ምዕራፍ አሥራ ሦስት
ትዳር በቋፍ ላይ በሚሆንበት ጊዜ
1, 2. ትዳር ውጥረት ውስጥ በሚገባበት ጊዜ የትኛውን ጥያቄ መጠየቅ ያስፈልጋል?
በ1988 ሉቺያ የምትባል አንዲት ጣሊያናዊት ሴት ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ ወድቃ ነበር። * ለአሥር ዓመታት የቆየው ትዳሯ ሊፈርስ ነው። ከባሏ ጋር ለመታረቅ ብዙ ጊዜ ሞከረች፤ ሆኖም አልተሳካም። እርስ በርስ መጣጣም ባለመቻላቸው የተነሳ ከባሏ ጋር ስለ ተለያየች ሁለት ሴቶች ልጆቿን በራሷ የማሳደግ ኃላፊነት ወደቀባት። ሉቺያ በዚያን ጊዜ የነበረውን ሁኔታ መለስ ብላ በማስታወስ “ትዳራችንን ከመፍረስ ሊያድነው የሚችል ምንም ነገር እንዳልነበረ እርግጠኛ ነበርኩ” ብላለች።
2 እናንተም በትዳራችሁ ውስጥ ችግር ካለ የሉቺያን ስሜት መረዳት ላይከብዳችሁ ይችላል። ትዳራችሁ ችግር ላይ ወድቆ ሊሆን ይችላል፤ በመሆኑም ከመፍረስ መዳኑ እያጠራጠራችሁ ይሆናል። ትዳራችሁ እንዲህ ዓይነት ችግር ላይ ከወደቀ የሚከተለውን ጥያቄ መመርመሩ ጠቃሚ ሆኖ ታገኙታላችሁ:- አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰጠውን ትዳርን የተሳካ ለማድረግ የሚረዳ ጥሩ ምክር ሙሉ በሙሉ ሠርቼበታለሁን?—መዝሙር 119:105
3. ፍቺ በጣም የተስፋፋ ቢሆንም እንኳ ብዙ የተፋቱ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው ምን እንደተሰማቸው ተዘግቧል?
3 በባልና በሚስት መካከል ከፍተኛ ውጥረት በሚፈጠርበት ጊዜ ከሁሉ ይበልጥ ቀላል የሆነው እርምጃ ትዳሩን ማፍረስ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። በብዙ አገሮች የሚፈርሱት ትዳሮች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ቢሄድም እንኳ በቅርብ ጊዜ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የተፋቱ ወንዶችና ሴቶች ትዳራቸው በመፍረሱ በጣም ተጸጽተዋል። ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ ካልተፋቱት ሰዎች ይበልጥ ለአካላዊም ሆነ ለአእምሯዊ ሕመም
ተጋልጠዋል። ልጆቹ ወላጆቻቸው በመፋታታቸው የሚሰማቸው የተመሰቃቀለ ስሜትና ሐዘን ብዙውን ጊዜ ለበርካታ ዓመታት አብሯቸው ይቆያል። የተፋቺዎቹ ወላጆችና ጓደኞችም ይጎዳሉ። የጋብቻ መሥራች የሆነው አምላክስ ሁኔታውን እንዴት ይመለከተዋል?4. በትዳር ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን እንዴት መፍታት ይገባል?
4 ቀደም ባሉት ምዕራፎች ላይ እንደተገለጸው አምላክ ጋብቻን ያቋቋመው የዕድሜ ልክ ጥምረት እንዲሆን አስቦ ነው። (ዘፍጥረት 2:24) ታዲያ ብዙ ትዳሮች የሚፈርሱት ለምንድን ነው? ይህ በቅጽበት የሚከሰት ነገር ላይሆን ይችላል። ብዙውን ጊዜ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ይታያሉ። በትዳር ውስጥ ትንንሽ የነበሩት ችግሮች ቀስ በቀስ እያደጉ ሄደው ፈጽሞ እልባት የማይገኝላቸው መስለው የሚታዩበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ። ሆኖም እነዚህ ችግሮች በመጽሐፍ ቅዱስ እርዳታ ወዲያውኑ ቢፈቱ ብዙ ትዳሮች ከመፍረስ ሊድኑ ይችላሉ።
ከገሐዱ ዓለም ውጭ የሆነ ነገር አትጠብቁ
5. በማንኛውም ትዳር ውስጥ የትኛውን እውነታ መቀበል ያስፈልጋል?
5 አንዳንድ ጊዜ ችግር የሚፈጥረው ነገር አንደኛው ወይም ሁለቱም
የትዳር ጓደኞች ከገሐዱ ዓለም ውጪ የሆኑ ነገሮች የሚጠብቁ መሆናቸው ነው። የፍቅር ታሪኮች፣ የታወቁ መጽሔቶች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ፊልሞች ከገሐዱ ዓለም ውጪ የሆነ ተስፋና ሕልም ሊፈጥሩ ይችላሉ። እነዚህ ሕልሞች መና ሲቀሩ አንድ ሰው እንደተታለለ ሊሰማውና ሊበሳጭ አልፎ ተርፎም ክፉኛ ሊያማርር ይችላል። ይሁን እንጂ ፍጹም ያልሆኑ ሁለት ሰዎች በትዳራቸው መደሰት የሚችሉት እንዴት ነው? ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል።6. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ጋብቻን በተመለከተ ምን ሚዛናዊ አመለካከት አለው? (ለ) በትዳር ውስጥ አለመግባባት እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
6 መጽሐፍ ቅዱስ እውነታውን ቁልጭ አድርጎ ይገልጻል። ትዳር ስለሚያስገኘው ደስታ በግልጽ ይናገራል፤ ሆኖም የሚያገቡ “በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል” የሚል ማስጠንቀቂያም ይሰጣል። (1 ቆሮንቶስ 7:28) ቀደም ሲል እንደተገለጸው ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ፍጹማን አይደሉም፤ የኃጢአት ዝንባሌ አላቸው። አስተሳሰባቸውም ሆነ ስሜታቸው እንዲሁም አስተዳደጋቸው የተለያየ ነው። አንዳንድ ጊዜ ባልና ሚስት በገንዘብ፣ በልጆቻቸውና በዘመዶቻቸው ሊጨቃጨቁ ይችላሉ። አንዳንድ ነገሮችን አብሮ ለመሥራት የሚያስችል በቂ ጊዜ ማጣትና ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ችግሮችም የግጭት መንስኤዎች ሊሆኑ ይችላሉ። * እንዲህ ዓይነቶቹን ችግሮች ለመፍታት ጊዜ ይጠይቃል፤ ሆኖም ተስፋ አትቁረጡ! አብዛኞቹ የትዳር ጓደኛሞች እንዲህ ዓይነቶቹን ችግሮች በመጋፈጥ በሁለቱም ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው መፍትሔዎች ማግኘት ችለዋል።
በመካከላችሁ አለመግባባት ሲፈጠር ተወያዩ
7, 8. የትዳር ጓደኛሞች ስሜታቸው በሚጎዳበት ወይም አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ መፍታት የሚቻልበት ቅዱስ ጽሑፋዊ መንገድ ምንድን ነው?
7 ብዙዎች ስሜታቸው ተጎድቶ፣ አለመግባባት ተፈጥሮ፣ ወይም ስህተት ሠርተው በጉዳዩ ላይ በሚወያዩበት ጊዜ በተረጋጋ መንፈስ መነጋገር ይቸግራቸዋል። “በትክክል የተረዳሽኝ/ኸኝ አልመሰለኝም”
ብለው በግልጽ ከመናገር ይልቅ ስሜታዊ ሊሆኑና ችግሩ ይባስ ሊጋነን ይችላል። ብዙዎቹ “ለራስሽ/ህ ብቻ ነው የምታስቢው/በው” ወይም ደግሞ “አትወጂኝም/ደኝም” ይላሉ። በዚህ ጊዜ እንዲህ የተባለው የትዳር ጓደኛ ከጭቅጭቅ ለመሸሽ ሲል ምንም ምላሽ ላይሰጥ ይችላል።8 ከዚህ ይልቅ የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መከተሉ የተሻለ ነው:- “ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ።” (ኤፌሶን 4:26) አንድ ደስተኛ ባልና ሚስት የጋብቻቸውን 60ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲያከብሩ ለትዳራቸው ስኬት ቁልፉ ምን እንደሆነ ተጠይቀው ነበር። ባልየው “በመካከላችን ቀላል የሆነ አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ እንኳ ጉዳዩን ለነገ አናሳድረውም” ብሏል።
9. (ሀ) በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሐሳብ ልውውጥ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ተብሎ የተገለጸው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ምንም እንኳ ድፍረትና ትሕትና የሚጠይቅ ቢሆንም የትዳር ጓደኛሞች ብዙውን ጊዜ ምን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል?
9 ባልና ሚስት በመካከላቸው አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ሁለቱም ‘ለመስማት የፈጠኑ፣ ለመናገርም የዘገዩ ለቁጣም የዘገዩ’ መሆን አለባቸው። (ያዕቆብ 1:19) ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች በጥሞና ከተደማመጡ በኋላ ይቅርታ የመጠየቅን አስፈላጊነት ሊገነዘቡ ይችላሉ። (ያዕቆብ 5:16) “ስለጎዳሁሽ/ሁህ ይቅርታ” ብሎ ከልብ ምሕረት መጠየቅ ትሕትናና ድፍረት ይጠይቃል። ሆኖም የትዳር ጓደኛሞች በመካከላቸው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በዚህ መንገድ መፍታታቸው ለችግሮቻቸው እልባት ለማግኘት ብቻ ሳይሆን በመካከላቸው ባለው ወዳጅነት ይበልጥ ደስታ የሚያስገኝላቸውን ፍቅርና የጠበቀ ዝምድና እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።
ትዳር የሚጠይቀውን ግዴታ ማሟላት
10. ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጥበቃ እንዲሆናቸው ያቀረበው የትኛው ሐሳብ በዛሬው ጊዜ ላለ ክርስቲያንም ሊሠራ ይችላል?
10 ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ሲጽፍ በጊዜው ‘ዝሙት በጣም ተስፋፍቶ ስለነበረ’ እንዲያገቡ ሐሳብ አቅርቦላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:2) በዛሬው ጊዜ ያለው ዓለም ከጥንቷ ቆሮንቶስ ባላነሰ እንዲያውም በከፋ መጠን ተበላሽቷል። የዓለም ሰዎች በግልጽ የሚነጋገሩባቸው የብልግና ወሬዎች፣ አሳፋሪ አለባበሳቸው፣ በመጽሔቶች፣ በመጽሐፎች፣ በቴሌቪዥንና በፊልሞች የሚቀርቡ ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ታሪኮች አንድ ላይ ተዳምረው ልቅ የጾታ ፍላጎት ይቀሰቅሳሉ። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን የቆሮንቶስ ሰዎች ሐዋርያው ጳውሎስ “በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላል” ብሏቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 7:9
11, 12. (ሀ) ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ምን የማድረግ ግዴታ አለባቸው? ይህንንስ በምን መንፈስ ሊያደርጉት ይገባል? (ለ) ለተወሰነ ጊዜ መከላከል ቢያስፈልግ ይህን ማድረግ የሚገባው እንዴት ነው?
11 ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የተጋቡ ክርስቲያኖችን እንዲህ ሲል ያዝዛቸዋል:- “ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፣ እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋ።” (1 ቆሮንቶስ 7:3) ይበልጥ ትኩረት የተሰጠው መቀበሉ ሳይሆን መስጠቱ እንደሆነ ልብ በሉ። ሁለቱም የትዳር ጓደኞች አንዳቸው ለሌላው ጥቅም የሚያስቡ ከሆነ የፆታ ግንኙነት በትዳር ውስጥ እውነተኛ ደስታ ሊያስገኝ ይችላል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ባሎች ሚስቶቻቸውን “በማስተዋል” እንዲይዟቸው ያዝዛል። (1 ጴጥሮስ 3:7) ይህ በተለይ ትዳር የሚጠይቀውን ግዴታ በመስጠትና በመቀበል ረገድ እንዲህ ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነው። አንዲት ሚስት ፍቅርና አሳቢነት በተሞላበት መንገድ ካልተያዘች በዚህ የትዳር መስክ ደስታ ለማግኘት ልትቸገር ትችላለች።
12 የትዳር ጓደኛሞች እርስ በርሳቸው የሚከላከሉባቸው ጊዜያት ሊኖሩ ይችላሉ። ሚስትየዋ በወሩ ውስጥ በተወሰኑ ወቅቶች ላይ ወይም ደግሞ በጣም በሚደክማት ጊዜ እንዲህ ማድረጓ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። (ከዘሌዋውያን 18:19 ጋር አወዳድሩ።) ባልየው በሥራ ቦታ ከባድ ችግር ሲያጋጥመውና ስሜቱ እንደተሟጠጠ ሲሰማው እንዲህ ሊያደርግ ይችላል። በእንዲህ ዓይነቶቹ ሁኔታዎች ወቅት ሁለቱም በግልጽ እስከተወያዩበትና ‘እስከተስማሙበት’ ድረስ ለጊዜው መከላከላቸው ችግር አይፈጥርም። (1 ቆሮንቶስ 7:5) ይህ ማንኛቸውም ቢሆኑ ተቻኩለው የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ እንዳይደርሱ ይረዳቸዋል። ይሁን እንጂ ሚስትየው ሆን ብላ ባሏ የሚገባውን የምትነፍገው ከሆነ ወይም ደግሞ ባልየው ሆን ብሎ ሚስቱ የሚገባትን ነገር ፍቅራዊ በሆነ መንገድ የማያደርግላት ከሆነ ተጽዕኖ የተደረገበት ወገን ለፈተና ሊጋለጥ ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ በትዳር ውስጥ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ።
13. ክርስቲያኖች አስተሳሰባቸውን ንጹሕ አድርገው መጠበቅ የሚችሉት እንዴት ነው?
13 እንደ ሌሎቹ ክርስቲያኖች ሁሉ የተጋቡ የአምላክ አገልጋዮችም ወራዳና ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ ወሲባዊ ፍላጎት ሊቀሰቅሱ ከሚችሉ ጽሑፎችና ፊልሞች መራቅ አለባቸው። (ቆላስይስ 3:5) በተጨማሪም ከማንኛውም ተቃራኒ ፆታ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት አስተሳሰባቸውንና ድርጊታቸውን መጠበቅ አለባቸው። ኢየሱስ “ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል” ሲል አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 5:28) ባልና ሚስት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት የሚሰጠውን ምክር ሥራ ላይ በማዋል ፈተና ውስጥ ከመውደቅና ምንዝር ከመፈጸም መጠበቅ መቻል ይኖርባቸዋል። የፆታ ግንኙነት የጋብቻ መሥራች ከሆነው ከይሖዋ የተገኘ ጤናማና ውድ ስጦታ እንደሆነ አድርገው በመመልከት በትዳራቸው ውስጥ አስደሳች የሆነ የጠበቀ ግንኙነት ይዘው መመላለስ ይችላሉ።—ምሳሌ 5:15-19
በቅዱስ ጽሑፉ መሠረት ለፍቺ የሚያበቃ ምክንያት
14. አንዳንድ ጊዜ ምን አሳዛኝ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል? ለምንስ?
14 የሚያስደስተው ነገር በክርስቲያናዊ ትዳሮች ውስጥ የሚፈጠሩት አብዛኞቹ ችግሮች እልባት ሊያገኙ የሚችሉ መሆናቸው ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን እንዲህ ማድረግ አይቻል ይሆናል። ሰዎች ፍጹማን ካለመሆናቸውም በላይ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው ኃጢአተኛ ዓለም ውስጥ ስለሚኖሩ አንዳንዶቹ ትዳሮች የመፍረስ አደጋ ያጠላባቸዋል። (1 ዮሐንስ 5:19) ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነቱን ትዕግሥትን እጅግ የሚፈታተን ሁኔታ መቋቋም ያለባቸው እንዴት ነው?
15. (ሀ) በቅዱስ ጽሑፋዊው መመሪያ መሠረት የትዳር ጓደኛን ፈትቶ ሌላ ማግባት የሚቻለው ምን ሲሆን ብቻ ነው? (ለ) አንዳንዶች የፆታ ብልግና የፈጸመውን የትዳር ጓደኛቸውን ላለመፍታት የወሰኑት ለምንድን ነው?
ምዕራፍ 2 ላይ እንደተገለጸው በቅዱስ ጽሑፋዊው መመሪያ መሠረት የትዳር ጓደኛን ፈትቶ ሌላ ማግባት የሚቻለው ምንዝር ሲፈጸም ብቻ ነው። * (ማቴዎስ 19:9) የትዳር ጓደኛችሁ ምንዝር እንደፈጸመ ወይም እንደፈጸመች በቂ ማስረጃ ካገኛችሁ ከባድ ውሳኔ ከፊታችሁ ይደቀናል። ትዳራችሁ እንዳለ እንዲቀጥል ታደርጋላችሁ ወይስ ትፋታላችሁ? እንዲህ አድርጉ የሚል ሕግ የለም። አንዳንድ ክርስቲያኖች ከልቡ ንስሐ የገባውን የትዳር ጓደኛቸውን ሙሉ በሙሉ ይቅር ብለው ትዳራቸው እንዳለ እንዲቀጥል አድርገዋል፤ እንዲህ ማድረጋቸውም ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። ሌሎቹ ደግሞ ለልጆቻቸው ሲሉ ላለመፋታት ወስነዋል።
15 በዚህ መጽሐፍ16. (ሀ) አንዳንዶች ኃጢአት የሠራውን የትዳር ጓደኛቸውን ለመፍታት የገፋፏቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) ተበዳዩ የትዳር ጓደኛ ለመፍታትም ሆነ ላለመፍታት በሚወስንበት ጊዜ ሌሎች ውሳኔውን መተቸት የሌለባቸው ለምንድን ነው?
16 በሌላ በኩል ደግሞ የተፈጸመው ኃጢአት እርግዝና ወይም ደግሞ በጾታ ግንኙነት የሚተላለፍ በሽታ ሊያስከትል ይችላል። ምናልባትም ደግሞ ልጆቹን በፆታ ከሚያስነውር ወላጅ መጠበቅ ሊያስፈልግ ይችላል። አንድ ውሳኔ ላይ ከመድረስ በፊት በጥሞና ማሰብ እንደሚገባ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ የትዳር ጓደኛችሁ የፆታ ብልግና እንደፈጸመ ብታውቁና ከዚያ በኋላ እንደ ወትሮው ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸማችሁን ብትቀጥሉ ይቅር እንዳላችሁትና ትዳራችሁ እንዳለ እንዲቀጥል እንደምትፈልጉ ያሳያል። ከዚህ በኋላ በቅዱስ ጽሑፋዊው መመሪያ መሠረት የትዳር ጓደኛችሁን ፈትታችሁ ሌላ ማግባት አትችሉም። ማንም ሰው በእናንተ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ በውሳኔያችሁ ላይ ተጽዕኖ ማድረግም ሆነ አንድ ውሳኔ ላይ ከደረሳችሁ በኋላ ውሳኔያችሁን መተቸት የለበትም። ውሳኔያችሁ ያስከተለውን ውጤት ተቀብላችሁ መኖር ይገባችኋል። “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና።”—ገላትያ 6:5
ለመለያየት የሚያበቁ ምክንያቶች
17. ቅዱሳን ጽሑፎች ዝሙት ተፈጽሞ ካልሆነ በስተቀር መለያየትን ወይም ፍቺን በተመለከተ ምን ገደቦች አስቀምጠዋል?
17 አንድ የትዳር ጓደኛ ዝሙት ባይፈጽምም እንኳ ከዚህ የትዳር ጓደኛ ለመለየት ምናልባትም ደግሞ ለመፋታት በቂ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎች ይኖራሉን? አዎ፣ ሆኖም በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ አንድ ክርስቲያን እንደገና ለማግባት በማሰብ ከሌላ ሰው ጋር ግንኙነት መመሥረት አይችልም። (ማቴዎስ 5:32) መጽሐፍ ቅዱስ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ መለያየትን የሚፈቅድ ቢሆንም እንኳ ለመለያየት የመረጠው ወገን ‘ሳያገባ መኖር ወይም ከትዳር ጓደኛው ጋር መታረቅ’ እንዳለበት ይገልጻል። (1 ቆሮንቶስ 7:11) መለያየት የተሻለ አማራጭ ሊሆን የሚችልባቸው አንዳንድ አስከፊ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
18, 19. እንደገና ማግባት የማይቻል ቢሆንም እንኳ አንድ ባለ ትዳር በሕጋዊ መንገድ መለያየት ወይም መፋታት የተሻለ መሆን አለመሆኑን እንዲመረምር ሊገፋፉት የሚችሉት አንዳንድ አስከፊ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
18 ቤተሰቡ በባልየው የለየለት ስንፍና እና መጥፎ ልማድ ሳቢያ ከፍተኛ ችግር ላይ ሊወድቅ ይችላል። * የቤተሰቡን ገቢ በቁማር ሊያጠፋው ወይም ደግሞ የአደንዛዥ ዕፅ ወይም የአልኮል ሱሱን ለማርካት ሊጠቀምበት ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።” (1 ጢሞቴዎስ 5:8) እንዲህ ዓይነቱ ሰው አካሄዱን ለመለወጥ ፈቃደኛ ካልሆነ፣ አልፎ ተርፎም ሚስቱ ራስዋ ሠርታ የምታገኘውን ገንዘብ የራሱን መጥፎ ልማድ ለማርካት የሚጠቀምበት ከሆነ ሚስትየዋ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ከባልዋ በመለያየት የራስዋንም ሆነ የልጆቿን ደህንነት ለመጠበቅ ልትወስን ትችላለች።
19 አንድ ባለትዳር የትዳር ጓደኛው ላይ ከባድ ጥቃት የሚፈጽም ከሆነ ምናልባትም ደግሞ የትዳር ጓደኛውን በተደጋጋሚ በመደብደብ ጤናዋንም ሆነ ሕይወቷን አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ሕጋዊ እርምጃ ሊታሰብበት ይችላል። በተጨማሪም አንድ ሥራ 5:29
ባለትዳር የትዳር ጓደኛው የአምላክን ሕግ በሆነ መንገድ እንድትጥስ ዘወትር ሊያስገድዳት የሚሞክር ከሆነና በተለይ ሁኔታው መንፈሳዊ ሕይወቷን አደጋ ላይ የሚጥልበት ደረጃ ላይ ከደረሰ ለመለያየት ልትመርጥ ትችላለች። ችግር ላይ የወደቀው ወገን ‘ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ’ በሕጋዊ መንገድ ከመለያየት ሌላ አማራጭ እንደሌለው ሆኖ ሊሰማው ይችላል።—20. (ሀ) ከቤተሰብ መፍረስ ጋር በተያያዘ የጎለመሱ ጓደኞችና ሽማግሌዎች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? ምን ማድረግስ የለባቸውም? (ለ) ያገቡ ግለሰቦች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መለያየትና ስለ ፍቺ የሚሰጠውን ሐሳብ ምን ለማድረግ ሰበብ አድርገው ሊጠቀሙበት አይገባም?
20 በትዳር ጓደኛ ላይ በሚፈጸም በማንኛውም ዓይነት ከባድ ጥቃት ወቅት ማንም ሰው ተበዳዩን የትዳር ጓደኛ እንዲለያይም ሆነ ከትዳር ጓደኛው ጋር አብሮ እንዲኖር መጫን የለበትም። የጎለመሱ ጓደኞችና ሽማግሌዎች እርዳታና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ሊሰጡ ቢችሉም በባልየውና በሚስትየው መካከል ያለውን እያንዳንዱን ነገር ማወቅ አይችሉም። ይህን ማየት የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። እርግጥ አንዲት ሚስት ሰንካላ በሆነ ምክንያት ከባሏ ብትለያይ አምላክ ላቋቋመው የጋብቻ ዝግጅት አክብሮት እንደሌላት ያሳያል። ሆኖም በጣም አደገኛ የሆነ ዘላቂ ሁኔታ ተፈጥሮ ከባሏ ለመለያየት ብትወስን ማንም ሊተቻት አይገባም። ለመለያየት የሚፈልግን ክርስቲያን ባልንም በተመለከተ ይኸው ሁኔታ ይሠራል። “ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለን።”—ሮሜ 14:10
የፈረሰ ትዳር እንዴት ዳግመኛ እንደተገነባ
21. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትዳር የሚሰጠው ምክር የሚሠራ መሆኑን የትኛው ተሞክሮ ያሳያል?
21 ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሉቺያ ከባሏ ከተለያየች ከሦስት ወራት በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘችና ከእነርሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። “ችግሬን ሊፈቱ የሚችሉ ተግባራዊ ሐሳቦችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሳገኝ በጣም ተገረምኩ” ስትል ገልጻለች። “በመጀመሪያው ሳምንት ካጠናሁ በኋላ ወዲያውኑ ከባሌ ጋር ለመታረቅ ወሰንኩ። በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ ከፍተኛ ችግር ውስጥ የወደቁ ትዳሮችን እንዴት ከመፍረስ ማዳን እንደሚችል ያውቃል
ማለት እችላለሁ፤ ምክንያቱም ትምህርቶቹ የትዳር ጓደኛሞች እርስ በርሳቸው እንዴት መከባበር እንደሚችሉ ያስተምሯቸዋል። አንዳንዶች እንደሚሉት የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰቦችን የሚከፋፈሉ አይደሉም። በእኔ ላይ የተፈጸመው ከዚህ ተቃራኒ የሆነው ነገር ነው።” ሉቺያ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሕይወቷ ውስጥ በሥራ ላይ ማዋል ተምራለች።22. ባለ ትዳሮች ሁሉ በምን ነገር ላይ ሙሉ እምነት ሊኖራቸው ይገባል?
22 ይህ ሁኔታ የታየው በሉቺያ ሕይወት ላይ ብቻ አይደለም። ትዳር ሸክም ሳይሆን በረከት መሆን ይኖርበታል። ይህ እንዲሆን ይሖዋ ትዳርን አስመልክቶ እስከ ዛሬ ከተጻፉት ሁሉ የላቀ ምክር የሚገኝበትን ምንጭ ማለትም ውድ ቃሉን አዘጋጅቷል። መጽሐፍ ቅዱስ “ማስተዋል ለጎደላቸው ጥበብን” [የ1980 ትርጉም] ሊሰጥ ይችላል። (መዝሙር 19:7-11) በቋፍ ላይ የነበሩ ብዙ ትዳሮችን አድኗል፤ ከባድ ችግር የነበረው ሌሎች ብዙ ትዳሮችም ችግራቸውን መፍታት እንዲችሉ ረድቷቸዋል። የትዳር ጓደኛሞች ሁሉ ይሖዋ አምላክ ትዳርን አስመልክቶ በሚሰጠው ምክር ላይ ሙሉ እምነት ይኖራቸው ዘንድ ምኞታችን ነው። ምክሩ ውጤታማ ነው!
^ አን.1 ስሟን ለውጠነዋል።
^ አን.6 ከእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዳንዶቹ ቀደም ባሉት ምዕራፎች ላይ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
^ አን.15 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዝሙት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ምንዝርን፣ ግብረ ሰዶምን፣ ከእንስሳት ጋር የሚፈጸምን የፆታ ግንኙነትና የፆታ ብልቶችን በመጠቀም ሆን ተብሎ የሚፈጸሙ ሌሎች ልቅ የፆታ ግንኙነቶችን ያጠቃልላል።
^ አን.18 ይህ ሁኔታ አንድ ባል አሳቢ ሆኖ እያለ እንደ በሽታ ወይም ደግሞ ሥራ አጥነት በመሳሰሉ ከአቅሙ በላይ በሆኑ ችግሮች ሳቢያ ለቤተሰቡ የሚገባውን ማሟላት የማይችልባቸውን ሁኔታዎች አይጨምርም።