ 64:10፤ ኤርምያስ 4:26፤ 9:10-12) ስለዚህ አይሁዳውያን ዳግመኛ በምድሪቱ ከመስፈራቸው በተጨማሪ ምድሪቱ ወደ ቀድሞ ሁኔታዋ ተመልሳ ልክ እንደ ኤድን ውኃ እንደ ልብ የሚንዶለዶልባት ምርታማና ፍሬያማ የአትክልት ሥፍራ መሆን ያስፈልጋታል። ምድሪቱ ሐሴት ታደርጋለች። ባድማ ሆና ከኖረችበት ዘመን ጋር ሲወዳደር ወደ ገነትነት የተለወጠች ያህል ትሆናለች። ቅቡዓን የሆኑት የአምላክ እስራኤል ቀሪዎች በ1919 ከዚህ ጋር ወደሚመሳሰል መንፈሳዊ ገነት ገብተዋል።—ኢሳይያስ 11:6 - 9፤ 35:1-7
በይሖዋ ለመተማመን የሚያስችሉ ምክንያቶች
7, 8. (ሀ) ይሖዋ ሕዝቡ ጆሯቸውን እንዲሰጡት ሲጠይቅ ምን ማለቱ ነበር? (ለ) ይሁዳ ይሖዋን መታዘዟ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
7 ይሖዋ ዳግመኛ በጥሞና እንዲያዳምጡት በመጠየቅ እንዲህ አለ:- “ወገኔ ሆይ፣ አድምጠኝ፤ ሕዝቤ ሆይ፣ ስማኝ፤ ሕግ ከእኔ ይወጣልና ፍርዴም ለአሕዛብ ብርሃን ይሆናልና። ጽድቄ ፈጥኖ ቀርቦአል፣ ማዳኔም ወጥቶአል፣ ክንዴም በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል፤ ደሴቶች እኔን በመተማመን ይጠባበቃሉ፣ በክንዴም ይታመናሉ።”—ኢሳይያስ 51:4, 5
8 ይሖዋ ጆሯቸውን እንዲሰጡት የጠየቀው እንዲሁ መልእክቱን እንዲሰሙት ብቻ ብሎ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ቃሉን በጥሞና ሰምተው ተግባራዊ እንዲያደርጉ መጠየቁ ነበር። (መዝሙር 49:1፤ 78:1) ሕዝቡ መመሪያ፣ ፍትሕም ሆነ መዳን የሚገኘው ከይሖዋ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋቸው ነበር። መንፈሳዊ ብርሃን ሊፈነጥቅ የሚችለው ከእሱ ብቻ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:6) የሰው ልጆች የመጨረሻው ከፍተኛ ዳኛ እሱ ነው። ይሖዋ የሚያወጣቸው ሕግጋትና የሚሰጣቸው ብያኔዎች ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች ብርሃን ሆነው ያገለግላሉ።—መዝሙር 43:3፤ 119:105፤ ምሳሌ 6:23
9. ከአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብ በተጨማሪ ይሖዋ በሚወስደው የማዳን እርምጃ የሚጠቀሙት እነማን ናቸው?
9 ይህ ሐቅ የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብን ብቻ ሳይሆን እጅግ ርቀው በሚገኙ የባሕር ደሴቶች የሚኖሩትን ጨምሮ በየትም ሥፍራ የሚገኙ ጥሩ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎችም ይመለከታል። በአምላክም ሆነ ታማኝ አገልጋዮቹን ለማዳን ባለው ችሎታ ላይ ያላቸው እምነት ከንቱ ሆኖ አይቀርም። በክንዱ የተመሰለው የአምላክ ኃይል ማንም ሊገታው የማይችል በመሆኑ እጅግ አስተማማኝ ነው። (ኢሳይያስ 40:10፤ ሉቃስ 1:51, 52) በዘመናችንም በምድር ላይ ያሉት የአምላክ እስራኤል አባላት በቅንዓት እያከናወኑት ያሉት የስብከት ሥራ በባሕር ደሴቶች የሚኖሩ በርካታ ሰዎችን ጨምሮ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡና እምነታቸውን በእሱ ላይ እንዲጥሉ አድርጓቸዋል።
10. (ሀ) ንጉሥ ናቡከደነፆር የትኛውን እውነታ ለመገንዘብ ይገደዳል? (ለ) የሚጠፉት “ሰማያት” እና “ምድር” የትኞቹ ናቸው?
10 በመቀጠል ይሖዋ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሊያውቀው የሚገባውን አንድ እውነታ ገልጿል። ይሖዋ ፈቃዱን እንዳይፈጽም ሊያግደው የሚችል ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ፍጥረት የለም። (ዳንኤል 4:34, 35) እንዲህ ሲል ተናገረ:- “ዓይናችሁን ወደ ሰማይ አንሡ፣ ወደ ታችም ወደ ምድር ተመልከቱ፤ ሰማያት እንደ ጢስ በንነው ይጠፋሉ፣ ምድርም እንደ ልብስ ታረጃለች፣ የሚኖሩባትም እንዲሁ ይሞታሉ [“እንደ አሸን ፈጥነው ይረግፋሉ፣” አ.መ.ት ]፤ ማዳኔ ግን ለዘላለም ይሆናል፣ ጽድቄም አይፈርስም።” (ኢሳይያስ 51:6) ምንም እንኳ የባቢሎናውያን ነገሥታት ፖሊሲ ግዞተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚፈቅድ ባይሆንም ይሖዋ ሕዝቡን ለማዳን የሚወስደውን እርምጃ ሊያጨናግፍ የሚችል አይኖርም። (ኢሳይያስ 14:16, 17) የባቢሎናውያን “ሰማያት” ወይም ገዥዎች ድል ተመትተው እንዳልነበሩ ይሆናሉ። የባቢሎናውያን “ምድር” ማለትም በእነዚህ ገዢዎች ሥር የሚተዳደረው ተራው ሕዝብም ቀስ በቀስ ደብዛው ይጠፋል። አዎን፣ በዘመኑ የነበረው ኃያል መንግሥት እንኳ የይሖዋን ኃይል ሊቋቋም ወይም ሕዝቡን ለማዳን የሚወስደውን እርምጃ ሊያሰናክል አይችልም።
11. የባቢሎናውያን “ሰማያት” እና “ምድር” እንደሚጠፉ የተነገረው ትንቢት ሙሉ በሙሉ መፈጸሙ በዘመናችን ላሉ ክርስቲያኖች አበረታች የሆነው ለምንድን ነው?
11 በዘመናችን ያሉ ክርስቲያኖች እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት ሙሉ በሙሉ ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ማወቃቸው ጥሩ ማበረታቻ ይሆንላቸዋል። ለምን? ሐዋርያው ጴጥሮስ ወደፊት ስለሚፈጸም ሁኔታ በተናገረ ጊዜ ተመሳሳይ የሆኑ መግለጫዎችን የተጠቀመ በመሆኑ ነው። ጴጥሮስ እጅግ እየቀረበ ስላለው የይሖዋ ቀን የተናገረ ሲሆን በዚያ ቀን “ሰማያት በእሳት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በታላቅ ትኩሳት ይፈታል።” አክሎም “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” ሲል ተናግሯል። (2 ጴጥሮስ 3:12, 13፤ ኢሳይያስ 34:4፤ ራእይ 6:12-14) ኃያላን ብሔራትና በከዋክብት የተመሰሉት የበላይ ገዥዎቻቸው ይሖዋን ለመቃወም ቢሞክሩም ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ በአንድ ጊዜ እንደ አሸን ረግፈው ድምጥማጣቸው ይጠፋል። (መዝሙር 2:1-9) ከዚያ በኋላ ጻድቅ በሆነው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ላይ የሚገዛው የአምላክ የጽድቅ መስተዳድር ብቻ ይሆናል።—ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 21:1-4
12. የአምላክ አገልጋዮች ተቃዋሚ የሆኑ ሰዎች የሚሰነዝሩባቸው ዘለፋና ትችት ሊያስፈራቸው የማይገባው ለምንድን ነው?
12 በመቀጠል ይሖዋ ‘ጽድቅን ለሚከተሉ ሰዎች’ እንዲህ አለ:- “ጽድቅን የምታውቁ ሕጌም በልባችሁ ያለ ሕዝብ ሆይ፣ ስሙኝ፤ የሰውን ተግዳሮት አትፍሩ፣ በስድባቸውም አትደንግጡ። እንደ ልብስም ብል ይበላቸዋል፣ እንደ በግ ጠጉርም ትል ይበላቸዋል፤ ጽድቄ ግን ለዘላለም ማዳኔም ለትውልድ ሁሉ ይሆናል።” (ኢሳይያስ 51:7, 8) በይሖዋ የሚታመኑት ሰዎች የጸና አቋም በመያዛቸው ምክንያት ዘለፋና ትችት ይደርስባቸዋል። ሆኖም ይህ ሊያስፈራቸው አይገባም። የሚያንቋሽሿቸው ግለሰቦች ብል እንደሚያነክተው ልብስ ‘የሚበሉ’ ሟች ሰዎች ናቸው። ልክ እንደ ጥንቶቹ ታማኝ አይሁዳውያን ዛሬ ያሉት እውነተኛ ክርስቲያኖችም ተቃዋሚዎቻቸውን የሚፈሩበት ምንም ምክንያት የለም። ዘላለማዊ አምላካቸው ይሖዋ ያድናቸዋል። (መዝሙር 37:1, 2) የይሖዋ አገልጋዮች ከአምላክ ጠላቶች የሚደርስባቸው ነቀፋ የይሖዋ መንፈስ እንዳላቸው የሚጠቁም ማስረጃ ነው።—ማቴዎስ 5:11, 12፤ 10:24-31
13, 14. “ረዓብ” እና “የባሕር ዘንዶ” የሚሉት መግለጫዎች ማንን ያመለክታሉ? ይህ ዘንዶ ‘የተቆራረጠውና የተወጋውስ’ እንዴት ነው?
13 ኢሳይያስ ይሖዋ በግዞት የሚኖሩትን ሕዝቡን እንዲታደግ ጥሪ የሚያቀርብ በሚመስል ሁኔታ እንዲህ ሲል ተናገረ:- “የእግዚአብሔር ክንድ ሆይ፣ ተነሥ፣ ተነሥ፣ ኃይልንም ልበስ፤ በቀድሞው ወራትና በጥንቱ ዘመን በነበረው ትውልድ እንደ ሆነው ተነሥ። ረዓብን የቈራረጥህ ዘንዶውንም [“የባሕር ዘንዶ፣” የ1980 ትርጉም ] የወጋህ አንተ አይደለህምን? ባሕሩንና የታላቁን ጥልቅ ውኃ ያደረቅኸው፣ የዳኑትም ይሻገሩ ዘንድ ጠሊቁን ባሕር መንገድ ያደረግህ አንተ አይደለህምን?”—ኢሳይያስ 51:9, 10
14 ኢሳይያስ የጠቀሳቸው ታሪካዊ ክንውኖች እጅግ ተስማሚ የሆኑ ምሳሌዎች ናቸው። የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ እንዴት ነፃ እንደወጣና ቀይ ባሕርን እንዴት እንደተሻገረ እያንዳንዱ እስራኤላዊ ጠንቅቆ ያውቃል። (ዘጸአት 12:24-27፤ 14:26-31) “ረዓብ” እና “የባሕር ዘንዶ” የሚሉት መግለጫዎች እስራኤላውያን እንዳይወጡ ከልክሎ በነበረው ፈርዖን ትተዳደር የነበረችውን ግብጽን ያመለክታሉ። (መዝሙር 74:13፤ 87:4፤ ኢሳይያስ 30:7) የናይል ወንዝ ደለል ከሚገኝበት ቦታ አንስቶ በመቶዎች የሚቆጠር ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለውን ለም የናይል ሸለቆ የምታካልለው የጥንቷ ግብጽ እጅግ ግዙፍ በሆነ ዘንዶ ተመስላለች። (ሕዝኤል 29:3 አ.መ.ት ) ይሁን እንጂ ይሖዋ አሥሩን መቅሠፍቶች ባወረደበት ጊዜ ይህ ዘንዶ ተቆራርጧል። ሠራዊቱ በቀይ ባሕር በሰጠመበት ጊዜ ተወግቶና ክፉኛ ቆስሎ ተሽመድምዷል። አዎን፣ ይሖዋ በግብጽ ላይ በወሰደው እርምጃ ክንዱ ምን ያህል ኃያል እንደሆነ በግልጽ አሳይቷል። በባቢሎን በግዞት የሚኖሩትን ሕዝቦቹን ለመታደግም ከዚህ ባልተናነሰ ሁኔታ እርምጃ እንደሚወስድ ጥርጥር የለውም።
15. (ሀ) የጽዮን ኀዘንና ልቅሶ የሚወገደው መቼና እንዴት ነው? (ለ) በዘመናችን የአምላክ እስራኤል አባላት ኀዘንና ልቅሶ የተወገደው መቼ ነው?
15 ትንቢቱ በመቀጠል ከረጅም ዘመን በኋላ አይሁዳውያን ከባቢሎን ነፃ የሚወጡበትን ሁኔታ በማስመልከት እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ ወደ ጽዮንም ይመጣሉ፤ የዘላለምም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ደስታንና ተድላን ያገኛሉ፣ ኀዘንና ልቅሶም ይሸሻል።” (ኢሳይያስ 51:11) የይሖዋን ጽድቅ የሚሹ በባቢሎን በግዞት የሚኖሩ አይሁዳውያን ለጊዜው ያሉበት ሁኔታ ምንም ያህል መጥፎና አሳዛኝ ቢሆን እጅግ አስደሳች ተስፋ ይጠብቃቸዋል። ኀዘንና ልቅሶ የሚቀሩበት ጊዜ ይመጣል። ይሖዋ የታደጋቸው ወይም የተቤዣቸው ሰዎች በታላቅ ደስታና ዝማሬ ሐሴት ያደርጋሉ። በዘመናችንም የአምላክ እስራኤል አባላት በ1919 ከባቢሎን ምርኮ ነፃ በወጡበት ጊዜ እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። በታላቅ ደስታ ወደ ቀድሞ መንፈሳዊ ርስታቸው የተመለሱ ሲሆን ይህ ደስታ እስከ ዘመናችን ድረስ ዘልቋል።
16. አይሁዳውያንን ለመቤዠት ምን ዋጋ ተከፍሏል?
16 አይሁዳውያንን ለመቤዠት የሚከፈለው ዋጋ ምንድን ነው? የኢሳይያስ ትንቢት ይሖዋ ‘ግብጽን ቤዛ፣ ኢትዮጵያንና ሳባንም ፋንታ’ አድርጎ እንደሰጠ ቀደም ብሎ ገልጿል። (ኢሳይያስ 43:1-4) ይህ የሚሆነው ቆየት ብሎ ነው። የፋርስ መንግሥት ባቢሎንን ድል አድርጎ አይሁዳውያን ምርኮኞችን ነፃ ካወጣ በኋላ ግብጽን፣ ኢትዮጵያንና ሳባን ወርሮ ይይዛል። እነዚህ ብሔራት በእስራኤላውያን ነፍሳት ፋንታ ይሰጣሉ። ይህ በምሳሌ 21:18 ላይ ከሚገኘው “ኀጥእ የጻድቅ ቤዛ ነው፤ በደለኛም የቅን ሰው ቤዛ ነው” ከሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር የሚስማማ ነው።
ተጨማሪ ማጽናኛ
17. አይሁዳውያን የባቢሎንን ቁጣ መፍራት የሌለባቸው ለምንድን ነው?
17 ይሖዋ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ተጨማሪ ማጽናኛ ሰጠ:- “የማጽናናችሁ እኔ ነኝ፣ እኔ ነኝ፤ የሚሞተውን ሰው እንደ ሣርም የሚጠወልገውን የሰው ልጅ ትፈራ ዘንድ አንተ ማን ነህ? ሰማያትንም የዘረጋውን ምድርንም የመሠረተውን ፈጣሪህን እግዚአብሔርን ረስተሃል፤ ያጠፋ ዘንድ ባዘጋጀ ጊዜ ከአስጨናቂው ቁጣ የተነሣ ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ፈርተሃል፤ የአስጨናቂው ቁጣ የት አለ?” (ኢሳይያስ 51:12, 13) አይሁዳውያን ለበርካታ ዓመታት በግዞት የመኖር ዕጣ ይጠብቃቸዋል። ያም ሆኖ የባቢሎንን ቁጣ የሚፈሩበት ምንም ምክንያት የለም። ምንም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ የተጠቀሰችው ሦስተኛዋ የዓለም ኃያል መንግሥት የአምላክን ሕዝብ ድል አድርጋ በመያዝ ‘ለማስጨነቅ’ ወይም ማምለጫ ቀዳዳ ለማሳጣት የምትሞክር ቢሆንም ታማኝ አይሁዳውያን ባቢሎን በቂሮስ እጅ እንደምትወድቅ አስቀድሞ እንደተተነበየ ያውቃሉ። (ኢሳይያስ 44:8, 24-28) የባቢሎን ነዋሪዎች ከፈጣሪ ማለትም ዘላለማዊ አምላክ ከሆነው ከይሖዋ ጋር ሲነጻጸሩ በበጋ ወራት በጠራራ ፀሐይ እንደሚጠወልግና እንደሚደርቅ ሣር በመሆናቸው ወዲያውኑ ይጠፋሉ። በዚያን ጊዜ ዛቻቸውና ቁጣቸው የሚፈይደው ነገር አይኖርም። ሰማይንና ምድርን የፈጠረውን ይሖዋን ረስቶ ሰውን መፍራት እንዴት ያለ ሞኝነት ነው!
18. ይሖዋ ሕዝቡ ለተወሰነ ጊዜ እስረኛ ሆነው የሚቆዩ ቢሆንም እንኳ ምን ዋስትና ሰጣቸው?
18 ምንም እንኳ የይሖዋ ሕዝቦች ለተወሰነ ጊዜ “ምርኮኛ” ሆነው ቢቆዩም በድንገት ነፃ ይወጣሉ። ዘራቸው በባቢሎን ምድር ጠፍቶ አይቀርም፤ ወይም እስረኛ በመሆናቸው በረሃብ አለንጋ ተገርፈው ወደ ጉድጓድ ማለትም ወደ ሲኦል አይወርዱም። (መዝሙር 30:3፤ 88:3-5) ይሖዋ የሚከተለውን ዋስትና ሰጣቸው:- “ምርኮኛ ፈጥኖ ይፈታል፤ አይሞትም ወደ ጉድጓድም አይወርድም፣ እንጀራም አይጐድልበትም።”—ኢሳይያስ 51:14
19. ታማኝ አይሁዳውያን ይሖዋ በገባው ቃል ላይ ሙሉ በሙሉ መተማመን የሚችሉት ለምንድን ነው?
19 አሁንም ይሖዋ ጽዮንን ማጽናናቱን በመቀጠል እንዲህ አለ:- “ሞገዱም እንዲተምም ባሕርን የማናውጥ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፣ ስሜም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። ሰማያትን እዘረጋ ዘንድ ምድርንም እመሠርት ዘንድ፣ ጽዮንንም:- አንቺ ሕዝቤ ነሽ እል ዘንድ ቃሌን በአፍህ አድርጌአለሁ፣ በእጄም ጥላ ጋርጄሃለሁ።” (ኢሳይያስ 51:15, 16) መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ባሕርን ለመቆጣጠር የሚያስችል ኃይል እንዳለው በተደጋጋሚ ጊዜያት ይናገራል። (ኢዮብ 26:12፤ መዝሙር 89:9፤ ኤርምያስ 31:35) ሕዝቡን ከግብጽ ነፃ ባወጣበት ጊዜ በግልጽ እንደታየው የተፈጥሮ ኃይሎችን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ይችላል። “የሠራዊት ጌታ” ከሆነው ከይሖዋ ጋር ሊወዳደር የሚችል ይኖራልን?—መዝሙር 24:10
20. ይሖዋ ጽዮንን ዳግመኛ በሚያቋቁምበት ጊዜ የሚመሠረቱት “ሰማይ” እና “ምድር” የትኞቹ ናቸው? ምን አጽናኝ ቃልስ ይናገራል?
20 አይሁዳውያን የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብ ሆነው ይቀጥላሉ። ይሖዋ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው እንደቀድሞው በእሱ ሕግ እየተመሩ እንደሚኖሩ ዋስትና ሰጥቷቸዋል። ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሱን ዳግመኛ ገንብተው ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት ከእነሱ ጋር በገባው ቃል ኪዳን ላይ የተገለጹትን ኃላፊነቶቻቸውን እንደገና መፈጸም ይጀምራሉ። ከምርኮ የተመለሱት እስራኤላውያንና የቤት እንስሶቻቸው ዳግም በምድሪቱ ላይ ሲሠፍሩ “አዲስ ምድር” ትመሠረታለች። በምድሪቱም ላይ “አዲስ ሰማይ” ማለትም አዲስ መስተዳድር ይዘረጋል። (ኢሳይያስ 65:17-19፤ ሐጌ 1:1, 14) ይሖዋ ጽዮንን ዳግመኛ “አንቺ ሕዝቤ ነሽ” ይላታል።
ለኢየሩሳሌም የቀረበ ጥሪ
21. ይሖዋ ምን ጥሪ አቀረበ?
21 ይሖዋ ጽዮንን ካጽናና በኋላ አንድ እርምጃ እንድትወስድ ጥሪ አቀረበ። መከራዋ ሁሉ ያበቃበት ጊዜ ላይ የደረሰች በሚመስል ሁኔታ እንዲህ ሲል ተናገረ:- “ከእግዚአብሔር እጅ የቁጣውን ጽዋ የጠጣሽ ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ንቂ፣ ንቂ፣ ቁሚ፤ የሚያንገደግድን ዋንጫ ጠጥተሻል ጨልጠሽውማል።” (ኢሳይያስ 51:17) አዎን፣ ኢየሩሳሌም ከደረሰባት አስከፊ ውድቀት በማንሰራራት የቀድሞ ግርማና ውበቷን መላበስ ይኖርባታል። ምሳሌያዊውን የመለኮታዊ ቁጣ ጽዋ ምንም ሳታስቀር ጨልጣ የምትጠጣበት ጊዜ ይመጣል።
22, 23. ኢየሩሳሌም የይሖዋን የቁጣ ጽዋ ስትጠጣ ምን ይደርስባታል?
22 ይሁንና ኢየሩሳሌም በምትቀጣበት ጊዜ ከነዋሪዎቿ ማለትም ‘ከልጆችዋ’ መካከል የሚደርስባትን መከራ ሊያስቀር የሚችል አይኖርም። (ኢሳይያስ 43:5-7፤ ኤርምያስ 3:14) ትንቢቱ እንዲህ ይላል:- “ከወለደቻቸው ልጆች ሁሉ የሚመራት የለም፣ ካሳደገቻቸውም ልጆች ሁሉ እጅዋን የሚይዝ የለም።” (ኢሳይያስ 51:18) በባቢሎናውያን እጅ የሚደርስባት መከራ ምንኛ አስከፊ ነው! “እነዚህ ሁለት ነገሮች ሆነውብሻል፣ ማንስ ያስተዛዝንሻል? መፈታትና ጥፋት ራብና ሰይፍ ናቸው፤ እንዴትስ አድርጌ አጽናናሻለሁ? ልጆችሽ ዝለዋል፤ በወጥመድ እንደ ተያዘ ሚዳቋ በአደባባይ ሁሉ ራስ ላይ ተኝተዋል፤ በእግዚአብሔር ቁጣና በአምላክሽ ተግሣጽ ተሞልተዋል።”—ኢሳይያስ 51:19, 20
23 ኢየሩሳሌም እጅግ አሳዛኝ ዕጣ ይጠብቃታል! “መፈታትና ጥፋት” እንዲሁም “ራብና ሰይፍ” ይመጡባታል። ‘ልጆቿ’ ሊመሯትም ሆነ እንዳትወድቅ እጅዋን ይዘው ሊደግፏት አይችሉም። የባቢሎንን ወራሪዎች መመከት ተስኗቸው እጃቸውን አጣምረው ይመለከታሉ። ተዝለፍልፈው፣ ደክመውና ዝለው በአደባባይ በጎዳና ራስ ወይም ዳር ላይ ይተኛሉ። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 2:19፤ 4:1, 2) የአምላክን የቁጣ ጽዋ ጠጥተው በወጥመድ እንደተያዘ እንስሳ ተሳስረው ቁጭ ይላሉ።
24, 25. (ሀ) በኢየሩሳሌም ላይ ዳግመኛ የማይደርሰው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ኢየሩሳሌም የይሖዋን የቁጣ ጽዋ ከጠጣች በኋላ ጽዋው ለማን ይሰጣል?
24 ይሁን እንጂ ይህ አሳዛኝ ክስተት የሚያበቃበት ጊዜ ይመጣል። ኢሳይያስ በሚያጽናና መንገድ እንዲህ ሲል ተናገረ:- “ስለዚህም ያለ ወይን ጠጅ የሰከርሽ አንቺ ችግረኛ፣ ይህን ስሚ፤ ስለ ወገኑ የሚምዋገት አምላክሽ ጌታሽ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- እነሆ፣ የሚያንገደግድን ጽዋ የቁጣዬንም ዋንጫ ከእጅሽ ወስጃለሁ፤ ደግመሽም ከእንግዲህ ወዲህ አትጠጪውም። ነፍስሽንም:- እንሻገር ዘንድ ዝቅ በዪ በሚሉአት በአስጨናቂዎችሽ እጅ አኖረዋለሁ፤ ጀርባሽንም ለሚሻገሩት እንደ መሬትና እንደ መንገድ አደረግሽላቸው።” (ኢሳይያስ 51:21-23) ይሖዋ ኢየሩሳሌምን ከቀጣት በኋላ እንደገና በመራራት ይቅር ሊላት ዝግጁ ነው።
25 ከዚህ በኋላ ይሖዋ ቁጣውን ከኢየሩሳሌም ላይ አንስቶ በባቢሎን ላይ ያደርጋል። ባቢሎን ኢየሩሳሌምን ድምጥማጧን በማጥፋት አዋርዳታለች። (መዝሙር 137:7-9) ሆኖም ባቢሎንም ሆነች ግብረ አበሮቿ ኢየሩሳሌምን ዳግመኛ እንዲህ ያለ ጽዋ ሊያጠጧት አይችሉም። ከዚህ ይልቅ ጽዋው ከኢየሩሳሌም እጅ ላይ ተወስዶ በእሷ ላይ በደረሰው ውርደት ሐሴት ላደረጉ ይሰጣል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 4:21, 22) ባቢሎን አቅሏን እስክትስት ድረስ ጠጥታ ትወድቃለች። (ኤርምያስ 51:6-8) ጽዮን ግን ተነስታ ትቆማለች! እንዴት የሚያስገርም ለውጥ ነው! በእርግጥም ይህ ተስፋ ጽዮንን ሊያጽናናት ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋ በሚወስዳቸው የማዳን እርምጃዎች ስሙ እንደሚቀደስ ፍጹም እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 167 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሕዝቡ ‘ተቆርጠው የወጡበት’ “ዐለት” ታላቁ አብርሃም ይሖዋ ነው
[በገጽ 170 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክን ሕዝብ የሚቃወሙ ሰዎች በብል እንደተበላ ጨርቅ በንነው ይጠፋሉ
[በገጽ 176, 177 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ የተፈጥሮ ኃይሎችን የመቆጣጠር ችሎታ እንዳለው አሳይቷል
[በገጽ 178 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሩሳሌም የምትጠጣው ጽዋ ለባቢሎንና ለአጋሮቿ ይሰጣል