ራሴን የማልወደው ለምንድን ነው?
ምዕራፍ 12
ራሴን የማልወደው ለምንድን ነው?
“መናኛ እንደሆንኩ ሆኖ ይሰማኛል” በማለት ሉዊዝ ኀዘኗን ትገልጻለች። አንዳንድ ጊዜ እናንተም ይህን የመሰለ ስሜት ይሰማችኋልን?
በእርግጥ ማንኛውም ሰው ለራሱ መጠነኛ የሆነ አክብሮት ሊኖረው ያስፈልጋል። ራስን በአክብሮት መመልከት “ለሰብዓዊ ሕልውና ክብር የሚሰጥ ቅመም” ተብሎ ተጠርቷል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ይላል። (ማቴዎስ 19:19 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ራሳችሁን ካልወደዳችሁ ግን ሌሎችንም ላትወዱ ትችላላችሁ።
‘ምንም ነገር በትክክል መሥራት አልችልም!’
ስለ ራሳችሁ እንዲህ ያለ አፍራሽ አመለካከት የሚኖራችሁ ለምንድን ነው? መጀመሪያ ነገር፣ አቅማችሁ ወይም ችሎታችሁ የተወሰነ መሆኑ ሊያበሳጫችሁ ይችላል። ገና በማደግ ላይ ያላችሁ በመሆናችሁ ብዙ ጊዜ በእጃችሁ የያዛችኋቸው ነገሮች አምልጠው እየወደቁባችሁ ወይም ከተለያዩ ነገሮች ጋር እየተጋጫችሁ በየዕለቱ እንድታፍሩ የሚያደርጋችሁ ሁኔታ ያጋጥማችሁ ይሆናል። ከዚህም ሌላ እንደ ትልልቅ ሰዎች ያበሳጫችሁን ሁኔታ የመርሳት ልምድና ተሞክሮ አላዳበራችሁም። ‘ልቦናችሁ [“የማመዛዘን ችሎታችሁ” አዓት]’ በበቂ ሁኔታ ‘ልምድ አግኝቶ’ የሠለጠነ ባለመሆኑ ሁልጊዜ ጥበብ ያለበት ውሳኔ ላታደርጉ ትችላላችሁ። (ዕብራውያን 5:14) አንዳንድ ጊዜ ምንም ነገር በትክክል መሥራት እንደማትችሉ ይሰማችሁ ይሆናል!
ወላጆቻችሁ ከእናንተ እንደሚጠብቁት ለመሆን አለመቻላችሁ ለራሳችሁ ያላችሁ አክብሮት ዝቅ እንዲል የሚያደርግ ሌላ ምክንያት ነው። “በትምህርት ቤት ያገኘሁት ውጤት ‘A ማይነስ’ ከሆነ” ይላል አንድ ወጣት “ወላጆቼ ለምን ሙሉ ‘A’ ሊሆን እንዳልቻለ ለማወቅ ይፈልጋሉ። ጨርሶ አትረባም ይሉኛል።” በእርግጥ ወላጆች ልጆቻቸው ምሳሌ 1:8, 9) ትችትና ወቀሳ ሲሰጣችሁ ተስፋ በመቁረጥ ፈንታ ወቀሳውን ተቀብላችሁ ከርሱ ትምህርት ለማግኘት ሞክሩ።
ከሌሎች ሁሉ እንዲልቁ መፈለጋቸው የተፈጥሮ ባሕርይ ነው። እነርሱ ከጠበቁት ምክንያታዊ ግብ ሳትደርሱ ስትቀሩ ደግሞ ቅር እንደሚሰኙ እርግጠኛ ልትሆኑ ትችላላችሁ። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ‘ልጄ ሆይ፣ የአባትህን/የአባትሽን ምክር ስማ/ስሚ፣ የእናትህንም/የእናትሽንም ሕግ አትተው/አትተይ’ ይላል። (ይሁን እንጂ ወላጆች ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከሌሎች ጋር ቢያወዳድሯችሁስ? (“እንደ ታላቅ ወንድምህ/ወንድምሽ እንደ ጳውሎስ ለምን አትሆንም/አትሆኝም? እርሱ ሁልጊዜ አንደኛ ይወጣል” ቢሉስ?) እንዲህ ማለታቸው በጊዜው ስሜታችሁን የሚጎዳ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ትክክለኛነት አለው። ወላጆቻችሁ ለእናንተ የሚመኙት ከሁሉ የተሻለውን ነው። በጣም ጥብቅ የሆኑባችሁ ከመሰላችሁ በጉዳዩ ላይ ከእነርሱ ጋር ረጋ ብላችሁ ለምን አትወያዩም?
ለራሳችሁ ያላችሁን የአክብሮት ስሜት ማሳደግ
ሊወድቅ የተቃረበውን ለራሳችሁ ያላችሁ የአክብሮት አመለካከት መልሳችሁ ልትገነቡ የምትችሉት እንዴት ነው? ከሁሉ አስቀድማችሁ ያላችሁን ጠንካራና ደካማ ጎን በሐቀኝነት መርምሩ። ደካማ ጎኖች ብላችሁ ከምትጠሯቸው ብዙዎቹ በጣም ጥቃቅን እንደሆኑ ትገነዘባላችሁ። ግልፍተኝነት ወይም ራስ ወዳድነትን የመሳሰሉ ከበድ ያሉ ጉድለቶች ካሉባችሁስ? እነዚህን ጉድለቶች ለማስወገድ በትጋት ጥረት ካደረጋችሁ ለራሳችሁ ያላችሁ የአክብሮት ስሜት ያድጋል።
በተጨማሪ አሁንም ቢሆን እንኳን አንዳንድ ጠንካራ ጎኖች ያላችሁ መሆኑን አትዘንጉ! ምግብ ማብሰል ወይም የተነፈሰ ጎማ መቀየር መቻል ይህን ያህል ትልቅ ነገር ነው ብላችሁ አታስቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ የተራበ ሰው ወይም ጎማ ተንፍሶበት መንገድ ላይ የቆመ
ባለ መኪና በዚህ ችሎታችሁ ያደንቃችኋል! በተጨማሪም ስለ ጥሩ ባሕሪዎቻችሁም እስቲ አስቡ። በሥራችሁ ታታሪ ናችሁን? ትዕግሥተኞች ናችሁን? ርኅሩኆች ናችሁን? ለጋሶች ናችሁን? ደጎች ናችሁን? እነዚህ ባሕርያት ያሉባችሁን ጥቃቅን ጉድለቶች በእጅጉ የሚያስንቁ ናቸው።በተጨማሪም የሚከተሉትን ማድረግ በጣም ሊረዳችሁ ይችላል:-
ልትደርሱባቸው የምትችሉ ምክንያታዊ ግቦችን አውጡ:- ሁልጊዜ በጣም ሩቅና ልትደርሱባቸው የማትችሏቸውን ዓይነት ግቦች የምታወጡ ከሆነ ከፍተኛ ብስጭት ይደርስባችኋል። ሊደረስባቸው የሚቻሉ ግቦችን አውጡ። የታይፕ ጽሕፈት የመሳሰሉ ሙያዎችን ብትማሩስ? የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት ወይም በሌላ ቋንቋ መናገር ተማሩ። ንባባችሁን አሻሽሉ ወይም የምታነቧቸውን ጽሑፎች ዓይነት አስፉ። የራስ ክብር አንድን ነገር ለማከናወን ከመቻል የሚመጣ ጠቃሚ ውጤት ነው።
ጥሩ ሥራ ሥሩ:- መናኛ ሥራ ከሠራችሁ ለራሳችሁ ጥሩ ግምት አይኖራችሁም። አምላክ በፍጥረት ሥራዎቹ በመርካቱ እያንዳንዱ የፍጥረት ዘመን ባለቀ ቁጥር “መልካም” እንደሆነ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 1:3–31) እናንተም ብትሆኑ በቤትም ሆነ በትምህርት ቤት የምትሠሯቸውን ነገሮች ሁሉ ጥርት አድርጋችሁ በጥንቃቄ ከሠራችሁ በሥራችሁ ልትረኩ ትችላላችሁ።— ምሳሌ 22:29 አዓት ተመልከቱ።
ሌሎችን የሚጠቅም ሥራ ሥሩ:- እጃችሁንና እግራችሁን አጣጥፋችሁ የምትቀመጡና ሌሎች እንዲያገለግሏችሁ የምታደርጉ ከሆነ ለራሳችሁ አክብሮት ሊሰማችሁ አይችልም። ኢየሱስ “ታላቅ ሊሆን የሚወድ . . . አገልጋይ” ወይም የሌሎች ባሪያ ይሁን ብሏል።— ማርቆስ 10:43–45
ለምሳሌ ያህል የ17 ዓመቷ ኪም በክረምት ዕረፍቷ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማሩ ለመርዳት በየወሩ 60 ሰዓት መደበች። እንዲህ ትላለች:- “ይህ አገልግሎት ከይሖዋ ጋር አቀራርቦኛል። ለሰዎችም ያለኝን እውነተኛ ፍቅር እንዳሳድግ ረድቶኛል።” ይህች ደስተኛ ወጣት ለራሷ አክብሮት አይኖራትም ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው!
ጓደኞቻችሁን በጥንቃቄ ምረጡ:- የ17 ዓመት ወጣት የሆነችው ባርባራ “ከራሴ ጋር ያለኝ ዝምድና በጣም ደስ የማይል ነው” ትላለች። “በእኔ ላይ እምነት ካላቸው ሰዎች ጋር በምሆንበት ጊዜ ጥሩ ሥራ እሠራለሁ። የአንድ መሣሪያ ቅጥያ እንደሆንኩ አድርገው ከሚቆጥሩኝ ሰዎች ጋር ስሆን ደግሞ ደደብ እሆናለሁ።”
ኩሩ ወይም ተሳዳቢ የሆኑ ሰዎች ስለ ራሳችሁ መጥፎ አመለካከት እንዲኖራችሁ ሊያደርጓችሁ ይችላሉ። ስለዚህ ለእናንተ በጎ ነገር የሚመኙላችሁና፣ የሚያንጹአችሁ ጓደኞች ምረጡ።—አምላክን ከማንም በላይ የቅርብ ወዳጃችሁ አድርጉት:- መዝሙራዊው ዳዊት “እግዚአብሔር መጠጊያዬና ጠንካራ ምሽጌ ነው” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 18:2 የ1980 ትርጉም) እርሱ የተመካው በራሱ ችሎታ ሳይሆን ከይሖዋ ጋር በነበረው የቅርብ ወዳጅነት ነበር። በመሆኑም ከጊዜ በኋላ መከራ በደረሰበት ጊዜ የተሰጠውን ከባድ ወቀሳ በተረጋጋ መንፈስ ለመቀበል ችሏል። (2 ሳሙኤል 16:7, 10) እናንተም ‘ወደ አምላክ ልትቀርቡና’ በራሳችሁ ሳይሆን በይሖዋ ልትመኩ ትችላላችሁ!— ያዕቆብ 2:21–23፤ 4:8፤ 1 ቆሮንቶስ 1:31
መጨረሻው የማያምር አካሄድ
አንድ ጸሐፊ “አንዳንድ ጊዜ ለራሱና ለማንነቱ ደካማና ዝቅተኛ የሆነ አመለካከት ያለው ጎረምሳ ዓለምን የሚጋፈጥበት የውሸት ግንባር ወይም መልክ ለመፍጠር ይሞክራል” ብለዋል። የአንዳንዶቹ የማስመሰያ ድርጊቶች ተመሳሳይነት አላቸው:- “ጉልበተኛ”፣ ዘማዊ፣ የፓንክ ፋሽን አሳዳጅ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉት ወጣቶች ለውጪው ዓለም ከሚያሳዩት የውሸት መልክ በስተጀርባ ካለባቸው የዝቅተኝነት ስሜት ጋር በመታገል ላይ የሚገኙ ናቸው።— ምሳሌ 14:13
ለምሳሌ ያህል “ከትካዜ ስሜት ለመሸሽና [ተፈላጊ እንደሆኑ እንዲሰማቸው በማድረግ] ለራሳቸው ያላቸውን ግምት ከፍ ለማድረግ፣ የቅርብ ወዳጅ ለማግኘትና በእርግዝና አማካኝነትም የሌላ ሰው ማለትም የሕፃን ፍቅርና ጥያቄ የሌለበት ተቀባይነት ለማግኘት ሲሉ” ወደ ዝሙት የሚገቡ ወጣቶችን ሁኔታ አስቡ። (ኮፒንግ ዊዝ ቲንኤጅ ዲፕሬሽን) አንዲት ግራ የተጋባች ወጣት “ከፈጣሪዬ ጋር ጠንካራ ዝምድና
ለመመሥረት ከመጣር ይልቅ ከጾታ ግንኙነት ማጽናኛ ለማግኘት ሞከርኩ። የገነባሁት ሁሉ ባዶነት፣ ብቸኝነትና የበለጠ ትካዜ ብቻ ሆነብኝ” ብላለች። እንግዲያውስ እንደዚህ ካሉት መጨረሻቸው ከማያምር አካሄዶች ተጠበቁ።የማስጠንቀቂያ ቃል
ቅዱሳን ጽሑፎች ራሳችንን ከሚገባው በላይ ከፍ አድርገን እንዳንመለከት በተደጋጋሚ ያስጠነቅቃሉ! ይህ የሆነው ለምንድን ነው? በግልጽ እንደሚታየው አብዛኞቻችን በራሳችን የመተማመን ስሜት እንዲያድርብን በምናደርገው ጥረት ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር ለመፈጸም ወደ መፈለግ ስለምናዘነብል ነው። ብዙዎች ለራሳቸው ከልክ ያለፈ ትኩረት በመስጠት አቅማቸውንና ችሎታቸውን አለቅጥ አጋንነው ይመለከታሉ። አንዳንዶች ደግሞ ሌሎችን በማዋረድ ራሳቸውን ከሌሎች በላይ ያደርጋሉ።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን በአይሁድና በአሕዛብ (አይሁድ ባልሆኑ ሰዎች) መካከል የነበረው ኃይለኛ ፉክክር በሮም በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ላይ ችግር አስከትሎ ነበር። በዚህም ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ አሕዛብ ክርስቲያኖች በአምላክ ሞገስ “እንዲታቀፉ” ያስቻላቸው የአምላክ “ምሕረት” ብቻ መሆኑን አሳስቧቸዋል። (ሮሜ 11:17–36) በራሳቸው ሥራ ለመጽደቅ ይጥሩ የነበሩት አይሁዳውያንም ፍጹማን አለመሆናቸውን መቀበል ነበረባቸው። ጳውሎስ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” ብሏል።— ሮሜ 3:23
ጳውሎስ “እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው ሮሜ 12:3) ስለዚህ አንድ ሰው ራሱን በአክብሮት መመልከቱ “ተገቢ” ቢሆንም በዚህ ረገድ ከመጠን ማለፍ አይኖርበትም።
አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ” አላቸው እንጂ ለራሳቸው የነበራቸውን ግምት አላንቋሸሸባቸውም። (ዶክተር አላን ፍሮም እንደሚከተለው ሲሉ ተናግረዋል:- “ስለ ራሱ በቂ ግንዛቤ ያለው ሰው ኀዘንተኛ አይደለም፤ ይሁን እንጂ ከመጠን በላይ በራሱ ተደስቶ መፈንጠዝም አይኖርበትም። . . . ሊሆን አይችልም የሚል አመለካከት ባይኖረውም ይሆናል የሚል አመለካከቱ ልጓም የሌለው አይሆንም። አጉል ጀብደኛ ወይም ከማንኛውም ዓይነት ፍርሃት ነፃ የሆነ ሰው አይደለም። . . . ሁልጊዜ የተሳካ ውጤት ሊያገኝ እንደማይችልና በሌላ በኩል ደግሞ ምንም ነገር የማይሳካለት ሰው እንዳልሆነ ይገነዘባል።”
ስለዚህ ልከኞች ሁኑ። “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፣ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።” (ያዕቆብ 4:6) ጠንካራ ጎኖች ያሏችሁ መሆኑን አምናችሁ ተቀበሉ፣ ይሁን እንጂ ጉድለቶች ያሏችሁ መሆኑንም አትዘንጉ። ጉድለቶቻችሁን ለማሻሻል ጣሩ። ያም ሆኖ ራሳችሁን አልፎ አልፎ መጠራጠራችሁ አይቀርም። ይሁን እንጂ ዋጋ ያላችሁ መሆናችሁን ወይም አምላክ የሚያስብላችሁ መሆኑን ፈጽሞ መጠራጠር የለባችሁም። ምክንያቱም “ማንም . . . እግዚአብሔርን ቢወድ እርሱ በእርሱ ዘንድ የታወቀ” ስለሆነ ነው።— 1 ቆሮንቶስ 8:3
የመወያያ ጥያቄዎች
◻ አንዳንድ ወጣቶች ስለ ራሳቸው አፍራሽ አመለካከት ያላቸው ለምንድን ነው? እናንተም እነዚህ ወጣቶች የሚሰማቸው ዓይነት ስሜት አላችሁን?
◻ ወላጆቻችሁ የሚፈልጉባችሁን ልታሟሉ የምትችሉት እንዴት ነው?
◻ ለራሳችሁ ያላችሁን አክብሮት ለማሳደግ የሚረዱ አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
◻ አንዳንዶች ለራሳቸው ያላቸውን አክብሮት ለማሳደግ ሲሉ የሚከተሏቸው መጨረሻቸው የማያምር አንዳንድ አካሄዶች ምንድን ናቸው?
◻ ስለ ራሳችሁ በትዕቢት እንዳታስቡ መጠንቀቅ ያለባችሁ ለምን ድን ነው?
[በገጽ 98 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ለራስ አክብሮት ማሳየት “ለሰብዓዊ ሕልውና ክብር የሚሰጥ ቅመም” ተብሎ ተጠርቷል
[በገጽ 99 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኀዘንና የዝቅተኝነት ስሜት ይሰማሃልን? እንዲህ ላለው ስሜት መፍትሔ አለው
[በገጽ 101 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጉረኛ መሆን ስለ ራሱ ዝቅተኛ የሆነ አመለካከት ላለው ሰው መፍትሔ አይሆነውም
[በገጽ 102 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንድ ጊዜ ምንም ነገር በትክክል መሥራት እንደማትችሉ ይሰማችኋልን?