በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 7

ብሔራት “እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ”

ብሔራት “እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ”

ሕዝቅኤል 25:17

ፍሬ ሐሳብ፦ እስራኤል የይሖዋን ስም ካቃለሉ ብሔራት ጋር ከነበራት ግንኙነት የምናገኘው ትምህርት

1, 2. (ሀ) እስራኤል፣ ብቻዋን በተኩላ መንጋ መካከል እንዳለች በግ የነበረችው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) የእስራኤል ሕዝብና ንጉሦቻቸው ምን ዓይነት አኗኗር ተከትለዋል?

 በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት እስራኤል፣ ብቻዋን በተኩላ መንጋ መካከል እንዳለች በግ ሆና ኖራለች። በስተ ምሥራቅ አሞናውያን፣ ሞዓባውያንና ኤዶማውያን ያስፈራሯታል። በስተ ምዕራብ፣ የሁልጊዜ ጠላቶቿ የሆኑት ፍልስጤማውያን ተደላድለው ሰፍረዋል። በስተ ሰሜን፣ እጅግ ሰፊ የሆነ የንግድ ግዛት የነበራት ባለጸጋዋ የጢሮስ ከተማ ትገኛለች። በስተ ደቡብ ደግሞ አምላክ ነኝ በሚለው ንጉሥዋ በፈርዖን የምትገዛው ጥንታዊቷ ግብፅ ተንሰራፍታ ተቀምጣለች።

2 እስራኤላውያን በይሖዋ ይታመኑ በነበረበት ጊዜ እሱ ከጠላቶቻቸው ይጠብቃቸው ነበር። ይሁን እንጂ የእስራኤል ሕዝብና ንጉሦቻቸው በዙሪያቸው የሚገኙትን ብሔራት ብልሹ አኗኗር ለመከተል መርጠዋል። ንጉሥ አክዓብ በሌሎች ተጽዕኖ ተሸንፈው ክህደት ከፈጸሙ ነገሥታት መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው። ንጉሥ አክዓብ ከይሁዳ ንጉሥ ከኢዮሳፍጥ ጋር በተመሳሳይ ወቅት የኖረ ሲሆን የአሥሩን ነገድ የእስራኤል መንግሥት ይገዛ ነበር። አክዓብ እጅግ ባለጸጋ የሆነችውን የጢሮስ ከተማ ይገዛ የነበረውን የሲዶናውያን ንጉሥ ሴት ልጅ አግብቶ ነበር። ኤልዛቤል የተባለችው ይህች ሴት የባአልን አምልኮ በእስራኤል ውስጥ ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች፤ ባሏንም ከዚያ በፊት ሆኖ በማያውቅ መጠን ንጹሕ አምልኮን እንዲበክል ተጽዕኖ አሳድራበታለች።—1 ነገ. 16:30-33፤ 18:4, 19

3, 4. (ሀ) አሁን ሕዝቅኤል ትኩረቱን ወደ ማን አዞረ? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 ይሖዋ እሱን መካድ ስለሚያስከትለው መዘዝ ሕዝቡን ሲያስጠነቅቅ ኖሯል። አሁን ግን ትዕግሥቱ አልቋል። (ኤር. 21:7, 10፤ ሕዝ. 5:7-9) በ609 ዓ.ዓ. የባቢሎናውያን ሠራዊት ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ተስፋይቱ ምድር ተመለሰ። ይህ የሆነው ለመጨረሻ ጊዜ ወረራ ካካሄደ ከአሥር ዓመት ገደማ በኋላ ነው። በዚህኛው ከበባ ወቅት ባቢሎናውያን የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ያፈረሱ ከመሆኑም ሌላ በናቡከደነጾር ላይ ያመፁትን ደምስሰዋል። ከበባው በጀመረበትና በመንፈስ መሪነት የተነገሩት የሕዝቅኤል ትንቢቶች አንድ በአንድ ፍጻሜያቸውን እያገኙ በነበረበት በዚህ ወቅት ነቢዩ ትኩረቱን ወደ ተስፋይቱ ምድር አጎራባች ብሔራት አዞረ።

የይሖዋን ስም ያቃለሉት ብሔራት የእጃቸውን ማግኘታቸው አይቀርም

4 ይሖዋ የይሁዳ ጠላቶች በኢየሩሳሌም መውደም እንደሚፈነጥዙና ከጥፋቱ የተረፉትን አይሁዳውያን እንደሚያንገላቱ ለሕዝቅኤል ገለጸለት። ይሁን እንጂ የይሖዋን ስም ያቃለሉትም ሆኑ ሕዝቡን ያሳደዱት ወይም የበከሉት ብሔራት የእጃቸውን ማግኘታቸው አይቀርም። እስራኤል ከእነዚህ ብሔራት ጋር ከነበራት ግንኙነት ምን ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን? ሕዝቅኤል ስለ እነዚህ ብሔራት የተናገራቸው ትንቢቶች ለእኛስ ተስፋ የሚሰጡን እንዴት ነው?

‘በንቀት የተሞሉ’ የእስራኤል ዘመዶች

5, 6. በአሞናውያንና በእስራኤላውያን መካከል ምን ዝምድና ነበር?

5 አሞን፣ ሞዓብና ኤዶም የእስራኤል የሥጋ ዘመዶች ነበሩ ማለት ይቻላል። እነዚህ ብሔራት ከእስራኤል ጋር የቤተሰብ ትስስርና የጋራ ታሪክ የነበራቸው ቢሆንም ለአምላክ ሕዝብ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ጥላቻና “ንቀት” ነበራቸው።—ሕዝ. 25:6

6 አሞናውያንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አሞናውያን የአብርሃም የወንድሙ ልጅ የሆነው የሎጥ ዘሮች ናቸው፤ ሎጥ ከታናሽየዋ ልጁ የወለደው ልጅ የአሞናውያን አባት ነው። (ዘፍ. 19:38) ቋንቋቸው ከዕብራይስጥ ጋር በጣም የተቀራረበ በመሆኑ የአምላክ ሕዝቦች አሞናውያን የሚናገሩትን ቋንቋ መረዳት ሳይችሉ አይቀሩም። ይሖዋም እስራኤላውያን በአሞናውያን ላይ ጦርነት እንዳይቀሰቅሱ የነገራቸው በመካከላቸው እንዲህ ያለ ዝምድና ስለነበረ ነው። (ዘዳ. 2:19) ሆኖም በመሳፍንት ዘመን አሞናውያን ኤግሎን ከተባለው ሞዓባዊ ንጉሥ ጋር በማበር እስራኤላውያንን ጨቁነዋል። (መሳ. 3:12-15, 27-30) በኋላ ላይም ሳኦል በነገሠበት ወቅት አሞናውያን በእስራኤል ላይ ጥቃት ሰንዝረው ነበር። (1 ሳሙ. 11:1-4) በተጨማሪም በንጉሥ ኢዮሳፍጥ ዘመን ከሞዓባውያን ጋር በድጋሚ ግንባር ፈጥረው በተስፋይቱ ምድር ላይ ዘምተዋል።—2 ዜና 20:1, 2

7. ሞዓባውያን፣ ዘመዶቻቸው በሆኑት የእስራኤል ዘሮች ላይ ምን አደረጉ?

7 ሞዓባውያንም ቢሆኑ ሎጥ ከመጀመሪያዋ ልጁ የወለደው ልጅ ዘሮች ናቸው። (ዘፍ. 19:36, 37) ይሖዋ ለእስራኤላውያን ከሞዓብ ጋር ጦርነት እንዳይገጥሙ ነግሯቸው ነበር። (ዘዳ. 2:9) ሞዓባውያን ግን ለተደረገላቸው ደግነት ውለታ ቢስ ሆነዋል። ከግብፅ ባርነት አምልጠው የመጡትን ዘመዶቻቸውን ከመርዳት ይልቅ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገቡ ለማገድ ሞከሩ። የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ፣ እስራኤላውያንን እንዲረግምለት በለዓምን ቀጠረ፤ በለዓምም እስራኤላውያን ወንዶች ዝሙት እንዲፈጽሙና ጣዖት እንዲያመልኩ ማድረግ የሚችልበትን መንገድ ለባላቅ ነገረው። (ዘኁ. 22:1-8፤ 25:1-9፤ ራእይ 2:14) ሞዓባውያን እስከ ሕዝቅኤል ዘመን ድረስ ለበርካታ መቶ ዓመታት ዘመዶቻቸውን ሲጨቁኑ ኖረዋል።—2 ነገ. 24:1, 2

8. ይሖዋ ኤዶማውያን የእስራኤላውያን ወንድሞች እንደሆኑ የተናገረው ለምንድን ነው? ኤዶማውያን ግን ምን አደረጉ?

8 ኤዶማውያን የያዕቆብ መንትያ ወንድም የሆነው የኤሳው ዘሮች ነበሩ። በኤዶማውያንና በእስራኤላውያን መካከል የቅርብ ዝምድና ስለነበር ይሖዋ ወንድማማቾች እንደሆኑ ተናግሯል። (ዘዳ. 2:1-5፤ 23:7, 8) ያም ቢሆን ኤዶማውያን፣ እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡበት ዘመን አንስቶ ኢየሩሳሌም በ607 ዓ.ዓ. እስከጠፋችበት ጊዜ ድረስ እስራኤልን ሲቃወሙ ኖረዋል። (ዘኁ. 20:14, 18፤ ሕዝ. 25:12) በ607 ዓ.ዓ. ኤዶማውያን፣ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን እንዲያወድሙ በመገፋፋት በእስራኤል ላይ በደረሰው መከራ መፈንጠዛቸው ሳያንስ ሸሽተው ያመለጡትን እስራኤላውያን እየያዙ ለጠላቶቻቸው አሳልፈው ይሰጡ ነበር።—መዝ. 137:7፤ አብ. 11, 14

9, 10. (ሀ) አሞን፣ ሞዓብና ኤዶም ምን ደረሰባቸው? (ለ) በእነዚህ ብሔራት ውስጥ ያሉ ሰዎች በሙሉ ለእስራኤላውያን ጥላቻ ነበራቸው ማለት እንዳልሆነ የሚያሳዩት የትኞቹ ምሳሌዎች ናቸው?

9 ይሖዋ የእስራኤላውያን ዘመዶች የሆኑት እነዚህ ብሔራት በሕዝቦቹ ላይ ለፈጸሙት በደል ፍርዳቸውን እንዲቀበሉ አድርጓል። ‘አሞናውያንን ለምሥራቅ ሰዎች ርስት አድርጌ እሰጣለሁ፤ ይህም አሞናውያን በብሔራት መካከል እንዳይታወሱ ለማድረግ ነው’ ብሎ ነበር። በተጨማሪም “በሞዓብም ላይ የፍርድ እርምጃ እወስዳለሁ፤ እነሱም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ” ብሏል። (ሕዝ. 25:10, 11) ኢየሩሳሌም ከወደቀች ከአምስት ዓመት ገደማ በኋላ ባቢሎናውያን አሞንንና ሞዓብን ድል ባደረጉ ጊዜ እነዚህ ትንቢቶች መፈጸም ጀመሩ። ይሖዋ ኤዶምን በተመለከተ ደግሞ “ከምድሪቱም ላይ ሰውንም ሆነ ከብትን አጠፋለሁ፤ ባድማም አደርጋታለሁ” ብሏል። (ሕዝ. 25:13) ልክ ይሖዋ እንደተናገረው አሞን፣ ሞዓብና ኤዶም የኋላ ኋላ ከሕልውና ውጭ ሆነዋል።—ኤር. 9:25, 26፤ 48:42፤ 49:17, 18

10 ይሁን እንጂ በእነዚህ ብሔራት ውስጥ ያሉ ሰዎች በሙሉ ለአምላክ ሕዝቦች ጥላቻ ነበራቸው ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል አሞናዊው ጼሌቅና ሞዓባዊው ይትማ ከንጉሥ ዳዊት ኃያላን ተዋጊዎች መካከል ተጠቅሰዋል። (1 ዜና 11:26, 39, 46፤ 12:1) ሞዓባዊቷ ሩትም ብትሆን ታማኝ የይሖዋ አምላኪ ሆናለች።—ሩት 1:4, 16, 17

ትንሽም እንኳ ቢሆን አቋማችንን ማላላት የለብንም

11. እስራኤል ከአሞን፣ ከሞዓብና ከኤዶም ጋር ከነበራት ግንኙነት ምን ትምህርት እናገኛለን?

11 እስራኤል ከእነዚህ ብሔራት ጋር ከነበራት ግንኙነት ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? በመጀመሪያ ደረጃ፣ እስራኤላውያን አቋማቸውን ባላሉበት ወቅት የዘመዶቻቸው በካይ የሐሰት ሃይማኖት ልማዶች ወደ እነሱ ሰርገው እንደገቡ ከታሪካቸው መመልከት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል የሞዓባውያን አምላክ የሆነውን የፌጎርን ባአልና የአሞናውያን አምላክ የሆነውን ሞሎክን ያመለኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። (ዘኁ. 25:1-3፤ 1 ነገ. 11:7) እኛም ተመሳሳይ ነገር ሊያጋጥመን ይችላል። የማያምኑ ዘመዶቻችን አቋማችንን እንድናላላ ግፊት ሊያደርጉብን ይችላሉ። ለምሳሌ ፋሲካን የማናከብረው፣ የገና ስጦታ የማንለዋወጠው ወይም ከሐሰት ሃይማኖት ጋር በተያያዙ ሌሎች ልማዶች የማንካፈለው ለምን እንደሆነ ላይገባቸው ይችላል። በቅን ልቦና ተነሳስተው ለቅጽበትም እንኳ ቢሆን አቋማችንን ላላ እንድናደርግ ሊጫኑን ይችላሉ። ይሁን እንጂ እንደዚህ ላሉት ተጽዕኖዎች ላለመሸነፍ ቁርጥ ውሳኔ ማድረጋችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! የእስራኤል ታሪክ እንደሚያሳየው ከአቋማችን ትንሽ እንኳ ሸርተት ማለት ከፍተኛ ውድቀት ሊያስከትልብን ይችላል።

12, 13. ምን ዓይነት ተቃውሞ ሊያጋጥመን ይችላል? ሆኖም በታማኝነት ከጸናን ምን ውጤት ልናገኝ እንችላለን?

12 እስራኤል ከአሞን፣ ከሞዓብና ከኤዶም ጋር ከነበራት ግንኙነት የምናገኘው ሌላም ትምህርት አለ። ከማያምኑ የቤተሰባችን አባላት ከባድ ተቃውሞ ሊደርስብን ይችላል። ኢየሱስ የምንሰብከው መልእክት አንዳንድ ጊዜ “ወንድ ልጅን ከአባቱ፣ ሴት ልጅን ከእናቷ” ሊለያይ እንደሚችል አስጠንቅቋል። (ማቴ. 10:35, 36) ይሖዋ ለእስራኤላውያን፣ ዘመዶቻቸው ከሆኑት ብሔራት ጋር ግጭት እንዳይፈጥሩ መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር፤ እኛም ከማያምኑ የቤተሰባችን አባላት ጋር መጋጨት አንፈልግም። ሆኖም ተቃውሞ ቢያጋጥመን ልንገረም አይገባም።—2 ጢሞ. 3:12

13 ዘመዶቻችን ለይሖዋ የምናቀርበውን አምልኮ በቀጥታ ባይቃወሙም እንኳ በሕይወታችን ውስጥ ከይሖዋ የበለጠ ቦታ እንዲኖራቸው መፍቀድ አይኖርብንም። ለምን? ምክንያቱም በልባችን ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ ሊይዝ የሚገባው ይሖዋ ነው። (ማቴዎስ 10:37ን አንብብ።) በተጨማሪም ለይሖዋ ታማኝ ሆነን ከቀጠልን አንዳንድ ዘመዶቻችን እንደ ጼሌቅ፣ ይትማና ሩት አብረውን በንጹሕ አምልኮ መካፈል ሊጀምሩ ይችላሉ። (1 ጢሞ. 4:16) ያን ጊዜ እነሱም፣ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን ማምለክ የሚያስገኘውን ደስታ ያጣጥማሉ፤ ፍቅሩንና ጥበቃውንም ያገኛሉ።

የይሖዋ ጠላቶች “ኃይለኛ ቅጣት” ተቀበሉ

14, 15. ፍልስጤማውያን በእስራኤላውያን ላይ ምን አደረጉ?

14 ፍልስጤማውያን፣ ከቀርጤስ ደሴት ተነስተው ይሖዋ ከጊዜ በኋላ ለአብርሃምና ለዘሮቹ ቃል ወደገባው ምድር የፈለሱ ሕዝቦች ናቸው። አብርሃምም ሆነ ይስሐቅ ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር የሚያገናኟቸው የተለያዩ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸው ነበር። (ዘፍ. 21:29-32፤ 26:1) እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር በገቡበት ወቅት ፍልስጤማውያን የማይበገር የጦር ሠራዊት ያለው ኃያል ብሔር ሆነው ነበር። ፍልስጤማውያን እንደ ባአልዜቡብና ዳጎን ያሉትን የሐሰት አማልክት ያመልኩ ነበር። (1 ሳሙ. 5:1-4፤ 2 ነገ. 1:2, 3) እስራኤላውያንም እነዚህን አማልክት አብረዋቸው ያመለኩባቸው ጊዜያት ነበሩ።—መሳ. 10:6

15 ይሖዋ እስራኤል በፈጸመችው ክህደት ምክንያት ፍልስጤማውያን ሕዝቦቹን ለበርካታ ዓመታት እንዲገዙ ፈቅዶላቸዋል። (መሳ. 10:7, 8፤ ሕዝ. 25:15) ፍልስጤማውያን በእስራኤላውያን ላይ ጨቋኝ ገደቦችን a የጣሉ ከመሆኑም በላይ የብዙዎችን ሕይወት አጥፍተዋል። (1 ሳሙ. 4:10) ሆኖም ይሖዋ እስራኤላውያን ንስሐ ገብተው ወደ እሱ ሲመለሱ ያድናቸው ነበር። ሕዝቡን ለመታደግ እንደ ሳምሶን፣ ሳኦልና ዳዊት ያሉትን ሰዎች አስነስቷል። (መሳ. 13:5, 24፤ 1 ሳሙ. 9:15-17፤ 18:6, 7) ፍልስጤማውያን መጀመሪያ በባቢሎናውያን፣ በኋላም በግሪካውያን በተወረሩበት ወቅት ሕዝቅኤል በተነበየው መሠረት “ኃይለኛ ቅጣት” ተቀብለዋል።—ሕዝ. 25:15-17

16, 17. እስራኤል ከፍልስጤማውያን ጋር ከነበራት ግንኙነት ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

16 እስራኤል ከፍልስጤማውያን ጋር ከነበራት ግንኙነት ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? በዘመናችንም የይሖዋ ሕዝቦች እጅግ ኃያል ከሚባሉ ብሔራት ተቃውሞ ደርሶባቸዋል። እርግጥ ነው፣ እኛ እንደ እስራኤላውያን መቼም ቢሆን ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት አናጓድልም። ያም ቢሆን የንጹሕ አምልኮ ጠላቶች ድል የተቀዳጁ የሚመስልበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ ያህል በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ድርጅቱን ግንባር ቀደም ሆነው በሚመሩ ወንድሞች ላይ ለአሥርተ ዓመታት የሚዘልቅ እስራት በመፍረድ የይሖዋን ሕዝቦች ሥራ ለማስቆም ሞክሮ ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ደግሞ በጀርመን የነበረው የናዚ ፓርቲ በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮችን በማሰርና በመቶዎች የሚቆጠሩትን በመግደል የአምላክ ሕዝቦችን ጠራርጎ ለማጥፋት ሞክሮ ነበር። ሶቪየት ኅብረትም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ወንድሞቻችንን የጉልበት ሥራ ወደሚሠራባቸው ካምፖች በመላክና ጠረፍ ወደሆኑ አካባቢዎች በማጋዝ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ለረጅም ዓመታት የዘለቀ ዘመቻ አካሂዳለች።

17 መንግሥታት አሁንም ቢሆን የስብከት ሥራችንን ሊያግዱ፣ የአምላክን ሕዝቦች ሊያስሩ አልፎ ተርፎም አንዳንዶቹን ሊገድሉ ይችላሉ። እንደነዚህ ያሉት ድርጊቶች በፍርሃት እንድንርድ ወይም እምነት እንድናጣ ሊያደርጉን ይገባል? በፍጹም! ይሖዋ ታማኝ ሕዝቦቹ እንዲጠፉ አይፈቅድም። (ማቴዎስ 10:28-31ን አንብብ።) ኃያልና ጨቋኝ የሆኑ መንግሥታት ከሕልውና ውጭ ሲሆኑ፣ የይሖዋ ሕዝቦች ግን ማደጋቸውንና መጠናከራቸውን ሲቀጥሉ አይተናል። ፍልስጤማውያን ይሖዋን ለማወቅ እንደተገደዱ ሁሉ ሰብዓዊ መንግሥታትም በቅርቡ ይሖዋን ለማወቅ ይገደዳሉ። እነዚህ መንግሥታት እንደ ጥንቶቹ ፍልስጤማውያን ከሕልውና ውጭ ይሆናሉ!

‘የተትረፈረፈ ሀብት’ ዘላቂ ጥበቃ አላስገኘም

18. ጢሮስ ምን ዓይነት ከተማ ነበረች?

18 ጥንታዊቷ የጢሮስ b ከተማ በጥንቱ ዓለም ከነበሩት ታላላቅ የንግድ ማዕከሎች አንዷ ነበረች። በምዕራብ በኩል በሜድትራንያን ባሕር ላይ የተዘረጉ የንግድ መስመሮችን የሚያካልሉ በርካታ መርከቦች ነበሯት። በምሥራቅ በኩል ደግሞ ራቅ ካሉ ግዛቶች ጋር የሚያገናኙ የየብስ ላይ የንግድ መስመሮች ነበሯት። ከእነዚህ ሩቅ አካባቢዎች ለበርካታ መቶ ዓመታት ያግበሰበሰችው ንብረት እጅግ ባለጸጋ አድርጓታል። ነጋዴዎቿ በጣም የበለጸጉ ከመሆናቸው የተነሳ ራሳቸውን እንደ መኳንንት ይቆጥሩ ነበር።—ኢሳ. 23:8

19, 20. በጢሮስና በገባኦን ነዋሪዎች መካከል ምን ልዩነት አለ?

19 እስራኤል በንጉሥ ዳዊትና በንጉሥ ሰለሞን ዘመን ከጢሮስ ነዋሪዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት ነበራት። የዳዊት ቤተ መንግሥትም ሆነ የሰለሞን ቤተ መቅደስ በተገነባበት ጊዜ የጢሮስ ሰዎች ቁሳቁስና ባለሙያ አቅርበው ነበር። (2 ዜና 2:1, 3, 7-16) በዚያ ወቅት የጢሮስ ሰዎች እስራኤላውያን ለይሖዋ ታማኝ በመሆናቸው ምን ያህል እንደተባረኩ የማየት አጋጣሚ አግኝተው ነበር። (1 ነገ. 3:10-12፤ 10:4-9) በሺዎች የሚቆጠሩ ጢሮሳውያን ስለ ንጹሕ አምልኮ የማወቅ፣ ስለ ይሖዋ የመማርና እውነተኛውን አምላክ ማገልገል የሚያስገኘውን ጥቅም በገዛ ዓይናቸው የማየት ግሩም አጋጣሚ ነበራቸው።

20 የጢሮስ ነዋሪዎች ይህን የመሰለ ግሩም አጋጣሚ ቢያገኙም ቁሳዊ ሀብት በማሳደድ ላይ ብቻ ያተኮረ ሕይወት መምራታቸውን ቀጥለዋል። ይሖዋ ስላደረጋቸው ታላላቅ ነገሮች በመስማት ብቻ አገልጋዮቹ ለመሆን የተነሳሱትን የታላቋን ከተማ የገባኦንን ነዋሪዎች ምሳሌ አልተከተሉም። (ኢያሱ 9:2, 3, 22 እስከ 10:2) እንዲያውም የጢሮስ ነዋሪዎች የአምላክን ሕዝቦች እስከመቃወም አልፎ ተርፎም አንዳንዶቹን ለባርነት እስከመሸጥ ደርሰዋል።—መዝ. 83:2, 7፤ ኢዩ. 3:4, 6፤ አሞጽ 1:9

ቁሳዊ ነገሮችን ጥበቃ እንደሚያስገኝ ግንብ አድርገን ልንመለከታቸው አይገባም

21, 22. ጢሮስ ምን ደረሰባት? ለምንስ?

21 ይሖዋ ሕዝቡን ለሚቃወሙት ለእነዚህ ሰዎች በሕዝቅኤል በኩል እንዲህ በማለት ትንቢት ተናግሯል፦ “ጢሮስ ሆይ፣ እነሆ በአንቺ ላይ ተነስቻለሁ፤ ባሕር ሞገዱን እንደሚያስነሳ ብዙ ብሔራትን በአንቺ ላይ አስነሳለሁ። እነሱ የጢሮስን ቅጥሮች ያፈርሳሉ፤ ማማዎቿንም ያወድማሉ፤ አፈሯን ከላይዋ ጠርጌ አስወግዳለሁ፤ የሚያንጸባርቅ ገላጣ ዓለትም አደርጋታለሁ።” (ሕዝ. 26:1-5) የጢሮስ ነዋሪዎች፣ ሀብታቸው 46 ሜትር ከፍታ እንደነበረው የከተማቸው ቅጥር ጥበቃ እንደሚያስገኝላቸው ይተማመኑ ነበር። ሰለሞን “የባለጸጋ ሰው ሀብት የተመሸገ ከተማው ነው፤ በሐሳቡም ጥበቃ እንደሚያስገኝ ግንብ አድርጎ ይመለከተዋል” በማለት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ ቢሉ ይበጃቸው ነበር።—ምሳሌ 18:11

22 በመጀመሪያ ባቢሎናውያን፣ በኋላም ግሪካውያን የሕዝቅኤል ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ ባደረጉበት ወቅት የጢሮስ ነዋሪዎች የከተማዋ ብልጽግናም ሆነ ረጅሙ ቅጥራቸው ጥበቃ ያስገኝልናል ብለው ማሰባቸው ስህተት እንደነበረ ተገነዘቡ። ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ካወደሙ በኋላ በጢሮስ ላይ ለ13 ዓመት የቆየ ዘመቻ አካሄዱ። (ሕዝ. 29:17, 18) ከዚያም በ332 ዓ.ዓ. ታላቁ እስክንድር በሕዝቅኤል በኩል የተላለፈው ትንቢት አስደናቂ በሆነ መንገድ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አደረገ። c የእስክንድር ሠራዊት በየብስ ላይ የነበረችውን የጢሮስ ከተማ ፍርስራሽ ጠራርጎ ድንጋዮቹን፣ ሳንቃዎቹንና አፈሩን ባሕር ውስጥ በመጣል ደሴት ላይ ወደምትገኘው የከተማዋ ክፍል የሚያደርስ መንገድ ደለደለ። (ሕዝ. 26:4, 12) እስክንድር ቅጥሩን አፍርሶ በመግባት ከተማዋን በዘበዘ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿንና ዜጎቿን ገደለ፤ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ለባርነት ሸጠ። የጢሮስ ነዋሪዎች “የተትረፈረፈ ሀብት” ዘላቂ ጥበቃ እንደማያስገኝ ከደረሰባቸው መከራ ከተማሩ በኋላ ይሖዋን ለማወቅ ተገድደዋል።—ሕዝ. 27:33, 34

ጢሮስ ምንም ነገር የማይበግራት መስላ ብትታይም ልክ ሕዝቅኤል እንደተነበየው ጠፍታለች (አንቀጽ 22⁠ን ተመልከት)

23. ከጢሮስ ነዋሪዎች ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

23 ከጢሮስ ነዋሪዎች ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን? “ሀብት ያለው የማታለል ኃይል” ቁሳዊ ነገሮችን ጥበቃ እንደሚያስገኝ ግንብ አድርገን እንድንመለከታቸው እንዲያደርገን መፍቀድ አይኖርብንም። (ማቴ. 13:22) “ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት” አንችልም። (ማቴዎስ 6:24ን አንብብ።) ያለስጋት መኖር የሚችሉት ይሖዋን በሙሉ ነፍስ የሚያገለግሉ ብቻ ናቸው። (ማቴ. 6:31-33፤ ዮሐ. 10:27-29) በጢሮስ ላይ የተነገሩት ትንቢቶች አንድ በአንድ እንደተፈጸሙ ሁሉ ስለዚህ ሥርዓት ፍጻሜ የተነገሩ ትንቢቶችም አንድም ሳይቀር ይፈጸማሉ። ይሖዋ የዚህን ዓለም ስግብግብና ራስ ወዳድ የንግድ ሥርዓት በሚያጠፋበት ጊዜ ሀብትን መታመኛቸው ያደረጉ ሁሉ ይሖዋን ለማወቅ ይገደዳሉ።

“ከአገዳ” የማይሻል የፖለቲካ ኃይል

24-26. (ሀ) ይሖዋ ግብፅን “አገዳ” ሲል የጠራት ለምን ነበር? (ለ) ንጉሥ ሴዴቅያስ የይሖዋን መመሪያ እንደናቀ ያሳየው እንዴት ነበር? ይህስ ምን ውጤት አስከተለበት?

24 ከዮሴፍ ዘመን በፊት አንስቶ ባቢሎናውያን በኢየሩሳሌም ላይ እስከዘመቱበት ጊዜ ድረስ ግብፅ በተስፋይቱ ምድር አካባቢ በነበሩ አገሮች ላይ ቀላል የማይባል ፖለቲካዊ ተጽዕኖ የምታሳድር አገር ነበረች። የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት መሆኑ ረጅም ዕድሜ እንዳስቆጠረ ዛፍ የማትነቃነቅ መስላ እንድትታይ አድርጓት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ከይሖዋ ጋር ስትወዳደር “ከአገዳ” የማትሻል ነበረች።—ሕዝ. 29:6

25 ከሃዲው ንጉሥ ሴዴቅያስ ግን ግብፅን በተመለከተ ይህን እውነታ አላስተዋለም ነበር። ይሖዋ ሴዴቅያስን ለባቢሎን ንጉሥ እንዲገዛ በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት መክሮት ነበር። (ኤር. 27:12) ሴዴቅያስ በናቡከደነጾር ላይ ላለማመፅ በይሖዋ ስም ሳይቀር ምሎ ነበር። ሆኖም የይሖዋን መመሪያ ንቆ ለናቡከደነጾር የገባውን መሐላ በማፍረስ ከባቢሎን ጋር በሚያደርገው ውጊያ ግብፅ እንድትረዳው ጠየቀ። (2 ዜና 36:13፤ ሕዝ. 17:12-20) ይሁን እንጂ በግብፅ ፖለቲካዊ ኃይል የተማመኑት እስራኤላውያን ራሳቸውን በእጅጉ ጎድተዋል። (ሕዝ. 29:7) ግብፅ እንደ “ግዙፍ የባሕር ፍጥረት” የማትደፈር ትመስል ይሆናል። (ሕዝ. 29:3, 4) ይሖዋ ግን አዳኞች የአባይን አዞዎች በሚይዙበት ወቅት እንደሚያደርጉት ‘በመንጋጋዋ መንጠቆ አስገብቶ’ ወደ ጥፋት እንደሚወስዳት ተናግሯል። ይሖዋ ባቢሎናውያን ይህችን ጥንታዊት አገር ድል እንዲነሱ በማድረግ ይህ ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል።—ሕዝ. 29:9-12, 19

26 ከሃዲው ሴዴቅያስስ ምን ደረሰበት? ይህ ‘መጥፎ አለቃ’ በይሖዋ ላይ ስላመፀ “አክሊሉ” እንደሚወሰድበትና ግዛቱ ፈራርሶ እንደሚጠፋ ሕዝቅኤል በትንቢት ተናግሯል። ሆኖም ሕዝቅኤል ተስፋ ሰጪ የሆነ ሐሳብም ጠቅሷል። (ሕዝ. 21:25-27) ይሖዋ ከንጉሣዊው ዘር የሚመጣ “ሕጋዊ መብት ያለው” ንጉሥ ዙፋኑን እንደሚረከብ በሕዝቅኤል አማካኝነት ተንብዮ ነበር። በዚህ መጽሐፍ ቀጣይ ምዕራፍ ላይ ይህ ንጉሥ ማን እንደሆነ እንመለከታለን።

27. እስራኤል ከግብፅ ጋር ከነበራት ግንኙነት ምን ልንማር እንችላለን?

27 እስራኤል ከግብፅ ጋር ከነበራት ግንኙነት ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን? በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ የይሖዋ ሕዝቦች የፖለቲካ ባለሥልጣናት ዘላቂ ሰላምና ጸጥታ ያስገኛሉ ብለው በማሰብ በእነሱ ላይ እምነት ከመጣል መቆጠብ ይኖርባቸዋል። በሐሳባችንም እንኳ “የዓለም ክፍል” መሆን አይገባንም። (ዮሐ. 15:19፤ ያዕ. 4:4) ፖለቲካዊው ሥርዓት ጠንካራ መስሎ ሊታይ ይችላል፤ ይሁን እንጂ ልክ እንደ ጥንቷ ግብፅ ምንም አቅም የሌለው አገዳ ነው። ሁሉን ቻይ ከሆነው የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ ይልቅ ሟች በሆኑ የሰው ልጆች ላይ ተስፋ መጣል እንዴት ያለ ሞኝነት ነው!—መዝሙር 146:3-6ን አንብብ።

ብቻችንን በምንሆንበት ጊዜም ጭምር በዚህ ዓለም የፖለቲካ ጉዳዮች አንዱን ወገን ከመደገፍ መቆጠብ ይኖርብናል (አንቀጽ 27⁠ን ተመልከት)

ብሔራት “ያውቃሉ”

28-30. ብሔራት ‘ይሖዋን ለማወቅ’ በሚገደዱበት መንገድና እኛ ይሖዋን በምናውቅበት መንገድ መካከል ምን ልዩነት አለ?

28 ይሖዋ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ ብሔራት “እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ” የሚለውን ሐሳብ በተደጋጋሚ ተናግሯል። (ሕዝ. 25:17) ይሖዋ በጥንት ዘመን በሕዝቡ ጠላቶች ላይ የቅጣት ፍርድ ባመጣበት ወቅት ይህ ትንቢት በትክክል ተፈጽሟል። በዘመናችን ደግሞ የላቀ ፍጻሜ ይኖረዋል። በምን መንገድ?

29 ጥንት እንደነበሩት የአምላክ ሕዝቦች ሁሉ እኛም ምንም መከላከያ እንደሌላት በግ ለጥቃት የተጋለጥን እንደሆንን አድርገው በሚያስቡ ብሔራት ተከበናል። (ሕዝ. 38:10-13) በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 17 እና 18 ላይ እንደሚብራራው በቅርቡ ብሔራት ባለ በሌለ ኃይላቸው በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ። ያን ጊዜ ግን ከማንም በላይ ኃያል የሆነው ማን እንደሆነ እንዲያውቁ ይደረጋሉ። ይሖዋ በአርማጌዶን ጦርነት ሲያጠፋቸው እሱን ለማወቅና ሉዓላዊነቱን አምነው ለመቀበል ይገደዳሉ።—ራእይ 16:16፤ 19:17-21

30 እኛን ግን ይሖዋ ይጠብቀናል እንዲሁም ይባርከናል። ለምን? ምክንያቱም በእሱ በመታመን፣ እሱን በመታዘዝና ለእሱ የሚገባውን ንጹሕ አምልኮ በማቅረብ ከወዲሁ ይሖዋን እንደምናውቀው አሳይተናል።—ሕዝቅኤል 28:26ን አንብብ።

a ለምሳሌ ያህል ፍልስጤማውያን በእስራኤል ውስጥ አንድም የብረታ ብረት ሠራተኛ እንዳይኖር አግደው ነበር። እስራኤላውያን የእርሻ መሣሪያዎቻቸውን ለማሳል ወደ ፍልስጤማውያን መሄድ ነበረባቸው፤ ለሥራውም የአንድ ሠራተኛ የብዙ ቀን ደሞዝ የሚያህል ገንዘብ ያስከፍሏቸው ነበር።—1 ሳሙ. 13:19-22

b የመጀመሪያዋ የጢሮስ ከተማ ከቀርሜሎስ ተራራ በስተ ሰሜን 48 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በሚገኝ ዓለታማ ደሴት ላይ የተገነባች ሳትሆን አትቀርም። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የከተማዋ ተጨማሪ ክፍል በየብስ ላይ ተገንብቷል። የከተማይቱ የዕብራይስጥ ስም ሱር ሲሆን “ዓለት” የሚል ትርጉም አለው።

c ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ኢዩኤል፣ አሞጽና ዘካርያስም በጢሮስ ላይ ትንቢት የተናገሩ ሲሆን ትንቢቶቹ አንድም ሳይቀር ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል።—ኢሳ. 23:1-8፤ ኤር. 25:15, 22, 27፤ ኢዩ. 3:4፤ አሞጽ 1:10፤ ዘካ. 9:3, 4