ምዕራፍ 12
‘ሌሎችን የሚያንጽ መልካም ቃል’ ተናገሩ
“ሌሎችን የሚያንጽ . . . መልካም ቃል ብቻ እንጂ የበሰበሰ ቃል ከቶ ከአፋችሁ አይውጣ።”—ኤፌሶን 4:29
1-3. (ሀ) ይሖዋ ከሰጠን መልካም ስጦታዎች አንዱ ምንድን ነው? ይህን ስጦታ አግባብ ባልሆነ መንገድ የምንጠቀምበት ምን ካደረግን ነው? (ለ) የመናገር ችሎታችንን እንዴት ልንጠቀምበት ይገባል?
አንድ አባት ለልጁ ብስክሌት ገዛለት እንበል። ይህ አባት ለልጁ እንዲህ ያለ ልዩ ስጦታ በመስጠቱ እንደሚደሰት የታወቀ ነው። ሆኖም ልጁ ብስክሌቱን በግዴለሽነት በመንዳት ሌላ ሰው ላይ ጉዳት ቢያደርስ አባትየው ምን የሚሰማው ይመስልሃል?
2 “መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ” የተገኘው ከይሖዋ ነው። (ያዕቆብ 1:17) ይሖዋ ከሰጠን መልካም ስጦታዎች አንዱ የመናገር ችሎታችን ነው። የመናገር ችሎታችን ሐሳባችንንና ስሜታችንን ለመግለጽ ያስችለናል። በዚህ ስጦታ ተጠቅመን ሌሎችን መርዳት እንዲሁም ደስ እንዲላቸው ማድረግ እንችላለን። በተቃራኒው ደግሞ፣ የምንናገረው ነገር ሌሎችን ሊጎዳና ስሜታቸውን ሊያቆስል ይችላል።
3 አንደበት ታላቅ ኃይል አለው፤ በመሆኑም ይሖዋ የመናገር ችሎታችንን እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንደምንችል ያስተምረናል። “እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎቹን ሊጠቅም የሚችል መልካም ቃል ብቻ እንጂ የበሰበሰ ቃል ከቶ ከአፋችሁ አይውጣ” ብሎናል። (ኤፌሶን 4:29) ከአምላክ ያገኘነውን ይህን ስጦታ እሱን በሚያስደስትና ሌሎችን በሚያበረታታ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
አንደበታችሁን በጥንቃቄ ተጠቀሙበት
4, 5. በምሳሌ መጽሐፍ ላይ የሚገኙት ሐሳቦች አንደበት ያለውን ኃይል በተመለከተ ምን ያስተምሩናል?
4 አንደበት ኃይል አለው፤ በመሆኑም የምንናገረውን ነገርም ሆነ የምንናገርበትን መንገድ በተመለከተ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። ምሳሌ 15:4 “የረጋ አንደበት የሕይወት ዛፍ ነው፤ ጠማማ ንግግር ግን ተስፋ ያስቆርጣል” ይላል። አንድ የሚያምር ዛፍ መንፈስን እንደሚያድስና ለሕይወት ጠቃሚ እንደሆነ ሁሉ ደግነት የተንጸባረቀበት ንግግርም መንፈስን ያድሳል። በሌላ በኩል ግን ደግነት የጎደለው ንግግር ሌሎችን ሊጎዳና ሊያስቀይም ይችላል።—ምሳሌ 18:21
5 ምሳሌ 12:18 “ሳይታሰብበት የሚነገር ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል” ይላል። ደግነት የጎደለው ንግግር ስሜትን ይጎዳል እንዲሁም በሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር ያደርጋል። ምናልባት አንተም አንድ ሰው በተናገረህ የሚያስከፋ ነገር ስሜትህ በጣም የተጎዳበትን ጊዜ ታስታውስ ይሆናል። ምሳሌ 12:18 “የጥበበኞች ምላስ ግን ፈውስ ነው” ይላል። አሳቢነት የሚንጸባረቅበት ንግግር ያዘነ ልብን ያጽናናል፤ እንዲሁም የሻከረ ግንኙነትን ለማደስ ያስችላል። (ምሳሌ 16:24ን አንብብ።) አንደበታችን ሌሎችን ደስ ሊያሰኝ አሊያም ሊጎዳ እንደሚችል ካስታወስን ስንናገር ጥንቃቄ እናደርጋለን።
6. አንደበታችንን መቆጣጠር ከፍተኛ ትግል የሚጠይቅብን ለምንድን ነው?
6 አንደበታችንን በጥንቃቄ እንድንጠቀም የሚያነሳሳን ሌላው ምክንያት ደግሞ ሁላችንም ፍጹማን አለመሆናችን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው የልብ ዝንባሌ . . . መጥፎ ነው” ይላል፤ ደግሞም አብዛኛውን ጊዜ የምንናገረው በልባችን ውስጥ የሞላውን ነው። (ዘፍጥረት 8:21፤ ሉቃስ 6:45) እርግጥ አንደበታችንን መቆጣጠር ከፍተኛ ትግል ሊጠይቅብን ይችላል። (ያዕቆብ 3:2-4ን አንብብ።) ያም ቢሆን ሌሎችን በምናነጋግርበት መንገድ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ሁልጊዜ መጣር አለብን።
7, 8. የምንናገረው ነገር ከይሖዋ ጋር ባለን ዝምድና ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?
7 የምንናገረውን ነገርም ሆነ የምንናገርበትን መንገድ በተመለከተ በይሖዋ ፊት ተጠያቂ እንደሆንን ማወቃችንም አንደበታችንን በጥንቃቄ እንድንጠቀም ያነሳሳናል። ያዕቆብ 1:26 “አንድ ሰው አምላክን እያመለከ እንዳለ ቢያስብም እንኳ አንደበቱን የማይገታ ከሆነ ይህ ሰው የገዛ ልቡን ያታልላል፤ አምልኮውም ከንቱ ነው” ይላል። እንግዲያው አንደበታችንን በጥንቃቄ ካልተጠቀምንበት ከይሖዋ ጋር ያለን ግንኙነት ሊሻክር ይባስ ብሎም ሊበላሽ ይችላል።—ያዕቆብ 3:8-10
8 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የምንናገረውን ነገርም ሆነ የምንናገርበትን መንገድ በተመለከተ ጥንቃቄ እንድናደርግ የሚገፋፉን ብዙ ምክንያቶች አሉ። ከይሖዋ ያገኘነውን የመናገር ችሎታ እሱ በሚፈልገው መንገድ መጠቀም እንድንችል፣ ከአነጋገራችን ጋር በተያያዘ አምላክ የሚጠላቸውን ነገሮች ማወቅ ያስፈልገናል።
ጎጂ ንግግር
9, 10. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ምን ዓይነት ንግግር በጣም የተለመደ ሆኗል? (ለ) ጸያፍ ንግግርን ማስወገድ ያለብን ለምንድን ነው?
9 ጸያፍ ወይም አሳፋሪ ንግግር በዛሬው ጊዜ በጣም የተለመደ ነገር ነው። ብዙዎች ካልተሳደቡ ወይም የብልግና ቃላት ካልተጠቀሙ ሐሳባቸውን ማስተላለፍ የሚችሉ አይመስላቸውም። ቀልድ የሚናገሩ ሰዎች፣ ሌሎችን ለማሳቅ ብዙውን ጊዜ የብልግና ቀልዶችን ወይም አስጸያፊ የሆኑ ቃላትን ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ “ቁጣን፣ ንዴትን፣ ክፋትንና ስድብን ሁሉ ከእናንተ አስወግዱ፤ ጸያፍ ንግግርም ከአፋችሁ አይውጣ” ሲል ተናግሯል። (ቆላስይስ 3:8) በተጨማሪም ‘ጸያፍ ቀልድ በመካከላችሁ ከቶ አይነሳ’ በማለት እውነተኛ ክርስቲያኖችን መክሯል።—ኤፌሶን 5:3, 4
10 ጸያፍ ንግግር ይሖዋንም ሆነ እሱን የሚወዱ ሰዎችን ያሳዝናል። ይሖዋ ጸያፍ ንግግርን እንደ ርኩሰት ይቆጥረዋል። “ርኩሰት” ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ከሥጋ ሥራዎች’ መካከል ተመድቧል። (ገላትያ 5:19-21) “ርኩሰት” የሚለው ቃል የተለያዩ የኃጢአት ድርጊቶችን ያካትታል፤ አንድ ርኩስ ልማድ ወደ ሌላ ርኩስ ልማድ መምራቱ አይቀርም። አንድ ሰው ርኩሰት የሚንጸባረቅበት ይባስ ብሎም በጣም አስጸያፊ የሆነ ነገር መናገር ልማድ ከሆነበትና አካሄዱን ለማስተካከል ፈቃደኛ ካልሆነ የክርስቲያን ጉባኤ አባል ሆኖ መቀጠል አይችልም።—2 ቆሮንቶስ 12:21፤ ኤፌሶን 4:19፤ ተጨማሪ ሐሳብ 23ን ተመልከት።
11, 12. (ሀ) ስለ ሌሎች የምናወራው ነገር ወደ ሐሜት ሊቀየር የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ስም ከማጥፋት መቆጠብ ያለብን ለምንድን ነው?
11 ልንርቀው የሚገባው ሌላው ነገር ሐሜት ነው። ስለ ሌሎች ለማወቅ መፈለግ ያለ ነገር ነው፤ ስለ ቤተሰባችንና ስለ ወዳጆቻችን ማውራትም ምንም ስህተት የለውም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችም እንኳ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ስላሉበት ሁኔታ መስማት እንዲሁም እነሱን እንዴት መርዳት እንደሚችሉ ማወቅ ፈልገው ነበር። (ኤፌሶን 6:21, 22፤ ቆላስይስ 4:8, 9) ሆኖም ስለ ሌሎች የምናደርገው ጭውውት ሳናስበው ወደ ሐሜት ሊቀየር ይችላል። የሰማነውን ሐሜት ለሌሎች የምናወራ ከሆነ ደግሞ እውነት ያልሆነ ነገር ልንናገር አሊያም በሚስጥር መያዝ ያለበትን ነገር ልናወጣ እንችላለን። ጥንቃቄ ካላደረግን እንዲህ ያለው አሉታዊ ወሬ የሌሎችን ስም ወደ ማጥፋት ሊመራን ይችላል። ፈሪሳውያን ኢየሱስን ባላደረገው ነገር ሲከስሱት ስሙን አጥፍተዋል። (ማቴዎስ 9:32-34፤ 12:22-24) እንዲህ ያለው ወሬ የአንድን ሰው መልካም ስም ያጎድፋል፣ ውዝግብ ይፈጥራል፣ ወዳጅነትን ያበላሻል እንዲሁም ለሐዘን ይዳርጋል።—ምሳሌ 26:20
12 ይሖዋ አንደበታችንን ሌሎችን ለመርዳትና ለማበረታታት እንጂ በወዳጆች መካከል ጠብ ለመፍጠር እንድንጠቀምበት አይፈልግም። ይሖዋ “በወንድማማቾች መካከል ጠብ [የሚዘሩ]” ሰዎችን ይጠላል። (ምሳሌ 6:16-19) የመጀመሪያው ስም አጥፊ ሰይጣን ዲያብሎስ ሲሆን እሱም የአምላክን ስም አጥፍቷል። (ራእይ 12:9, 10) በዛሬው ጊዜ ስለ ሌሎች ውሸት መናገር የተለመደ ነው። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ግን እንዲህ ያለው ድርጊት ጨርሶ ቦታ የለውም። (ገላትያ 5:19-21) እንግዲያው ስለምንናገረው ነገር መጠንቀቅ እንዲሁም ምንጊዜም ከመናገራችን በፊት ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል። ስለ አንድ ሰው የሰማኸውን ወሬ ለሌሎች ከመናገርህ በፊት የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራስህን ጠይቅ፦ ‘ልናገር ያሰብኩት ነገር እውነት ነው? ለሌላ ሰው ባወራው ደግነት ይሆናል? ይህን ማውራቱስ ጠቃሚ ነው? ግለሰቡ ስለ እሱ የማወራውን ቢሰማ ምን ይላል? ሌላ ሰው ስለ እኔ እንዲህ ያለ ነገር ቢያወራ ምን ይሰማኛል?’—1 ተሰሎንቄ 4:11ን አንብብ።
13, 14. (ሀ) ስድብ ምን ጉዳት ያስከትላል? (ለ) ክርስቲያኖች መሳደብ ልማድ እንዳይሆንባቸው መጠንቀቅ ያለባቸው ለምንድን ነው?
13 ሁላችንም ብንሆን በኋላ ላይ የምንጸጸትበትን ነገር ልንናገር እንችላለን። ይሁን እንጂ ሌሎችን መንቀፍ ወይም ደግነት የጎደለውና ስሜት የሚጎዳ ነገር መናገር ልማድ እንዲሆንብን አንፈልግም። ክርስቲያኖች በፍጹም መሳደብ የለባቸውም። ጳውሎስ “የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ . . . ከእናንተ መካከል ይወገድ” ብሏል። (ኤፌሶን 4:31) አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ስድብ” የሚለውን ቃል “ክፉ ቃላት” እና “ጎጂ ንግግር” ሲሉ ተርጉመውታል። ስድብ፣ ሌሎችን የሚያዋርድ ከመሆኑም ሌላ ዋጋ እንደሌላቸው እንዲሰማቸው ያደርጋል። በተለይ ልጆች ስሜታቸው በቀላሉ ይጎዳል፤ በመሆኑም የምንናገራቸው ቃላት እንዳይጎዷቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል።—ቆላስይስ 3:21
14 መጽሐፍ ቅዱስ ተሳዳቢነትን ይኸውም ሌሎችን የሚያዋርዱና የሚያቃልሉ ቃላት የመናገር ልማድን አጥብቆ ያወግዛል። አንዳንዶች የትዳር ጓደኛቸውን ወይም ልጆቻቸውን የመሳደብ ልማድ ያላቸው መሆኑ ምንኛ የሚያሳዝን ነው! በመሠረቱ አንድ ሰው እንዲህ ዓይነት ልማድ ካለው የጉባኤው አባል ሆኖ መቀጠል አይችልም። (1 ቆሮንቶስ 5:11-13፤ 6:9, 10) እስካሁን እንደተመለከትነው ጸያፍ ወይም ደግነት የጎደለው ንግግር እንዲሁም ውሸት፣ ከይሖዋና ከሌሎች ጋር ያለንን ዝምድና ያበላሹብናል።
ሌሎችን የሚያንጽ ንግግር
15. ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያጠናክረው ምን ዓይነት ንግግር ነው?
15 የመናገር ችሎታችንን ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ምን መናገር እንዳለብን ወይም እንደሌለብን በዝርዝር ባይገልጽም “ሌሎችን የሚያንጽ . . . መልካም ቃል ብቻ” እንድንናገር ይመክረናል። (ኤፌሶን 4:29) የሚያንጽ ንግግር ንጹሕ፣ እውነት የሆነና ደግነት የሚንጸባረቅበት ነው። ይሖዋ አንደበታችንን ሌሎችን ለማበረታታትና ለመርዳት እንድንጠቀምበት ይፈልጋል። እርግጥ ይህን ማድረግ ቀላል ላይሆን ይችላል። ምክንያቱም ሰዎች ስንባል ደግነትና አሳቢነት የጎደለው ነገር መናገር ይቀናናል፤ መልካም ነገር መናገር ግን የበለጠ ጥረት ይጠይቅብናል። (ቲቶ ) በንግግራችን ሌሎችን ማነጽ የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመልከት። 2:8
16, 17. (ሀ) ሌሎችን ማመስገን ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) እነማንን ማመስገን እንችላለን?
16 ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ ሌሎችን በማመስገን ረገድ ግሩም ምሳሌ ናቸው። እኛም የእነሱን ምሳሌ መከተል እንፈልጋለን። (ማቴዎስ 3:17፤ 25:19-23፤ ዮሐንስ 1:47) አንድን ሰው በሚያበረታታ መንገድ ለማመስገን፣ ስለ ግለሰቡ ማሰብ እንዲሁም ለእሱ ትኩረት መስጠት ያስፈልገናል። ምሳሌ 15:23 “በትክክለኛው ጊዜ የተነገረ [ቃል] ምንኛ መልካም ነው!” ይላል። በትጋት ላከናወንነው ሥራ አንድ ሰው ከልቡ ሲያመሰግነን ወይም አድናቆቱን ሲገልጽልን በጣም እንደምንበረታታ የታወቀ ነው።—ማቴዎስ 7:12ን አንብብ፤ ተጨማሪ ሐሳብ 27ን ተመልከት።
17 የሌሎችን መልካም ጎን የመመልከት ልማድ ካዳበርን እነሱን ከልብ ማመስገን ቀላል ይሆንልናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የጉባኤያችሁ አባል የሚያቀርባቸውን ክፍሎች ጥሩ አድርጎ እንደሚዘጋጅ ወይም በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ለመስጠት ጥረት እንደሚያደርግ ተመልክተህ ይሆናል። አንድ ወጣት በትምህርት ቤት እምነቱን ደግፎ እንደሚቆም ሰምተህ አሊያም በዕድሜ የገፉ አንድ ክርስቲያን በአገልግሎት አዘውትረው እንደሚካፈሉ አስተውለህ ሊሆን ይችላል። ለእነዚህ ሰዎች አድናቆትህን መግለጽህ በእጅጉ ይጠቅማቸዋል። በተጨማሪም አንድ ባል፣ እንደሚወዳትና እንደሚያደንቃት ለባለቤቱ መንገሩ በጣም አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 31:10, 28) ተክሎች የፀሐይ ብርሃንና ውኃ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ ሰዎችም ሌሎች እንደሚያደንቋቸው ማወቅ ይፈልጋሉ። በተለይ ልጆች የሌሎችን አድናቆት ይሻሉ። ስለዚህ መልካም ባሕርያቸውንና የሚያደርጉትን ጥረት እንደምታደንቅ ንገራቸው። ልጆች፣ ሌሎች እንደሚያደንቋቸው ሲያውቁ በራሳቸው ይበልጥ ይተማመናሉ፣ ድፍረት ይኖራቸዋል እንዲሁም መልካም የሆነውን ለማድረግ የበለጠ ይነሳሳሉ።
18, 19. ወንድሞቻችንን ለማበረታታትና ለማጽናናት የምንችለውን ያህል ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?
18 ሌሎችን የምናበረታታና የምናጽናና ከሆነ የይሖዋን ምሳሌ እንከተላለን። ይሖዋ ‘መንፈሳቸው ለተደቆሰ’ እና ‘የተሰበረ ልብ ላላቸው’ በጥልቅ ያስባል። (ኢሳይያስ 57:15) ይሖዋ ‘እርስ በርስ እንድንበረታታ’ እንዲሁም ‘የተጨነቁትን እንድናጽናና’ ይፈልጋል። (1 ተሰሎንቄ 5:11, 14) ይህን ስናደርግ ይሖዋ የሚያስተውል ከመሆኑም ሌላ ጥረታችንን ያደንቃል።
19 አንድ የጉባኤያችሁ አባል ተስፋ እንደቆረጠ ወይም በመንፈስ ጭንቀት እንደተዋጠ ታስተውሉ ይሆናል። ግለሰቡን ለማጽናናት ምን ማለት ትችላላችሁ? ግለሰቡ ያጋጠመውን ችግር መፍታት ባትችሉም እንኳ እንደምታስቡለት እንዲያውቅ ማድረግ ትችላላችሁ። ለምሳሌ፣ ከእሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ትችሉ ይሆናል። የሚያበረታታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ልታነቡለት አልፎ ተርፎም አብራችሁ ልትጸልዩ ትችላላችሁ። (መዝሙር 34:18፤ ማቴዎስ 10:29-31) ተስፋ የቆረጡ ወንድሞችና እህቶችን፣ የጉባኤያቸው አባላት እንደሚወዷቸው ንገሯቸው። (1 ቆሮንቶስ 12:12-26፤ ያዕቆብ 5:14, 15) በተጨማሪም ከልብ በመነጨ ስሜት አነጋግሯቸው።—ምሳሌ 12:25ን አንብብ።
20, 21. ለመቀበል የማይከብድ ምክር መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
20 ሌሎችን ማነጽ የምንችልበት ሌላው መንገድ ጥሩ ምክር መስጠት ነው። ሁላችንም ፍጹማን ባለመሆናችን አልፎ አልፎ ምክር ያስፈልገናል። ምሳሌ 19:20 “የኋላ ኋላ ጥበበኛ እንድትሆን ምክርን ስማ፤ ተግሣጽንም ተቀበል” ይላል። ለሌሎች ምክር መስጠት የሚችሉት የጉባኤ ሽማግሌዎች ብቻ አይደሉም። ወላጆች ለልጆቻቸው መመሪያ መስጠት ይጠበቅባቸዋል። (ኤፌሶን 6:4) እህቶችም ቢሆኑ አንዳቸው ለሌላው ግሩም ምክር መስጠት ይችላሉ። (ቲቶ 2:3-5) ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ስለምንወዳቸው፣ የምንሰጣቸው ምክር ቅር እንዲያሰኛቸው አንፈልግም። ይሁንና ቅር በማያሰኝ መንገድ ምክር መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
21 አንድ ሰው ግሩም የሆነ ምክር ሰጥቶህ ያውቅ ይሆናል፤ ምክሩ ለመቀበል የሚከብድ አልነበረም። ሆኖም ምክሩ ውጤታማ እንዲሆን ያደረገው ምን ነበር? ግለሰቡ ስለ አንተ ከልብ እንደሚያስብ ተሰምቶህ ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ ምክሩን የሰጠህ ደግነትና ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ይሆናል። (ቆላስይስ 4:6) በተጨማሪም ምክሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) እኛም ምክር ስንሰጥ በቀጥታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ጠቀስንም አልጠቀስን፣ የምንሰጠው ምክር ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያለው ሊሆን ይገባል። ማንም ሰው ሌሎች የግል አመለካከቱን እንዲቀበሉ መጫን አሊያም የራሱን ሐሳብ ለመደገፍ ሲል ጥቅሶችን በተሳሳተ መንገድ መጥቀስ የለበትም። ከዚህ በፊት ምክር የሰጠን ሰው ያደረጋቸውን ነገሮች ማስታወሳችን ለሌሎች ምክር በምንሰጥበት ጊዜ ይጠቅመናል።
22. የመናገር ችሎታህን እንዴት ልትጠቀምበት ትፈልጋለህ?
22 የመናገር ችሎታችን ከአምላክ ያገኘነው ስጦታ ነው። ለአምላክ ያለን ፍቅር ይህን ስጦታ በአግባቡ እንድንጠቀምበት ሊያነሳሳን ይገባል። ቃላት ሌሎችን የመጉዳት አሊያም የማነጽ ኃይል አላቸው። እንግዲያው አንደበታችንን ሌሎችን በሚያበረታታና በሚያንጽ መንገድ ለመጠቀም የምንችለውን ሁሉ እናድርግ።