በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 5

የአምላክን ግሩም ባሕርያት ማወቅ

የአምላክን ግሩም ባሕርያት ማወቅ

በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የአምላክ ድንቅ ባሕርያት ተገልጸዋል፤ ይህ መሆኑም እሱን እንድናውቀው ያስችለናል። ለምሳሌ ያህል፣ ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ አምላክ አራት ዋና ዋና ባሕርያት ማለትም ስለ ኃይሉ፣ ፍትሑ፣ ጥበቡና ፍቅሩ ይናገራሉ። እስቲ እነዚህን ባሕርያት አንድ በአንድ እንመልከት።

ኃይሉ ገደብ የለውም

የአምላክ ኃይል ታላቅ ነው

ይሖዋ ለአብርሃም (ለኢብራሂም) “እኔ ሁሉን ቻይ አምላክ ነኝ” በማለት ነግሯቸዋል። (ዘፍጥረት 17:⁠1) በኃይል ረገድ አምላክን የሚወዳደር የለም፤ ኃይሉም ማከናወን የማይችለው ነገር የለም፤ ደግሞም የማይነጥፍ ነው። አምላክ መላውን አጽናፈ ዓለም የፈጠረው በኃይሉ ነው።

አምላክ ኃይሉን ፈጽሞ ያለአግባብ አይጠቀምበትም። ምንጊዜም ቢሆን ኃይሉን የሚጠቀምበት በገደብና በዓላማ ነው። ኃይሉን የሚጠቀመው ከፍትሑ፣ ከጥበቡና ከፍቅሩ ጋር ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ነው።

ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ለመርዳት ሲል ኃይሉን ይጠቀማል። “በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን ያሳይ ዘንድ የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመላለሳሉ።” (2 ዜና መዋዕል 16:⁠9) ታዲያ እንዲህ ያለውን ኃያል ሆኖም አሳቢ አምላክ ለመቅረብ አትገፋፋም?

የፍትሕ አምላክ

“ይሖዋ ፍትሕን ይወዳል።” (መዝሙር 37:​28) አምላክ የሚያደርገው ነገር በሙሉ ትክክለኛና ፍትሐዊ ነው፤ እሱ ራሱ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ይጠብቃል።

አምላክ አያዳላም

አምላክ ኢፍትሐዊነትን ይጠላል። እሱ “ለማንም የማያዳላና ጉቦ የማይቀበል አምላክ ነው።” (ዘዳግም 10:​17) ሌሎችን የሚጨቁኑ ሰዎችን ይቃወማል፤ እንዲሁም “መበለቲቱን ወይም አባት የሌለውን ልጅ” ጨምሮ ለጥቃት የተጋለጡ ሰዎችን ለመርዳት ሲል እርምጃ ይወስዳል። (ዘፀአት 22:​22) አምላክ ሁሉንም ሰዎች የሚመለከተው በእኩል ዓይን ነው። “አምላክ [አያዳላም]፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።”​—⁠የሐዋርያት ሥራ 10:​34, 35

የይሖዋ ፍትሕ ሚዛኑን የጠበቀ ነው። በጣም ልል ወይም በጣም ጥብቅ አይደለም። ንስሐ የማይገቡ ጥፋተኞችን የሚቀጣ ቢሆንም ንስሐ ለሚገቡት ምሕረት ያደርግላቸዋል። “ይሖዋ መሐሪና ሩኅሩኅ፣ ለቁጣ የዘገየ እንዲሁም ታማኝ ፍቅሩ የበዛ ነው። እሱ ሁልጊዜ ስህተት አይፈላልግም፤ ለዘላለምም ቂም አይዝም። እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፤ ለበደላችን የሚገባውንም ብድራት አልከፈለንም።” (መዝሙር 103:​8-10) በተጨማሪም አምላክ አገልጋዮቹ በታማኝነት ያከናወኑትን ሥራ አይረሳም፤ እንዲሁም ወሮታቸውን ይከፍላቸዋል። ታዲያ እንዲህ ያለውን ፍትሐዊ አምላክ ልትተማመንበት አይገባም?

የጥበብ አምላክ

ቅዱሳን መጻሕፍት የአምላክን ጥበብ ይዘዋል

ይሖዋ የጥበብ ሁሉ ምንጭ ነው። “የአምላክ ብልጽግና፣ ጥበብና እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው!” (ሮም 11:​33) አምላክን በጥበቡ የሚስተካከለው የለም፤ ለጥበቡም ዳርቻ የለውም።

አምላክ የፈጠራቸው ነገሮች የእሱን ጥበብ በግልጽ ያሳያሉ። አንድ የመዝሙር መጽሐፍ ጸሐፊ “ይሖዋ ሆይ፣ ሥራህ ምንኛ ብዙ ነው! ሁሉንም በጥበብ ሠራህ” ብሏል።​—⁠መዝሙር 104:​24

የአምላክ ጥበብ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥም ተንጸባርቋል። ንጉሥ ዳዊት (ዳውድ) “የይሖዋ ማሳሰቢያ አስተማማኝ ነው፤ ተሞክሮ የሌለውን ጥበበኛ ያደርጋል” በማለት ጽፈዋል። (መዝሙር 19:⁠7) እስቲ አስበው፤ አንተም ተዝቆ ከማያልቀው ከዚህ የጥበብ ጎተራ ብዙ ጥቅም ማግኘት ትችላለህ! ታዲያ ይህን አጋጣሚ ለምን አትጠቀምበትም?

“አምላክ ፍቅር ነው”

የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይ ፍቅር ነው። “አምላክ ፍቅር ነው” በማለት ቅዱሳን መጻሕፍት ይነግሩናል። (1 ዮሐንስ 4:⁠8) አምላክ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ ነው።

አምላክ ስፍር ቁጥር በሌላቸው መንገዶች ፍቅሩን አሳ​ይቶናል። መልካም ነገሮችን ይሰጠናል። ‘ከሰማይ ዝናብ በማዝነብና ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠት እንዲሁም የተትረፈረፈ ምግብ በማቅረብና ልባችንን በደስታ በመሙላት መልካም ነገር አድርጎልናል።’ (የሐዋርያት ሥራ 14:​17) በእርግጥም “መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ ከላይ ነው፤ ይህ የሚወርደው ከሰማይ ብርሃናት አባት [ነው]።” (ያዕቆብ 1:​17) አምላክ በዋጋ ሊተመን የማይችል ውድ ስጦታ ማለትም ቅዱስ መጽሐፉን ሰጥቶናል፤ በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት ስለ ራሱ እውነቱን የገለጸልን ከመሆኑም ሌላ ፍቅር የሚንጸባረቅባቸውን ሕጎቹንና መመሪያዎቹን ያስተምረናል። ኢየሱስ (ኢሳ) በጸሎቱ ላይ “ቃልህ እውነት ነው” በማለት ተናግሯል።​—⁠ዮሐንስ 17:​17

አምላክ የፈጠራቸውን ነገሮች ስንመለከት በጥበቡ እንደመማለን

በተጨማሪም አምላክ መከራ ሲደርስብን ይረዳናል። “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል። ጻድቁ እንዲወድቅ ፈጽሞ አይፈቅድም።” (መዝሙር 55:​22) በሌላ በኩል ደግሞ ኃጢአታችንን ይቅር ይላል። የአምላክ ቃል እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጥሩ ነህና፤ ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ፤ አንተን ለሚጠሩ ሁሉ የምታሳየው ታማኝ ፍቅር ወሰን የለውም።” (መዝሙር 86:⁠5) አልፎ ተርፎም ለዘላለም መኖር የምንችልበትን ዝግጅት አድርጎልናል። ‘እንባን ሁሉ ከዓይናችን ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።’ (ራእይ 21:⁠4) ታዲያ አምላክ ላሳየህ ፍቅር ምን ምላሽ ትሰጣለህ? አንተም በአጸፋው ለእሱ ያለህን ፍቅር ለማሳየት አትነሳሳም?

ከአምላክ ጋር ተቀራረብ

ጸሎትና በአምላክ ባሕርያት ላይ ማሰላሰል ከአምላክ ጋር እንድትቀራረብ ይረዱሃል

አምላክ እሱን በደንብ እንድታውቀው ይፈልጋል። ቃሉ ‘ወደ አምላክ ቅረብ፤ እሱም ወደ አንተ ይቀርባል’ በማለት ያበረታታሃል። (ያዕቆብ 4:⁠8) አምላክ ታማኝ የነበሩትን ነቢዩ አብርሃምን “ወዳጄ” ብሎ ጠርቷቸዋል። (ኢሳይያስ 41:⁠8) ይሖዋ አንተም ወዳጁ እንድትሆን ይፈልጋል።

ስለ አምላክ ይበልጥ እያወቅህ ስትሄድ ወደ እሱ ይበልጥ ትቀርባለህ፤ ይህም ደስታህ እንዲጨምር ያደርጋል። ‘በይሖዋ ሕግ ደስ የሚለውና ሕጉን በቀንና በሌሊት የሚያነብ’ ሰው “ደስተኛ” ነው። (መዝሙር 1:​1, 2) በመሆኑም ቅዱሳን መጻሕፍትን ማጥናትህን ቀጥል። በአምላክ ባሕርያትና ሥራዎች ላይ አሰላስል። የምትማረውን ነገር በሥራ ላይ በማዋል አምላክን እንደምትወደው አሳይ። “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነውና፤ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባድ አይደሉም።” (1 ዮሐንስ 5:⁠3) እንግዲያው ልክ እንደ መዝሙራዊው አንተም “ይሖዋ ሆይ፣ መንገድህን አሳውቀኝ፤ ጎዳናህንም አስተምረኝ። . . . በእውነትህ እንድመላለስ አድርገኝ” ብለህ ጸልይ። (መዝሙር 25:​4, 5) እንዲህ የምታደርግ ከሆነ አምላክ “ከእያንዳንዳችን የራቀ” እንዳልሆነ ትገነዘባለህ።​—⁠የሐዋርያት ሥራ 17:​27