ኢየሱስ፣ አምላክ የጠየቀውን ነገር ሁሉ ይፈጽማል
ምዕራፍ 133
ኢየሱስ፣ አምላክ የጠየቀውን ነገር ሁሉ ይፈጽማል
ተዋጊው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣንንና የእሱን ዓመፀኛ ዓለም በሚያጠፋበት ጊዜ እንዴት ያለ ደስታ ይሆናል! በመጨረሻ ሰላማዊው የኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ይጀምራል!
በኢየሱስና በተባባሪዎቹ ነገሥታት አመራር ከአርማጌዶን የተረፉት ሰዎች በዚያ የጽድቅ ጦርነት የወደሙትን ነገሮች ያጸዳሉ። በምድር ላይ በሕይወት የተረፉት ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ ልጆች ሳይወልዱ አይቀርም። እነዚህ ልጆች ምድርን በጣም ውብ ወደሆነ መናፈሻ መሰል የአትክልት ሥፍራነት በመለወጡ አስደሳች ሥራ ይካፈላሉ።
ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ በዚህች ውብ ገነት ውስጥ እንዲኖሩ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከመቃብሮቻቸው ያስነሳቸዋል። ይህም “በመታሰቢያ መቃብሮች ያሉት ሁሉ . . . የሚወጡበት ሰዓት ደርሷል” በማለት ራሱ የሰጠው ዋስትና ፍጻሜ ይሆናል።— NW
ኢየሱስ ከሞት ከሚያስነሳቸው ሰዎች መካከል ከጎኑ በመከራ እንጨት ላይ የሞተው ቀደም ሲል ክፉ አድራጊ የነበረው ሰው ይገኝበታል። ኢየሱስ “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” (NW) ብሎ ቃል እንደገባለት አስታውስ። ይህ ሰው ከኢየሱስ ጋር ንጉሥ ሆኖ እንዲገዛ ወደ ሰማይ አይወሰድም፤ ኢየሱስም ቢሆን እንደገና ሰው ሆኖ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ከእርሱ ጋር አይኖርም። ከዚህ ይልቅ በሚቀጥለው ገጽ ላይ በሥዕል እንደተገለጸው ኢየሱስ ቀደም ሲል ክፉ አድራጊ የነበረውን ይህን ሰው በገነት ውስጥ በሕይወት እንዲኖር ከሞት በማስነሳትና የሚያስፈልጉት ሥጋዊም ሆኑ መንፈሳዊ ነገሮች እንዲሟሉለት በማድረግ ከእሱ ጋር ይሆናል።
እስቲ አስበው! በኢየሱስ ፍቅራዊ አሳቢነት መላው ሰብዓዊ ቤተሰብ ማለትም ከአርማጌዶን የተረፉት ሰዎች፣ የእነርሱ ልጆችና እሱን የሚታዘዙት በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ከሞት የተነሱ ሰዎች ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና ይደርሳሉ። ይሖዋ ንጉሥ በሆነው ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በመንፈሳዊ ሁኔታ ከሰው ዘር ጋር ይኖራል። ዮሐንስ ከሰማይ የሰማው ድምፅ እንዳለው “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም።” በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ሰው አይታመምም ወይም ሥቃይ አይደርስበትም።
በኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ማብቂያ ላይ ሁኔታው አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ባልና ሚስት ማለትም አዳምንና ሔዋንን ተባዝተው ምድርን እንዲሞሏት ባዘዛቸው ጊዜ አስቦት የነበረውን ዓይነት ይሆናል። አዎን፣ ምድር ፍጹማን የሆኑ ሰዎችን ባቀፈ ጻድቅ ዘር ትሞላለች። ይህ የሚሆነው ሁሉም ሰው የኢየሱስን ቤዛዊ መሥዋዕት ጥቅሞች እንዲያገኝ ስለሚደረግ ነው። በአዳም ኃጢአት ምክንያት የመጣው ሞት ይወገዳል!
በዚህ መንገድ ኢየሱስ ይሖዋ የጠየቀውን ነገር ሁሉ ይፈጽማል። ስለዚህ በሺው ዓመት ፍጻሜ ላይ መንግሥቱንና ፍጹም የሆነውን ሰብዓዊ ቤተሰብ ለአባቱ ያስረክባል። ከዚያ በኋላ አምላክ ከሞት ባልተለየ መልኩ ከእንቅስቃሴ ውጪ ተደርገው የነበሩትን ሰይጣንንና አጋንንቱን ከጥልቁ ያወጣቸዋል። ይህን የሚያደርገው ለምንድን ነው?
በሺው ዓመት ፍጻሜ ላይ በገነት ውስጥ በሕይወት ከሚኖሩት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ እምነታቸው ተፈትኖ የማያውቅ ከሞት የተነሱ ሰዎች ናቸው። ከመሞታቸው በፊት አምላክ የሰጣቸውን ተስፋዎች አያውቁም ነበር፤ ስለዚህ በተስፋዎቹ ላይ እምነት እንዳላቸው ማሳየት አልቻሉም ነበር። ከዚያም ከሞት ተነስተው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ከተማሩ በኋላ በገነት ውስጥ ያላንዳች ተቃውሞ አምላክን ማገልገል ለእነርሱ ቀላል ይሆንላቸዋል። ይሁን እንጂ ሰይጣን አምላክን ማገልገላቸውን እንዲያቆሙ ለማድረግ ሙከራ እንዲያደርግ አጋጣሚ ቢሰጠው በፈተና ሥር ታማኝነታቸውን ማስመስከር ይችሉ ይሆን? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት እንዲቻል ሰይጣን ይፈታል።
ለዮሐንስ የተሰጠው ራእይ ከኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት በኋላ ሰይጣን ቁጥራቸው ያልተወሰነ ሰዎችን ከአምላክ አገልግሎት በማራቅ ረገድ እንደሚሳካለት ይገልጻል። ሆኖም የመጨረሻው ፈተና ካበቃ በኋላ ሰይጣን፣ አጋንንቱና ያሳታቸው ሰዎች በሙሉ ለዘላለም ይጠፋሉ። በሌላ በኩል ግን ሙሉ በሙሉ ተፈትነው ታማኝነታቸውን ያስመሰከሩ በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች የሰማያዊ አባታቸውን በረከቶች እያገኙ ለዘላለም ይኖራሉ።
ኢየሱስ የአምላክን ታላላቅ ዓላማዎች በመፈጸም ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳበረከተና ወደፊትም እንደሚያበረክት ጥርጥር የለውም። በአምላክ የተሾመ ታላቅ ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ በሚያከናውናቸው ነገሮች አማካኝነት እጅግ አስደሳች የሆነ ጊዜ ይጠብቀናል። ሆኖም ሰው በነበረበት ጊዜ ያደረጋቸውን ነገሮች ሁሉ ከቶ ልንረሳቸው አይገባም።
ኢየሱስ በፈቃደኝነት ወደ ምድር መጥቶ ስለ አባቱ አስተምሮናል። ከዚህም በላይ የአምላክን ውድ ባሕርያት አንጸባርቋል። በጣም የሚያስደንቀውን ድፍረቱንና ወንድነቱን፣ ወደር የለሽ ጥበቡን፣ ድንቅ የማስተማር ችሎታውን፣ ቆራጥ አመራሩን፣ ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄውንና ለሰው ችግር ያለውን አሳቢነት ስናስብ ልባችን በጥልቅ ይነካል። ያለ እሱ ሕይወት ልናገኝ የማንችልበትን ቤዛውን ሲያቀርብ የደረሰበትን በቃላት ሊገለጽ የማይችል መከራ ስናስታውስ ልባችን በከፍተኛ የአመስጋኝነትና የአድናቆት ስሜት ይሞላል!
ስለ ኢየሱስ ሕይወት ባደረግነው በዚህ ጥናታችን የተመለከትነው ሰው በእርግጥም ምንኛ ታላቅ ነው! ታላቅነቱ ጎልቶ የሚታይና እጅግ የሚያስደንቅ ነው። ሮማዊው ገዥ ጴንጤናዊው ጲላጦስ “እነሆ ሰውዬው!” በማለት የተናገራቸውን ቃላት ለማስተጋባት እንገፋፋለን። አዎን፣ በእርግጥም “ሰውዬው፣” እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው!
የቤዛዊ መሥዋዕቱን ዝግጅት በመቀበል ከአዳም የወረስነውን የኃጢአትና የሞት ሸክም ማስወገድ እንችላለን፤ ኢየሱስም ‘ዘላለማዊ አባታችን’ ሊሆንልን ይችላል። የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ አምላክን ብቻ ሳይሆን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስንም ማወቅ አለባቸው። ይህን መጽሐፍ ማንበብህና ማጥናትህ እንዲህ ዓይነቱን ሕይወት ሰጪ እውቀት ለማግኘት እንዲረዳህ እንመኝልሃለን! 1 ዮሐንስ 2:17፤ 1:7፤ ዮሐንስ 5:28, 29፤ 3:16፤ 17:3፤ 19:5፤ ሉቃስ 23:43፤ ዘፍጥረት 1:28፤ 1 ቆሮንቶስ 15:24-28፤ ራእይ 20:1-3, 6-10፤ 21:3, 4፤ ኢሳይያስ 9:6
▪ ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉ ሰዎችና ልጆቻቸው ምን አስደሳች መብት ይኖራቸዋል?
▪ አርማጌዶንን በሕይወት ከሚያልፉ ሰዎችና ከልጆቻቸው ሌላ በገነት የመኖር መብት የሚያገኙት እነማን ናቸው? ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር የሚሆነውስ በምን መንገድ ነው?
▪ በሺው ዓመት ፍጻሜ ላይ የሚኖረው ሁኔታ ምን ዓይነት ይሆናል? ኢየሱስስ በዚያን ጊዜ ምን ያደርጋል?
▪ ሰይጣን ከጥልቁ ውስጥ የሚፈታው ለምንድን ነው? በመጨረሻ በእሱና እርሱን በሚከተሉት ሁሉ ላይ ምን ይደርስባቸዋል?
▪ ኢየሱስ ‘ዘላለማዊ አባታችን’ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?