ምን ዓይነት መዝናኛ ብመርጥ ይሻላል?
ምዕራፍ 32
ምን ዓይነት መዝናኛ ብመርጥ ይሻላል?
የሚከተሉት ዓረፍተ ነገሮች እውነት ናቸው ወይስ ሐሰት?
ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር . . .
በማንኛውም ስፖርት መካፈል ሁልጊዜ ስህተት ነው።
□ እውነት □ ሐሰት
ሁሉም ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች መጥፎ ናቸው።
□ እውነት □ ሐሰት
ማንኛውም ዳንስ የተከለከለ ነው።
□ እውነት □ ሐሰት
ምሳሌ 20:29) አሁን ትንሽ ዘና ማለት አምሮሃል።
ሳምንቱን ሙሉ ስትለፋ ሰንብተሃል። ዛሬ የሳምንቱ መጨረሻ ስለሆነ ትምህርት የለህም። የቤት ውስጥ ሥራዎችህንም አጠናቅቀሃል። ያም ሆኖ የድካም ስሜት የሚባል ነገር የለህም፤ ወጣት የመሆን ጥቅሙ ይሄ ነው። (እኩዮችህ፣ መጽሐፍ ቅዱስ መዝናናትን እንደሚከለክልና ጥሩ ጊዜ እንዳታሳልፍ እንቅፋት እንደሆነብህ ይሰማቸው ይሆናል። ይሁንና ይህ እውነት ነው? እስቲ እውነት ወይም ሐሰት ብለህ እንድትመልስ በፊተኛው ገጽ ላይ የቀረቡትን ዓረፍተ ነገሮች እንመርምር፤ ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መዝናናት ምን እንደሚል እንመለከታለን።
● በማንኛውም ስፖርት መካፈል ሁልጊዜ ስህተት ነው።
ሐሰት። መጽሐፍ ቅዱስ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጥቂቱ ይጠቅማል” ይላል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) በዛሬው ጊዜ ጥሩ የሰውነት እንቅስቃሴ ለማድረግና ለመዝናናት የሚረዱ እንደ ብስክሌት መንዳት፣ ሶምሶማ ሩጫ፣ ቴኒስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ እግር ኳስና መረብ ኳስ ያሉ በርካታ ስፖርቶች አሉ።
ታዲያ ይህ ሲባል ጥንቃቄ ማድረግ አያስፈልግህም ማለት ነው? እስቲ ከላይ ያለውን ጥቅስ ሙሉ ሐሳብ እንመልከት። ሐዋርያው ጳውሎስ ለወጣቱ ጢሞቴዎስ ሲጽፍ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጥቂቱ ይጠቅማል፤ ለአምላክ ማደር ግን ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ ሕይወት የሚሆን ተስፋ ስላለው ለሁሉም ነገር ይጠቅማል።” ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ ምንጊዜም ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባው ነገር አምላክን ማስደሰት እንደሆነ ያጎላል። የምትካፈልባቸውን የስፖርት ዓይነቶች ስትመርጥም እንኳ ለአምላክ ማደር በሕይወትህ ውስጥ ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ እንዲሆን ለማድረግ ከዚህ በታች የቀረቡትን ሦስት ጥያቄዎች ራስህን መጠየቅህ ጥሩ ነው፦
1. የመረጥኩት ስፖርት ምን ያህል ለአደጋ ያጋልጠኛል? በሰዎች ወሬ ተመርተህ ወይም እኩዮችህ ስላዳነቁት ብቻ በስፖርቱ ለመካፈል መነሳሳት የለብህም። ከዚህ ይልቅ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት ጥረት አድርግ። ለምሳሌ የሚከተሉትን ነገሮች ለማጣራት ሞክር፦ በዚህ ስፖርት ሲካፈሉ ምን ያህል ሰዎች ጉዳት ይደርስባቸዋል? በስፖርቱ የሚካፈሉ ሰዎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ምን ዓይነት ቅድመ ጥንቃቄ ይደረጋል? አደጋ በማያስከትል መንገድ ለመጫወት ምን ዓይነት ሥልጠና እና ቁሳቁስ ያስፈልጋል? ማንኛውንም እንቅስቃሴ
ስናደርግ አደጋ ሊያጋጥመን እንደሚችል የታወቀ ቢሆንም የዚህ ስፖርት ዋነኛ ዓላማ ራስን ለከባድ አደጋ ወይም ለሞት በማጋለጥ የጀብደኝነት ድርጊት መፈጸም ነው?ሕይወት ከአምላክ የተገኘ ስጦታ ነው፤ አምላክ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ መሠረት አንድ ሰው ሳያስበው ሕይወት ቢያጠፋ ከባድ ቅጣት ይጣልበት ነበር። (ዘፀአት 21:29፤ ዘኍልቍ 35:22-25) የአምላክ ሕዝቦች ለአደጋ የሚያጋልጡ ነገሮችን እንዲያስወግዱ የሚጠበቅባቸው ለዚህ ነበር። (ዘዳግም 22:8) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖችም ለሕይወት አክብሮት የማሳየት ግዴታ አለባቸው።
2. የመረጥኩት ስፖርት ጥሩ ጓደኞች እንዳፈራ ይረዳኛል? በአትሌቲክስ ጥሩ ችሎታ ካለህ እኩዮችህና አስተማሪዎችህ በትምህርት ቤቱ የስፖርት ቡድን ውስጥ እንድትገባ ጫና ያሳድሩብህ ይሆናል። አንተም የቀረበልህን ግብዣ ለመቀበል ትፈተን ይሆናል። ማርክ የተባለ አንድ ክርስቲያን ወጣት “ወላጆቼ በትምህርት ቤታችን የስፖርት ቡድን ውስጥ እንዳልገባ መከልከላቸው ምክንያታዊ መስሎ አይታየኝም” በማለት ይናገራል። ይሁን እንጂ ወላጆችህን ለማሳመን ከመጣር ይልቅ እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች አስብባቸው፦ ብዙውን ጊዜ ልምምድና ግጥሚያ የሚካሄደው ከመደበኛው የትምህርት ሰዓት ውጪ ነው። ጎበዝ ተጫዋች ከሆንክ ለስፖርቱ ተጨማሪ ጊዜ እንድትመድብ ግፊት ይደረግብሃል። ያን ያህል ጎበዝ ካልሆንክ ደግሞ ለልምምድ የምታውለውን ጊዜ መጨመር እንደሚያስፈልግህ ይሰማሃል። ከዚህም በተጨማሪ የአንድ ቡድን አባላት
ድል ሲያደርጉም ሆነ ሲሸነፉ አንዳቸው የሌላውን ስሜት ስለሚጋሩ ብዙውን ጊዜ የተለየ ቅርርብ ይፈጥራሉ።እስቲ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘እንደ እኔ ዓይነት መንፈሳዊ አቋም ከሌላቸው ወጣቶች ጋር የቀረበ ጓደኝነት እንድመሠርት በሚያደርግ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በመካፈል ትርፍ ጊዜዬን ከእነዚህ ወጣቶች ጋር ማሳለፌ በጎ ተጽዕኖ ያሳድርብኛል?’ (1 ቆሮንቶስ 15:33) ‘በአንድ ቡድን ውስጥ ገብቼ ለመጫወት ስል ምን ያህል መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ ነኝ?’
3. የመረጥኩት ስፖርት ምን ያህል ጊዜና ወጪ ይጠይቅብኛል? መጽሐፍ ቅዱስ ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይተን ለማወቅ’ እንድንጥር ይመክረናል። (ፊልጵስዩስ 1:10) ይህን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ እንድትችል ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በዚህ ስፖርት መካፈሌ ለትምህርትና ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የመደብኩትን ጊዜ ይሻማብኛል? ምን ያህል ወጪ ይጠይቅብኛል? ይህን ወጪ ለመሸፈን አቅሜ ይፈቅድልኛል?’ በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ማሰብህ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች ቅድሚያ እንድትሰጥ ይረዳሃል።
● ሁሉም ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች መጥፎ ናቸው።
ሐሰት። መጽሐፍ ቅዱስ ‘መልካም የሆነውን አጥብቀው እንዲይዙና ከማንኛውም ዓይነት ክፋት እንዲርቁ’ ክርስቲያኖችን ያዛል። (1 ተሰሎንቄ 5:21, ) ከዚህ መመሪያ ጋር የሚጋጩት ሁሉም ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች አይደሉም። 22 *
ከጓደኞችህ ጋር ሆነህ ፊልም ለማየት ሲኒማ ቤት መግባት ደስ የሚል እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ሊ የምትባል በደቡብ አፍሪካ የምትኖር ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ፊልም ማየት ካማረኝ ለአንዷ ጓደኛዬ ደውዬ እነግራትና ወሬው ለጓደኞቻችን እንዲዳረስ እናደርጋለን።” አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ወጣቶች ቀን ላይ የሚታየውን ፊልም ከተመለከቱ በኋላ ወላጆቻቸው መጥተው ይወስዷቸዋል፤ ከዚያም ሬስቶራንት በመሄድ አንድ ላይ ሰብሰብ ብለው ይመገባሉ።
ፊልምና ቴሌቪዥን ዘመን አመጣሽ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ሆኖም አቀራረቡ መልኩን ቀይሮ መጣ እንጂ በድሮ ዘመንም ሰዎች የተለያዩ ታሪኮችን ያወሩ ነበር። ኢየሱስ በተለያዩ ታሪኮች ተጠቅሞ የሰዎችን ልብ በመንካት ረገድ የተዋጣለት ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ደጉ ሳምራዊ የተናገረው ታሪክ የሌሎችን ስሜት የምንረዳ እንድንሆን የሚያበረታታ ከመሆኑም ሌላ ከግብረ ገብነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቁም ነገር ያዘለ ነው።—ሉቃስ 10:29-37
በዛሬው ጊዜ ያሉ ፊልም ሠሪዎችም በሥነ ምግባር ረገድ የሚያስተላልፉት መልእክት በሰዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። የፊልም አዘጋጆች ታሪኩን የሚያቀርቡት ተመልካቾች በፊልሙ ውስጥ ያሉትን ገጸ ባሕርያት ስሜት እንዲጋሩ በሚያደርግ መንገድ ነው፤ በፊልሙ ውስጥ ያለው ዋና ተዋናይ ወንጀለኛ ወይም ጨካኝና የሥልጣን ጥመኛ ቢሆንም እንኳ የፊልሙ አቀራረብ ተመልካቹ እሱን እንዲደግፍ ሊያደርገው ይችላል። ካልተጠነቀቅህ አንተም ወንጀለኛው ለሚፈጽመው የጭካኔ ወይም ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ሰበብ በመፍጠር እሱን መደገፍ ልትጀምር ትችላለህ! ታዲያ ከዚህ ወጥመድ ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?
ኤፌሶን 4:32) “ወይስ በሌላው ሰው መከራ እንድደሰት ተጽዕኖ ያደርግብኛል?” (ምሳሌ 17:5) “‘ክፋትን መጥላት’ ከባድ እንዲሆንብኝ ያደርጋል?” (መዝሙር 97:10) “ይህን ፊልም መመልከት ‘ክፉዎችን’ እንደመደገፍ ይሆንብኛል?”—መዝሙር 26:4, 5
አንድ ፊልም ወይም የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለማየት ስትወስን እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ “የማየው ነገር ‘ከአንጀት የምራራ’ እንድሆን ይረዳኛል?” (ባለሙያዎች የሰጧቸው አስተያየቶችና የፊልሙ ማስታወቂያዎች በተወሰነ መጠን ስለ ፊልሙ ይዘት ለማወቅ ያስችሉሃል። ሆኖም እንደ ሞኝ ‘ሁሉን አትመን።’ (ምሳሌ 14:15) ለምን? ባለሙያዎች የሚሰጡት አስተያየት የራሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብሃል። ከዚህም ሌላ በማስታወቂያዎች ላይ የፊልሙ መጥፎ ገጽታ ሆን ተብሎ ሊሸፋፈን ይችላል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኘው ካኒ “የፊልሙ ዋና ተዋናዮች እነማን እንደሆኑ ማወቄ አብዛኛውን ጊዜ ፊልሙ ምን ዓይነት ይዘት እንዳለው ለመገመት ይረዳኛል” ብላለች።
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የሥነ ምግባር አቋምህን የሚጋሩ ክርስቲያን ወጣቶች አንድ ፊልም ተቀባይነት ያለው መሆን አለመሆኑን ለመለየት ሊረዱህ ይችላሉ። ያም ቢሆን ሰዎች ስለ አንድ ፊልም ሲያወሩልህ የወደዱትን ክፍል ብቻ ሊጠቅሱ እንደሚችሉ አስታውስ። በፊልሙ ውስጥ ምን መጥፎ ነገር እንዳለ ለምን አትጠይቃቸውም? ስለ ፊልሙ በዝርዝር ለማወቅ ሞክር። ለምሳሌ፣ በፊልሙ ውስጥ ዓመፅ፣ የፆታ ብልግና ወይም መናፍስታዊ ድርጊት ይታይ እንደሆነ ጠይቃቸው። ወላጆችህም በዚህ ረገድ ጥሩ ምክር ሊሰጡህ ይችላሉ። ቨኔሳ የተባለችው ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼን አማክራቸዋለሁ። ፊልሙን ብመለከተው ችግር እንደሌለው ከተሰማቸው ሄጄ አየዋለሁ።”
የምትመለከተውን ፊልም ወይም የቴሌቪዥን ፕሮግራም መምረጥን አቅልለህ ልታየው አይገባም። ለምን? ምክንያቱም የምትመርጠው መዝናኛ፣ በልብህ ውስጥ ያለው በሌላ አባባል ከፍ አድርገህ የምትመለከተው ምን እንደሆነ ያሳያል። (ሉቃስ 6:45) የምታያቸው ፊልሞች ስለ አንተ ማንነት ብዙ ይናገራሉ፤ ለምሳሌ ከጓደኛ ምርጫ፣ ከአነጋገርና ከፆታ ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ ያለህ አቋም ጠንካራ መሆን አለመሆኑን ያሳያሉ። ስለዚህ መራጭ ሁን!
● ማንኛውም ዳንስ የተከለከለ ነው።
ሐሰት። እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን ከተሻገሩና ከግብፃውያን ሠራዊት ካመለጡ በኋላ ማርያምና ሌሎቹ ሴቶች ደስታቸውን በጭፈራ ገልጸው ነበር። (ዘፀአት 15:20) በተጨማሪም ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ ልጁ ወደ ቤቱ ሲመለስ ቤተሰቡ ‘በሙዚቃና በጭፈራ’ ደስታቸውን ገልጸዋል።—ሉቃስ 15:25
ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በብዙ ባሕሎች ውስጥ ወዳጅ ዘመድ አንድ ላይ ሲሰባሰብ ወጣቶችም ሆኑ ትልልቅ ሰዎች መጨፈር ደስ ይላቸዋል። ይሁንና ጥንቃቄ የሚያሻው ነገር አለ። መጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓታማ በሆነ መንገድ አንድ ላይ ሰብሰብ ብሎ ጊዜ ማሳለፍን ባያወግዝም ‘ከፈንጠዝያ’ ወይም መረን ከለቀቀ ግብዣ መራቅ እንዳለብን ያስጠነቅቃል። (ገላትያ 5:19-21) ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የሚያሰክር መጠጥ ፍለጋ ማልደው ለሚነሡ፣ እስኪያነዳቸውም ወይን በመጠጣት ሌሊቱን ለሚያነጉ ወዮላቸው! በግብዣቸው ላይ በገናና መሰንቆ፣ ከበሮና ዋሽንት እንዲሁም የወይን ጠጅ አለ፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ሥራ ቦታ አልሰጡም።”—ኢሳይያስ 5:11, 12
እንዲህ ባሉ ግብዣዎች ላይ “የሚያሰክር መጠጥ” እንዲሁም መረን የለቀቀ ሙዚቃ ነበር። ግብዣው በጠዋቱ ጀምሮ እስከ ምሽት ድረስ ይቀጥል ነበር። በግብዣው ላይ የነበሩትን ሰዎች ዝንባሌም ልብ በል፤ አኳዃናቸው አምላክ የለም የሚሉ ያህል ነበር! በእርግጥም አምላክ እንዲህ ያሉ ግብዣዎችን ማውገዙ ምንም አያስገርምም።
ጭፈራ ባለበት አንድ ፓርቲ ላይ እንድትገኝ ግብዣ ከቀረበልህ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘እነማን ይገኛሉ? በሌሎች ዘንድ ምን ዓይነት ስም አትርፈዋል? ግብዣውን በኃላፊነት የሚከታተለው ማን ነው? ምን ዓይነት ቁጥጥር ይደረጋል? ወላጆቼ በግብዣው ላይ እንድገኝ ይፈቅዱልኛል? ምን ዓይነት ዳንሶች ይኖራሉ?’ ብዙዎቹ የዳንስ ዓይነቶች የፆታ ፍላጎት መቀስቀስን ዓላማ ያደረጉ ናቸው። እንዲህ ባለው ዳንስ መካፈል ሌላው ቀርቶ ዳንሱን መመልከት እንኳ “ከዝሙት ሽሹ” የሚለውን መመሪያ መከተል ከባድ እንዲሆንብህ የሚያደርግ አይመስልህም?—የምሽት ክበብ በመሄድ እንድትጨፍር ግብዣ ቢቀርብልህስ? ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ብዙ ጊዜ ወደ ዳንስ ቤቶች ይሄድ የነበረ ሾን የተባለ ወጣት የሰጠውን ሐሳብ ልብ በል፦ “አብዛኛውን ጊዜ ሙዚቃው ወራዳ፣ ዳንሱ ደግሞ ለፆታ ብልግና የሚያነሳሳ ሲሆን ወደነዚህ ቦታዎች የሚሄዱት ብዙዎቹ ሰዎች አንድ ዓላማ አላቸው።” ሾን እንደተናገረው ዓላማቸው ከጭፈራው በኋላ አብሯቸው የሚተኛ ሰው ማግኘት ነው። ሾን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ካጠና በኋላ አመለካከቱ ተቀየረ። ስለ እነዚህ ቦታዎች ምን ይላል? “ለክርስቲያኖች የሚሆኑ አይደሉም።”
መዘናጋት የሌለብህ ለምንድን ነው?
አንድ ወታደር ለጥቃት ይበልጥ የሚጋለጠው መቼ ይመስልሃል? በጦር ሜዳ ሲሆን ነው? ወይስ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ሲዝናና? እንደ እውነቱ ከሆነ፣
የሚሰነዘርበትን ጥቃት ለመመከት ያን ያህል ዝግጁ የማይሆነውና ለጥቃት የሚጋለጠው በሚዝናናበት ጊዜ ነው። በተመሳሳይ አንተም በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ ስትሆን መንፈሳዊ ጥቃትን ለመመከት ይበልጥ ዝግጁ ትሆናለህ። ሊያጋጥሙህ የሚችሉትን አደጋዎች በንቃት ትከታተላለህ። ከጓደኞችህ ጋር ሆነህ ዘና በምትልበት ጊዜ ግን የሥነ ምግባር አቋምህን እንድታላላ ለሚሰነዘርብህ ጥቃት ይበልጥ ትጋለጣለህ።አንዳንድ እኩዮችህ በመዝናኛ ረገድ ላቅ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች አጥብቀህ በመከተልህ ይቀልዱብህ ይሆናል። ክርስቲያን የሆኑ ወላጆች ያሏቸው አንዳንድ ወጣቶችም ጭምር ተጽዕኖ ያሳድሩብህ ይሆናል። ሆኖም እንደነዚህ ያሉት ወጣቶች ሕሊናቸው በጋለ ብረት የተተኮሰ ያህል ደንዝዟል። (1 ጢሞቴዎስ 4:2) ሚዛናዊ እንዳልሆንክ ወይም ራስህን እንደምታመጻድቅ አድርገው ይናገሩህ ይሆናል። አንተ ግን ለእኩዮችህ ተጽዕኖ ከመሸነፍ ይልቅ ‘ጥሩ ሕሊና እንዲኖርህ’ ጥረት አድርግ።—1 ጴጥሮስ 3:16
ትልቁ ነገር እኩዮችህ ስለ አንተ ያላቸው አመለካከት ሳይሆን ይሖዋ ለአንተ ያለው አመለካከት ነው! ጓደኞችህ ሕሊናህ የሚልህን በመስማትህ የሚያሾፉብህ ከሆነ ሌሎች ጓደኞች ማፍራት ይኖርብሃል። (ምሳሌ 13:20) በምትዝናናበት ጊዜም እንኳ ሥነ ምግባራዊ አቋምህን የመጠበቁ ኃላፊነት በዋነኝነት የወደቀው በአንተ ላይ መሆኑን አትዘንጋ።—ምሳሌ 4:23
ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 37 ተመልከት
ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ የብልግና ምስሎች በጣም የተስፋፉ ከመሆኑም ሌላ እነዚህን ነገሮች ማግኘት ቀላል ሆኗል። ከዚህ ወጥመድ ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.22 ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 36 ተመልከት።
ቁልፍ ጥቅስ
“አንተ ወጣት፣ በወጣትነትህ ጊዜ ደስ ይበልህ፣ . . . የልብህን መንገድና ዓይንህ የሚያያቸውን ነገሮች ተከተል። ሆኖም በእነዚህ ነገሮች ሁሉ የተነሳ እውነተኛው አምላክ ወደ ፍርድ እንደሚያመጣህ እወቅ።”—መክብብ 11:9 NW
ጠቃሚ ምክር
በወር አንዴ ቴሌቪዥናችሁን በማጥፋት በቤተሰብ ሆናችሁ ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ የምትችሉበትን ቋሚ ፕሮግራም ማውጣት ይችሉ እንደሆነ ወላጆችህን ጠይቃቸው።
ይህን ታውቅ ነበር?
ውዝዋዜና ሙዚቃ ከእውነተኛው አምልኮ ጋር በተያያዘ በእስራኤላውያን ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ነገሮች ነበሩ።—መዝሙር 150:4
ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች
ከትምህርት ሰዓት ውጪ በስፖርት ቡድን ውስጥ ገብቼ እንድጫወት ከተጠየቅሁ እንዲህ እላለሁ፦ ․․․․․
ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ የማየው ፊልም መጥፎ ነገር እንዳለበት ከተመለከትኩ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․
ምን ይመስልሃል?
● ክርስቲያኖች ለሕይወት አደገኛ ከሆኑ ስፖርቶች መራቅ ያለባቸው ለምንድን ነው?
● አንድ ፊልም ለክርስቲያኖች እንደሚሆን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?
● በአንተ አመለካከት ተገቢ የሚባለው ምን ዓይነት ዳንስ ነው?
[በገጽ 269 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
መደነስ በጣም የምወድ ቢሆንም በዚህ ረገድ የወላጆቼን ምክር መስማት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ተምሬያለሁ። ዳንስ በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ቦታ እንዲይዝ አላደርግም።”—ቲና
[በገጽ 268 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ወታደር ለጥቃት የሚጋለጠው ዘና በሚልበት ጊዜ ነው፤ አንተም የሥነ ምግባር አቋምህን እንድታላላ ለሚሰነዘርብህ ጥቃት የምትጋለጠው በምትዝናናበት ጊዜ ነው