በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 26

ጥሩ ነገር መሥራት ከባድ የሆነው ለምንድን ነው?

ጥሩ ነገር መሥራት ከባድ የሆነው ለምንድን ነው?

ሳኦል መጥፎ ነገር በሠራ ጊዜ የተደሰተው ማን ነው?— ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። የአይሁዳውያን የሃይማኖት መሪዎችም ተደስተው ነበር። በኋላ ግን ሳኦል የታላቁ አስተማሪ ደቀ መዝሙር ሆኖ ጳውሎስ ተብሎ ሲጠራ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ይጠሉት ጀመር። ስለዚህ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የሆነ ሰው ጥሩ ነገር መሥራት ከባድ የሚሆንበት ለምን እንደሆነ ገባህ?—

ጳውሎስ ጥሩ ነገር ሲሠራ ምን ሥቃይ ደረሰበት?

በአንድ ወቅት ሐናንያ የተባለው ሊቀ ካህናት ሰዎች ጳውሎስን ፊቱ ላይ እንዲመቱት አዝዞ ነበር። እንዲያውም ሐናንያ ጳውሎስን እስር ቤት ለማስገባት ሞክሮ ነበር። ጳውሎስ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር በሆነ ጊዜ ብዙ ሥቃይ ደርሶበታል። ለምሳሌ ያህል፣ መጥፎ ሰዎች የደበደቡት ሲሆን በድንጋይ ወግረው ሊገድሉትም ሞክረው ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 23:1, 2፤ 2 ቆሮንቶስ 11:24, 25

ብዙ ሰዎች አምላክን የማያስደስት መጥፎ ነገር እንድንሠራ ለማድረግ ይጥራሉ። በመሆኑም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልታስብባቸው ይገባል:- ጥሩ የሆነውን ነገር የምትወደው ምን ያህል ነው? ጥሩ ለሆነው ነገር ያለህ ፍቅር ሌሎች ሊጠሉህ ቢችሉም እንኳን ጥሩ ማድረግህን እንድትቀጥል ይገፋፋሃል? እንዲህ ማድረግ ድፍረት ይጠይቃል፣ አይደል?—

‘ጥሩ ነገር በመሥራታችን ሰዎች መደሰት ሲገባቸው የሚጠሉን ለምንድን ነው?’ ብለህ ትገረም ይሆናል። ሊደሰቱ ይገባቸዋል ብለህ ማሰብህ ትክክል ነው። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ኢየሱስ በሠራቸው ጥሩ ነገሮች ይደሰቱ ነበር። በአንድ ወቅት፣ በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ኢየሱስ በነበረበት ቤት በር ላይ ተሰብስበው ነበር። ሰዎቹ የመጡት ኢየሱስ የታመሙ ሰዎችን እየፈወሰ ስለነበር ነው።—ማርቆስ 1:33

ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ኢየሱስ የሚያስተምረው ነገር አያስደስታቸውም ነበር። ኢየሱስ ምንጊዜም ትክክል የሆነ ነገር ያስተምር የነበረ ቢሆንም አንዳንዶቹ ሰዎች ኢየሱስ እውነትን በመናገሩ ለእሱ ጥላቻ አድሮባቸው ነበር። አንድ ቀን ኢየሱስ ባደገባት በናዝሬት ከተማ እንዲህ ያለ ነገር ተከሰተ። ኢየሱስ አይሁዳውያን አምላክን ለማምለክ ወደሚሰበሰቡበት ወደ ምኩራብ ሄዶ ነበር።

እዚያም ኢየሱስ ከቅዱሳን መጻሕፍት ጠቅሶ ጥሩ ንግግር አቀረበ። ሰዎቹ መጀመሪያ ላይ ንግግሩን ወደውት ነበር። ከኢየሱስ አፍ በሚወጡት ጥሩ ቃላት ተገርመው ነበር። ይህን ጥሩ ንግግር የሰጠው በራሳቸው ከተማ ያደገው ወጣት መሆኑን ማመን አቅቷቸው ነበር።

በኋላ ግን ኢየሱስ አንድ ሌላ ነገር ተናገረ። አምላክ አይሁዳውያን ላልሆኑ ሰዎች ልዩ ፍቅር ያሳየባቸው ጊዜያት እንደነበሩ ነገራቸው። ኢየሱስ ይህን ሲናገር በምኩራቡ የነበሩት ሰዎች ተቆጡ። ለምን እንደተቆጡ ታውቃለህ?— አምላክ ልዩ ፍቅር የሚያሳየው ለእነሱ ብቻ እንደሆነ አድርገው ያስቡ ስለነበረ ነው። እነሱ ከሌሎች ሰዎች የተሻሉ እንደሆኑ ያስቡ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ እንደዚህ ብሎ በመናገሩ ጠሉት። ከዚያም ምን ሊያደርጉት እንደሞከሩ ታውቃለህ?—

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- ‘ኢየሱስን ይዘው እያጣደፉ ከከተማው አስወጡት። ወደ አንድ ተራራ ጫፍ ወሰዱትና ወደ ታች ወርውረው ሊገድሉት አሰቡ። እሱ ግን አምልጧቸው ሄደ።’—ሉቃስ 4:16-30

እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን ለመግደል ጥረት ያደረጉት ለምንድን ነው?

ይህ ነገር በአንተ ላይ ደርሶ ቢሆን ኖሮ ለእነዚህ ሰዎች ስለ አምላክ ለመንገር ተመልሰህ ትሄድ ነበር?— እንዲህ ማድረግ ድፍረት ይጠይቃል፣ አይደል?— ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከአንድ ዓመት በኋላ ተመልሶ ወደ ናዝሬት ሄዷል። መጽሐፍ ቅዱስ “በምኩራባቸው ያስተምራቸው ጀመር” ይላል። ኢየሱስ ለአምላክ ፍቅር የሌላቸውን ሰዎች ፈርቶ እውነትን መናገሩን አላቆመም።—ማቴዎስ 13:54

ሌላ ጊዜ ደግሞ በሰንበት ቀን ኢየሱስ ወደ አንድ ምኩራብ ገባ፤ በዚያም እጁ የሰለለ ወይም ሽባ የሆነ አንድ ሰው ነበር። ኢየሱስ ይህን ሰው ለመፈወስ የሚያስችል ከአምላክ የተሰጠው ኃይል ነበረው። ይሁን እንጂ በምኩራቡ ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ በኢየሱስ ላይ ችግር ለመፍጠር ሞከሩ። ታዲያ ታላቁ አስተማሪ ምን አደረገ?— በመጀመሪያ እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው:- ‘በግ ቢኖራችሁና በጉ በሰንበት ቀን ትልቅ ጉድጓድ ውስጥ ቢገባ ከጉድጓዱ አታወጡትም?’

አዎ፣ ሰንበት ሊያርፉበት የሚገባ ቀን ቢሆንም እንኳን በጉን ከጉድጓድ ያወጡት ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ‘ሰው ከበግ ስለሚበልጥ ሰውን በሰንበት ቀን መርዳት የበለጠ አስፈላጊ ነው’ ብሎ ነገራቸው። ኢየሱስ ይህን ሰው በመፈወስ እሱን መርዳቱ አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ ነበር!

ኢየሱስ ሰውየውን እጁን እንዲዘረጋ ነገረው። ወዲያውኑም እጁ ዳነ። ይህ ሰው ምን ያህል ተደስቶ ይሆን! ይሁን እንጂ እዚያ የነበሩት ሌሎቹ ሰዎችስ? እነሱም ተደስተው ነበር?— በፍጹም። እንዲያውም ኢየሱስን ይበልጥ ጠሉት። ከዚያ ወጥተው በመሄድ እሱን ለመግደል መመካከር ጀመሩ።—ማቴዎስ 12:9-14

ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ምንም ብናደርግ ሁሉንም ሰው ማስደሰት አንችልም። ስለዚህ ማንን ማስደሰት እንደምንፈልግ መወሰን ይኖርብናል። ይሖዋ አምላክንና ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ማስደሰት የምንፈልግ ከሆነ ሁልጊዜ እነሱ የሚያስተምሩንን ነገር ማድረግ አለብን። ይሁን እንጂ እንዲህ ስናደርግ ማን ይጠላናል? ጥሩ የሆነውን ነገር ማድረግ እንዲከብደን የሚያደርገው ማን ነው?—

ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ይሁን እንጂ ከሰይጣን በተጨማሪ ጥሩ የሆነውን ነገር ማድረግ እንዲከብደን የሚያደርጉት እነማን ናቸው?— ዲያብሎስ የተሳሳቱ ነገሮችን አምነው እንዲቀበሉ ያታለላቸው ሰዎች ናቸው። ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች “እናንተ የአባታችሁ የዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት መፈጸም ትሻላችሁ” ብሏቸዋል።—ዮሐንስ 8:44

ዲያብሎስ የሚወዳቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች “ዓለም” ብሎ ጠርቷቸዋል። ኢየሱስ “ዓለም” ሲል ምን ማለቱ ነው?— ይህን ጥያቄ ለመመለስ ዮሐንስ ምዕራፍ 15 ቁጥር 19ን እናንብብ። በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “የዓለም ክፍል ብትሆኑ ኖሮ ዓለም የራሱ የሆነውን በወደደ ነበር። አሁን ግን እኔ ከዓለም መረጥኳችሁ እንጂ የዓለም ክፍል ስላልሆናችሁ ከዚህ የተነሳ ዓለም ይጠላችኋል።”

ስለዚህ የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት የሚጠላው ዓለም፣ የኢየሱስ ተከታዮች ያልሆኑትን ሰዎች በሙሉ ያጠቃልላል። ዓለም የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት የሚጠላው ለምንድን ነው?— እስቲ ለማሰብ ሞክር። የዓለም ገዥ ማን ነው?— መጽሐፍ ቅዱስ ‘መላው ዓለም በክፉው ኃይል ሥር ነው’ ይላል። ክፉው የተባለው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው።—1 ዮሐንስ 5:19

ጥሩ ነገር መሥራት በጣም ከባድ የሆነው ለምን እንደሆነ አሁን ገብቶሃል?— ጥሩ ነገር መሥራት ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርጉት ሰይጣንና የእሱ ዓለም ናቸው። ይሁን እንጂ ጥሩ ነገር መሥራት ከባድ እንዲሆን የሚያደርግ ሌላም ነገር አለ። ይህ ምን እንደሆነ ታስታውሳለህ?— በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 23 ላይ ሁላችንም ኃጢአተኞች ሆነን እንደተወለድን ተምረናል። ታዲያ ኃጢአት፣ ዲያብሎስና የእሱ ዓለም የማይኖሩበት ጊዜ ቢመጣ በጣም ደስ አይልም?—

ይህ ዓለም ሲያልፍ ጥሩ ነገር የሚያደርጉ ሰዎች ምን ይሆናሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዓለም በማለፍ ላይ ነው’ የሚል ተስፋ ይሰጣል። ይህ ማለት ደግሞ የታላቁ አስተማሪ ተከታዮች ያልሆኑ ሰዎች በሙሉ ይጠፋሉ ማለት ነው። ለዘላለም እንዲኖሩ አይፈቀድላቸውም። ለዘላለም የሚኖሩት እነማን እንደሆኑ ታውቃለህ?— መጽሐፍ ቅዱስ በመቀጠል “የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” ይላል። (1 ዮሐንስ 2:17) አዎ፣ በአምላክ አዲስ ዓለም ለዘላለም የሚኖሩት ጥሩ ነገር የሚያደርጉ ማለትም “የአምላክን ፈቃድ” የሚያደርጉ ሰዎች ብቻ ናቸው። ስለዚህ ከባድ ቢሆንም እንኳን ጥሩ ነገር ማድረግ እንፈልጋለን፣ አይደል?—

ጥሩ ነገር ማድረግ ቀላል ያልሆነው ለምን እንደሆነ የሚገልጹትን የሚከተሉትን ጥቅሶች አብረን እናንብብ:- ማቴዎስ 7:13, 14፤ ሉቃስ 13:23, 24፤ የሐዋርያት ሥራ 14:21, 22