ትምህርት 12
ወደ አምላክ መቅረብ የምትችለው እንዴት ነው?
1. አምላክ ማንኛውንም ዓይነት ጸሎት ይሰማል?
አምላክ፣ ሰዎች ሁሉ በጸሎት አማካኝነት ወደ እሱ እንዲቀርቡ ይጋብዛል። (መዝሙር 65:2) ይሁንና የሚሰማው ወይም የሚቀበለው ሁሉንም ጸሎቶች አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ በሚስቱ ላይ በደል የሚፈጽም ባል ወደ አምላክ የሚያቀርበው ጸሎት ሊታገድበት ይችላል። (1 ጴጥሮስ 3:7) በተጨማሪም እስራኤላውያን መጥፎ አካሄዳቸውን ለመተው አሻፈረን በማለታቸው አምላክ የሚያቀርቡትን ጸሎት ለመስማት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። ያም ቢሆን አምላክ፣ ከባድ ኃጢአት የሠሩ ሰዎችም እንኳ ተጸጽተው ንስሐ እስከገቡ ድረስ ጸሎታቸውን ይሰማል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የጸሎት መብታችንን አቅልለን ልንመለከተው አይገባም።—ኢሳይያስ 1:15ን እና 55:7ን አንብብ።
አምላክ ማንኛውንም ዓይነት ጸሎት ይሰማል? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት
2. መጸለይ ያለብን እንዴት ነው?
ጸሎት የአምልኳችን ክፍል በመሆኑ መጸለይ ያለብን ፈጣሪያችን ወደሆነው ወደ ይሖዋ ብቻ ነው። (ማቴዎስ 4:10፤ 6:9) ፍጹማን ባለመሆናችን ኢየሱስ ለኃጢአታችን ሲል ሞቶልናል፤ በመሆኑም መጸለይ ያለብን በኢየሱስ ስም ነው። (ዮሐንስ 14:6) ይሖዋ ከልብ በመነጨ ስሜት እንድንጸልይ እንጂ አንድን ሐሳብ በመሸምደድ ወይም በማንበብ ሁልጊዜ ተመሳሳይ ጸሎት እንድናቀርብ አይፈልግም።—ማቴዎስ 6:7ን እና ፊልጵስዩስ 4:6, 7ን አንብብ።
ፈጣሪያችን በልባችን የምናቀርበውን ጸሎት እንኳ ይሰማል። (1 ሳሙኤል 1:12, 13) አምላክ ዘወትር ወደ እሱ እንድንጸልይ ለምሳሌ ጠዋት ስንነቃም ሆነ ማታ ከመተኛታችን በፊት፣ በምግብ ሰዓት እንዲሁም ችግሮች ሲያጋጥሙን ወደ እሱ እንድንቀርብ ይጋብዘናል።—መዝሙር 55:22ን እና ማቴዎስ 15:36ን አንብብ።
3. ክርስቲያኖች አንድ ላይ የሚሰበሰቡት ለምንድን ነው?
የምንኖረው በአምላክ ላይ እምነት በሌላቸው እንዲሁም እሱ በምድር ላይ ሰላም እንደሚያሰፍን በገባው ቃል ላይ በሚያፌዙ ሰዎች መካከል ስለሆነ ወደ አምላክ መቅረብ ቀላል አይደለም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 4፤ 2 ጴጥሮስ 3:3, 13) በመሆኑም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አንድ ላይ በመሰብሰብ እርስ በርስ መበረታታት ያስፈልገናል።—ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብብ።
አምላክን ከሚወዱ ሰዎች ጋር መወዳጀታችን ወደ አምላክ ለመቅረብ ይረዳናል። የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘታችን የሌሎችን እምነት በማየት ለመበረታታት የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ይከፍትልናል።—ሮም 1:11, 12ን አንብብ።
4. ወደ አምላክ መቅረብ የምትችለው እንዴት ነው?
ከመጽሐፍ ቅዱስ በተማርካቸው ነገሮች ላይ በማሰላሰል ወደ ይሖዋ መቅረብ ትችላለህ። ይሖዋ ባደረጋቸው ነገሮች፣ በሰጣቸው ምክሮችና በገባቸው ተስፋዎች ላይ አሰላስል። ጸሎትና ማሰላሰል ለአምላክ ፍቅርና ጥበብ ከልብ የመነጨ አድናቆት እንድናዳብር ይረዱናል።—ኢያሱ 1:8ን እና መዝሙር 1:1-3ን አንብብ።
ወደ አምላክ መቅረብ የምትችለው በእሱ ላይ እምነት የምታሳድር ወይም በእሱ የምትተማመን ከሆነ ብቻ ነው። ይሁንና እምነት፣ ልክ እንደ ተክል ዘወትር እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል። ለምታምንባቸው ነገሮች መሠረት የሆኑትን ሐሳቦች ሁልጊዜ መለስ ብለህ በመከለስ እምነትህ ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ይኖርብሃል።—ማቴዎስ 4:4ን እና ዕብራውያን 11:1, 6ን አንብብ።
5. ወደ አምላክ መቅረብህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?
ይሖዋ ለሚወዱት ሰዎች ያስብላቸዋል። እምነታቸውንና የዘላለም ሕይወት ተስፋቸውን አደጋ ላይ ሊጥል ከሚችል ከማንኛውም ነገር ይጠብቃቸዋል። (መዝሙር 91:1, 2, 7-10) አምላክ ጤንነታችንን እና ደስታችንን ሊያሳጣን ከሚችል የአኗኗር ዘይቤ እንድንርቅ ያስጠነቅቀናል። ይሖዋ ሕይወታችንን ከሁሉ በተሻለ መንገድ መምራት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል።—መዝሙር 73:27, 28ን እና ያዕቆብ 4:4, 8ን አንብብ።