በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለፍቅርና ለመልካም ሥራ የሚያነቃቁ ስብሰባዎች

ለፍቅርና ለመልካም ሥራ የሚያነቃቁ ስብሰባዎች

ለፍቅርና ለመልካም ሥራ የሚያነቃቁ ስብሰባዎች

የቀድሞ ክርስቲያኖች ትምህርት ለማግኘትና እርስበርስ ተገናኝተው ለመተናነጽ አብዛኛውን ጊዜ በግል ቤቶች ይሰበሰቡ ነበር። በአሁኑ ጊዜም የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በሳምንት ሦስት ጊዜ ይሰበሰባሉ። ከእነዚህ ስብሰባዎች በአንዱ እንድትገኝ ተጋብዘሃል። ስብሰባዎቻቸው የሚደረጉት የቅዳሴ ወይም ሌላ ዓይነት የአምልኮ ሥርዓት ለመፈጸም ሳይሆን መለኰታዊ ሥልጠና ወይም ትምህርት ለመስጠት ነው። የጉባኤ ስብሰባዎች የሚጀመሩትና የሚዘጉት በመዝሙርና በጸሎት ነው። በስብሰባው ለመገኘት ምንም ዓይነት የመግቢያ ዋጋ አይከፈልም። መዋጮ ለመሰብሰብም ሙዳየ ምፅዋት አይዞርም።—ሥራ 4:23–31፤ 14:22፤ 15:32, 35፤ ሮሜ 16:5፤ ቆላስይስ 4:15

ምናልባት ለመጀመሪያ ጊዜ የምትገኝበት ስብሰባ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችና ትንቢቶች የሚብራሩበት ወይም ስለ ክርስቲያናዊ አኗኗር ምክር የሚሰጥበት የ45 ደቂቃ የሕዝብ ንግግር ይሆናል። ከዚህ ንግግር በኋላ በተለይ ለጉባኤ ጥናት በሚዘጋጀው የመጠበቂያ ግንብ ርዕሰ ትምህርት በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይደረጋል። ጥናቱ በሚከተለው መንገድ ይካሄዳል:- ከመጠበቂያ ግንብ አንድ አንቀጽ ይነበብና የጥናቱ መሪ በተነበበው አንቀጽ ላይ የተመሠረቱ ጥያቄዎችን ያቀርባል። ተሰብሳቢዎቹ እጃቸውን እያወጡ በፈቃዳቸው መልስ ሊሰጡ ይችላሉ። ብዙ ጊዜ በእያንዳንዱ አንቀጽ ላይ ሦስት አራት ሰዎች ሐሳብ ይሰጣሉ። ስብሰባው አንድ ሰዓት ይፈጃል።

ከዚያም በኋላ ቆየት ብሎ በሳምንቱ ወስጥ እያንዳንዳቸው 45 ደቂቃ የሚፈጁ ሁለት ስብሰባዎች ይደረጋሉ። አንደኛው ቲኦክራቲካዊው የአገልግሎት ትምህርት ቤት ሲሆን በዚህ ስብሰባ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ልዩ ልዩ ማስረጃዎችን እንዴት መሰብሰብ እንደሚቻልና እንዴት ጥሩ አስተማሪ መሆን እንደሚቻል ማሠልጠኛ ይሠጣል። ልዩ የሆነ ትምህርታዊ ንግግር ለ21 ደቂቃ ከተሰጠ በኋላ በቅድሚያ የተዘጋጁ ተማሪዎች አጫጭር መልእክቶችን ያቀርባሉ። እያንዳንዱ ክፍል ከቀረበ በኋላ የትምህርት ቤቱ አስተማሪ ወይም የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ተማሪው እንዴት ሊያሻሽል እንደሚችል የሚገልጽ ምክር ይሰጣል። ለዚህ ትምህርት ቤት አገልግሎት የሚውሉ አያሌ የመማሪያ መጻሕፍት ተዘጋጅተዋል። በስብሰባው ላይ አዘውትረው የሚገኙ ሁሉ ከክርስቲያን መሠረታዊ ሥርዓት ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ከሆኑ በትምህርት ቤቱ ለመሳተፍ ሊመዘገቡ ይችላሉ።

ቀጥሎ የሚቀርበው ስብሰባ የአገልግሎት ስብሰባ ይባላል። በዚህም ስብሰባ ከቤት ወደቤት በሚደረገውና በሌሎቹ የአገልግሎት ዓይነቶች ምሥራቹን እንዴት ማቅረብ እንደሚቻል የሚገልጹ ሦስት ወይም አራት ክፍሎች ይቀርባሉ። እነዚህ ክፍሎች በንግግር፣ በውይይት ወይም በትዕይንት መልክ ይቀርባሉ። አድማጮችም መጠነኛ ተሳትፎ ያደርጋሉ። አብዛኛው የፕሮግራሙ ክፍል በየወሩ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ታትሞ በሚወጣው ባለ አራት ገጽ የመንግሥት አገልግሎታችን የተባለ ጽሑፍ ላይ የተመሠረተ ነው።

ሦስተኛው ስብሰባ በአነስተኛ ቡድን አብዛኛውን ጊዜ በጉባኤው ክልል ውስጥ በሚገኙ የግል ቤቶች የሚደረገው ሳምንታዊ ጥናት ነው። ጥናቱ በመጽሐፍ ቅዱስና ማኅበሩ በቅርብ ጊዜ ባወጣው መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ ነው። ቡድኑ አነስተኛ ስለሆነ ሁሉም በውይይቱ ለመሳተፍ የተሻለ አጋጣሚ ያገኛሉ። በተጨማሪም በስብሰባው የሚገኙት ሁሉ በይበልጥ የሚተዋወቁበት ጥሩ አጋጣሚ ያገኛሉ።

አብዛኞቹ ጉባኤዎች ስብሰባዎቻቸውን የሚያደርጉት የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸው በሠሩአቸው የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ነው። አዳራሹን ለመሥራትና ከዚያ በኋላ ለሚደረግለት እንክብካቤ የሚያስፈልገው ወጪ የሚሸፈነው ምሥክሮቹ ራሳቸው በፈቃደኝነት በሚሰጡት መዋጮ ነው። ሥራው የሚሠራው አብዛኛውን ጊዜ ምንም ገንዘብ ሳይከፈላቸው የነፃ አገልግሎት በሚሰጡ ሠራተኞች ነው። የገንዘብ መዋጮ ለመስጠት የሚፈልጉ ሰዎች እርዳታቸውን የሚጨምሩበት የመዋጮ ሳጥን በሁሉም ስብሰባዎች ጊዜ ይገኛል።

የጉባኤ ስብሰባዎች የይሖዋ ምሥክሮች በዕብራውያን 10:24, 25 ላይ ያለውን ምክር እንዲፈጽሙ ይረዱአቸዋል:- “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።”

● በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ የትኞቹን የጥንት ክርስቲያኖች የስብሰባዎች ባሕርይ መመልከት ይቻላል?

● የይሖዋ ምሥክሮች ዘወትር በሚያደርጓቸው አምስት ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡትን ፕሮግራሞች ዘርዝር።

● የስብሰባ አዳራሾች የሚገኙት እንዴት ነው?

[በገጽ 14 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አንድ ሽማግሌ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ሲመራ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

በቲኦክራቲካዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት፣ ፌሮ ደሴቶች

በግል ቤት ውስጥ የሚደረግ የቡድን ጥናት፣ ያፕ

በኒው ብራውንፌልስ፣ ቴክሳስ ዩ ኤስ ኤ የይሖዋ ምሥክሮች በሁለት ቀን ውስጥ ሠርተው የጨረሱት የመንግሥት አዳራሽ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የመንግሥት አዳራሾች በተለያዩ አገሮች

ጃፓን

አውስትራሊያ

ኦስትሪያ

ስፔይን