ምዕራፍ ሰባት
“በጽናት የተቋቋመውን እሱን በጥሞና አስቡ”
1-3. (ሀ) ኢየሱስ በጌትሴማኒ ምን ያህል ተጨንቆ ነበር? የተጨነቀውስ ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በጽናት ረገድ ስለተወው ምሳሌ ምን ማለት ይቻላል? ምን ጥያቄዎችስ ይነሳሉ?
ሁኔታው በጣም አስጨናቂ ነበር። ኢየሱስ ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ የአእምሮና የስሜት ሥቃይ ደርሶበት አያውቅም። ምድራዊ ሕይወቱ ሊጠናቀቅ ተቃርቧል። በዚህ ጊዜ ከሐዋርያቱ ጋር ወደሚያዘወትሩት ስፍራ ይኸውም ወደ ጌትሴማኒ የአትክልት ቦታ መጣ። ኢየሱስ በዚህ ስፍራ ከሐዋርያቱ ጋር ጊዜ ያሳልፍ ነበር። በዚህ ምሽት ግን ለተወሰነ ጊዜ ብቻውን መሆን ፈልጎ ስለነበር ከሐዋርያቱ ተለይቶ ወደ አትክልቱ ስፍራ በመዝለቅ ተንበርክኮ መጸለይ ጀመረ። ላቡ “መሬት ላይ እንደሚንጠባጠብ ደም” እስኪሆን ድረስ በከፍተኛ ጭንቀት ተውጦ አጥብቆ ጸለየ።—ሉቃስ 22:39-44
2 ኢየሱስ እንዲህ የተጨነቀው ለምንድን ነው? እውነት ነው፣ ከፊቱ ከፍተኛ አካላዊ ሥቃይ እንደሚጠብቀው ያውቃል፤ ያም ሆኖ የተጨነቀበት ምክንያት ይህ አልነበረም። ከዚህ ይበልጥ እጅግ አሳሳቢ የሆኑ ጉዳዮች በአእምሮው ይመላለሱ ነበር። የአባቱ ስም እጅግ ያሳሰበው ከመሆኑም በተጨማሪ የሰው ልጆች የወደፊት ተስፋ እሱ ታማኝ ሆኖ በመጽናቱ ላይ የተመካ እንደሆነ ያውቃል። ኢየሱስ መጽናቱ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቧል። በፈተናው ከተሸነፈ በይሖዋ ስም ላይ ከፍተኛ ነቀፌታ ያመጣል። ኢየሱስ ግን በፈተናው አልተሸነፈም። እንዲያውም በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የላቀ የጽናት ምሳሌ ሆኗል፤ ኢየሱስ በዚያኑ ዕለት ሕይወቱ ሊያልፍ ሲል በድል አድራጊነት ስሜት ድምፁን ከፍ አድርጎ “ተፈጸመ!” አለ።—ዮሐንስ 19:30
3 መጽሐፍ ቅዱስ “በጽናት የተቋቋመውን እሱን [ኢየሱስን] በጥሞና አስቡ” የሚል ማበረታቻ ይሰጠናል። (ዕብራውያን 12:3) ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚከተሉት ወሳኝ ጥያቄዎች ይነሳሉ፦ ኢየሱስ በጽናት ከተቋቋማቸው ፈተናዎች አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው? እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? የእሱን አርዓያ መከተል የምንችለውስ እንዴት ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ከማግኘታችን በፊት ግን ጽናት ምን ነገሮችን እንደሚጨምር እስቲ እንመልከት።
ጽናት ምንድን ነው?
4, 5. (ሀ) “ጽናት” ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) መጽናት ሲባል ልንሸሸው የማንችለውን መከራ መቀበል ማለት ብቻ እንዳልሆነ በምሳሌ ማስረዳት የምንችለው እንዴት ነው?
4 ሁላችንም አንዳንድ ጊዜ በሚያጋጥሙን ‘ልዩ ልዩ ፈተናዎች መጨነቃችን የግድ ነው።’ (1 ጴጥሮስ 1:6) ይሁንና ፈተና ስለደረሰብን ብቻ ጸንተናል ሊባል ይችላል? እንደዚያ ሊባል አይችልም። “ጽናት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “አስቸጋሪ ለሆኑ ሁኔታዎች እጅ ሳይሰጡ ችግሮችን ተቋቁሞ የማለፍ ችሎታን” ያመለክታል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የጠቀሱትን የጽናት ዓይነት በተመለከተ አንድ ምሁር እንዲህ የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል፦ “ቃሉ፣ አንድን ነገር በትዕግሥት ብቻ ሳይሆን ደስ የሚያሰኝ ተስፋ ይዞ የመቻልን መንፈስ ያመለክታል። . . . አንድ ሰው ችግርን ተቋቁሞ ሳይንገዳገድ እንዲቆም የሚያስችለው ባሕርይ ነው። ከባዱን መከራ ወደ ክብር ለመለወጥ የሚያስችል መልካም ባሕርይ ነው፤ ምክንያቱም ከሥቃዩ በስተ ጀርባ ያለውን ግቡን አሻግሮ ይመለከታል።”
5 በመሆኑም መጽናት ሲባል ልንሸሸው የማንችለውን መከራ መቀበል ማለት ብቻ አይደለም። ጽናት የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተሠራበት አንጻር ከአቋም ፍንክች አለማለትን እንዲሁም በፈተና ውስጥ ትክክለኛ አስተሳሰብና ብሩህ ተስፋ ይዞ መቀጠልን ያመለክታል። እስቲ የሚከተለውን ምሳሌ ተመልከት፦ ሁለት ሰዎች በአንድ እስር ቤት ውስጥ ታስረዋል፤ የታሰሩበት ምክንያት ግን ፈጽሞ የተለያየ ነው። አንዱ ወንጀለኛ ሲሆን በምሬትና በብስጭት የእስር ጊዜውን ይገፋል። ሌላኛው ደግሞ በታማኝነት አቋሙ የተነሳ ለእስር የተዳረገ እውነተኛ ክርስቲያን ነው፤ ይህ ሰው ያለበትን ሁኔታ እምነቱን ለማሳየት እንደሚያስችለው አጋጣሚ አድርጎ ስለተመለከተው በአቋሙ የጸና ከመሆኑም ሌላ አዎንታዊ አመለካከት አለው። መቼም ወንጀለኛው የጽናት ምሳሌ ተደርጎ ሊታይ እንደማይችል የታወቀ ነው፤ ታማኝ የሆነው ክርስቲያን ግን ለዚህ ግሩም ባሕርይ ምሳሌ ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል።—ያዕቆብ 1:2-4
6. ጽናትን ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
6 መዳን ከፈለግን ጽናትን ማዳበራችን እጅግ አስፈላጊ ነው። (ማቴዎስ 24:13) ይሁንና ይህ ወሳኝ ባሕርይ በተፈጥሮ የምናገኘው አይደለም። ጽናትን ማዳበር ጥረት ይጠይቃል። ታዲያ ይህን ባሕርይ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? ሮም 5:3 “መከራ ጽናትን እንደሚያስገኝ” ይናገራል። አዎ፣ ጽናትን ለማዳበር ከልብ የምንፈልግ ከሆነ የእምነት ፈተናዎች ባጋጠሙን ቁጥር መሸሽ አይኖርብንም። ፍርሃት ቢያድርብንም እንኳ ፈተናዎቹን በድፍረት መጋፈጥ ያስፈልገናል። በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን ቀላልም ሆኑ ከባድ ፈተናዎች ስንጋፈጥና ተቋቁመን ስናልፍ ጽናትን እናዳብራለን። አንድን ፈተና ተቋቁመን ስናልፍ ቀጣዩን መከራ ለመጋፈጥ የሚያስችል ጥንካሬ እናገኛለን። እርግጥ ነው፣ በራሳችን ጥረት ብቻ ጽናትን ማዳበር አንችልም። “አምላክ በሚሰጠው ኃይል [መተማመን]” ይኖርብናል። (1 ጴጥሮስ 4:11) ይሖዋ ጸንተን እንድንቆም እኛን ለመርዳት ሲል ልንከተለው የሚገባ ከሁሉ የተሻለ ምሳሌ ይኸውም ልጁን ሰጥቶናል። እስቲ ኢየሱስ በጽናት ረገድ ያስመዘገበውን እንከን የለሽ ታሪክ በጥልቀት እንመርምር።
ኢየሱስ በጽናት የተቋቋማቸው ፈተናዎች
7, 8. ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ መገባደጃ ላይ ምን ነገሮችን በጽናት መቋቋም አስፈልጎታል?
7 ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ መገባደጃ ላይ የደረሱበትን ተደራራቢ የጭካኔ ድርጊቶች በጽናት መቋቋም አስፈልጎታል። በመጨረሻው ምሽት ከነበረበት ከፍተኛ ጭንቀት በተጨማሪ ያጋጠሙትን አሳዛኝና ክብሩን የሚነኩ ሁኔታዎች ተመልከት። የቅርብ ጓደኛው ክዶታል፣ የልብ ወዳጆቹ ትተውት ሸሽተዋል እንዲሁም አግባብነት በሌለው የፍርድ ሂደት ተዳኝቷል፤ በፍርድ ቤቱ የተገኙት የአገሪቱ ከፍተኛ ሃይማኖታዊ ሸንጎ አባላት አፊዘውበታል፣ ተፍተውበታል ብሎም በቡጢ መትተውታል። ያም ሆኖ የደረሰበትን መከራ ሁሉ በተረጋጋ መንፈስና በድፍረት ተቋቁሟል።—ማቴዎስ 26:46-49, 56, 59-68
8 ኢየሱስ ሊሞት በተቃረበበት ጊዜ የደረሰበትን እጅግ አሰቃቂ አካላዊ ሥቃይ በጽናት ተቋቁሟል። አንድ ጽሑፍ እንደገለጸው “ሰውነቱ እስኪተለተልና ብዙ ደም እስኪፈሰው” ድረስ ክፉኛ ተገርፏል። ከዚያም “ከፍተኛ ሕመምና ሥቃይ በሚያስከትል” ሁኔታ ተሰቅሎ ተገድሏል። በእንጨት ላይ በተቸነከረበት ጊዜ ትላልቅ ምስማሮች እጁንና እግሩን በስተው ሲገቡ ምን ያህል ተሠቃይቶ እንደሚሆን ገምት። (ዮሐንስ 19:1, 16-18) እንጨቱን ለማቆም ሲሞክሩ ይታይህ፤ የሰውነቱ ክብደት በሙሉ በምስማሮቹ ላይ ሲያርፍ እንዲሁም የተተለተለው ጀርባው ከእንጨቱ ጋር ሲፋተግ ምን ያህል አሰቃቂ ሕመም ሊሰማው እንደሚችል አስብ። ኢየሱስ ይህን ሁሉ አካላዊ ሥቃይ በጽናት መቋቋሙ ሳያንስ በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ የተገለጹት ነገሮችም አስጨንቀውት ነበር።
9. የራሳችንን “የመከራ እንጨት” መሸከምና ኢየሱስን መከተል ምን ነገሮችን ይጨምራል?
9 የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ምን ነገሮችን በጽናት መቋቋም ሊያስፈልገን ይችላል? ኢየሱስ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር . . . የራሱን የመከራ እንጨት ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ” ብሏል። (ማቴዎስ 16:24) እዚህ ላይ “የመከራ እንጨት” የሚለው መግለጫ ሥቃይን፣ ውርደትን አልፎ ተርፎም ሞትን ለማመልከት ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ተሠርቶበታል። ስለሆነም ክርስቶስን መከተል ቀላል አይደለም። ክርስቲያናዊ አቋማችን ከሌሎች የተለየን እንድንሆን ያደርገናል። የዓለም ክፍል ስላልሆንን ይህ ዓለም ይጠላናል። (ዮሐንስ 15:18-20፤ 1 ጴጥሮስ 4:4) ያም ሆኖ የራሳችንን የመከራ እንጨት ለመሸከም ፈቃደኞች ነን፤ አዎ፣ ምሳሌያችን የሆነውን ኢየሱስን ከመከተል ወደኋላ ከማለት ይልቅ ሥቃይ ለመቀበል ሌላው ቀርቶ ለመሞት እንኳ ዝግጁ ነን።—2 ጢሞቴዎስ 3:12
10-12. (ሀ) ኢየሱስ በዙሪያው የነበሩት ሰዎች አለፍጽምና ጽናቱን የፈተነው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ በጽናት የተቋቋማቸው አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?
10 ኢየሱስ አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ጊዜ በዙሪያው ያሉት ሰዎች አለፍጽምና ራሱን የቻለ ሌላ ፈተና ሆኖበት ነበር። ኢየሱስ፣ ይሖዋ ምድርንና በላይዋ ያሉትን ሕይወት ያላቸው ነገሮች ለመፍጠር የተጠቀመበት “የተዋጣለት ሠራተኛ” እንደነበር አስታውስ። (ምሳሌ 8:22-31) በመሆኑም ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ይኸውም የእሱን ባሕርያት እንዲያንጸባርቁና ፍጹም ጤናሞች ሆነው አስደሳች ሕይወት እንዲመሩ እንደሚፈልግ ያውቃል። (ዘፍጥረት 1:26-28) ኢየሱስ በምድር ላይ በኖረበት ወቅት ኃጢአት ያስከተለውን አሳዛኝ ውጤት ከተለየ አቅጣጫ ተመልክቷል፤ እሱ ራሱ ሰው ሆኖ በምድር ላይ ሲኖር የሰው ልጆች የሚሰማቸው ስሜት ተሰምቶታል። የሰው ልጆች አዳምና ሔዋን ከነበሩበት የፍጽምና ደረጃ ምን ያህል እንዳሽቆለቆሉ በመካከላቸው ሆኖ ሲያይ ምንኛ አዝኖ ይሆን! ይህ የኢየሱስን ጽናት የሚፈትን ነበር። ኃጢአተኛ የሆኑትን የሰው ልጆች ሊሻሻሉ እንደማይችሉ አድርጎ በመቁጠር ተስፋ ቆርጦባቸው ይሆን? እስቲ እንመልከት።
11 ኢየሱስ አይሁዳውያን ልበ ደንዳና መሆናቸው በጣም ስለረበሸው በሰው ፊት አልቅሷል። ታዲያ ቸልተኝነታቸው ቅንዓቱ እንዲቀዘቅዝ ወይም መስበኩን እንዲያቆም አድርጎት ነበር? በጭራሽ! እንዲያውም “በየዕለቱ በቤተ መቅደሱ ማስተማሩን ቀጠለ።” (ሉቃስ 19:41-44, 47) ኢየሱስ አንድን ሰው በሰንበት ይፈውሰው እንደሆነ ለማየት በትኩረት ይከታተሉት በነበሩት ፈሪሳውያን ልበ ደንዳናነት “በጣም አዝኖ” ነበር። ታዲያ ራሳቸውን ያመጻድቁና ይቃወሙት የነበሩትን እነዚህን ሰዎች ፈርቷቸው ይሆን? በፍጹም! ይልቁንም እዚያው ምኩራቡ ውስጥ ሰውየውን በድፍረት ፈወሰው!—ማርቆስ 3:1-5
12 የኢየሱስን ጽናት የፈተነው ሌላው ነገር ደግሞ የቅርብ ደቀ መዛሙርቱ ድክመት ነው። ምዕራፍ 3 ላይ እንደተመለከትነው ደቀ መዛሙርቱ ከሌሎች ልቆ የመታየት ፍላጎት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ይታይ ነበር። (ማቴዎስ 20:20-24፤ ሉቃስ 9:46) ኢየሱስም የትሕትናን አስፈላጊነት አስመልክቶ ተደጋጋሚ ምክር ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 18:1-6፤ 20:25-28) ይሁንና ምክሩን ተግባራዊ ማድረግ ጊዜ ወስዶባቸዋል። እስቲ አስበው፣ ከእነሱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት እንኳ “‘ከመካከላችን ታላቅ የሆነው ማን ነው?’ በሚል በመካከላቸው የጦፈ ክርክር” ተነስቶ ነበር! (ሉቃስ 22:24) ታዲያ ኢየሱስ ሊለወጡ እንደማይችሉ በማሰብ ተስፋ ቆረጠባቸው? በጭራሽ! ከዚህ ይልቅ ሁልጊዜ መልካም ጎናቸውን በመመልከት በትዕግሥት ይይዛቸው የነበረ ሲሆን ሊሻሻሉ ይችላሉ የሚል አዎንታዊ አመለካከት ነበረው። ይሖዋን ከልባቸው እንደሚወዱትና ፈቃዱን የመፈጸም ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ያውቅ ነበር።—ሉቃስ 22:25-27
13. ኢየሱስ በጽናት ከተቋቋማቸው ጋር የሚመሳሰሉ ምን ዓይነት ፈተናዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ?
13 እኛም ኢየሱስ በጽናት እንደተቋቋማቸው ያሉ ፈተናዎች ያጋጥሙን ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ የመንግሥቱን ምሥራች ለመስማት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሌላው ቀርቶ ተቃዋሚ የሆኑ ሰዎች ያጋጥሙናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ቅንዓታችን ይቀዘቅዛል ወይስ በግለት መስበካችንን እንቀጥላለን? (ቲቶ 2:14) በሌላ በኩል ደግሞ የክርስቲያን ወንድሞቻችን አለፍጽምና ሊፈትነን ይችላል። አሳቢነት የጎደለው ንግግር አሊያም ድርጊት ስሜታችንን ይጎዳው ይሆናል። (ምሳሌ 12:18) የእምነት ባልንጀሮቻችን ያለባቸው ድክመት ተስፋ እንድንቆርጥባቸው ያደርገናል? ወይስ ስህተታቸውን ለማለፍና መልካም ጎናቸውን ለማየት እንጥራለን?—ቆላስይስ 3:13
ኢየሱስ እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው?
14. ኢየሱስን እንዲጸና የረዱት ሁለት ነገሮች ምንድን ናቸው?
14 ኢየሱስ ክብሩን የሚነኩ፣ ተስፋ የሚያስቆርጡና ለሥቃይ የሚዳርጉ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም እንዲጸናና ንጹሕ አቋሙን እንዲጠብቅ የረዳው ምንድን ነው? ኢየሱስ እንዲጸና በዋነኝነት የረዱት ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛው፣ ወደ ላይ ማለትም ‘ጽናትን ወደሚሰጠው አምላክ’ መመልከቱ ነው። (ሮም 15:5) ሁለተኛው ደግሞ ወደፊት ይኸውም ጽናቱ የሚያስገኘውን ውጤት አሻግሮ ማየቱ ነው። እስቲ እነዚህን ነገሮች አንድ በአንድ እንመርምር።
15, 16. (ሀ) ኢየሱስ ለመጽናት በራሱ ችሎታ እንዳልተማመነ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በአባቱ ላይ ምን ትምክህት ነበረው? ለምንስ?
15 ኢየሱስ ፍጹም የሆነ የአምላክ ልጅ ቢሆንም ለመጽናት በራሱ ችሎታ አልተማመነም። ከዚህ ይልቅ በሰማይ ወደሚኖረው አባቱ ዞር ያለ ሲሆን የእሱን እርዳታ ለማግኘትም ጸልዮአል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ክርስቶስ በምድር ላይ በኖረበት ዘመን ከሞት ሊያድነው ለሚችለው በከፍተኛ ጩኸትና እንባ ብዙ ምልጃና ልመና አቀረበ” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 5:7) ኢየሱስ ልመና ብቻ ሳይሆን ምልጃም ‘ማቅረቡን’ ልብ በል። “ምልጃ” ከልብ በመነጨ ስሜት አጥብቆ መለመንን፣ እርዳታ ለማግኘት መማጸንን ያመለክታል። ጥቅሱ “ብዙ ምልጃ” ማለቱ ኢየሱስ ከአንድ ጊዜ በላይ ይሖዋን መማጸኑን ያሳያል። በእርግጥም ኢየሱስ በጌትሴማኒ የአትክልት ቦታ ደጋግሞ ከልብ የመነጨ ጸሎት አቅርቧል።—ማቴዎስ 26:36-44
16 ኢየሱስ፣ አባቱ “ጸሎት ሰሚ” እንደሆነ ስለሚያውቅ ላቀረበው ምልጃ መልስ እንደሚሰጠው ሙሉ በሙሉ ይተማመን ነበር። (መዝሙር 65:2) ይህ የበኩር ልጅ፣ ሰው ከመሆኑ በፊት አባቱ ታማኝ አገልጋዮቹ ለሚያቀርቡት ጸሎት መልስ ሲሰጥ ተመልክቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ወልድ በሰማይ እያለ ነቢዩ ዳንኤል ላቀረበው ልባዊ ጸሎት መልስ ለመስጠት ይሖዋ ወዲያውኑ መልአክ ሲልክለት ተመልክቷል፤ ይህ የሆነው ዳንኤል ገና ጸሎቱን አቅርቦ ሳይጨርስ ነበር። (ዳንኤል 9:20, 21) ታዲያ አብ አንድያ ልጁ “በከፍተኛ ጩኸትና እንባ” ልቡን በፊቱ ሲያፈስ እንዴት ምላሽ አይሰጠው? ይሖዋ ልጁ ያቀረበውን ልመና በመስማት፣ የሚደርስበትን መከራ መቋቋም እንዲችል የሚያበረታታው መልአክ ልኮለታል።—ሉቃስ 22:43
17. መጽናት ከፈለግን ወደ ሰማይ መመልከት ያለብን ለምንድን ነው? ይህንንስ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
17 እኛም መጽናት ከፈለግን ወደ ሰማይ ይኸውም ‘ኃይልን ወደሚሰጠው’ አምላክ መመልከት አለብን። (ፊልጵስዩስ 4:13) ፍጹም የሆነው የአምላክ ልጅ፣ ይሖዋ እንዲረዳው ምልጃ ማቅረብ እንደሚያስፈልገው ከተሰማው እኛማ ይህን ማድረግ ይበልጥ እንደሚያስፈልገን ጥርጥር የለውም! ልክ እንደ ኢየሱስ ይሖዋን ደጋግመን መለመን አለብን። (ማቴዎስ 7:7) ምንም እንኳ አንድ መልአክ መጥቶ ያበረታታናል ብለን ባንጠብቅም አፍቃሪው አምላካችን “ሌት ተቀን ያለማሰለስ ምልጃና ጸሎት” የሚያቀርቡትን ታማኝ ክርስቲያኖች እንደሚሰማቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (1 ጢሞቴዎስ 5:5) የደረሰብን መከራ የጤና ችግርም ሆነ የምንወደውን ሰው በሞት ማጣት አሊያም ተቃዋሚዎች የሚያደርሱብን ስደት ይሖዋ ለመጽናት የሚያስችል ጥበብ፣ ድፍረትና ብርታት እንዲሰጠን የምናቀርበውን ከልብ የመነጨ ጸሎት ይሰማል።—2 ቆሮንቶስ 4:7-11፤ ያዕቆብ 1:5
18. ኢየሱስ ከመከራው ባሻገር ያለውን ነገር የተመለከተው እንዴት ነው?
18 ኢየሱስን እንዲጸና የረዳው ሁለተኛው ነገር ወደፊት ይኸውም ከመከራው ባሻገር የሚጠብቀውን ነገር መመልከቱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን አስመልክቶ ሲናገር “እሱ ከፊቱ ለሚጠብቀው ደስታ ሲል . . . በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ጸንቷል” ይላል። (ዕብራውያን 12:2) ኢየሱስ የተወው ምሳሌ ተስፋ፣ ደስታና ጽናት ተያያዥነት እንዳላቸው ያሳያል። በአጭር አነጋገር ተስፋ ደስታን፣ ደስታ ደግሞ ጽናትን ያስገኛል ሊባል ይችላል። (ሮም 15:13፤ ቆላስይስ 1:11) ኢየሱስ ከፊቱ አስደናቂ ተስፋ ተዘርግቶለት ነበር። ታማኝ መሆኑ የአባቱን ስም ለማስቀደስና የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ለመዋጀት እንደሚያስችለው ያውቃል። በተጨማሪም ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ የመግዛትና ሊቀ ካህናት ሆኖ የማገልገል ተስፋ ነበረው፤ ይህም ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ተጨማሪ በረከቶችን ያስገኝላቸዋል። (ማቴዎስ 20:28፤ ዕብራውያን 7:23-26) ኢየሱስ ከፊቱ ባሉት ነገሮችና በተስፋው ላይ ትኩረት ማድረጉ ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶለታል፤ ይህ ደስታ ደግሞ እንዲጸና ረድቶታል።
19. የእምነት ፈተና ሲያጋጥመን ተስፋና ደስታ ለመጽናት የሚረዱን እንዴት ነው?
19 እኛም እንደ ኢየሱስ ለመጽናት ተስፋና ደስታ ያስፈልጉናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በተስፋው ደስ ይበላችሁ” ብሏል፤ አክሎም “መከራን በጽናት ተቋቋሙ” በማለት ጽፏል። (ሮም 12:12) እምነትህን የሚፈትን ከባድ ችግር አጋጥሞሃል? ከሆነ በተቻለህ መጠን ወደ ፊት አሻግረህ ለመመልከት ጥረት አድርግ። መጽናትህ የይሖዋ ስም እንዲወደስ እንደሚያደርግ ፈጽሞ አትዘንጋ። ውድ የሆነው የመንግሥቱ ተስፋ ብሩህ ሆኖ ይታይህ። አምላክ ወደሚያመጣው አዲስ ዓለም ገብተህ ገነት በሆነችው ምድር ላይ በምታገኛቸው በረከቶች ስትደሰት በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። የይሖዋ ስም መቀደሱን፣ ክፋት ከምድር ገጽ መወገዱን፣ በሽታና ሞት መጥፋቱን ጨምሮ ይሖዋ ቃል የገባልን አስደናቂ ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙበትን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅህ ልብህ በደስታ እንዲሞላ ያደርጋል፤ ይህ ደስታ ደግሞ ምንም ዓይነት መከራ ቢደርስብህ በጽናት መቋቋም እንድትችል ይረዳሃል። በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚያጋጥመን ማንኛውም መከራ በአምላክ መንግሥት ውስጥ ፍጻሜያቸውን ከሚያገኙት ተስፋዎች ጋር ሲወዳደር በእርግጥም “ጊዜያዊና ቀላል” ነው።—2 ቆሮንቶስ 4:17
‘የእሱን ፈለግ በጥብቅ ተከተሉ’
20, 21. ከጽናት ጋር በተያያዘ ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀው ምንድን ነው? ቁርጥ ውሳኔያችንስ ምን መሆን ይኖርበታል?
20 ኢየሱስ የእሱ ተከታይ መሆን ጽናትን የሚጠይቁ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያስከትል እንደሚችል ያውቃል። (ዮሐንስ 15:20) የእሱ ምሳሌ ሌሎችን ሊያበረታታ እንደሚችል ስለሚያውቅ መከራን በጽናት በማለፍ ረገድ ፈር ቀዳጅ ሆኗል። (ዮሐንስ 16:33) እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ በጽናት ረገድ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል፤ እኛ ግን ከፍጽምና የራቅን ነን። ታዲያ ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀው ምንድን ነው? ጴጥሮስ “ክርስቶስ . . . የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራ ተቀብሏል” ሲል ገልጿል። (1 ጴጥሮስ 2:21) ኢየሱስ ፈተናዎችን በመወጣት ረገድ ልንኮርጀው የሚገባ “አርዓያ” ትቶልናል። a በጽናት ረገድ ያስመዘገበው ታሪክ ‘ከእሱ ፈለግ’ ወይም ከእግሩ ዱካ ጋር ተመሳስሏል። የኢየሱስን የእግር ዱካ ፍጹም በሆነ መንገድ መከተል ባንችልም “በጥብቅ” ማለትም በቅርበት መከተል ግን እንችላለን።
21 ስለዚህ የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናድርግ። የኢየሱስን ዱካ በጥብቅ ለመከተል ጥረት ባደረግን መጠን “እስከ መጨረሻው” ለመጽናት የሚያስችል ጥንካሬ እንደምናገኝ አንዘንጋ፤ “መጨረሻው” የዚህ አሮጌ ሥርዓት ፍጻሜ አሊያም የሕይወታችን ማብቂያ ሊሆን ይችላል። ቀድሞ የሚመጣው የሥርዓቱ ፍጻሜም ይሁን የእኛ ሕይወት ማብቂያ ይሖዋ ላሳየነው ጽናት ለዘላለም እንደሚባርከን እናውቃለን።—ማቴዎስ 24:13
a “አርዓያ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲፈታ “ከሥር የተጻፈ” ማለት ነው። ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጸሐፊዎች መካከል ይህን ቃል የተጠቀመው ሐዋርያው ጴጥሮስ ብቻ ነው፤ ቃሉ “አንድ አስተማሪ፣ ተማሪው በተቻለ መጠን እሱ የጻፈለትን አስመስሎ እንዲገለብጥ በተማሪው ደብተር ላይ የሚያሰፍርለትን በትክክል የተጻፉ ፊደላት” ያመለክታል።