በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከወንድሞቼና ከእህቶቼ ጋር ተስማምቼ ለመኖር ምን ላድርግ?

ከወንድሞቼና ከእህቶቼ ጋር ተስማምቼ ለመኖር ምን ላድርግ?

ምዕራፍ 6

ከወንድሞቼና ከእህቶቼ ጋር ተስማምቼ ለመኖር ምን ላድርግ?

ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር ያለህን ግንኙነት ይበልጥ በሚገልጸው ሐሳብ ላይ ✔ አድርግ።

□ በጣም የምንዋደድ ጓደኛሞች ነን

□ አብዛኛውን ጊዜ እንስማማለን

□ እንደምንም እንቻቻላለን

□ ሁልጊዜ እንጣላለን

አንዳንድ ወንድማማቾችና እህትማማቾች በጣም ይቀራረባሉ። ለምሳሌ ያህል፣ 19 ዓመት የሆናት ፈሊሻ “የ16 ዓመቷ እህቴ ኢሬና በጣም ከምቀርባቸው ጓደኞቼ አንዷ ናት” ብላለች። የ17 ዓመቷ ካርሊ ደግሞ 20 ዓመት ስለሆነው ወንድሟ ስለ ኤሪክ ስትናገር “በጣም እንስማማለን፤ አንድም ቀን ተጣልተን አናውቅም” ብላለች።

ሎረንና ማርላ የተባሉትን እህትማማቾች ደግሞ እንመልከት፤ ሎረን “የማንጣላበት ነገር የለም ማለት ይቻላል። በሆነ ባልሆነው እንጨቃጨቃለን” በማለት ተናግራለች። ከወንድሞቻቸውና ከእህቶቻቸው ጋር እንዲህ ዓይነት ግንኙነት ያላቸው ብዙዎች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ የ12 ዓመት ልጅ የሆነችው አሊስ 14 ዓመት ስለሆነው ወንድሟ ስትናገር “ዴኒስ ሊያሳብደኝ ደርሷል! ክፍሌን በርግዶ ይገባና ሳያስፈቅደኝ ዕቃዎቼን ይወስዳል። ነገረ ሥራው ሁሉ እንደ ሕፃን ነው!” ብላለች። አንተም እንዲህ ይሰማህ ይሆናል።

ወንድምህ ወይም እህትህ የሚያደርጉት ነገር ያበሳጭሃል? እርግጥ ነው፣ በቤተሰቡ ውስጥ ሥርዓት የማስፈን ኃላፊነት ያለባቸው ወላጆችህ ናቸው። ይሁንና ይዋል ይደር እንጂ፣ ከሌሎች ጋር እንዴት ተስማምተህ እንደምትኖር መማር አለብህ። ይህን ችሎታ ቤት እያለህ ልታዳብረው ትችላለህ።

እስቲ ከወንድምህ ወይም ከእህትህ ጋር ስለተጋጫችሁባቸው ጉዳዮች ለማሰብ ሞክር። ብዙውን ጊዜ የሚያጣሏችሁ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው? ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት ነገሮች መካከል አንተን በሚያበሳጩህ ነጥቦች ላይ ✔ አድርግ።

ንብረት፦ ወንድሜ ወይም እህቴ ሳያስፈቅዱኝ ዕቃዎቼን ይወስዳሉ።

የባሕርይ አለመጣጣም፦ ወንድሜ ወይም እህቴ ራስ ወዳድና ስለ ሌላው ጨርሶ የማያስቡ ናቸው፤ በዚያ ላይ ደግሞ እያንዳንዷን እንቅስቃሴዬን ለመቆጣጠር ይሞክራሉ።

መብትን አለማክበር፦ ወንድሜ ወይም እህቴ ሳያንኳኩ ወደ ክፍሌ ይገባሉ፤ አሊያም የኢ-ሜይል ወይም የጽሑፍ መልእክቶቼን ሳያስፈቅዱኝ ያነባሉ።

ሌላ ․․․․․

ወንድምህ ወይም እህትህ በአንተ ላይ ሥልጣናቸውን ለማሳየት በመሞከር አለዚያም መብትህን ባለመጠበቅ ሁልጊዜ የሚያበሳጩህ ከሆነ ቅሬታ ሊያድርብህ ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “አፍንጫን ሲያሹት እንደሚደማ፣ ቍጣን ማነሣሣትም ጥልን ይፈጥራል” ይላል። (ምሳሌ 30:33) አፍንጫ ሲታሽ እንደሚደማ ሁሉ ቂም ከያዝክም በቁጣ ልትገነፍል ትችላለህ። ይህ ደግሞ ችግሩን ከማባባስ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም። (ምሳሌ 26:21) ወንድምህ ወይም እህትህ አንተን የሚያበሳጭ ነገር ሲያደርጉ በቁጣ ላለመገንፈል ምን ማድረግ ትችላለህ? የመጀመሪያው እርምጃ የችግሩን ትክክለኛ መንስኤ ማወቅ ነው።

የተፈጠረው ሁኔታ ወይስ መንስኤው?

በወንድማማቾችና በእህትማማቾች መካከል የሚፈጠሩት ግጭቶች እንደ ብጉር ናቸው። ብጉር በቆዳችን ላይ የሚታይ ከውጭ ያለ ችግር ብቻ ሊመስል ይችላል፤ ይሁንና ከላይ የሚታየው ቁስል ከቆዳችን ሥር ኢንፌክሽን መፈጠሩን የሚጠቁም ምልክት ነው። በተመሳሳይም በወንድማማቾችና በእህትማማቾች መካከል የሚነሳ ጭቅጭቅ ብዙውን ጊዜ ከበስተ ጀርባ ሌላ ችግር መኖሩን የሚያመለክት ነው።

ብጉሩን በማፍረጥ ልታጠፋው ትሞክር ይሆናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ብታደርግ ለማስወገድ እየጣርክ ያለኸው ከላይ ያለውን ቁስል ይኸውም ከሥር ችግር መኖሩን የሚጠቁመውን ምልክት ብቻ ነው፤ ደግሞም እንዲህ ማድረግህ ቁስሉ ጠባሳ እንዲተው ሊያደርግ አልፎ ተርፎም ኢንፌክሽኑን ሊያባብሰው ይችላል። የተሻለ የሚሆነው ኢንፌክሽኑን በማከም ሌላ ብጉር እንዳይወጣ ብትከላከል ነው። ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አለመግባባት በሚኖርበት ጊዜ የችግሩን መንስኤ ለይተህ ለማወቅ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል፤ እንዲህ ካደረግህ በተፈጠረው ሁኔታ ላይ ሳይሆን በመንስኤው ላይ ማተኮር ትችላለህ። በተጨማሪም “ጥበብ ሰውን ታጋሽ ታደርገዋለች” የሚለውን የጠቢቡን ንጉሥ የሰለሞንን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ትችላለህ።—ምሳሌ 19:11

እስቲ ቀደም ሲል የተጠቀሰችውን አሊስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ አሊስ ስለ ወንድሟ ስለ ዴኒስ ስትናገር “ክፍሌን በርግዶ ይገባና ሳያስፈቅደኝ ዕቃዎቼን ይወስዳል” ብላ ነበር። አሊስ እንድትናደድ ያደረጋት ሁኔታ ይህ ነው። ሆኖም የችግሩ ትክክለኛ መንስኤ ምን ይመስልሃል? አክብሮት ከማሳየት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። አሊስ፣ ዴኒስን ክፍሏ ድርሽ እንዳይል ወይም ዕቃዋን ጨርሶ እንዳይነካ በማስጠንቀቅ ችግሩን ለማስወገድ ልትጥር ትችላለች። ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረግ በወቅቱ የተፈጠረውን ግጭት ይኸውም በመካከላቸው ችግር መኖሩን የሚጠቁመውን ምልክት ብቻ ለማስወገድ እንደ መሞከር ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ሌላ ግጭት ሊያስነሳ ይችላል። በሌላ በኩል ግን አሊስ መብቷን እንዲያከብርላትና ዕቃዋን ሳያስፈቅድ እንዳይነካ ዴኒስን ቀስ ብላ ብታሳምነው ግንኙነታቸው እንደሚሻሻል ጥርጥር የለውም።

አለመግባባቶችን መፍታት አሊያም ማስቀረት

እርግጥ ነው፣ ከወንድምህ ወይም ከእህትህ ጋር ለተፈጠሩት አለመግባባቶች መንስኤውን ለይተህ ስላወቅህ ብቻ ችግሮቹ ይፈታሉ ማለት አይደለም። ታዲያ የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታትና ወደፊትም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይከሰት ለማድረግ ምን እርምጃ መውሰድ ትችላለህ? የሚከተሉትን ስድስት እርምጃዎች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር።

1. መሠረታዊ ደንቦች አውጡ። በአንተና በወንድምህ ወይም በእህትህ መካከል ለተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ናቸው ብለህ ምልክት ያደረግህባቸውን በገጽ 41 ላይ የሚገኙትን ነጥቦች እስቲ መለስ ብለህ ተመልከት። ከዚያም የችግሩን ዋና መንስኤ ለማስወገድ የሚረዱ ሁላችሁም የምትስማሙባቸውን ደንቦች አውጡ። ለምሳሌ ያህል፣ የሚያጋጫችሁ አንዱ የሌላውን ንብረት የመንካቱ ጉዳይ ከሆነ ደንብ ቁጥር 1 “አንድ ሰው የሌላውን ሰው ንብረት ከመውሰዱ በፊት ሁልጊዜ ፈቃድ መጠየቅ አለበት” የሚል ሊሆን ይችላል። ደንብ ቁጥር 2 ደግሞ “አንድ ሰው ‘አይሆንም፣ ይህን ዕቃ አላውስህም’ ካለ መብቱ መከበር አለበት” የሚል ሊሆን ይችላል። እነዚህን ደንቦች ስታወጡ “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ ልታደርጉላቸው ይገባል” በማለት ኢየሱስ የሰጠውን ትእዛዝ አስታውሱ። (ማቴዎስ 7:12) ይህን ምክር ተግባራዊ ካደረጋችሁ አንተም ሆንክ ወንድምህ ወይም እህትህ ልታከብሯቸው የምትችሏቸውን ደንቦች ማውጣት ትችላላችሁ። ከዚያም ወላጆቻችሁ ባወጣችኋቸው ደንቦች ይስማሙ እንደሆነ ለማወቅ ከእነሱ ጋር ተነጋገሩ።—ኤፌሶን 6:1

2. አንተ ራስህ ደንቦቹን አክብር። ሐዋርያው ጳውሎስ “ታዲያ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርም? አንተ ‘አትስረቅ’ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህ?” በማለት ጽፏል። (ሮም 2:21) ይህን መመሪያ በሥራ ላይ ማዋል የምትችለው እንዴት ነው? አንድ ምሳሌ እንውሰድ፤ ወንድምህ ወይም እህትህ የአንተን መብት እንዲያከብሩ የምትፈልግ ከሆነ ወደ ክፍላቸው ከመግባትህ በፊት በሩን አንኳኳ እንዲሁም የኢ-ሜይል ወይም የጽሑፍ መልእክቶቻቸውን ሳታስፈቅድ አታንብብ።

3. ቶሎ ቅር አትሰኝ። ይህ ምክር ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንደሚገልጸው “ለቁጣ የሚቸኩሉትና ቂም የሚይዙት ሞኞች ብቻ” ናቸው። (መክብብ 7:9 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን) በቀላሉ የምትቀየም ከሆነ ደስታህን ታጣለህ። ወንድምህ ወይም እህትህ አንተን የሚያበሳጭ ነገር ማድረጋቸው የማይቀር ነው። ይሁን እንጂ ‘እኔስ ከዚህ በፊት አበሳጭቻቸው አላውቅም?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። (ማቴዎስ 7:1-5) ጄኒ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “የ13 ዓመት ልጅ ሳለሁ ሁሉንም ነገር እንደማውቅ ይሰማኝ ነበር። እኔ የምሰጠው ሐሳብ ከሁሉ የተሻለ እንደሆነና የእኔ ሐሳብ መሰማት እንዳለበት አድርጌ አስብ ነበር። ታናሽ እህቴ አሁን ያለችበት ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ በምትናገረው ነገር ላለመበሳጨት ጥረት አደርጋለሁ።”

4. ይቅር በል እንዲሁም ጉዳዩን እርሳው። የተፈጠረው አለመግባባት ከባድ ከሆነ ተወያይታችሁ ልትፈቱት ይገባል። ይህ ሲባል ግን ወንድምህ ወይም እህትህ ስህተት በሠሩ ቁጥር ቁጭ ብላችሁ መነጋገር አለባችሁ ማለት ነው? ይሖዋ አምላክ ‘በደልን ንቀህ ለመተው’ ፈቃደኛ ስትሆን ደስ ይለዋል። (ምሳሌ 19:11) የ19 ዓመቷ አሊሰን እንዲህ ብላለች፦ “እኔና እህቴ ሬቸል በመካከላችን የሚፈጠሩትን አለመግባባቶች ብዙውን ጊዜ ራሳችን እንፈታቸዋለን። ሁለታችንም ይቅርታ ለመጠየቅ አናንገራግርም፤ እንዲሁም ለተፈጠረው አለመግባባት መንስኤ ነው ብለን የምናስበውን ነገር በግልጽ እንነጋገራለን። አንዳንድ ጊዜ ስለ አንድ ችግር ወዲያውኑ ከማንሳት ይልቅ ስለ ጉዳዩ በነጋታው ለመወያየት እመርጣለሁ። ብዙውን ጊዜ በማግስቱ ሳስበው ጉዳዩ ቀላል እንደሆነ ይሰማኛል፤ ላነሳው እንኳ አልፈልግም።”

5. ወላጆቻችሁን እንዲያስታርቋችሁ ጠይቋቸው። አንተና ወንድምህ ወይም እህትህ በአንድ ከበድ ያለ ጉዳይ ላይ የተፈጠረን አለመግባባት መፍታት ካቃታችሁ ወላጆቻችሁ ሊያስታርቋችሁ ይችላሉ። (ሮም 14:19) ይሁንና ያለ ወላጆቻችሁ እርዳታ አለመግባባትን መፍታት መቻላችሁ እውነተኛ ብስለት እንዳላችሁ የሚጠቁም እንደሆነ አስታውስ።

6. የወንድምህን ወይም የእህትህን ጥሩ ባሕርያት አድንቅ። ወንድምህ ወይም እህትህ፣ የምታደንቅላቸው ባሕርይ እንደሚኖራቸው የታወቀ ነው። ወንድሞችህና እህቶችህ ካላቸው ባሕርያት መካከል የምታደንቅላቸውን ባሕርይ ጻፍ።

ስም

․․․․․

የማደንቀው ባሕርይ

․․․․․

በወንድምህ ወይም በእህትህ ደካማ ጎን ላይ ከማተኮር ይልቅ ያሏቸውን መልካም ባሕርያት እንደምታደንቅ ለምን አትነግራቸውም?—መዝሙር 130:3፤ ምሳሌ 15:23

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ወንድሞቻችን ወይም እህቶቻችን የቅርብ ጓደኛችን የሚሆኑት ሁልጊዜ ላይሆን ይችላል። (ምሳሌ 18:24) ይሁን እንጂ ወንድሞችህ ወይም እህቶችህ ‘ቅር የሚያሰኝህ’ ነገር ቢያደርጉም እንኳ ‘እርስ በርስ ለመቻቻል’ የምትጥር ከሆነ በመካከላችሁ ያለው ወዳጅነት እንዲጠናከር ማድረግ ትችላለህ። (ቆላስይስ 3:13) እንዲህ ካደረግህ ወንድሞችህና እህቶችህ የሚያደርጉት ነገር አንተን እምብዛም አያበሳጭህም። አንተም ብትሆን እነሱን ያን ያህል አታበሳጫቸውም!

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ራስህን ችለህ ለመኖር ዝግጁ መሆንህን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

ቁልፍ ጥቅስ

“ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን።”—ፊልጵስዩስ 4:5

ጠቃሚ ምክር

ከወንድምህ ወይም ከእህትህ ጋር መስማማት ከባድ ከሆነብህ ሁኔታውን አዎንታዊ በሆነ መንገድ ለማየት ሞክር፤ የወንድምህ ወይም የእህትህ ባሕርይ፣ ወደፊት የሚጠቅምህ ችሎታ እንድታዳብር ይረዳሃል!

ይህን ታውቅ ነበር?

ራስህን ችለህ መኖር ስትጀምር የሚያበሳጭ ባሕርይ ያላቸው ሰዎች ሊያጋጥሙህ ይችላሉ፤ ለምሳሌ ሥርዓት ከሌላቸው፣ ለሌሎች ከማያስቡ እና ራስ ወዳድ ከሆኑ ሰዎች ጋር በሥራ ቦታህ ወይም በሌሎች አጋጣሚዎች ልትገናኝ ትችላለህ። እንደዚህ ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማለፍን መማር የምትችለው ቤት እያለህ ነው።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ከወንድሞቼና ከእህቶቼ ጋር በጋራ ልናወጣቸው የምንችላቸው ደንቦች ․․․․․

ወንድሞቼን ወይም እህቶቼን ላለማበሳጨት እንዲህ ማድረግ እችላለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● በሚያበሳጩ ሁኔታዎችና እነዚህ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ባደረገው ዋና መንስኤ መካከል ያለውን ልዩነት ማወቁ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

● ወንድም ወይም እህት ያለህ መሆኑ ምን ጥቅም አለው?

[በገጽ 46 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ወንድምና እህት ባይኖረኝ ኖሮ አሁን ያሉኝ አስደሳች ትዝታዎች አይኖሩም ነበር። እንደ እኔ ወንድሞችና እህቶች ላሏቸው ሁሉ ልነግራቸው የምፈልገው ነገር እንዲህ ያለ አጋጣሚ በማግኘታቸው ሊደሰቱ እንደሚገባ ነው።”—ሜርሊን

[በገጽ 42 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የመልመጃ ሣጥን

የችግሩን ትክክለኛ መንስኤ ለይተህ እወቅ

በወንድማማቾችና በእህትማማቾች መካከል ለሚነሱ ጭቅጭቆች መንስኤ የሚሆኑትን ነገሮች ለይቶ የማወቅ ችሎታህን ማሻሻል ትፈልጋለህ? ከሆነ ኢየሱስ፣ ከቤተሰቡ ተለይቶ ስለሄደውና በውርስ ያገኘውን ሀብት ስላባከነው ልጅ የተናገረውን ምሳሌ አንብብ። (ሉቃስ 15:11-32) ታላቁ ልጅ፣ ታናሽ ወንድሙ ወደ ቤት ተመልሶ ሲመጣ ምን እንደተሰማው ልብ በል። ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦

ታላቁ ልጅ እንዲበሳጭ ያደረገው ሁኔታ ምን ይመስልሃል? ․․․․․

ታላቁ ልጅ እንዲህ እንዲሰማው ያደረገው ዋነኛው መንስኤ ምንድን ነው? ․․․․․

አባትየው ለችግሩ ዋነኛ መንስኤ መፍትሔ ለመስጠት የሞከረው እንዴት ነው? ․․․․․

ታላቁ ልጅ ለችግሩ መንስኤ ለሆነው ነገር መፍትሔ ለማግኘት ምን ማድረግ ነበረበት? ․․․․․

እስቲ አሁን ደግሞ በቅርቡ ከወንድምህ ወይም ከእህትህ ጋር ስለተጣላህበት ጉዳይ አስብከዚያም ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ስጥ።

ግጭቱ እንዲነሳ ያደረገው ሁኔታ ምንድን ነው? ․․․․․

የችግሩ ዋነኛ መንስኤ ምን ይመስልሃል? ․․․․․

የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታትና ወደፊትም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይከሰት ለማድረግ የሚረዷችሁ ምን ደንቦች ማውጣት ትችላላችሁ? ․․․․․

[በገጽ 43 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በወንድማማቾችና በእህትማማቾች መካከል የሚፈጠሩት ግጭቶች እንደ ብጉር ናቸው፤ መፍትሔው ከላይ የሚታየውን ምልክት ለማጥፋት መሞከር ሳይሆን የችግሩን መንስኤ ማስወገድ ነው