ምዕራፍ 21
‘ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ ነኝ’
የጳውሎስ የአገልግሎት ቅንዓትና ለሽማግሌዎች የሰጠው ምክር
በሐዋርያት ሥራ 20:1-38 ላይ የተመሠረተ
1-3. (ሀ) ከአውጤኪስ ሞት ጋር በተያያዘ የነበረውን ሁኔታ ግለጽ። (ለ) ጳውሎስ ምን አደረገ? ይህ አጋጣሚስ ስለ እሱ ምን ያስገነዝበናል?
ጳውሎስ አሁን ያለው ጥሮአስ ነው፤ ፎቅ ላይ በሚገኝ አንድ ክፍል ውስጥ ብዙ ሰው ተሰብስቧል። ጳውሎስ ለተሰብሳቢዎቹ ንግግር እየሰጠ ረጅም ሰዓት ቆየ፤ ምክንያቱም ይህ ከእነሱ ጋር የሚያሳልፈው የመጨረሻ ምሽት ነው። ጊዜው እኩለ ሌሊት ሆነ። ጭል ጭል የሚሉ ኩራዞች እዚያም እዚህም በርተዋል፤ ለዚያ ሳይሆን አይቀርም ክፍሉ ይሞቃል፣ ጭሱም እፍን ያደረገው ይመስላል። አንደኛው መስኮት ላይ አውጤኪስ የሚባል ወጣት ተቀምጧል። ጳውሎስ እየተናገረ ሳለ አውጤኪስ እንቅልፍ ጣለውና ከሁለተኛ ፎቅ ወደ ታች ወደቀ!
2 አውጤኪስን ለማንሳት እየተንደረደሩ ከወረዱት አንዱ ሐኪሙ ሉቃስ ሳይሆን አይቀርም። የሚያሳዝነው ግን ምንም ሊያደርጉለት አልቻሉም። ወጣቱን ‘ሲያነሱት ሞቶ ነበር።’ (ሥራ 20:9) ከዚያ ግን አንድ ተአምር ተፈጸመ። ጳውሎስ ወጣቱ ላይ ተኛ፤ ከዚያም ሰዎቹን “በሕይወት ስላለ አትንጫጩ” አላቸው። አውጤኪስን ከሞት አስነሳው!—ሥራ 20:10
3 ይህ አጋጣሚ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ምን ያህል ኃይል እንዳለው ያሳያል። እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ ለአውጤኪስ ሞት ተጠያቂ ሊሆን አይችልም። ይሁንና የወጣቱ ሞት፣ በዚህ ልዩ ፕሮግራም ላይ መጥፎ ትዝታ እንዲተው ወይም ለወንድሞች መሰናክል እንዲሆን አልፈለገም። ጳውሎስ አውጤኪስን ከሞት ማስነሳቱ የጉባኤውን አባላት አጽናንቷቸዋል፤ በአገልግሎታቸው እንዲገፉም ብርታት ሰጥቷቸዋል። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ጳውሎስ ለሕይወት ትልቅ ቦታ ይሰጥ ነበር። በዚህ ወቅት ያደረገው ነገር “ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ [እንደሆነ]” የተናገረውን ሐሳብ ያስታውሰናል። (ሥራ 20:26) ጳውሎስ የተወው ምሳሌ እኛም ለሕይወት አክብሮት እንድናዳብር የሚረዳን እንዴት ነው? እስቲ እንመልከት።
“ወደ መቄዶንያ ጉዞ ጀመረ” (የሐዋርያት ሥራ 20:1, 2)
4. ጳውሎስ ምን ዓይነት አስጨናቂ ሁኔታ አሳልፏል?
4 ባለፈው ምዕራፍ ላይ እንደተብራራው ጳውሎስ አስጨናቂ ሁኔታ አሳልፏል። በኤፌሶን ያከናወነው አገልግሎት ከፍተኛ ሁከት አስነስቶ ነበር። አዎ፣ መተዳደሪያቸው በአርጤምስ አምልኮ ላይ የተመሠረተው የብር አንጥረኞች ሆ ብለው ተነስተውበታል! የሐዋርያት ሥራ 20:1 “ሁከቱ ከበረደ በኋላ” ምን እንደተፈጸመ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱን አስጠራቸው፤ ካበረታታቸውና ከተሰናበታቸው በኋላ ወደ መቄዶንያ ጉዞ ጀመረ።”
5, 6. (ሀ) ጳውሎስ በመቄዶንያ ምን ያህል ጊዜ ቆይቶ ሊሆን ይችላል? በዚያ ለሚገኙ ወንድሞችስ ምን አድርጎላቸዋል? (ለ) ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው?
5 ጳውሎስ ወደ መቄዶንያ ሲጓዝ እግረ መንገዱን ጥሮአስ ወደብ ላይ አረፍ አለ፤ በዚያም የተወሰነ ጊዜ አሳለፈ። ቲቶን እዚህ እንደሚያገኘው ተስፋ አድርጎ ነበር። (2 ቆሮ. 2:12, 13) ቲቶ ወደ ቆሮንቶስ ተልኮ ነበር፤ ይሁንና ጳውሎስ ቲቶ እንደማይመጣ ሲያውቅ ወደ መቄዶንያ ጉዞውን ቀጠለ፤ በዚያም “የሚያገኛቸውን ደቀ መዛሙርት በብዙ ቃል እያበረታታ” አንድ ዓመት አካባቢ ሳይቆይ አልቀረም። a (ሥራ 20:2) በመጨረሻም ቲቶ በመቄዶንያ ከጳውሎስ ጋር ተገናኘ፤ የቆሮንቶስ ሰዎች ጳውሎስ ለላከላቸው የመጀመሪያ ደብዳቤ የሰጡትን ምላሽ በተመለከተም መልካም ዜና ይዞለት መጥቷል። (2 ቆሮ. 7:5-7) ጳውሎስ ይህን ሲሰማ ሌላ ደብዳቤ ሊጽፍላቸው ተነሳ፤ ይህ ደብዳቤ በአሁኑ ጊዜ 2 ቆሮንቶስ ተብሎ ይጠራል።
6 ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶንም ሆነ በመቄዶንያ የሚገኙ ወንድሞችን ሲጎበኝ ‘እንዳበረታታቸው’ ሉቃስ ጠቅሷል። ይህ አገላለጽ ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ ያለውን አመለካከት ጥሩ አድርጎ ያሳያል! ፈሪሳውያን ሌሎችን ዝቅ አድርገው ይመለከቱ ነበር፤ በተቃራኒው ግን ጳውሎስ ወንድሞቹንና እህቶቹን አብረውት የሚያገለግሉ የሥራ ባልደረቦች አድርጎ ይመለከታቸው ነበር። (ዮሐ. 7:47-49፤ 1 ቆሮ. 3:9) ጠንከር ያለ ምክር መስጠት ባስፈለገው ጊዜ እንኳ ለእነሱ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ነበረው።—2 ቆሮ. 2:4
7. በዛሬው ጊዜ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?
7 በዛሬው ጊዜ የጉባኤ ሽማግሌዎችና የወረዳ የበላይ ተመልካቾች የጳውሎስን ምሳሌ ለመከተል ጥረት ያደርጋሉ። ተግሣጽ በሚሰጡበት ጊዜም እንኳ ዓላማቸው እርዳታ የሚያስፈልገውን ሰው ማበረታታት ነው። የበላይ ተመልካቾች ወንድሞቻቸውን ከመኮነን ይልቅ ስሜታቸውን በመረዳት እነሱን ለማበረታታት ይጥራሉ። ተሞክሮ ያካበተ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሁኔታውን እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ “አብዛኞቹ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ይፈልጋሉ፤ ብዙውን ጊዜ ግን ነገሮች እንዳሰቡት አለመሆናቸው ከሚፈጥረው ስሜት ጋር ይታገላሉ፤ አሊያም ስጋት የሚያሳድሩባቸው ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል፤ ወይም ደግሞ ሁኔታው ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል።” የበላይ ተመልካቾች እንዲህ ላሉ የእምነት ባልንጀሮቻቸው የብርታት ምንጭ መሆን ይችላሉ።—ዕብ. 12:12, 13
‘ሴራ ጠነሰሱበት’ (የሐዋርያት ሥራ 20:3, 4)
8, 9. (ሀ) ጳውሎስ በመርከብ ወደ ሶርያ ለመሄድ የነበረውን ዕቅድ ያስተጓጎለበት ምንድን ነው? (ለ) አይሁዳውያን ለጳውሎስ ጥላቻ ያደረባቸው ለምን ሊሆን ይችላል?
8 ጳውሎስ ከመቄዶንያ ተነስቶ ወደ ቆሮንቶስ ተጓዘ። b በዚያ ሦስት ወር ከቆየ በኋላ ወደ ክንክራኦስ መሄድ ፈለገ፤ ከዚያ መርከብ ተሳፍሮ ወደ ሶርያ የማምራት ዕቅድ ነበረው። ከሶርያ ደግሞ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ እዚያ ላሉ የተቸገሩ ወንድሞች የተሰበሰበውን መዋጮ ያስረክባል። c (ሥራ 24:17፤ ሮም 15:25, 26) ይሁን እንጂ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ዕቅዱን አስቀየሩት። የሐዋርያት ሥራ 20:3 “አይሁዳውያን ሴራ [እንደጠነሰሱበት]” ይናገራል።
9 አይሁዳውያን ጳውሎስን በጥላቻ ዓይን ማየታቸው አያስገርምም፤ በእነሱ ዓይን ከሃዲ ነበር። ከዚህ ቀደም ባከናወነው አገልግሎት በቆሮንቶስ ምኩራብ ትልቅ ቦታ የነበረው ቀርስጶስ ክርስትናን ተቀብሏል። (ሥራ 18:7, 8፤ 1 ቆሮ. 1:14) በሌላ ወቅት ደግሞ እነዚህ የቆሮንቶስ አይሁዳውያን ጳውሎስን በአካይያ አገረ ገዢ በጋልዮስ ፊት ከስሰውት ነበር። ጋልዮስ ግን ክሱን መሠረት ቢስ እንደሆነ ቆጥሮ ውድቅ አደረገው፤ ይህ የጳውሎስን ጠላቶች በጣም አበሳጭቷቸው ነበር። (ሥራ 18:12-17) እነዚህ አይሁዳውያን፣ ጳውሎስ በአቅራቢያቸው ከምትገኘው ከክንክራኦስ መርከብ እንደሚሳፈር ሰምተው አሊያም ጠርጥረው ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ በዚያ አድብተው በእሱ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር አሴሩ። ታዲያ ጳውሎስ ምን ያደርግ ይሆን?
10. ጳውሎስ በክንክራኦስ ማለፍ አለመፈለጉ ፈሪ ያስብለዋል? አብራራ።
10 ጳውሎስ በክንክራኦስ በኩል ከመጓዝ ይልቅ በመጣበት መንገድ ተመልሶ በመቄዶንያ በኩል ለመሄድ ወሰነ፤ ይህን ያደረገው ለደህንነቱ ሲል ብቻ ሳይሆን በአደራ የተሰጠውን ገንዘብ ለመጠበቅም ነው። እርግጥ ነው፣ በየብስ መጓዝ የራሱ የሆኑ አደጋዎች አሉት። በጥንት ዘመን መንገድ ላይ አድፍጠው የሚዘርፉ ወንበዴዎች አይጠፉም ነበር። የእንግዳ ማረፊያዎቹ እንኳ ለአደጋ ሊያጋልጡ ይችላሉ። ያም ሆኖ ጳውሎስ በክንክራኦስ ከሚጠብቀው ጥቃት ይልቅ በእግር መጓዝ የሚያስከትለውን አደጋ ለመጋፈጥ መረጠ። ደግነቱ የሚጓዘው ብቻውን አልነበረም። በዚህ የሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ሲኮንዱስ፣ ሶጳጥሮስ፣ ቲኪቆስ፣ አርስጥሮኮስ፣ ጋይዮስ፣ ጢሞቴዎስና ጢሮፊሞስ ከእሱ ጋር ነበሩ።—ሥራ 20:3, 4
11. በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ ጥንቃቄ የሚያደርጉት እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ኢየሱስ ምን ምሳሌ ትቷል?
11 ጳውሎስ እንዳደረገው ሁሉ ዛሬም ክርስቲያኖች በአገልግሎት ላይ ራሳቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ያደርጋሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች ብቻቸውን ከመሆን ይልቅ በቡድን አሊያም ሁለት ሁለት ሆነው ያገለግላሉ። ስደት ሲደርስባቸውስ? ክርስቲያኖች ስደት አይቀሬ መሆኑን ይገነዘባሉ። (ዮሐ. 15:20፤ 2 ጢሞ. 3:12) ይሁንና እያወቁ ራሳቸውን ለአደጋ አያጋልጡም። የኢየሱስን ምሳሌ ተመልከት። በአንድ ወቅት ኢየሩሳሌም ውስጥ ተቃዋሚዎች እሱን ለመውገር ድንጋይ ሲያነሱ “ተሰወረና ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ ሄደ።” (ዮሐ. 8:59) በሌላ ጊዜም አይሁዳውያኑ እሱን ለመግደል አሲረው ነበር፤ በመሆኑም “ኢየሱስ ከዚያን ጊዜ አንስቶ በአይሁዳውያን መካከል በይፋ መንቀሳቀስ አቆመ፤ ከዚህ ይልቅ በምድረ በዳ አቅራቢያ ወዳለ ስፍራ ሄደ።” (ዮሐ. 11:54) ኢየሱስ፣ አምላክ ለእሱ ካለው ፈቃድ ጋር የሚጋጭ እስካልሆነ ድረስ ራሱን ከአደጋ ለመጠበቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ያደርግ ነበር። ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዳሉ።—ማቴ. 10:16
“እጅግ ተጽናኑ” (የሐዋርያት ሥራ 20:5-12)
12, 13. (ሀ) የአውጤኪስ ትንሣኤ በጉባኤው ላይ ምን ስሜት አሳድሯል? (ለ) በዛሬው ጊዜ የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ሰዎች በየትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይጽናናሉ?
12 ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ መቄዶንያን አቋርጠው የተጓዙት አብረው ነው፤ ከዚያ ግን ለተወሰነ ጊዜ የተለያዩ ይመስላል። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው፣ የጉዞ ቡድኑ እንደገና የተሰባሰበው ጥሮአስ ላይ ነው። d ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “በአምስት ቀን ጊዜ ውስጥም እነሱ ወዳሉበት ወደ ጥሮአስ ደረስን።” e (ሥራ 20:6) በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ወጣቱ አውጤኪስ ከሞት የተነሳው በጥሮአስ ነበር። በዚያ የነበሩት ክርስቲያኖች፣ የእምነት አጋራቸው አውጤኪስ ከሞት በመነሳቱ ምን ያህል ተደስተው እንደሚሆን አስበው! ዘገባው “እጅግ ተጽናኑ” ይላል።—ሥራ 20:12
13 እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ እንዲህ ዓይነት ተአምራት አይፈጸሙም። ይሁንና የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ያጡ ግለሰቦች መጽሐፍ ቅዱስ በያዘው የትንሣኤ ተስፋ ‘እጅግ ተጽናንተዋል።’ (ዮሐ. 5:28, 29) እስቲ አስበው፤ አውጤኪስ ፍጹም ስላልሆነ ውሎ አድሮ በድጋሚ ሞቷል። (ሮም 6:23) በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች ግን ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው! ከዚህ በተጨማሪ በሰማይ ከኢየሱስ ጋር ለመግዛት የሚነሱ ሰዎች የማይሞት ሕይወት ያገኛሉ። (1 ቆሮ. 15:51-53) በእርግጥም ቅቡዓንም ሆኑ “ሌሎች በጎች” ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች በሙሉ ‘እጅግ እንዲጽናኑ’ የሚያደርግ አጥጋቢ ምክንያት አላቸው።—ዮሐ. 10:16
የሐዋርያት ሥራ 20:13-24)
“በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት” (14. ጳውሎስ ሚሊጢን ላይ ከኤፌሶን ጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር ሲገናኝ ምን አላቸው?
14 ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ ከጥሮአስ ወደ አሶስ አቀኑ፤ ከዚያም ወደ ሚጢሊኒ፣ ኪዮስ፣ ሳሞስና ሚሊጢን ተጓዙ። የጳውሎስ ዕቅድ ለጴንጤቆስጤ በዓል ኢየሩሳሌም መድረስ ነው። በዚህ የመልስ ጉዞ፣ ኤፌሶን ላይ የማይቆም መርከብ ለመሳፈር የመረጠው ለጴንጤቆስጤ በዓል ኢየሩሳሌም ለመድረስ በጣም ስለቸኮለ መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ጳውሎስ የኤፌሶንን ሽማግሌዎች ማነጋገር ስለፈለገ ወደ ሚሊጢን እንዲመጡ መልእክት ላከባቸው። (ሥራ 20:13-17) እዚያ በደረሱ ጊዜም እንዲህ አላቸው፦ “በእስያ አውራጃ እግሬ ከረገጠበት ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ በመካከላችሁ እንዴት እንደተመላለስኩ ታውቃላችሁ፤ በአይሁዳውያን ሴራ ምክንያት ብዙ መከራ ቢደርስብኝም እንኳ በታላቅ ትሕትናና በእንባ ጌታን አገለግል ነበር፤ ደግሞም የሚጠቅማችሁን ማንኛውንም ነገር ከመንገርም ሆነ በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት ከማስተማር ወደኋላ ብዬ አላውቅም። ከዚህ ይልቅ አይሁዳውያንም ሆኑ ግሪካውያን ንስሐ እንዲገቡና ወደ አምላክ እንዲመለሱ እንዲሁም በጌታችን በኢየሱስ እንዲያምኑ በተሟላ ሁኔታ መሥክሬላቸዋለሁ።”—ሥራ 20:18-21
15. ከቤት ወደ ቤት መመሥከር ያሉት አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?
15 በዛሬው ጊዜ ምሥራቹን ለሰዎች ለማድረስ የምንጠቀምባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም ሰዎች ወደሚገኙበት ቦታ ሁሉ እንሄዳለን፤ በአውቶቡስ ፌርማታ፣ መንገደኛ በሚበዛባቸው ጎዳናዎች ወይም በገበያ ስፍራዎች እንሰብካለን። ይሁንና የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን ለመስበክ የሚጠቀሙበት ዋነኛው ዘዴ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ነው። ለምን? አንደኛ ነገር፣ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስበክ፣ ሁሉም ሰው በየተወሰነ ጊዜ የመንግሥቱን መልእክት የሚሰማበት አጋጣሚ እንዲያገኝ ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ አምላክ እንደማያዳላ በተጨባጭ ያሳያል። በተጨማሪም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እንደየሁኔታቸው የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ በግል እንዲያገኙ ያስችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ከቤት ወደ ቤት የምናገለግለው እኛም እምነታችን ይጠናከራል፤ ጽናትም እናዳብራለን። በእርግጥም በዛሬው ጊዜ የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት “በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት” በቅንዓት መመሥከር ነው።
16, 17. ጳውሎስ ፍርሃት እንደማይበግረው ያሳየው እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችስ የእሱን ምሳሌ የሚከተሉት በምን መንገድ ነው?
16 ጳውሎስ፣ ኢየሩሳሌም ሲደርስ የሚጠብቀውን ነገር እንደማያውቅ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች ነገራቸው። “ይሁንና ሩጫዬን እስካጠናቀቅኩ እንዲሁም ስለ አምላክ ጸጋ የሚገልጸውን ምሥራች በተሟላ ሁኔታ በመመሥከር ከጌታ ኢየሱስ የተቀበልኩትን አገልግሎት እስከፈጸምኩ ድረስ ሕይወቴ ምንም አያሳሳኝም” አላቸው። (ሥራ 20:24) ጳውሎስ በፍርሃት አልተበገረም፤ ማንኛውም ነገር፣ የጤና እክልም ሆነ የከረረ ተቃውሞ ተልእኮውን ዳር ከማድረስ እንዲያግደው አልፈቀደም።
17 በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እየጸኑ ነው። አንዳንዶች መንግሥት የጣለውን እገዳና የሚያደርስባቸውን ስደት ይጋፈጣሉ። ሌሎች ደግሞ ከከባድ የጤና እክል ወይም ከመንፈስ ጭንቀት ጋር ይታገላሉ፤ ሆኖም እጅ አይሰጡም። ክርስቲያን ወጣቶች ትምህርት ቤት ውስጥ የእኩዮቻቸውን ተጽዕኖ መቋቋም ያስፈልጋቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥማቸው እንደ ጳውሎስ ከአቋማቸው ፍንክች አይሉም። ‘ምሥራቹን በሚገባ ለመመሥከር’ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል።
‘ለራሳችሁም ሆነ ለመንጋው ሁሉ ትኩረት ስጡ’ (የሐዋርያት ሥራ 20:25-38)
18. ጳውሎስ ከደም ዕዳ ነፃ ለመሆን ምን አድርጓል? የኤፌሶን ሽማግሌዎችስ የእሱን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?
18 በመቀጠል ጳውሎስ የራሱን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እየጠቀሰ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች ቀጥተኛ ምክር ሰጣቸው። በቅድሚያ ግን፣ ምናልባት እሱን በአካል የሚያዩት ለመጨረሻ ጊዜ ሊሆን እንደሚችል ነገራቸው። ከዚያም “ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ [ነኝ] . . .፤ ምክንያቱም የአምላክን ፈቃድ ሁሉ ለእናንተ ከመንገር ወደኋላ አላልኩም” አላቸው። ታዲያ የኤፌሶን ሽማግሌዎች የጳውሎስን ምሳሌ በመከተል ከደም ዕዳ ነፃ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? ጳውሎስ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ለራሳችሁም ሆነ አምላክ በገዛ ልጁ ደም የዋጀውን ጉባኤውን እረኛ ሆናችሁ እንድትጠብቁ መንፈስ ቅዱስ የበላይ ተመልካቾች አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ትኩረት ስጡ።” (ሥራ 20:26-28) ጳውሎስ “ጨካኝ ተኩላዎች” ወደ መንጋው ሰርገው እንደሚገቡና “ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር” እንደሚናገሩ አስጠነቀቃቸው። ታዲያ ሽማግሌዎቹ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ጳውሎስ እንዲህ ሲል አሳሰባቸው፦ “ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ሦስት ዓመት ሙሉ ሌሊትና ቀን እያንዳንዳችሁን በእንባ ከማሳሰብ ወደኋላ እንዳላልኩ አስታውሱ።”—ሥራ 20:29-31
19. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ የተፈጠረው ክህደት ምንድን ነው? ይህስ በቀጣዮቹ መቶ ዘመናት ምን እንዲከሰት አድርጓል?
19 “ጨካኝ ተኩላዎች” በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ ብቅ አሉ። በ98 ዓ.ም. ገደማ ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አሁንም እንኳ ብዙ ፀረ ክርስቶሶች መጥተዋል፤ . . . በእኛ መካከል ነበሩ፤ ሆኖም ከእኛ ወገን ስላልነበሩ ትተውን ሄደዋል። ከእኛ ወገን ቢሆኑማ ኖሮ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር።” (1 ዮሐ. 2:18, 19) በሦስተኛው መቶ ዘመን፣ በጉባኤ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ የነበራቸው አንዳንዶች የክህደት ጎዳና ተከትለው ነበር፤ ይህም የሕዝበ ክርስትና የቀሳውስት ክፍል እንዲፈጠር አደረገ፤ በአራተኛው መቶ ዘመን ደግሞ ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ፣ በክህደት ለተበከለው “ክርስትና” ይፋዊ እውቅና ሰጠ። የሃይማኖት መሪዎች አረማዊ የአምልኮ ሥርዓቶችን ከክርስትና ጋር በመቀላቀልና “የክርስትና” ገጽታ በማላበስ “ጠማማ ነገር የሚናገሩ” መሆናቸውን በተጨባጭ አሳይተዋል። ይህ ክህደት ያሳደረው ተጽዕኖ ዛሬም በሕዝበ ክርስትና ትምህርቶችና ልማዶች ላይ ይንጸባረቃል።
20, 21. ጳውሎስ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ያሳየው እንዴት ነው? ዛሬ ያሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎችስ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
20 የጳውሎስ የሕይወት ጎዳና በኋለኞቹ ዘመናት መንጋውን መጠቀሚያ ካደረጉት ሰዎች ፈጽሞ የተለየ ነው። ጳውሎስ በጉባኤው ላይ ሸክም ላለመሆን ሲል የሚያስፈልገውን ለማሟላት እየሠራ ነበር። የእምነት ባልንጀሮቹን ለመርዳት ቢለፋም ይህን ያደረገው ከእነሱ ጥቅም ለማግኘት ብሎ አይደለም። ጳውሎስ፣ የኤፌሶን ሽማግሌዎች የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ እንዲያሳዩ አበረታቷል። “ደካማ የሆኑትን መርዳት [አለባችሁ]፤ ‘ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል’ በማለት ጌታ ኢየሱስ ራሱ የተናገረውን ቃል ማስታወስ ይኖርባችኋል” ብሏቸዋል።—ሥራ 20:35
21 በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎችም ልክ እንደ ጳውሎስ የራሳቸውን ጥቅም ይሠዋሉ። እንደ ሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት መንጎቻቸውን አይበዘብዙም፤ ከዚህ በተቃራኒ ‘ጉባኤውን እረኛ ሆነው የመጠበቅ’ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው በመገንዘብ ራሳቸውን ሳይቆጥቡ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ። ኩራትና ለሥልጣን መቋመጥ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ቦታ የላቸውም፤ ምክንያቱም ‘የራስን ክብር መሻት’ የኋላ ኋላ ለውድቀት ይዳርጋል። (ምሳሌ 25:27) እብሪት ከመጣ ውርደት መከተሉ አይቀርም።—ምሳሌ 11:2
22. የኤፌሶን ሽማግሌዎች ጳውሎስን እንዲወዱት ያደረጋቸው ምንድን ነው?
22 ጳውሎስ ለወንድሞቹ ያለው ልባዊ ፍቅር በእነሱ ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆን አድርጎታል። ከእነሱ ተለይቶ የሚሄድበት ጊዜ ሲደርስ “ሁሉም እጅግ አለቀሱ፤ ጳውሎስንም እቅፍ አድርገው ሳሙት።” (ሥራ 20:37, 38) እንደ ጳውሎስ ራሳቸውን ሳይቆጥቡ መንጋውን የሚያገለግሉ እረኞችም በእምነት ባልንጀሮቻቸው ልብ ውስጥ ልዩ ቦታ አላቸው። ጳውሎስ የተወውን ግሩም ምሳሌ ተመልክተናል፤ ታዲያ ‘ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ ነኝ’ ብሎ ሲናገር እየተኩራራ ወይም እያጋነነ አልነበረም ቢባል አትስማማም?—ሥራ 20:26
a “ ጳውሎስ ከመቄዶንያ የጻፋቸው ደብዳቤዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
b ጳውሎስ ለሮም ሰዎች የላከውን ደብዳቤ የጻፈው በዚህ ወቅት ቆሮንቶስን ሲጎበኝ ሊሆን ይችላል።
c “ ጳውሎስ ለእርዳታ የተዋጣውን ገንዘብ አደረሰ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
d ሉቃስ የሐዋርያት ሥራ 20:5, 6 ላይ ያለውን ዘገባ ሲጽፍ በአንደኛ መደብ ተውላጠ ስም በመጠቀም ራሱንም ታሪኩ ውስጥ አካትቷል፤ ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው፣ ጳውሎስ ቀደም ሲል ፊልጵስዩስ ላይ የተወውን ሉቃስን እዚያው ዳግም ያገኘው ይመስላል፤ ከዚያም አብረው ወደ ጥሮአስ ሄደዋል።—ሥራ 16:10-17, 40