በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አንድ

‘ቢሞትም እንኳ አሁንም ይናገራል’

‘ቢሞትም እንኳ አሁንም ይናገራል’

1. የአዳምንና የሔዋንን ልጆች ወደ ኤደን የአትክልት ስፍራ እንዳይገቡ ያገዳቸው ምን ነበር? አቤል ከሁሉ ይበልጥ የሚፈልገው ነገር ምንድን ነው?

 አቤል በጎቹ ኮረብታው ላይ ተረጋግተው ሲግጡ እየተመለከተ ነው። በጎቹ ካሉበት ወደ ማዶ አሻግሮ ሲመለከት ደግሞ አንድ የሚያብረቀርቅ ነገር በርቀት ይታየዋል። አቤል እዚያ ቦታ ላይ ያለው ያለማቋረጥ የሚገለባበጥ የነበልባል ሰይፍ ማንም ወደ ኤደን የአትክልት ስፍራ እንዳይገባ የሚያግድ መሆኑን ያውቃል። ወላጆቹ በአንድ ወቅት በዚያ ይኖሩ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው ወደዚያ መግባት አይችሉም። አቤል አንገቱን ወደ ላይ ቀና አድርጎ ሰማዩን እያየ ስለ ፈጣሪው ሲያስብና አመሻሹ ላይ ያለው ነፋሻማ አየር ፀጉሩን ሲያመሰቃቅለው በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። አቤል ‘በሰው ልጆችና በአምላክ መካከል የተፈጠረው ክፍተት ይጠገን ይሆን?’ የሚል ሐሳብ ወደ አእምሮው መጥቶ ሊሆን ይችላል፤ ደግሞም ከዚህ ይበልጥ የሚፈልገው ነገር የለም።

2-4. በዛሬው ጊዜ አቤል የሚያናግረን እንዴት ነው?

2 በዛሬው ጊዜ አቤል እያናገረህ ነው፤ ድምፁ ይሰማሃል? ይህ ፈጽሞ የማይመስል ነገር እንደሆነ ታስብ ይሆናል። ደግሞም የአዳም ሁለተኛ ልጅ የሆነው አቤል ከሞተ ብዙ ዘመናት ተቆጥረዋል። አካሉ ከአፈር ጋር ከተቀላቀለ ወደ 6,000 የሚጠጉ ዓመታት አልፈዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለሞቱ ሰዎች ሲናገር “ሙታን ግን ምንም አያውቁም” ይላል። (መክ. 9:5, 10) ከዚህም ሌላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኝ አቤል የተናገረው አንድም ቃል የለም። ታዲያ አቤል እንዴት ሊያናግረን ይችላል?

3 ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ስለ አቤል ሲናገር “ቢሞትም እንኳ . . . አሁንም ይናገራል” ብሏል። (ዕብራውያን 11:4ን አንብብ።) ታዲያ አቤል የሚናገረው በምን አማካኝነት ነው? በእምነቱ አማካኝነት ነው። ግሩም የሆነውን ይህን ባሕርይ ያዳበረው የመጀመሪያው ሰው አቤል ነው። አቤል እምነት ያሳየበት መንገድ እጅግ አስደናቂ ከመሆኑ የተነሳ በዚህ ረገድ ሕያው ምሳሌ ነው፤ ዛሬም የእሱን አርዓያ ልንከተል እንችላለን። እሱ ካሳየው እምነት ትምህርት የምንቀስምና ምሳሌውን ለመከተል የምንጥር ከሆነ አቤል ሲያናግረን እየሰማን ነው ሊባል ይችላል።

4 ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አቤል የሚናገረው ነገር በጣም ጥቂት ሆኖ ሳለ ስለ እሱም ሆነ ስላሳየው እምነት ያን ያህል የምንማረው ነገር ይኖራል? እስቲ እንመልከት።

‘ዓለም በተመሠረተበት’ ወቅት የኖረ ሰው

5. ኢየሱስ አቤልን “ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ” ጋር አያይዞ መጥቀሱ ምን ትርጉም አለው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

5 አቤል የተወለደው በሰው ልጆች ታሪክ መባቻ ላይ ነው። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ፣ አቤልን “ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ” ጋር አያይዞ ጠቅሶታል። (ሉቃስ 11:50, 51ን አንብብ።) ኢየሱስ እዚህ ላይ የጠቀሰው ዓለም፣ በቤዛው አማካኝነት ከኃጢአት ነፃ የመውጣት ተስፋ ያላቸውን የሰው ልጆች የሚያመለክት መሆን አለበት። አቤል ወደ ሕልውና ከመጡት ሰዎች አራተኛው ቢሆንም ይሖዋ ከኃጢአት ነፃ መውጣት እንደሚችል አድርጎ የተመለከተው የመጀመሪያው ሰው እሱ ይመስላል። a አቤል ያደገው በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩበት በሚችሉ ሰዎች መካከል እንዳልነበረ ግልጽ ነው።

6. የአቤል ወላጆች ምን ዓይነት ነበሩ?

6 የሰው ልጆች ታሪክ ገና መጀመሩ ቢሆንም እንኳ በሰው ዘር ቤተሰብ ላይ የሐዘን ድባብ አጥልቶ ነበር። የአቤል ወላጆች የሆኑት አዳምና ሔዋን ውብ ቁመናና ብሩሕ አእምሮ እንደነበራቸው ግልጽ ነው። ይሁንና በሕይወታቸው ውስጥ ከባድ ስህተት እንደፈጸሙ ያውቁ ነበር። በአንድ ወቅት ፍጹማን የነበሩ ከመሆኑም ሌላ ለዘላለም የመኖር ተስፋም ነበራቸው። የኋላ ኋላ ግን በይሖዋ አምላክ ላይ ዓምፀው መኖሪያቸው ከነበረችው ከኤደን ገነት ተባረሩ። አዳምና ሔዋን ከማንኛውም ነገር፣ ሌላው ቀርቶ የአብራካቸው ክፋይ ከሆኑት ልጆቻቸውም እንኳ በላይ የራሳቸውን ፍላጎት በማስቀደማቸው ፍጽምናቸውንም ሆነ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚያቸውን አጡ።—ዘፍ. 2:15 እስከ 3:24

7, 8. ሔዋን ቃየን በተወለደ ጊዜ ምን አለች? ይህን የተናገረችው ምን አስባ ሊሆን ይችላል?

7 አዳምና ሔዋን ይኖሩበት ከነበረው ገነት ከተባረሩ በኋላ ሕይወት አስቸጋሪ ሆነባቸው። ይሁንና የመጀመሪያ ልጃቸው የሆነው ቃየን ሲወለድ ሔዋን “በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ርዳታ ወንድ ልጅ አገኘሁ” ብላ ነበር። ሔዋን ይህን ስትናገር ይሖዋ በገነት ውስጥ የገባውን ቃል አስባ ሊሆን ይችላል፤ ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋንን ወደ ጥፋት የመራቸውን ክፉ አካል የሚያጠፋ ‘ዘር’ ስለምታስገኝ አንዲት ሴት ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ዘፍ. 3:15፤ 4:1) ሔዋን፣ በትንቢቱ ላይ የተጠቀሰችው ሴት እሷ እንደሆነችና ተስፋ የተሰጠበት ‘ዘር’ ደግሞ ቃየን እንደሆነ አስባ ይሆን?

8 ከሆነ በጣም ተሳስታለች። በተጨማሪም እሷና አዳም፣ ቃየንን ሲያሳድጉ እንዲህ ያሉ ሐሳቦችን ይነግሩት ከነበረ ቃየን ትዕቢተኛ እንዲሆን አድርገውት ሊሆን ይችላል። ከጊዜ በኋላ ሔዋን ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ይሁንና ከእሱ ጋር በተያያዘ ለቃየን እንደተናገረችው ያለ ኩራት የተንጸባረቀበት ሐሳብ አልተናገረችም። አዳምና ሔዋን ሁለተኛ ልጃቸውን አቤል ብለው የሰየሙት ሲሆን ትርጉሙም “ትንፋሽ” ወይም “ከንቱ” ማለት ሳይሆን አይቀርም። (ዘፍ. 4:2) ልጃቸውን እንዲህ ብለው መሰየማቸው አቤልን ትልቅ ተስፋ ከጣሉበት ከቃየን አሳንሰው መመልከታቸውን የሚጠቁም ይሆን? በእርግጠኝነት መናገር አንችልም።

9. በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ወላጆች ከመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ምን ሊማሩ ይችላሉ?

9 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ወላጆች ከመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ብዙ ሊማሩ የሚችሉት ነገር አለ። እናንት ወላጆች፣ የምትናገሩት ወይም የምታደርጉት ነገር ልጆቻችሁ ኩሩዎችና ራስ ወዳዶች እንዲሆኑ ወይም ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ ምኞት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ነው? ወይስ ይሖዋ አምላክን እንዲወዱና ከእሱ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ጥረት እንዲያደርጉ ታሠለጥኗቸዋላችሁ? የሚያሳዝነው ነገር የመጀመሪያዎቹ ወላጆች ይህን ኃላፊነታቸውን አልተወጡም። ያም ቢሆን ግን ልጃቸው የእነሱን አካሄድ አልተከተለም።

አቤል እምነት ማዳበር የቻለው እንዴት ነው?

10, 11. ቃየንና አቤል በምን ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበር? አቤልስ ምን ዓይነት ባሕርይ አዳበረ?

10 ሁለቱ ወንዶች ልጆች እያደጉ ሲሄዱ አዳም፣ ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ለማቅረብ የሚያስችሉ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ሳያሠለጥናቸው አልቀረም። ቃየን በግብርና ሥራ ሲሰማራ አቤል ደግሞ እረኛ ሆነ።

11 ይሁን እንጂ አቤል ከዚህ ሥራው ይበልጥ ከፍ ተደርጎ የሚታይ ነገር አከናውኗል። አቤል በጊዜ ሂደት እምነት አዳብሯል፤ ከጊዜ በኋላም ጳውሎስ ይህን ግሩም ባሕርይ አስመልክቶ ጽፏል። እስቲ አስበው፣ ለአቤል ጥሩ ምሳሌ ሊሆንለት የሚችል ሰው አልነበረም። ታዲያ በይሖዋ አምላክ ላይ እምነት ማዳበር የቻለው እንዴት ነው? ቀጥሎ የተጠቀሱት ሦስት ነገሮች አቤል ጠንካራ እምነት እንዲያዳብር ረድተውት ሊሆን ይችላል።

12, 13. አቤል የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች በትኩረት መመልከቱ እምነቱ እንዲጠናከር ረድቶት ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

12 የይሖዋ የፍጥረት ሥራ። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ምድሪቱን ስለረገማት እሾኽና አሜከላ ታበቅል ነበር፤ ይህም ለግብርናው ሥራ እንቅፋት መፍጠሩ አይቀርም። ያም ቢሆን ምድር የአቤልን ቤተሰብ በሕይወት ለማቆየት የሚያስችል የተትረፈረፈ ምርት ትሰጥ ነበር። ከዚህም ሌላ አእዋፍንና ዓሣዎችን ጨምሮ ሁሉም እንስሳት እንዲሁም ተራሮች፣ ሐይቆች፣ ወንዞች፣ ባሕሮች፣ ሰማያት፣ ደመናት፣ ፀሐይ፣ ጨረቃ እና ከዋክብት አልተረገሙም ነበር። አቤል ዓይኑ በሚያርፍበት ቦታ ሁሉ፣ የሁሉ ነገር ፈጣሪ የሆነውን የይሖዋ አምላክን ጥልቅ ፍቅር፣ ጥበብና ጥሩነት መመልከት ይችል ነበር። (ሮም 1:20ን አንብብ።) አቤል በእነዚህ ነገሮች ላይ በአድናቆት ማሰላሰሉ እምነቱ እንዲጠናከር አስተዋጽኦ እንዳደረገ ምንም ጥርጥር የለውም።

አቤል የፍጥረት ሥራዎችን መመልከቱ አፍቃሪ በሆነው ፈጣሪ ላይ እምነት ለማዳበር ጠንካራ መሠረት ሆኖለታል

13 አቤል በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ጊዜ ወስዶ ያሰላስል እንደነበረ ግልጽ ነው። አቤል መንጋውን ሲንከባከብ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። አንድ የበግ እረኛ ብዙ መጓዝ ይጠበቅበት ነበር። ለእነዚህ ገራም ፍጥረታት ለምለም ሣር፣ ንጹሕ ውኃና ጥላ ያለበት ቦታ ለማግኘት ኮረብታ መውጣት፣ ሸለቆ ማቋረጥና ወንዝ መሻገር ነበረበት። በጎች የሰው ልጅ እንዲመራቸውና ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ታስቦ የተፈጠሩ ይመስል ከአምላክ ፍጥረታት ሁሉ ይበልጥ እንክብካቤ የሚያሻቸው እነሱ እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ። አቤል፣ እሱም ቢሆን ከማንኛውም ሰው በላይ ጥበበኛና ኃያል ከሆነ አካል አመራር፣ ጥበቃና እንክብካቤ ማግኘት እንደሚያስፈልገው አስተውሎ ይሆን? አቤል እነዚህን የመሰሉ በርካታ ነገሮችን እየጠቀሰ ይጸልይ እንደነበርና ይህም እምነቱን እንዳጠናከረለት ጥርጥር የለውም።

14, 15. አቤል ይሖዋ በተናገራቸው በየትኞቹ ነገሮች ላይ ማሰላሰል ይችል ነበር?

14 ይሖዋ የተናገራቸው ነገሮች። አዳምና ሔዋን ከኤደን የአትክልት ስፍራ እንዲባረሩ ያደረጓቸውን ሁኔታዎች ለልጆቻቸው ሳይነግሯቸው አይቀሩም። በመሆኑም አቤል የሚያሰላስልባቸው በርካታ ነገሮች ነበሩት።

15 ይሖዋ ምድሪቱ የተረገመች እንደምትሆን ተናግሮ ነበር። አቤል በምድሪቱ ላይ የበቀለውን እሾኽና አሜከላ ሲመለከት አምላክ የተናገረው ነገር እንደተፈጸመ በግልጽ ማየት ችሏል። በተጨማሪም ይሖዋ፣ ሔዋን በእርግዝናዋ ወቅትም ሆነ ልጅ በምትወልድበት ጊዜ እንደምትሠቃይ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። አቤል ታናናሾቹ ሲወለዱ የዚህን ቃል ፍጻሜ ተመልክቶ መሆን አለበት። ይሖዋ፣ ሔዋን የባሏን ፍቅርና ትኩረት ከሚገባው በላይ እንደምትፈልግ፣ አዳም ደግሞ የበላይዋ እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል። አቤል ይህን አሳዛኝ እውነታ በገዛ ዓይኑ ተመልክቷል። አቤል፣ ይሖዋ የተናገረው ነገር ሁሉ እምነት የሚጣልበት መሆኑን ማስተዋል ችሎ ነበር። በመሆኑም አቤል፣ በኤደን የተፈጸመው ኃጢአት ያስከተላቸውን ጉዳቶች የሚያስተካክል ‘ዘር’ እንደሚመጣ አምላክ በሰጠው ተስፋ ላይ እምነት ለመጣል የሚያስችል በቂ ምክንያት ነበረው።—ዘፍ. 3:15-19

16, 17. አቤል ከይሖዋ መላእክት ምን ትምህርት አግኝቶ ሊሆን ይችላል?

16 የይሖዋ አገልጋዮች። አቤል በወቅቱ ከነበሩት የሰው ልጆች መካከል ጥሩ ምሳሌ ሊሆነው የሚችል ሰው አላገኘም፤ ይሁንና በዚያን ጊዜ በምድር ላይ የነበሩት የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት የሰው ልጆች ብቻ አልነበሩም። አዳምና ሔዋን ከኤደን ሲባረሩ ይሖዋ እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው ወደ ገነት መግባት እንዳይችሉ አገዳቸው። ይሖዋ የኤደንን መግቢያ እንዲጠብቁ ኪሩቤል የተባሉ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው መላእክትንና ያለማቋረጥ የሚገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን አስቀምጦ ነበር።—ዘፍጥረት 3:24ን አንብብ።

17 አቤል ልጅ እያለ እነዚያን መላእክት ሲመለከት ምን እንደሚሰማው አስብ። ኪሩቤል የሰው አካል ለብሰው ስለነበር ምን ያህል ኃያል እንደሆኑ ከቁመናቸው ማስተዋል ይችል ነበር። አቤል ያለማቋረጥ በሚገለባበጠው የነበልባል ‘ሰይፍም’ ተደንቆ መሆን አለበት። ታዲያ አቤል እያደገ ሲሄድ መላእክቱ ሥራቸው ሰልችቷቸው የተመደቡበትን ቦታ ትተው ሲሄዱ ተመልክቶ ይሆን? በፍጹም። የማሰብ ችሎታ ያላቸው እነዚህ ኃያላን ፍጥረታት ቀንና ሌሊት፣ ከዓመት እስከ ዓመት ለረጅም ዘመናት ከቦታቸው ንቅንቅ አላሉም። በመሆኑም አቤል ይሖዋ አምላክ ጻድቅና ታማኝ የሆኑ አገልጋዮች እንዳሉት መገንዘብ ይችል ነበር። የእሱ ቤተሰብ ለይሖዋ ታማኝና ታዛዥ ባይሆንም መላእክቱ እነዚህ ባሕርያት እንዳሏቸው ማየት ችሏል። የኪሩቤል ምሳሌነት የአቤልን እምነት እንዳጠናከረለት ምንም ጥርጥር የለውም።

አቤል፣ ኪሩቤል ታማኝና ታዛዥ የይሖዋ አገልጋዮች መሆናቸውን በሕይወቱ ሙሉ መመልከት ችሎ ነበር

18. በዛሬው ጊዜ እምነት ለማዳበር የሚያስችል ምን ጥሩ መሠረት አለን?

18 አቤል፣ ይሖዋ በፍጥረት ሥራዎቹ፣ በተናገራቸው ነገሮችና አገልጋዮቹ የሆኑት መላእክት በተዉት ምሳሌ አማካኝነት ስለ ራሱ በገለጻቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰሉ እምነቱ ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጓል። ታዲያ አቤል በተወው ምሳሌ አማካኝነት ዛሬም ያናግረናል መባሉ ትክክል አይደለም? በተለይም ወጣቶች፣ የቤተሰባቸው አባላት ምንም አደረጉ ምን በይሖዋ አምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ማሳደር እንደሚችሉ መገንዘባቸው ያበረታታቸዋል። በዛሬው ጊዜም በዙሪያችን ያሉት አስደናቂ የሆኑ የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች፣ በእጃችን የሚገኘው ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም በእምነታቸው ምሳሌ የሚሆኑን በርካታ ሰዎች እምነት ለማዳበር የሚያስችል ጥሩ መሠረት ይሆኑናል።

የአቤል መሥዋዕት የበለጠ የሆነው ለምንድን ነው?

19. አቤል ትልቅ ትርጉም ያለውን የትኛውን እውነታ ተገንዝቦ ነበር?

19 አቤል በይሖዋ ላይ ያለው እምነት እያደገ ሲሄድ እምነቱን በተግባር ማሳየት ፈለገ። ይሁንና አንድ ተራ ሰው ለጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ ምን መስጠት ይችላል? አምላክ ከሰው ልጆች ስጦታ መቀበል ወይም የእነሱን እርዳታ ማግኘት እንደማያስፈልገው ጥያቄ የለውም። ውሎ አድሮ አቤል ትልቅ ትርጉም ያለውን አንድ እውነታ ተገነዘበ፦ በትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ተነሳስቶ፣ ካለው ነገር ምርጡን ለይሖዋ እስካቀረበ ድረስ አፍቃሪ የሆነው አባቱ ይደሰታል።

አቤል በእምነት መሥዋዕት አቅርቧል፤ ቃየን ግን እንዲህ አላደረገም

20, 21. ቃየንና አቤል ለይሖዋ ምን መሥዋዕት አቀረቡ? ይሖዋስ ምን ተሰማው?

20 አቤል ከመንጋው መካከል የተወሰኑ በጎችን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ወሰነ። ከመንጋው መካከል በኩርና ምርጥ የሆኑትን በጎች እንዲሁም ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ ያሰበውን ሥጋ መርጦ አዘጋጀ። ቃየንም በበኩሉ የአምላክን በረከትና ሞገስ ማግኘት ስለፈለገ ካመረተው እህል መባ ለማቅረብ ወሰነ። የልቡ ዝንባሌ ግን እንደ አቤል አልነበረም። ሁለቱ ወንድማማቾች መሥዋዕታቸውን ባቀረቡበት ወቅት ይህ ልዩነት በግልጽ ታይቷል።

21 ሁለቱም የአዳም ልጆች መሥዋዕታቸውን ለማቅረብ መሠዊያ ሠርተው እንዲሁም እሳት አንድደው ሊሆን ይችላል፤ ምናልባትም ይህን ያደረጉት በወቅቱ በምድር ላይ ይሖዋን ይወክሉ የነበሩት ብቸኛ ፍጥረታት ማለትም ኪሩቤል ካሉበት ቦታ ብዙም ሳይርቁ ሊሆን ይችላል። ይሖዋም ያደረጉትን ነገር ተመልክቷል! ጥቅሱ “እግዚአብሔርም በአቤልና በመሥዋዕቱ ደስ አለው” ይላል። (ዘፍ. 4:4 የ1980 ትርጉም) መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በመሥዋዕቱ መደሰቱን ያሳየው እንዴት እንደሆነ አይናገርም።

22, 23. ይሖዋ በአቤል መሥዋዕት ደስ የተሰኘው ለምንድን ነው?

22 አምላክ በአቤል መሥዋዕት የተደሰተው ለምንድን ነው? አምላክን ያስደሰተው የመሥዋዕቱ ዓይነት ነው? እርግጥ ነው፣ አቤል መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው ሕይወት ያለውን ፍጡር ነበር፤ ይህንንም ያደረገው ውድ የሆነውን የእንስሳውን ደም በማፍሰስ ነው። አቤል እንዲህ ዓይነቱ መሥዋዕት ወደፊት ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ተደርጎ እንደሚታይ ተገንዝቦ ይሆን? አቤል ከሞተ ከበርካታ ዘመናት በኋላ ይሖዋ “የአምላክ በግ” ተብሎ የተጠራውንና ኃጢአት የሌለበት ደሙ እንደሚፈስ የተነገረለትን ፍጹም የሆነውን የገዛ ልጁን መሥዋዕት ለማመልከት እንከን የሌለበትን በግ መሥዋዕት እንደ ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሟል። (ዮሐ. 1:29፤ ዘፀ. 12:5-7) ይሁንና አቤል ስለዚህ ጉዳይ እምብዛም የሚያውቀው ነገር ያለ አይመስልም።

23 በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር ቢኖር አቤል ካለው ነገር ምርጡን ማቅረቡን ነው። ይሖዋ የተደሰተው በመሥዋዕቱ ብቻ ሳይሆን በአቤልም ጭምር ነው። አቤል መሥዋዕቱን እንዲያቀርብ ያነሳሳው ለይሖዋ ያለው ፍቅርና በእሱ ላይ ያለው ጠንካራ እምነት ነው።

24. (ሀ) ቃየን ያቀረበው መሥዋዕት በራሱ ጉድለት አልነበረበትም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ቃየን በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች የሚያንጸባርቁትን የትኛውን ዝንባሌ አሳይቷል?

24 የቃየን ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነበር። ይሖዋ “በቃየንና በመሥዋዕቱ . . . አልተደሰተም።” (ዘፍ. 4:5) ቃየን ያቀረበው መሥዋዕት በራሱ ምንም ጉድለት አልነበረበትም፤ አምላክ ከጊዜ በኋላ የሰጠው ሕግ የምድርን ፍሬ መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ እንደሚቻል ይናገራል። (ዘሌ. 6:14, 15) ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቃየን ሲናገር ‘ሥራው ክፉ እንደነበር’ ይገልጻል። (1 ዮሐንስ 3:12ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜ እንዳሉ ብዙ ሰዎች ሁሉ ቃየንም ለአምላክ ያደረ መስሎ መታየቱ ብቻ በቂ እንደሆነ ሳያስብ አልቀረም። ብዙም ሳይቆይ ግን ቃየን በይሖዋ ላይ እምነት እንደሌለውና አምላክን ከልቡ እንደማይወደው በድርጊቱ አሳይቷል።

25, 26. ይሖዋ ለቃየን ምን ማስጠንቀቂያ ሰጠው? ቃየን ግን ምን አደረገ?

25 ቃየን፣ የአምላክን ሞገስ እንዳላገኘ ሲመለከት ከአቤል ምሳሌ ለመማር ሞክሮ ይሆን? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ ወንድሙን አጥብቆ ጠላው። ይሖዋ በቃየን ልብ ውስጥ ያለውን ስላስተዋለ በትዕግሥት ሊያስረዳው ሞከረ። እንዲያውም አካሄዱ ከባድ ኃጢአት ወደመፈጸም ሊመራው እንደሚችል አስጠነቀቀው፤ አካሄዱን ካስተካከለ ደግሞ ‘ተቀባይነት እንደሚያገኝ’ ተስፋ ሰጠው።—ዘፍ. 4:6, 7

26 ቃየን ግን አምላክ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ አልሰማም። ከዚህ ይልቅ ክፉ ነገር ያደርግብኛል ብሎ ያልጠረጠረውን ታናሽ ወንድሙን አብሮት ወደ ሜዳ እንዲሄድ ጠየቀው። በዚያም ቃየን አቤልን ደብድቦ ገደለው። (ዘፍ. 4:8) በመሆኑም አቤል በእምነቱ ምክንያት ስደት የደረሰበት የመጀመሪያው ሰማዕት ነው ማለት እንችላለን። አቤል ቢሞትም ታሪኩ ግን በዚህ አላበቃም።

27. (ሀ) አቤል ከሞት እንደሚነሳ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) አቤልን ለማግኘት ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

27 በምሳሌያዊ አነጋገር የአቤል ደም የበቀል እርምጃ እንዲወሰድለት ወይም ፍትሕ እንዲሰጠው ወደ ይሖዋ አምላክ ጮዃል። አምላክም ክፉ የሆነው ቃየን ለፈጸመው ወንጀል ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ በማድረግ ፍትሕ እንዲፈጸም አድርጓል። (ዘፍ. 4:9-12) ከዚህም በላይ አቤል ስላሳየው እምነት የሚገልጸው ዘገባ ዛሬም ድረስ እያናገረን ያለ ያህል ነው። ምናልባት አቤል የኖረው ከ100 ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ሊሆን ይችላል፤ ይህ ደግሞ በወቅቱ የነበሩት ሰዎች ከሚኖሩበት ዕድሜ አንጻር ሲታይ አጭር ነው፤ ያም ሆኖ አቤል ሕይወቱን በሚገባ ተጠቅሞበታል። በሰማይ ያለው አባቱ ይሖዋ እንደሚወደውና የእሱ ሞገስ እንዳልተለየው ያውቅ ነበር። (ዕብ. 11:4) በመሆኑም ወደር የለሽ የሆነ የማስታወስ ችሎታ ያለው ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይረሳውና ገነት በሆነችው ምድር ላይ ከሞት እንደሚያስነሳው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዮሐ. 5:28, 29) ታዲያ አቤል ከሞት ሲነሳ በዚያ ትገኝ ይሆን? አቤል ሲናገር ለማዳመጥና ታላቅ እምነት በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ ካደረግክ በዚያ መገኘት ትችላለህ።

a ‘ዓለም ሲመሠረት’ የሚለው አገላለጽ ዘር መዝራትን ይኸውም መዋለድን ያመለክታል፤ በመሆኑም ይህ አገላለጽ መጀመሪያ ከተወለደው የሰው ልጅ ጋር የተያያዘ መሆን አለበት። ታዲያ ኢየሱስ የአዳምና የሔዋን የመጀመሪያ ልጅ የሆነውን ቃየንን ሳይሆን አቤልን ‘ከዓለም መመሥረት’ ጋር አያይዞ የጠቀሰው ለምንድን ነው? ከሁኔታዎች መመልከት እንደሚቻለው ቃየን ያደረገው ውሳኔና የፈጸመው ድርጊት በይሖዋ አምላክ ላይ ሆን ብሎ ከማመፅ አይተናነስም። በመሆኑም እንደ ወላጆቹ ሁሉ ቃየንም የኃጢአት ይቅርታም ሆነ ትንሣኤ የሚያገኝ አይመስልም።