በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም

የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም

ፍቺ:- የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ከዕብራይስጥ፣ ከአረማይክና ከግሪክኛ ቋንቋዎች በቀጥታ ወደ ዘመናዊ እንግሊዝኛ በመተርጎም የተዘጋጀ የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ሲሆን ተርጓሚው ከቅቡዓን የይሖዋ ምሥክሮች የተውጣጣ ኮሚቴ ነው። የዚህ ኮሚቴ አባሎች ስለ ሥራቸው እንደሚከተለው በማለት ገልጸዋል:- “የቅዱሳን ጽሑፎች ባለቤት የሆነውን መለኮት የሚፈሩትና የሚያፈቅሩት የዚህ ጽሑፍ ተርጓሚዎች የእርሱን ሐሳብና መግለጫዎች የተቻለውን ያህል በትክክል ለማስተላለፍ ልዩ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። እንዲሁም በልዑል አምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈውን ቃል በመመርመር የዘላላም መዳንን ለማግኘት ለሚጥሩ ተመራማሪ አንባቢዎች ኃላፊነት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል።” ይህ ትርጉም በመጀመሪያ የወጣው ከ1950 እስከ 1960 ባሉት ዓመታት በተለያዩ ክፍሎች እየተዘጋጀ ነበር። በሌሎች ቋንቋዎች የታተሙት የአዲሲቱ ዓለም ትርጉሞች መሠረት ያደረጉት የእንግሊዝኛውን ትርጉም ነው።

“የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም” የተመሠረተው በምን ላይ ነው?

የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ለመተርጎም መሠረት ሆኖ ያገለገለው ከ1951–1955 ባለው ጊዜ ውስጥ የታተመው ቢብሊያ ሂብራይካ የተባለው የሩዶልፍ ኪተል ጽሑፍ ነው። በ1984 ታርሞ የታተመው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ተሻሽሎ ከወጣው ከ1977ቱ ቢብሊያ ሂብራይካ ስቱትጋርቴንሲያ እትም ብዙ ጠቃሚ ማስተካከያዎችን አግኝቷል። በተጨማሪም ተርጓሚዎቹ ከሙት ባሕር ጥቅሎችና በተለያዩ ቋንቋዎች ከተዘጋጁ ጥንታዊነት ያላቸው ትርጉሞች ጋር አመሳክረዋል። የግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎችን በሚተረጉሙበት ጊዜ በዋነኛነት የተጠቀሙት በዌስትኮትና ሆርት በ1881 የተዘጋጀውን የግሪክኛ ጽሑፍ ቢሆንም የተለያዩ የጥንት ጽሑፎችንና በሌሎች ቋንቋዎች የተዘጋጁ ትርጉሞችን አመሳክረዋል።

ተርጓሚዎቹ እነማን ነበሩ?

የአዲሲቱ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ የማሳተም መብቱን ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በስጦታነት ባስረከበበት ጊዜ የኮሚቴው አባሎች ስም እንዳይገለጽ ጠይቋል። የፔንስልቫንያ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበርም ጥያቄያቸውን አክብሮላቸዋል። የተርጓሚዎቹ ዋነኛ ፍላጎት የቅዱሳን ጽሑፎች ባለቤት የሆነው መለኮት እንዲከበር እንጂ ለራሳቸው ከፍተኛ ዝና ማትረፍ አልነበረም።

ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴዎችም ተመሳሳይ አቋም ወስደዋል። ኒው አሜሪካን ስታንዳርድ ባይብል (1971) በመጽሐፉ ሽፋን ባሰፈረው መግለጫ ላይ እንዲህ ይላል:- “የአምላክ ቃል በማንም ላይ ሳይደገፍ ራሱ በራሱ መቆም ስለሚችል የማንንም ምሁር ስም በመጥቀስ ትርጉሙ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ አልሞከርንም።”

የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በእርግጥ የምሁራን ትርጉም ነውን?

ተርጓሚዎቹ ስማቸው እንዳይገለጽ ስለጠየቁ ስለ ትምህርት ደረጃቸው በመግለጽ ይህን ጥያቄ መመለስ አይቻልም። ትርጉሙ ራሱ ባለው የጥራት ደረጃ መመዘን ይኖርበታል።

ትርጉሙ ምን ዓይነት ትርጉም ነው? ትርጉሙ ትክክለኛና በአብዛኛው ከመጀመሪያዎቹ ቋንቋዎች ቃል በቃል የተተረጐመ ነው። ተርጓሚዎች አስፈላጊ አይደሉም ያሏቸውን ዝርዝር ነጥቦች በመተው ይጠቅማሉ ብለው ያመኑባቸውን ሐሳቦች በመጨመር እንደሚተረጉሟቸው ትርጉሞች ውርስ ትርጉም (ፓራፍሬዝ) አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ ሰዎችን ለመርዳት ታስቦ ጥቅሶች እንዴት ያለ የተለያየ አተረጓጎም ሊኖራቸው እንደሚችልና አንዳንድ አተረጓጎሞች በየትኞቹ ጥንታዊ ጽሑፎች ላይ የተመሠረቱ እንደሆኑ የሚገልጹ የግርጌ ማስታወሻዎች ቀርበዋል።

የአንዳንድ ጥቅሶች አተረጓጎም አንባቢው ከዚህ በፊት ከለመደው አተረጓጎም የተለየ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ትክክለኛው አተረጓጎም የትኛው ነው? አንባቢው በባለማጣቀሻው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ ላይ የተዘረዘሩትን የጥንት ጽሑፎች እንዲመረምር፣ በመጽሐፉ መጨረሻ ላይ የሰፈረውን ተጨማሪ ማብራሪያ (አፔንዲክስ) እንዲያነብና አተረጓጎሙን ከሌሎች ትርጉሞች ጋር እንዲያወዳድር ተጋብዟል። በአብዛኛው ሌሎች ተርጓሚዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ እንዳገኙት መገንዘብ ይቻላል።

ይሖዋ የሚለው ስም በግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ለምን ገባ?

የይሖዋን ስም በግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀመ መጽሐፍ ቅዱስ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ብቻ አለመሆኑን ማወቅ ይገባል። መለኮታዊው ስም ወደ ዕብራይስጥ ቋንቋ በተተረጐሙት የግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎችና በመንፈስ አነሣሽነት ከተጻፉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በቀጥታ በተጠቀሱት ምንባቦች ውስጥ ይገኛል። ዘ ኤምፋቲክ ዳይግሎት (1864) በተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ውስጥ ይሖዋ የሚለው ስም 18 ጊዜ ይገኛል። በሌሎች 38 ቋንቋዎች የተተረጐሙ ግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች በቋንቋቸው የተለመደውን የመለኮታዊ ስም አጠራር አስገብተዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርቱ ውስጥ ለአባቱ ስም ከፍተኛ ቦታ መስጠቱ አዘወትሮ በዚህ ስም ይጠቀም እንደነበረ ይጠቁመናል። (ማቴ. 6:9፤ ዮሐ. 17:6, 26) በአራተኛ መቶ ዘመን ይኖር የነበረው ጀሮም ሐዋርያው ማቴዎስ ወንጌሉን በመጀመሪያ የጻፈው በዕብራይስጥ መሆኑን ገልጿል። ይህ ወንጌል መለኮታዊው ስም ከሚገኝባቸው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ብዙ ምንባቦችን ይጠቅሳል። ሌሎች ግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ጸሐፊዎችም ከግሪክኛው ሴፕቱጀንት ትርጉም ጠቅሰዋል። (ሴፕቱጀንት ወይም ሰባ ሊቃናት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የግሪክኛ ትርጉም ሲሆን ሥራው የተጀመረው በ280 ከዘአበ ገደማ ነበር።) በዚህ ትርጉም የመጀመሪያ ቅጂዎች ላይ መለኮታዊው ስም በዕብራይስጥ ፊደላት ተጽፎ ይገኛል። ይህንንም እስካሁን ድረስ ተጠብቀው ከቆዩት የመጽሐፉ ቁርጥራጮች መመልከት ይቻላል።

የጆርጂያ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆርጅ ሐዋርድ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ቴትራግራም የሚባሉት [መለኮታዊውን ስም የሚወክሉትን አራት የዕብራይስጥ ፊደላት] በግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ውስጥ እንዳሉ ይጻፉ ስለነበረ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ከቅዱሳን ጽሑፎች በሚጠቅሱበት ጊዜ መለኮታዊውን ስም የሚወክሉትን አራት የዕብራይስጥ ፊደላት እንዳሉ ይገልብጡአቸው ነበር ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነው።”—ጆርናል ኦቭ ቢቢሊካል ሊትሬቸር፣ መጋቢት 1977፣ ገጽ 77

አንዳንድ ጥቅሶች በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ውስጥ የማይገኙት ለምንድን ነው?

በአንዳንድ ትርጉሞች ውስጥ ሰፍረው የሚገኙት አንዳንድ ጥቅሶች አሁን በእጅ በሚገኙት የድሮ መጻሕፍት ውስጥ አይገኙም። በተጨማሪም እንደ ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል እና እንደ የካቶሊኩ ጀሩሳሌም ባይብል የመሰሉትን ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በማገናዘብ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎችም እነዚህ አጠያያቂ የሆኑ ጥቅሶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መኖር የማይገባቸው ጥቅሶች መሆናቸውን እንደተገነዘቡ መረዳት ይቻላል። አንዳንዶቹ ጸሐፊዎች በሚገለብጡበት ጊዜ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አዛውረው በስህተት የገለበጧቸው ናቸው።

አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-

‘እናንተ የራሳችሁ መጽሐፍ ቅዱስ አላችሁ’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘እርስዎ ያለዎት የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው? የእርስዎ መጽሐፍ ቅዱስ . . . ትርጉም ነው? (በቋንቋህ የተተረጐሙትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ዘርዝር።) ብዙ ትርጉሞች አሉ።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘እርስዎ በመረጡት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ብንጠቀም ደስ ይለኛል። ይሁን እንጂ ለምን በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ለመጠቀም እንደምመርጥ ሊያውቁ ይፈልጉ ይሆናል። ይህ ትርጉም ለመረዳት ቀላል ከመሆኑም ሌላ ተርጓሚዎቹ በመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋዎች የተገለጸውን ሐሳብ በትክክል ለማስተላለፍ ከፍተኛ ጥረት ስላደረጉ ነው።’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘ከአነጋገርዎ ለመረዳት እንደምችለው እቤትዎ መጽሐፍ ቅዱስ ሳይኖርዎት አይቀርም። የሚጠቀሙት የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው? . . . ፈቃድዎ ቢሆንና መጽሐፍ ቅዱስዎን ቢያመጡት?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘ሁላችንም ብንሆን የትኛውንም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ብንጠቀም ኢየሱስ በ⁠ዮሐንስ 17:3 ላይ ልንዘነጋው የማይገባንን አንድ ትልቅ ጉዳይ ገልጿል። እዚህ በራስዎ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለማየት እንደሚችሉት . . .’

ሌላ አማራጭ:- ‘ብዙ ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አሉ። ድርጅታችን መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ ሁሉ ትክክለኛውን የቅዱሳን ጽሑፎች ስሜት ለመረዳት እንዲችሉ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን እንዲያመሳክሩ ያበረታታል። ምናልባት እንደሚያውቁት መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ የተጻፈው በዕብራይስጥ፣ በአርማይክና በግሪክኛ ቋንቋዎች ነው። ስለዚህ ተርጓሚዎች መጽሐፍ ቅዱስን በቋንቋችን ለማዘጋጀት ያደረጉትን ጥረት በጣም እናደንቃለን። እርስዎ የሚጠቀሙት በየትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው?’

ተጨማሪ አማራጭ:- ‘የአምላክን ቃል የሚወዱ ሰው እንደሆኑ ከሁኔታዎ መረዳት ችያለሁ። ስለዚህ በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም እና በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መካከል ካሉት ልዩነቶች አንዱን ትልቅ ልዩነት ቢያውቁ ደስ እንደሚልዎት እርግጠኛ ነኝ። ይህም ልዩነት ቅዱሳን ጹሑፎች አዘውትረው የሚጠቅሱትን ስም የሚመለከት ነው። ይህ ስም ማን እንደሆነ ያውቃሉ?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘ይህ የተጸውኦ ስም በመጀመሪያው የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 7,000 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ እንደሚገኝ ያውቃሉ? የዚህን ስም ያህል ብዙ ጊዜ የተጠቀሰ ሌላ ስም የለም።’ (2) ‘በአምላክ የግል ስም ብንጠቀም ወይም ባንጠቀም ምን ልዩነት ያመጣል? ስሙን የማያውቁት ግን የቅርብ ወዳጄ የሚሉት ሰው ይኖራል እንዴ? . . . ከአምላክ ጋር የግል ወዳጅነትና ዝምድና እንዲኖረን ከፈለግን የመጀመሪያው እርምጃችን ስሙን ማወቅ መሆን ይኖርበታል። ኢየሱስ በ⁠ዮሐንስ 17:3, 6 ላይ የተናገረውን ልብ ይበሉ። (መዝ. 83:18 አዓት ወይም ዘጸ. 6:3 የ1879 እትም)’