ምዕራፍ 96
ኢየሱስ የታመሙ ሰዎችን ፈወሰ
ኢየሱስ በሄደበት ሁሉ የታመሙ ሰዎችን ይፈውስ ነበር። በየመንደሩና በየከተሞቹ የሚኖሩ ሁሉ ኢየሱስ ስለፈጸማቸው ተአምራት ሰሙ። ስለዚህ ሰዎች አካለ ስንኩሎችን፣ ዓይነ ስውሮችን፣ መስማት የተሳናቸውንና ሌሎች የታመሙ ብዙ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ አመጡአቸው። ኢየሱስ ሁሉንም ፈወሳቸው።
ዮሐንስ ኢየሱስን ካጠመቀው ከሦስት ዓመት በላይ አልፎ ነበር። ኢየሱስ ሐዋርያቱን ብዙም ሳይቆይ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድና በዚያም እንደሚገደል፣ ከዚያም ከሞት እንደሚነሳ ነገራቸው። እስከዚያው ድረስ ግን ኢየሱስ የታመሙ ሰዎችን መፈወሱን ቀጥሎ ነበር።
ከዕለታት አንድ ቀን ኢየሱስ በሰንበት እያስተማረ ነበር። ሰንበት አይሁዳውያን የሚያርፉበት ቀን ነው። ሥዕሉ ላይ የምታያት ሴት በጣም ታማ ነበር። ለ18 ዓመታት ያህል ጎብጣ ነበር፤ ቀጥ ብላ መቆም አትችልም ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ እጁን ጫነባትና ቀጥ ብላ ቆመች። ተፈወሰች!
ይህ የሃይማኖት መሪዎቹን አስቆጣቸው። ከእነርሱ መካከል አንዱ ሕዝቡን ‘ሥራ የምንሠራባቸው ስድስት ቀኖች አሉ። ከበሽታችሁ ለመዳን መጥታችሁ መፈወስ የምትችሉት በእነዚህ ቀኖች እንጂ በሰንበት አይደለም!’ አላቸው።
ኢየሱስ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው:- ‘እናንተ ክፉዎች፣ ማናችሁም ብትሆኑ በሰንበት ቀን አህያችሁን ከታሰረበት ፈትታችሁ ውኃ ለማጠጣት ትወስዱታላችሁ። ታዲያ ለ18 ዓመታት ታማ የኖረችው ይቺ ምስኪን ሴት በሰንበት መፈወስ አይገባትም?’ የኢየሱስ መልስ እነዚህን ክፉ ሰዎች አሳፈራቸው።
በኋላ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ወደ ኢየሩሳሌም መጓዝ ጀመሩ። ልክ ከኢያሪኮ እንደወጡ ሁለት ዓይነ ስውር ለማኞች ኢየሱስ በዚያ በኩል እያለፈ እንዳለ ሰሙ። ስለዚህ ‘ኢየሱስ ሆይ፣ እርዳን!’ እያሉ ጮኹ።
ኢየሱስ ዓይነ ስውሮቹን ጠርቶ ‘ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?’ አላቸው። ‘ጌታ ሆይ፣ ዓይኖቻችን እንዲከፈቱ አድርግልን’ አሉት። ኢየሱስ ዓይኖቻቸውን ዳሰሳቸው፤ ወዲያውኑ ማየት ቻሉ! ኢየሱስ እነዚህን ሁሉ አስደናቂ ተአምራት ይፈጽም የነበረው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? ሰዎችን ይወድ ስለነበረና በእርሱ እንዲያምኑ ይፈልግ ስለነበረ ነው። እንግዲያው እኛም ንጉሥ ሆኖ በሚገዛበት ጊዜ በምድር ላይ የሚኖር ማንም ሰው ዳግመኛ እንደማይታመም እርግጠኞች መሆን እንችላለን።