የእኩዮችን ግፊት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
ምዕራፍ 9
የእኩዮችን ግፊት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
ካረን ገና በ14 ዓመት ዕድሜዋ አደንዛዥ ዕፅ አብዝታ መውሰድና አዘውትራ ሩካቤ ሥጋ መፈጸም ጀምራ ነበር። ጂም በ17 ዓመት ዕድሜው የለየለት ጠጪና በብልግና አኗኗር የሚመላለስ ወጣት ሆኖ ነበር። ሁለቱም በአኗኗራቸውም ሆነ በሚያደርጓቸው ነገሮች እንደማይደሰቱ አምነዋል። ታዲያ እነዚህን መጥፎ ተግባሮች የሚፈጽሙት ለምን ነበር? ከእኩዮቻቸው በደረሰባቸው ግፊት ምክንያት ነበር!
ካረን “በአካባቢዬ የነበሩት ሁሉ እነዚህን ነገሮች ያደርጉ ነበር፣ ያ ደግሞ በእኔ ላይ ትልቅ ውጤት አስከትሏል” ትላለች። ጂምም “ከእነርሱ የተለየሁ በመሆን ጓደኞቼን ማጣት አልፈለግሁም ነበር” በማለት ከካረን ጋር የሚስማማ ሐሳብ ሰጥቷል።
ወጣቶች እኩዮቻቸውን የሚከተሉት ለምንድን ነው?
አንዳንድ ወጣቶች እያደጉ ሲሄዱ ወላጆቻቸው የሚያሳድሩባቸው ተጽእኖ እየተዳከመ ስለሚሄድ በእኩዮቻቸው ዘንድ ታዋቂ የመሆንና ተቀባይነት የማግኘት ፍላጎት እያየለባቸው ይሄዳል። ሌሎቹ ደግሞ “ስሜታቸውን ከሚረዳላቸው” ወይም ተወዳጆችና ተፈላጊዎች እንደሆኑ እንዲሰማቸው ከሚያደርግ ሰው ጋር ማውራት እንደሚያስፈልጋቸው ይሰማቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ ሐሳብ ለሐሳብ መለዋወጥ በቤት ውስጥ በማይኖርበት ጊዜ ደግሞ፣ ብዙውን ጊዜም ስለ ሌለ በእኩዮቻቸው ዘንድ ተደማጭነት ለማግኘት ይሻሉ። በተጨማሪም ብዙውን ጊዜ በራስ የመተማመን ጉድለትና መተማመኛ የማጣት ስሜት አንዳንዶች ለእኩዮቻቸው ተጽእኖ እንዲሸነፉ ያደርጋቸዋል።
የእኩዮች ተጽእኖ ሙሉ በሙሉ መጥፎ ነው ማለት አይቻልም። አንድ ምሳሌ “ብረት ብረትን ይስለዋል፣ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል” ይላል። (ምሳሌ 27:17) አንድ የብረት ቢላዋ ስለቱ የደነዘውን ሌላ ቢላዋ እንደሚስለው ሁሉ ከሌሎች ወጣቶች ጋር መወዳጀትም ባሕርያችሁን ‘ሊሞርደውና’ የተሻላችሁ ሰዎች እንድትሆኑ ሊያደርጋችሁ ይችላል። ታዲያ ይህ የሚሆነው እነዚህ እኩዮቻችሁ የበሰለና ጤናማ አስተሳሰብ ያላቸው ከሆኑ ነው።
ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች አእምሯዊም ሆነ መንፈሳዊ ብስለት ይጎድላቸዋል። ብዙ ወጣቶች ጤናማ ያልሆነ፣ እምነት ሊጣልበት የማይችል፣ እንዲያውም የደንታ ቢስነት አመለካከትና አስተያየት አላቸው። ስለዚህ አንድ ወጣት በጭፍን በእኩዮቹ ተጽእኖ ሥር በሚሆንበት ጊዜ ዕውር ዕውርን ከመምራት የማይሻል ነገር ይሆናል። (ከማቴዎስ 15:14 ጋር አወዳድሩ።) ውጤቱም በጣም አደገኛ ሊሆን ይችላል።
እኩዮች ወደ መጥፎ ባሕርይ የማይገፋፏችሁ ቢሆኑም እንኳን ተጽእኗቸው በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል። “በሌሎች ልጆች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት በጣም ትፈልጋላችሁ” ትላለች ዴቢ። “አሥራ ስምንት ዓመት ሲሆነኝ በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ አለመሆን በጣም ያስፈራኝ ነበር። ምክንያቱም ወደ አንዳንድ መዝናኛዎች እንድሄድ የሚጋብዘኝ ሰው አላገኝ ይሆናል ብዬ እፈራ ስለ ነበር ነው። ከሰው የተነጠልኩ ብቸኛ እሆናለሁ ብዬ እሰጋ ነበር።” ስለዚህ ዴቢ በእኩዮቿ ዘንድ ተወዳጅ ለመሆን ብርቱ ጥረት አደረገች።
ግፊት እየተደረገብኝ ነውን?
ታዲያ እናንተም እኩዮቻችሁን ለመምሰል ስትሉ እንደ እኩዮቻችሁ መልበስ፣ መናገር ወይም እነሱ የሚያደርጉትን ማድረግ ጀምራችኋልን? የአሥራ ሰባት ዓመቷ ሱዚ “እናንተ ልታደርጉ የማትፈልጉትን ነገር በሌላ ልጅ ግፊት ልታደርጉት አትችሉም” በማለት ትናገራለች። ይሁን እንጂ የእኩዮች ግፊት በጣም የረቀቀ ከመሆኑ የተነሳ ምን ያህል እየለወጣችሁ እንዳለ ላትገነዘቡት ትችላላችሁ። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጴጥሮስን እንውሰድ። ጴጥሮስ ጠንካራ እምነት የነበረው ደፋር ሰው ስለነበረ የክርስትና ዓምድ ሆኖ ነበር። አምላክ ከሁሉም አሕዛብና ዘር የተውጣጡ ሕዝቦች የአምላክን ሞገስ ሊያገኙ እንደሚችሉ የገለጸው ለጴጥሮስ ነው። ስለዚህ ጴጥሮስ የመጀመሪያዎቹ የአሕዛብ አማኞች ክርስቲያኖች እንዲሆኑ ረድቷል።— ሥራ 10:28
ይሁን እንጂ ጊዜያት ካለፉ በኋላ ጴጥሮስ አይሁዳውያን ያልሆኑ ብዙ ክርስቲያኖች ወደነበሩባት የአንጾኪያ ከተማ ሄደ። ጴጥሮስ ከእነዚህ አሕዛብ የነበሩ ክርስቲያኖች ጋር ያላንዳች ገደብ ተቀላቅሎ ነበር። ከዕለታት
አንድ ቀን ግን ለአሕዛብ የነበራቸው አግባብ የሌለው ጥላቻ ገና ያልለቀቃቸው አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ መጡ። ታዲያ በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ እነዚህ አይሁዳውያን መሰሎቹ ባሉበት ምን ያደርግ ይሆን?ጴጥሮስ ከአሕዛብ ክርስቲያኖች ተለይቶ ከእነርሱ ጋር ለመብላት እምቢተኛ ሆነ! ለምን? አይሁዳውያን መሰሎቹን እንዳያስቀይማቸው ብሎ በመፍራት ሊሆን ይችላል። ምናልባት ‘እነርሱ እዚህ እስካሉ ድረስ እንደሚፈልጉት ልሁንላቸውና ሲሄዱ ግን ከአሕዛብ ጋር መብላቴን እቀጥላለሁ። በዚህ ትንሽ ነገር ከእነርሱ ጋር ያለኝን ዝምድና ለምን አበላሻለሁ?’ ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል። በዚህ መንገድ ጴጥሮስ የማያምንበትን ነገር በማድረግ የሚያምንበትን መሠረታዊ ሥርዓት ስለ ጣሰ አስመሳይ ሆነ። (ገላትያ 2:11–14) የእኩዮች ተጽእኖ ፈጽሞ ሊያሸንፈኝ አይችልም ሊል የሚችል ሰው እንደማይኖር ግልጽ ነው።
ምን አደርጋለሁ?
ስለዚህ ‘ሌሎች ምን ይሉኛል ብዬ አልጨነቅም!’ ብሎ መናገሩ ቀላል ቢሆንም የእኩዮች ግፊት በሚያጋጥምበት ጊዜ ግን ይህንን ቆራጥ
አቋም ይዞ መገኘት በጣም የተለየ ነገር ነው። ለምሳሌ ያህል የሚከተሉት ሁኔታዎች ቢያጋጥሙህ/ቢያጋጥሙሽ ምን ታደርጋለህ/ታደርጊያለሽ?ከክፍል ጓደኞችህ አንዱ በሌሎች ወጣቶች ፊት ሲጋራ አጭስ ብሎ ይሰጥሃል። ማጨስ ስህተት እንደሆነ ታውቃለህ። ይሁንና ምን እንደምታደርግ ለማየት ሁሉም ዙሪያውን ከበው ይመለከቱሃል . . .
በትምህርት ቤቱ ያሉት ሴት ልጆች ከወንድ ጓደኞቻቸው ጋር ሩካቤ ሥጋ እንደፈጸሙ ያወራሉ። ከልጃገረዶቹ አንዷ “መቼም እስካሁን ድንግል አይደለሽም፤ አይደል?” ትልሻለች።
ሌሎቹ ልጃገረዶች የሚለብሱትን ዓይነት ቀሚስ መልበስ ፈልገሽ ነበር። እናትሽ ግን በጣም አጭር ነው ብላ ከልክላሻለች። እናትሽ እንድትለብሺ በተደጋጋሚ የምትነግርሽ ልብስ የስድስት ዓመት ልጅ የሚያስመስልሽ መስሎ የሚሰማሽን ልብስ ነው። የክፍልሽ ልጆች ይቀልዱብሻል። አንዷ ልጅ “ለምን ለምሳ የሚሰጥሽን ገንዘብ አጠራቅመሽ ደህና ልብስ አትገዢም? ለእናትሽ መናገር አያስፈልግሽም። የትምህርት ቤት ልብስሽን መሳቢያሽ ውስጥ አስቀምጪው” ትልሻለች።
እነዚህ በቀላሉ ልትቋቋሙ የምትችሏቸው ሁኔታዎች ናቸውን? አይደሉም። ይሁን እንጂ ለእኩዮቻችሁ እምቢ ለማለት የምትፈሩ ከሆነ ለገዛ ራሳችሁ፣ ለራሳችሁ አቋምና ለወላጆቻችሁ እምቢ ባዮች ትሆናላችሁ። ታዲያ የእኩዮችን ግፊት ለመቋቋም የሚያስችላችሁን ጥንካሬ ልታዳብሩ የምትችሉት እንዴት ነው?
“የማሰብ ችሎታ”
የአሥራ አምስት ዓመቷ ሮቢን እሷ ስለፈለገች ሳይሆን ሌሎች ስለሚያጨሱ ብቻ ማጨስ ጀመረች። “በኋላ ግን ‘ሲጋራውን አልወደውም። ታዲያ ለምን አጨሳለሁ?’ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። ከዚያ ከአሁን ወዲያ አላጨስም” ብላ እንደወሰነች ትናገራለች። ለራሷ የሚያዋጣትን በማሰቧ የእኩዮቿን ተጽእኖ ለመቋቋም ቻለች!
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ወጣቶች “እውቀትንና የማሰብ ችሎታን” እንዲያዳብሩ አጥብቆ ማሳሰቡ ተገቢ ነው። (ምሳሌ 1:1–5 አዓት ) የማሰብ ችሎታ ያለው ሰው ተሞክሮ የሌላቸው እኩዮቹ እንዲመሩት አይፈቅድም። በተጨማሪም የማሰብ ችሎታ ያለው ሰው በራሱ በመተማመን የሌሎችን አስተያየት አይንቅም። (ምሳሌ 14:16) ‘ጠቢብ ይሆን ዘንድ ምክርን ለመስማትና ተግሣጽን ለመቀበል’ ፈቃደኛ ይሆናል።— ምሳሌ 19:20
ይሁንና የራሳችሁን የማሰብ ችሎታ በመጠቀማችሁ ብትጠሉ ወይም ቢሳቅባችሁ አትደነቁ። ምሳሌ 14:17 (አዓት) “የማሰብ ችሎታ ያለው [ያላት] ሰው [ሴት] ይጠላል [ትጠላለች]” ይላል። ይሁን እንጂ በእርግጥ የበለጠ ጥንካሬ ያላቸው እነማን ናቸው? ለወረትና ለስሜታቸው የሚሸነፉት ናቸው ወይስ ተገቢ ላልሆኑ ፍላጎቶቻቸው እምቢ ማለት የሚችሉት? (ከምሳሌ 16:32 ጋር አወዳድሩ።) የሚያሾፉባችሁ እኩዮቻችሁ ሕይወት የሚያመራው ወዴት ነው? የእናንተም ሕይወት መጨረሻው እንደ እነርሱ እንዲሆን ትፈልጋላችሁን? በእናንተ ትክክለኛ አቋም የሚያሾፉባችሁ በእናንተ ንጹሕ አቋም በመቅናትና ውስጣዊ ችግራቸውን ለመሸፋፈን ብለው ሊሆን አይችልምን?
ወጥመዱን ማምለጥ
ምሳሌ 29:25 “ሰውን መፍራት ወጥመድ ያመጣል” ይላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ ያልጠረጠረ እንስሳ እርሱን ለማጥመድ የተቀመጠውን ምግብ ሊያነሳ ሲል በድንገት በወጥመድ ይያዝ ነበር። ዛሬም በእኩዮቻችሁ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ያላችሁ ፍላጎት ምግብ እንዳለበት የወጥመዱ ተስፈንጣሪ ክፍል ሊሆን ይችላል። አምላካዊ የሥነ ምግባር ደረጃዎችን በመተላለፍ ወጥመድ ውስጥ አታልሎ ሊያስገባችሁ ይችላል። ታዲያ ሰውን መፍራት የሚያመጣውን ወጥመድ እንዴት ልታመልጡ ወይም ልትርቁ ትችላላችሁ?
በመጀመሪያ ጓደኞቻችሁን በጥንቃቄ ምረጡ! (ምሳሌ 13:20) ጓደኝነታችሁን ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርና የአቋም ደረጃ ካላቸው ጋር አድርጉ። እርግጥ እንዲህ ማድረጉ ጓደኝነት ልትመሠርቱ የምትችሉበትን ክልል ይወስንባችኋል። በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ አንድ ወጣት ሲናገር “በትምህርት ቤት ካሉት ልጆች ጋር አደንዛዥ ዕፆችን በመውሰድና ሩካቤ ሥጋ በመፈጸም እንደማልተባበራቸው ሲመለከቱ ወዲያውኑ ተዉኝ። ይህም እነሱን እንድመስል የሚያመጡብኝን ብዙ ግፊት ከላዬ ቢያነሳልኝም በመጠኑ የብቸኝነት ስሜት እንዲሰማኝ አድርጎኝ ነበር” ብሏል። ይሁን እንጂ የእኩዮች ተጽእኖ ወደ መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ አዘቅጥ እንዲጥላችሁ ከመፍቀድ ይልቅ መጠነኛ የብቸኝነት ስሜት ቢደርስባችሁ ይሻላል። ከቤተሰቦቻችሁ ጋርና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ካሉት ጋር ጓደኛ መሆን ብቸኝነት እንዳይሰማችሁ ሊረዳ ይችላል።
ወላጆቻችሁን ማዳመጥም የእኩዮችን ተጽእኖ እንድትቋቋሙ ይረዳችኋል። (ምሳሌ 23:22) ወላጆቻችሁ ትክክለኛ ሥነ ምግባርን ሊያስተምሯችሁ እየጣሩ ሊሆን ይችላል። አንዲት ወጣት “ወላጆቼ በእኔ ላይ ጥብቅ ነበሩ። እንዲህ መሆናቸውን አንዳንድ ጊዜ አልወደውም ነበር። ይሁን እንጂ ከአቋማቸው ፍንክች ሳይሉ [ከእኩዮቼ ጋር] የማደርገውን ቅርርቦሽ በመግታታቸው [አሁን] ደስ ይለኛል” በማለት ተናግራለች። ከወላጆቿ ባገኘችው እርዳታ ምክንያት አደንዛዥ ዕፆችን እንድትወስድና የጾታ ግንኙነት እንድትፈጽም ለሚመጣባት ግፊት ሳትሸነፍ ቀርታለች።
የወጣቶች አማካሪ የሆኑት ቤት ዊንሽፕ በተጨማሪ ሲናገሩ “አንድ ዓይነት ችሎታ ያላቸው ወጣቶች በችሎታቸው ምክንያት ተፈላጊዎች እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ስለ ራሳቸው ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው የእኩዮቻቸውን አድናቆት ማግኘት አያስፈልጋቸውም” ብለዋል። ታዲያ በትምህርት ቤትም ሆነ በቤት አካባቢ በምትሠሩት ነገር ችሎታና ብቃት ያላችሁ ለመሆን ለምን አትጥሩም? በተለይም ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች 2 ጢሞቴዎስ 2:15
በክርስቲያናዊ አገልግሎታቸው ‘የእውነትን ቃል በትክክል የሚናገር የማያሳፍር ሠራተኛ’ ለመሆን ይጣጣራሉ።—ምሳሌ 29:25 ሰውን መፍራት ስለሚያስከትለው “ወጥመድ” ካስጠነቀቀ በኋላ በመቀጠል “በእግዚአብሔር የሚታመን ግን እርሱ ይጠበቃል” ይላል። ምናልባትም ከምንም ነገር በላይ የእኩዮቻችሁን ግፊት እንድትቋቋሙ ሊያጠነክራችሁ የሚችለው ከአምላክ ጋር ያላችሁ ዝምድና ነው። ለምሳሌ ያህል ዴቢ (ቀደም ብለን የጠቀስናት ወጣት) በከባድ ጠጪነትና አደንዛዥ ዕፆችን በመውሰድ ለተወሰነ ጊዜ የብዙኃኑ ተከታይ ሆና ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን በቁም ነገር ማጥናት ከጀመረች በኋላ ግን በይሖዋ ላይ ያላት እምነት እየጨመረ ሄደ። ውጤቱስ ምን ሆነ? “የእኩዮቼ አነስተኛ ቡድን የሚያደርገውን ነገር ላለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ” ትላለች ዴቢ። የቀድሞ ጓደኞቿን “እናንተም በምትፈልጉት መንገድ ሂዱ፣ እኔም በምፈልገው መንገድ እሄዳለሁ። ጓደኝነቴን ከፈለጋችሁ እኔ የማከብራቸውን የአቋም ደረጃዎች ማክበር ይኖርባችኋል። ይቅርታ አድርጉልኝ እንጂ እናንተ ስለምታስቡት ነገር አልጨነቅም። የማደርገው ይህንን ነው” ብላ ነገረቻቸው። ዴቢ የያዘችውን አዲስ እምነት በአክብሮት የተመለከቱት ሁሉም ጓደኞቿ አልነበሩም። ይሁን እንጂ ዴቢ ስትናገር “ውሳኔውን ካደረግሁ በኋላ ከቀድሞው የበለጠ በራሴ ተደሰትኩ” ብላለች።
እናንተም እንደዚሁ የእኩዮች ግፊት ከሚያስከትለው ወጥመድ ካመለጣችሁ ‘በራሳችሁ ይበልጥ ትደሰታላችሁ፤’ ከብዙ ኃዘንም ትድና ላችሁ!
የመወያያ ጥያቄዎች
◻ ወጣቶች በእኩዮቻቸው ግፊት ወደመነዳት የሚያዘነብሉት ለምንድን ነው? ይህስ ሁልጊዜ መጥፎ ነው ማለት ይቻላልን?
◻ የሐዋርያው ጴጥሮስ ተሞክሮ የእኩዮችን ተጽእኖ በተመለከተ ምን ያስተምራል?
◻ እምቢ ለማለት ያላችሁን ችሎታ የሚፈትኑ አንዳንድ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? (አንዳንድ የግል ተሞክሮዎች ካሉም መጨመር ይቻላል።)
◻ አንድ ተገቢ ያልሆነ ነገር እንድታደርጉ ግፊት ሲደረግባችሁ ልታስቡባቸው የምትችሏቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
◻ ሰውን መፍራት ከሚያስከትለው ወጥመድ እንድታመልጡ ሊረዷችሁ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 74 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በሌሎች ልጆች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት በጣም ትፈልጋላችሁ” ትላለች ዴቢ። “በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ ካልሆንኩ . . . ከሰው የተነጠልኩ ብቸኛ እሆናለሁ ብዬ እሰጋ ነበር”
[በገጽ 75 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
‘እስቲ ወንድ!’
ሊዛን የክፍል ጓደኞቿ “እስቲ አስተማሪዋን አፍሽ ይገማል በያት!” እያሉ ይወተውቷታል። ይህን የሚሉት የአፍ ንጽሕና አጠባበቅ ጉዳይ ስላሳሰባቸው አይደለም። ሊዛ ደፋር መሆኗን እንድታሳይ መጠየቃቸው ነው። በእርግጥም አደገኛ የሆነ ድፍረት ነው! አዎን፣ አንዳንድ ወጣቶች ከመጠነኛ ጉዳት ራስን እስከ መግደል የሚያደርሱ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ ሌሎችን በማደፋፈር በተሳሳተ መንገድ ደስታ ለማግኘት የሚፈልጉ ይመስላል።
ይሁን እንጂ ሌሎች የቂልነት፣ የጭካኔ፣ ወይም ፍጹም አደገኛ የሆነ ድርጊት እንድትፈጽሙ በሚያደፋፍሯችሁ ጊዜ ቆም ብላችሁ ማሰብ ይኖርባችኋል። አንድ ጥበበኛ ሰው “የሞቱ ዝንቦች የተቀመመውን የዘይት ሽቱ ያገሙታል፤ እንዲሁም ትንሽ ስንፍና [“ሞኝነት” አዓት ] ጥበብንና ክብርን ያጠፋል” ብሏል። (መክብብ 10:1) በጥንት ጊዜ አንድ ጥሩ የቅባት ዘይት ወይም ሽቶ የሞተ ዝንብን በሚያህል ትንሽ ነገር ሊበላሽ ይችል ነበር። በተመሳሳይም አንድ ሰው በብዙ ልፋት ያገኘው መልካም ዝና ‘በትንሽ ሞኝነት’ ብቻ ሊበላሽበት ይችላል።
ልጆች ለማሳቅ ብለው የሚያደርጉት የተንኮል ድርጊት ብዙውን ጊዜ ዝቅተኛ የፈተና ውጤት ማግኘትን፣ ከትምህርት ቤት መታገድን፣ እንዲያውም መታሰርን ሳይቀር ሊያስከትል ይችላል! ይሁንና እንደማይነቃባችሁ ቢሰማችሁስ? ራሳችሁን እንደሚከተለው እያላችሁ ጠይቁ:- እንዳደርግ የተጠየቅሁት ነገር ምክንያታዊ ነውን? ፍቅራዊ ነውን? የመጽሐፍ ቅዱስን ወይም ወላጆቼ ያስተማሩኝን የሥነ ምግባር መስፈርት የሚያስጥስ ነውን? የሚያስጥስ ከሆነ ለመሳቅ ብለው የተንኮል ድርጊት ለማድረግ የሚፈልጉ ወጣቶች ሕይወቴን እንዲቆጣጠሩት እፈልጋለሁን? ሕይወቴንና መልካም ስሜን አደጋ ላይ እንድጥል የሚጠይቁኝ ወጣቶችስ እውነተኛ ወደጆቼ ሊሆኑ ይችላሉን?— ምሳሌ 18:24
እንግዲያውስ ‘እስቲ ወንድ’ እያለ ከሚገዳደራችሁ ወጣት ጋር ምክንያት እያቀረባችሁ ለመወያየት ሞክሩ። የአሥራ ስምንት ዓመቷ ቴሪ ‘ይህን የማደርገው ለምንድን ነው? ይህን ማድረጌስ ምን ነገር ሊያረጋግጥ ይችላል?’ ብላ ጥያቄያቸው ምንም ዓይነት ደስታ የማያስገኝ መሆኑን ለማስረዳት ትሞክራለች። በተጨማሪም የምትመሩባቸው የታወቁ የሥነ ምግባር መስፈርቶች ያሏችሁ መሆኑን አሳውቁ። አንዲት ወጣት ልጃገረድ አንድን ወጣት ወንድ ወደ ብልግና ለመገፋፋት “እንዴት ያለ ነገር እንደቀረብህ አታውቅም” በማለት ልታደፋፍረው ሞክራ ነበር። “አሳምሬ አውቃለሁ” አለ ልጁ ሲመልስ፣ “ኸርፐስ (የሚያቆስል የአባለ ዘር በሽታ)፣ ጨብጥ፣ ቂጥኝ፣ . . . [ቀርቶብኛል]” አላት።
አዎን፣ እኩዮቻችሁ አድርጉ የሚሏችሁን ነገር እምቢ ለማለት ድፍረት ከኖራችሁ የኋላ ኋላ የምትጸጸቱበትን ነገር ከማድረግ ልትቆጠቡ ትችላላችሁ!
[በገጽ 76 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣቶች ብዙውን ጊዜ ድጋፍ ለማግኘት እርስ በርሳቸው ይረዳዳሉ
[በገጽ 77 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስህተት እንደሆነ የምታውቁትን ነገር እንድታደርጉ የእኩዮች ግፊት ደርሶባችሁ ያውቃልን?
[በገጽ 78 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የእኩዮችን ግፊት ለመቋቋም ጥንካሬ ይኑራችሁ!