ክፍል 21
ኢየሱስ ከሞት ተነሳ!
ኢየሱስ ለተከታዮቹ በመገለጥ መመሪያና ማበረታቻ ሰጣቸው
ኢየሱስ በሞተ በሦስተኛው ቀን፣ ደቀ መዛሙርቱ የሆኑ አንዳንድ ሴቶች ወደ መቃብሩ ቦታ ሲሄዱ በመቃብሩ ደጃፍ ላይ የነበረው ድንጋይ ተንከባሎ አገኙት። መቃብሩም ባዶ ነበር!
በዚህ ጊዜ ሁለት መላእክት ተገለጡላቸው። ከዚያም አንደኛው “የምትፈልጉት . . . የናዝሬቱን ኢየሱስን ነው። እሱ ተነስቷል” አላቸው። (ማርቆስ 16:6) ሴቶቹም ጊዜ ሳያጠፉ ወሬውን ለሐዋርያቱ ለመንገር እየሮጡ ሄዱ። በመንገድ ላይ ሳሉ ኢየሱስን አገኙት። እሱም እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ! ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው፤ እዚያም ያዩኛል።”—ማቴዎስ 28:10
በዚያው ቀን ሁለት ደቀ መዛሙርት ከኢየሩሳሌም ተነስተው ኤማሁስ ወደምትባል መንደር እየተጓዙ ነበር። በጉዟቸው ላይ ሳሉ አንድ የማያውቁት ሰው አብሯቸው መሄድ ጀመረ፤ ግለሰቡም ስለ ምን እንደሚያወሩ ጠየቃቸው። የሚያነጋግራቸው ሰው ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ነበር፤ ሆኖም የተገለጠላቸው ቀደም ሲል በሚያውቁት መልክ አይደለም። በሐዘን የተዋጡት ደቀ መዛሙርት የሚነጋገሩት ስለ ኢየሱስ እንደሆነ ገለጹለት። በዚህ ጊዜ እንግዳው ሰው ስለ መሲሑ በቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ያብራራላቸው ጀመር። በእርግጥም መሲሑን በተመለከተ የተነገሩት ትንቢቶች አንድም ሳይቀር በኢየሱስ ላይ ተፈጽመዋል። * ደቀ መዛሙርቱ ሲያነጋግራቸው የነበረው እንግዳ ሰው መንፈሳዊ አካል ለብሶ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ መሆኑን ሲገነዘቡ ኢየሱስ ከአጠገባቸው ተሰወረ።
ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ወዲያውኑ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። በዚያም ሐዋርያቱ የነበሩበትን ቤት ቆላልፈው አንድ ላይ ተቀምጠው ነበር። ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ያጋጠማቸውን ሁኔታ ለሐዋርያቱ እየነገሯቸው ሳለ ኢየሱስ በመካከላቸው ቆመ። በአድናቆት የተዋጡት ተከታዮቹ ዓይናቸውን ማመን አቃታቸው! በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ‘ለምን በልባችሁ ውስጥ ጥርጣሬ ያድራል?’ ብሎ ጠየቃቸው። ከዚያም “እንደሚከተለው ተብሎ ተጽፏል፤ ክርስቶስ መከራ ይቀበላል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሳል” አላቸው።—ሉቃስ 24:38, 46
ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለ40 ቀናት ያህል በተለያዩ አጋጣሚዎች ለደቀ መዛሙርቱ ተገለጠላቸው። በአንድ ወቅት ከ500 ለሚበልጡ ደቀ መዛሙርት ተገልጦላቸዋል! የሚከተለውን ከባድ ኃላፊነት የሰጣቸው በዚህ ወቅት ሳይሆን አይቀርም፦ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው። እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”—ማቴዎስ 28:19, 20
ኢየሱስ ከ11 ታማኝ ሐዋርያቱ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ በተገናኘበት ወቅት እንደሚከተለው በማለት ቃል ገብቷል፦ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ . . . እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።” (የሐዋርያት ሥራ 1:8) ከዚያም ኢየሱስ ወደ ላይ ወጣ፤ ወደ ሰማይም ሲያርግ ደመና ከዓይናቸው ሰወረው።
—በማቴዎስ ምዕራፍ 28፤ በማርቆስ ምዕራፍ 16፤ በሉቃስ ምዕራፍ 24፤ በዮሐንስ ምዕራፍ 20 እና ምዕራፍ 21 እንዲሁም በ1 ቆሮንቶስ 15:5, 6 ላይ የተመሠረተ።
^ አን.6 በኢየሱስ ላይ የተፈጸሙ መሲሐዊ ትንቢቶችን ለማግኘት በዚህ ብሮሹር ላይ ክፍል14፣ ክፍል 15 እና ክፍል 16 እንዲሁም ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ተጨማሪ ክፍል ላይ “ኢየሱስ ክርስቶስ—አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ” የሚለውን ክፍል ተመልከት።