“ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል”
“ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል”
“ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው።”—ያዕቆብ 5:11
1, 2. በፖላንድ የሚገኙ አንድ ባልና ሚስት ምን ችግሮችን ተቋቁመዋል?
የሂትለር ወታደሮች በሰሜን ፖላንድ የምትገኘውን ዳንዚግን (አሁን ገዳንስክ ትባላለች) ሲቆጣጠሩ፣ ሃራልት አፕት የሚባለው ሰው የይሖዋ ምሥክር ከሆነ ገና ዓመት አልሞላውም ነበር። ሁኔታዎች በጣም እየከበዱ መጡ፤ አዎን፣ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች የሚያሰጉ ነገሮች መከሰት ጀመሩ። የናዚ ፖሊሶች ሃራልት እምነቱን እንደካደ በሚገልጽ ሰነድ ላይ እንዲፈርም ሊያስገድዱት ቢሞክሩም ፈቃደኛ አልሆነም። ጥቂት ሳምንታት እስር ቤት ከቆየ በኋላ፣ ተደጋጋሚ ዛቻና ድብደባ ወደደረሰበት ወደ ዛክሰንሃውዘን ማጎሪያ ካምፕ ተላከ። አንድ ባለ ሥልጣን የሬሳ ማቃጠያ ሕንጻውን ጭስ ማውጫ ለሃራልት እያሳየ “እምነትህን ካልተውክ በ14 ቀናት ውስጥ ወደ ይሖዋህ ታርጋለህ” አለው።
2 ሃራልት ሲታሰር ሚስቱ ኤልዘ የአሥር ወር ሴት ልጃቸውን ጡት ታጠባ ነበር። የሂትለር ፖሊሶች ግን እርሷንም አልተዉአትም። ብዙም ሳይቆይ ልጅዋን ተቀማችና ኦሽዊትዝ ወደሚገኘው የግድያ ካምፕ ተላከች። ሆኖም እርሷም ሆነች ሃራልት ከሞት ተርፈው ለበርካታ ዓመታት በሕይወት መቆየት ችለዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች እንዴት እንደጸኑ በይበልጥ ለማወቅ የሚያዝያ 15, 1980 መጠበቂያ ግንብን (እንግሊዝኛ) ማንበብ ትችላለህ። ሃራልት እንዲህ ብሎ ጽፏል:- “በአምላክ በማመኔ ምክንያት ከሕይወት ዘመኔ ውስጥ በድምሩ አሥራ አራቱን ዓመታት በማጎሪያ ካምፖችና በእስር ቤቶች ውስጥ አሳልፌያለሁ። ‘ባለቤትህ ይህንን ሁሉ ችግር እንድትወጣ ረድታሃለች?’ የሚል ጥያቄ ቀርቦልኝ ነበር። በእርግጥ ትረዳኝ ነበር! መጀመሪያም ቢሆን ፈጽሞ እምነቷን እንደማትክድ አውቅ ነበር፤ ይህን ማወቄም አበረታቶኛል። እምነቴን ክጄ መለቀቄን ከምትሰማ ይልቅ ሞቼ ቃሬዛ ላይ ብታየኝ እንደምትመርጥ አውቃለሁ። . . . ኤልዘ በጀርመን የማጎሪያ ካምፖች ውስጥ በነበረችባቸው ዓመታት የደረሱባትን በርካታ ችግሮች ተቋቁማለች።”
3, 4. (ሀ) ክርስቲያኖች እንዲጸኑ የእነማን ምሳሌ ማበረታቻ ሊሆናቸው ይችላል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ የኢዮብን ታሪክ እንድንመረምር የሚያሳስበን ለምንድን ነው?
3 በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች መናገር እንደሚችሉት በመከራ ውስጥ ማለፍ እንዲህ ቀላል አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉንም ክርስቲያኖች “በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያት የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ አድርጋችሁ ተመልከቱ” በማለት የሚመክረው ለዚህ ነው። (ያዕቆብ 5:10) ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ ብዙ የአምላክ አገልጋዮች ያለምክንያት ሲሰደዱ ኖረዋል። የእነዚህ እንደ ታላቅ ‘ደመና ያሉ ምስክሮች’ ምሳሌነት ክርስቲያናዊ ሩጫችንን በጽናት መሮጣችንን እንድንቀጥል ያበረታታናል።—ዕብራውያን 11:32-38፤ 12:1
4 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጽናትን በተመለከተ ኢዮብ እንደ ናሙና ተደርጎ ተገልጿል። ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ፤ ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው።” (ያዕቆብ 5:11) የኢዮብ ታሪክ፣ ይሖዋ የባረካቸው ታማኞች ምን ዓይነት ሽልማት እንደሚያገኙ በጥቂቱ ፍንጭ ይሰጠናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ መከራ በሚያጋጥመን ጊዜ ሊጠቅመን የሚችል እውነታም ይዟል። የኢዮብ መጽሐፍ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመለስ እንድንችል ይረዳናል:- መከራ በሚደርስብን ጊዜ ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ዋነኞቹን አከራካሪ ጥያቄዎች ለመረዳት መሞከር ያለብን ለምንድን ነው? ለመጽናት የሚረዳን እንዴት ያለ ባሕርይና አመለካከት ነው? መከራ የሚደርስባቸውን የእምነት ባልንጀሮቻችንን ማበረታታት የምንችለው እንዴት ነው?
አጠቃላይ ሁኔታውን መገንዘብ
5. መከራ ወይም ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመን በአእምሯችን መያዝ ያለብን የትኛውን ዋነኛ ጉዳይ ነው?
5 መከራ በሚያጋጥመን ጊዜ መንፈሳዊ ሚዛናችንን ለመጠበቅ እንድንችል ሁኔታውን በጠቅላላ መገንዘብ አለብን። እንዲህ ካላደረግን የግል ችግሮቻችን መንፈሳዊ እይታችንን ሊጋርዱብን ይችላሉ። ልብ ልንለው የሚገባን ዋነኛ ጉዳይ ለአምላክ ታማኝ መሆናችን ነው። በሰማይ የሚኖረው አባታችን “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” በማለት ሁላችንም ልብ ልንለው የሚገባ ሐሳብ አቅርቦልናል። (ምሳሌ 27:11 የ1954 ትርጉም) ይህ እንዴት ያለ ልዩ መብት ነው! ድክመትና ኃጢአት ቢኖርብንም ፈጣሪያችንን ማስደሰት እንችላለን። እንዲህ የምናደርገው ለይሖዋ ባለን ፍቅር ተነሳስተን መከራዎችንና ፈተናዎችን ስንቋቋም ነው። እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅር ሁልጊዜ ጸንቶ ይቆማል። ከቶም አይወድቅም።—1 ቆሮንቶስ 13:7, 8
6. ሰይጣን ይሖዋን የሚሳደበው እንዴት ነው? ስድቡስ ምን ያህል ስፋት አለው?
6 የኢዮብ መጽሐፍ ይሖዋን የሚሳደበው ሰይጣን እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። እንዲሁም የዚህን የማይታይ ጠላት ክፉ ባሕርይና ከአምላክ ጋር ያለንን ወዳጅነት ለማበላሸት ያለውን ምኞት ይገልጻል። በኢዮብ ታሪክ ላይ እንደታየው ሰይጣን ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች አምላክን የሚያገለግሉት በራስ ወዳድነት ተነሳስተው ነው ብሎ ይከስሳል፤ እንዲሁም ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ሊቀዘቅዝ እንደሚችል ማረጋገጥ ይፈልጋል። ሰይጣን ላለፉት በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት አምላክን ሲሳደብ ኖሯል። ከሰማይ በተወረወረበት ወቅት እርሱ “የወንድሞቻችን ከሳሽ” እንደሆነ የሚገልጽ ድምጽ ከሰማይ የተሰማ ሲሆን እንዲህ ያሉትን ክሶች “ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት” እንደሚያቀርብ ተነግሯል። (ራእይ 12:10) እኛም በታማኝነት በመጽናት ክሶቹ መሠረተ ቢስ እንደሆኑ ማሳየት እንችላለን።
7. አካላዊ ድካምን በተሻለ መንገድ መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
7 ዲያብሎስ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም መከራ እኛን ከይሖዋ ለማራቅ እንደሚጠቀምበት ማስታወስ አለብን። ሰይጣን ኢየሱስን የፈተነው መቼ ነበር? ኢየሱስ ለበርካታ ቀናት ጾሞ በተራበበት ጊዜ ነው። (ሉቃስ 4:1-3) ነገር ግን ኢየሱስ የነበረው መንፈሳዊ ጥንካሬ ዲያብሎስ ባቀረበለት ፈተና ፈጽሞ እንዳይሸነፍ ረድቶታል። በሕመም ወይም በዕድሜ መግፋት ምክንያት ሊያጋጥም የሚችልን ማንኛውንም አካላዊ ድካም በመንፈሳዊ ጠንካራ በመሆን መቋቋም ምንኛ አስፈላጊ ነው! “ውጫዊው ሰውነታችን እየጠፋ ቢሄድም” እንኳን ‘ውስጣዊው ሰውነታችን ዕለት ዕለት ስለሚታደስ’ ተስፋ አንቆርጥም።—2 ቆሮንቶስ 4:16
8. (ሀ) አሉታዊ አመለካከቶች ጎጂ ውጤት ሊኖራቸው የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ምን ዓይነት አስተሳሰብ ነበረው?
8 በተጨማሪም አሉታዊ አመለካከት መንፈሳዊ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። አንድ ሰው ‘ይሖዋ ለምን ይህ እንዲሆን ፈቀደ?’ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል። ሌላው ደግሞ የማይገባ ነገር ሲደረግበት ‘ወንድም እንዴት እንዲህ ያደርግብኛል?’ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። እንዲህ ያሉት ስሜቶች ዋነኞቹን አከራካሪ ጥያቄዎች ችላ እንድንልና ሙሉ በሙሉ በግል ሁኔታዎቻችን ላይ እንድናተኩር ያደርጉናል። የሦስቱ አሳሳች ጓደኞቹ ሁኔታ ኢዮብን ጤና ማጣት ካስከተለበት አካላዊ ጉዳት ጋር የሚተካከል የስሜት ጉዳት ሳያስከትልበት አልቀረም። (ኢዮብ 16:20፤ 19:2) በተመሳሳይም ተቆጥቶ ለረጅም ጊዜ መቆየት ‘ለዲያብሎስ ስፍራ’ ወይም አጋጣሚ ሊሰጠው እንደሚችል ሐዋርያው ጳውሎስ ገልጿል። (ኤፌሶን 4:26, 27) ክርስቲያኖች ብስጭታቸውንና ንዴታቸውን በግለሰቦች ላይ ከመወጣት ወይም ደግሞ በተፈጸመው የፍትሕ መጓደል ላይ ከልክ በላይ ከማተኮር ይልቅ “በጽድቅ ለሚፈርደው” ለይሖዋ አምላክ ‘ራሳቸውን አሳልፈው’ በመስጠት ረገድ ኢየሱስን ቢኮርጁ የበለጠ ይጠቀማሉ። (1 ጴጥሮስ 2:21-23) የኢየሱስን ዓይነት “አሳብ” መያዝ የሰይጣን ጥቃቶች ዋነኛ መከላከያ ሊሆን ይችላል።—1 ጴጥሮስ 4:1 የ1954 ትርጉም
9. አምላክ የሚያጋጥመንን ሸክም ወይም ፈተና በተመለከተ ምን ማረጋገጫ ሰጥቶናል?
9 ከሁሉም በላይ ችግሮቻችንን አምላክ እንዳልተደሰተብን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች እንደሆኑ አድርገን ማየት የለብንም። ኢዮብ ይህን የመሰለ የተሳሳተ ግንዛቤ መያዙ አጽናኝ ተብዬዎቹ በሻካራ ቃላት ባዋከቡት ጊዜ እንዲጎዳ አድርጎታል። (ኢዮብ 19:21, 22) መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንም፤ እርሱም ማንንም አይፈትንም” በማለት ያረጋግጥልናል። (ያዕቆብ 1:13) በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ ምንም ዓይነት ሸክም ቢጫንብን እንድንችለው እንደሚረዳን እንዲሁም ያጋጠመንን ፈተና የምንወጣበትን መንገድ እንደሚያዘጋጅልን ቃል ገብቶልናል። (መዝሙር 55:22፤ 1 ቆሮንቶስ 10:13) በችግር ጊዜ ወደ አምላክ ይበልጥ በመቅረብ ለነገሮች ተገቢ የሆነ አመለካከት መያዝና ዲያብሎስን በሚገባ መቃወም እንችላለን።—ያዕቆብ 4:7, 8
ለመጽናት የሚረዳ እገዛ
10, 11. (ሀ) ኢዮብ እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? (ለ) ኢዮብ ንጹሕ ሕሊና ያለው መሆኑ የረዳው እንዴት ነው?
10 ኢዮብ ‘አጽናኞቹ’ ይሰነዝሯቸው የነበሩትን መጥፎ ቃላት ጨምሮ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም እንዲሁም የችግሩ እውነተኛ መንስኤ ምን እንደሆነ ግራ ቢገባውም ንጹሕ አቋሙን ጠብቋል። ከኢዮብ ጽናት ምን ትምህርት እናገኛለን? ስኬታማ እንዲሆን ያስቻለው መሠረታዊ ነገር ለይሖዋ ያለው ታማኝነት እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ኢዮብ “እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ነበር።” (ኢዮብ 1:1) በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እንዲህ ዓይነት አቋም ይዟል። ኢዮብ ነገሮች በድንገት የተበላሹበትን ምክንያት በማያውቅበት ጊዜም እንኳን ለይሖዋ ጀርባውን ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበረም። አምላክን ማገልገል ያለበት በጥሩም ሆነ በመጥፎ ጊዜ እንደሆነ ያምን ነበር።—ኢዮብ 1:21፤ 2:10
11 ኢዮብ ጥሩ ሕሊና ያለው መሆኑም የመጽናናት ምንጭ ሆኖለታል። ሌሎችን ለመርዳት የተቻለውን ሁሉ እንዳደረገ፣ የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች እንደጠበቀና ከማንኛውም ዓይነት የሐሰት ሃይማኖት እንደራቀ ማወቁ ለሞት የተቃረበ በመሰለበት ጊዜ ላይ አጽናንቶታል።—ኢዮብ 31:4-11
12. ኢዮብ ኤሊሁ ላደረገለት እርዳታ የሰጠው ምላሽ ምን ነበር?
12 ኢዮብ በአንዳንድ ጉዳዮች ረገድ አመለካከቱን ለማስተካከል እርዳታ አስፈልጎት እንደነበር እሙን ነው። እርሱም ቢሆን የተሰጠውን እርዳታ በትሕትና ተቀብሏል፤ ይህም በሚገባ እንዲጸና የረዳው አንዱ ቁልፍ ነው። ኢዮብ ኤሊሁ የሰጠውን ጥበብ ያዘለ ምክር በአክብሮት አዳምጧል፤ እንዲሁም ከይሖዋ ላገኘው እርማት አዎንታዊ ምላሽ ሰጥቷል። “ያልገባኝን ነገር . . . ተናገርሁ። . . . ራሴን እንቃለሁ፤ በትቢያና በዐመድ ላይ ተቀምጬ ንስሓ እገባለሁ” በማለት ሐቁን ተናግሯል። (ኢዮብ 42:3, 6) ኢዮብ ገና ከበሽታው ባልዳነበት ጊዜም እንኳን አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል የተሰጠው እርማት ከአምላክ ጋር ይበልጥ ስላቀራረበው ተደስቷል። “አንተ [ይሖዋ] ሁሉን ማድረግ እንደምትችል . . . ዐወቅሁ” ብሏል። (ኢዮብ 42:2) ይሖዋ ራሱ ምን ያህል ታላቅ አምላክ እንደሆነ ስለ ገለጸለት ኢዮብ ከፈጣሪ ጋር ሲነጻጸር ቦታው ምን እንደሆነ ይበልጥ ግልጽ ሆኖለታል።
13. መሐሪ መሆን ኢዮብን የጠቀመው እንዴት ነው?
13 በመጨረሻም፣ ኢዮብ ምሕረት በማሳየት ረገድ ትልቅ ምሳሌ ትቷል። የሐሰት አጽናኞቹ ኢዮብን ክፉኛ ቢጎዱትም እንዲጸልይላቸው ይሖዋ በነገረው ጊዜ የተባለውን አድርጓል። ከዚያ በኋላ ይሖዋ የኢዮብን ጤና መልሶለታል። (ኢዮብ 42:8, 10) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ፍቅርና ምሕረት እንድንጸና የሚረዱን ሲሆን ቂም መያዝ ግን ምንም ጥቅም የለውም። ቂም የማንይዝ መሆናችን በመንፈሳዊ እንድንታደስ የሚያደርገን ከመሆኑም በላይ የይሖዋን በረከት ያስገኝልናል።—ማርቆስ 11:25
እንድንጸና የሚረዱን ጥበበኛ መካሪዎች
14, 15. (ሀ) ምክር የሚሰጥ ሰው ሌሎችን ለመፈወስ የሚያስችሉት የትኞቹ ባሕርያት ናቸው? (ለ) ኤሊሁ ኢዮብን በመርዳት ረገድ የተሳካለት ለምን እንደሆነ አብራራ።
14 ከኢዮብ ታሪክ የምንማረው ሌላው ነገር ደግሞ ጥበበኛ መካሪዎች ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ ነው። እነዚህ መካሪዎች ‘ለክፉ ቀን የተወለዱ’ ወንድሞች ያህል ናቸው። (ምሳሌ 17:17) ነገር ግን አንዳንድ መካሪዎች ከመፈወስ ይልቅ ጉዳት ሊያደርሱ እንደሚችሉ የኢዮብ ታሪክ ያሳያል። ጥሩ መካሪ ልክ እንደ ኤሊሁ አዘኔታ፣ አክብሮትና ደግነት ማሳየት አለበት። ሽማግሌዎችና ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች በችግሮች ምክንያት ሸክም የከበደባቸውን ወንድሞች አስተሳሰብ ማስተካከል ሊኖርባቸው ይችላል፤ ምክር የሚሰጡ ወንድሞች የሌሎችን አስተሳሰብ በማስተካከል ረገድ ከኢዮብ መጽሐፍ ብዙ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ።—ገላትያ 6:1፤ ዕብራውያን 12:12, 13
15 ኤሊሁ ጉዳዩን ከያዘበት መንገድ በርካታ ጠቃሚ ትምህርቶችን እናገኛለን። የኢዮብ ሦስት ጓደኞች ለሰነዘሩት የተሳሳተ አስተያየት መልስ ከመስጠቱ በፊት በትዕግሥት አዳምጧል። (ኢዮብ 32:11፤ ምሳሌ 18:13) ኤሊሁ ሲናገር የኢዮብን ስም ይጠራ የነበረ ሲሆን እንደ ወዳጅ ሆኖ ቀርቦታል። (ኢዮብ 33:1) ኤሊሁ እንደ ሦስቱ የሐሰት አጽናኞች ከኢዮብ እንደሚበልጥ አድርጎ አላሰበም። “የተፈጠርሁትም ደግሞ ከዐፈር ነው” ብሏል። አሳቢነት የጎደላቸው ቃላት በመናገር በኢዮብ ላይ መከራ መጨመር አልፈለገም። (ኢዮብ 33:6, 7፤ ምሳሌ 12:18) ኤሊሁ፣ የቀድሞ ባሕርዩን እያነሳ ኢዮብን ከመኮነን ይልቅ ለጻድቅነቱ አመስግኖታል። (ኢዮብ 33:32 NW) በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር ኤሊሁ ነገሮችን የሚያየው ከይሖዋ አመለካከት አንጻር የነበረ መሆኑ ነው፤ እንዲሁም ኢዮብን ይሖዋ ፍትሐዊ ያልሆነ ነገር የማያደርግ በመሆኑ ሐቅ ላይ እንዲያተኩር ረድቶታል። (ኢዮብ 34:10-12) ኢዮብ ጻድቅነቱን ለማሳየት ከመጣጣር ይልቅ ይሖዋን እንዲጠብቅ አበረታቶታል። (ኢዮብ 35:2፤ 37:14, 23) የጉባኤ ሽማግሌዎችና ሌሎችም እንዲህ ካለው ትምህርት በእርግጥ ጥቅም ማግኘት ይችላሉ።
16. ሦስቱ የኢዮብ የሐሰት አጽናኞች የሰይጣን መሣሪያ የሆኑት እንዴት ነው?
16 ኤሊሁ የሰጠው ጥበብ ያለበት ምክር ኤልፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር ከተናገሯቸው ጎጂ ቃላት ተቃራኒ ነበር። ይሖዋ ‘ስለ እኔ ቅን ነገር አልተናገራችሁም’ ብሏቸዋል። (ኢዮብ 42:7) በጎ ዓላማ እንዳላቸው ቢናገሩም ድርጊታቸው የሰይጣን መሣሪያዎች እንጂ ታማኝ ወዳጆች እንደሆኑ የሚያሳይ አልነበረም። ሦስቱም ገና ከጅምሩ ኢዮብ ለደረሰበት ችግር ተጠያቂው እርሱ ራሱ እንደሆነ አድርገው ገምተው ነበር። (ኢዮብ 4:7, 8፤ 8:6፤ 20:22, 29) የኤልፋዝ ንግግር አምላክ በአገልጋዮቹ አይተማመንም እንዲሁም ጻድቅ ሆንም አልሆን እርሱን አይገደውም የሚል አንድምታ አለው። (ኢዮብ 15:15፤ 22:2, 3) እንዲያውም ኢዮብን ባልሠራቸው ስህተቶች ጭምር ከሶታል። (ኢዮብ 22:5, 9) በሌላ በኩል ደግሞ ኤሊሁ ኢዮብን በመንፈሳዊ ረድቶታል፤ ይህ ደግሞ አፍቃሪ መካሪ ምንጊዜም ሊኖረው የሚገባ ግብ ነው።
17. መከራ በሚያጋጥመን ጊዜ በአእምሯችን ምን መያዝ አለብን?
17 ጽናትን በተመለከተ ከኢዮብ መጽሐፍ ሌላም ትምህርት ማግኘት እንችላለን። አፍቃሪው አምላካችን ያለንበትን ሁኔታ ይመለከታል፤ እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች ሊረዳን ፈቃደኛ ከመሆኑም በላይ ችሎታውም አለው። ቀደም ሲል የኤልዘ አፕትን ተሞክሮ አይተን ነበር። የደረሰችበትን መደምደሚያ በማስታወስ እንዲህ ብላለች:- “ከመታሰሬ በፊት፣ ከባድ መከራ ሲደርስብን የይሖዋ መንፈስ መረጋጋት እንደሚሰጠን የሚገልጽ አንዲት እህት የጻፈችውን ደብዳቤ አንብቤ ነበር። በወቅቱ ትንሽ አጋንና መሆን አለበት የሚል ስሜት አድሮብኝ ነበር። ሆኖም በራሴ ላይ ችግሮች ሲደርሱብኝ እህት ተናግራ የነበረው ነገር እውነት መሆኑን አወቅኩ። የሆነውም ልክ እንዳለችው ነው። ካልደረሰባችሁ በስተቀር ሁኔታውን ለመገመት በጣም ያስቸግራል። እኔ ግን በትክክል አጋጥሞኛል። ይሖዋ ይረዳል።” ኤልዘ የተናገረችው ይሖዋ ማድረግ ስለሚችለው ነገር ወይም ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት በኢዮብ ዘመን ስላደረገው ነገር አይደለም። የተናገረችው ስለ ዘመናችን ነው። አዎን፣ “ይሖዋ ይረዳል”!
የሚጸና ሰው ደስተኛ ነው
18. ኢዮብ መጽናቱ ምን ጥቅሞችን አስገኝቶለታል?
18 አንዳንዶቻችን እንደ ኢዮብ ከባድ መከራ ሊያጋጥመን ይችላል። ነገር ግን ይህ ሥርዓት ምንም ዓይነት መከራዎችን ቢያመጣብን ኢዮብ እንዳደረገው ጽኑ አቋማችንን የምንጠብቅባቸው በቂ ምክንያቶች አሉን። እንዲያውም ጽናት ኢዮብን በእጅጉ ረድቶታል። ፍጹምና ሙሉ እንዲሆን አድርጎታል። (ያዕቆብ 1:2-4) ከአምላክ ጋር ያለውንም ወዳጅነት አጠንክሮለታል። ኢዮብ “ጆሮዬ ስለ አንተ ሰምታ ነበር፤ አሁን ግን ዐይኔ አየችህ” በማለት አረጋግጧል። (ኢዮብ 42:5) ሰይጣን፣ ኢዮብ ጽኑ አቋሙን እንዲያበላሽ ማድረግ ስላልቻለ ሐሰተኛ መሆኑ ተረጋግጧል። ይሖዋ በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላም እንኳን አገልጋዩን ኢዮብን የጽድቅ ምሳሌ አድርጎ ጠቅሶታል። (ሕዝቅኤል 14:14) ያሳየው የታማኝነትና የጽናት ምሳሌ በዛሬው ጊዜ ያሉትን የአምላክ ሕዝቦች ሳይቀር ያነቃቃል።
19. መጽናት ጥቅም እንዳለው የሚሰማህ ለምንድን ነው?
19 ያዕቆብ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ክርስቲያኖች ጽናትን በተመለከተ በጻፈላቸው ጊዜ መጽናት ስለሚያስገኘው እርካታ ጠቅሶላቸዋል። እንዲሁም ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን አብዝቶ እንደሚባርካቸው ለማሳሰብ የኢዮብን ምሳሌ ተጠቅሟል። (ያዕቆብ 5:11) ኢዮብ 42:12 “እግዚአብሔርም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን የኢዮብን ሕይወት ባረከ” በማለት ይናገራል። አምላክ ኢዮብ አጥቶት የነበረውን ንብረት እጥፍ አድርጎ የመለሰለት ከመሆኑም በላይ ረጅም ዕድሜና አስደሳች ሕይወት ሰጥቶታል። (ኢዮብ 42:16, 17) እኛም በተመሳሳይ በዚህ ሥርዓት መጨረሻ ላይ ማንኛውም ዓይነት ሕመም፣ ሥቃይ ወይም ሐዘን ቢደርስብን በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚወገድና የሚረሳ ነገር ነው። (ኢሳይያስ 65:17፤ ራእይ 21:4) ስለ ኢዮብ ጽናት ሰምተናል፤ በይሖዋ እርዳታም የእርሱን ምሳሌ ለመኮረጅ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ተስፋ ይሰጣል:- “በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ምክንያቱም ፈተናን ሲቋቋም እግዚአብሔር ለሚወዱት የሰጠውን ተስፋ፣ የሕይወትን አክሊል ያገኛል።”—ያዕቆብ 1:12
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• የይሖዋን ልብ ደስ ማሰኘት የምንችለው እንዴት ነው?
• ችግሮች የደረሱብን አምላክ ስላልተደሰተብን ነው ብለን መደምደም የሌለብን ለምንድን ነው?
• ኢዮብ እንዲጸና የረዱት ነገሮች ምንድን ናቸው?
• የእምነት ባልንጀሮቻችንን በማበረታታት ረገድ ኤሊሁን መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥሩ መካሪ አዘኔታ፣ አክብሮትና ደግነት ያሳያል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤልዘ እና ሃራልት አፕት