ምዕራፍ 58
ዳዊትና ጎልያድ
ፍልስጤማውያን እንደገና እስራኤላውያንን ለመውጋት መጡ። በዚህ ወቅት የዳዊት ሦስት ታላላቅ ወንድሞች በሳኦል ሠራዊት ውስጥ ነበሩ። ስለዚህ ከዕለታት አንድ ቀን እሴይ ዳዊትን ‘ጥቂት እሸትና ዳቦ ለወንድሞችህ ይዘህላቸው ሂድ። ደህንነታቸውንም አጣርተህ ንገረኝ’ አለው።
ዳዊት ሠራዊቱ ወደ ተከማቸበት ሰፈር ሲደርስ ወንድሞቹን ለመፈለግ ወደ ውጊያው ግንባር ሮጠ። ግዙፉ ፍልስጤማዊ ጎልያድ በእስራኤላውያን ላይ ለማሾፍ መጣ። ለ40 ቀናት በየዕለቱ ጠዋትና ማታ እንዲህ ሲያደርግ ቆይቷል። ‘ከእኔ ጋር የሚገጥም አንድ ሰው ከመካከላችሁ ምረጡ። እሱ ካሸነፈኝና ከገደለኝ እኛ ባሪያዎች እንሆንላችኋለን። እኔ ካሸነፍኩትና ከገደልሁት ግን እናንተ የእኛ ባሪያዎች ትሆናላችሁ። ከእኔ ጋር የሚገጥም ሰው ምረጡና አምጡ’ እያለ ይጮኽ ነበር።
ዳዊት ‘ይህን ፍልስጤማዊ ለገደለና እስራኤላውያንን ከዚህ ውርደት ላዳነ ምን ይደረግለታል?’ ሲል ከወታደሮቹ መካከል አንዳንዶቹን ጠየቃቸው።
‘ሳኦል ይህን ለሚያደርግ ሰው ብዙ ሀብት ይሰጠዋል፤ የራሱንም ልጅ ሚስት አድርጎ ይድርለታል’ ብለው መለሱለት።
ይሁን እንጂ ጎልያድ በጣም ትልቅ ስለነበረ እስራኤላውያን ሁሉ ይፈሩት ነበር። ቁመቱ ከ9 ጫማ በላይ (3 ሜትር ገደማ) ነበር፤ የእሱን ጋሻ ይዞ የሚጠብቀው ሌላ ወታደርም ነበረው።
ዳዊት ጎልያድን ሊገጥመው እንደሚፈልግ ወታደሮቹ ለንጉሥ ሳኦል ነገሩት። ይሁን እንጂ ሳኦል ዳዊትን ‘ይህን ፍልስጤማዊ መግጠም አትችልም። አንተ ገና ልጅ ነህ፤ እሱ ዕድሜውን ሙሉ ወታደር ነው’ አለው። ‘የአባቴን በጎች የወሰዱትን አንድ ድብና አንድ አንበሳ ገድያለሁ። ይህንንም ፍልስጤማዊ እንደነርሱ እገድለዋለሁ። ይሖዋ ይረዳኛል’ ሲል ዳዊት መለሰለት። በዚህ ጊዜ ሳኦል ‘ሂድ፤ ይሖዋ ከአንተ ጋር ይሁን’ አለው።
ዳዊት ወደ ወንዝ ሄደና አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች ለቀመና በኮሮጆው ውስጥ ጨመራቸው። ከዚያም ወንጭፉን ያዘና ግዙፉን ሰው ለመግጠም ሄደ። ጎልያድ ዳዊትን ሲያየው በጣም ተገረመ። ዳዊትን መግደል በጣም ቀላል ነገር እንደሆነ አድርጎ አስቦ ነበር።
ጎልያድ ዳዊትን ‘ወደ እኔ ና፤ ሥጋህን የወፎችና የእንስሳት እራት አደርገዋለሁ’ አለው። ይሁን እንጂ ዳዊት እንዲህ አለው:- ‘አንተ ሰይፍና ጦር ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን በይሖዋ ስም እመጣብሃለሁ። ዛሬ ይሖዋ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጥሃል፤ እገድልህማለሁ።’
ከዚያም ዳዊት ወደ ጎልያድ ሮጠ። ከኮሮጆው ውስጥ አንድ ድንጋይ አወጣና ወንጭፉ ላይ አድርጎ ባለ ኃይሉ ተጠቅሞ ወረወረው። ድንጋዩ ተወርውሮ ሄደና ጎልያድን ግንባሩን አለው፤ ጎልያድም ወደቀና ሞተ! ፍልስጤማውያን ይዋጋላቸው የነበረው ኃይለኛ ሰው እንደሞተ ሲያዩ ሁሉም ወደ ኋላ ሸሹ። እስራኤላውያን ፍልስጤማውያንን አሳደዱአቸውና በውጊያው አሸነፉ።