በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ መመሪያ

የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ መመሪያ

የርዕስ ማውጫ

1. በዚህ ሰነድ ውስጥ የቀረቡት መመሪያዎች በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ላይ ክፍል ለሚያቀርቡ በሙሉ ጠቃሚ ናቸው። ክፍል ያላቸው ሁሉ፣ ክፍሉን ከመዘጋጀታቸው በፊት በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ እና በዚህ ሰነድ ላይ ክፍላቸውን አስመልክቶ የቀረቡትን መመሪያዎች መከለስ ይጠበቅባቸዋል። ሁሉም አስፋፊዎች የተማሪ ክፍሎችን ለማቅረብ ራሳቸውን እንዲያቀርቡ ማበረታቻ ሊሰጣቸው ይገባል። በቋሚነት ከጉባኤው ጋር በመተባበር ላይ ያሉ ሌሎች ሰዎችም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር የሚስማሙና ሕይወታቸውን በክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመሩ ከሆነ ሊሳተፉ ይችላሉ። የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት የበላይ ተመልካቹ መመዝገብ እንደሚፈልጉ ጥያቄ ካቀረቡ አስፋፊ ያልሆኑ ሰዎች ጋር መወያየት ይኖርበታል፤ ከዚያም ለግለሰቡ ብቃቶቹን ማሟላት ወይም አለማሟላቱን ሊገልጽለት ይገባል። ይህ መደረግ የሚኖርበት ግለሰቡን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠናው ሰው (ወይም አማኝ የሆነ ወላጁ) በተገኘበት ነው። ብቃቶቹ ያልተጠመቀ አስፋፊ ለመሆን ከሚያስፈልጉት ብቃቶች ጋር ተመሳሳይ ናቸው።—od ምዕ. 8 አን. 8

 የመግቢያ ሐሳብ

2. አንድ ደቂቃ። በእያንዳንዱ ሳምንት፣ የመክፈቻ መዝሙርና ጸሎት ከቀረበ በኋላ የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ሊቀ መንበሩ አድማጮች የሚቀርቡትን ክፍሎች በጉጉት እንዲጠባበቁ ያደርጋል። ሊቀ መንበሩ ጉባኤውን ይበልጥ በሚጠቅሙ ነጥቦች ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርበታል።

  ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት

 3ንግግር፦ አሥር ደቂቃ። ጭብጡ እንዲሁም ሁለት ወይም ሦስት ዋና ነጥቦችን የያዘ ሐሳብ በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ ላይ ይገኛል። ይህ ንግግር መሰጠት ያለበት ለአንድ ሽማግሌ ወይም ብቃት ላለው የጉባኤ አገልጋይ ነው። በሳምንታዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ላይ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የሚጀመር ከሆነ መጽሐፉን የሚያስተዋውቅ ቪዲዮ ይታያል። ተናጋሪው ቪዲዮው ከጭብጡ ጋር እንዴት እንደሚያያዝ መናገር ይችላል። ያም ሆኖ በስብሰባው አስተዋጽኦ ላይ የቀረቡትን ነጥቦች መሸፈን ይገባዋል። በተጨማሪም ጊዜ በፈቀደለት መጠን በክፍሉ ውስጥ የተካተተውን ትምህርት ለማጠናከር ታስበው የተካተቱትን ሥዕላዊ መግለጫዎች ጥሩ አድርጎ ሊጠቀምባቸው ይገባል። በአስተዋጽኦው ላይ ያሉትን ነጥቦች ለማዳበር የሚረዳው ከሆነ ተጨማሪ ማመሣከሪያ ጽሑፎችንም መጠቀም ይችላል።

 4መንፈሳዊ ዕንቁዎች፦ አሥር ደቂቃ። ይህ ክፍል ምንም መግቢያና መደምደሚያ ሳይኖረው በጥያቄና መልስ የሚሸፈን ነው። ለአንድ ሽማግሌ ወይም ብቃት ላለው የጉባኤ አገልጋይ መሰጠት ይኖርበታል። ክፍሉን የሚያቀርበው ወንድም፣ ሁለቱንም ጥያቄዎች ለአድማጮች ማቅረብ ይኖርበታል። በተጨማሪም የቀረቡት ጥቅሶች መነበብ ያስፈልጋቸው እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን ይችላል። አድማጮች ሐሳብ መስጠት ያለባቸው በ30 ሴኮንድ ወይም ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው።

 5የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ አራት ደቂቃ። ይህን የተማሪ ክፍል የሚያቀርቡት ወንዶች ናቸው። ተማሪው መግቢያ ወይም መደምደሚያ መናገር ሳያስፈልገው ክፍሉን በንባብ ብቻ ያቀርበዋል። የስብሰባው ሊቀ መንበር ተማሪዎቹ በጥራትና የሚያነቡትን ነገር በሚገባ እንደተረዱ በሚያሳይ መንገድ ብሎም በቅልጥፍና፣ ቁልፍ ቃላትን በተገቢው ሁኔታ በማጥበቅ፣ ድምፅን በመለዋወጥ፣ በተገቢው ቦታ ቆም በማለትና የራሳቸውን ተፈጥሯዊ አነጋገር በመጠቀም ማንበብ እንዲችሉ ለመርዳት ጥረት ያደርጋል። አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍሎች አጠር ያሉ ሌሎቹ ደግሞ ረዘም ያሉ ናቸው፤ በመሆኑም የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ የበላይ ተመልካቹ እነዚህን ክፍሎች በሚመድብበት ወቅት የተማሪዎቹን ችሎታ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል።

 በአገልግሎት ውጤታማ ለመሆን ተጣጣር

6. አሥራ አምስት ደቂቃ። ይህ የስብሰባው ምዕራፍ ሁሉም ለአገልግሎት መለማመድ እንዲሁም ከሰዎች ጋር የመነጋገር፣ የመስበክና የማስተማር ችሎታቸውን ማሻሻል እንዲችሉ ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። እንደ አስፈላጊነቱ አንዳንድ የተማሪ ክፍሎች ለሽማግሌዎችም ሊሰጡ ይችላሉ። እያንዳንዱ ተማሪ በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ ላይ ከተመደበለት ክፍል አጠገብ በቅንፍ የተቀመጠውን ማስተማር ወይም ሰዎችን ውደዱ ከሚለው ብሮሹር የተወሰደ ነጥብ ሊሠራበት ይገባል። አንዳንድ ጊዜ በውይይት የሚቀርብ ክፍል በፕሮግራሙ ላይ ሊካተት ይችላል። ይህ ክፍል ለአንድ ሽማግሌ ወይም ብቃት ላለው የጉባኤ አገልጋይ መሰጠት ይኖርበታል።—የውይይት ክፍሎችን ማቅረብ የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ  አንቀጽ 15ን ተመልከት።

 7ውይይት መጀመር፦ ይህን የተማሪ ክፍል ወንዶች ወይም ሴቶች ሊያቀርቡት ይችላሉ። ረዳት ሆነው የሚመደቡት የአንድ ቤተሰብ አባላት ወይም ተመሳሳይ ፆታ ያላቸው ተማሪዎች መሆን ይኖርባቸዋል። ተማሪውም ሆነ ረዳቱ ሊቆሙ ወይም ሊቀመጡ ይችላሉ።—የዚህን ክፍል ይዘትና መቼት በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት  አንቀጽ 12 እና  13ን ተመልከት።

 8ተመላልሶ መጠየቅ፦ ይህን የተማሪ ክፍል ወንዶች ወይም ሴቶች ሊያቀርቡት ይችላሉ። ረዳት ሆኖ የሚመደበው ሰው ተመሳሳይ ፆታ ያለው ሊሆን ይገባል። (km 12/06 ገጽ 4) ተማሪውም ሆነ ረዳቱ ሊቆሙ ወይም ሊቀመጡ ይችላሉ። ክፍሉ፣ ተማሪው ከዚህ በፊት ካነጋገረው ሰው ጋር ውይይት ሲቀጥል የሚያሳይ ሊሆን ይገባል።—የዚህን ክፍል ይዘትና መቼት በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት  አንቀጽ 12 እና  13ን ተመልከት።

 9ደቀ መዛሙርት ማድረግ፦ ይህን የተማሪ ክፍል ወንዶች ወይም ሴቶች ሊያቀርቡት ይችላሉ። ረዳት ሆኖ የሚመደበው ሰው ተመሳሳይ ፆታ ያለው ሊሆን ይገባል። (km 12/06 ገጽ 4) ተማሪውም ሆነ ረዳቱ ሊቆሙ ወይም ሊቀመጡ ይችላሉ። ይህ ክፍል ከዚያ ቀደም መመራት የጀመረ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቀጣይ ክፍል እንደሆነ ተደርጎ መቅረብ ይኖርበታል። ተማሪው ከመግቢያ እና መደምደሚያ ጋር በተያያዙ የምክር መስጫ ነጥቦች ዙሪያ እንዲሠራ ተጠይቆ ካልሆነ በስተቀር መግቢያም ሆነ መደምደሚያ መጠቀም አያስፈልግም። ለክፍሉ የተመደቡትን አንቀጾች ጮክ ብሎ ማንበብ የሚቻል ቢሆንም የግድ አስፈላጊ አይደለም።

 10እምነታችንን ማብራራት፦ ይህ ክፍል በንግግር መልክ የሚቀርብ ከሆነ ወንዶች ሊያቀርቡት ይገባል። በሠርቶ ማሳያ መልክ የሚቀርብ ከሆነ ደግሞ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ሊያቀርቡት ይችላሉ። ረዳት ሆነው የሚመደቡት የአንድ ቤተሰብ አባላት ወይም ተመሳሳይ ፆታ ያላቸው ተማሪዎች መሆን ይኖርባቸዋል። ተማሪው በማመሣከሪያ ጽሑፉ ላይ ያለውን ሐሳብ ተጠቅሞ በጭብጡ ላይ ላለው ጥያቄ በግልጽና በዘዴ መልስ ሊሰጥ ይገባል። ተማሪው በክፍሉ ላይ የማመሣከሪያ ጽሑፉን ለመጥቀስ ወይም ላለመጥቀስ መምረጥ ይችላል።

 11ንግግር፦ ይህን የተማሪ ክፍል ወንዶች በንግግር መልክ ሊያቀርቡት ይገባል። ንግግሩ የተመሠረተው ሰዎችን ውደዱ በተባለው ብሮሹር ተጨማሪ መረጃ ሀ ላይ ከሆነ ተማሪው ጥቅሱን በአገልግሎት ላይ መጠቀም የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ሊገልጽ ይገባል። ለምሳሌ ጥቅሱን መቼ መጠቀም እንደሚቻል፣ የጥቅሱን ትርጉም እንዲሁም ጥቅሱን ተጠቅሞ ሰዎችን ማስረዳት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ሊገልጽ ይችላል። ንግግሩ የተመሠረተው ሰዎችን ውደዱ በተባለው ብሮሹር ላይ ባሉት ምዕራፎች ላይ ከሆነ ተማሪው ነጥቡን በአገልግሎት ላይ ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ መግለጽ ይኖርበታል። አስፈላጊ ከሆነ በምዕራፉ ውስጥ ነጥብ 1 ላይ የተጠቀሰውን ምሳሌ ወይም በምዕራፉ ውስጥ ካሉት ተጨማሪ ጥቅሶች መካከል የፈለገውን ሊያጎላ ይችላል።

   12ይዘት፦ በዚህና በሚቀጥለው አንቀጽ ውስጥ ያሉት ሐሳቦች የሚናገሩት “ውይይት መጀመር” እና “ተመላልሶ መጠየቅ” ስለሚሉት ክፍሎች ነው። ሌላ መመሪያ ካልተሰጠ በቀር የተማሪው ዓላማ ለግለሰቡ የሚጠቅም አጭር የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ማካፈልና ለቀጣዩ ውይይት መሠረት መጣል ሊሆን ይገባል። ተማሪው ወቅታዊና ለአካባቢው ተስማሚ የሆነ ርዕሰ ጉዳይ መምረጥ ይኖርበታል። በማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን ውስጥ የሚገኝ አንድ ጽሑፍ ወይም ቪዲዮ ለማስተዋወቅ ወይም ላለማስተዋወቅ ሊመርጥ ይችላል። ተማሪዎች በቃል የሸመደዱትን አቀራረብ ከመጠቀም ይልቅ ውይይት የማድረግ ክህሎት ሊለማመዱ ይገባል፤ ይህም አሳቢነት ማሳየትንና ተፈጥሯዊ አነጋገር መጠቀምን ይጨምራል።

   13መቼት፦ ተማሪው የተመደበለትን መቼት ለአካባቢው ሁኔታ በሚስማማ መልኩ ሊጠቀምበት ይገባል። ለምሳሌ፦

  1.  (1) ከቤት ወደ ቤት፦ ይህ መቼት በአካል፣ በስልክም ሆነ በደብዳቤ ተጠቅሞ ከቤት ወደ ቤት የሚደረገውን አገልግሎት እንዲሁም ከዚህ በፊት ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ለተገኘ ሰው ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግን ያካትታል።

  2.  (2) መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት፦ ይህ መቼት የዕለት ተዕለት ጭውውቶችን ወደ ምሥክርነት መቀየርን ያመለክታል። ይህም በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ በሰፈራችን፣ በሕዝብ መጓጓዣ ላይ እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችንን ስናከናውን ለምናገኛቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ ማካፈልን ሊያካትት ይችላል።

  3.  (3) የአደባባይ ምሥክርነት፦ ይህ መቼት የጋሪ ምሥክርነትን፣ በገበያ ቦታ የሚሰጠውን ምሥክርነት እንዲሁም መንገድ ላይ፣ መናፈሻ ውስጥ፣ በመኪና ማቆሚያዎች ወይም ሰዎች በሚገኙበት በማንኛውም ቦታ መመሥከርን ሊያካትት ይችላል።

 14ቪዲዮዎችንና ጽሑፎችን መጠቀም፦ ተማሪው እንደ ሁኔታው አንድን ቪዲዮ ወይም ጽሑፍ ለመጠቀም ሊወስን ይችላል። አንድ የተማሪ ክፍል ቪዲዮ ካለው ወይም ተማሪው ቪዲዮ ለመጠቀም ከመረጠ ቪዲዮውን ማስተዋወቅና ማወያየት ይኖርበታል፤ ሆኖም ክፍሉ ላይ ቪዲዮውን ማጫወት አይኖርበትም።

  ክርስቲያናዊ ሕይወት

15. ይህ ክፍል በመዝሙር ከተጀመረ በኋላ ባሉት 15 ደቂቃዎች ውስጥ አድማጮች የአምላክን ቃል ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚረዱ አንድ ወይም ሁለት ክፍሎች ይቀርባሉ። የተለየ መግለጫ ካልተሰጠ በስተቀር እነዚህ ክፍሎች ለሽማግሌዎች ወይም ብቃት ላላቸው የጉባኤ አገልጋዮች ሊሰጡ ይገባል፤ “ለጉባኤው እንደሚያስፈልግ” የሚለውን ክፍል ማቅረብ ያለባቸው ግን ሽማግሌዎች ናቸው። ክፍሉ በውይይት የሚቀርብ ከሆነ ተናጋሪው በጽሑፉ ላይ ካሉት ጥያቄዎች በተጨማሪ በሌሎች ቦታዎችም ላይ ጥያቄዎችን ሊጠይቅ ይችላል። ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ለመሸፈንና አድማጮችን ለማሳተፍ የሚያስችል በቂ ጊዜ እንዲኖረው መግቢያውን ማሳጠር ይኖርበታል። ክፍሉ ቃለ መጠይቅ የሚያካትት በሚሆንበት ጊዜ ቃለ መጠይቅ የሚደረግለት ግለሰብ የሚቻል ከሆነ ቦታው ላይ ሆኖ ከሚናገር ይልቅ መድረክ ላይ ወጥቶ ቃለ መጠይቅ ቢደረግለት ይመረጣል።

  16የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፦ ሠላሳ ደቂቃ። ይህ ክፍል ብቃት ላለው ሽማግሌ መሰጠት ይኖርበታል። (የሽማግሌዎች ቁጥር ውስን በሆነባቸው ጉባኤዎች ውስጥ ብቃት ያላቸውን የጉባኤ አገልጋዮች እንደ አስፈላጊነቱ መጠቀም ይቻል ይሆናል።) የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን የመምራት ብቃት ያላቸው እነማን እንደሆኑ የሚወስነው የጉባኤው የሽማግሌዎች አካል ሊሆን ይገባል። የሽማግሌዎች አካል የመረጣቸው ወንድሞች ለጥናቱ የተመደበውን ጊዜ በመጠበቅ፣ ቁልፍ ጥቅሶችን ጎላ አድርጎ በመግለጽ እና በትምህርቱ ውስጥ የተካተቱትን ተግባራዊ ነጥቦች ሁሉም እንዲያስተውሉ በመርዳት ጥናቱን ትርጉም ባለው መንገድ መምራት ይኖርባቸዋል። ጥናቱን እንዲመሩ የተፈቀደላቸው ወንድሞች የጥያቄና መልስ ክፍል እንዴት መመራት እንዳለበት የሚገልጹ ከዚህ ቀደም የወጡ መመሪያዎችን መከለሳቸው ጠቃሚ ነው። (w23.04 ገጽ 24 ሣጥን) ለሳምንቱ የተመደበው ክፍል በሚገባ ከተሸፈነ ሰዓቱን ለመጨረስ ሲባል ብቻ ጥናቱን ማራዘም አያስፈልግም። በተቻለ መጠን በየሳምንቱ እንዲመሩ እና እንዲያነቡ የሚመደቡት ወንድሞች የተለያዩ መሆን ይኖርባቸዋል። የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ሊቀ መንበሩ ጥናቱ አጠር ብሎ እንዲቀርብ መመሪያ ከሰጠው ጥናቱን የሚመራው ወንድም ጥናቱን እንዴት ማሳጠር እንደሚችል ይወስናል። ምናልባት አንዳንድ አንቀጾች ሳይነበቡ ወደ ጥያቄው ለመሄድ ሊወስን ይችል ይሆናል።

  የመደምደሚያ ሐሳብ

17. ሦስት ደቂቃ። የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ሊቀ መንበሩ በስብሰባው ላይ የቀረቡትን ጠቃሚ ነጥቦች ይከልሳል። በሚቀጥለው ሳምንት የሚቀርበውን ትምህርት ማስተዋወቅም ይኖርበታል። ጊዜ የሚበቃ ከሆነ፣ በሚቀጥለው ሳምንት ክፍል እንዲያቀርቡ የተመደቡ ተማሪዎችን ስም ሊናገር ይችላል። የተለየ መግለጫ ካልተሰጠ በስተቀር አስፈላጊ የሆኑ ማስታወቂያዎችን መናገርም ሆነ ደብዳቤዎችን ማንበብ ያለበት ሊቀ መንበሩ ነው፤ ይህን የሚያደርገው የመደምደሚያውን ሐሳብ ሲያቀርብ ነው። መደበኛ የመስክ አገልግሎት ዝግጅቶችንና የጽዳት ፕሮግራምን የመሰሉ የተለመዱ ክንውኖች ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ መለጠፍ ይኖርባቸዋል እንጂ ከመድረክ በማስታወቂያ ሊነገሩ አይገባም። ሊቀ መንበሩ የመደምደሚያ ሐሳቡን እንዲያቀርብ የተመደበለት ጊዜ ማስታወቂያዎችን ለመናገር ወይም ደብዳቤዎችን ለማንበብ በቂ ካልሆነ “ክርስቲያናዊ ሕይወት” የሚለውን ክፍል የሚያቀርቡ ወንድሞች እንደ አስፈላጊነቱ ክፍላቸውን እንዲያሳጥሩ ሊጠይቃቸው ይችላል። ( አንቀጽ 16 እና  19ን ተመልከት።) ስብሰባው በመዝሙርና በጸሎት ይደመደማል።

  ምስጋና እና ምክር

18. ከእያንዳንዱ የተማሪ ክፍል በኋላ የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ሊቀ መንበሩ ለተማሪው የተመደበውን የጥናት ነጥብ ተጠቅሞ በአንድ ደቂቃ ገደማ ውስጥ ለተማሪው ምስጋናና ምክር ይሰጣል። ሊቀ መንበሩ የተማሪ ክፍሉን ሲያስተዋውቅ የጥናት ቁጥሩን አይናገርም። ይሁን እንጂ ተማሪው ክፍሉን አቅርቦ ሲጨርስ ካመሰገነው በኋላ የጥናት ቁጥሩን መጥቀስ ይችላል። ከዚያም ተማሪው ነጥቡን በጥሩ መንገድ ሠርቶበታል ያለበትን ምክንያት መናገር ወይም ተማሪው ይህን ነጥብ በሌላ ጊዜ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ለምን እና እንዴት እንደሆነ በደግነት መግለጽ ይችላል። ሊቀ መንበሩ ተማሪውን ወይም አድማጮቹን እንደሚጠቅም ከተሰማው ሌሎች የክፍሉን ገጽታዎች በማንሳት ሐሳብ ሊሰጥባቸው ይችላል። ከስብሰባው በኋላ ወይም በሌላ ጊዜ ሰዎችን ውደዱ በተባለው ብሮሹር፣ በማስተማር ብሮሹር ወይም በአገልግሎት ትምህርት ቤት መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ ገንቢ የሆነ ተጨማሪ ምክር በግል መስጠት ይችላል፤ ምክሩን የሚሰጠው ተማሪው እንዲሠራበት በተሰጠው የጥናት ነጥብ ወይም በሌላ የጥናት ነጥብ ላይ ሊሆን ይችላል።—የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ሊቀ መንበሩና ረዳት ምክር ሰጪው ያላቸውን ሚና በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት  አንቀጽ 19,  24 እና  25ን ተመልከት።

     ጊዜ አጠባበቅ

19የትኛውም ክፍል ከተመደበለት ጊዜ ማለፍ የለበትም፤ የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ሊቀ መንበሩም ቢሆን ሰዓት ሊያሳልፍ አይገባም። የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦው ለእያንዳንዱ ክፍል የተመደበውን ጊዜ የሚገልጽ ቢሆንም ትምህርቱ በበቂ ሁኔታ እስከተሸፈነ ድረስ ሰዓቱን ለመሙላት ሲባል ብቻ ተጨማሪ ነገር መናገር አያስፈልግም። ክፍሎችን የሚያቀርቡ ወንድሞች ሰዓት ካሳለፉ የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ሊቀ መንበሩ ወይም ረዳት ምክር ሰጪው በግል ምክር ሊሰጧቸው ይገባል። ( አንቀጽ 24 እና  25ን ተመልከት።) መዝሙርንና ጸሎትን ጨምሮ ጠቅላላው ስብሰባ 1 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ይፈጃል።

 የወረዳ የበላይ ተመልካች ጉብኝት

20. የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉባኤውን የሚጎበኝ ከሆነ ስብሰባው መካሄድ ያለበት በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ ላይ ባለው መመሪያ መሠረት ቢሆንም የሚከተሉት ማስተካከያዎች ይደረጋሉ፦ “ክርስቲያናዊ ሕይወት” በሚለው ክፍል ሥር ያለው “የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት” የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በሚያቀርበው የ30 ደቂቃ የአገልግሎት ንግግር ይተካል። የአገልግሎት ንግግሩ ከመቅረቡ በፊት የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ሊቀ መንበሩ የቀረቡትን ክፍሎች ይከልሳል፤ በሚቀጥለው ሳምንት የሚቀርቡትን ክፍሎች ያስተዋውቃል፤ አስፈላጊ የሆኑ ማስታወቂያዎችን ይናገራል፤ ደብዳቤዎችን ያነብባል፤ ከዚያም የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ያስተዋውቃል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ የአገልግሎት ንግግሩን ካቀረበ በኋላ በመረጠው መዝሙር ስብሰባውን ይደመድማል። ሌላ ወንድም የመደምደሚያውን ጸሎት እንዲያቀርብ ሊጋብዝ ይችላል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በሚጎበኝበት ሳምንት ጉባኤው በሚካሄድበት ቋንቋ በተጨማሪ አዳራሾች የሚቀርብ ክፍል አይኖርም። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በሥሩ ቡድን ያቀፈ ጉባኤን በሚጎበኝበት ጊዜ ቡድኑ የራሱን ስብሰባ ሊያካሂድ ይችላል። ይሁን እንጂ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ የአገልግሎት ንግግሩን የሚያቀርብበት ሰዓት ሲደርስ ቡድኑ ከዋናው ጉባኤ ጋር ሆኖ ንግግሩን ያዳምጣል።

 የወረዳ ወይም የክልል ስብሰባ የሚደረግበት ሳምንት

21. የወረዳ ወይም የክልል ስብሰባ በሚደረግበት ሳምንት ላይ ምንም ዓይነት የጉባኤ ስብሰባዎች አይደረጉም። በእነዚህ ወቅቶች የሚወሰዱት ክፍሎች በግል ወይም በቤተሰብ መጠናት እንደሚኖርባቸው ለጉባኤው ማሳሰቢያ መስጠት ያስፈልጋል።

 የመታሰቢያው በዓል ሳምንት

22. የመታሰቢያው በዓል በሳምንቱ መካከል ባሉት ቀናት ላይ የሚውል ከሆነ በሳምንቱ መካከል የሚደረገው የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አይኖርም።

  የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ የበላይ ተመልካች

23. በሽማግሌዎች አካል የተመረጠ አንድ ሽማግሌ የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለግላል። ስብሰባው በሚገባ የተደራጀ እንዲሆንና በእነዚህ መመሪያዎች መሠረት እንዲካሄድ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። ከረዳት ምክር ሰጪው ጋር ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል። የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ የበላይ ተመልካቹ፣ የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ እንደደረሰው የሁለቱን ወር የሳምንቱ መሃል ስብሰባ ክፍሎች ፕሮግራም ያወጣል። ይህም የተማሪ ክፍሎችንም ሆነ ከዚያ ውጭ ያሉትን የስብሰባ ክፍሎች ያጠቃልላል፤ በተጨማሪም በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ ሊቀ መንበር እንዲሆኑ በሽማግሌዎች አካል ከተመረጡ ወንድሞች መካከል ሊቀ መንበር ይመድባል። ( ከአንቀጽ 3-16 እና  24ን ተመልከት።) የተማሪ ክፍል የሚያቀርቡትን ሰዎች ሲመድብ የተማሪውን ዕድሜ፣ ተሞክሮ እንዲሁም በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ያለውን የመናገር ነፃነት ከግምት ማስገባት ይኖርበታል። ሌሎቹን የስብሰባ ክፍሎች በሚመድብበት ጊዜም በተመሳሳይ የማመዛዘን ችሎታውን ሊጠቀም ይገባል። እያንዳንዱ የተማሪ ክፍል፣ ክፍሉ ከመቅረቡ ቢያንስ ከሦስት ሳምንት በፊት ለተማሪው ሊሰጥ ይገባል። የተማሪ ክፍሎቹን ለመስጠት የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ክፍል መስጫ (S-89) ቅጽ መጠቀም ይገባል። የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ የበላይ ተመልካቹ የስብሰባው አጠቃላይ ፕሮግራም በማስታወቂያ ሰሌዳው ላይ እንዲለጠፍ ማድረግ ይኖርበታል። የስብሰባ የበላይ ተመልካቹን ለማገዝ አንድ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ እንዲመደብ የሽማግሌዎች አካል ሊወስን ይችላል። ይሁንና ከተማሪ ክፍሎች ውጭ ያሉትን የስብሰባ ክፍሎች ፕሮግራም ማውጣት ያለባቸው ሽማግሌዎች ብቻ ናቸው።

   የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ሊቀ መንበር

24. በየሳምንቱ አንድ ሽማግሌ በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ላይ ሊቀ መንበር ሆኖ ያገለግላል። (የሽማግሌዎች ቁጥር ውስን ከሆነ ብቃት ያላቸው የጉባኤ አገልጋዮች እንደ አስፈላጊነቱ ሊቀ መንበር ሆነው ሊመደቡ ይችላሉ።) ሊቀ መንበሩ የመግቢያና የመደምደሚያ ሐሳቦቹን የመዘጋጀት ኃላፊነት አለበት። እንዲሁም ሁሉንም ክፍሎች ያስተዋውቃል፤ በተጨማሪም ጉባኤው ካለው የሽማግሌዎች ብዛት አንጻር በስብሰባው ላይ ሌሎች ክፍሎችን፣ በተለይም ውይይት ማድረግ ሳያስፈልግ እንዲሁ የሚታዩ ቪዲዮዎችን እንዲያቀርብ ሊመደብ ይችላል። በየክፍሎቹ መካከል የሚሰጣቸው ሐሳቦች በጣም አጭር መሆን ይኖርባቸዋል። ለዚህ ኃላፊነት ብቁ የሆኑ ሽማግሌዎች የትኞቹ እንደሆኑ የሽማግሌዎች አካል ይወስናል። ብቁ የሆኑት ሽማግሌዎች በዙር ሊቀ መንበር ሆነው እንዲያገለግሉ ይመደባሉ። ጉባኤው ካለው ሁኔታ አንጻር የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ የበላይ ተመልካቹ ከሌሎች ብቁ የሆኑ ሽማግሌዎች ይልቅ ቶሎ ቶሎ ሊቀ መንበር ሆኖ እንዲያገለግል ሊመደብ ይችላል። አንድ ሽማግሌ የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ብቁ ከሆነ በአብዛኛው የስብሰባው ሊቀ መንበር ሆኖ ለማገልገልም ብቃት ይኖረዋል። ይሁን እንጂ ሊቀ መንበር ሆኖ የሚያገለግለው ሽማግሌ የተማሪ ክፍሎች ለሚያቀርቡት ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ምስጋናና አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ምክር መስጠት እንደሚጠበቅበት ማስታወስ ይገባል። በተጨማሪም ሊቀ መንበሩ ስብሰባው በሰዓቱ እንዲያልቅ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። ( አንቀጽ 17 እና  19ን ተመልከት።) ሊቀ መንበሩ ከፈለገ እንዲሁም በቂ ቦታ ካለ መድረኩ ላይ ሌላ ማይክሮፎን እንዲቆም ማድረግ ይችላል፤ ይህም ቀጣዩን ክፍል የሚያቀርበው ወንድም ወደ አትራኖሱ ሄዶ ቦታውን እስኪይዝ ድረስ ሊቀ መንበሩ ክፍሉን እንዲያስተዋውቅ ያስችለዋል። በተጨማሪም ሊቀ መንበሩ ከፈለገ የተማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ሲቀርብም ሆነ “በአገልግሎት ውጤታማ ለመሆን ተጣጣር” በሚለው የስብሰባው ምዕራፍ ወቅት መድረኩ ላይ ጠረጴዛና ወንበር አድርጎ መቀመጥ ይችላል። እንዲህ ማድረግ ጊዜ ሊቆጥብ ይችላል።

   ረዳት ምክር ሰጪ

25. ይህ ኃላፊነት የሚሰጠው ሽማግሌ፣ የሚቻል ከሆነ ልምድ ያለው ተናጋሪ ቢሆን ጥሩ ነው። ረዳት ምክር ሰጪው ከመድረክ ለሚያስተምሩ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች እንደ አስፈላጊነቱ በግል ምክር የመስጠት ኃላፊነት አለበት፤ ይህም የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ክፍሎችንና የሕዝብ ንግግሮችን የሚያቀርቡ እንዲሁም የመጠበቂያ ግንብ ጥናትና የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚመሩ ወይም በእነዚህ ወቅቶች የሚያነብቡ ሽማግሌዎችንና የጉባኤ አገልጋዮችን ያካትታል። ( አንቀጽ 19ን ተመልከት።) በጉባኤው ውስጥ ንግግር የማቅረብና የማስተማር ብቃት ያላቸው በርካታ ሽማግሌዎች ካሉ እነዚህ ወንድሞች በየዓመቱ እየተፈራረቁ ረዳት ምክር ሰጪ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ። ረዳት ምክር ሰጪው ወንድሞች ክፍል ባቀረቡ ቁጥር ምክር መስጠት አያስፈልገውም።

 ተጨማሪ አዳራሾች

26. ጉባኤዎች፣ ያላቸውን የተማሪ ቁጥር ግምት ውስጥ በማስገባት የተማሪ ክፍሎች በሌሎች አዳራሾችም እንዲቀርቡ ማድረግ ይችላሉ። በእነዚህ አዳራሾች ጥሩ ችሎታ ያለው ምክር ሰጪ ሊመደብ ይገባል፤ ከተቻለ ሽማግሌ ቢሆን ይመረጣል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቃት ያለው የጉባኤ አገልጋይ መጠቀም ይቻላል። ይህን ኃላፊነት ማን መያዝ እንዳለበት እና በዙር ሊያደርጉት ይገባ እንደሆነና እንዳልሆነ የሚወስነው የሽማግሌዎች አካል ነው። ምክር ሰጪው በ አንቀጽ 18 ላይ የቀረበውን መመሪያ መከተል ይኖርበታል። በተጨማሪ አዳራሽ ውስጥ ክፍሎች የሚቀርቡ ከሆነ “ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት” በሚለው ክፍል ውስጥ ካለው “መንፈሳዊ ዕንቁዎች” ከሚለው ክፍል በኋላ ተማሪዎቹ ወደ አዳራሹ እንዲሄዱ ማሳወቅ ያስፈልጋል። የመጨረሻው የተማሪ ክፍል ሲያልቅ ወደ ዋናው አዳራሽ ይመለሳሉ።

 ቪዲዮዎች

27. በዚህ ስብሰባ ላይ አንዳንድ የተመረጡ ቪዲዮዎች ይቀርባሉ። በሳምንቱ መካከል በሚካሄደው ስብሰባ ላይ የሚቀርቡ ቪዲዮዎችን የተለያዩ መሣሪያዎችን በመጠቀም ከJW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ማግኘት ይቻላል።

© 2023 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania

S-38-AM 11/23