ምዕራፍ 2
‘አምላክ ስጦታቸውን ተቀብሏል’
ፍሬ ሐሳብ፦ ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ስላደረገው ዝግጅት የሚገልጽ ታሪክ
1-3. (ሀ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን? (ለ) ንጹሕ አምልኮ የሚጠይቃቸውን የትኞቹን አራት መሠረታዊ መሥፈርቶች እንመለከታለን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
አቤል መንጋውን በትኩረት እየተመለከተ ነው። እነዚህን እንስሳት ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ በፍቅርና በእንክብካቤ አሳድጓቸዋል። አሁን ደግሞ አንዳንዶቹን መርጦ ካረደ በኋላ ለአምላክ ስጦታ አድርጎ ሊያቀርባቸው ነው። ታዲያ ይህ ፍጹም ያልሆነ ሰው በዚህ መንገድ ያቀረበውን አምልኮ ይሖዋ ይቀበለው ይሆን?
2 ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ ስለ አቤል ሲጽፍ “አምላክ ስጦታውን [ተቀበለ]” ብሏል። ሆኖም ይሖዋ ቃየን ያቀረበውን ስጦታ አልተቀበለም። (ዕብራውያን 11:4ን አንብብ።) ይህም አንዳንድ ጥያቄዎችን ያስነሳል። አምላክ አቤል ያቀረበውን አምልኮ ተቀብሎ የቃየንን ያልተቀበለው ለምንድን ነው? ከቃየንና ከአቤል እንዲሁም በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ ከተጠቀሱት ሌሎች ሰዎች ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ንጹሕ አምልኮ ስለሚያካትታቸው ነገሮች ያለንን ግንዛቤ ያሰፋልናል።
3 በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ከአቤል እስከ ሕዝቅኤል ዘመን የተከናወኑትን ነገሮች በአጭሩ እንዳስሳለን፤ እነዚህን ክንውኖች ስትመረምር አንድ ሰው የሚያቀርበው አምልኮ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ የግድ መሟላት ያለባቸውን የሚከተሉትን አራት መሠረታዊ መሥፈርቶች ልብ ለማለት ሞክር፦ አምልኮ የሚቀርብለት አካል ይሖዋ መሆን አለበት፤ የሚቀርበው ነገር ጥራት ያለው ማለትም ምርጥ ሊሆን ይገባል፤ አምልኮው የሚቀርብበት መንገድ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሆን ይኖርበታል፤ እንዲሁም ግለሰቡ አምልኮ ለማቅረብ የሚነሳሳበት የልብ ዝንባሌ ንጹሕ መሆን አለበት።
ቃየን ያቀረበው አምልኮ ተቀባይነት ያላገኘው ለምንድን ነው?
4, 5. ቃየን ስጦታ ማቅረብ ያለበት ለይሖዋ እንደሆነ እንዲገነዘብ ያደረገው ምን ሊሆን ይችላል?
4 ዘፍጥረት 4:2-5ን አንብብ። ቃየን ስጦታውን ማቅረብ ያለበት ለይሖዋ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ቃየን ስለ ይሖዋ የሚማርበት በቂ ጊዜና አጋጣሚ አግኝቷል። እሱና ወንድሙ አቤል ስጦታቸውን ባቀረቡበት ጊዜ ዕድሜያቸው 100 ዓመት ገደማ ሳይሆን አይቀርም። a ሁለቱም ሰዎች ከልጅነታቸው አንስቶ ስለ ኤደን ገነት ያውቃሉ፤ እንዲያውም ያንን ለምለም የአትክልት ቦታ ከሩቅ የመመልከት አጋጣሚ አግኝተው ሊሆን ይችላል። መግቢያውን የሚጠብቁ ኪሩቤል እንዳሉም አይተው መሆን አለበት። (ዘፍ. 3:24) ወላጆቻቸው ሕይወት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ የፈጠረው ይሖዋ እንደሆነና እሱ ለሰው ልጆች የነበረው ዓላማ ሰዎች እንዲያረጁና እንዲሞቱ እንዳልሆነ ነግረዋቸው እንደሚሆን አያጠራጥርም። (ዘፍ. 1:24-28) ቃየን ለአምላክ ስጦታ ማቅረብ እንዳለበት እንዲገነዘብ ያደረገው እነዚህን ነገሮች ማወቁ ሊሆን ይችላል።
5 ቃየን መሥዋዕት እንዲያቀርብ ያነሳሳው ሌላ ነገር ምን ሊሆን ይችላል? ይሖዋ አንድ “ዘር” እንደሚያስነሳና ይህ “ዘር” ሔዋን አሳዛኝ ውሳኔ እንድታደርግ ያታለላትን ‘እባብ’ ጭንቅላት እንደሚቀጠቅጥ ተንብዮ ነበር። (ዘፍ. 3:4-6, 14, 15) ቃየን የበኩር ልጅ እንደመሆኑ መጠን በተስፋ የሚጠበቀው ይህ “ዘር” እሱ እንደሆነ አስቦ ሊሆን ይችላል። (ዘፍ. 4:1) በተጨማሪም ይሖዋ ኃጢአተኛ ከሆኑ የሰው ልጆች ጋር መነጋገሩን ሙሉ በሙሉ አላቆመም ነበር፤ አዳም ኃጢአት ከሠራ በኋላም እንኳ (በአንድ መልአክ አማካኝነት ሳይሆን አይቀርም) አነጋግሮታል። (ዘፍ. 3:8-10) ቃየንንም ቢሆን መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ አነጋግሮት ነበር። (ዘፍ. 4:6) ቃየን፣ ይሖዋ አምልኮ ሊቀርብለት እንደሚገባ ያውቅ ነበር።
6, 7. ቃየን ያቀረበው መሥዋዕት ጥራቱ ወይም የቀረበበት መንገድ ችግር ነበረበት? አብራራ።
6 ታዲያ ይሖዋ የቃየንን መሥዋዕት ያልተቀበለው ለምን ነበር? ስጦታው የጥራት ችግር ነበረበት? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚገልጸው ነገር የለም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ቃየን “የምድር ፍሬዎችን” እንዳቀረበ ብቻ ነው። ይሖዋ ከዘመናት በኋላ ለሙሴ በሰጠው ሕግ ላይ እንዲህ ያለው መሥዋዕት ተቀባይነት እንዳለው አመልክቷል። (ዘኁ. 15:8, 9) በተጨማሪም በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው። በዚያ ዘመን ሰዎች የሚበሉት አትክልት ብቻ ነበር። (ዘፍ. 1:29) ከዚህም ሌላ ከኤደን ውጭ ያለውን ምድር አምላክ ረግሞት ስለነበር ቃየን ስጦታ አድርጎ ያቀረበውን የምድር ፍሬ ለማምረት ብዙ ድካም ጠይቆበታል። (ዘፍ. 3:17-19) በመሆኑም ቃየን ያቀረበው በብዙ ልፋት ያገኘውንና ለሕይወት አስፈላጊ የሆነውን ምግብ ነው! ሆኖም ይሖዋ የቃየንን መሥዋዕት አልተቀበለም።
7 ታዲያ ችግሩ ያለው ስጦታው የቀረበበት መንገድ ላይ ይሆን? ቃየን መሥዋዕቱን ተቀባይነት ባለው መንገድ አላቀረበውም ማለት ነው? እንደዚያ ማለት ይከብዳል። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ የቃየንን መሥዋዕት ባይቀበልም መሥዋዕቱ የቀረበበትን መንገድ አላወገዘም። እንዲያውም ቃየንም ሆነ አቤል መሥዋዕታቸውን ስላቀረቡበት መንገድ የተጠቀሰ ምንም ነገር የለም። ታዲያ ችግሩ ምን ላይ ነው?
8, 9. (ሀ) ይሖዋ ቃየንንም ሆነ የቃየንን መሥዋዕት በሞገስ ዓይን ያልተመለከተው ለምን ነበር? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቃየንና ስለ አቤል ከሚሰጠው መረጃ ጋር በተያያዘ ምን ትኩረት የሚስብ ነገር አለ?
8 ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የጻፈው መልእክት ቃየን ለይሖዋ ስጦታ ያቀረበው በንጹሕ የልብ ዝንባሌ ተነሳስቶ እንዳልነበረ ይጠቁማል። ቃየን እምነት ይጎድለው ነበር። (ዕብ. 11:4፤ 1 ዮሐ. 3:11, 12) ይሖዋ የቃየንን መሥዋዕት ብቻ ሳይሆን ቃየንን ራሱን ጭምር በሞገስ ዓይን ያላየው ለዚህ ነው። (ዘፍ. 4:5-8) ይሖዋ አፍቃሪ አባት በመሆኑ ልጁን በደግነት ሊያርመው ሞክሮ ነበር። ቃየን ግን እሱን ለመርዳት የተዘረጋውን የይሖዋን እጅ ገፈተረ። እንደ ‘ጥላቻ፣ ጠብና ቅናት’ ያሉት የሥጋ ሥራዎች በቃየን ምሳሌያዊ ልብ ውስጥ ሥር ሰደው ነበር። (ገላ. 5:19, 20) ቃየን ልቡ ክፉ መሆኑ፣ ያቀረበው አምልኮ የነበሩትን መልካም ገጽታዎች ሁሉ ከንቱ አድርጎበታል። የቃየን ታሪክ ንጹሕ አምልኮ፣ የሚታይ የአምልኮ ሥርዓት ከመፈጸም ያለፈ ነገርን እንደሚጠይቅ ያስተምረናል።
9 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቃየን ብዙ የሚነግረን ነገር አለ፤ ይሖዋ እንዳነጋገረውና እሱ ምን ምላሽ እንደሰጠ ሌላው ቀርቶ የልጆቹ ስምና ያደረጓቸው አንዳንድ ነገሮች ጭምር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው እናገኛለን። (ዘፍ. 4:17-24) አቤልን በተመለከተ ግን ልጆች ይኑሩት አይኑሩት ተመዝግቦ የምናገኘው ነገር የለም፤ እንዲሁም አቤል የተናገረው አንድም ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ይሁንና የአቤል ተግባር እስከ ዛሬ ድረስ ይናገራል። በምን መንገድ?
ንጹሕ አምልኮን በተመለከተ አቤል የተወው ምሳሌ
10. አቤል ንጹሕ አምልኮን በተመለከተ ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል?
10 አቤል አምልኮ ሊቀርብ የሚገባው ለይሖዋ ብቻ እንደሆነ ስላወቀ መሥዋዕት ያቀረበው ለይሖዋ ነው። የስጦታው ጥራትም ቢሆን እንከን የሚወጣለት አልነበረም፤ ያቀረበው “ከመንጋው በኩራት መካከል የተወሰኑትን” መርጦ ነበር። ዘገባው አቤል መሥዋዕቱን ያቀረበው በመሠዊያ ላይ ይሁን አይሁን ባይናገርም መሥዋዕቱን ያቀረበበት መንገድ ተቀባይነት እንደነበረው ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ አቤል ካቀረበው መሥዋዕት ጋር በተያያዘ ጎልቶ የሚታየውና ከስድስት ሺህ ዓመታት በኋላ ለምንኖረው ለእኛ ትልቅ ትምህርት የያዘልን ስጦታውን ለማቅረብ ያነሳሳው የልብ ዝንባሌ ነው። አቤልን መሥዋዕት እንዲያቀርብ ያነሳሳው በአምላክ ላይ ያለው እምነትና ለይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች የነበረው ፍቅር ነው። ይህን እንዴት እናውቃለን?
11. ኢየሱስ አቤል ጻድቅ ሰው እንደሆነ የተናገረው ለምንድን ነው?
11 በመጀመሪያ ኢየሱስ ስለ አቤል ምን እንዳለ እስቲ እንመልከት። ኢየሱስ አቤልን በደንብ ያውቀው ነበር፤ አቤል በሕይወት በነበረበት ወቅት ኢየሱስ በሰማይ ይኖር ነበር። ኢየሱስ የአቤልን ሁኔታ በቅርበት ይከታተል እንደነበር ጥያቄ የለውም። (ምሳሌ 8:22, 30, 31፤ ዮሐ. 8:58፤ ቆላ. 1:15, 16) ስለዚህ ኢየሱስ፣ አቤል ጻድቅ ሰው እንደሆነ ሲናገር በዓይኑ ስላየው ነገር መናገሩ ነበር። (ማቴ. 23:35) ጻድቅ የሆነ ሰው ትክክልና ስህተት ስለሆኑት ነገሮች መሥፈርት የሚያወጣው ይሖዋ መሆኑን አምኖ ይቀበላል። ይሁን እንጂ በዚህ ብቻ አይወሰንም፤ እነዚህን መሥፈርቶች እንደሚቀበል በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ ያሳያል። (ከሉቃስ 1:5, 6 ጋር አወዳድር።) ጻድቅ ሰው የሚል ስም ለማትረፍ ጊዜ ይጠይቃል። ስለዚህ አቤል ለአምላክ መሥዋዕት ከማቅረቡ በፊትም ቢሆን የይሖዋን መሥፈርቶች ጠብቆ በመኖር ረገድ ጥሩ ታሪክ አስመዝግቦ መሆን አለበት። እንዲህ ያለውን አካሄድ መከተል ቀላል አልነበረም። ታላቅ ወንድሙ ቃየን ልቡ ክፉ ሆኖ ስለነበር ለእሱ ጥሩ ምሳሌ ሊሆነው እንደማይችል የታወቀ ነው። (1 ዮሐ. 3:12) እናቱ ደግሞ አምላክ የሰጠውን ቀጥተኛ ትእዛዝ የጣሰች ሲሆን አባቱም ቢሆን መልካምና ክፉ የሆነውን በራሱ ለመወሰን ስለፈለገ በይሖዋ ላይ ዓምፆአል። (ዘፍ. 2:16, 17፤ 3:6) አቤል ከቤተሰቡ ፈጽሞ የተለየ አካሄድ ለመምረጥ ከፍተኛ ድፍረት ጠይቆበት መሆን አለበት!
12. በቃየንና በአቤል መካከል የነበረው መሠረታዊ ልዩነት ምንድን ነው?
12 ቀጥሎ ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ እምነትና ጽድቅ ያላቸውን ዝምድና እንዴት እንደገለጸ እንመልከት። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አቤል፣ ቃየን ካቀረበው የበለጠ ዋጋ ያለው መሥዋዕት ለአምላክ በእምነት አቀረበ፤ አምላክ ስጦታውን ስለተቀበለ በዚህ እምነቱ የተነሳ ጻድቅ እንደሆነ ተመሥክሮለታል።” (ዕብ. 11:4) ጳውሎስ የተጠቀመበት አገላለጽ፣ ከቃየን በተለየ መልኩ አቤል ዕድሜውን በሙሉ በይሖዋና እሱ ነገሮችን በሚያከናውንበት መንገድ ላይ ልባዊ እምነት እንደነበረውና ይህም ለአምላክ መሥዋዕት ለማቅረብ እንዳነሳሳው ያሳያል።
13. አቤል ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?
13 አቤል የተወው ምሳሌ ንጹሕ አምልኮ ሊመነጭ የሚችለው ከንጹሕ የልብ ዝንባሌ ብቻ እንደሆነ ያስተምረናል፤ አንድ ሰው ንጹሕ አምልኮ ማቅረብ የሚችለው በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት ካለውና ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ ከሆነ ብቻ ነው። በተጨማሪም ንጹሕ አምልኮ አንድ ጊዜ ብቻ ከሚቀርብ የአምልኮ ሥርዓት ያለፈ ነገርን እንደሚጠይቅ እንማራለን። ንጹሕ አምልኮ መላ ሕይወታችንን ማለትም አኗኗራችንንና ምግባራችንን በሙሉ የሚመለከት ነገር ነው።
ጥንት የነበሩ ሌሎች ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች
14. ይሖዋ ኖኅ፣ አብርሃምና ያዕቆብ ያቀረቡትን መሥዋዕት የተቀበለው ለምን ነበር?
14 ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ያቀረበው የመጀመሪያው ፍጹም ያልሆነ ሰው አቤል ነው፤ የመጨረሻው ሰው ግን አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ ያመለኩ እንደ ኖኅ፣ አብርሃምና ያዕቆብ ያሉ ሌሎች ሰዎችንም ጠቅሷል። (ዕብራውያን 11:7, 8, 17-21ን አንብብ።) እነዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ለይሖዋ መሥዋዕት ያቀረቡባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ አምላክም ስጦታቸውን ተቀብሏል። ለምን? ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች መሥዋዕት ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ንጹሕ አምልኮ የሚጠይቃቸውን መሠረታዊ መሥፈርቶች በሙሉ አሟልተዋል። እስቲ የተዉትን ምሳሌ እንመልከት።
15, 16. ኖህ ንጹሕ አምልኮ የሚጠይቃቸውን አራት መሠረታዊ መሥፈርቶች ያሟላው እንዴት ነው?
15 ኖኅ የተወለደው አዳም ከሞተ ከ126 ዓመት በኋላ ነው። ኖኅ በተወለደበት ወቅት ዓለም በሐሰት አምልኮ እጅግ ተበክሎ ነበር። b (ዘፍ. 6:11) ከጥፋት ውኃው ጥቂት ቀደም ብሎ በምድር ላይ ይኖሩ ከነበሩት ቤተሰቦች መካከል ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ ያመልኩ የነበሩት ኖኅና ቤተሰቡ ብቻ ነበሩ። (2 ጴጥ. 2:5) ኖኅ ከጥፋት ውኃው ከዳነ በኋላ መሠዊያ ለመሥራትና ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ ተነሳሳ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መሠዊያ እንደሠራ በቀጥታ የተጠቀሰው የመጀመሪያው ሰው ኖኅ ነው። ኖኅ ከልቡ ተነሳስቶ የፈጸመው ይህ ድርጊት ለቤተሰቡና ከእሱ በኋላ ለሚመጡት ዘሮቹ አምልኮ ሊቀርብለት የሚገባው አካል ይሖዋ ብቻ እንደሆነ ግልጽ መልእክት ያስተላልፋል። ኖኅ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው “ንጹሕ ከሆኑት እንስሳት ሁሉ እንዲሁም ንጹሕ ከሆኑት የሚበርሩ ፍጥረታት ሁሉ የተወሰኑትን” መርጦ ነው። (ዘፍ. 8:20) መሥዋዕቱ በጥራት ረገድ ከሁሉ የተሻለ ነበር፤ ምክንያቱም ይሖዋ ራሱ እነዚህ እንስሳት ንጹሕ እንደሆኑ ተናግሯል።—ዘፍ. 7:2
16 ኖኅ እነዚህን የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ያቀረበው ራሱ በሠራው መሠዊያ ላይ ነበር። ታዲያ አምልኮ ያቀረበበት መንገድ ተቀባይነት ነበረው? አዎ። ዘገባው፣ ይሖዋ ከመሥዋዕቱ በወጣው መዓዛ እንደተደሰተ እንዲሁም ኖኅንና ልጆቹን እንደባረካቸው ይገልጻል። (ዘፍ. 8:21፤ 9:1) ይሁን እንጂ ይሖዋ መሥዋዕቱን እንዲቀበል ያደረገው ዋነኛ ምክንያት ኖኅ መሥዋዕት ለማቅረብ የተነሳሳበት የልብ ዝንባሌ ነበር። መሥዋዕቱ ኖኅ በይሖዋና እሱ ማንኛውንም ነገር በሚያከናውንበት መንገድ ላይ ያለውን ጠንካራ እምነት የሚያሳይ ተጨማሪ መግለጫ ነበር። ኖኅ አንዴም ዝንፍ ሳይል ይሖዋን በመታዘዙና የጽድቅ መሥፈርቶቹን በማክበሩ መጽሐፍ ቅዱስ “ኖኅ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ ነበር” በማለት ሊናገር ችሏል። በዚህ የተነሳ ኖኅ “ጻድቅ ሰው” የሚል ዘላለማዊ ስም አትርፏል።—ዘፍ. 6:9፤ ሕዝ. 14:14፤ ዕብ. 11:7
17, 18. አብርሃም ንጹሕ አምልኮ የሚጠይቃቸውን አራት መሠረታዊ መሥፈርቶች ያሟላው እንዴት ነው?
17 አብርሃም የሚኖረው በሐሰት አምልኮ ተከቦ ነበር። የአብርሃም መኖሪያ በሆነችው በዑር ከተማ ውስጥ ናና ለተባለው የጨረቃ አምላክ ክብር የተሠራ ግዙፍ ቤተ መቅደስ ይገኝ ነበር። c የአብርሃም አባትም እንኳ በአንድ ወቅት የሐሰት አማልክትን ያመልክ ነበር። (ኢያሱ 24:2) ሆኖም አብርሃም ይሖዋን ለማምለክ መረጠ። አብርሃም ስለ እውነተኛው አምላክ የተማረው ከኖኅ ልጆች አንዱ ከሆነው ከቅድመ አያቱ ከሴም ሳይሆን አይቀርም። አብርሃም 150 ዓመት ገደማ እስኪሆነው ድረስ ሴም በሕይወት ነበር።
18 አብርሃም በሕይወት በኖረባቸው በርካታ ዓመታት ውስጥ ብዙ መሥዋዕቶችን አቅርቧል። ይሁንና እነዚህን መሥዋዕቶች በሙሉ ያቀረበው አምልኮ ሊቀርብለት የሚገባው ብቸኛ አካል ለሆነው ለይሖዋ ነው። (ዘፍ. 12:8፤ 13:18፤ 15:8-10) አብርሃም ከሁሉ የተሻለ ጥራት ያለውን መሥዋዕት ለይሖዋ ለማቅረብ ፈቃደኛ ነበር? የሚወደውን ልጁን ይስሐቅን ለመሠዋት ፈቃደኛ መሆኑን ባሳየበት ጊዜ ይህ ጥያቄ በማያሻማ ሁኔታ መልስ አግኝቷል። በዚህ ወቅት አብርሃም መሥዋዕቱን የሚያቀርብበትን መንገድ በተመለከተ ይሖዋ ዝርዝር መመሪያ ሰጥቶታል። (ዘፍ. 22:1, 2) አብርሃምም የተሰጠውን መመሪያ አንድም ሳያጓድል ለመከተል ፈቃደኛ ሆኗል። ይሖዋ ባያስቆመው ኖሮ ልጁን ከማረድ እንኳ አይመለስም ነበር። (ዘፍ. 22:9-12) ይሖዋ አብርሃም ያቀረበውን አምልኮ ተቀብሏል፤ ምክንያቱም አብርሃም ለይሖዋ አምልኮ ያቀርብ የነበረው በንጹሕ የልብ ዝንባሌ ተነሳስቶ ነው። ጳውሎስ “አብርሃም በይሖዋ አመነ፤ ይህም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት” ሲል ጽፏል።—ሮም 4:3
19, 20. ያዕቆብ ንጹሕ አምልኮ የሚጠይቃቸውን አራት መሠረታዊ መሥፈርቶች ያሟላው እንዴት ነው?
19 ያዕቆብ አብዛኛውን ሕይወቱን ያሳለፈው ይሖዋ ለአብርሃምና ለዘሮቹ ለመስጠት ቃል በገባው በከነዓን ምድር ነው። (ዘፍ. 17:1, 8) የከነዓን ነዋሪዎች እጅግ ብልሹ በሆነ አምልኮ የተተበተቡ ከመሆናቸው የተነሳ ይሖዋ ‘ምድሪቱ ነዋሪዎቿን እንደምትተፋቸው’ ተናግሮ ነበር። (ዘሌ. 18:24, 25) ያዕቆብ በ77 ዓመት ዕድሜው ከከነዓን የወጣ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ትዳር መሥርቶና ሰፊ ቤተሰብ ይዞ ወደዚያው ተመለሰ። (ዘፍ. 28:1, 2፤ 33:18) ይሁን እንጂ ከቤተሰቡ አባላት መካከል አንዳንዶቹን የሐሰት አምልኮ ተጽዕኖ አሳድሮባቸው ነበር። ሆኖም ይሖዋ ያዕቆብን ወደ ቤቴል እንዲሄድና በዚያም መሠዊያ እንዲሠራ በጠየቀው ጊዜ ወዲያውኑ እርምጃ ወስዷል። በመጀመሪያ ቤተሰቡን “በመካከላችሁ ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ራሳችሁን አንጹ” አላቸው። ከዚያም የተሰጠውን መመሪያ በታማኝነት ፈጸመ።—ዘፍ. 35:1-7
20 ያዕቆብ በተስፋይቱ ምድር ውስጥ በርካታ መሠዊያዎችን የገነባ ቢሆንም ሁልጊዜም አምልኮ ያቀርብ የነበረው ለይሖዋ ነው። (ዘፍ. 35:14፤ 46:1) ያቀረባቸው መሥዋዕቶች ጥራት፣ አምልኮ ያቀረበበት መንገድ እንዲሁም አምልኮ ለማቅረብ ያነሳሳው የልብ ዝንባሌ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ስለነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ያዕቆብን “ነቀፋ የሌለበት ሰው” በማለት ጠርቶታል፤ ይህ መግለጫ የሚያገለግለው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ ሰዎችን ለማመልከት ነው። (ዘፍ. 25:27) ያዕቆብ በሕይወት ዘመኑ በሙሉ ያደረገው ነገር ዘሮቹ ለሆኑት እስራኤላውያን ግሩም አርዓያ የሚሆን ነበር።—ዘፍ. 35:9-12
21. ጥንት የነበሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ከተዉት ምሳሌ ስለ ንጹሕ አምልኮ ምን መማር እንችላለን?
21 ጥንት የነበሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ከተዉት ምሳሌ ስለ ንጹሕ አምልኮ ምን መማር እንችላለን? እኛም በዙሪያችን ያሉት ሰዎች ምናልባትም የቤተሰባችን አባላት ለይሖዋ ብቻ የሚገባውን አምልኮ ለእሱ እንዳናቀርብ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን ይችላሉ። እንዲህ ያለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት ማዳበርና እሱ ያወጣቸው የጽድቅ መሥፈርቶች ከሁሉ የተሻሉ መሆናቸውን አምነን መቀበል ይኖርብናል። ይሖዋን በመታዘዝ እንዲሁም ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ንብረታችንን ለእሱ አገልግሎት በማዋል እንዲህ ያለ እምነት እንዳለን እናሳያለን። (ማቴ. 22:37-40፤ 1 ቆሮ. 10:31) ይሖዋን አቅማችን በሚፈቅደው መጠን፣ እሱ በሚጠይቀው መንገድና በንጹሕ የልብ ዝንባሌ ተነሳስተን ስናመልከው ጻድቅ አድርጎ እንደሚመለከተን ማወቃችን ምንኛ የሚያበረታታ ነው!—ያዕቆብ 2:18-24ን አንብብ።
ለንጹሕ አምልኮ የተወሰነ ብሔር
22-24. ሕጉ እስራኤላውያን መሥዋዕት የሚያቀርቡለትን አካል፣ የመሥዋዕቱን ጥራትና የሚቀርብበትን መንገድ በተመለከተ ግልጽ መመሪያ የሰጣቸው እንዴት ነበር?
22 ይሖዋ ለያዕቆብ ዘሮች ሕጉን ሰጥቷቸው ስለነበር አምላክ ከእነሱ ምን እንደሚፈልግ በግልጽ ማወቅ ይችሉ ነበር። ይሖዋን ከታዘዙ የእሱ ‘ልዩ ንብረቶች’ እንዲሁም “ቅዱስ ብሔር” የመሆን አጋጣሚ ያገኙ ነበር። (ዘፀ. 19:5, 6) ሕጉ ከንጹሕ አምልኮ ጋር በተያያዘ መሟላት ያለባቸውን አራት መሥፈርቶች እንዴት ጎላ አድርጎ እንደሚገልጽ ልብ በል።
23 ይሖዋ እስራኤላውያን አምልኮ ማቅረብ ያለባቸው ለማን እንደሆነ በግልጽ ነግሯቸዋል። “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ” ብሏቸው ነበር። (ዘፀ. 20:3-5) ለእሱ የሚያቀርቧቸው መሥዋዕቶች ከፍተኛ ጥራት ያላቸው መሆን ነበረባቸው። ለምሳሌ ያህል፣ መሥዋዕት አድርገው የሚያቀርቧቸው እንስሳት ጤናማና ምንም ዓይነት እንከን የሌለባቸው ሊሆኑ ይገባል። (ዘሌ. 1:3፤ ዘዳ. 15:21፤ ከሚልክያስ 1:6-8 ጋር አወዳድር።) ሌዋውያን ለይሖዋ ከሚቀርበው ስጦታ ተጠቃሚ ቢሆኑም እነሱም ለይሖዋ መባ ማቅረብ ነበረባቸው። ‘ከሚቀበሏቸው ስጦታዎች ሁሉ ላይ ምርጥ የሆነውን’ መስጠት ይጠበቅባቸው ነበር። (ዘኁ. 18:29) እስራኤላውያን አምልኮ የሚያቀርቡበትን መንገድ በተመለከተም ማለትም ምን፣ የትና እንዴት መሥዋዕት ማቅረብ እንዳለባቸው ግልጽ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል። አኗኗራቸውንና ምግባራቸውን የሚመለከቱ በአጠቃላይ ከ600 የሚበልጡ ሕጎች ተሰጥተዋቸው ነበር፤ “አምላካችሁ ይሖዋ ያዘዛችሁን በጥንቃቄ ፈጽሙ። ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር አትበሉ” ተብለዋል።—ዘዳ. 5:32
24 እስራኤላውያን መሥዋዕት የሚያቀርቡበት ቦታ ለውጥ ያመጣል? አዎ። ይሖዋ ሕዝቦቹን የማደሪያ ድንኳን እንዲሠሩ አዟቸው ነበር፤ ይህ የማደሪያ ድንኳን የንጹሕ አምልኮ ማዕከል ሆኖ አገልግሏል። (ዘፀ. 40:1-3, 29, 34) በዚያ ዘመን እስራኤላውያን የሚያቀርቡት ስጦታ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፈለጉ ስጦታውን ወደ ማደሪያ ድንኳኑ ማምጣት ነበረባቸው። d—ዘዳ. 12:17, 18
25. መሥዋዕት ከማቅረብ ጋር በተያያዘ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ምንድን ነው? አብራራ።
25 ይሁን እንጂ ከሁሉ ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው አንድ እስራኤላዊ ስጦታ ለማቅረብ የተነሳሳበት የልብ ዝንባሌ ነው! ለይሖዋና እሱ ላወጣቸው መሥፈርቶች ባለው ልባዊ ፍቅር ተነሳስቶ አምልኮ ማቅረብ ይጠበቅበት ነበር። (ዘዳግም 6:4-6ን አንብብ።) ይሖዋ፣ እስራኤላውያን እንዲሁ በዘልማድ አምልኮ በሚያቀርቡበት ጊዜ መሥዋዕታቸውን አይቀበልም ነበር። (ኢሳ. 1:10-13) ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት “ይህ ሕዝብ . . . [በከንፈሩ] ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው” በማለት የተናገረው ሐሳብ ለይስሙላ ያህል በሚቀርብ አምልኮ እንደማይታለል በግልጽ ያሳያል።—ኢሳ. 29:13
በቤተ መቅደሱ ይቀርብ የነበረው አምልኮ
26. ሰለሞን የሠራው ቤተ መቅደስ ከንጹሕ አምልኮ ጋር በተያያዘ መጀመሪያ ላይ ምን ሚና ተጫውቷል?
26 እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ገብተው መኖር ከጀመሩ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ንጉሥ ሰለሞን ከማደሪያ ድንኳኑ እጅግ የሚበልጥ የንጹሕ አምልኮ ማዕከል ገነባ። (1 ነገ. 7:51፤ 2 ዜና 3:1, 6, 7) መጀመሪያ ላይ በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ መሥዋዕት የሚቀርበው ለይሖዋ ብቻ ነበር። ሰለሞንም ሆነ ተገዢዎቹ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን እጅግ ብዙ መሥዋዕቶች የአምላክ ሕግ በሚያዝዘው መንገድ አቅርበዋል። (1 ነገ. 8:63) ይሁን እንጂ በቤተ መቅደሱ ይቀርብ የነበረው አምልኮ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያስቻለው ሕንፃውን ለመሥራት የወጣው ከፍተኛ ወጪና የመሥዋዕቶቹ ብዛት አልነበረም። ትልቅ ቦታ የተሰጠው ነገር ሰዎቹ መሥዋዕቶቹን ለማቅረብ የተነሳሱበት የልብ ዝንባሌ ነበር። ሰለሞን ቤተ መቅደሱ በተወሰነበት ዕለት ይህን ጎላ አድርጎ ተናግሯል። “እንደ ዛሬው ዕለት ሁሉ በአምላካችን በይሖዋ ሥርዓቶች በመሄድና ትእዛዛቱን በመጠበቅ ልባችሁ በእሱ ዘንድ ሙሉ ይሁን” ብሏል።—1 ነገ. 8:57-61
27. የእስራኤል ነገሥታትና ተገዢዎቻቸው ምን አደረጉ? ይሖዋስ በዚህ ጊዜ ምን አደረገ?
27 የሚያሳዝነው ግን እስራኤላውያን ንጉሡ የሰጣቸውን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር መከተላቸውን አልቀጠሉም። ንጹሕ አምልኮ ከሚጠይቃቸው መሠረታዊ መሥፈርቶች መካከል አንዱን ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑትን ሳያሟሉ ቀርተዋል። የእስራኤል ነገሥታትና ተገዢዎቻቸው ልባቸው እንዲበከል ፈቀዱ፤ በይሖዋ ላይ የነበራቸውን እምነት አጡ፤ የጽድቅ መሥፈርቶቹንም ወደ ጎን ገሸሽ አደረጉ። አፍቃሪ አምላክ የሆነው ይሖዋ እነሱን ለማረምና የሚከተሉት አካሄድ ስለሚያስከትለው ውጤት ለማስጠንቀቅ ሲል በተደጋጋሚ ነቢያትን ወደ እነሱ ይልክ ነበር። (ኤር. 7:13-15, 23-26) በዋነኝነት ከሚጠቀሱት ነቢያት መካከል አንዱ ታማኙ ሕዝቅኤል ነው። ሕዝቅኤል የኖረው በንጹሕ አምልኮ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ ነበር።
ሕዝቅኤል ንጹሕ አምልኮ ሲበከል ተመልክቷል
28, 29. ስለ ሕዝቅኤል ምን የምናውቀው ነገር አለ? (“ሕዝቅኤል—ያሳለፈው ሕይወትና የኖረበት ዘመን” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
28 ሕዝቅኤል፣ ሰለሞን በገነባው ቤተ መቅደስ ውስጥ ይካሄድ ስለነበረው አምልኮ በሚገባ ያውቅ ነበር። አባቱ ካህን የነበረ ሲሆን ተራው ሲደርስ በቤተ መቅደሱ ያገለግል ነበር። (ሕዝ. 1:3) የሕዝቅኤል የልጅነት ሕይወት አስደሳች ሳይሆን አይቀርም። አባቱ ስለ ይሖዋና ስለ ሕጉ እንዳስተማረው ጥርጥር የለውም። እንዲያውም ሕዝቅኤል በተወለደበት ጊዜ አካባቢ ‘የሕጉ መጽሐፍ’ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ተገኝቶ ነበር። e በወቅቱ ንጉሥ የነበረው ኢዮስያስ የሕጉ መጽሐፍ ሲነበብ በሰማው ነገር ልቡ እጅግ ስለተነካ ንጹሕ አምልኮን ለማስፋፋት የሚያደርገውን ጥረት ይበልጥ አጧጧፈ።—2 ነገ. 22:8-13
29 ሕዝቅኤል ከእሱ በፊት እንደኖሩት ታማኝ ሰዎች ሁሉ ንጹሕ አምልኮ የሚጠይቃቸውን አራት መሥፈርቶች አሟልቷል። የሕዝቅኤልን መጽሐፍ ስንመረምር ሕዝቅኤል ይሖዋን ብቻ እንዳመለከ፣ ምንጊዜም ለይሖዋ ምርጡን እንደሰጠ እንዲሁም ይሖዋ እንዲያደርግ የጠየቀውን ነገር ሁሉ እሱ በሚፈልገው መንገድ በታዛዥነት እንደፈጸመ መረዳት እንችላለን። ሕዝቅኤል ይህን ሁሉ እንዲያደርግ የገፋፋው በይሖዋ ላይ ያለው ከልብ የመነጨ እምነት ነው። በዘመኑ የነበሩት አብዛኞቹ እስራኤላውያን ግን እንደ እሱ አልነበሩም። ሕዝቅኤል በ647 ዓ.ዓ. አገልግሎቱን የጀመረውንና ስለ መጪው የይሖዋ ፍርድ በቅንዓት ያስጠነቅቅ የነበረውን የኤርምያስን ትንቢቶች ከልጅነቱ ጀምሮ ሲሰማ ኖሯል።
30. (ሀ) ሕዝቅኤል የጻፋቸው ትንቢቶች ምን ይገልጻሉ? (ለ) ትንቢት ምንድን ነው? ሕዝቅኤል የተናገራቸውን ትንቢቶች መረዳት የሚኖርብንስ እንዴት ነው? (“የሕዝቅኤልን ትንቢቶች መረዳት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
30 ሕዝቅኤል በመንፈስ ተመርቶ የጻፈው መልእክት የአምላክ ሕዝቦች ከይሖዋ አምልኮ ምን ያህል እንደራቁ ያሳያል። (ሕዝቅኤል 8:6ን አንብብ።) ይሖዋ በአይሁዳውያን ላይ የቅጣት እርምጃ መውሰድ በጀመረበት ወቅት ወደ ባቢሎን በግዞት ከተወሰዱት አይሁዳውያን መካከል ሕዝቅኤልም ይገኝበት ነበር። (2 ነገ. 24:11-17) ሆኖም ሕዝቅኤል በግዞት የተወሰደው እንዲቀጣ አይደለም። ይሖዋ ግዞት ላይ በሚገኙ ሕዝቦቹ መካከል እንዲሠራ የፈለገው ሥራ ነበር። ሕዝቅኤል የመዘገባቸው አስደናቂ ራእዮችና ትንቢቶች ንጹሕ አምልኮ እንዴት በኢየሩሳሌም መልሶ እንደሚቋቋም ያሳያሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ንጹሕ አምልኮ ይሖዋን ለሚወዱ ሁሉ ሙሉ በሙሉ መልሶ የሚቋቋመው እንዴት እንደሆነ ያስገነዝቡናል።
31. በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
31 በቀጣዮቹ የዚህ መጽሐፍ ክፍሎች ላይ የይሖዋ ማደሪያ የሆነው ሰማይ ምን እንደሚመስል ትንሽ ፍንጭ እናገኛለን፤ በተጨማሪም ንጹሕ አምልኮ ምን ያህል ተበክሎ እንደነበረ፣ ይሖዋ ሕዝቡን የጠበቀውና ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንዲቋቋም ያደረገው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ሁሉም ሰው ይሖዋን ብቻ የሚያመልክበት ጊዜ ሲመጣ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር እንመለከታለን። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ሕዝቅኤል የመዘገበውን የመጀመሪያ ራእይ እንመረምራለን። ይህ ራእይ ይሖዋንና የድርጅቱን ሰማያዊ ክፍል በዓይነ ሕሊናችን መሣል እንድንችል የሚረዳን ሲሆን ይህም ንጹሕ አምልኮ ሊቀርብለት የሚገባው ይሖዋ ብቻ የሆነው ለምን እንደሆነ እንድንገነዘብ ያስችለናል።
a አቤል የተጸነሰው አዳምና ሔዋን ከገነት ከተባረሩ ብዙም ሳይቆይ እንደሆነ መገመት ይቻላል። (ዘፍ. 4:1, 2) ዘፍጥረት 4:25 አምላክ ‘በአቤል ፋንታ’ ሴትን እንደተካው ይናገራል። አዳም ሴትን ሲወልድ 130 ዓመቱ ነበር፤ ሴት የተወለደው አቤል በአሰቃቂ ሁኔታ ከተገደለ በኋላ ነው። (ዘፍ. 5:3) ስለዚህ ቃየን አቤልን ሲገድለው የአቤል ዕድሜ 100 ዓመት ገደማ ሊሆን ይችላል።
b ዘፍጥረት 4:26 የአዳም የልጅ ልጅ በሆነው በሄኖስ ዘመን “ሰዎች የይሖዋን ስም መጥራት” እንደጀመሩ ይናገራል። ሆኖም የይሖዋን ስም ይጠሩ የነበረው አክብሮት በጎደለው መንገድ እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል፤ ምናልባትም ስሙን ለጣዖቶቻቸው ሰጥተው ሊሆን ይችላል።
c ናና የተባለው አምላክ ሲን በሚል ስምም ይታወቅ ነበር። የዑር ነዋሪዎች በርካታ አማልክትን ያመልኩ የነበረ ቢሆንም በዚህች ከተማ የነበሩት ቤተ መቅደሶችና መሠዊያዎች በዋነኝነት ይህ አምላክ የሚመለክባቸው ነበሩ።
d ታቦቱ ከማደሪያ ድንኳኑ ከወጣ በኋላ ይሖዋ መሥዋዕቶች በሌሎች ቦታዎችም እንዲቀርቡ የፈቀደ ይመስላል።—1 ሳሙ. 4:3, 11፤ 7:7-9፤ 10:8፤ 11:14, 15፤ 16:4, 5፤ 1 ዜና 21:26-30