በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኅዳር 17, 2020
ሞዛምቢክ

የማቴዎስ መጽሐፍ በጊቶንጋ እና በሮንጋ ቋንቋ ወጣ

የማቴዎስ መጽሐፍ በጊቶንጋ እና በሮንጋ ቋንቋ ወጣ

ኅዳር 14 እና 15, 2020 በኤሌክትሮኒክ ቅጂ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በደቡባዊ ሞዛምቢክ በሚነገሩ ሁለት ቋንቋዎች ማለትም በጊቶንጋ እና በሮንጋ ቋንቋ ወጣ። የጊቶንጋ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑት 524 አስፋፊዎችና የሮንጋ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑት 1,911 አስፋፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው ይህ መጽሐፍ በትክክለኛው ጊዜ ላይ ከይሖዋ የተሰጠ ስጦታ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል።

የሞዛምቢክ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም አማሮ ቴሼራ እነዚህ ትርጉሞች መውጣታቸውን አስቀድሞ በተቀዳ ንግግር አማካኝነት ያበሰረ ሲሆን አስፋፊዎችም ፕሮግራሙን ከቤታቸው ተከታትለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ወንድሞቻችን ይህን ፕሮግራም በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያና በአካባቢው ባሉ የተለያዩ የሬዲዮ ጣቢያዎች እንዲያስተላልፉ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል። አብዛኞቹ አንባቢዎች የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ስለሌላቸው የማቴዎስ መጽሐፍ ባለ 64 ገጽ ቡክሌት ሆኖ እንዲወጣም ይደረጋል።

ወንድም ቴሼራ እንዲህ ብሏል፦ “በእነዚህ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው። የማቴዎስ መጽሐፍን በማግኘታችን በጣም ተደስተናል፤ ምክንያቱም ይህ የወንጌል ዘገባ የኢየሱስን የዘር ሐረግና ትውልድ፣ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀውን የተራራ ስብከቱን እንዲሁም የመጨረሻዎቹን ቀናት አስመልክቶ የተናገረውን ትኩረት የሚስብ ትንቢት ይዟል።”

አንድ ተርጓሚ ይህ ትክክለኛና ለመረዳት ቀላል የሆነ ትርጉም መዘጋጀቱ ስላለው ጥቅም ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የማቴዎስ መጽሐፍ በጣም ብዙ ትምህርቶችን የያዘ መጽሐፍ ነው። አንባቢዎች የተራራውን ስብከት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲያነብቡ የደስታ እንባ ማንባታቸው እንደማይቀር ይሰማኛል።”

ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ 224,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ጊቶንጋ የሚናገሩ ሲሆን 423,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ሮንጋ ይናገራሉ። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ብዙዎች ‘ወደ ሕይወት የሚወስደውን መንገድ’ ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ትልቅ ድጋፍ እንደሚሆኗቸው ተስፋ እናደርጋለን።—ማቴዎስ 7:14