ምዕራፍ አሥር
መንፈሳዊ ፍጡራን—ሊጠቅሙን ወይም ሊጎዱን የሚችሉት እንዴት ነው?
-
መላእክት ሰዎችን ይረዳሉ?
-
ክፉ መናፍስት በሰዎች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት ነው?
-
ክፉ መናፍስትን ልንፈራቸው ይገባል?
1. ስለ መላእክት ማወቅ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
ብዙውን ጊዜ ከአንድ ሰው ጋር መተዋወቅ ስለ ቤተሰቡም አንዳንድ ነገሮችን ማወቅን ይጨምራል። በተመሳሳይም ይሖዋ አምላክን ማወቅ በሰማይ ስላለው ቤተሰቡ ማለትም ስለ መላእክት ይበልጥ ማወቅን ያጠቃልላል። መጽሐፍ ቅዱስ መላእክትን ‘የእግዚአብሔር ልጆች’ ሲል ይጠራቸዋል። (ኢዮብ 38:7 የ1954 ትርጉም) ታዲያ መላእክት በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወቱት ሚና ምንድን ነው? በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ያበረከቱት ድርሻስ አለ? መላእክት በሕይወትህ ላይ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ? ከሆነስ እንዴት?
2. መላእክት የተገኙት ከየት ነው? ምን ያህል መላእክትስ አሉ?
2 መላእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ ተጠቅሰዋል። ስለ መላእክት ይበልጥ ማወቅ እንድንችል እስቲ ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት። መላእክት የተገኙት ከየት ነው? ቈላስይስ 1:16 ‘በሰማይና በምድር ያለው ነገር ሁሉ በእርሱ [በኢየሱስ ክርስቶስ] ተፈጥሯል’ ይላል። ስለዚህ መላእክት በመባል የሚታወቁትን መንፈሳዊ ፍጡራን በሙሉ በበኩር ልጁ አማካኝነት አንድ በአንድ የፈጠረው ይሖዋ አምላክ ነው። ምን ያህል መላእክት አሉ? መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ መላእክት እንደተፈጠሩ የሚጠቁም ሲሆን ሁሉም ኃያላን ናቸው።—መዝሙር 103:20 a
3. ኢዮብ 38:4-7 ስለ መላእክት ምን ይገልጽልናል?
3 የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ስትመሠረት ‘የእግዚአብሔር ልጆች እልል እንዳሉ’ ይገልጽልናል። (ኢዮብ 38:4-7 የ1954 ትርጉም) ስለዚህ መላእክት የተፈጠሩት ሰዎች ከመፈጠራቸው ከረጅም ጊዜ በፊት፣ ሌላው ቀርቶ ምድርም ከመፈጠሯ በፊት ነው። በተጨማሪም ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ መላእክት ‘ተደስተው [የ1980 ትርጉም] በአንድነት እንደዘመሩ’ ስለሚገልጽ ስሜት እንዳላቸውም ይጠቁመናል። ‘የእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ’ በአንድነት እንደተደሰቱ ልብ በል። በዚያ ጊዜ ሁሉም መላእክት ይሖዋ አምላክን የሚያገለግል፣ አንድነት ያለው ቤተሰብ አባላት ነበሩ።
መላእክታዊ እርዳታና ጥበቃ
4. መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ የሆኑ መላእክት የሰው ልጆችን እንቅስቃሴዎች እንደሚከታተሉ የሚያሳየው እንዴት ነው?
4 ታማኝ የሆኑት መንፈሳዊ ፍጥረታት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ሲፈጠሩ ካዩበት ጊዜ አንስቶ የሰብዓዊውን ቤተሰብ መበራከትና የአምላክን ዓላማ አፈጻጸም በትኩረት ሲከታተሉ ቆይተዋል። (ምሳሌ 8:30, 31፤ 1 ጴጥሮስ 1:11, 12) ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ መላእክት ከሰብዓዊው ቤተሰብ መካከል አብዛኞቹ አፍቃሪ የሆነውን ፈጣሪያቸውን ከማገልገል ወደኋላ እንዳሉ ተመልክተዋል። ታማኝ የሆኑት መላእክት በዚህ እንዳዘኑ ጥርጥር የለውም። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰውም እንኳ ቢሆን ወደ ይሖዋ በሚመለስበት ጊዜ “በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል።” (ሉቃስ 15:10) መላእክት አምላክን የሚያገለግሉ ሰዎች ደኅንነት በእጅጉ ስለሚያሳስባቸው ይሖዋ በምድር ያሉትን ታማኝ አገልጋዮቹን ለማበርታትና ለመጠበቅ በተደጋጋሚ ጊዜያት በመላእክት መጠቀሙ ምንም አያስደንቅም። (ዕብራውያን 1:7, 14) አንዳንድ ምሳሌዎች ተመልከት።
5. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መላእክት እርዳታ እንዳደረጉ የሚገልጹ የትኞቹን ታሪኮች እናገኛለን?
5 ሁለት መላእክት፣ ጻድቁ ሎጥና ሁለት ሴቶች ልጆቹ ብልሹ በነበሩት የሰዶምና የገሞራ ከተሞች ላይ ከደረሰው ጥፋት እንዲተርፉ እየመሩ ከአካባቢው አውጥተዋቸዋል። (ዘፍጥረት 19:15, 16) ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ ነቢዩ ዳንኤል በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ቢጣልም ምንም ጉዳት ሳይደርስበት ሊተርፍ ችሏል። “አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ” ሲል ተናግሯል። (ዳንኤል 6:22) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ አንድ መልአክ ሐዋርያው ጴጥሮስን ከእስር አስፈትቶታል። (የሐዋርያት ሥራ 12:6-11) ከዚህም ሌላ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ሲጀምር መላእክት አበረታተውት ነበር። (ማርቆስ 1:13) በተጨማሪም ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት አንድ መልአክ ተገልጦለት ‘አበረታቶታል።’ (ሉቃስ 22:43) በሕይወቱ ውስጥ በጣም ወሳኝ በነበሩት በእነዚህ ጊዜያት እንዲህ ያለ ማበረታቻ ማግኘቱ በእጅጉ አጽናንቶት መሆን አለበት!
6. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ መላእክት የአምላክን ሕዝቦች የሚጠብቁት እንዴት ነው? (ለ) ቀጥለን የምንመረምራቸው ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
6 በአሁኑ ጊዜ መላእክት እንደ ቀድሞው በምድር ላይ ላሉ የአምላክ አገልጋዮች በዓይን አይታዩም። ኃያላን የሆኑት የአምላክ መላእክት በሰብዓዊ ዓይን ባይታዩም እንኳ ዛሬም ሕዝቡን በተለይ መንፈሳዊ ጉዳት ከሚያስከትል ማንኛውም ነገር ይጠብቋቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል፤ ያድናቸዋልም” ይላል። (መዝሙር 34:7) እነዚህ ቃላት በእጅጉ ሊያጽናኑን የሚገባው ለምንድን ነው? እኛን ማጥፋት የሚፈልጉ አደገኛ የሆኑ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡራን ስላሉ ነው! እነዚህ መንፈሳዊ ፍጡራን እነማን ናቸው? የመጡትስ ከየት ነው? ሊጎዱን የሚሞክሩት እንዴት ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት በሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ ላይ የተፈጸመውን ነገር በአጭሩ እንመልከት።
ጠላቶቻችን የሆኑ መንፈሳዊ ፍጡራን
7. ሰይጣን ሰዎችን ከአምላክ በማራቅ ረገድ ምን ያህል ተሳክቶለታል?
7 በዚህ መጽሐፍ ሦስተኛ ምዕራፍ ላይ እንደተማርነው ከመላእክት አንዱ ሌሎችን የመግዛት ምኞት ስላደረበት በአምላክ ላይ ዓመጸ። ከጊዜ በኋላ ይህ መልአክ ሰይጣን ዲያብሎስ ተባለ። (ራእይ 12:9) ሰይጣን ሔዋንን ካታለላት በኋላ በነበሩት 1,600 የሚያክሉ ዓመታት እንደ አቤል፣ ሔኖክና ኖኅ ካሉት ጥቂት ታማኝ ሰዎች በስተቀር አብዛኞቹን ሰዎች ከአምላክ እንዲርቁ በማድረግ ረገድ ተሳክቶለታል።—ዕብራውያን 11:4, 5, 7
8. (ሀ) አንዳንድ መላእክት አጋንንት የሆኑት እንዴት ነው? (ለ) አጋንንት ከኖኅ የጥፋት ውኃ ለመትረፍ ሲሉ ምን ለማድረግ ተገደዱ?
8 በኖኅ ዘመን ሌሎች መላእክትም በይሖዋ ላይ ዓምጸዋል። በአምላክ ሰማያዊ ቤተሰብ ውስጥ የነበራቸውን ቦታ ትተው ወደ ምድር በመምጣት ሥጋዊ አካል ለበሱ። ለምን? ዘፍጥረት 6:2 “የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች የሰዎችን ሴቶች ልጆች ውብ ሆነው አዩአቸው፤ ከመካከላቸውም የመረጧቸውን አገቡ” ሲል ይገልጽልናል። ሆኖም ይሖዋ አምላክ፣ እነዚህ መላእክት የወሰዱት እርምጃና በዚህ ሳቢያ በሰው ዘር ላይ የተከሰተው የሥነ ምግባር ብልሹነት እንዳለ እንዲቀጥል አልፈቀደም። በምድር ላይ ዓለም አቀፍ የሆነ የጥፋት ውኃ አምጥቶ ታማኝ የሆኑ አገልጋዮቹን ብቻ በማዳን ክፉ ሰዎችን በሙሉ ጠራርጎ አጠፋ። (ዘፍጥረት 7:17, 23) በመሆኑም ዓመጸኞቹ መላእክት ወይም አጋንንት ሥጋዊ አካላቸውን በመተው መንፈሳዊ ፍጡራን ሆነው ወደ ሰማይ ለመመለስ ተገደዱ። እነዚህ አጋንንት ከዲያብሎስ ጎን የተሰለፉ በመሆናቸው ሰይጣን ‘የአጋንንት አለቃ’ ሊሆን ችሏል።—ማቴዎስ 9:34
9. (ሀ) አጋንንት ወደ ሰማይ ሲመለሱ ምን ሁኔታ ገጠማቸው? (ለ) አጋንንትን በተመለከተ ቀጥለን የምንመለከተው ነገር ምንድን ነው?
9 ዓመጸኞቹ መላእክት ወደ ሰማይ ሲመለሱ ገዥያቸው እንደሆነው እንደ ሰይጣን እነሱም የአምላክ ሰማያዊ ቤተሰብ አባላት የመሆን መብት ተነፈጉ። (2 ጴጥሮስ 2:4) በአሁኑ ጊዜ ሰብዓዊ አካል መልበስ የማይችሉ ቢሆንም እንኳ በሰዎች ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። እንዲያውም ሰይጣን በእነዚህ አጋንንት እየታገዘ ‘ዓለምን ሁሉ እያሳተ ነው።’ (ራእይ 12:9፤ 1 ዮሐንስ 5:19) እንዴት? አብዛኛውን ጊዜ አጋንንት ሰዎችን ለማሳት የረቀቁ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። (2 ቆሮንቶስ 2:11) ከእነዚህ ዘዴዎች መካከል አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት።
አጋንንት የሚያስቱት እንዴት ነው?
10. መናፍስታዊ ድርጊት ምንድን ነው?
10 አጋንንት ሰዎችን ለማሳት መናፍስታዊ ድርጊቶችን ይጠቀማሉ። መናፍስታዊ ድርጊት በቀጥታም ሆነ በሌላ ሰው አማካኝነት ከአጋንንት ጋር የሚደረግ ግንኙነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ መናፍስታዊ ድርጊቶችን የሚያወግዝ ከመሆኑም በላይ እንዲህ ካሉ ድርጊቶች ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖረን ያስጠነቅቀናል። (ገላትያ 5:19-21) ዓሣ አጥማጆች ዓሣን ለማጥመድ ማጥመጃው ላይ እንደ ምግብ ያለ ነገር እንደሚያስቀምጡ ሁሉ አጋንንትም መናፍስታዊ ድርጊቶችን ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ይጠቀሙባቸዋል። አንድ ዓሣ አጥማጅ የተለያዩ ዓይነት ዓሣዎችን ለማጥመድ የተለያዩ ማታለያዎችን ይጠቀማል። በተመሳሳይም ክፉ መናፍስት በሁሉም ዓይነት ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የተለያዩ ዓይነት መናፍስታዊ ድርጊቶችን ይጠቀማሉ።
11. ጥንቆላ ምንድን ነው? ልንርቀው የሚገባንስ ለምንድን ነው?
11 አጋንንት የሚጠቀሙበት አንዱ ማታለያ ጥንቆላ ነው። ጥንቆላ ምንድን ነው? ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ወይም ስለማይታወቅ ነገር ለማወቅ የሚደረግ ጥረት ነው። አንዳንዶች በኮከብ ቆጠራ፣ በአውደ ነገሥት፣ ጠጠር በመጣል፣ የእጅ አሻራ በማየት፣ በካርታ መጫወቻ ካርዶችና እነዚህን በመሳሰሉ መንገዶች ይጠነቁላሉ። ብዙ ሰዎች ጥንቆላ ምንም ጉዳት እንደሌለው አድርገው ቢያስቡም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ጠንቋዮች የሚጠነቁሉት በአጋንንት መንፈስ እንደሆነ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል የሐዋርያት [የ1980 ትርጉም] አንዲት ልጃገረድ ‘በጥንቈላ የሚያናግር ርኩስ መንፈስ አድሮባት’ እንደነበረ ይገልጻል። ሆኖም ጋኔኑ ከእርሷ ሲወጣ ይህን ችሎታዋን አጥታለች። ሥራ 16:16-18
12. ከሙታን ጋር ለመነጋገር መሞከር አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?
12 አጋንንት ሰዎችን የሚያስቱበት ሌላው መንገድ ሙታንን እንዲያማክሩ በመገፋፋት ነው። የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣታቸው ሐዘን ላይ የወደቁ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ስለ ሙታን በሚነገሩ የተሳሳቱ ሐሳቦች ይታለላሉ። አንድ ሙታን ሳቢ ልዩ መረጃ ሊሰጥ ወይም የሞተውን ሰው ድምፅ አስመስሎ ሊናገር ይችላል። በዚህ ምክንያት ብዙ ሰዎች ሙታን በሕይወት እንዳሉና እነሱን ማነጋገር ሐዘንን ለመቋቋም እንደሚረዳ አድርገው ያስባሉ። ይሁንና እንዲህ ያለው “ማጽናኛ” የተሳሳተ ከመሆኑም በላይ አደገኛ ነው። ለምን? አጋንንት የሞተውን ሰው ድምፅ አስመስለው መናገርና ሙታን ሳቢ ለሆነው ሰው ስለሞተው ግለሰብ መረጃ መስጠት ስለሚችሉ ነው። (1 ሳሙኤል 28:3-19) ከዚህም በተጨማሪ ምዕራፍ 6 ላይ እንደተመለከትነው ሙታን ከሕልውና ውጭ ናቸው። (መዝሙር 115:17) ስለዚህ ‘ሙታንን የሚያነጋግር’ ማንኛውም ሰው በክፉ መናፍስት ከመታለሉም በላይ የአምላክን ፈቃድ የሚጻረር ድርጊት እየፈጸመ ነው። (ዘዳግም 18:10, 11፤ ኢሳይያስ 8:19) ስለዚህ አጋንንት በሚጠቀሙበት በዚህ አደገኛ ማታለያ እንዳትጠመድ ተጠንቀቅ።
13. በአንድ ወቅት አጋንንትን ይፈሩ የነበሩ ብዙ ሰዎች ምን ማድረግ ችለዋል?
13 ክፉ መናፍስት ሰዎችን ከማሳት በተጨማሪ ያስፈራሯቸዋል። ሰይጣንና አጋንንቱ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳይችሉ የሚታሰሩበት ጊዜ “ጥቂት ዘመን ብቻ እንደ ቀረው” ስለሚያውቁ ከምንጊዜውም ይበልጥ ጨካኞች ሆነዋል። (ራእይ 12:12, 17) ያም ሆኖ እነዚህን ክፉ መናፍስት በመፍራት ከዛሬ ነገ ምን ያደርጉኝ ይሆን በሚል ጭንቀት ተውጠው ይኖሩ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከዚህ ፍርሃት መላቀቅ ችለዋል። ይህን ማድረግ የቻሉት እንዴት ነው? አንድ ሰው በመናፍስታዊ ድርጊቶች በመካፈል ላይ ያለ ቢሆንም እንኳ ምን እርምጃ መውሰድ ይችላል?
ክፉ መናፍስትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
14. በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኤፌሶን ይኖሩ እንደነበሩት ክርስቲያኖች ከክፉ መናፍስት መላቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?
14 መጽሐፍ ቅዱስ ክፉ መናፍስትን እንዴት መቋቋምም ሆነ ከእነሱ እንዴት መላቀቅ እንደሚቻል ይነግረናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኤፌሶን ከተማ ይኖሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች ምሳሌ ተመልከት። አንዳንዶቹ ክርስቲያኖች ከመሆናቸው በፊት መናፍስታዊ በሆኑ ድርጊቶች ይካፈሉ ነበር። ከመናፍስታዊ ድርጊት ለመላቀቅ በወሰኑ ጊዜ ምን አደረጉ? መጽሐፍ ቅዱስ “ሲጠነቁሉ ከነበሩትም መካከል ብዙዎች መጽሐፋቸውን ሰብስበው በማምጣት በሕዝብ ፊት አቃጠሉ” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 19:19) እነዚህ አዳዲስ ክርስቲያኖች ለአስማት ድርጊት ይጠቀሙባቸው የነበሩትን መጻሕፍት በማስወገድ በዛሬው ጊዜ ክፉ መናፍስትን መቃወም ለሚፈልጉ ሁሉ ግሩም ምሳሌ ትተዋል። ይሖዋን ለማገልገል የሚፈልጉ ሰዎች ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ ያለውን ነገር ሁሉ ማስወገድ ያስፈልጋቸዋል። ይህም መናፍስታዊ ድርጊቶችን የሚያበረታቱ፣ አስደሳችና ማራኪ አድርገው የሚያቀርቡ መጻሕፍትን፣ መጽሔቶችን፣ ፊልሞችን፣ ፖስተሮችንና ዘፈኖችን ያጠቃልላል። በተጨማሪም ከክፉ ነገር ይጠብቃሉ በሚል የሚደረጉ እንደ ክታብ ያሉ ነገሮችን ማስወገድ ያስፈልጋል።—1 ቆሮንቶስ 10:21
15. ክፉ መንፈሳዊ ኃይሎችን ለመቋቋም ምን ማድረግ ያስፈልገናል?
15 የኤፌሶን ክርስቲያኖች ለአስማት ድርጊት ይጠቀሙባቸው የነበሩትን መጻሕፍት ካቃጠሉ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ “ተጋድሎአችን . . . ከርኩሳን መናፍስት ሰራዊት ጋር ነው” ሲል ጽፎላቸዋል። (ኤፌሶን 6:12) ጳውሎስ በዚያም ወቅት ተጋድሎ እንዳለባቸው መግለጹ አጋንንት ተስፋ አለመቁረጣቸውን ያሳያል። በእነሱ ላይ ለመሠልጠን ጥረት ማድረጋቸውን አልተዉም ነበር። ስለዚህ በኤፌሶን የነበሩት ክርስቲያኖች ቀደም ሲል ከወሰዱት እርምጃ ሌላ ምን ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር? ጳውሎስ “ከእነዚህም ሁሉ ጋር፣ የሚንበለበሉትን የክፉውን [የሰይጣንን] ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ” ብሏል። (ኤፌሶን 6:16) የእምነት ጋሻችን ጠንካራ በሆነ መጠን ክፉ መንፈሳዊ ኃይሎችን ለመቋቋም ያለን አቅም የዚያኑ ያህል ይጨምራል።—ማቴዎስ 17:20
16. እምነታችንን ማጠንከር የምንችለው እንዴት ነው?
16 ታዲያ እምነታችንን ማጠንከር የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ነው። አንድ ግንብ ጸንቶ መቆም የሚችለው መሠረቱ ጠንካራ ከሆነ ነው። በተመሳሳይ የእምነታችን ጽናትም በመሠረቱ ጥንካሬ ላይ በእጅጉ የተመካ ነው። የእምነታችን መሠረት ደግሞ የአምላክ ቃል የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የምናነብና የምናጠና ከሆነ እምነታችን ይጠነክራል። እንዲህ ያለው እምነት ልክ እንደ አንድ ጠንካራ ግንብ ከክፉ መናፍስት ተጽዕኖ ሊጠብቀን ይችላል።—1 ዮሐንስ 5:5
17. ክፉ መናፍስትን ለመቋቋም ምን እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው?
17 በኤፌሶን የነበሩት ክርስቲያኖች ምን ሌላ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋቸው ነበር? የሚኖሩበት ከተማ በአጋንንታዊ ድርጊቶች የተሞላ በመሆኑ ተጨማሪ ጥበቃ ያስፈልጋቸው ነበር። ስለሆነም ጳውሎስ “በሁሉ ዐይነት ጸሎትና ልመና፣ በማንኛውም ሁኔታ በመንፈስ ጸልዩ” ብሏቸዋል። (ኤፌሶን 6:18) እኛም የምንኖረው በአጋንንታዊ ድርጊቶች በተሞላ ዓለም ውስጥ በመሆኑ ክፉ መናፍስትን መቋቋም እንድንችል ይሖዋ ጥበቃ እንዲያደርግልን አጥብቀን መጸለያችን በጣም አስፈላጊ ነው። በምንጸልይበት ጊዜ ደግሞ የይሖዋን ስም መጥራት ያስፈልገናል። (ምሳሌ 18:10) ስለዚህ “ከክፉው” ማለትም ከሰይጣን ዲያብሎስ ‘እንዲያድነን’ ወደ አምላክ መጸለያችንን መቀጠል አለብን። (ማቴዎስ 6:13) ይሖዋ እንዲህ ያሉትን ከልብ የመነጩ ጸሎቶች ይሰማል።—መዝሙር 145:19
18, 19. (ሀ) ከክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታት ጋር በምናደርገው ውጊያ ድል እንደምንቀዳጅ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ለየትኛው ጥያቄ መልስ እናገኛለን?
18 ክፉ መናፍስት አደገኞች ናቸው፤ ሆኖም ዲያብሎስን የምንቃወምና የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ወደ ይሖዋ የምንቀርብ ከሆነ ልንፈራቸው አይገባም። (ያዕቆብ 4:7, 8) ክፉ መናፍስት ያላቸው ኃይል ውስን ነው። በኖኅ ዘመን ቅጣት የደረሰባቸው ሲሆን ወደፊት ደግሞ የመጨረሻ ፍርዳቸውን ይቀበላሉ። (ይሁዳ 6) ከዚህም ሌላ ኃያላን የሆኑት የይሖዋ መላእክት ጥበቃ እንደሚያደርጉልን አስታውስ። (2 ነገሥት 6:15-17) እነዚህ መላእክት ክፉ መናፍስትን መቋቋም መቻላችን ያስደስታቸዋል። ጻድቃን የሆኑት መላእክት እያበረታቱን ነው ሊባል ይችላል። እንግዲያው ይሖዋንና ታማኝ የሆኑትን መንፈሳዊ ፍጥረታት ያቀፈውን ቤተሰቡን የሙጥኝ ብለን እንኑር። በተጨማሪም ማንኛውንም ዓይነት መናፍስታዊ ድርጊት በማስወገድ ምንጊዜም የአምላክ ቃል የሚሰጠንን ምክር ተግባራዊ እናድርግ። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7፤ 2 ጴጥሮስ 2:9) እንዲህ ካደረግን ከክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታት ጋር በምናደርገው ውጊያ ድል እንደምንቀዳጅ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
19 ይሁንና አምላክ በክፉ መናፍስት ላይም ሆነ ሰዎችን ለከፍተኛ መከራና ሥቃይ በዳረገው የክፋት ድርጊት ላይ እርምጃ ያልወሰደው ለምንድን ነው? የሚቀጥለው ምዕራፍ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል።