ጥያቄ 3
መመሪያዎቹ ከየት መጡ?
ይህን የመሰለ መልክና ቁመና ሊኖርህ የቻለው እንዴት ነው? የዓይንህን፣ የፀጉርህንና የቆዳህን ቀለም የሚወስነው ምንድን ነው? ቁመትህንና ተክለ ሰውነትህንስ? አባትህን ወይም እናትህን አሊያም ሁለቱንም ልትመስል የቻልከው እንዴት ነው? የጣቶችህ ጫፍ በአንድ ወገን ለስለስ ያለ ሥጋ በሌላው ወገን ደግሞ ጠንከር ያለ ነገር ይኸውም ከጉዳት የሚከላከል ጥፍር እንዲኖረው የሚያደርገው ምንድን ነው?
በቻርልስ ዳርዊን ዘመን እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች መልስ አልተገኘላቸውም ነበር። ዳርዊን ራሱ አንዳንድ ባሕርያት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉበት መንገድ ያስገርመው ነበር። ይሁን እንጂ በሴል ውስጥ የዘር ውርስን ስለሚቆጣጠረው ሂደት ቀርቶ ስለ ሥነ ባሕርይ (genetics) ሕጎች እንኳ እምብዛም የሚያውቀው ነገር አልነበረም። በዚህ ዘመን ግን የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች ስለ ሰው ሥነ ባሕርይና አስደናቂ በሆነው ዲ ኤን ኤ (ዲኦክሲራይቦኑክሊክ አሲድ) የሚባል ሞለኪውል ውስጥ ተመዝግቦ ስለሚገኘው ዝርዝር መመሪያ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ጥናት ሲያደርጉ ቆይተዋል። አሁን የሚነሳው ትልቁ ጥያቄ ‘እነዚህ መመሪያዎች ከየት መጡ?’ የሚለው ነው።
ብዙ ሳይንቲስቶች ምን ይላሉ? በርካታ የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎችም ሆኑ ሌሎች ሳይንቲስቶች ዲ ኤን ኤ እና በኮድ የሚያስተላልፋቸው መመሪያዎች የተገኙት በሚሊዮን በሚቆጠሩ ዘመናት ሂደት በዘፈቀደ በተከሰቱ ድንገተኛ አጋጣሚዎች እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይህ ሞለኪውል የተዋቀረበት መንገድ፣ የያዘውም ሆነ የሚያስተላልፈው መረጃ ብሎም ሥራውን የሚያከናውንበት መንገድ ንድፍ እንዳለው የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም ይላሉ።17
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? መጽሐፍ ቅዱስ፣ የእያንዳንዱ የሰውነታችን ክፍል አፈጣጠር ሌላው ቀርቶ የሚፈጠርበት ጊዜ ከአምላክ በተገኘ ምሳሌያዊ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበ እንደሆነ ይጠቁማል። ንጉሥ ዳዊት በመንፈስ ተመርቶ ስለ አምላክ ሲናገር ምን እንዳለ ልብ በል፦ “ፅንስ በነበርኩበት ጊዜ ዓይኖችህ አዩኝ፣ የአካል ክፍሎቼ ከመሠራታቸው በፊት፣ የተሠሩባቸውን ቀኖች በተመለከተ አንድ በአንድ በመጽሐፍህ ተጻፈ።”—መዝሙር 139:16 NW
ማስረጃው ምን ያመለክታል? የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ በእርግጥ እውነት ከሆነ ዲ ኤን ኤ ድንገተኛ በሆኑ ተከታታይ ክስተቶች አማካኝነት ሊገኝ ይችላል የሚለው መላምት ቢያንስ ቢያንስ የሚመስል ነገር ሆኖ መገኘት አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከሆነ ደግሞ ዲ ኤን ኤ ራሱ የማሰብ ችሎታ ባለው አካል በሥርዓት የተዋቀረ መሆኑን የሚጠቁም አሳማኝ ማስረጃ ሊኖረው ይገባል።
ስለ ዲ ኤን ኤ የሚቀርበውን ማብራሪያ ቀለል ባለ መንገድ ስንመረምረው ለመረዳት የማያዳግትና ቀልብ የሚስብ እንደሆነ እንገነዘባለን። ስለዚህ አሁንም በድጋሚ የሴልን ውስጠኛ ክፍል እንጎብኝ። በዚህ ጊዜ ግን የምንጎበኘው የሰውን ሴል ነው። የሰው ሴል ተግባሩን እንዴት እንደሚያከናውን ለማስተማር የተሠራ ሙዚየም
እንደምትጎበኝ አድርገህ አስብ። መላው ሙዚየም የሰውን ሴል እንዲመስል ተደርጎ የተሠራ ነው፤ ሆኖም የሴሉ መጠን 13,000,000 እጥፍ ያህል እንዲያድግ ተደርጓል። መጠኑ 70,000 ገደማ ሕዝብ ሊይዝ የሚችል ትልቅ ስታዲየም ያክላል።ወደ ሙዚየሙ ስትገባ ለየት ያለ ቅርጽ ያላቸው ነገሮች በሞሉበት በዚህ አስደናቂ ሕንፃ በጣም ትደመማለህ። በሴሉ ማዕከላዊ ክፍል አካባቢ 20 ፎቅ የሚያክል ከፍታ ያለው ኒውክሊየስ የሚባል ክብ ነገር ይገኛል። በዚህ ጊዜ ወደ ኒውክሊየሱ ታመራለህ።
በኒውክሊየሱ ውጫዊ ሽፋን በሚገኝ በር በኩል ገብተህ በዙሪያህ ያለውን ነገር መመልከት ትጀምራለህ። በዚህ ክፍል አብዛኛውን ቦታ የያዙት 46 ክሮሞዞሞች ናቸው። ተመሳሳይ የሆኑ ክሮሞዞሞች ጥንድ ጥንድ እየሆኑ የተደረደሩ ሲሆን የአንዱ ጥንድ ቁመት ከሌላው ይለያል፤ አጠገብህ ያለው ጥንድ ክሮሞዞም ግን 12 ፎቅ የሚያክል ቁመት አለው (1)። እያንዳንዱ ክሮሞዞም መሃሉ አካባቢ ሰርጎድ ያለ በመሆኑ ሁለት የተቀጣጠሉ ቋሊማዎች ይመስላል፤ ውፍረቱ ግን የትልቅ ዛፍ ግንድ ያክላል። በክሮሞዞም ናሙናዎቹ ላይ የተጠመጠመ ገመድ ትመለከታለህ። ቀረብ ብለህ ስትመለከት ገመዱ ከላይ ወደ ታች በተዘረጉ መስመሮች የተከፋፈለ እንደሆነ ትገነዘባለህ። በእነዚህ መካከል ደግሞ አጫጭር የሆኑ አግዳሚ መስመሮች አሉ (2)። እነዚህ ነገሮች የተከመሩ መጻሕፍት ይሆኑ እንዴ? አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ የተነባበሩና በጣም ጥብቅ ብለው የተጠመጠሙ ነገሮች ናቸው፤ አንተ እያየህ ያለኸው የውጨኛውን ጠርዝ ነው። አንዱን ጫፍ ብትስበው ይተረተራል። ይህ የተጠመጠመ ነገር ሥርዓት ባለው መንገድ ከተቀመጡ ትናንሽ ጥቅልሎች (3) የተሠራ መሆኑን ስትመለከት በጣም ትደነቃለህ። በእነዚህ ጥቅልሎች ውስጥ ደግሞ የዚህ ሁሉ ዋነኛ ክፍል የሆነ በጣም ረጅም ገመድ የሚመስል ነገር ታገኛለህ። ይህ ደግሞ ምን ይሆን?
በጣም አስደናቂ የሆነ ሞለኪውል አወቃቀር
በናሙና ክሮሞዞሙ ውስጥ የሚገኘውን ይህን ክፍል ገመድ ብለን እንጥራው። የገመዱ ውፍረት 2.6 ሴንቲ ሜትር ያክላል። ገመዱ፣ በጥቅልሎቹ ውስጥ ሌሎች ጥቅልሎችን ለመሸብለል በሚያገለግሉ ክብ ቅርጽ (4) ባላቸው ነገሮች ላይ ጠበቅ ተደርጎ ተጠምጥሟል። እነዚህ ጥቅልሎች ቦታቸውን እንዳይለቁ ደግፎ የሚይዛቸው ነገር አለ። መግለጫ በሚሰጠው ስክሪን ላይ ያለው ጽሑፍ ገመዱ ብዙ ቦታ በማይዝ መንገድ በጥሩ ሁኔታ እንደተጠቀለለ ይገልጻል። በእያንዳንዱ የናሙና ክሮሞዞም ውስጥ ያለውን ገመድ መዝዘህ በማውጣት ቀጣጥለህ ብትዘረጋው ከጫፍ እስከ ጫፍ ያለው ርዝመት የምድርን ወገብ ግማሽ ያህላል! a
አንድ የሳይንስ መጽሐፍ ገመዱ የተጠቀለለበትን መንገድ “ዕጹብ ድንቅ የምሕንድስና ጥበብ” በማለት ገልጾታል።18 እንዲህ ካለው ድንቅ ጥበብ በስተጀርባ ምንም መሐንዲስ የለም ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ይመስልሃል? ይህ ሙዚየም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ለሽያጭ የተዘጋጁ ዕቃዎች ያሉበት ትልቅ መደብር ቢኖረውና ዕቃዎቹ ደግሞ በቀላሉ ሊገኙ በሚችሉበት መንገድ የተደረደሩ ቢሆኑ መደብሩን ያደራጀ ሰው አይኖርም ብለህ ታስባለህ? እንዲህ ብለህ እንደማታስብ የታወቀ ነው! ያም ሆኖ ይህ መደብር የተደራጀበት ሁኔታ ክሮሞዞም ከተዋቀረበት ሁኔታ ጋር ጨርሶ ሊወዳደር አይችልም።
ሙዚየሙ ውስጥ መግለጫ በሚሰጠው ስክሪን ላይ ያለው ጽሑፍ፣ ገመዱን በእጅህ ይዘህ ጠጋ ብለህ እንድትመለከት ይጋብዝሃል (5)። በእጅህ ስትነካካው ገመዱ ተራ ገመድ እንዳልሆነ ትገነዘባለህ። ገመዱ እርስ በርሳቸው ከተጠላለፉ ሁለት ፈትሎች የተሠራ ነው። ፈትሎቹ እኩል ርቀት ባላቸው በጣም ትናንሽ የሆኑ ዘንጎች የተያያዙ ናቸው። ገመዱ መሰላል የሚመስል ከመሆኑም ሌላ እንደ ጠመዝማዛ ደረጃ የተጠማዘዘ ነው (6)። በዚህ ጊዜ እጅግ አስደናቂ ከሆኑት የሕይወት ሚስጥሮች አንዱ የሆነውን የዲ ኤን ኤ ሞለኪውል ናሙና በእጅህ እንደያዝክ ትገነዘባለህ።
አንድ ነጠላ የዲ ኤን ኤ ሞለኪውል፣ በሥርዓት ከተጠቀለለባቸው ክብ ነገሮችና ደግፈው ከሚይዙት ነገሮች ጋር አንድ ላይ ተዳምሮ አንድ ክሮሞዞም ይፈጥራል። የመሰላሉ መወጣጫዎች ጥንድ ኬሚካሎች (7) ናቸው። ሥራቸው ምንድን ነው? የዚህ ሁሉ ነገር ዓላማስ ምንድን ነው? መግለጫ በሚሰጠው ስክሪን ላይ ያለው ጽሑፍ ቀለል ያለ ማብራሪያ ይሰጣል።
እጅግ አስደናቂ የሆነ የመረጃ ማዕከል
መግለጫ በሚሰጠው ስክሪን ላይ ያለው ጽሑፍ እንደሚያመለክተው ዋነኛው የዲ ኤን ኤ ሚስጥር ያለው ሁለቱን የመሰላል ቋሚዎች በሚያገናኙት መወጣጫ ዘንጎች ላይ ነው። መሰላሉ ለሁለት እንደተከፈለ አድርገህ አስብ። እያንዳንዱ ክፋይ መሃል ላይ የተቆረጠ መወጣጫ ይኖረዋል። እነዚህ የተቆረጡ መወጣጫዎች አራት ዓይነት ናቸው። ሳይንቲስቶች ኤ፣ ቲ፣ ጂ እና ሲ
የሚል ስያሜ ሰጥተዋቸዋል። የእነዚህ ፊደሎች ቅደም ተከተል በኮድ መልክ የሚያስተላልፈው መረጃ እንዳለ ሲገነዘቡ ሳይንቲስቶች በእጅጉ ተደንቀዋል።የሞርስ ኮድ የሚባለው የቴሌግራፍ መልእክት መለዋወጫ ኮድ በ19ኛው መቶ ዘመን እንደተፈለሰፈ ታውቅ ይሆናል። ይህ ኮድ ሁለት “ፊደላት” ይኸውም ነጥብና ሰረዝ ብቻ አሉት። ያም ሆኖ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ቃላትን ወይም ዓረፍተ ነገሮችን ለማስተላለፍ ያስችላል። ዲ ኤን ኤ ደግሞ ባለ አራት ፊደል ኮድ አለው። ኤ፣ ቲ፣ ጂ እና ሲ የተባሉት ፊደላት የሚሰፍሩበት ቅደም ተከተል ኮዶን የሚባል መጠሪያ የተሰጣቸውን “ቃላት” ያስገኛል። ኮዶኖች፣ ጂን ተብለው በሚጠሩ “ታሪኮች” ተቀናብረዋል። እያንዳንዱ ጂን በአማካይ 27,000 ፊደላት ይይዛል። እነዚህ ጂኖችና በመካከላቸው ያለው ክፍት ቦታ አንድ ላይ ተቀናብረው “ምዕራፎች” ይኸውም ራሳቸውን የቻሉ ክሮሞዞሞች ያስገኛሉ። ሙሉውን “መጽሐፍ” ማለትም የአንድን ሕያው ፍጡር የተሟላ የጄኔቲክ መረጃ የሚይዘውን ጂኖም ለማስገኘት 23 ክሮሞዞሞች ያስፈልጋሉ። b
አንድ ጂኖም በጣም ትልቅ መጽሐፍ ይወጣዋል። ለመሆኑ አንድ ጂኖም ምን ያህል መረጃ ይይዛል? በጥቅሉ ሲታይ የሰው ጂኖም በዲ ኤን ኤ መሰላል ላይ የሚገኙ ወደ ሦስት ቢሊዮን የሚጠጉ መወጣጫዎች አሉት።19 እስቲ አንድን ኢንሳይክሎፒዲያ ወደ አእምሮህ ለማምጣት ሞክር፤ እያንዳንዱ ጥራዝ ከአንድ ሺህ ገጾች በላይ ቢኖሩት በጂኖም ውስጥ ያለውን መረጃ እንዲህ ባለ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ ለማስፈር 428 ጥራዞች ያስፈልጋሉ። በእያንዳንዱ ሴል ውስጥ የሚገኘው ሁለተኛ ቅጂ ሲታከልበት ደግሞ 856 ጥራዞች ይወጣዋል። ጂኖም የያዘውን መረጃ በታይፕ መገልበጥ ቢኖርብህና ምንም እረፍት ሳትወስድ ሙሉ ቀን ብትሠራ 80 ዓመት ይፈጅብሃል!
እርግጥ ነው፣ ያን ያህል ደክመህ በታይፕ የገለበጥከው መረጃ ለሰውነትህ የሚፈይደው አንዳች ነገር አይኖርም። በሰውነትህ ውስጥ በዓይን የማይታዩ 100 ትሪሊዮን የሚሆኑ ሴሎች አሉ፤ ታዲያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትላልቅ መጻሕፍትን በእያንዳንዱ ሴል ውስጥ እንዴት ልትከት ትችላለህ? ይህን የሚያክል ብዙ መረጃ ጨምቆና አሳንሶ መክተት ከአቅማችን በላይ ነው።
አንድ የሞለኪውላር ባዮሎጂና የኮምፒውተር ሳይንስ ፕሮፌሰር እንዲህ ብለዋል፦ “ደረቅ በሚሆንበት ጊዜ ከአንድ ሴንቲ ሜትር ኩብ ያልበለጠ መጠን የሚኖረው አንድ ግራም ዲ ኤን ኤ በግምት አንድ ትሪሊዮን ሲዲዎች ሊይዙ የሚችሉትን የሚያክል መረጃ መያዝ ይችላል።”20 ይህ ምን ማለት ነው? በዲ ኤን ኤ ውስጥ በዓይነቱ ልዩ የሆነውን የሰው አካል ለመገንባት የሚያስፈልጉት መመሪያዎች የሚገኙባቸው ጂኖች እንዳሉ አስታውስ። እያንዳንዱ ሴል የተሟሉ መመሪያዎች አሉት። በዲ ኤን ኤ ውስጥ የታመቀው መረጃ እጅግ ብዙ ከመሆኑ የተነሳ አንድ የሻይ ማንኪያ የሚሆን ዲ ኤን ኤ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የዓለም ሕዝብ 350 እጥፍ የሚበልጥ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ለማስገኘት የሚያስችሉ መመሪያዎችን መያዝ ይችላል! በአሁኑ ጊዜ በምድራችን ላይ ለሚኖሩት ሰባት ቢሊዮን የሚያክሉ ሰዎች የሚያስፈልገው ዲ ኤን ኤ በሻይ ማንኪያው ላይ ከሚኖር ትንሽ ጠብታ አይበልጥም።21
ደራሲ የሌለው መጽሐፍ አለ?
መረጃ የሚይዙ የተለያዩ መሣሪያዎችን አሳንሶ በመሥራት ረገድ የታየው እድገት ቀላል ባይሆንም ከዚህ የመረጃ ማዕከል ጋር ሊጠጋጋ የሚችል አንድም ሰው ሠራሽ መሣሪያ መፈልሰፍ አልተቻለም። ያም ሆኖ ከሲዲ ጋር ልናነጻጽረው እንችላለን። አንድ ሲዲ ቅርጹ፣ አንጸባራቂነቱና የረቀቀ ንድፉ ሊያስደንቀን ይችላል። ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች እንደሠሩት ፈጽሞ አንጠራጠርም።
ይሁን እንጂ የያዘው መረጃ ምንም ጥቅም የሌለው ሳይሆን አንድ የተራቀቀ ማሽን እንዴት እንደሚገነባ እንዲሁም እንዴት እድሳትና ጥገና እንደሚደረግለት የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያ የያዘ አንድ ወጥ መረጃ ቢሆንስ? ይህ መረጃ በሲዲው ክብደት ወይም መጠን ላይ ያን ያህል ለውጥ አያመጣም። ይሁን እንጂ ከሁሉ በላይ አስፈላጊ የሆነው የሲዲው ገጽታ ይህ መረጃ ነው። በጽሑፍ የሠፈሩት እነዚህ መመሪያዎች ይህን ሥራ ያከናወነ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል እንዳለ አያሳምኑህም? ጸሐፊ የሌለው ጽሑፍ ይኖራል ብለህ ታስባለህ?ዲ ኤን ኤን ከሲዲ ወይም ከመጽሐፍ ጋር ማነጻጸር የማይመስል ነገር ነው ሊባል አይችልም። እንዲያውም ስለ ጂኖም የሚገልጽ አንድ መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “ጂኖም መጽሐፍ ነው ሲባል እንዲሁ ዘይቤያዊ አነጋገር አይደለም። ከዚህ ይልቅ ቃል በቃል የሚወሰድ አባባል ነው። መጽሐፍ የዲጂታል መረጃ ስብስብ ነው። . . . ጂኖምም ከዚህ የተለየ አይደለም።” የዚህ መጽሐፍ ደራሲ አክለው ሲናገሩ “ጂኖም ልዩ ችሎታ ያለው መጽሐፍ ነው፤ ምክንያቱም ተስማሚ ሁኔታ ሲፈጠርለት ራሱን መገልበጥና ማንበብ ይችላል” ብለዋል።22 ይህ ደግሞ በጣም አስፈላጊ ወደሆነ ሌላ የዲ ኤን ኤ ገጽታ ያሸጋግረናል።
በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ማሽኖች
በዚህ ፀጥታ በሰፈነበት ሙዚየም ውስጥ ሳለህ ‘የሴል ኒውክሊየስ እንደዚህ ሙዚየም ፀጥ ረጭ ያለ ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። በዚህ ጊዜ መግለጫ በሚሰጠው ስክሪን ላይ ሌላ ጽሑፍ ትመለከታለህ። የዲ ኤን ኤ ናሙና ከተቀመጠበት የመስታወት ሣጥን በላይ “ትዕይንቱን ለማየት ቁልፉን ተጫን” የሚል ጽሑፍ ታያለህ። ቁልፉን ጫን ስታደርግ ተራኪው እንዲህ ይላል፦ “ዲ ኤን ኤ ቢያንስ ሁለት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ተግባሮች አሉት። አንደኛው ራሱን ለማባዛት የሚያካሂደው ተግባር ነው። እያንዳንዱ አዲስ ሴል የጄኔቲክ መረጃው ሙሉ ቅጂ እንዲኖረው ዲ ኤን ኤው መባዛት ይኖርበታል። ይህ እንዴት እንደሚከናወን እስቲ ተመልከት።”
ትዕይንቱ በሚታይበት ቦታ፣ በአንደኛው ጫፍ በሚገኝ በር በኩል በጣም ውስብስብ የሆነ ማሽን ብቅ ይላል። ይህ ማሽን እርስ በርሳቸው የተያያዙ በርካታ ሮቦቶች ስብስብ ነው። ማሽኑ ወደ ዲ ኤን ኤው ይሄድና ራሱን ከዲ ኤን ኤው ጋር ካጣበቀ በኋላ ሐዲዱን ተከትሎ እንደሚሄድ ባቡር በዲ ኤን ኤው ላይ ማለፍ ይጀምራል። በፍጥነት ስለሚያልፍ ምን እያደረገ እንዳለ በደንብ
ማየት ባትችልም በአንዱ የዲ ኤን ኤ ገመድ ምትክ ሁለት ራሳቸውን የቻሉ ገመዶች ከኋላው እየተወ ሲሄድ ትመለከታለህ።ተራኪው እንዲህ በማለት ያብራራል፦ “ይህ ትዕይንት ዲ ኤን ኤ በሚባዛበት ጊዜ የሚከናወነውን ሁኔታ በጣም ቀላል በሆነ መንገድ የሚያሳይ ነው። ኢንዛይም ተብለው የሚጠሩ የተወሰኑ ሞለኪውላዊ ማሽኖች በዲ ኤን ኤ ላይ ያልፉና በመጀመሪያ ለሁለት ይከፍሉታል፤ ከዚያም እያንዳንዱን ክፋይ እንደ ንድፍ በመጠቀም አዲስ የማሟያ ፈትል ይሠራሉ። በዚህ ተግባር ላይ የሚካፈሉትን ነገሮች በሙሉ ይኸውም ከማባዣው ማሽን ፊት እንደምትሄደውና ዲ ኤን ኤው ጥብቅ ብሎ ከመጠምጠም ይልቅ ፈታ ብሎ እየተጠማዘዘ እንዲሄድ አንድ ጎኑን እንደምትቆርጠው በጣም አነስተኛ የሆነች ማሽን ያሉ ነገሮችን ልናሳይህ አንችልም። ዲ ኤን ኤው በሚገለበጥበት ጊዜ ስህተት እንዳይኖር እንዴት በተደጋጋሚ እንደሚታረምም ልናሳይህ አንችልም። ስህተቶቹ በጣም በሚያስገርም ሁኔታ አንድ በአንድ እየተለቀሙ ይታረማሉ።”— በገጽ 16 እና 17 ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።
ተራኪው በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “በግልጽ ልናሳይህ የምንችለው ነገር ቢኖር ፍጥነቱን ነው። ይህ ሮቦት በከፍተኛ ፍጥነት እንደሚንቀሳቀስ አስተውለሃል። እውነተኛው የኢንዛይም ማሽን በእያንዳንዱ ሴኮንድ በዲ ኤን ኤው ‘ሐዲድ’ ላይ 100 ገደማ የሚሆኑ መወጣጫዎችን ወይም ጥንድ ኬሚካሎችን አልፎ ይሄዳል።23 ‘ሐዲዱ’ የባቡር ሐዲድ ያክላል ብለን ብናስብ ይህ ‘ሞተር’ በሰዓት ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ ይጓዛል ማለት ነው። በባክቴሪያ ውስጥ እነዚህ ትናንሽ የማባዣ ማሽኖች ከዚህ አሥር እጥፍ በሚበልጥ ፍጥነት ይጓዛሉ! በሰው ሴል ውስጥ እንዲህ ያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የማባዣ ማሽኖች በዲ ኤን ኤው ‘ሐዲድ’ ላይ ወደተለያዩ ቦታዎች ተሰማርተው ተግባራቸውን ያከናውናሉ። ሙሉውን ጂኖም ለማባዛት የሚወስድባቸው ጊዜ ስምንት ሰዓት ብቻ ነው።”24 (በገጽ 20 ላይ የሚገኘውን “ ሊነበብና ሊባዛ የሚችል ሞለኪውል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
ዲ ኤን ኤን “ማንበብ”
ዲ ኤን ኤውን የሚያባዙት ሮቦቶች ቀስ በቀስ ከቦታው ገለል ይላሉ። ከዚያም ሌላ ማሽን ብቅ ይላል። ይህም ማሽን ቢሆን በዲ ኤን ኤው ላይ ያልፋል፤ ፍጥነቱ ግን አነስ ያለ ነው። የዲ ኤን ኤው ገመድ በማሽኑ አንድ ጫፍ ገብቶ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይደረግበት በሌላኛው ጫፍ ሲወጣ ትመለከታለህ። ነገር ግን አዲስ የሆነ አንድ ፈትል በማደግ ላይ እንዳለ ጅራት ማሽኑ ላይ በሚገኝ ሌላ ቀዳዳ በኩል ሲወጣ ታያለህ። ምን እየተከናወነ ነው?
አሁንም ተራኪው እንደሚከተለው በማለት ማብራሪያ ይሰጣል፦ “ዲ ኤን ኤ የሚያከናውነው ሁለተኛው ተግባር መገልበጥ ነው። ዲ ኤን ኤ አስተማማኝ መኖሪያው ከሆነው ከኒውክሊየስ ፈጽሞ አይወጣም። ታዲያ መላው የአካልህ ክፍሎች የተገነቡባቸው ፕሮቲኖች በሙሉ እንዴት እንደሚመረቱ የሚገልጹት መመሪያዎች ማለትም ጂኖቹ ሊነበቡና ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉት እንዴት ነው? ይህ የኢንዛይም ማሽን ዲ ኤን ኤው ላይ፣ ከሴሉ ኒውክሊየስ ውጭ በመጡ ኬሚካላዊ መልእክቶች የተከፈተ ጂን ያለበት አንድ ቦታ ያገኛል። ከዚያም ይህ ማሽን አር ኤን ኤ (ራይቦኑክሊክ አሲድ) የሚባል ሞለኪውል ተጠቅሞ ይህን ጂን ይገለብጠዋል።
አር ኤን ኤ አንዱን የዲ ኤን ኤ ፈትል ቢመስልም ከዲ ኤን ኤ የተለየ ነው። ተግባሩም በጂኖች ውስጥ በኮድ መልክ የተቀመጠውን መረጃ መውሰድ ነው። አር ኤን ኤ በኢንዛይም ማሽን ውስጥ እያለ መረጃውን ከወሰደ በኋላ ከኒውክሊየሱ ወጥቶ ወደ አንዱ ራይቦዞም ይሄዳል፤ በዚያም መረጃው ፕሮቲን ለመገንባት ያገለግላል።”ትዕይንቱን በምትመለከትበት ጊዜ በአድናቆት ስሜት ፈዘህ ትቀራለህ። በዚህ ሙዚየም እንዲሁም በውስጡ ያሉትን ማሽኖች ንድፍ ባወጡትና በገነቡት ሰዎች ጥበብ በጣም ትገረማለህ። ይሁን እንጂ በሰው ሴል ውስጥ በአንድ ጊዜ የሚከናወኑትን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተግባራት በትዕይንት መልክ ለማሳየት በዚህ ቦታ ውስጥ ያለ ነገር ሁሉ እንዲንቀሳቀስ ቢደረግስ? እንዴት ያለ አስደናቂ ትዕይንት ይሆን ነበር!
ይሁን እንጂ እጅግ ጥቃቅንና ውስብስብ በሆኑ ማሽኖች የሚከናወኑት እነዚህ ሂደቶች በሙሉ፣ በዚህች ቅጽበት ብቻ እንኳ በገዛ አካልህ ውስጥ በሚገኙ 100 ትሪሊዮን የሚሆኑ ሴሎች ውስጥ በመከናወን ላይ መሆናቸውን ትገነዘባለህ። ዲ ኤን ኤህ በሚነበብበት ጊዜ መላው አካላትህ ማለትም ኢንዛይሞችህ፣ ሕብረ ሕዋሶችህ፣ ብልቶችህ ወዘተ የተገነቡባቸውን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን የተለያዩ የፕሮቲን ዓይነቶች ለመገንባት የሚያስፈልገውን መመሪያ ይሰጣል። በእያንዳንዱ አዲስ ሴል ውስጥ የሚነበቡ አዳዲስ መመሪያዎች እንዲዘጋጁ ለማድረግ በዚህች ቅጽበት ውስጥ ዲ ኤን ኤህ በመባዛትና ስህተቶቹ እየተለቀሙ በመታረም ላይ ነው።
ለእነዚህ እውነታዎች ትኩረት መስጠት ለምን አስፈለገ?
አሁንም በድጋሚ ‘እነዚህ መመሪያዎች በሙሉ ከየት መጡ?’ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይህ “መጽሐፍ” እና በውስጡ የሠፈረው ጽሑፍ ከሰው የላቀ ኃይል ካለው ደራሲ የተገኘ እንደሆነ ይናገራል። እንዲህ ብሎ መደምደም ኢሳይንሳዊ ወይም ዘመን ያለፈበት ነው?
እስቲ ይህን አስብ፦ የሰው ልጆች ከላይ የተገለጸውን ሙዚየም እንኳ መሥራት ይችላሉ? ለመሥራት ቢሞክሩ እንኳ ሊወጡት የማይችሉት ችግር ውስጥ ይገባሉ። ስለ ሰው ጂኖም ምንነትም ሆነ ተግባሩን ስለሚያከናውንበት መንገድ ገና ብዙ ያልተደረሰበት ነገር አለ። ሳይንቲስቶች ጂኖች በሙሉ የት እንደሚገኙና ምን እንደሚያከናውኑ ለማወቅ ዛሬም ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። በዚያ ላይ ደግሞ ጂኖች የሚይዙት የዲ ኤን ኤን ፈትል አነስተኛ ክፍል ብቻ ነው። ጂኖች የሌሉባቸው አብዛኞቹ የፈትሉ ክፍሎችስ? ሳይንቲስቶች እነዚህን ክፍሎች አሰስ ገሰስ ዲ ኤን ኤ ብለው ይጠሯቸው ነበር፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህን አመለካከታቸውን ለመለወጥ ተገድደዋል። እነዚህ ክፍሎች፣ ጂኖቹ እንዴትና እስከ ምን ድረስ አገልግሎት ላይ እንደሚውሉ የሚቆጣጠሩ ሳይሆኑ አይቀሩም። ሳይንቲስቶች
የዲ ኤን ኤን እንዲሁም ዲ ኤን ኤን የሚያባዙትንና የሚያርሙትን ማሽኖች ሙሉ ናሙና ሊሠሩ ቢችሉ እንኳ እንደ እውነተኛው ዲ ኤን ኤ እንዲሠራ ሊያደርጉት ይችላሉ?ሪቻርድ ፋይንማን የተባሉት ዝነኛ ሳይንቲስት ከመሞታቸው ጥቂት ቀደም ብለው “ልፈጥር የማልችለውን ነገር መረዳት አልችልም” የሚል ማስታወሻ ጥቁር ሰሌዳ ላይ አስፍረው ነበር።25 በትሕትና እንዲህ ብለው በግልጽ መናገራቸው ደስ የሚል ነገር ነው፤ አባባላቸውም ቢሆን ከዲ ኤን ኤ ጋር በተያያዘ እውነትነት እንዳለው ግልጽ ነው። ሳይንቲስቶች የሚያባዛና የሚገለብጥ ማሽን ያለውን ዲ ኤን ኤ መፍጠርም ሆነ እንዲህ ያለውን ዲ ኤን ኤ ሙሉ በሙሉ መረዳት አይችሉም። ያም ሆኖ አንዳንዶች ይህ ሁሉ ነገር በዘፈቀደ በሚከሰቱ ድንገተኛ አጋጣሚዎች የተገኘ እንደሆነ እንደሚያውቁ አድርገው በእርግጠኝነት ይናገራሉ። እስካሁን የተመለከትከው ማስረጃ እንዲህ ያለውን መደምደሚያ ይደግፋል?
አንዳንድ ምሑራን ማስረጃው የሚያረጋግጠው ተቃራኒውን ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የተጠማዘዘ ቅርጽ ያለውን የዲ ኤን ኤን ባለ ሁለት ፈትል አወቃቀር በምርምር ካገኙት ሳይንቲስቶች አንዱ የሆኑት ፍራንሲስ ክሪክ፣ ይህ ሞለኪውል በጣም የተደራጀ በመሆኑ በዘፈቀደ በተከሰቱ ሁኔታዎች ሊገኝ አይችልም ብለዋል። ከምድር ውጭ ያለ የማሰብ ችሎታ ያለው አንድ አካል በምድር ላይ ሕይወት ያለው ነገር እንዲገኝ ለመርዳት ሲል ዲ ኤን ኤን ወደ ምድር ልኮ ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል።26
አሁን በቅርቡ ደግሞ ለ50 ዓመታት ያህል አምላክ የለም ብለው ሲከራከሩ የኖሩት እውቁ ፈላስፋ አንተኒ ፍሉ በአመለካከታቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ አድርገዋል። እኚህ ሰው በ81 ዓመታቸው፣ በሕይወት አፈጣጠር ላይ ድርሻ የነበረው የማሰብ ችሎታ ያለው አንድ አካል መኖር አለበት ብለው እንደሚያምኑ መናገር ጀምረዋል። እንዲህ ያለውን የአመለካከት ለውጥ እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? በዲ ኤን ኤ ላይ የተደረገው ጥናት ነው። ፍሉ ይህ አዲስ አመለካከታቸው በሳይንቲስቶች ዘንድ ተቀባይነት አያገኝ እንደሆነ ተጠይቀው ምላሽ ሲሰጡ “ባይቀበሉ እንግዲህ አዝናለሁ። ዕድሜዬን በሙሉ ስከተለው የኖርኩት ‘የትም ያድርስህ የት ማስረጃውን ተከተል’ የሚለውን . . . መሠረታዊ ደንብ ነው” ብለዋል።27
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ማስረጃው የሚያደርሰን ወዴት ነው? በአንድ ፋብሪካ ማዕከላዊ ቦታ ወደሚገኝ አንድ የኮምፒውተር ክፍል ገባህ እንበል። ኮምፒውተሩ የፋብሪካውን አጠቃላይ ሥራ የሚቆጣጠረውንና ውስብስብ የሆነውን ዋና ፕሮግራም የሚያንቀሳቅስ ነው። ከዚህ በላይ ደግሞ ይህ ፕሮግራም በዚያ ያለው እያንዳንዱ ማሽን እንዴት እንደሚገነባና እንደሚታደስ የሚገልጹ መመሪያዎችን ሳያቋርጥ ይልካል፤ በተጨማሪም ራሱን የሚያባዛ ከመሆኑም ሌላ ስህተቶቹን እየለቀመ ያርማል። እንዲህ ያለው ማስረጃ ወደ ምን መደምደሚያ ይመራሃል? ኮምፒውተሩና ፕሮግራሙ ራሳቸውን በራሳቸው አስገኙ ትላለህ ወይስ የማሰብ ችሎታ ባላቸው ሰዎች በሥርዓት የተዋቀሩ ናቸው ወደሚል መደምደሚያ ትደርሳለህ? ማስረጃው ራሱ ይመሠክራል!
a ሞለኪውላር ባዮሎጂ ኦቭ ዘ ሴል የተባለው መጽሐፍ ንጽጽሩን በተለየ መንገድ ገልጾታል። እነዚህን ረጃጅም ገመዶች በአንድ የሴል ኒውክሊየስ ውስጥ ጠቅልሎ ለማስገባት መሞከር፣ 40 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን በጣም ቀጭን የሆነ ክር በሜዳ ቴኒስ ኳስ ውስጥ ጠቅልሎ ለማስቀመጥ እንደ መሞከር ይቆጠራል፤ ይሁንና እያንዳንዱን የክሩን ክፍል በቀላሉ ማግኘት እንዲቻል ክሩ ሳይዘበራረቅ ሥርዓት ባለው መንገድ መጠምጠም ይኖርበታል።
b እያንዳንዱ ሴል የጂኖም ሁለት የተሟሉ ቅጂዎች ስለሚኖሩት በጠቅላላው 46 ክሮሞዞሞች ይኖሩታል።