በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሞቼ ብገላገልስ?

ሞቼ ብገላገልስ?

ምዕራፍ 14

ሞቼ ብገላገልስ?

“ከምኖር መሞት ይሻለኛል።” ይህን የተናገረው ማን ይመስልሃል? በአምላክ የማያምን ወይም አምላክን የማያገለግል ሰው ይሆን? ወይስ አምላክ ያዘነበት ሰው? በፍጹም አይደለም። ይህን የተናገረው ታማኝ የአምላክ አገልጋይ የነበረው ዮናስ ነው፤ ዮናስ በወቅቱ በጣም ተበሳጭቶ ነበር።—ዮናስ 4:3

ዮናስ ይህን በተናገረበት ወቅት ሕይወቱን ሊያጠፋ አስቦ እንደነበር የሚገልጽ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አናገኝም። ያም ቢሆን ዮናስ በጣም ተስፋ ቆርጦ በነበረበት ወቅት የተናገረው ይህ ሐሳብ አንድ ሐቅ ያስገነዝበናል፦ የአምላክ አገልጋዮችም እንኳ አንዳንድ ጊዜ በከፍተኛ ጭንቀት ሊዋጡ ይችላሉ።—መዝሙር 34:19

አንዳንድ ወጣቶች በጣም ሲጨንቃቸው ወይም በሐዘን ሲዋጡ መኖር ያስጠላቸዋል። እነዚህ ወጣቶች የ16 ዓመቷ ሎራ የነበራት ዓይነት ስሜት ይኖራቸው ይሆናል፤ ሎራ እንዲህ ብላለች፦ “የመንፈስ ጭንቀት በተደጋጋሚ እያገረሸብኝ ለበርካታ ዓመታት አሠቃይቶኛል። ብዙ ጊዜ ራሴን ለማጥፋት አስባለሁ።” አንድ ሰው ራሱን የማጥፋት ሐሳብ እንዳለው ብታውቅ ወይም አንተ ራስህ እንዲህ የማድረግ ሐሳብ ቢመጣብህ ምን ማድረግ ትችላለህ? እስቲ በቅድሚያ እንዲህ ያለ ሐሳብ እንዲፈጠር የሚያደርገው ምን ሊሆን እንደሚችል እንመልከት።

ምክንያቱ ምንድን ነው?

አንድ ሰው ሕይወቱን ለማጥፋት እንዲያስብ የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል? በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። አንደኛ ነገር፣ የምንኖረው ‘ለመቋቋም በሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን’ ውስጥ ነው፤ በመሆኑም በርካታ ወጣቶች በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ተጽዕኖዎች መቋቋም ይከብዳቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ከዚህም ሌላ አንዳንድ ወጣቶች በራሳቸው ድክመቶችና የሰው ልጆች ፍጹም ባለመሆናቸው የተነሳ በዓለም ላይ በሚከሰቱት ነገሮች ከመጠን በላይ ስለሚጨነቁ ሁሉ ነገር ይጨልምባቸዋል። (ሮሜ 7:22-24) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ወጣቶች ራሳቸውን ለማጥፋት እንዲያስቡ የሚያደርጋቸው የደረሰባቸው በደል ወይም ጥቃት ይሆናል። የጤና ችግርም እንዲህ ዓይነት ሐሳብ እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። እንዲያውም በአንድ አገር ውስጥ በተደረገ ጥናት መሠረት ሕይወታቸውን ካጠፉት ሰዎች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአእምሮ ሕመም ይሠቃዩ የነበሩ ሰዎች እንደሆኑ ይገመታል። a

በእርግጥ ሁሉም ሰው መከራ ያጋጥመዋል። መጽሐፍ ቅዱስም “ፍጥረት ሁሉ . . . በአንድነት ሆኖ በመቃተትና አብሮ በመሠቃየት ላይ እንደሚገኝ” ይናገራል። (ሮም 8:22) ይህ ደግሞ ወጣቶችንም ይጨምራል። ከታች እንደተጠቀሱት ያሉ መጥፎ ሁኔታዎች በወጣቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ፦

የዘመድ ወይም የጓደኛ ሞት

በቤተሰብ መካከል የሚፈጠር ግጭት

መጥፎ የትምህርት ውጤት

ከፍቅረኛ ጋር መለያየት

በደል (አካላዊ ጥቃት ወይም በፆታ መነወር)

መቼም ይሁን መች ሁሉም ወጣቶች ከላይ ከተገለጹት ሁኔታዎች አንዳንዶቹ ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉ የታወቀ ነው። ታዲያ አንዳንድ ወጣቶች ከሌሎቹ በተሻለ እነዚህን ሁኔታዎች መቋቋም የሚችሉት ለምንድን ነው? ራሳቸውን ለማጥፋት የሚሞክሩ ወጣቶች እንዲህ የሚያደርጉት የሚረዳቸው እንደሌለና ያጋጠማቸው ችግር መፍትሔ እንደሌለው ስለሚሰማቸው እንደሆነ ምሁራን ይናገራሉ። በሌላ አባባል እነዚህ ወጣቶች ምንም የተስፋ ጭላንጭል አይታያቸውም። ወጣቶቹ ራሳቸውን ለማጥፋት የሚሞክሩት ከሥቃያቸው የሚገላገሉበት መንገድ ስላጡ እንጂ መሞት ፈልገው አይደለም።

መፍትሔ የለውም?

አንድ ሰው፣ በሕይወት በጣም ከመማረሩ የተነሳ ‘ሞቼ ብገላገልስ’ ብሎ እያሰበ እንደሆነ ብታውቅ ምን ማድረግ ትችላለህ?

አንድ ጓደኛህ መሞት እስኪመኝ ድረስ በጣም እንደተጨነቀ ካወቅህ እርዳታ ለማግኘት ጥረት እንዲያደርግ አበረታታው። ግለሰቡ ስለ ጉዳዩ ለማንም እንድትናገር ባይፈልግ እንኳ እምነት ለሚጣልበት አንድ ሰው ከመናገር ወደኋላ አትበል። ‘ጓደኝነታችን ይበላሻል’ ብለህ አትስጋ። ጉዳዩን ለሌሎች በመናገር የጓደኛህን ሕይወት ልታድን ትችል ይሆናል!

‘ሞቼ ብገላገልስ’ የሚል ሐሳብ ያለህ አንተ ራስህ ከሆንክስ? የሚሰማህን ነገር ከሌሎች አትደብቅ። ለወላጆችህ፣ ለጓደኛህ ወይም ስለ አንተ ለሚያስብና ያስጨነቀህን ነገር ትኩረት ሰጥቶ ለሚያዳምጥህ ሰው ተናገር። ችግርህን ለሌላ ሰው አውጥተህ መናገርህ ይጠቅምሃል እንጂ አይጎዳህም። b

እርግጥ ነው፣ የሚሰማህን መናገርህ ብቻ ችግሩን ያስወግደዋል ማለት አይደለም። ያም ሆኖ የምትተማመንበት ጓደኛህ የሚሰጥህ ድጋፍ ሁኔታውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንድትመለከተው ይረዳህ ይሆናል። አልፎ ተርፎም ለችግሩ መፍትሔ እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል።

ሁኔታዎች ይለወጣሉ

የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥምህ አንድ ነገር አስታውስ፦ ያለህበት ሁኔታ ምንም ተስፋ የሌለው ቢመስልም ውሎ አድሮ ነገሮች መለወጣቸው አይቀርም። በሕይወቱ በርካታ መከራዎች የተፈራረቁበት መዝሙራዊው ዳዊት በአንድ ወቅት ወደ አምላክ ሲጸልይ “ልቅሶዬን ለደስታ ለወጥህልኝ” ማለት ችሎ ነበር።—መዝሙር 30:11 የ1954 ትርጉም

በእርግጥ ዳዊት ሁልጊዜ ደስተኛ ሆኖ እንደሚኖር አልጠበቀም። በሕይወት ውስጥ ደስታና መከራ እንደሚፈራረቁ ከተሞክሮ ያውቅ ነበር። አንተስ ይህ እውነት መሆኑን በራስህ ሕይወት አስተውለሃል? አንዳንዶቹ ችግሮች ከአቅምህ በላይ እንደሆኑ ሊሰማህ ይችላል። ያም ቢሆን ታጋሽ መሆን ያስፈልጋል። አብዛኛውን ጊዜ ሁኔታዎች ይስተካከላሉ። አንዳንድ ጊዜ ችግሮቹ አንተ ጨርሶ ባልጠበቅኸው መንገድ ይቃለሉ ይሆናል። በሌላ ጊዜ ደግሞ ከዚህ በፊት ባላሰብከው አቅጣጫ ለችግሩ መፍትሔ ታገኝለት ይሆናል። ያም ሆነ ይህ የሚያስጨንቁህ ችግሮች ዕድሜ ልክ አብረውህ እንደማይኖሩ አስታውስ።—2 ቆሮንቶስ 4:17

ጸሎት ያለው ጥቅም

የሚሰማህን ለሌሎች አውጥተህ መናገርህ ጠቃሚ እንደሆነ አይካድም፤ በዚህ ረገድ ከሁሉ የበለጠ ጥቅም የምታገኘው ግን ወደ አምላክ በመጸለይ ነው። አንተም እንደ ዳዊት እንዲህ ብለህ መጸለይ ትችላለህ፦ “አምላክ ሆይ፣ በሚገባ መርምረኝ፤ ልቤንም እወቅ። ፈትነኝ፤ የሚያስጨንቁኝንም ሐሳቦች እወቅ፤ በውስጤ ጎጂ የሆነ ዝንባሌ ካለ እይ፤ በዘላለምም መንገድ ምራኝ።”—መዝሙር 139:23, 24 NW

ጸሎት ጭንቀትህን አውጥተህ በመናገር ጊዜያዊ እፎይታ የምታገኝበት መንገድ ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ‘ልብህን እንድታፈስለት’ ከሚፈልገው በሰማይ ካለው አባትህ ጋር የምትገናኝበት መንገድ ነው። (መዝሙር 62:8) እስቲ አምላክን በተመለከተ የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በል፦

ለጭንቀትህ አስተዋጽኦ ያደረጉትን ነገሮች በሚገባ ያውቃል።—መዝሙር 103:14

አንተ ራስህን ከምታውቀው በላይ ያውቅሃል።—1 ዮሐንስ 3:20

‘ስለ አንተ ያስባል።’—1 ጴጥሮስ 5:7

ወደፊት በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ “እንባን ሁሉ [ከዓይንህ] ላይ ይጠርጋል።”—ራእይ 21:4

የጤና ችግር ከሆነ

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ራስን የማጥፋት ሐሳብ የሚመጣው አብዛኛውን ጊዜ በጤና ችግር ምክንያት ነው። የአንተም ሁኔታ እንዲህ ከሆነ በዚህ ተሸማቅቀህ እርዳታ ከመፈለግ ወደኋላ አትበል። ኢየሱስ የታመሙ ሰዎች ሐኪም እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል። (ማቴዎስ 9:12) ደስ የሚለው ነገር፣ ለአብዛኞቹ የጤና እክሎች ሕክምና ማግኘት ይቻላል። አንተም የሕክምና እርዳታ ማግኘትህ ጤንነትህ እንዲሻሻል ሊያደርግ ይችላል! c

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ‘“ታምሜአለሁ” የሚል እንደማይኖር’ የሚገልጽ አስደሳች ተስፋ ይዟል። (ኢሳይያስ 33:24) አምላክ ስለዚያ ወቅት ሲናገር “ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤ አይታወሱም” ብሏል። (ኢሳይያስ 65:17) አምላክ በወሰነው ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት ሙሉ በሙሉ እንደሚወገድ በመተማመን ያ ጊዜ እስኪመጣ በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ።—ራእይ 21:1-4

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 9 ተመልከት

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ወላጆችህ እያንዳንዱን እንቅስቃሴህን ሌላው ቀርቶ እንዲያውቁት የማትፈልገውን ነገር እንኳ ለማወቅ ይሞክራሉ። ታዲያ ወላጆችህ በግል ሕይወትህ በምታደርጋቸው ነገሮች የተወሰነ ነፃነት እንዲሰጡህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a እርግጥ ነው፣ የአእምሮ ሕመም ካለባቸው ወጣቶች መካከል አብዛኞቹ ራሳቸውን እንደማያጠፉ ልብ ማለት ያስፈልጋል።

b በጭንቀት የተዋጡ ክርስቲያኖች ከጉባኤ ሽማግሌዎችም እርዳታ ማግኘት ይችላሉ።—ያዕቆብ 5:14, 15

c ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት ምዕራፍ 13⁠ን ተመልከት።

ቁልፍ ጥቅስ

“ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

ጠቃሚ ምክር

ጭንቅ ሲልህ ወይም በሐዘን ስትዋጥ ወጣ ብለህ ተንሸራሸር። ከቤት ወጣ ማለትና ስፖርት መሥራት እንድትረጋጋና ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ ያደርጋል።

ይህን ታውቅ ነበር?

ሕይወታቸውን የሚያጠፉ ሰዎች የሚጎዱት ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የሚወዷቸውን ሰዎች ጭምር ነው።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

የማልረባ እንደሆንኩ እንዲሁም ማንም እንደማይወደኝ ሲሰማኝ ስሜቴን አውጥቼ ልነግረው የምችለው ሰው ․․․․․

በሕይወቴ ውስጥ አመስጋኝ እንድሆን ከሚያነሳሱኝ ነገሮች አንዱ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● በጣም ከባድ የሚባሉት ችግሮች እንኳ ማለፋቸው አይቀርም። ይህን ማወቅህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

● አንድ ሰው ራሱን ሲያጠፋ ችግሩ ለሌሎች የሚተርፈው እንዴት ነው?

[በገጽ 104 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ተውጬ ሞትን የተመኘሁባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ አዘውትሬ በመጸለዬና የሕክምና እርዳታ በማግኘቴ አሁን ጤንነቴ ተመልሶልኛል።”—ሃይዲ

[በገጽ 100 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በከፍተኛ ጭንቀት ስትዋጥ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ታማኝ ሰዎች እንኳ በሕይወታቸው ውስጥ ባጋጠሟቸው ችግሮች የተነሳ በከፍተኛ ጭንቀት የተዋጡበት ጊዜ ነበር። እስቲ አንዳንዶቹ የተናገሩትን እንመልከት፦

ርብቃ፦ “መኖር አስጠልቶኛል፤ . . . ሞቴን እመርጣለሁ።”—ዘፍጥረት 27:46

ሙሴ፦ “አሁኑኑ ግደለኝ፤ የሚደርስብኝን ጥፋት አልይ።”—ዘኍልቍ 11:15

ኤልያስ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በቅቶኛል፤ እኔ ከቀደሙት አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰዳት።”—1 ነገሥት 19:4

ኢዮብ፦ “ምነው መቃብር ውስጥ በሰወርኸኝ! . . . ምነው ቀጠሮ ሰጥተህ፣ ከዚያ በኋላ ባስታወስኸኝ!”—ኢዮብ 14:13

ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም ሰዎች የነበሩበት ሁኔታ እነሱ ባልጠበቁት መንገድ ከጊዜ በኋላ ተሻሽሏል። አንተም ያለህበት ሁኔታ ሊሻሻል እንደሚችል እርግጠኛ መሆን ትችላለህ!

[በገጽ 102 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዝናብ እንዳዘለ ደመና የሐዘን ስሜትም ውሎ አድሮ ማለፉ አይቀርም