የአምላክን ቃል በድፍረት መናገርህን ቀጥል
ምዕራፍ አሥራ ዘጠኝ
የአምላክን ቃል በድፍረት መናገርህን ቀጥል
1. (ሀ) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያውጁት የነበረው ምሥራች ምንድን ነው? ሆኖም አንዳንድ አይሁዶች ምን ምላሽ ሰጡ? (ለ) ምን ጥያቄዎች ልናነሳ እንችላለን?
ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደፊት በመላዋ ምድር ላይ የሚገዛ ንጉሥ ሆኖ ተቀብቷል። ኢየሱስ በሃይማኖታዊ ጠላቶቹ ቆስቋሽነት የተገደለ ቢሆንም ይሖዋ ከሞት አስነስቶታል። በመሆኑም በኢየሱስ አማካኝነት የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚቻልበት በር ተከፍቷል። ሆኖም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህን ምሥራች በይፋ በማወጃቸው ስደት ተነሣ። አንዳንዶቹ ወደ ወኅኒ የተጣሉ አልፎ ተርፎም የተገረፉ ሲሆን ዳግመኛ ስለ ኢየሱስ እንዳይናገሩም ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 4:1-3, 17፤ 5:17, 18, 40) ታዲያ ምን ያደርጉ ይሆን? አንተ ብትሆን ምን ታደርግ ነበር? በድፍረት መመሥከርህን ትቀጥል ነበር?
2. (ሀ) በዘመናችን መታወጅ ያለበት አስደናቂ ምሥራች ምንድን ነው? (ለ) ምሥራቹን የመስበክ ኃላፊነት ያለበት ማን ነው?
2 በ1914 የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ‘በጠላቶቹ መካከል’ ለመግዛት በሰማይ ዙፋኑን ያዘ። (መዝሙር 110:2) ከዚያም ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ ምድር ተጣሉ። (ራእይ 12:1-5, 7-12) በዚህ ጊዜ የዚህ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ጀመሩ። ይህ ጊዜ ሲያበቃ አምላክ በሰይጣን የሚተዳደረውን መላውን ሥርዓት ይደመስሰዋል። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 24:21) ከጥፋቱ የሚተርፉ ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይኖራቸዋል። ይህን የምሥራች ተቀብለህ ከሆነ አንተም ለሌሎች ለመንገር መፈለግህ አይቀርም። (ማቴዎስ 24:14) ይሁንና ምን ምላሽ ሊያጋጥምህ ይችላል?
3. (ሀ) ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ምን ምላሽ ይሰጣሉ? (ለ) የትኛውን ጥያቄ ራሳችንን መጠየቅ አለብን?
3 የመንግሥቱን ምሥራች በምታውጅበት ጊዜ አንዳንዶች በደስታ ቢቀበሉህም አብዛኞቹ ሰዎች ግን ግድ የለሾች ይሆናሉ። (ማቴዎስ 24:37-39) አንዳንዶች ሊያፌዙብህ ወይም ሊቃወሙህ ይችላሉ። ኢየሱስ ከገዛ ቤተሰቦችህና ዘመዶችህ ተቃውሞ ሊነሳብህ እንደሚችል አስጠንቅቋል። (ሉቃስ 21:16-19) ከዚህም በተጨማሪ በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት ተቃውሞ ሊያጋጥምህ ይችላል። እንዲያውም በአንዳንድ አገሮች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ መንግሥታዊ እገዳ ተጥሏል። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ የአምላክን ቃል በድፍረት በመናገር ‘በእምነት ትጸናለህ’?—1 ቆሮንቶስ 16:13
በራሳችን ኃይል አለመመካት
4. (ሀ) ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች መሆናችንን ለማስመሥከር የሚያስችለን መሠረታዊ ብቃት ምንድን ነው? (ለ) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በጣም አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?
4 አንድ ሰው የይሖዋ ታማኝ አገልጋይ መሆን ይችል ዘንድ በይሖዋ ዝግጅቶች ላይ መታመኑ በጣም አስፈላጊ ነው። ከእነዚህ ዝግጅቶች አንዱ የጉባኤ ስብሰባ ነው። ቅዱሳን ጽሑፎች ስብሰባዎችን ቸል እንዳንል አጥብቀው ያሳስቡናል። (ዕብራውያን 10:23-25) የይሖዋ ታማኝ ምሥክሮች ሆነው ማገልገላቸውን የቀጠሉ ሁሉ ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር በስብሰባዎች ላይ አዘውትረው ለመገኘት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች ያለን እውቀት እያደገ ይሄዳል። ከዚህም በተጨማሪ በስፋት የሚታወቁትን እውነቶች በተመለከተ ያለን ግንዛቤ የሚጨምር ከመሆኑም በላይ እነዚህን እውነቶች ሥራ ላይ ማዋል የምንችልባቸው መንገዶች ይበልጥ ግልጽ እየሆኑልን ይሄዳሉ። ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር ይበልጥ በአምልኮ አንድነት እንተሳሰራለን፤ እንዲሁም የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስችል ብርታት እናገኛለን። የይሖዋ መንፈስ በጉባኤው በኩል አመራር የሚሰጠን ሲሆን ኢየሱስም በዚህ መንፈስ አማካኝነት በመካከላችን ይገኛል።—ማቴዎስ 18:20፤ ራእይ 3:6
5. የይሖዋ ምሥክሮች በእገዳ ሥር በሚሆኑበት ጊዜ ስብሰባቸውን የሚያደርጉት እንዴት ነው?
5 በሁሉም ስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ ትገኛለህ? እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ የምታገኘውን ትምህርት በሥራ ላይ ለማዋል ትጥራለህ? የይሖዋ ምሥክሮች በእገዳ ሥር በሚሆኑበት ጊዜ በአነስተኛ ቡድን ተከፋፍለው በግል ቤቶች ውስጥ ለመሰብሰብ ይገደዳሉ። ስብሰባዎቹ የሚደረጉባቸው ቦታዎችም ሆኑ ጊዜያት ሊለዋወጡ ስለሚችሉ ስብሰባዎቹ ላይ መገኘት ሁልጊዜ አመቺ ላይሆን ይችላል፤ አንዳንዶቹ ስብሰባዎች የሚካሄዱት ከመሸ በኋላ ሊሆን ይችላል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የማይመች ወይም አደገኛ ሊሆን ቢችልም ታማኝ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።
6. በይሖዋ እንደምንታመን የምናሳየው እንዴት ነው? ይህስ በድፍረት መስበካችንን እንድንቀጥል ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
6 የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልገን በመገንዘብ አዘውትረን ከልብ የምንጸልይ ከሆነ በይሖዋ ላይ ያለን እምነት እየጠነከረ ይሄዳል። አንተ ይህን ታደርጋለህ? ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት በተደጋጋሚ ይጸልይ ነበር። (ሉቃስ 3:21፤ 6:12, 13፤ 22:39-44) በተጨማሪም ከመሰቀሉ በፊት በነበረው ምሽት ደቀ መዛሙርቱን “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፤ ጸልዩም” ሲል አጥብቆ አሳስቧቸዋል። (ማርቆስ 14:38) ለመንግሥቱ መልእክት ጥሩ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች እምብዛም የማይገኙ ከሆነ ለአገልግሎት ያለን ቅንዓት ሳናውቀው እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል። ሰዎች የሚያፌዙብን ወይም የሚቃወሙን ከሆነ ከችግር ለመሸሽ ስንል የስብከት ሥራችንን ለማቆም ልንፈተን እንችላለን። ሆኖም የአምላክ መንፈስ በድፍረት መስበካችንን እንድንቀጥል ይረዳን ዘንድ አጥብቀን የምንጸልይ ከሆነ ለእንዲህ ዓይነቱ ፈተና አንሸነፍም።—ሉቃስ 11:13፤ ኤፌሶን 6:18-20
በድፍረት ስለመሠከሩ ሰዎች የሚገልጽ ታሪክ
7. (ሀ) በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ያለው ታሪክ ትኩረታችንን በእጅጉ የሚስበው ለምንድን ነው? (ለ) ትምህርቱ እንዴት ሊጠቅመን እንደሚችል ጎላ አድርገህ በመግለጽ ከአንቀጹ በታች የቀረቡትን ጥያቄዎች መልስ።
7 በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ታሪክ የሁላችንንም ትኩረት በእጅጉ የሚስብ ነው። እንደ እኛው ዓይነት ስሜት የነበራቸው ሐዋርያትና ሌሎች የጥንት ደቀ መዛሙርት ያጋጠሟቸውን እንቅፋቶች በመወጣት ደፋርና ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል። የሚከተሉትን ጥያቄዎችና ጥቅሶች በመጠቀም ከዚህ ታሪክ መካከል የተወሰነውን እንመርምር። ይህን በምናደርግበት ጊዜ አንተ በግልህ ከምታነበው ነገር እንዴት ልትጠቀም እንደምትችል አስብ።
ሐዋርያት ከፍተኛ ትምህርት የቀሰሙ ሰዎች ነበሩ? በተፈጥሯቸው የመጣው ቢመጣ ፍርሃት የሚባል ነገር የማይሰማቸው ግለሰቦችስ ነበሩ? (ዮሐንስ 18:17, 25-27፤ 20:19፤ የሐዋርያት ሥራ 4:13)
ጴጥሮስ በአምላክ ልጅ ላይ በፈረደው የአይሁድ ፍርድ ቤት ቀርቦ በድፍረት እንዲናገር የረዳው ምንድን ነው? (ማቴዎስ 10:19, 20፤ የሐዋርያት ሥራ 4:8)
ሐዋርያት በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ከመቅረባቸው በፊት በነበሩት ሳምንታት ምን ሲያደርጉ ነበር? (የሐዋርያት ሥራ 1:14፤ 2:1, 42)
ገዥዎቹ ሐዋርያቱን በኢየሱስ ስም መስበካቸውን እንዲያቆሙ ባዘዟቸው ጊዜ ጴጥሮስና ዮሐንስ ምን መልስ ሰጡ? (የሐዋርያት ሥራ 4:19, 20)
ሐዋርያት ከተለቀቁም በኋላ የማንን እርዳታ ለማግኘት ጥረዋል? የጸለዩትስ ስደቱ እንዲቆምላቸው ነው ወይስ ምን እንዲደረግላቸው? (የሐዋርያት ሥራ 4:24-31)
ተቃዋሚዎች የስብከቱን ሥራ ለማስቆም በሞከሩበት ጊዜ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ድጋፍ የሰጠው በምን መንገድ ነው? (የሐዋርያት ሥራ 5:17-20)
ሐዋርያት ከእስር እንዲፈቱ የተደረገበትን ምክንያት እንደተረዱ ያሳዩት እንዴት ነው? (የሐዋርያት ሥራ 5:21, 41, 42)
ብዙዎቹ ደቀ መዛሙርት በስደት የተነሳ ወደተለያዩ ቦታዎች በተበተኑበት ጊዜም እንኳ ምን ማድረጋቸውን ቀጥለዋል? (የሐዋርያት ሥራ 8:3, 4፤ 11:19-21)
8. የጥንቶቹ ደቀ መዛሙርት ያከናወኑት አገልግሎት ምን አስደሳች ውጤት አስገኝቷል? እኛስ በዚህ ሥራ ተካፋይ የሆንነው እንዴት ነው?
8 የምሥራቹ ስብከት ሥራ ከንቱ ሆኖ አልቀረም። በ33 በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት 3,000 ገደማ የሚሆኑ ደቀ መዛሙርት ተጠምቀዋል። “ብዙ ወንዶችና ሴቶችም ከጊዜ ወደ ጊዜ በጌታ እያመኑ ወደ እነርሱ ይጨመሩ ነበር።” (የሐዋርያት ሥራ 2:41፤ 4:4፤ 5:14) ውሎ አድሮ የአምላክ ሕዝብ ኃይለኛ አሳዳጅ የነበረው የጠርሴሱ ሳውል እንኳ ሳይቀር ክርስቲያን የሆነ ሲሆን እውነትን በድፍረት መመሥከር ጀምሯል። ይህ ሰው ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ ተጠርቷል። (ገላትያ 1:22-24) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተጀመረው ሥራ አልቆመም። በዚህ የመጨረሻ ዘመን ሥራው ይበልጥ እየተፋጠነ ከመሆኑም ሌላ ምሥራቹ በመላዋ ምድር ተዳርሷል። እኛም በዚህ ሥራ የመካፈል መብት ያለን ሲሆን በሥራው በምንካፈልበት ጊዜም ከእኛ በፊት የነበሩት ታማኝ ምሥክሮች ከተዉት ምሳሌ መማር እንችላለን።
9. (ሀ) ጳውሎስ ምሥክርነት ለመስጠት ምን አጋጣሚዎችን ይጠቀም ነበር? (ለ) የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ለማዳረስ በየትኞቹ መንገዶች ትጠቀማለህ?
9 ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገልጸውን እውነት ሲማር ምን አደረገ? “ወዲያውም፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን . . . መስበክ ጀመረ።” (የሐዋርያት ሥራ 9:20) አምላክ ላደረገለት ይገባኛል የማይለው ደግነት አመስጋኝ ከመሆኑም በላይ እሱ የደረሰው ምሥራች ሰዎች ሁሉ ሊደርሳቸው እንደሚገባ ተገንዝቧል። ጳውሎስ አይሁዳዊ የነበረ ሲሆን በዘመኑ በነበረው ልማድ መሠረት ምሥክርነት ለመስጠት ወደ ምኩራቦች ይሄድ ነበር። በተጨማሪም ከቤት ወደ ቤት ይሰብክ የነበረ ከመሆኑም በላይ በገበያ ቦታ ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ጥሩ ውይይት ማድረግ ችሏል። ከዚህም ሌላ ወደ አዳዲስ ክልሎች በመሄድ ምሥራቹን ለመስበክ ፈቃደኛ ሆኗል።—የሐዋርያት ሥራ 17:17፤ 20:20፤ ሮሜ 15:23, 24
10. (ሀ) ጳውሎስ ይመሠክር የነበረበት መንገድ ደፋር ብቻ ሳይሆን አስተዋይም እንደነበረ የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ለዘመዶቻችን፣ ለሥራ ባልደረቦቻችን ወይም አብረውን ለሚማሩ በምንመሠክርበት ጊዜ የጳውሎስን ባሕርያት ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?
10 ጳውሎስ ደፋር ብቻ ሳይሆን አስተዋይም ነበር፤ እኛም እንዲሁ መሆን ይኖርብናል። አይሁዶችን ሲያገኝ አምላክ ለቀድሞ አባቶቻቸው የገባውን ቃል መሠረት አድርጎ ያነጋግራቸው ነበር። ግሪኮችን ሲያገኝ ደግሞ የሚያውቋቸውን ነገሮች መሠረት አድርጎ ያወያያቸው ነበር። አንዳንድ ጊዜም እሱ ራሱ ወደ እውነት የመጣበትን ሁኔታ ለሌሎች ምሥክርነት ለመስጠት እንደ መሣሪያ አድርጎ ተጠቅሞበታል። “ይህን ሁሉ የማደርገው፣ ከወንጌል በረከት [“ከሌሎች ጋር፣” NW] እካፈል ዘንድ፣ ስለ ወንጌል ብዬ ነው” ሲል ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 9:20-23፤ የሐዋርያት ሥራ 22:3-21
11. (ሀ) ጳውሎስ በተደጋጋሚ ጊዜያት ከተቃዋሚዎቹ ጋር ላለመጋጨት ሲል ምን አድርጓል? (ለ) እኛም ጳውሎስ የወሰደውን ዓይነት የጥበብ እርምጃ ልንወስድ የምንችለው ምን ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ነው? እንዴትስ? (ሐ) በድፍረት መናገራችንን እንድንቀጥል የሚረዳንን ኃይል የምናገኘው ከየት ነው?
11 ጳውሎስ ተቃውሞ ሲያጋጥመው ለተወሰነ ጊዜ ወደ ሌላ አካባቢ ሄዶ መስበክ የተሻለ እንደሆነ ከተሰማው ከተቃዋሚዎቹ ጋር በተደጋጋሚ ከመጋጨት ይልቅ ይህን ማድረግ ይመርጥ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 14:5-7፤ 18:5-7፤ ሮሜ 12:18) ሆኖም በምሥራቹ አፍሮ አያውቅም። (ሮሜ 1:16) ጳውሎስ ተቃዋሚዎቹ ያደርሱበት የነበረው እንግልት አልፎ ተርፎም ድብደባ ባያስደስተውም በስብከቱ ሥራ ለመቀጠል የሚያስችል ‘ድፍረት ከአምላክ አግኝቷል።’ “መልእክቱ በእኔ አማካይነት በሙላት እንዲሰበክ . . . ጌታ በአጠገቤ ቆሞ አበረታኝ” ሲል ተናግሯል። (1 ተሰሎንቄ 2:2፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:17) የክርስቲያን ጉባኤ ራስ የሆነው ኢየሱስ በእኛ ዘመን እንደሚሠራ አስቀድሞ የተነበየለትን ሥራ ለማከናወን የሚያስችለንን ኃይል መስጠቱን ቀጥሏል።—ማርቆስ 13:10
12. ክርስቲያናዊ ድፍረት እንዳለን የምናሳየው እንዴት ነው? ለእንዲህ ዓይነቱ ድፍረት መሠረት የሚሆነንስ ምንድን ነው?
12 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስም ሆነ ሌሎች የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች እንዳደረጉት የአምላክን ቃል በድፍረት መናገራችንን እንድንቀጥል የሚያደርገን በቂ ምክንያት አለን። እንዲህ ሲባል የሌሎችን ስሜት ግምት ውስጥ አናስገባም ወይም ፍላጎት የሌላቸው ሰዎች መልእክቱን በግድ እንዲቀበሉ ለማድረግ እንሞክራለን ማለት አይደለም። ሆኖም ሰዎች ለመልእክቱ ግድ የለሾች ስለሆኑ ብቻ መስበካችንን አናቆምም ወይም ለተቃውሞ አንንበረከክም። ኢየሱስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም መላዋን ምድር ለመግዛት ትክክለኛ መብት ያለው የአምላክ መንግሥት መሆኑን እናሳውቃለን። የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ የሆነው የይሖዋ ወኪሎች ስለሆንና የምናውጀው የእኛን ሳይሆን የእሱን መልእክት በመሆኑ በልበ ሙሉነት እንናገራለን። በተጨማሪም ይሖዋን እንድናወድሰው የሚያነሳሳን ዋነኛ ምክንያት ለእሱ ያለን ፍቅር መሆን አለበት።—ፊልጵስዩስ 1:27, 28፤ 1 ተሰሎንቄ 2:13
የክለሳ ውይይት
• በተቻለ መጠን ላገኘነው ሰው ሁሉ የመንግሥቱን መልእክት መንገራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሆኖም ምን ምላሽ ሊያጋጥመን ይችላል?
• ይሖዋን የምናገለግለው በራሳችን ኃይል ተመክተን እንዳልሆነ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
• ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ምን ጠቃሚ ትምህርቶች እናገኛለን?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 173 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
እንደ ጥንቶቹ ሁሉ ዛሬ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮችም የአምላክን ቃል በድፍረት ይናገራሉ