ወደ ሰማይ የሚሄዱት እነማን ናቸው?

ወደ ሰማይ የሚሄዱት እነማን ናቸው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አምላክ የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ታማኝ ክርስቲያኖች በመምረጥ ከሞቱ በኋላ ትንሣኤ አግኝተው በሰማይ ላይ እንዲኖሩ ዝግጅት አድርጓል። (1 ጴጥሮስ 1:3, 4) እነዚህ ሰዎች ከተመረጡ በኋላ ሰማያዊ ውርሻቸውን እንዳያጡ ጠንካራ እምነትና ንጹሕ ምግባር ይዘው መቀጠል አለባቸው።—ኤፌሶን 5:5፤ ፊልጵስዩስ 3:12-14

ወደ ሰማይ የሚሄዱት እዚያ ምን ያደርጋሉ?

 ነገሥታትና ካህናት በመሆን ከኢየሱስ ጋር ለ1,000 ዓመት ይገዛሉ። (ራእይ 5:9, 10፤ 20:6) “አዲስ ሰማያት” ወይም ሰማያዊ መስተዳድር የሚያቋቁሙ ሲሆን በምድር ላይ የሚኖረውን ማኅበረሰብ የሚያመለክተውን “አዲስ ምድር” ይገዛሉ። ከሰማይ ሆነው የሚገዙት እነዚህ ነገሥታት፣ የሰው ልጆች አምላክ መጀመሪያ አስቦላቸው በነበረው ጽድቅ የሰፈነበት ሁኔታ መኖር እንዲችሉ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።—ኢሳይያስ 65:17፤ 2 ጴጥሮስ 3:13

ወደ ሰማይ የሚሄዱት ምን ያህል ሰዎች ናቸው?

 መጽሐፍ ቅዱስ፣ 144,000 ሰዎች ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ይናገራል። (ራእይ 7:4) በራእይ 14:1-3 ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ “በጉ በጽዮን ተራራ ላይ [ቆሞ]” እንዳየ እንዲሁም ‘ከእሱ ጋር 144,000ዎቹ’ እንደነበሩ ተገልጿል። በዚህ ራእይ ላይ “በጉ” ትንሣኤ ያገኘውን ኢየሱስን ያመለክታል። (ዮሐንስ 1:29፤ 1 ጴጥሮስ 1:19) ‘የጽዮን ተራራ’ የሚለው አገላለጽ ደግሞ ኢየሱስና ከእሱ ጋር በሰማይ ላይ የሚገዙት 144,000 ሰዎች ያላቸውን ከፍ ያለ ቦታ ያመለክታል።—መዝሙር 2:6፤ ዕብራውያን 12:22

 በአምላክ መንግሥት ውስጥ ከክርስቶስ ጋር እንዲገዙ ‘የተጠሩትና የተመረጡት’ ሰዎች “ትንሽ መንጋ” ተብለው ተጠርተዋል። (ራእይ 17:14፤ ሉቃስ 12:32) ይህም የእነዚህ ሰዎች ቁጥር፣ ከኢየሱስ በጎች አጠቃላይ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ እንደሚሆን ያሳያል።—ዮሐንስ 10:16

ብዙዎች ወደ ሰማይ የሚሄዱትን በተመለከተ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ጥሩ ሰዎች በሙሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ።

 እውነታው፦ አምላክ ለአብዛኞቹ ጥሩ ሰዎች በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል።—መዝሙር 37:11, 29, 34

  •   ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ወደ ሰማይ የወጣ የለም።” (ዮሐንስ 3:13) ይህም ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በሞት ያንቀላፉ እንደ አብርሃም፣ ሙሴ፣ ኢዮብና ዳዊት ያሉ ጥሩ ሰዎች ወደ ሰማይ እንዳልሄዱ ያሳያል። (የሐዋርያት ሥራ 2:29, 34) የእነዚህ ሰዎች ተስፋ፣ ትንሣኤ አግኝተው በምድር ላይ መኖር ነው።—ኢዮብ 14:13-15

  •   ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች የሚያገኙት ትንሣኤ ‘የመጀመሪያው ትንሣኤ’ ተብሎ ተጠርቷል። (ራእይ 20:6) እንዲህ መባሉ፣ ሌላም ዓይነት ትንሣኤ እንደሚኖር ይጠቁማል። ይህም ከሞት ተነስተው በምድር ላይ የሚኖሩት ሰዎች የሚያገኙት ትንሣኤ ነው።

  •   መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ መንግሥት በሚገዛበት ወቅት ስለሚኖረው ሁኔታ ሲናገር “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም” ይላል። (ራእይ 21:3, 4) ይህ ተስፋ የሚፈጸመው በምድር ላይ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም በሰማይ ሞት ኖሮ አያውቅም።

 የተሳሳተ አመለካከት፦ እያንዳንዱ ሰው በሰማይ ወይም በምድር ላይ ለመኖር መምረጥ ይችላል።

 እውነታው፦ “የሰማያዊውን ሕይወት ሽልማት” ማለትም በሰማይ ላይ የመኖርን ተስፋ የሚያገኙት እነማን እንደሆኑ የሚወስነው አምላክ ነው። (ፊልጵስዩስ 3:14) አንድ ሰው ለዚህ ተስፋ መመረጡ፣ በግለሰቡ ፍላጎት ወይም ምኞት ላይ የተመካ አይደለም።—ማቴዎስ 20:20-23

 የተሳሳተ አመለካከት፦ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ፣ ወደ ሰማይ ለመሄድ ብቁ ላልሆኑ ሰዎች የሚሰጥና ዝቅተኛ ደረጃ ያለው ተስፋ ነው።

 እውነታው፦ አምላክ፣ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ የሚያገኙትን ሰዎች “ሕዝቤ፣” “የመረጥኳቸው አገልጋዮቼ” እንዲሁም “ይሖዋ የባረከው ዘር” በማለት ጠርቷቸዋል። (ኢሳይያስ 65:21-23) እነዚህ ሰዎች፣ አምላክ በመጀመሪያ ለሰው ልጆች በነበረው ዓላማ መሠረት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ፍጹማን ሆነው ለዘላለም የመኖር መብት ያገኛሉ።—ዘፍጥረት 1:28፤ መዝሙር 115:16፤ ኢሳይያስ 45:18

 የተሳሳተ አመለካከት፦ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው 144,000 የሚለው ቁጥር ቃል በቃል የሚወሰድ ሳይሆን ምሳሌያዊ ነው።

 እውነታው፦ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ምሳሌያዊ ትርጉም ያላቸው ቁጥሮች የሚገኙ ቢሆንም አንዳንዶቹ ቁጥሮች ግን ቃል በቃል የሚወሰዱ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ የራእይ መጽሐፍ ስለ “12ቱ የበጉ ሐዋርያት 12 ስሞች” ይናገራል። (ራእይ 21:14) በተመሳሳይም 144,000 የሚለው ቁጥር ቃል በቃል ሊወሰድ ይገባል ብለን እንድንደመድም የሚያደርጉንን ማስረጃዎች እንመልከት።

 ራእይ 7:4 ‘የታተሙት [ማለትም ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ማረጋገጫ የተሰጣቸው] ሰዎች ቁጥር 144,000’ እንደሆነ ይናገራል። በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ “አንድም ሰው ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሕዝብ” ተብሎ የተጠራ ሌላ ቡድን ተጠቅሷል። “እጅግ ብዙ ሕዝብ” የተባሉትንም አምላክ ከጥፋት ያድናቸዋል። (ራእይ 7:9, 10) እንግዲያው 144,000 የሚለው ቁጥር፣ ይህ ነው የማይባል ብዛት ያለውን የሰዎች ቡድን የሚያመለክት ምሳሌያዊ ቁጥር ከሆነ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ንጽጽር ትርጉም አልባ ይሆናል። a

 በተጨማሪም 144,000ዎቹ “እንደ በኩራት ሆነው ከሰዎች መካከል [እንደተዋጁ]” ተገልጿል። (ራእይ 14:4) “በኩራት” የሚለው አገላለጽ ሌሎችን እንዲወክሉ የተመረጡ ጥቂት ሰዎችን ያመለክታል። ይህ ቃል በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ሆነው፣ በምድር ላይ የሚኖሩ ቁጥራቸው ያልተወሰነ ተገዥዎችን የሚያስተዳድሩትን ነገሥታት የሚያመለክት ተስማሚ መግለጫ ነው።—ራእይ 5:10

a በተመሳሳይም ፕሮፌሰር ሮበርት ቶማስ በራእይ 7:4 ላይ የተጠቀሰውን 144,000 የሚለውን ቁጥር በተመለከተ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “በምዕራፍ 7 ቁጥር 9 ላይ ከሚገኘው ብዛቱ ያልተወሰነ ቁጥር በተለየ መልኩ ይህ ቁጥር [144,000] የተወሰነ ብዛትን ያመለክታል። ይህ ቁጥር ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ከተወሰደ [በራእይ] መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ የትኛውም ቁጥር ቃል በቃል ሊወሰድ አይችልም።”—ሬቨሌሽን 1-7: አን ኤክሴጄቲካል ኮሜንተሪ፣ ገጽ 474