የጠፋ ሕዝብ፤ ግን ሁሉም አይደለም
ምዕራፍ 79
የጠፋ ሕዝብ፤ ግን ሁሉም አይደለም
ኢየሱስ በአንድ ፈሪሳዊ ቤት ደጃፍ ተሰብስበው ከነበሩት ሰዎች ጋር ከተወያየ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የተወሰኑ ሰዎች “[የሮማው ገዥ ጴንጤናዊው] ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስላደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች” ነገሩት። እነዚህ የገሊላ ሰዎች የተገደሉት ጲላጦስ ውኃ ወደ ኢየሩሳሌም የሚያስገባ ትልቅ ቦይ ለማሠራት ከቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት ገንዘብ ማውጣቱን በሺህ የሚቆጠሩ አይሁዳውያን በተቃወሙ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። ይህን ሁኔታ ለኢየሱስ ያወሩለት ሰዎች ይህ ጥፋት በገሊላ ሰዎች ላይ ሊደርስ የቻለው ራሳቸው በፈጸሟቸው መጥፎ ድርጊቶች የተነሳ ነው የሚል የጥቆማ ሐሳብ መሰንዘራቸው ሊሆን ይችላል።
ይሁን እንጂ ኢየሱስ የሚከተለውን ጥያቄ በማቅረብ አረማቸው:- “እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ስለ ደረሰባቸው ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሉአችኋልን? እላችኋለሁ፣ አይደለም” ሲል ኢየሱስ መለሰ። ከዚያም “ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ” በማለት አይሁዶችን ለማስጠንቀቅ አጋጣሚውን ተጠቀመበት።
ኢየሱስ በመቀጠል በአካባቢው የተፈጸመ ሌላ አሳዛኝ ሁኔታ ጠቀሰ፤ ይህም ከውኃው ቦይ ግንባታ ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ የሚከተለውን ጥያቄ አቀረበ:- “ወይስ በሰሊሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ አሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን?” አይደሉም፤ እነዚህ ሰዎች የሞቱት በክፋታቸው የተነሳ እንዳልሆነ ኢየሱስ ገለጸ። ከዚህ ይልቅ አብዛኛውን ጊዜ ለእንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ገጠመኞች መንስኤው “ጊዜና ያልታሰበ አጋጣሚ” ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ” በማለት አሁንም አጋጣሚውን ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ተጠቀመበት።
ከዚያም ኢየሱስ የሚከተለውን ተስማሚ ምሳሌ ሰጠ:- “ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፣ ፍሬም ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም። የወይን አትክልት ሠራተኛውንም:- እነሆ፣ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም፤ ቍረጣት፤ ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቍላለች? አለው። እርሱ ግን መልሶ:- ጌታ ሆይ፣ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት። ወደ ፊትም ብታፈራ፣ ደኅና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ አለው።”
ኢየሱስ በአይሁድ ሕዝብ መካከል እምነት ለማብቀል ከሦስት ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ደክሟል። ሆኖም የድካሙ ፍሬ ተደርገው ሊቆጠሩ የሚችሉት በጥቂት መቶዎች የሚቆጠሩ ደቀ መዛሙርት ብቻ ነበሩ። አሁን በዚህ በአራተኛው የአገልግሎቱ ዓመት ላይ ጥረቱን አፋፍሟል። በይሁዳና በፍርጊያ በቅንዓት በመስበክና በማስተማር በምሳሌያዊ አነጋገር በአይሁዶች የተመሰለውን የበለስ ዛፍ ኮትኩቶ ፋንድያ አፍስሶበታል። ሆኖም የተገኘ ውጤት የለም! ሕዝቡ ንስሐ ለመግባት አሻፈረኝ በማለታቸው ወደ ጥፋት እየተጓዙ ነበር። ከሕዝቡ መካከል አዎንታዊ ምላሽ የሰጡት ጥቂቶች ብቻ ናቸው።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በአንድ ምኩራብ ማስተማር ጀመረ። እዚያም ጋኔን ይዟት ለ18 ዓመታት ጎባጣ ሆና የኖረች አንዲት ሴት አየ። ኢየሱስ በርኅራኄ መንፈስ “አንቺ ሴት፣ ከድካምሽ ተፈትተሻል” አላት። ከዚያም እጁን ሲጭንባት ወዲያውኑ ቀጥ አለችና አምላክን ማመስገን ጀመረች።
ይሁን እንጂ የምኩራቡ አለቃ ተቆጣ። “ሊሠራባቸው የሚገባ ስድስት ቀኖች አሉ” ሲል ተቃወመ። “እንግዲህ በእነርሱ መጥታችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት አይደለም አለ።” የምኩራቡ አለቃ በዚህ አነጋገሩ ኢየሱስ የመፈወስ ኃይል እንዳለው አምኖ ተቀብሏል፤ ሆኖም ሕዝቡ በሰንበት ቀን ለመፈወስ በመምጣታቸው አውግዟቸዋል!
“እናንት ግብዞች፣” ሲል ኢየሱስ መለሰ፤ “ከእናንተ እያንዳንዱ በሰንበት በሬውን ወይስ አህያውን ከግርግሙ [ከታሰረበት፣” የ1980 ትርጉም] ፈትቶ ውኃ ሊያጠጣው ይወስደው የለምን? ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሰራት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን?”
ኢየሱስን ሲቃወሙ የነበሩት ሰዎች ይህን ሲሰሙ አፈሩ። ሕዝቡ ግን ኢየሱስ ሲፈጽማቸው ባዩአቸው ድንቅ ነገሮች ተደሰቱ። ኢየሱስ በምላሹ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት በገሊላ ባሕር ጀልባ ላይ ሆኖ የተናገራቸውን ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጹ ሁለት ትንቢታዊ ምሳሌዎችን ደግሞ ተናገረ። ሉቃስ 13:1-21፤ መክብብ 9:11 NW፤ ማቴዎስ 13:31-33
▪ እዚህ ላይ የተጠቀሱት አሳዛኝ ገጠመኞች ምንድን ናቸው? ኢየሱስ በእነዚህ ገጠመኞች ተጠቅሞ ምን ትምህርት ሰጥቷል?
▪ ፍሬ ያልሰጠችው የበለስ ዛፍም ሆነች ዛፏ ፍሬያማ እንድትሆን የተደረገው ጥረት ለምን ነገር ምሳሌ ሊሆን ይችላል?
▪ የምኩራቡ አለቃ ኢየሱስ የመፈወስ ችሎታ እንዳለው አምኖ የተቀበለው እንዴት ነው? ሆኖም ኢየሱስ የሰውየውን ግብዝነት ያጋለጠው እንዴት ነው?