ምዕራፍ 128
ጲላጦስም ሆነ ሄሮድስ ምንም ጥፋት አላገኙበትም
ማቴዎስ 27:12-14, 18, 19 ማርቆስ 15:2-5 ሉቃስ 23:4-16 ዮሐንስ 18:36-38
-
ጲላጦስና ሄሮድስ ኢየሱስን መረመሩት
ኢየሱስ፣ ንጉሥ መሆኑን ከጲላጦስ ለመደበቅ አልሞከረም። ያም ቢሆን መንግሥቱ በሮም መንግሥት ላይ የሚፈጥረው ስጋት የለም። እንዲህ አለ፦ “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም። መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል ቢሆን ኖሮ በአይሁዳውያን እጅ እንዳልወድቅ አገልጋዮቼ ይዋጉልኝ ነበር። አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም።” (ዮሐንስ 18:36) አዎን፣ ኢየሱስ መንግሥት አለው፤ ይሁንና መንግሥቱ ከዚህ ዓለም አይደለም።
ሆኖም ጲላጦስ ጉዳዩን በዚህ አልተወውም። “እንግዲያው አንተ ንጉሥ ነህ?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም እንደሚከተለው ብሎ በመመለስ ጲላጦስ ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ እንደደረሰ ገለጸ፦ “እኔ ንጉሥ እንደሆንኩ አንተ ራስህ እየተናገርክ ነው። እኔ የተወለድኩትና ወደ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመሥከር ነው። ከእውነት ጎን የቆመ ሁሉ ቃሌን ይሰማል።”—ዮሐንስ 18:37
ኢየሱስ ከዚህ ቀደም ለቶማስ “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ” ብሎታል። አሁን ደግሞ፣ ወደ ምድር የመጣው “ስለ እውነት” በተለይም ስለ መንግሥቱ የሚገልጸውን እውነት ለመመሥከር መሆኑን ለጲላጦስ እንኳ ነገረው። ኢየሱስ፣ ሕይወቱን የሚያሳጣው ቢሆንም ለዚህ እውነት ታማኝ ለመሆን ዝግጁ ነው። ጲላጦስ “እውነት ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀው፤ ሆኖም መልስ እንዲሰጠው አልጠበቀም። በዚህ ሰው ላይ ለመፍረድ የሚያስችል በቂ መረጃ እንዳገኘ ተሰምቶታል።—ዮሐንስ 14:6፤ 18:38
ጲላጦስ ከቤተ መንግሥቱ ውጭ ሆኖ ወደሚጠባበቀው ሕዝብ ተመለሰ። የካህናት አለቆቹንና አብረዋቸው ያሉትን ሰዎች “በዚህ ሰው ላይ ምንም ወንጀል አላገኘሁበትም” አላቸው፤ ይህን ያለው ኢየሱስን ከጎኑ አቁሞ ሳይሆን አይቀርም። የተሰበሰቡት ሰዎች በዚህ ውሳኔ ተበሳጭተው “በመላው ይሁዳ፣ ከገሊላ አንስቶ እስከዚህ ድረስ እያስተማረ ሕዝቡን ይቀሰቅሳል” በማለት አጥብቀው ተናገሩ።—ሉቃስ 23:4, 5
የአይሁዳውያኑ ጭፍንና ግትር የሆነ አቋም ጲላጦስን ሳያስገርመው አይቀርም። የካህናት አለቆቹና የሕዝቡ ሽማግሌዎች መጮኻቸውን ሲቀጥሉ ጲላጦስ ወደ ኢየሱስ ዞር አለና “በስንት ነገር እየመሠከሩብህ እንዳሉ አትሰማም?” ሲል ጠየቀው። (ማቴዎስ 27:13) ኢየሱስ ምንም መልስ አልሰጠም። ኢየሱስ፣ ቁጣ የተሞላበት ይህ ሁሉ ክስ እየተሰነዘረበት መረጋጋቱ ጲላጦስን አስደነቀው።
አይሁዳውያን ኢየሱስ ‘ከገሊላ እንደተነሳ’ ገልጸዋል። ጲላጦስ ስለዚህ ጉዳይ ሲያጣራ ኢየሱስ በእርግጥም የገሊላ ሰው መሆኑን ተረዳ። ይህን ሲያውቅ በኢየሱስ ላይ ከመፍረድ ራሱን ነፃ ማውጣት የሚችልበት መንገድ እንዳለ ተሰማው። የገሊላ ገዢ ሄሮድስ አንቲጳስ (የታላቁ ሄሮድስ ልጅ) ሲሆን እሱ ደግሞ በፋሲካ በዓል ወቅት ኢየሩሳሌም መጥቷል። በመሆኑም ጲላጦስ ኢየሱስን ወደ ሄሮድስ ላከው። የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ ያስቆረጠው ሄሮድስ አንቲጳስ ነው። ከጊዜ በኋላ ሄሮድስ፣ ኢየሱስ ተአምራት እየፈጸመ እንዳለ ሲሰማ ዮሐንስ ከሞት እንደተነሳና ኢየሱስ የተባለው እሱ እንደሆነ ስለተሰማው ጉዳዩ አሳስቦት ነበር።—ሉቃስ 9:7-9
አሁን ሄሮድስ ኢየሱስን የሚያይበት አጋጣሚ በማግኘቱ ተደሰተ። ሄሮድስ የተደሰተው ኢየሱስን ሊረዳው አስቦ አሊያም ደግሞ በእሱ ላይ የተሰነዘሩት ክሶች እውነተኛ መሆናቸውን በሚገባ ለማጣራት ፈልጎ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የማወቅ ፍላጎት ስላደረበትና ኢየሱስ “አንዳንድ ተአምራት ሲፈጽም ለማየት” ተስፋ ስላደረገ ነው። (ሉቃስ 23:8) ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ ሄሮድስ የጓጓለትን ነገር ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነም። እንዲያውም ሄሮድስ ሲጠይቀው ኢየሱስ አንድም ቃል አልተነፈሰም። ሄሮድስ፣ የጠበቀውን ነገር ኢየሱስ ስላላደረገ በመበሳጨቱ ከወታደሮቹ ጋር ሆኖ “አቃለለው።” (ሉቃስ 23:11) ያማረ ልብስ አልብሰው አፌዙበት። ከዚያም ሄሮድስ፣ ኢየሱስን መልሶ ወደ ጲላጦስ ላከው። ቀደም ሲል ጠላቶች የነበሩት ሄሮድስና ጲላጦስ አሁን ጥሩ ወዳጆች ሆኑ።
ኢየሱስ ተመልሶ ሲመጣ ጲላጦስ የካህናት አለቆችን፣ የአይሁድ መሪዎችንና ሕዝቡን አንድ ላይ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ይህን ሰው . . . በፊታችሁ መረመርኩት፤ ሆኖም በእሱ ላይ ያቀረባችሁትን ክስ የሚደግፍ ምንም ነገር አላገኘሁም። ሄሮድስም ቢሆን ምንም ጥፋት ስላላገኘበት ወደ እኛ መልሶ ልኮታል፤ በመሆኑም ለሞት የሚያበቃ ምንም ሉቃስ 23:14-16
ነገር አልፈጸመም። ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ።”—ካህናቱ ኢየሱስን አሳልፈው የሰጡት በቅናት ተነሳስተው እንደሆነ ጲላጦስ ስለተገነዘበ ኢየሱስን ሊፈታው ፈልጓል። ጲላጦስ ኢየሱስን ለመፍታት እየሞከረ እያለ ይህንን ጥረቱን ይበልጥ እንዲገፋበት የሚያነሳሳ ሌላ ነገር አጋጠመው። ፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ “በእሱ ምክንያት ዛሬ በሕልም [ምንጩ መለኮታዊ ሳይሆን አይቀርም] ብዙ ስለተሠቃየሁ በዚያ ጻድቅ ሰው ላይ ምንም ነገር እንዳታደርግ” የሚል መልእክት ላከችበት።—ማቴዎስ 27:19
ጲላጦስ ይህን ንጹሕ ሰው መፍታት እንዳለበት ግልጽ ነው፤ ታዲያ እንዴት ሊፈታው ይችላል?