ምዕራፍ 92
የሥጋ ደዌ የነበረበት ሰው አመስጋኝነት አሳየ
-
ኢየሱስ የሥጋ ደዌ የያዛቸውን አሥር ሰዎች ፈወሰ
ኢየሱስ ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን ምሥራቅ ወደምትገኘው ኤፍሬም የተባለች ከተማ ተጓዘ፤ በመሆኑም የሳንሄድሪን ሸንጎ እሱን ለመግደል ያወጣው ዕቅድ ከሸፈ። ኢየሱስ ከጠላቶቹ ርቆ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚህች ከተማ ተቀመጠ። (ዮሐንስ 11:54) ይሁን እንጂ በ33 ዓ.ም. የሚከበረው የፋሲካ በዓል እየተቃረበ በመሆኑ ኢየሱስ ብዙም ሳይቆይ እንደገና መጓዝ ጀመረ። ሰማርያን አቋርጦ በስተ ሰሜን ወደ ገሊላ ተጓዘ፤ ይህ ከመሞቱ በፊት ወደዚህ አካባቢ ያደረገው የመጨረሻ ጉዞው ነው።
ኢየሱስ ጉዞውን የጀመረ አካባቢ፣ ከአንድ መንደር ወደ ሌላ መንደር እየሄደ ሳለ የሥጋ ደዌ የያዛቸው አሥር ሰዎች አገኘ። አንዳንድ ጊዜ ይህ በሽታ የእጅና የእግር ጣት ወይም ጆሮ የመሳሰሉ የሰውነት ክፍሎችን ቀስ በቀስ ይቆራርጣል። (ዘኁልቁ 12:10-12) በአምላክ ሕግ መሠረት፣ የሥጋ ደዌ ያለበት ሰው “ርኩስ ነኝ፣ ርኩስ ነኝ!” እያለ መጮኽና ከሌሎች ተገልሎ መኖር አለበት።—ዘሌዋውያን 13:45, 46
በዚህም ምክንያት፣ የሥጋ ደዌ የያዛቸው አሥሩ ሰዎች ከኢየሱስ ርቀው ቆሙ። ሆኖም ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ “ኢየሱስ፣ መምህር፣ ምሕረት አድርግልን!” አሉ። ኢየሱስም ባያቸው ጊዜ “ሄዳችሁ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” አላቸው። (ሉቃስ 17:13, 14) ኢየሱስ እንዲህ ማለቱ ለአምላክ ሕግ አክብሮት እንዳለው ያሳያል፤ በሕጉ መሠረት፣ የሥጋ ደዌ ሕመምተኛ የነበረ ሰው ከበሽታው እንደዳነ የማስታወቅ ሥልጣን ያላቸው ካህናት ናቸው። አንድ ካህን ሕመምተኛው ንጹሕ መሆኑን ከገለጸ፣ ግለሰቡ ከጤናማ ሰዎች ጋር እንደገና ተቀላቅሎ መኖር ይችላል።—ዘሌዋውያን 13:9-17
የሥጋ ደዌ የያዛቸው አሥሩ ሰዎች፣ ኢየሱስ ተአምር የመሥራት ኃይል እንዳለው ሙሉ በሙሉ ተማምነዋል። ስለዚህ ገና ያልተፈወሱ ቢሆንም እንኳ ወደ ካህናቱ ሄዱ። በኢየሱስ ላይ ያላቸው እምነት እንደካሳቸው መንገድ ላይ ሳሉ መመልከት ቻሉ። ሰውነታቸውን ሲያዩ ጤንነታቸው እንደተመለሰ የተገነዘቡ ከመሆኑም ሌላ በሽታው እንደለቀቃቸው ታወቃቸው!
ከሥጋ ደዌ ከተፈወሱት መካከል ዘጠኙ መንገዳቸውን ቀጠሉ። አንዱ ግን ተመለሰ። ሳምራዊ የሆነው ይህ ሰው የተመለሰው ኢየሱስን ለማግኘት ነው። እንዲህ ያደረገው ለምን ይሆን? ሰውየው ለተደረገለት ነገር ኢየሱስን ከልቡ ማመስገን ስለፈለገ ነው። ከበሽታው የተፈወሰው ይህ ሰው ጤንነቱን የመለሰለት ይሖዋ መሆኑን ስለተገነዘበ “አምላክን በታላቅ ድምፅ” አመሰገነ። (ሉቃስ 17:15) ኢየሱስን ሲያገኘውም እግሩ ላይ ተደፍቶ አመሰገነው።
ኢየሱስ በአካባቢው ላሉት ሰዎች እንዲህ አለ፦ “የነጹት አሥሩም አይደሉም እንዴ? ታዲያ ዘጠኙ የት አሉ? ከዚህ ከባዕድ አገር ሰው በስተቀር አምላክን ለማመስገን የተመለሰ ሌላ አንድም ሰው የለም?” ከዚያም ኢየሱስ ሳምራዊውን “ተነስና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።—ሉቃስ 17:17-19
ኢየሱስ አሥሩን የሥጋ ደዌ በሽተኞች መፈወሱ፣ ይሖዋ አምላክ እንደሚደግፈው ያሳያል። ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ከበሽታው ነፃ ከመሆኑም ሌላ የሕይወትን መንገድ ማግኘት የቻለ ይመስላል። እርግጥ ነው፣ በምንኖርበት ዘመን አምላክ በኢየሱስ አማካኝነት እንዲህ ዓይነት ፈውሶችን አያከናውንም። ይሁንና በኢየሱስ በማመን፣ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኘውን መንገድ መያዝ እንችላለን። ታዲያ እኛስ ይህን አጋጣሚ በማግኘታችን እንደ ሳምራዊው አመስጋኝ መሆናችንን እናሳያለን?