የበላይ አካሉ መልእክት
ውድ ወንድሞችና እህቶች፦
ጥር 1, 2008 የወጣው የሚበረከተው የመጠበቂያ ግንብ እትም “በእምነታቸው ምሰሏቸው” በሚል ርዕስ በተከታታይ የሚወጡ ግሩም ርዕሰ ትምህርቶች እንደሚኖሩ አሳውቆን ነበር። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በዚህ ርዕስ ሥር በየሦስት ወሩ አንድ አዲስ አስደሳች ትምህርት ሲወጣ ቆይቷል!
አንባቢያን እነዚህን ተከታታይ ርዕሶች አስመልክተው ምን አስተያየት ሰጥተዋል? አንዲት አንባቢ ስለ ማርታ የወጣውን ርዕስ ካነበበች በኋላ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “እኔም ልክ እንደ እሷ ዓይነት ባሕርይ ስለነበረኝ ይህን ርዕስ ሳነብ በጣም ነው የሳቅኩት፤ ብዙውን ጊዜ ሰዎችን ማስተናገድ ያስደስተኝ ነበር፤ ሆኖም እንግዶቼን በማስተናገድ በጣም ስለምባክን ከወዳጆቼ ጋር አረፍ ብዬ መጨዋወት ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን የምዘነጋበት ጊዜ ነበር።” በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ አንዲት ወጣት ስለ አስቴር የሚናገረውን ታሪክ ካነበበች በኋላ የሚከተለውን ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ሰጥታለች፦ “ለአለባበሳችንም ሆነ በየወቅቱ ለሚወጡት ፋሽኖች ከልክ በላይ ትኩረት ወደመስጠት ልናዘነብል እንችላለን። መዘነጣችን በራሱ ስህተት አይደለም፤ ይሁን እንጂ ሚዛናዊ መሆን ይኖርብናል።” አክላም “ይሖዋ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለውስጣዊ ማንነታችን ነው” ብላለች። አንዲት እህት ስለ ሐዋርያው ጴጥሮስ የሚገልጸውን ርዕስ ካነበበች በኋላ እንደሚከተለው በማለት አድናቆቷን ገልጻለች፦ “ርዕሱን ሳነብ በጣም ከመመሰጤ የተነሳ ሁለንተናዬን ተቆጣጥሮት ነበር። ልክ እኔ ራሴ በቦታው እንዳለሁ ሆኖ ተሰምቶኝ ነበር! በታሪኩ ላይ የተገለጹት ክንውኖች ሁሉ በዓይነ ሕሊናዬ ይታዩኝ ነበር።”
እነዚህም ሆኑ ይህን ርዕስ አስመልክቶ አድናቆታቸውን በደብዳቤ የገለጹ ሌሎች በርካታ አንባቢያን ከረጅም ዘመን በፊት ሐዋርያው ጳውሎስ “ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል” በማለት የጻፈው ሐሳብ ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጠዋል። (ሮም 15:4) አዎ፣ ይሖዋ እነዚህ ዘገባዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍሩልን ያደረገው ጠቃሚ ትምህርቶችን ሊያስተምረን ስለፈለገ ነው። በእውነት ውስጥ የቆየንበት ጊዜ ምንም ያህል ይሁን ሁላችንም ከእነዚህ ዘገባዎች ትምህርት እናገኛለን።
ይህን መጽሐፍ በተቻለ መጠን ወዲያው እንድታነቡት እናበረታታችኋለን። የቤተሰብ አምልኮ በምታደርጉበት ወቅት ተጠቀሙበት፤ ልጆቻችሁ መጽሐፉን እንደሚወዱት ምንም ጥርጥር የለውም! ይህ መጽሐፍ በጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ በሚጠናበት ወቅት አንድም ሳምንት እንዳያመልጣችሁ ጥረት አድርጉ! ጊዜ ወስዳችሁ በጥንቃቄ አንብቡት። ክንውኖቹን በዓይነ ሕሊናችሁ ለመመልከት ጣሩ፤ ሕያው ሆነው ይታዩአችሁ። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባው ላይ የተጠቀሱት ባለ ታሪኮች የተሰማቸው ስሜት ይሰማችሁ፣ እነሱ ያዩትን ነገር እናንተም ለማየት ጣሩ። በሕይወታቸው ውስጥ አንድ ነገር ሲያጋጥማቸው ምን ምላሽ እንደሰጡ ስታነቡ እናንተ ብትሆኑ ምን ታደርጉ እንደነበር ለማሰብ ሞክሩ።
ይህ መጽሐፍ በመውጣቱ የተሰማንን ደስታ እንደምትጋሩን እንተማመናለን። ለእናንተም ሆነ ለቤተሰባችሁ በረከት እንደሚያስገኝላችሁም ተስፋ እናደርጋለን። ፍቅራችንና መልካም ምኞታችን ይድረሳችሁ።
የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል