ሣጥን 16ሀ
ኢየሩሳሌም ለሕዝበ ክርስትና ጥላ ነች?
ቀደም ባሉት ዓመታት ጽሑፎቻችን ከሃዲዋ ኢየሩሳሌም ለሕዝበ ክርስትና ጥላ እንደሆነች ይናገሩ ነበር። ጣዖት አምልኮንና ምግባረ ብልሹነትን ጨምሮ በከሃዲዋ ኢየሩሳሌም ውስጥ ይታዩ የነበሩት ሁኔታዎች በዛሬው ጊዜ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚታየውን ሁኔታ እንደሚያስታውሱን ጥያቄ የለውም። ይሁን እንጂ ይህን መጽሐፍ ጨምሮ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሚወጡ ጽሑፎቻችን፣ በግልጽ የተጠቀሰ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ከሌለ በቀር ትንቢቶችን ወደፊት ለሚመጣ የላቀ ነገር ጥላ እንደሆኑ አድርገው ለማብራራት አይሞክሩም። ታዲያ ኢየሩሳሌም ለሕዝበ ክርስትና ጥላ እንደሆነች የሚጠቁም ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት አለ? የለም።
የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በል፦ ኢየሩሳሌም በአንድ ወቅት የንጹሕ አምልኮ ማዕከል ነበረች፤ ከጊዜ በኋላ ግን ነዋሪዎቿ ከሃዲዎች ሆኑ። በአንጻሩ ግን ሕዝበ ክርስትና ጨርሶ ንጹሕ አምልኮ አቅርባ አታውቅም። ሕዝበ ክርስትና ወደ ሕልውና ከመጣችበት ከአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. አንስቶ ሁሌም ስታስተምር የኖረችው የሐሰት መሠረተ ትምህርቶችን ነው።
በተጨማሪም ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን ከጠፋች በኋላ ይሖዋ ለከተማዋ ሞገሱን መልሶ ያሳያት ሲሆን ዳግመኛ የንጹሕ አምልኮ ማዕከል መሆን ችላለች። ሕዝበ ክርስትና ግን የአምላክን ሞገስ አግኝታ አታውቅም፤ በታላቁ መከራ ከጠፋች በኋላም ቢሆን ዳግመኛ የማንሰራራት ተስፋ የላትም።
ከላይ ከተመለከትናቸው ነጥቦች አንጻር ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? በከዳተኛይቱ ኢየሩሳሌም ላይ የተፈጸሙትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በምንመረምርበት ጊዜ ‘ይህ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያለውን ሁኔታ ያስታውሰናል’ እንል ይሆናል። ሆኖም ኢየሩሳሌም ለሕዝበ ክርስትና ጥላ ነች ለማለት የሚያበቃ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ያለ አይመስልም።