በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 34

ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን መማር ከጀመርክ ወዲህ ወደ አምላክ ይበልጥ እንደቀረብክ ይሰማሃል? ከእሱ ጋር ያለህ ወዳጅነት ይበልጥ እንዲጠናከር ትፈልጋለህ? ከሆነ ለይሖዋ ያለህ ፍቅር እየጨመረ ሲሄድ እሱም ይበልጥ እንደሚወድህና እንደሚንከባከብህ አስታውስ። ለመሆኑ ለይሖዋ ያለህን ፍቅር ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

1. ይሖዋን እንደምንወደው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

ለይሖዋ ያለንን ፍቅር የምናሳየው እሱን በመታዘዝ ነው። (1 ዮሐንስ 5:3⁠ን አንብብ።) ይሖዋ ማንም ሰው እንዲታዘዘው አያስገድድም። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ ሰው እሱን ለመታዘዝ ወይም ላለመታዘዝ እንዲመርጥ አጋጣሚውን ሰጥቷል። ለምን? ይሖዋ ‘ከልብ እንድንታዘዘው’ ስለሚፈልግ ነው። (ሮም 6:17) በሌላ አባባል፣ ግዴታ ስለሆነብህ ሳይሆን ለእሱ ባለህ ፍቅር ተነሳስተህ እንድትታዘዘው ይፈልጋል። የዚህ መጽሐፍ ክፍል 3 እና 4 ዓላማ፣ ይሖዋን የሚያስደስተውን ነገር በማድረግና እሱን ከሚያሳዝነው ነገር በመራቅ ለእሱ ያለህን ፍቅር እንድታሳይ መርዳት ነው።

2. ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማሳየት ተፈታታኝ ሊሆንብን የሚችለው ለምንድን ነው?

“የጻድቅ ሰው መከራ ብዙ ነው።” (መዝሙር 34:19) ሁላችንም ፍጹማን ስላልሆንን የተለያዩ ድክመቶች አሉብን። ከዚህም በተጨማሪ የኢኮኖሚ ችግር፣ የፍትሕ መዛባት እንዲሁም ሌሎች ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ፈታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ይሖዋ ያዘዘንን ማድረግ ሊከብደን እንደሚችል አይካድም። ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ የተሳሳተውን ነገር ማድረግ ትክክል የሆነውን ነገር ከማድረግ ሊቀል ይችላል። ሆኖም በታማኝነት ይሖዋ ያዘዘህን ነገር ስታደርግ ከምንም በላይ እሱን እንደምትወደው ታሳያለህ። በተጨማሪም ለእሱ ታማኝ እንደሆንክ ታረጋግጣለህ። እንዲህ ስታደርግ ይሖዋም ለአንተ ታማኝ ይሆናል። ፈጽሞ አይተውህም።—መዝሙር 4:3⁠ን አንብብ።

ጠለቅ ያለ ጥናት

ይሖዋ ለእሱ ለምታሳየው ታዛዥነት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለምን እንደሆነና ለእሱ ታማኝ ሆነህ እንድትቀጥል የሚረዳህ ምን እንደሆነ እንመለከታለን።

3. አንተንም የሚመለከት ጉዳይ

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የኢዮብ መጽሐፍ ላይ እንደምናነበው ሰይጣን ኢዮብ በተባለው ሰው ላይ ብቻ ሳይሆን ይሖዋን ማገልገል በሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ላይ አንድ ክስ ሰንዝሯል። ኢዮብ 1:1ን እና ኢዮብ 1:6–2:10ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • እንደ ሰይጣን አባባል፣ ኢዮብ ይሖዋን የሚታዘዘው ለምንድን ነው?—ኢዮብ 1:9-11⁠ን ተመልከት።

  • ሰይጣን አንተን ጨምሮ ሁሉንም የሰው ልጆች በተመለከተ ምን ብሏል?—ኢዮብ 2:4⁠ን ተመልከት።

ኢዮብ 27:5ለን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • ኢዮብ ይሖዋን ከልቡ እንደሚወደው ያሳየው እንዴት ነው?

ኢዮብ ለይሖዋ ታማኝ በመሆን ለእሱ ያለውን ፍቅር አሳይቷል

ለይሖዋ ታማኝ በመሆን ለእሱ ያለንን ፍቅር ማሳየት እንችላለን

4. የይሖዋን ልብ ደስ አሰኝ

ምሳሌ 27:11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ይሖዋ ጥበበኛ ስትሆንና እሱን ስትታዘዘው ምን ይሰማዋል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

5. ለይሖዋ ታማኝ መሆን ትችላለህ

ለይሖዋ ያለን ፍቅር ለሌሎች ስለ እሱ እንድንናገር ይገፋፋናል። ለይሖዋ ያለን ታማኝነት ደግሞ ከባድ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ እንዲህ እንድናደርግ ብርታት ይሰጠናል። ቪዲዮውን ተመልከቱ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ስለ ይሖዋ ለሌሎች መናገር ይከብድሃል?

  • በቪዲዮው ላይ ግሬሰን ፍርሃቱን እንዲያሸንፍ የረዳው ምንድን ነው?

ይሖዋ የሚወደውን የምንወድና የሚጠላውን የምንጠላ ከሆነ ለእሱ ታማኝ መሆን ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል። መዝሙር 97:10ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • እስካሁን ከተማርከው ነገር በመነሳት፣ ይሖዋ የሚወዳቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? የሚጠላቸው ነገሮችስ ምንድን ናቸው?

  • ጥሩ የሆነውን ነገር እንድትወድና ክፉ የሆነውን ነገር እንድትጠላ ምን ይረዳሃል?

6. ይሖዋን መታዘዛችን ይጠቅመናል

ይሖዋን መታዘዛችን ሁሌም ቢሆን ይጠቅመናል። ኢሳይያስ 48:17, 18ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ይሖዋ ሁሌም ለእኛ የተሻለውን እንደሚያውቅ ልንተማመንበት እንችላለን? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

  • ስለ መጽሐፍ ቅዱስና እውነተኛ አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋ መማርህ እስካሁን ምን ጥቅም አስገኝቶልሃል?

አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “እኔ የማደርገው ነገር በአምላክ ላይ ምንም ለውጥ አያመጣም።”

  • የምናደርገው ነገር ይሖዋን ሊያስደስተው ወይም ሊያሳዝነው እንደሚችል ለማስረዳት የትኛውን ጥቅስ ልትጠቀም ትችላለህ?

ማጠቃለያ

ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችለው እሱን በመታዘዝና ፈታኝ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ለእሱ ታማኝ በመሆን ነው።

ክለሳ

  • ከኢዮብ ታሪክ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

  • ለይሖዋ ያለህን ፍቅር ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

  • ምንጊዜም ለይሖዋ ታማኝ እንድትሆን የሚረዳህ ምንድን ነው?

ግብ

ምርምር አድርግ

ለይሖዋና ለጉባኤው ታማኝ እንደሆንክ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

“ታማኝ ለሆነ ሰው ታማኝ ትሆናለህ” (16:49)

ሰይጣን በሰው ልጆች ላይ ስለሰነዘረው ክስ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ?

“ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ጠበቀ” (መጽሐፍ ቅዱስ—የያዘው መልእክት ምንድን ነው? ክፍል 6)

ልጆችም እንኳ ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

ይሖዋን ደስ አሰኘው (8:16)

ወጣቶች እኩዮቻቸው የሚያሳድሩባቸውን ተጽዕኖ ተቋቁመው ለአምላክ ታማኝ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?

በእኩዮች ተጽዕኖ አትሸነፍ! (3:59)