ምዕራፍ አንድ
የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበት ቁልፍ ይኖራልን?
1. በሰብዓዊው ኅብረተሰብ ውስጥ ጠንካራ ቤተሰቦች መኖራቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ቤተሰብ በምድር ላይ ካሉት ተቋሞች ሁሉ እጅግ ጥንታዊ ነው፤ በሰብዓዊው ኅብረተሰብ ውስጥም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። በታሪክ ዘመናት ሁሉ ጠንካራ ቤተሰቦች ጠንካራ ኅብረተሰቦችን ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ ቆይተዋል። ቤተሰብ ልጆችን ኮትኩቶ በማሳደግ የጎለመሱ አዋቂዎች መሆን ወደሚችሉበት ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ከሁሉ የተሻለ ዝግጅት ነው።
2-5. (ሀ) ደስተኛ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ የሚያድግ ልጅ የሚሰማውን ደህንነት ግለጽ። (ለ) በአንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ ምን ችግሮች አሉ?
2 ደስተኛ ቤተሰብ ሰላምና የተረጋጋ ሕይወት የሰፈነበት ቦታ ነው። እስቲ ለትንሽ ጊዜ፣ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን አንድ ቤተሰብ በዓይነ ሕሊናችን እንመልከት። ማታ እራታቸውን ሲበሉ አሳቢ የሆኑ ወላጆች በእራት ሰዓት ከልጆቻቸው ጋር ተቀምጠው በቀኑ ውስጥ ስለተከናወኑት ሁኔታዎች ይወያያሉ። ልጆቹ በደስታ ስሜት እየተፍለቀለቁ በትምህርት
ቤት ስለተፈጸሙት ነገሮች ለአባታቸውና ለእናታቸው ያወራሉ። አንድ ላይ ሆነው ራሳቸውን ዘና በማድረግ ያሳለፉት ጊዜ ሁሉም በሚቀጥለው ቀን ከቤት ውጪ ለሚያከናውኗቸው ነገሮች ኃይላቸውና መንፈሳቸው እንዲታደስ ይረዳቸዋል።3 በአንድ ደስተኛ ቤተሰብ ውስጥ የሚገኝ ልጅ በሚታመምበት ጊዜ አባትና እናቱ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚያደርጉለትና ምናልባትም ደግሞ ሌሊት እየተፈራረቁ አልጋው አጠገብ ሆነው እንደሚያስታምሙት ያውቃል። በልጅነቱ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለእናቱ ወይም ለአባቱ መንገርና ምክርና እርዳታ ማግኘት እንደሚችል ያውቃል። አዎ፣ በውጪ ያለው ዓለም ምንም ያህል በችግር የተሞላ ቢሆን ልጁ ሥጋት አያድርበትም።
4 ብዙውን ጊዜ ልጆች ሲያድጉ ትዳር ይዘው የራሳቸውን ቤተሰብ ይመሰርታሉ። “አንድ ሰው ወላጆቹ ምን ያህል ውለታ እንደዋሉለት የሚገነዘበው ወልዶ ሲቀምሰው ነው” የሚል አንድ የሩቅ ምሥራቅ ሰዎች አባባል አለ። ለአካለ መጠን የደረሱት ልጆች ጥልቅ የሆነ የአመስጋኝነትና የፍቅር ስሜት ስለሚያድርባቸው የየራሳቸውን ቤተሰብ ደስተኛ ለማድረግ የሚጥሩ ከመሆኑም በላይ የልጅ ልጆች በማየታቸው የሚደሰቱትን በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን ይጦራሉ።
5 ከላይ ያለውን ስታነቡ ‘እርግጥ እኔም ቤተሰቤን እወዳለሁ፤ ግን የእኔ ቤተሰብ ከላይ የተገለጸውን ዓይነት አይደለም። የባለቤቴና የእኔ የሥራ ፕሮግራም የተለያየ በመሆኑ እምብዛም አንገናኝም። ብንገናኝም በአብዛኛው የምናወራው ስለ ገንዘብ ነክ ችግሮች ነው’ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ወይም ደግሞ ‘ልጆቼና የልጅ ልጆቼ የሚኖሩት በሌላ ከተማ ስለሆነ አግኝቻቸው አላውቅም’ የሚል ሐሳብ ወደ አእምሯችሁ መጥቶ ይሆን? አዎ፣ ብዙውን ጊዜ ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ምክንያት የበርካታዎቹ ቤተሰቦች ሕይወት ጥሩ ምሳሌ ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል ዓይነት አይደለም። ያም ሆኖ ግን ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት የሚመሩ አንዳንድ ቤተሰቦች አሉ። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበት ቁልፍ ይኖራልን? መልሱ አዎ የሚል ነው። ይህ ቁልፍ ምን እንደሆነ ከመመልከታችን በፊት ግን በጣም አስፈላጊ ለሆነ አንድ ጥያቄ መልስ ማግኘት ይኖርብናል።
ቤተሰብ ምንድን ነው?
6. በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ማብራሪያ የሚሰጠው ምን ዓይነት ቤተሰቦችን በተመለከተ ነው?
6 በምዕራቡ ዓለም ቤተሰብ የሚለው ቃል በአብዛኛው የሚያመለክተው
አባትን፣ እናትንና ልጆችን ነው። አያቶች አቅማቸውና ሁኔታቸው እስከፈቀደ ድረስ በራሳቸው ቤት ውስጥ ሊኖሩ ይችላሉ። ከሌሎች ዘመዶች ጋር አንዳንድ ግንኙነቶች ቢኖሩም እነሱን በተመለከተ ያሉት ግዴታዎች የተወሰኑ ናቸው። በመሠረቱ፣ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የምንወያየው አባትን፣ እናትንና ልጆችን ስላቀፈው ቤተሰብ ነው። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሌሎች ቤተሰቦች ማለትም ነጠላ ወላጅ ያለባቸው ቤተሰቦች፣ የእንጀራ ወላጅ ያለባቸው ቤተሰቦችና በሆነ ምክንያት ወላጆች ተለያይተው የሚኖሩባቸው ቤተሰቦች እየተበራከቱ መጥተዋል።7. ሰፊ ቤተሰብ የሚባለው ምን ዓይነት ነው?
7 በአንዳንድ ባህሎች ደግሞ አብዛኞቹ ቤተሰቦች ሰፊ ናቸው። እንዲህ ዓይነት ቤተሰቦች ባሉባቸው ባህሎች በተቻለ መጠን ልጆች ወላጆቻቸውን ይጦራሉ። ከዚህም በተጨማሪ ከዘመዶቻቸው ጋር የቅርብ ትስስር ያላቸው ከመሆኑም በላይ እነርሱን የመርዳት ኃላፊነት አለባቸው። ለምሳሌ ያህል የእኅትና የወንድም ልጆችን ወይም ደግሞ የሩቅ ዘመዶችን ሊረዱ፣ ሊያሳድጉ አልፎ ተርፎም እየከፈሉ ሊያስተምሯቸው ይችላሉ። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚብራሩት መሠረታዊ ሥርዓቶች ለእንዲህ ዓይነቶቹም ሰፋ ያሉ ቤተሰቦች ይሠራሉ።
በተጽዕኖ ሥር የወደቀው የቤተሰብ ሕይወት
8, 9. የቤተሰብ ሕይወት እየተለወጠ እንደመጣ የሚያሳዩ በአንዳንድ አገሮች እየታዩ ያሉ ችግሮች ምንድን ናቸው?
8 ዛሬ የቤተሰብ ሕይወት እየተለወጠ ሄዷል፤ የሚያሳዝነው ግን ይህ ለውጥ አሉታዊ መሆኑ ነው። በሕንድ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለዚህ እንደ ምሳሌ አድርጎ መጥቀስ ይቻላል። በሕንድ አንዲት ሚስት በአማቾቿ አመራር ሥር ሆና ቤት ውስጥ እየሠራች ከባሏ ቤተሰብ ጋር መኖር ትችል ነበር። ዛሬ ግን ሕንዳውያን ሚስቶች ከቤት ውጪ ሥራ ሲፈልጉ መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም። ሆኖም ባለው ባህል መሠረት ከቤት ውጪ እየሠሩም ቢሆን በቤት ውስጥ ሊያከናውኑት የሚገባውን የሥራ ድርሻ ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው ካሉት ሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። በብዙ አገሮች የሚነሳው ጥያቄ፣ ከቤት ውጪ ሌላ ሥራ ያላት አንዲት ሴት ከሌሎቹ የቤተሰብ አባላት ጋር ሲነጻጸር በቤት ውስጥ ልታከናውነው የሚገባት ሥራ ምን ያህል ነው? የሚል ነው።
9 በሩቅ ምሥራቃውያን ኅብረተሰቦች ዘንድ ባለው ባህል መሠረት ጠንካራ የሆነ ሰፊ የቤተሰብ ትስስር አለ። ይሁን እንጂ በሁሉም ነገር
ራስን መቻል የሚለው የምዕራባውያን የአኗኗር ዘይቤና የኢኮኖሚ ችግሮች የሚፈጥሩት ውጥረት ሰፊውን የቤተሰብ ትስስር እያዳከሙት ነው። በዚህም ምክንያት በብዙዎች ዘንድ በዕድሜ የገፉ ወላጆችን መጦር እንደ ኃላፊነት ወይም መብት መቆጠሩ ቀርቶ እንደ ሸክም እየታየ መጥቷል። አንዳንድ በዕድሜ የገፉ ወላጆች ከባድ እንግልት ይደርስባቸዋል። እንዲያውም በዛሬው ጊዜ አረጋውያንን ማንገላታት ወይም ችላ ማለት በብዙ አገሮች ውስጥ የተለመደ ነገር ነው።10, 11. በአውሮፓ አገሮች ውስጥ የቤተሰብ ሕይወት እየተለወጠ እንዳለ የሚያሳዩት ማስረጃዎች የትኞቹ ናቸው?
10 ፍቺ ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም እየተስፋፋ መጥቷል። በስፔይን በ20ኛው መቶ ዘመን የመጨረሻ አሥርተ ዓመት መጀመሪያ ላይ የፍቺው ቁጥር በመጨመር ከ8 ትዳሮች ውስጥ አንዱ የሚፈርስበት ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ከ25 ዓመት በፊት ግን ከ100 ትዳሮች የሚፈርሰው አንዱ ብቻ የነበረ መሆኑ የፍቺው ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡን ያሳያል። በአውሮፓ ከፍተኛውን የፍቺ ቁጥር በያዘችው በብሪታንያ (ከ10 ትዳሮች አራቱ ይፈርሳሉ) በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት አድጓል።
11 በጀርመን የሚኖሩት ብዙዎቹ ሰዎች ቤተሰብ መሥርቶ የመኖሩን ልማድ ከናካቴው የተዉት ይመስላል። በ1990ዎቹ ዓመታት እንደታየው በጀርመን ከሚገኙት ቤቶች ውስጥ 35 በመቶ የሚሆኑት አንድ ነጠላ ሰው ብቻ የሚኖርባቸው ሲሆኑ 31 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሁለት ግለሰቦች ብቻ የሚኖሩባቸው ናቸው። በፈረንሳይም የሚጋቡት ሰዎች ቁጥር ቀንሷል፤ ከሚጋቡትም መካከል የሚፋቱት ሰዎች ቁጥር ከመጨመሩም በላይ ከበፊቱ አንጻር ሲታይ ተጋብተው የሚቆዩት ለጥቂት ጊዜ ነው። ከጋብቻ ኃላፊነቶች ራሳቸውን ነጻ አድርገው ሳይጋቡ አንድ ላይ ለመኖር የሚፈልጉት ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲህ ዓይነት አዝማሚያዎች እየታዩ ነው።
12. በአሁኑ ጊዜ በሚገኙት ቤተሰቦች ላይ እየታዩ ባሉት ለውጦች ሳቢያ ልጆች የሚሰቃዩት እንዴት ነው?
12 ስለ ልጆችስ ምን ማለት ይቻላል? በዩናይትድ ስቴትስና በሌሎች ብዙ አገሮች ውስጥ በርካታ ልጆች ከጋብቻ ውጪ እየተወለዱ ነው፤ አንዳንዶቹ የተወለዱት በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ወጣቶች ነው። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣት ሴቶች ከተለያዩ
አባቶች የወለዷቸው በርከት ያሉ ልጆች አሏቸው። በዓለም ዙሪያ የሚወጡት ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ማደሪያ የሌላቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ልጆች በጎዳናዎች ላይ ይንከራተታሉ፤ ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ በልጆች ላይ ከፍተኛ በደል ከሚፈጸምባቸው ቤተሰቦች ሸሽተው የወጡ ወይም ሊያሳድጓቸው ያልቻሉ ወላጆች ከቤት ያባረሯቸው ልጆች ናቸው።13. ቤተሰብን ደስታ እያሳጡ ያሉ በጣም ተስፋፍተው የሚገኙ ችግሮች ምንድን ናቸው?
13 አዎ፣ ቤተሰብ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ገብቷል። ከላይ ከተጠቀሱት ነገሮች በተጨማሪ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የሚፈጽሙት ዓመፅ፣ ልጆችን ማስነወር፣ የትዳር ጓደኛን መደብደብ፣ የአልኮል ሱሰኝነትና ሌሎች ጠንቀኛ ችግሮች ብዙ ቤተሰቦችን ደስታ አሳጥተዋል። እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ልጆችና አዋቂዎች ቤተሰብ ደህንነት የሚያገኙበት ቦታ አልሆነላቸውም።
14. (ሀ) አንዳንዶች ቤተሰብ ቀውስ ውስጥ እንዲገባ ምክንያት ሆነዋል ብለው የሚጠቅሷቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረ ሕግ ዐዋቂ በአሁኑ ጊዜ ያለውን ዓለም የገለጸው እንዴት ነው? እርሱ የተናገራቸው ቃላት ፍጻሜ በቤተሰብ ሕይወት ላይ ምን ተጽዕኖ እያሳደረ ነው?
14 ቤተሰብ እንዲህ ቀውስ ውስጥ የገባው ለምንድን ነው? አንዳንዶች በዛሬው ጊዜ ቤተሰብ እንዲህ ያለ ቀውስ ሊያጋጥመው የቻለው ሴቶች ወደ ሥራው ዓለም በመግባታቸው ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ለዚህ መንሥኤው በዛሬው ጊዜ ያለው የሥነ ምግባር ውድቀት እንደሆነ ይናገራሉ። ሌሎች ምክንያቶችም ይጠቀሳሉ። አንድ የታወቀ ሕግ ዐዋቂ ከሁለት ሺህ ዓመታት ገደማ በፊት እንደሚከተለው በማለት በጻፈ ጊዜ በቤተሰብ ላይ ብዙ ተጽዕኖዎች እንደሚደርሱ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር:- “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:1-4) እነዚህ ቃላት በዛሬው ጊዜ እየተፈጸሙ መሆናቸውን የሚጠራጠር ይኖራልን? እንዲህ የመሰሉ ሁኔታዎች ባሉበት ዓለም ውስጥ ብዙ ቤተሰቦች ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ቢገቡ ያስደንቃልን?
ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
15-17. የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበትን ቁልፍ ይዟል ተብሎ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተጠቀሰው መጽሐፍ የትኛው ነው?
15 ቤተሰብ እንዴት ደስታ ማግኘት እንደሚችል የሚጠቁም ምክር ከየአቅጣጫው ይጎርፋል። በምዕራቡ ዓለም ራስ አገዝ የሆኑ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው መጻሕፍትና መጽሔቶች ምክር ይሰጣሉ። ችግሩ የተለያዩ ሰብዓዊ አማካሪዎች የሚሰጡት ሐሳብ እርስ በርሱ የሚጋጭ መሆኑ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ዛሬ በጣም ወቅታዊ ነው የተባለው ምክር ነገ ጨርሶ አይሠራም ሊባል ይችላል።
16 ታዲያ አስተማማኝ የሆነ የቤተሰብ መመሪያ ልናገኝ የምንችለው ከየት ነው? መመሪያውን ለማግኘት ከዛሬ 1,900 ዓመታት ገደማ በፊት ተጽፎ ያለቀውን አንድ መጽሐፍ ለምን አትመረምሩም? ይሄማ ያረጀና ያፈጀ መጽሐፍ ነው ብላችሁ ታስባላችሁን? እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው፤ የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበት እውነተኛው ቁልፍ ያለው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ነው።
17 ይህ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ማስረጃዎቹ ሁሉ እንደሚያሳዩት መጽሐፉ የተጻፈው በራሱ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚከተለው ሐሳብ ሰፍሮ እናገኛለን:- “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና ለትምህርት፣ ለተግሳጽ፣ ነገሮችን ለማቅናት እንዲሁም በጽድቅ ላለው ምክር የሚጠቅም ነው።” (2 ጢሞቴዎስ 3:16 NW) በዛሬው ጊዜ ቤተሰቦች የሚደርሱባቸውን ተጽዕኖዎችና የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመቋቋም በምታደርጉት ጥረት መጽሐፍ ቅዱስ “ነገሮችን ለማቅናት” እንዴት ሊረዳችሁ እንደሚችል ልብ እንድትሉ በዚህ ጽሑፍ አማካኝነት እናበረታታችኋለን።
18. ከሁሉ የላቀ የቤተሰብ መመሪያ የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው ብሎ ማመኑ ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?
18 መጽሐፍ ቅዱስ ቤተሰቦች ደስተኛ እንዲሆኑ ሊረዳቸው ይችላል ብላችሁ ለማመን የምትቸገሩ ከሆነ የሚከተለውን ነጥብ ልብ በሉ:- መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈሱ አነሳሽነት ያስጻፈው የጋብቻ ዝግጅት መሥራች የሆነው አምላክ ነው። (ዘፍጥረት 2:18-25) ስሙ ይሖዋ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (መዝሙር 83:18 NW) ይሖዋ ፈጣሪና ‘እያንዳንዱ ቤተሰብ ስሙን የሚያገኝበት አባት’ ነው። (ኤፌሶን 3:14, 15) ይሖዋ ከሰው ዘር መጀመሪያ ጀምሮ የቤተሰብን ሕይወት ሲመለከት ቆይቷል። ሊነሱ የሚችሉትን ችግሮች የሚያውቅ ከመሆኑም በላይ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ምክር ሰጥቷል። ባለፉት የታሪክ ዘመናት ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በቤተሰባቸው ሕይወት ውስጥ ከልባቸው ሥራ ላይ ያዋሉ ሰዎች ከፍተኛ ደስታ አግኝተዋል።
19-21. መጽሐፍ ቅዱስ በትዳር ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን የመፍታት ኃይል እንዳለው የሚያሳዩት የትኞቹ ዘመናዊ ተሞክሮዎች ናቸው?
19 ለምሳሌ ያህል በኢንዶኔዥያ የምትኖር አንዲት የቤት እመቤት የቁማር ሱሰኛ ሆና ነበር። ለበርካታ ዓመታት ሦስት ልጆቿን ችላ ብላቸው የነበረ ሲሆን ከባሏም ጋር ሁልጊዜ ትጣላ ነበር። ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። ሴትየዋ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር እውነት መሆኑን ቀስ በቀስ እየተረዳች ሄደች። የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ በመተርጎሟ ጥሩ ሚስት ለመሆን በቃች። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ በመመርኮዝ የምታደርጋቸው ጥረቶች ለመላው ቤተሰቧ ደስታ ሊያስገኙ ችለዋል።
20 በስፔይን የምትገኝ አንዲት የቤት እመቤት “በመካከላችን ከባድ ችግሮች መፈጠር የጀመሩት በተጋባን በአንድ ዓመት ውስጥ ነበር” ስትል ተናግራለች። ከባሏ ጋር ሊግባቡ አልቻሉም፤ አብዛኛው ንግግራቸው ጭቅጭቅ ብቻ ነበር። አንዲት ትንሽ ልጅ የነበረቻቸው ቢሆንም በሕግ ለመለያየት ወሰኑ። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲመረምሩ ማበረታቻ ተሰጣቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ለተጋቡ ወንዶችና ሴቶች የሚሰጠውን ምክር ካጠኑ በኋላ ምክሩን በሥራ ላይ ማዋል ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ በሰላማዊ መንገድ መነጋገርና መግባባት በመቻላቸው ትንሹ ቤተሰባቸው አንድነት አግኝቷል።
21 መጽሐፍ ቅዱስ በዕድሜ ጠና ያሉ ሰዎችንም ይረዳል። ለምሳሌ ያህል የአንድ ጃፓናውያን ባልና ሚስትን ተሞክሮ ተመልከቱ። ባልየው ግልፍተኛ ከመሆኑም በላይ አንዳንዴ ይማታ ነበር። በመጀመሪያ፣ ምንም እንኳ ወላጆቻቸው ቢቃወሟቸውም ሴቶች ልጆቻቸው መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩ። ከዚያም ባልየውም እንደ ልጆቹ ማጥናት ጀመረ፤ ሚስትየዋ ግን አሁንም ተቃውሞዋን ገፋችበት። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በቤተሰቧ ላይ ያመጡትን ጥሩ ለውጥ አስተዋለች። ልጆቿ ጥሩ እንክብካቤ የሚያደርጉላት ከመሆኑም ሌላ ባልዋ በጣም ገር ሆነ። ሴትየዋ እነዚህን ለውጦች ማየቷ እርሷም መጽሐፍ ቅዱስን እንድትመረምር ገፋፋት፤ ይህን ማድረጓ በእሷም ላይ ጥሩ ለውጥ አመጣ። ይህች በዕድሜ የገፋች
ሴት “አሁን እውነተኛ ባልና ሚስት ሆነናል” በማለት በተደጋጋሚ ትናገራለች።22, 23. መጽሐፍ ቅዱስ በሁሉም ብሔራት ውስጥ ያሉ ሰዎች በቤተሰብ ሕይወታቸው ደስታ እንዲያገኙ የሚረዳቸው እንዴት ነው?
22 እነዚህ ግለሰቦች የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበትን ቁልፍ ካወቁት እጅግ በርካታ ሰዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በመቀበል በሥራ ላይ አውለዋል። እንደ ማንኛውም ሰው እነርሱም የሚኖሩት ጠበኛ በሆነ፣ እንዲሁም በሥነ ምግባር በረከሰና በኢኮኖሚ ውጥረት ተቀስፎ በተያዘ ዓለም ውስጥ ነው። ከዚህም በላይ ፍጹማን አይደሉም፤ ቢሆንም ግን የቤተሰብ ዝግጅት መሥራች የሆነውን አምላክ ፈቃድ ለመፈጸም በመጣር ደስታ አግኝተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ‘የሚረባችሁን መንገድ የሚያስተምራችሁ ልትሄዱበት በሚገባ መንገድም የሚመራችሁ’ ይሖዋ አምላክ ነው።—ኢሳይያስ 48:17
23 መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ያለቀው ከሁለት ሺህ ዓመታት ገደማ በፊት ቢሆንም እንኳ የሚሰጠው ምክር አሁንም የሚሠራ ነው። ከዚህም በላይ የተጻፈው ለሁሉም ሰዎች ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የአሜሪካ ወይም የምዕራቡ ዓለም መጽሐፍ አይደለም። ይሖዋ ‘የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ የፈጠረ’ ከመሆኑም ሌላ በየትኛውም ቦታ የሚገኙ ሰዎችን አፈጣጠር ያውቃል። (ሥራ 17:26) የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለሁሉም ሰው ይሠራሉ። እናንተም እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ካዋላችሁ የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበትን ቁልፍ ማወቅ ትችላላችሁ።