ምዕራፍ 5
በችግር የተሞላ ኑሮ ተጀመረ
ከኤደን የአትክልት ቦታ ውጪ አዳምና ሔዋን ብዙ ችግሮች አጋጠሟቸው። የሚበሉት ምግብ ለማግኘት ላባቸው ጠብ እስኪል ድረስ መሥራት ነበረባቸው። በአካባቢያቸው ጥሩ ፍሬ በሚያፈሩ ውብ ዛፎች ፋንታ ብዙ እሾህና አሜኬላ በቅሎ ነበር። አዳምና ሔዋን ይህ ነገር የደረሰባቸው አምላክን ባለመታዘዛቸውና ከእርሱ ጋር የነበራቸው ወዳጅነት በመቋረጡ ነበር።
ይሁን እንጂ ከዚያም የከፋ ነገር ደረሰባቸው፤ አዳምና ሔዋን ወደ ሞት ማዝገም ጀመሩ። ከዚያ ዛፍ ፍሬ ከበሉ እንደሚሞቱ አምላክ አስጠንቅቋቸው እንደነበር አስታውስ። የዚያን ዛፍ ፍሬ ከበሉበት ቀን ጀምሮ ወደ ሞት ማዝገም ጀመሩ። አምላክ ያላቸውን አለመስማታቸው እንዴት ያለ ትልቅ ሞኝነት ነበር!
የአዳምና የሔዋን ልጆች በሙሉ የተወለዱት አምላክ ወላጆቻቸውን ከኤደን የአትክልት ስፍራ ካስወጣቸው በኋላ ነበር። ስለዚህ ልጆቹም ቢሆኑ አርጅተው ይሞታሉ ማለት ነው።
አዳምና ሔዋን ይሖዋን ታዝዘው ቢሆን ኖሮ እነርሱም ሆኑ ልጆቻቸው ደስ ብሏቸው ይኖሩ ነበር። ሁሉም በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ መኖር ይችሉ ነበር። ማንም ሰው አያረጅም፣ አይታመምም፣ እንዲሁም አይሞትም ነበር።
አምላክ ሰዎች ለዘላለም በደስታ እንዲኖሩ ይፈልጋል። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚኖሩበት ጊዜም እንደሚመጣ ቃል ገብቷል። በዚያ ጊዜ መላዋ ምድር ውብ ከመሆኗም በላይ ሰዎች በሙሉ ጤናማ ይሆናሉ። እያንዳንዱ ሰው ከሁሉም ሰዎችና ከአምላክ ጋር ጥሩ ወዳጅነት ይኖረዋል።
ይሁን እንጂ ሔዋን ከአምላክ ጋር የነበራት ወዳጅነት ተቋርጧል። ስለዚህ ልጆችዋን ስትወልድ ምጡ ቀላል አልነበረም። በጣም ትሠቃይ ነበር። ይሖዋን አለመታዘዟ በእርግጥም ብዙ ሐዘን አምጥቶባታል። በዚህ አትስማማምን?
አዳምና ሔዋን ብዙ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ነበሯቸው። የመጀመሪያ ልጃቸው ሲወለድ ቃየን ብለው ስም አወጡለት። ሁለተኛ ልጃቸውን አቤል ብለው ጠሩት። እነዚህ ልጆች ምን ሁኔታ እንዳጋጠማቸው ታውቃለህ?