በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 40

አምላክን ማስደሰት የምንችለው እንዴት ነው?

አምላክን ማስደሰት የምንችለው እንዴት ነው?

አምላክን ለማስደሰት ምን ማድረግ እንችላለን? ልንሰጠው የምንችለው ነገር አለ?— ይሖዋ “የዱር አራዊት ሁሉ . . . የእኔ ነው” ብሏል። በተጨማሪም “ብሩ የእኔ ነው፤ ወርቁም የእኔ ነው” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 24:1፤ 50:10፤ ሐጌ 2:8) ሆኖም ለአምላክ ልንሰጠው የምንችለው ነገር አለ። ልንሰጠው የምንችለው ምንድን ነው?—

ይሖዋ እሱን የማገልገልም ሆነ ያለማገልገል ምርጫ ሰጥቶናል። እሱ የሚፈልገውን ነገር እንድናደርግ አያስገድደንም። አምላክ እሱን ለማገልገልም ሆነ ላለማገልገል መምረጥ እንድንችል አድርጎ የፈጠረን ለምን እንደሆነ ለመረዳት እንሞክር።

ሮቦት ምን እንደሆነ ታውቅ ይሆናል። ሮቦት፣ ሠሪው የሚፈልገውን ነገር ሁሉ እንዲያከናውን ተደርጎ የተሠራ ማሽን ነው። ስለዚህ ሮቦት በራሱ ምርጫ የሚያደርገው ነገር የለም። ይሖዋ ቢፈልግ ኖሮ ሁላችንንም እንደ ሮቦት አድርጎ ሊፈጥረን ይችል ነበር። እሱ የሚፈልገውን ነገር ብቻ ማድረግ የምንችል ዓይነት ሰዎች አድርጎ ሊፈጥረን ይችል ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ እንዲህ አላደረገም። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— አንዳንድ መጫወቻዎች እንደ ሮቦት ናቸው። እነዚህ መጫወቻዎች ማብሪያና ማጥፊያቸው ሲነካ ማከናወን የሚችሉት የሠራቸው ሰው የወሰነላቸውን ተግባር ብቻ ነው። እንዲህ ዓይነት መጫወቻ አይተህ ታውቃለህ?— ብዙውን ጊዜ ሰዎች፣ በተገጠመላቸው ፕሮግራም መሠረት ብቻ በሚንቀሳቀሱ አሻንጉሊቶች መጫወት ይሰለቻቸዋል። አምላክ እሱን እንድናገለግል ብቻ ተደርገን የተሠራን ሮቦቶች ሆነን እንድንታዘዘው አይፈልግም። ይሖዋ የሚፈልገው ለእሱ ባለን ፍቅርና እሱን ለመታዘዝ ባለን ፍላጎት ተገፋፍተን እንድናገለግለው ነው።

አምላክ እንደዚህ ሮቦት አድርጎ ያልፈጠረን ለምንድን ነው?

የሰማዩ አባታችን በራሳችን ፍላጎት ተነሳስተን ስንታዘዘው ምን የሚሰማው ይመስልሃል?— አንተ የምታሳየው ጠባይ ወላጆችህ ምን እንዲሰማቸው ሊያደርግ እንደሚችል እስቲ ንገረኝ።— መጽሐፍ ቅዱስ ጥበበኛ የሆነ ልጅ ‘አባቱን ደስ እንደሚያሰኝ’ ሞኝ ልጅ ግን “ለእናቱ ሐዘን” እንደሆነ ይናገራል። (ምሳሌ 10:1) እናትህና አባትህ ያዘዙህን ነገር ስትፈጽም ደስ እንደሚላቸው አስተውለህ ታውቃለህ?— ይሁን እንጂ የሰጡህን ትእዛዝ ስትጥስ ምን ይሰማቸዋል?—

ይሖዋንም ሆነ ወላጆችህን ማስደሰት የምትችለው እንዴት ነው?

አሁን ደግሞ እስቲ ስለ ሰማዩ አባታችን ስለ ይሖዋ እናስብ። ይሖዋ እሱን እንዴት ማስደሰት እንደምንችል ገልጾልናል። እስቲ መጽሐፍ ቅዱስህን ግለጥና ምሳሌ 27:11ን አውጣ። እዚህ ጥቅስ ላይ አምላክ “ልጄ ሆይ፤ ጠቢብ ሁን፤ ልቤን ደስ አሰኘው፤ ለሚንቁኝ ሁሉ [“ለሚሳለቅብኝ፣” NW] መልስ መስጠት እችል ዘንድ” በማለት ይነግረናል። መሳለቅ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?— አንድ ሰው እየሳቀብህ፣ አደርገዋለሁ ያልከውን ነገር ማድረግ እንደማትችል ከተናገረ እየተሳለቀብህ ነው ማለት ነው። ሰይጣን በይሖዋ ላይ የሚሳለቀው እንዴት ነው?— እስቲ እንመልከት።

በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ላይ ሰይጣን ከሁሉ የበላይ መሆን ስለሚፈልግ ማንኛውም ፍጡር እሱን እንዲታዘዘው እንደሚፈልግ ተምረን እንደነበር አስታውስ። ሰይጣን ሰዎች ይሖዋን የሚያመልኩት የዘላለም ሕይወት ስለሚሰጣቸው ብቻ ነው ይላል። ሰይጣን፣ አዳምና ሔዋን የይሖዋን ትእዛዝ እንዲጥሱ ካደረጋቸው በኋላ አምላክን በመዳፈር በእሱ ላይ የሚከተለውን ክስ አቀረበ:- ‘ሰዎች የሚያገለግሉህ ከአንተ ለሚያገኙት ጥቅም ሲሉ ብቻ ነው። አጋጣሚውን ከሰጠኸኝ ሁሉም ሰው ከአንተ እንዲርቅ ማድረግ እችላለሁ።’

አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ሰይጣን ይሖዋን በመዳፈር ምን ክስ አቅርቧል?

እርግጥ ነው፣ እነዚህ ቃላት ቃል በቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኙም። ይሁን እንጂ የኢዮብን ታሪክ በምናነብበት ጊዜ ሰይጣን ለአምላክ የተናገረው ቃል ከዚህ ጋር እንደሚመሳሰል በግልጽ መረዳት እንችላለን። ኢዮብ ለአምላክ ታማኝ መሆን አለመሆኑ ለሰይጣንም ሆነ ለይሖዋ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ጉዳይ ነበር። የሆነውን ነገር ለመረዳት መጽሐፍ ቅዱሳችንን ገልጠን ኢዮብ ምዕራፍ 1 እና ምዕራፍ 2ን እንመልከት።

ኢዮብ ምዕራፍ 1 በሰማይ የተከናወነውን ነገር ሲናገር መላእክት በይሖዋ ፊት ለመቅረብ እንደመጡና ሰይጣንም በመካከላቸው እንደተገኘ ይገልጻል። ስለዚህ ይሖዋ ሰይጣንን “ከወዴት መጣህ?” በማለት ጠየቀው። ሰይጣንም በምድር ዙሪያ ሲመላለስ እንደቆየ ተናገረ። ስለዚህ ይሖዋ ‘ኢዮብ እኔን እንደሚያገለግልና ምንም መጥፎ ነገር እንደማይሠራ አየህ?’ አለው።—ኢዮብ 1:6-8

ሰይጣንም ወዲያውኑ ሰበብ አቀረበ። ‘ኢዮብ የሚያመልክህ ምንም ችግር ስላልደረሰበት ነው። ለእሱ ጥበቃ ማድረግህንና እሱን መባረክህን ብትተው በፊትህ ይሰድብሃል’ አለው። ስለዚህ ይሖዋ ‘በል እሺ፣ የምትፈልገውን ሁሉ በኢዮብ ላይ ማድረግ ትችላለህ። ብቻ እሱ ላይ ምንም ጉዳት እንዳታደርስ’ አለው።—ኢዮብ 1:9-12

ሰይጣን ምን ያደርግ ይሆን?— የኢዮብ ከብቶችና አህዮች እንዲሰረቁ እንዲሁም ጠባቂዎቹ እንዲገደሉ አደረገ። ከዚያም መብረቅ ወደቀና በጎቹንና ጠባቂዎቹን ገደላቸው። በኋላ ደግሞ ሰዎች መጡና ግመሎቹን ሰርቀው ጠባቂዎቹን ገደሏቸው። በመጨረሻም ሰይጣን አውሎ ነፋስ አምጥቶ የኢዮብ አሥር ልጆች ያሉበትን ቤት በማፍረስ በእነሱ ላይ እንዲወድቅባቸውና ሁሉም እንዲሞቱ አደረገ። ኢዮብ ይህ ሁሉ ቢደርስበትም ይሖዋን ማገልገሉን አልተወም።—ኢዮብ 1:13-22

ይሖዋ እንደገና ሰይጣንን ሲያገኘው ኢዮብ አሁንም ታማኝ እንደሆነ ነገረው። በዚህ ጊዜ ሰይጣን ‘በሰውነቱ ላይ ጉዳት እንዳደርስ ብትፈቅድልኝ በፊትህ ይሰድብሃል’ በማለት ሰበብ ፈጠረ። ስለዚህ ይሖዋ፣ ሰይጣን በሰውነቱ ላይ ጉዳት እንዲያደርስበት ፈቀደለት፤ ይሁን እንጂ ኢዮብን እንዳይገድለው አስጠነቀቀው።

ኢዮብ በጽናት የተቋቋመው ነገር ምንድን ነው? ይህስ አምላክን ያስደሰተው ለምንድን ነው?

ሰይጣን የኢዮብ ሰውነት በሙሉ እንዲቆስል አደረገ። ቁስሉ በጣም ይሸት ስለነበር ማንም ሰው ወደ ኢዮብ መቅረብ አይፈልግም ነበር። የኢዮብ ሚስትም እንኳን “እግዚአብሔርን ስደብና ሙት” አለችው። የኢዮብ ጓደኞች ነን የሚሉ ሰዎች ሊጠይቁት መጡና ይህ ሁሉ መከራ የደረሰብህ አንድ መጥፎ ነገር ብትሠራ ነው በማለት ይበልጥ እንዲያዝን አደረጉት። ኢዮብ፣ ሰይጣን ይህን ሁሉ መከራና ሥቃይ ቢያደርስበትም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገሉን ቀጥሏል።—ኢዮብ 2:1-13፤ 7:5፤ 19:13-20

ኢዮብ ታማኝ መሆኑ ይሖዋን ምን እንዲሰማው ያደረገው ይመስልሃል?— ይሖዋ ለሰይጣን ‘ኢዮብን ተመልከተው! የሚያገለግለኝ በራሱ ፍላጎት ተነሳስቶ ነው’ ብሎ መናገር ስለሚችል የኢዮብ ታማኝነት እንዳስደሰተው ግልጽ ነው። አንተስ እንደ ኢዮብ ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ማሳየት ትችላለህ? ይሖዋ አንተን እንደ ኢዮብ ምሳሌ አድርጎ ሊጠቅስህ ይችላል?— ሰይጣን ‘ሁሉም ሰው ይሖዋን ማገልገሉን እንዲተው ማድረግ እችላለሁ’ ብሎ ስለተናገረ ለዚህ መልስ መስጠት በእርግጥም ክብር ነው። ኢየሱስ ይህን እንደ ክብር እንደቆጠረው ጥርጥር የለውም።

ታላቁ አስተማሪ፣ ሰይጣን ቢገፋፋውም መጥፎ ነገር አልሠራም። የእሱ ምሳሌነት አባቱን ምን ያህል አስደስቶት ሊሆን እንደሚችል አስበው! ይሖዋ ወደ ኢየሱስ እያመለከተ ‘ልጄን እየው! ስለሚወደኝ ለእኔ ሙሉ በሙሉ ታማኝ ሆኗል!’ ብሎ ለሰይጣን መልስ መስጠት ይችላል። ኢየሱስም የአባቱን ልብ በማስደሰቱ ምን ያህል ተደስቶ ሊሆን እንደሚችል አስበው! ኢየሱስ በዚህ ደስታ የተነሳ በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ጸንቷል።—ዕብራውያን 12:2

አንተም እንደ ታላቁ አስተማሪ በመሆን የይሖዋን ልብ ማስደሰት ትፈልጋለህ?— እንግዲያው ይሖዋ ምን እንድታደርግ እንደሚፈልግ መማርህን ቀጥል፤ እንዲሁም የተማርከውን ተግባራዊ በማድረግ ደስ አሰኘው!

ኢየሱስ አምላክን ለማስደሰት ምን እንዳደረገና እኛም ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገን ለማወቅ ምሳሌ 23:22-25፤ ዮሐንስ 5:30፤ 6:38፤ 8:28 እና 2 ዮሐንስ 4ን አንብቡ።