ተጨማሪ መረጃ
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍቺና ስለ መለያየት ምን ይላል?
ይሖዋ ባልና ሚስቶች ለጋብቻ ቃል ኪዳናቸው ታማኝ እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል። ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት በጋብቻ ባጣመረበት ወቅት “ሰው . . . ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ብሏል። ከጊዜ በኋላም ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ቃላት ደግሞ ከተናገረ በኋላ “ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” ብሏል። (ዘፍጥረት 2:24፤ ማቴዎስ 19:3-6) ስለሆነም ይሖዋና ኢየሱስ ጋብቻን የሚመለከቱት አንደኛው የትዳር ጓደኛ በሚሞትበት ጊዜ ብቻ የሚፈርስ የዕድሜ ልክ ቁርኝት እንደሆነ አድርገው ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:39) ጋብቻ ቅዱስ በመሆኑ ፍቺ እንደ ቀላል ነገር መታየት የለበትም። እንዲያውም ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ሳይኖር የሚፈጸምን ፍቺ ይጠላል።—ሚልክያስ 2:15, 16
በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ለፍቺ በቂ ምክንያት ነው የሚባለው ምንድን ነው? ይሖዋ ምንዝርንና ዝሙትን ይጠላል። (ዘፍጥረት 39:9፤ 2 ሳሙኤል 11:26, 27፤ መዝሙር 51:4) በእርግጥም ይሖዋ ዝሙትን አጥብቆ ስለሚጸየፍ ፍቺ ለመፈጸም በቂ ምክንያት እንደሚሆን ተናግሯል። (ዝሙት ምን ምን ነገሮችን እንደሚጨምር ለመረዳት ምዕራፍ 9 አንቀጽ 7ን ተመልከት።) ከትዳር ጓደኛው ጋር አብሮ ለመኖርም ሆነ ለመፋታት የመወሰን መብቱ የተሰጠው በደል ለተፈጸመበት ወገን ነው። (ማቴዎስ 19:9) በመሆኑም በደል የተፈጸመበት ወገን ለመፋታት ቢመርጥ ይሖዋ የሚጠላውን እርምጃ እንደወሰደ አይቆጠርበትም። ሆኖም የክርስቲያን ጉባኤ ማንም ሰው ፍቺ እንዲፈጽም አያበረታታም። እንዲያውም ዝሙት የፈጸመው ወገን ልባዊ ንስሐ ከገባ፣ በደል የተፈጸመበት ወገን ከበደለኛው ጋር አብሮ ለመኖር እንዲወስን የሚገፋፉት አንዳንድ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ያም ሆነ ይህ ለመፋታት የሚያስችል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያላቸው ሰዎች፣ ይሻላል የሚሉትን የራሳቸውን ውሳኔ ማድረግና ውሳኔያቸው የሚያመጣውን ማንኛውንም ውጤት መቀበል ይኖርባቸዋል።—ገላትያ 6:5
አንዳንድ ክርስቲያኖች ለየት ያሉ ሁኔታዎች በሚያጋጥሟቸው ጊዜ የትዳር ጓደኛቸው ዝሙት ባይፈጽምም እንኳ ለመለየት ወይም ፍቺ ለመፈጸም ወስነዋል። እንዲህ ባለው ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የተለየው ወገን ‘ሳያገባ እንዲኖር ካልሆነም እንዲታረቅ’ ያዛል። (1 ቆሮንቶስ 7:11) እንዲህ ያደረገ ክርስቲያን ከሌላ ሰው ጋር ጋብቻ ለመመሥረት ነፃ አይደለም። (ማቴዎስ 5:32) አንዳንዶች ከትዳር ጓደኛቸው ለመለየት ምክንያት ይሆናሉ ብለው የሚያስቧቸውን ለየት ያሉ ምክንያቶች እንመልከት።
መሠረታዊ ነገሮችን ለማቅረብ ፈቃደኛ አለመሆን። አንድ ባል አቅምና ችሎታ እያለው ቤተሰቡ ለኑሮ የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ነገሮች ለማቅረብ ፈቃደኛ ባይሆን ቤተሰቡ ለድህነት ሊዳረግ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ሰው . . . ለቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማያቀርብ ከሆነ እምነትን የካደ ከመሆኑም በላይ እምነት የለሽ ከሆነ ሰው የከፋ ነው” ይላል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) እንዲህ ያለው ባል አካሄዱን ለመለወጥ ፈቃደኛ ካልሆነ ሚስቱ በሕግ ለመለያየት በመጠየቅ የራሷንም ሆነ የልጆቿን ደህንነት ማስጠበቅ ይኖርባት እንደሆነ ለመወሰን ትገደዳለች። የጉባኤ ሽማግሌዎች አንድ ክርስቲያን ቤተሰቡን ለመደገፍ ፈቃደኛ እንዳልሆነ ክስ ሲደርሳቸው ጉዳዩን በጥንቃቄ መመልከት ይኖርባቸዋል። ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ለማቅረብ ፈቃደኛ የማይሆን ሰው እስከ መወገድ ሊደርስ ይችላል።
ከባድ አካላዊ ጥቃት። ጠበኛ የሆነ አንድ ባለትዳር የኃይል ጥቃት የሚፈጽም ከሆነ በትዳር ጓደኛው ጤንነት ሌላው ቀርቶ በሕይወት ላይ አደጋ ሊደርስ ይችላል። ይህ ግለሰብ ክርስቲያን ከሆነ የጉባኤ ሽማግሌዎች የቀረበበት ክስ እውነት መሆን አለመሆኑን ማጣራት ይኖርባቸዋል። በቁጣ መገንፈልና ጠበኝነት ከጉባኤ ሊያስወግዱ የሚችሉ ኃጢአቶች ናቸው።—ገላትያ 5:19-21
መንፈሳዊ ሕይወት ሙሉ በሙሉ አደጋ ላይ ሲሆን። አንድ ባለትዳር የትዳር ጓደኛው እውነተኛው አምልኮ የሚጠይቅበትን ተግባር እንዳይፈጽም ለማድረግ ወይም በሆነ መንገድ የአምላክን ሕግ እንዲጥስ ለማስገደድ ይሞክር ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥም መንፈሳዊ ሕይወቱ አደጋ ላይ የወደቀው ወገን ‘ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዥው አድርጎ ለመታዘዝ’ የሚችልበት ብቸኛው መንገድ በሕግ መለያየት እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን ይኖርበታል።—የሐዋርያት ሥራ 5:29
ከላይ እንደቀረቡት ያሉ የተለዩ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ሁሉ፣ የተበደለው ወገን እንዲለይም ሆነ አብሮ እንዲኖር ማንም ሰው ጫና ማሳደር አይኖርበትም። በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወዳጆችና ሽማግሌዎች ድጋፍም ሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር ሊሰጡ ቢችሉም በባልና ሚስቱ መካከል ያለውን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ሊያውቁ አይችሉም። ይህን የሚያውቀው ይሖዋ ብቻ ነው። አንዲት ክርስቲያን ሚስት ወይም አንድ ክርስቲያን ባል ከትዳር ጓደኛቸው ለመለየት ሲሉ ብቻ በቤት ውስጥ የሚደርስባቸውን በደል አጋንነው ቢናገሩ አምላክን ወይም ጋብቻን ማቃለል ይሆንባቸዋል። አንድ ሰው ምንም ያህል ለመሸሸግ ቢሞክር ከትዳር ጓደኛ ለመለየት ሲባል የሚሸረበው ተንኮልና ሴራ ከይሖዋ ዓይን የተሰወረ አይሆንም። በእርግጥም “ተጠያቂዎች በሆንበት በእሱ ዓይኖች ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና ገሃድ የወጣ ነው።” (ዕብራውያን 4:13) ይሁን እንጂ በጣም አደገኛ የሆነው ሁኔታ ለረዥም ጊዜ በመቀጠሉ ምክንያት የተበደለው ወገን የመጨረሻውን አማራጭ በመጠቀም ለመለየት ቢወስን ማንም ሰው ሊተቸው አይገባም። በመጨረሻ “ሁላችንም በአምላክ የፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለን።”—ሮም 14:10-12