ነቅታችሁ ጠብቁ!
ፖለቲከኞች አርማጌዶን ሊመጣ እንደሆነ እያስጠነቀቁ ነው—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ጥቅምት 10, 2022 ጠዋት ላይ የሩሲያ ሚሳኤሎች በመላዋ ዩክሬን የሚገኙ ከተሞችን መቱ፤ ይህ የሆነው ከሁለት ቀናት በፊት ለተከሰተው ክራይሚያንና ሩሲያን በሚያገናኘው ወሳኝ ድልድይ ላይ ከባድ ጉዳት ያስከተለ ፍንዳታ የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት ነው። እነዚህ ክንውኖች የተፈጸሙት ፖለቲከኞች አርማጌዶን ሊመጣ እንደሚችል ካስጠነቀቁ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።
“[በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ] ኬኔዲ ዘመን ከተከሰተው የኩባ የሚሳኤል አደጋ ወዲህ ለአርማጌዶን የዚህን ያህል ተቃርበን አናውቅም። . . . የኑክሌር መሣሪያ ጥቅም ላይ ከዋለ አርማጌዶን መምጣቱ አይቀሬ እንደሆነ ይሰማኛል።”—የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ ጥቅምት 6, 2022
“ወደ አርማጌዶን እየተቃረብን እንደሆነ እስማማለሁ፤ መላዋ ፕላኔት አደጋ ተጋርጦባታል።”—የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ፣ የኑክሌር መሣሪያ መጠቀም ስለሚያስከትለው ውጤት በተጠየቁበት ወቅት፣ ቢቢሲ ዜና፣ ጥቅምት 8, 2022
የኑክሌር መሣሪያዎች ጥቅም ላይ መዋላቸው ወደ አርማጌዶን ይመራ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
የኑክሌር መሣሪያዎች አርማጌዶንን ያስጀምሩ ይሆን?
አያስጀምሩም። “አርማጌዶን” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው አንድ ቦታ ይኸውም ራእይ 16:16 ላይ ነው። ይህ ቃል የሚያመለክተው በብሔራት መካከል የሚካሄድን ጦርነት ሳይሆን በአምላክና ‘በዓለም ነገሥታት ሁሉ’ መካከል የሚካሄድን ጦርነት ነው። (ራእይ 16:14) አምላክ በአርማጌዶን ጦርነት አማካኝነት የሰዎችን አገዛዝ ያስወግዳል።—ዳንኤል 2:44
አርማጌዶን በምድር ላይ ምን እንደሚያስከትል ለማወቅ የአርማጌዶን ጦርነት ምንድን ነው? የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ምድርና በምድር ላይ ያሉ ሰዎች በኑክሌር ጦርነት ይጠፉ ይሆን?
አይጠፉም። መሪዎች ወደፊት የኑክሌር መሣሪያ ሊጠቀሙ የሚችሉ ቢሆንም አምላክ ምድር እንድትጠፋ አይፈቅድም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦
“ምድር . . . ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።”—መክብብ 1:4
“ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29
ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢትም ሆነ በዓለም ላይ የሚታዩት ሁኔታዎች በቅርቡ በሰው ዘር ታሪክ ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚመጣ ይጠቁማሉ። (ማቴዎስ 24:3-7፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ያዘጋጀነውን አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በነፃ በመውሰድ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን እንደሚል መማር ትችላለህ።