ምዕራፍ 5
ከዓለም የተለየን መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
‘የዓለም ክፍል አይደላችሁም።’—ዮሐንስ 15:19
1. ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ስለ የትኛው ጉዳይ ተናግሯል?
ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት፣ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የሚለያይበት ጊዜ እንደቀረበ ስላወቀ የተከታዮቹ ጉዳይ አሳስቦት ነበር። በዚያ ምሽት፣ ተከታዮቹን ‘የዓለም ክፍል አይደላችሁም’ ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 15:19) ከዚያም እነሱን በተመለከተ ወደ አባቱ ሲጸልይ “እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም” ብሏል። (ዮሐንስ 17:15, 16) ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር?
2. ኢየሱስ “ዓለም” ሲል ምንን ማመልከቱ ነበር?
2 ኢየሱስ “ዓለም” ሲል አምላክን የማያገለግሉና በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያሉ ሰዎችን ማመልከቱ ነበር። (ዮሐንስ 14:30፤ ኤፌሶን 2:2፤ ያዕቆብ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ታዲያ “የዓለም ክፍል” እንዳልሆንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምንችልባቸውን የተለያዩ መንገዶች በዚህ ምዕራፍ ውስጥ እንመለከታለን፦ ለአምላክ መንግሥት ታማኝ እንሆናለን እንዲሁም በፖለቲካዊ ጉዳዮች የትኛውንም ወገን ባለመደገፍ የገለልተኝነት አቋማችንን እንጠብቃለን። የዓለምን መንፈስ እንቋቋማለን። በአለባበሳችንና በአጋጌጣችን ልከኛ እንሆናለን። ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት እንይዛለን። በተጨማሪም አምላክ ያዘጋጀልንን የጦር ትጥቅ እንለብሳለን።—ተጨማሪ ሐሳብ 16ን ተመልከት።
የአምላክን መንግሥት በታማኝነት መደገፍ
3. ኢየሱስ ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ምን አቋም ነበረው?
3 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት፣ ሕዝቡ በርካታ ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸውና አስቸጋሪ ሕይወት እንደሚመሩ አስተውሎ ነበር። ኢየሱስ ለእነዚህ ሰዎች ከልቡ ያስብላቸውና ሊረዳቸው ይፈልግ ነበር። ታዲያ ኢየሱስ እነሱን ለመርዳት ሲል የፖለቲካ መሪ ሆኗል? በፍጹም። የሰዎቹን ችግር ሙሉ በሙሉ ሊፈታ የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ያውቅ ነበር። የዚህ መንግሥት ንጉሥ ኢየሱስ ነው፤ ኢየሱስ በዋነኝነት የሰበከውም ስለዚህ መንግሥት ነው። (ዳንኤል 7:13, 14፤ ሉቃስ 4:43፤ 17:20, 21) ኢየሱስ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ከመግባት ይልቅ ምንጊዜም ገለልተኛ ነበር። በሮማዊው አገረ ገዢ በጳንጥዮስ ጲላጦስ ፊት በቀረበበት ወቅት “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 18:36) ደቀ መዛሙርቱም ቢሆኑ የገለልተኝነት አቋም ይዘው ነበር። ወደ ሥልጣኔ በሚወስደው ጎዳና ላይ (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች “የፖለቲካ ሥልጣን አይዙም ነበር” ይላል። በዛሬው ጊዜ የምንኖር እውነተኛ ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ አቋም አለን። የአምላክን መንግሥት በታማኝነት እንደግፋለን፤ እንዲሁም ከዚህ ዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የገለልተኝነት አቋማችንን እንጠብቃለን።—ማቴዎስ 24:14
4. እውነተኛ ክርስቲያኖች የአምላክን መንግሥት እንደሚደግፉ የሚያሳዩት እንዴት ነው?
4 አምባሳደሮች፣ አገራቸውን ወክለው በሌላ አገር የሚሠሩ ሰዎች ናቸው፤ በመሆኑም ለሥራ በተመደቡበት አገር የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ አይገቡም። ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የመግዛት ተስፋ ያላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። ጳውሎስ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ሲጽፍ “እኛ ክርስቶስን ተክተን የምንሠራ አምባሳደሮች ነን” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 5:20) ቅቡዓን ክርስቲያኖች የአምላክ መንግሥት ተወካዮች ናቸው። በመሆኑም በዚህ ዓለም ፖለቲካዊም ሆነ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ አይገቡም። (ፊልጵስዩስ 3:20) ከዚህ ይልቅ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት እንዲማሩ እየረዱ ነው። አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው “ሌሎች በጎች” ደግሞ ቅቡዓኑን ይደግፋሉ። እነሱም ቢሆኑ የገለልተኝነት አቋም ይይዛሉ። (ዮሐንስ 10:16፤ ማቴዎስ 25:31-40) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ በዚህ ዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ አይገቡም።—ኢሳይያስ 2:2-4ን አንብብ።
5. ክርስቲያኖች በጦርነት የማይካፈሉበት አንዱ ምክንያት ምንድን ነው?
5 እውነተኛ ክርስቲያኖች ሁሉንም የእምነት ባልንጀሮቻቸውን የሚመለከቱት እንደ ቤተሰባቸው አድርገው ነው፤ ዜግነታቸው ወይም አስተዳደጋቸውና ባሕላቸው ምንም ይሁን ምን ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር አንድነት አላቸው። (1 ቆሮንቶስ 1:10) በመሆኑም ለጦርነት ቢዘምቱ የሚዋጉት ከራሳቸው ቤተሰብ ጋር ይሆናል ማለት ነው። ኢየሱስ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን እንዲወዱ ክርስቲያኖችን አዟቸዋል። (ዮሐንስ 13:34, 35፤ 1 ዮሐንስ 3:10-12) እንዲያውም ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ጠላቶቻቸውንም ጭምር መውደድ እንዳለባቸው ተናግሯል።—ማቴዎስ 5:44፤ 26:52
6. ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ክርስቲያኖች ለመንግሥታት ምን አመለካከት አላቸው?
6 ክርስቲያኖች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኛ ብንሆንም በምንኖርበት አገር ውስጥ ጥሩ ዜጎች ለመሆን ጥረት እናደርጋለን። ለምሳሌ ያህል፣ መንግሥት ያወጣቸውን ሕጎች በመታዘዝና የተጣለብንን ግብር በመክፈል መንግሥትን እንደምናከብር እናሳያለን። ይሁንና ምንጊዜም ቢሆን ‘የአምላክ የሆነውን ለአምላክ እንሰጣለን።’ (ማርቆስ 12:17፤ ሮም 13:1-7፤ 1 ቆሮንቶስ 6:19, 20) “የአምላክ የሆነውን” ለአምላክ መስጠት ሲባል እሱን መውደድን፣ መታዘዝን እንዲሁም ማምለክን ያካትታል። የይሖዋን ሕግ ከምንጥስ ይልቅ ሕይወታችንን ብናጣ እንመርጣለን።—ሉቃስ 4:8፤ 10:27፤ የሐዋርያት ሥራ 5:29ን እና ሮም 14:8ን አንብብ።
“የዓለምን መንፈስ” መቋቋም
7, 8. ‘የዓለም መንፈስ’ ምንድን ነው? በሰዎች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?
7 ከሰይጣን ዓለም የተለየን መሆን ከፈለግን ‘የዓለም መንፈስ’ እንዳይቆጣጠረን መጠንቀቅ አለብን። የዓለም መንፈስ የሚለው አገላለጽ ሰይጣን፣ ሰዎች እንዲኖራቸው የሚፈልገውን አስተሳሰብና አኗኗር ያመለክታል፤ ይህ መንፈስ ይሖዋን የማያገለግሉ ሰዎችን ይቆጣጠራል። ክርስቲያኖች ግን ይህን መንፈስ ለመቋቋም ጥረት ያደርጋሉ። ጳውሎስ “ከአምላክ የሆነውን መንፈስ ተቀበልን እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም” ብሏል።—1 ቆሮንቶስ 2:12፤ ኤፌሶን 2:2, 3፤ ተጨማሪ ሐሳብ 17ን ተመልከት።
8 የዓለም መንፈስ ራስ ወዳድ፣ ኩሩና ዓመፀኛ እንዲሆኑ ሰዎችን ይገፋፋል። አምላክን መታዘዝ እንደሌለባቸው እንዲያስቡም ያደርጋቸዋል። ሰይጣን፣ ሰዎች ድርጊታቸው ስለሚያስከትለው ውጤት ሳያስቡ የተመኙትን ሁሉ እንዲያደርጉ ይፈልጋል። በሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ‘የሥጋ ምኞትንና የዓይን አምሮትን’ ማርካት እንደሆነ እንዲያስቡም ይፈልጋል። (1 ዮሐንስ 2:16፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ዲያብሎስ የይሖዋን አገልጋዮች ለማታለልና የእሱን ዓይነት አስተሳሰብ እንዲያዳብሩ ለማድረግ ደግሞ የተለየ ጥረት ያደርጋል።—ዮሐንስ 8:44፤ የሐዋርያት ሥራ 13:10፤ 1 ዮሐንስ 3:8
9. የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን የሚችለው እንዴት ነው?
9 የዓለም መንፈስ፣ ልክ እንደምንተነፍሰው አየር በሁሉም ቦታ ይገኛል። የዓለምን መንፈስ ለመቋቋም ከፍተኛ ጥንቃቄ ካላደረግን ይህ መንፈስ ተጽዕኖ ያሳድርብናል። (ምሳሌ 4:23ን አንብብ።) ተጽዕኖው ቀላል በሚመስሉ ነገሮች ሊጀምር ይችላል፤ ለምሳሌ ይሖዋን የማያመልኩ ሰዎችን አስተሳሰብና ዝንባሌ መኮረጅ እንጀምር ይሆናል። (ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33) አሊያም ደግሞ ክህደት፣ የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ወይም ከፍተኛ ፉክክር የሚታይባቸው ስፖርቶች የዓለምን መንፈስ እንድናንጸባርቅ ሊያደርጉን ይችላሉ።—ተጨማሪ ሐሳብ 18ን ተመልከት።
10. የዓለምን መንፈስ መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
10 የዓለም መንፈስ እንዳይቆጣጠረን ምን ማድረግ እንችላለን? ምንጊዜም ከይሖዋ ጋር መቀራረብና በአምላካዊ ጥበብ መመራት ይኖርብናል። ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን አዘውትረን መጸለይ እንዲሁም ለእሱ በምናቀርበው አገልግሎት መጠመድ ያስፈልገናል። ይሖዋ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከማንም የበለጠ ኃይል አለው። በመሆኑም የዓለምን መንፈስ ለመቋቋም እንደሚረዳን መተማመን እንችላለን።—1 ዮሐንስ 4:4
አምላክን በሚያስከብር መንገድ መልበስ
11. የብዙዎች አለባበስ የዓለምን መንፈስ የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው?
11 ከዓለም የተለየን መሆናችንን የምናሳይበት ሌላው መንገድ ደግሞ አለባበሳችንና አጋጌጣችን ነው። በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች አለባበስ የሌሎችን ትኩረት የሚስብ፣ የፆታ ስሜት የሚያነሳሳ፣ ዓመፀኝነት ወይም የይታይልኝ መንፈስ የሚንጸባረቅበት ነው። ሌሎች ደግሞ ለአለባበሳቸው ምንም ግድ የላቸውም። የተዝረከረከ ወይም የቆሸሸ ልብስ ይለብሳሉ። ክርስቲያኖች በአለባበስና በአጋጌጥ ረገድ በዓለም ላይ ያለው አመለካከት ተጽዕኖ እንዳያሳድርባቸው መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።
12, 13. አለባበሳችንን በተመለከተ ምርጫ ስናደርግ በየትኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ልንመራ ይገባል?
12 የይሖዋ አገልጋዮች አለባበሳችን ምንጊዜም ሥርዓታማ፣ ንጹሕ፣ ጨዋነት የሚንጸባረቅበትና ለሁኔታው ተስማሚ መሆን ይኖርበታል። “ለአምላክ ያደርን” መሆናችንን በሚያሳይ መንገድ “በልከኝነትና በማስተዋል” ልንለብስ ይገባል።—1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10፤ ይሁዳ 21
13 አለባበሳችን ሌሎች ስለ ይሖዋና ስለ ሕዝቦቹ በሚኖራቸው አመለካከት ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። “ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር” ማድረግ አለብን። (1 ቆሮንቶስ 10:31) “ልከኝነት” ሲባል የሌሎችን ስሜትና አመለካከት ማክበርን ያካትታል። በመሆኑም አለባበሳችንንና አጋጌጣችንን በተመለከተ ምርጫ ስናደርግ የሌሎችን ስሜት ግምት ውስጥ ማስገባታችን አስፈላጊ ነው።—1 ቆሮንቶስ 4:9፤ 2 ቆሮንቶስ 6:3, 4፤ 7:1
14. በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ስንካፈል የምንለብሰውን ልብስ በምንመርጥበት ጊዜ ልናስብባቸው የሚገቡ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
14 በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ወይም በአገልግሎት ስንካፈል አለባበሳችን ምን ይመስላል? ተገቢ ያልሆነ ትኩረት እንዲሰጠን የሚያደርግ ነው? አለባበሳችን ሌሎችን የሚያሸማቅቅ ነው? ስለ እኛ አለባበስ ማንም እንደማይመለከተው ይሰማናል? (ፊልጵስዩስ 4:5፤ 1 ጴጥሮስ 5:6) ሁላችንም ብንሆን አምሮብን መታየት እንደምንፈልግ ጥያቄ የለውም፤ ሆኖም እውነተኛ ውበት የሚያስገኝልን ግሩም የሆኑ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማዳበራችን እንደሆነ ማስታወሳችን አስፈላጊ ነው። ይሖዋ እኛን ሲመለከት ትኩረት የሚያደርገው በእነዚህ ባሕርያት ላይ ነው። “የተሰወረ የልብ ሰው” የተባለው ውስጣዊ ማንነታችን የሚታየውም በእነዚህ ክርስቲያናዊ ባሕርያት ነው፤ “በአምላክ ፊት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው” ደግሞ ይህ ማንነታችን ነው።—1 ጴጥሮስ 3:3, 4
15. ይሖዋ ምን ዓይነት ልብሶችን መልበስ እንዳለብን የሚገልጹ ዝርዝር መመሪያዎችን ያልሰጠን ለምንድን ነው?
15 ይሖዋ ምን ዓይነት ልብሶችን መልበስ እንዳለብንና እንደሌለብን የሚገልጹ ዝርዝር መመሪያዎችን አልሰጠንም። ከዚህ ይልቅ ጥሩ ምርጫ ለማድረግ የሚረዱ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሮልናል። (ዕብራውያን 5:14) የምናደርጋቸው ትላልቅም ሆኑ ትናንሽ ውሳኔዎች ለእሱና ለሰዎች ባለን ፍቅር ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ ይፈልጋል። (ማርቆስ 12:30, 31ን አንብብ።) በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች እንደየባሕላቸውና እንደየምርጫቸው የተለያየ ዓይነት ልብስ ይለብሳሉ። እንዲህ ያለው የተለያየ አለባበስ ማራኪና ደስ የሚል ነው።
ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
16. ይህ ዓለም ለገንዘብ ያለው አመለካከት ኢየሱስ ካስተማረው ነገር ጋር የሚቃረነው እንዴት ነው? ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?
16 ሰዎች ‘ደስታ የሚገኘው ገንዘብና ቁሳዊ ነገሮችን በማካበት ነው’ የሚል አመለካከት እንዲያዳብሩ ሰይጣን ይፈልጋል፤ የይሖዋ አገልጋዮች ግን ደስታ የሚያስገኙት እነዚህ ነገሮች እንዳልሆኑ ያውቃሉ። ኢየሱስ “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ንብረቱ ሕይወት ሊያስገኝለት አይችልም” በማለት የተናገረው ሐሳብ እውነት መሆኑን ይገነዘባሉ። (ሉቃስ 12:15) ገንዘብ እውነተኛ ደስታ ሊያስገኝልን አይችልም። የልብ ጓደኞች፣ የአእምሮ ሰላም ወይም የዘላለም ሕይወት ሊሰጠንም አይችልም። እርግጥ ነው ቁሳዊ ነገሮች ያስፈልጉናል፤ በሕይወታችን ለመደሰት መፈለጋችንም ስህተት አይደለም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንዳስተማረው፣ እውነተኛ ደስታ የምናገኘው ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ካለንና በሕይወታችን ውስጥ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነ ነው። (ማቴዎስ 5:3፤ 6:22) እንግዲያው ራስህን እንደዚህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ይህ ዓለም ለገንዘብ ያለው አመለካከት ተጽዕኖ አሳድሮብኛል? ሐሳቤና ወሬዬ ሁሉ ገንዘብ ላይ ያተኮረ ነው?’—ሉቃስ 6:45፤ 21:34-36፤ 2 ዮሐንስ 6
17. ገንዘብን በተመለከተ ዓለም ያለው ዓይነት አመለካከት አለመያዛችን የተሻለ ሕይወት ለመምራት የሚረዳን እንዴት ነው?
17 ይሖዋን በማገልገል ላይ ትኩረት ካደረግንና ገንዘብን በተመለከተ ዓለም ያለው ዓይነት አመለካከት ካላዳበርን ሕይወታችን ዓላማ ያለው ይሆናል። (ማቴዎስ 11:29, 30) እውነተኛ እርካታ እንዲሁም ውስጣዊ ሰላም እናገኛለን። (ማቴዎስ 6:31, 32፤ ሮም 15:13) ስለ ቁሳዊ ነገሮች ከልክ በላይ አንጨነቅም። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10ን አንብብ።) በመስጠት የሚገኘውን ደስታ እናጣጥማለን። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) በተጨማሪም እንዲህ ያለ ሕይወት መምራታችን፣ ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር የበለጠ ጊዜ ለማሳለፍ አጋጣሚ ይሰጠናል። እንቅልፋችን እንኳ ጣፋጭ ይሆናል።—መክብብ 5:12
“ሙሉ የጦር ትጥቅ”
18. ሰይጣን ምን ለማድረግ ይሞክራል?
18 ሰይጣን ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ለማበላሸት ይሞክራል፤ በመሆኑም ይህ ዝምድናችን እንዳይበላሽ የተቻለንን ሁሉ ማድረግ አለብን። “ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር” ውጊያ ገጥመናል። (ኤፌሶን 6:12) ሰይጣንና አጋንንቱ ደስታ እንድናገኝም ሆነ ለዘላለም እንድንኖር አይፈልጉም። (1 ጴጥሮስ 5:8) የምንዋጋው ከእነዚህ ኃያል ጠላቶች ጋር ቢሆንም በይሖዋ እርዳታ በውጊያው እናሸንፋለን!
19. ኤፌሶን 6:14-18 ክርስቲያኖች ስለሚለብሱት የጦር ትጥቅ ሲገልጽ ምን ይላል?
19 በጥንት ዘመን የሚኖሩ ወታደሮች በውጊያ ላይ ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል የጦር ትጥቅ ይለብሱ ነበር። እኛም በተመሳሳይ ይሖዋ ያዘጋጀልንን “የጦር ትጥቅ” መልበስ ይኖርብናል። (ኤፌሶን 6:13) ይህ የጦር ትጥቅ ከጉዳት ይጠብቀናል። ኤፌሶን 6:14-18 ስለዚህ የጦር ትጥቅ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ወገባችሁን በእውነት ቀበቶ ታጥቃችሁና የጽድቅን ጥሩር ለብሳችሁ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እንዲሁም የሰላምን ምሥራች ተጫምታችሁ ቁሙ። ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ማምከን የምትችሉበትን ትልቅ የእምነት ጋሻ አንሱ። በተጨማሪም የመዳንን የራስ ቁር አድርጉ፤ እንዲሁም የመንፈስን ሰይፍ ይኸውም የአምላክን ቃል ያዙ፤ ከዚህም በተጨማሪ በሁሉም ዓይነት ጸሎትና ምልጃ በማንኛውም ጊዜ በመንፈስ መጸለያችሁን ቀጥሉ።”
20. ‘የጦር ትጥቃችን’ ከጥቃት እንዲከላከልልን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
20 አንድ ወታደር ከጦር ትጥቁ መካከል አንዱን ቢረሳ፣ ጠላቱ ጥቃት የሚሰነዝረው ባልተሸፈነው የወታደሩ የሰውነት ክፍል ላይ እንደሆነ የታወቀ ነው። እኛም ጠላቶቻችን የሚሰነዝሩብን ጥቃት ጉዳት እንዳያደርስብን ከፈለግን ‘ከጦር ትጥቃችን’ መካከል አንዱንም መርሳት የለብንም። ሙሉውን የጦር ትጥቅ ሁልጊዜ መልበስና ትጥቃችን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዲገኝ ማድረግ ያስፈልገናል። ውጊያችን የሚያቆመው የሰይጣን ዓለም ሲጠፋ እንዲሁም ሰይጣንና አጋንንቱ ከምድር ሲወገዱ ነው። (ራእይ 12:17፤ 20:1-3) እንግዲያው ከመጥፎ ምኞት ወይም ከአንዳንድ ድክመቶቻችን ጋር እየታገልን ከሆነ ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም!—1 ቆሮንቶስ 9:27
21. በምናደርገው ውጊያ ድል ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
21 በራሳችን ኃይል ዲያብሎስን ማሸነፍ አንችልም። በይሖዋ እርዳታ ግን ይህን ጠላታችንን ድል ማድረግ እንችላለን! በታማኝነት መጽናት እንድንችል ወደ ይሖዋ መጸለይ፣ ቃሉን ማጥናት እንዲሁም ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር መሰብሰብ ያስፈልገናል። (ዕብራውያን 10:24, 25) እንዲህ ማድረጋችን ምንጊዜም ለአምላክ ታማኝ እንድንሆንና ለእምነታችን ጥብቅና ለመቆም እንድንዘጋጅ ይረዳናል።
ለእምነታችሁ ጥብቅና ለመቆም ዝግጁ ሁኑ
22, 23. (ሀ) በማንኛውም ጊዜ ለእምነታችን ጥብቅና ለመቆም ዝግጁ እንድንሆን ምን ይረዳናል? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንመለከታለን?
22 በማንኛውም ጊዜ ለእምነታችን ጥብቅና ለመቆም ዝግጁ መሆን ይኖርብናል። (ዮሐንስ 15:19) የይሖዋ ምሥክሮች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ያላቸው አቋም ከአብዛኞቹ ሰዎች በጣም የተለየ ነው። በመሆኑም ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘እንዲህ ያለ አቋም የያዝንበት ምክንያት በደንብ ገብቶኛል? መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ታማኝና ልባም ባሪያ የሚያስተምሩት ነገር ትክክል እንደሆነ አምናለሁ? (ማቴዎስ 24:45፤ ዮሐንስ 17:17) የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ እኮራለሁ? (መዝሙር 34:2፤ ማቴዎስ 10:32, 33) ስለማምንባቸው ነገሮች ለሌሎች ማስረዳት እችላለሁ?’—1 ጴጥሮስ 3:15ን አንብብ።
23 ከአብዛኞቹ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ፣ ከዓለም መለየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ምንም ጥያቄ አይፈጠርብንም። በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ ግን እንዴት ከዓለም መለየት እንደምንችል ግልጽ ላይሆንልን ይችላል። ሰይጣን በተለያዩ መንገዶች ተጠቅሞ ሊያጠምደን ይሞክራል። ከሚጠቀምባቸው ወጥመዶች መካከል አንዱ መዝናኛ ነው። ታዲያ ጥሩ መዝናኛ መምረጥ የምንችለው እንዴት ነው? በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይህን እንመለከታለን።