በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ”

“ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ”

“ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ”

“ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል።”​—⁠ያዕቆብ 4:8

1, 2. (ሀ) አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ምን ብለው ይናገራሉ? (ለ) ያዕቆብ ምን ምክር ሰጥቷል? ምክሩስ አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?

 “አምላክ ከእኛ ጋር ነው” የሚሉት ቃላት በብሔራዊ ባንዲራዎች ላይ አልፎ ተርፎም በወታደሮች የደንብ ልብስ ላይ ተጽፈው ይታያሉ። “በአምላክ እንታመናለን” የሚሉት ቃላት በዚህ ዘመን በሚሠራባቸው ቁጥር ስፍር በሌላቸው ሳንቲሞችና የብር ኖቶች ላይ ታትመዋል። ብዙ ሰዎች ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዳላቸው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ስላሉ ወይም ከላይ እንደተጠቀሱት ያሉትን ጥቅሶች በየቦታው ስለ ለጠፉ ብቻ ከአምላክ ጋር ዝምድና ሊኖራቸው የሚችል ይመስልሃል?

2 መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ ጋር ዝምድና መመሥረት እንደሚቻል ይገልጻል። ይሁንና ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንኳ ከይሖዋ አምላክ ጋር የመሠረቱትን ዝምድና ማጠናከር አስፈልጓቸው ነበር። ክርስቲያን የበላይ ተመልካች የነበረው ያዕቆብ አንዳንዶች ሥጋዊ አስተሳሰብ የነበራቸው በመሆኑና መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን ሳይጠብቁ በመቅረታቸው ማስጠንቀቂያ መስጠት አስፈልጎታል። በሰጣቸው ምክር ውስጥ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” የሚል ብርቱ ማሳሰቢያ ይገኝበታል። (ያዕቆብ 4:​1-12) ያዕቆብ “ቅረቡ” ሲል ምን ማለቱ ነበር?

3, 4. (ሀ) “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ” የሚለው የያዕቆብ ማሳሰቢያ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ አንባቢዎችን ምን አስታውሷቸው ሊሆን ይችላል? (ለ) ወደ አምላክ መቅረብ እንደሚቻል እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

3 ያዕቆብ እዚህ ላይ የተጠቀመበት አገላለጽ ለአብዛኛው አንባቢ እንግዳ አልነበረም። የሙሴ ሕግ ካህናቱ ሕዝቡን ወክለው ወደ ይሖዋ ‘በሚቀርቡበት ጊዜ’ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያ ይዟል። (ዘጸአት 19:​22) በመሆኑም የያዕቆብን መልእክት የሚያነብቡ ሰዎች ወደ ይሖዋ የመቅረብን ጉዳይ አቅልለው እንዳይመለከቱት ሳያስታውሳቸው አልቀረም። ይሖዋ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የመጨረሻውን ከፍተኛ ሥልጣን የያዘ አካል ነው።

4 በሌላ በኩል አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር “[በያዕቆብ 4:​8] ላይ የሚገኘው ጥብቅ ምክር በከፍተኛ ደረጃ አዎንታዊ አመለካከት ይንጸባረቅበታል” ብለዋል። ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን ፍጽምና የሚጎድላቸው ሰዎች ወደ እሱ እንዲቀርቡ በፍቅር ተነሳስቶ ጥሪ ያቀርብላቸው እንደነበር ያዕቆብ ያውቃል። (2 ዜና መዋዕል 15:​2) የኢየሱስ መሥዋዕት ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ የሚቻልበትን መንገድ ከፍቷል። (ኤፌሶን 3:​11, 12) በዛሬው ጊዜ ወደ አምላክ መቅረብ የሚቻልበት መንገድ በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ክፍት ነው! ይሁንና በዚህ ግሩም አጋጣሚ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? ወደ ይሖዋ አምላክ መቅረብ የምንችልባቸውን ሦስት መንገዶች በአጭሩ እንመረምራለን።

ስለ አምላክ ‘እውቀት መቅሰማችሁን’ ቀጥሉ

5, 6. የወጣቱ ሳሙኤል ምሳሌ ስለ አምላክ ‘እውቀት መቅሰምን’ በተመለከተ ምን ትምህርት ይሰጠናል?

5 ኢየሱስ በዮሐንስ 17:​3 ላይ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት ተናግሯል። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ጥቅስ የተረጎሙበት መንገድ ከአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በመጠኑ የተለየ ነው። ስለ አምላክ “እውቀት መቅሰም [NW ]” ከማለት ይልቅ አምላክን “ማወቅ” የሚለውን ግስ ተጠቅመዋል። ይሁን እንጂ በርካታ ምሁራን መጀመሪያ የተሠራበት የግሪክኛ ቃል ከዚያ የበለጠ ስፋት ያለው ሐሳብ እንደሚያስተላልፍ ተናግረዋል። ይህም ከሌላው ወገን ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ወደመመሥረት ሊያደርስ የሚችል ቀጣይነት ያለውን ሂደት የሚያመለክት ነው።

6 አምላክን በቅርብ ማወቅ ኢየሱስ ያመጣው አዲስ ሐሳብ አልነበረም። ለምሳሌ ያህል በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሳሙኤል ልጅ እያለ “እግዚአብሔርን አላወቀም ነበር” የሚል ሐሳብ እናገኛለን። (1 ሳሙኤል 3:​7) እንዲህ ሲባል ታዲያ ሳሙኤል ስለ አምላኩ የነበረው እውቀት በጣም ውስን ነበር ማለት ነው? አይደለም። ወላጆቹና ካህናቱ ስለ አምላክ ብዙ ነገር አስተምረውት እንደሚሆን የታወቀ ነው። ሆኖም አንድ ምሁር እንደተናገሩት በዚህ ጥቅስ ላይ የገባውን የዕብራይስጥ ቃል “በጣም የቀረበ ትውውቅ ላላቸው ወዳጆችም መጠቀም” ይቻላል። ሳሙኤል የይሖዋ ቃል አቀባይ ሆኖ ባገለገለበት ወቅት ይሖዋን ከበፊቱ በበለጠ በቅርብ ሊያውቀው ችሏል። ሳሙኤል እያደገ ሲሄድ ይሖዋን ይበልጥ በማወቁ ከእሱ ጋር የጠበቀ የግል ዝምድና መመሥረት ችሏል።​—⁠1 ሳሙኤል 3:​19, 20

7, 8. (ሀ) ጥልቀት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ከማጥናት ወደኋላ ማለት የማይኖርብን ለምንድን ነው? (ለ) የአምላክ ቃል የያዛቸው ልናጠናቸው የሚገቡ አንዳንድ ጥልቀት ያላቸው ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው?

7 አንተስ ይሖዋን በቅርብ ለማወቅ የሚያስችልህን እውቀት እየቀሰምክ ነው? እንዲህ ለማድረግ አምላክ ለሚያቀርበው መንፈሳዊ ምግብ ‘ምኞት’ ማሳደር ይኖርብሃል። (1 ጴጥሮስ 2:​2) የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረተ ትምህርቶች ማወቅህ ብቻውን በቂ አይደለም። ጥልቀት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ለማወቅ ጥረት አድርግ። (ዕብራውያን 5:​12-14) እንደዚህ ዓይነት ትምህርቶች ለመረዳት ይከብዳሉ በማለት ፈርተህ ትተዋቸዋለህ? ከሆነ ይሖዋ ‘ታላቅ አስተማሪ’ መሆኑን አትዘንጋ። (ኢሳይያስ 30:​20) ፍጽምና ለሚጎድላቸው ሰዎች ጥልቀት ያላቸው ትምህርቶችን እንዴት ማስተማር እንዳለበት ያውቃል። እንዲሁም የሚሰጥህን ትምህርት ለመረዳት ከልብ የምታደርገውን ጥረት ሊባርክልህ ይችላል።​—⁠መዝሙር 25:​4

8 “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር” በተመለከተ ምን አመለካከት እንዳለህ ለማወቅ ለምን ራስህን አትመረምርም? (1 ቆሮንቶስ 2:​10) እነዚህ ጉዳዮች የሃይማኖት ምሁራንና ቀሳውስት ዘወትር እያነሱ የሚነጋገሩባቸው ዓይነት አሰልቺ ርዕሶች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ስለ አፍቃሪው አባታችን በጣም ማራኪ እውቀት የምንቀስምባቸው ጠቃሚ መሠረተ ትምህርቶች ናቸው። ለምሳሌ ያህል ቤዛው፣ ይሖዋ የገለጠው ቅዱስ “ምሥጢር” እና ይሖዋ ሕዝቡን ለመባረክና ዓላማዎቹን ከግብ ለማድረስ ከሰዎች ጋር የገባቸው የተለያዩ ቃል ኪዳኖች እንዲሁም እነዚህን የመሳሰሉ በርካታ ርዕሶች በግል ምርምርና ጥናት ማድረግ የምንችልባቸው አስደሳችና የሚክሱ ርዕሶች ናቸው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 2:​7 አ.መ.ት 

9, 10. (ሀ) ኩራት መጥፎ ባሕርይ ነው የሚባለው ለምንድን ነው? ኩራትን እንድናስወግድስ ምን ይረዳናል? (ለ) ይሖዋ ማለቂያ የሌለው እውቀት እንዳለው ማወቃችን ትሑት እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

9 ጥልቀት ስላላቸው መንፈሳዊ ትምህርቶች ያለህ እውቀት እያደገ በሄደ መጠን ብዙ አውቃለሁ በሚል ኩራት እንዳያድርብህ ተጠንቀቅ። (1 ቆሮንቶስ 8:​1) ኩራት ሰዎችን ከአምላክ የሚያርቅ መጥፎ ባሕርይ ነው። (ምሳሌ 16:​5፤ ያዕቆብ 4:​6) ማንኛውም ሰው ቢሆን በእውቀቱ የሚኩራራበት ምክንያት እንደሌለ አስታውስ። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል የሰው ልጅ በቅርቡ ስላገኘው ሳይንሳዊ እድገት የሚያትት አንድ መጽሐፍ በመግቢያው ላይ ያሰፈረውን ሐሳብ ተመልከት:- “ብዙ ባወቅን መጠን እውቀታችን ምን ያህል ቁንጽል እንደሆነ እንገነዘባለን። . . . እስካሁን ያካበትነውን እውቀት ወደፊት ከምንማረው ጋር ስናስተያየው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።” እንዲህ ዓይነቱ የትሕትና ባሕርይ ያስደስታል። እኛ ያለንን ኢምንት የሆነ እውቀት ይሖዋ አምላክ ካለው ማለቂያ የሌለው እውቀት ጋር ስናነጻጽር ደግሞ የበለጠ ትሑት መሆን እንዳለብን እንዲሰማን ያደርጋል። ለምን?

10 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ የሚናገራቸውን አንዳንድ ሐሳቦች ተመልከት። ‘አሳብህ እጅግ ጥልቅ ነው።’ (መዝሙር 92:​5) ይሖዋ ‘ለጥበቡ ቁጥር የለውም።’ (መዝሙር 147:​5) የይሖዋ ‘ማስተዋል አይመረመርም።’ (ኢሳይያስ 40:​28) “የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው።” (ሮሜ 11:​33) ስለ ይሖዋ ማወቅ የሚቻለውን ሁሉ አውቀን መጨረስ እንደማንችል ግልጽ ነው። (መክብብ 3:​11) አስደናቂ የሆኑ ብዙ ነገሮችን አስተምሮናል። ሆኖም መቼም ቢሆን እውቀት የምንቀስምበት ማለቂያ የሌለው የእውቀት ክምችት አለ። ይህን ማወቃችን አስደሳችና ራሳችንን ዝቅ እንድናደርግ የሚያስገድድ ሐቅ አይደለም? በመሆኑም በእውቀት እያደግን በሄድን መጠን እውቀታችንን ራሳችንን ከፍ ከፍ ለማድረግ ሳይሆን ወደ ይሖዋ ለመቅረብና ሌሎችም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ለመርዳት ልንጠቀምበት ይገባናል።​—⁠ማቴዎስ 23:​12፤ ሉቃስ 9:​48

ለይሖዋ ያለህን ፍቅር በተግባር አሳይ

11, 12. (ሀ) ስለ ይሖዋ የምንቀስመው እውቀት በእኛ ላይ ምን ውጤት ሊኖረው ይገባል? (ለ) አንድ ሰው ለአምላክ ያለው ፍቅር እውነተኛ መሆን አለመሆኑ የሚታወቀው በምንድን ነው?

11 ሐዋርያው ጳውሎስ በእውቀትና በፍቅር መካከል ዝምድና መኖሩን መግለጹ ትክክል ነው። “ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ” ሲል ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 1:​9) ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ የምንማረው ውድ እውነት በትዕቢት እንድንነፋ ከማድረግ ይልቅ ለሰማያዊ አባታችን ያለንን ፍቅር ሊያሳድግልን ይገባል።

12 ብዙ ሰዎች ለአምላክ ፍቅር እንዳላቸው ቢናገሩም ለእሱ እውነተኛ ፍቅር እንደሌላቸው የታወቀ ነው። አምላክን ከልብ እንደሚወድዱት በቅንነት ይናገሩ ይሆናል። አምላክን መውደድ በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ከሆነ ጥሩ ባሕርይ ከመሆኑም በላይ የሚያስመሰግንም ነው። ይህ ማለት ግን ለአምላክ እውነተኛ ፍቅር አላቸው ማለት አይደለም። ለምን? የአምላክ ቃል እውነተኛ ፍቅርን በተመለከተ ምን እንደሚል ልብ በል:- “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም።” (1 ዮሐንስ 5:3) በመሆኑም አንድ ሰው ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር አለኝ ማለት የሚችለው ታዛዥነቱን በተግባር በመግለጽ ብቻ ነው።

13. አምላካዊ ፍርሃት ለይሖዋ ያለንን ፍቅር በተግባር እንድንገልጽ የሚረዳን እንዴት ነው?

13 አምላካዊ ፍርሃት ካለን ይሖዋን መታዘዝ ቀላል ይሆንልናል። ለይሖዋ ከፍተኛ አድናቆትና ጥልቅ አክብሮት የሚያድርብን ስለ እሱ እውቀት ስንቀስም ነው። ይህም ወደር የለሽ ስለሆነው ቅድስናው፣ ክብሩ፣ ኃይሉ፣ ፍትሑ፣ ጥበቡና ፍቅሩ መማርን ይጨምራል። እንዲህ ዓይነቱ ፍርሃት ወደ እሱ እንድንቀርብ በማስቻል ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አለው። እንዲያውም መዝሙር 25:​14 “እግዚአብሔር ለሚፈሩት ኃይላቸው [“ወዳጃቸው፣” የ1980 ትርጉም ] ነው” እንደሚል ልብ በል። በመሆኑም ተወዳጅ የሆነውን ሰማያዊ አባታችንን ላለማሳዘን ጤናማ ፍርሃት የሚሰማን ከሆነ ወደ እሱ መቅረብ እንችላለን። አምላካዊ ፍርሃት “በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” የሚለውን በምሳሌ 3:​6 ላይ የሚገኘውን ጥበብ ያዘለ ምክር እንድንከተል ይረዳናል። ይህ ምን ማለት ነው?

14, 15. (ሀ) በዕለታዊ ሕይወታችን የሚያጋጥሙን አንዳንድ ውሳኔ የሚጠይቁ ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) አምላካዊ ፍርሃት እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ውሳኔዎችን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

14 ከባድም ይሁን ቀላል ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቁ ነገሮች በየቀኑ ያጋጥሙሃል። ለምሳሌ ያህል ከሥራ ባልደረቦችህ፣ በትምህርት ቤት አብረውህ ከሚማሩት ተማሪዎችና ከጎረቤቶችህ ጋር የምትጫወተው ስለምን ጉዳይ ነው? (ሉቃስ 6:​45) የተሰጠህን ሥራ በትጋት ታከናውናለህ ወይስ የግብር ይውጣ ሥራ መሥራት ይቀናሃል? (ቆላስይስ 3:​23) ለይሖዋ ፍቅር ከሌላቸው ሰዎች ጋር የመቀራረብ ፍላጎት አለህ? ወይስ መንፈሳዊ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች ጋር ዝምድናህን ለማጠናከር የምትችለውን ሁሉ ታደርጋለህ? (ምሳሌ 13:​20) አነስተኛ በሚመስሉ ጉዳዮችም እንኳ የአምላክን መንግሥት ለማስቀደም ጥረት ታደርጋለህ? (ማቴዎስ 6:​33) በየቀኑ ውሳኔ ስታደርግ ከላይ እንደተጠቀሱት ባሉት ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች የምትመራ ከሆነ በእርግጥም “በመንገድህ ሁሉ” ይሖዋን አውቀሃል ማለት ይቻላል።

15 በሌላ አባባል ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ሁሉ እንዲህ እያልን ማሰብ ይኖርብናል:- ‘ይሖዋ ምን እንዳደርግ ይፈልግብኛል? ከሁሉ ይበልጥ እሱን የሚያስደስተው እንዴት ያለ ውሳኔ ባደርግ ነው?’ (ምሳሌ 27:​11) በዚህ መንገድ አምላካዊ ፍርሃት ማሳየታችን ለይሖዋ ያለንን ፍቅር የምንገልጽበት ግሩም መንገድ ነው። በተጨማሪም አምላካዊ ፍርሃት መንፈሳዊ፣ ሥነ ምግባራዊና አካላዊ ንጽሕናችንን እንድንጠብቅ ይገፋፋናል። ያዕቆብ ክርስቲያኖች ‘ወደ አምላክ እንዲቀርቡ’ ባሳሰበበት በዚያው ጥቅስ ላይ “እናንተ ኃጢአተኞች፣ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፣ ልባችሁን አጥሩ” የሚል ምክርም እንደሰጠ ልብ በል።​—⁠ያዕቆብ 4:​8

16. ለይሖዋ በመስጠታችን ምን እንዳደረግንለት ሊሰማን አይገባም? ሆኖም የምናደርገው ነገር የምን መግለጫ ሊሆን ይችላል?

16 እርግጥ ነው፣ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር የምንገልጸው ከመጥፎ ነገር በመራቅ ብቻ አይደለም። ፍቅር ጥሩ እንድናደርግም ይገፋፋናል። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ ለሚያሳየን የተትረፈረፈ ልግስና ምን ምላሽ እንሰጣለን? ያዕቆብ “በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፣ . . . ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 1:17) ከሃብታችን ውስጥ የተወሰነውን ለይሖዋ ብንሰጥም እንኳ ምንም እንደማንጨምርለት የታወቀ ነው። በዓለም ላይ ያለው ሀብት ሁሉ የእሱ ነው። (መዝሙር 50:​12) እንዲሁም ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ለይሖዋ ስንሰጥ የግድ የእኛ እርዳታ ያስፈልገዋል ማለት አይደለም። የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ ፈቃደኞች ባንሆን እንኳ ድንጋዮች እንዲናገሩ ማድረግ ይችላል! ታዲያ ጥሪታችንን፣ ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ለይሖዋ የምንሰጠው ለምንድን ነው? እንዲህ በማድረግ በሙሉ ልባችን፣ ነፍሳችን፣ ሐሳባችንና ኃይላችን እንደምንወደው መግለጽ ስለምንፈልግ ነው።​—⁠ማርቆስ 12:​29, 30

17. ለይሖዋ በደስታ እንድንሰጥ ሊያነሳሳን የሚችለው ምንድን ነው?

17 ‘አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ስለሚወድ’ ለይሖዋ ስንሰጥ በደስታ መሆን አለበት። (2 ቆሮንቶስ 9:​7) ዘዳግም 16:​17 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው “አምላክህ እግዚአብሔር በረከት እንደ ሰጠህ መጠን እያንዳንዱ ሰው እንደ ችሎታው ይስጥ” የሚለው መሠረታዊ ሥርዓት በደስታ እንድንሰጥ ያበረታታናል። ይሖዋ ያሳየንን ልግስና ስናስብ ለእሱ በደስታ የመስጠት ፍላጎት ያድርብናል። አንድ ወላጅ ከሚወድደው ልጁ የተሰጠው ትንሽ ስጦታ እንደሚያስደስተው ሁሉ ይሖዋም በደስታ ስንሰጥ ይደሰታል። በዚህ መንገድ ፍቅራችንን መግለጻችን ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ ይረዳናል።

በጸሎት አማካኝነት የጠበቀ ወዳጅነት ገንቡ

18. የጸሎታችንን ይዘት ማሻሻላችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

18 በግል የምናቀርበው ጸሎት ወደ ሰማያዊ አባታችን ይበልጥ ለመቅረብና የልባችንን አውጥተን እንድንነግረው የሚያስችል ልዩ አጋጣሚ ይከፍትልናል። (ፊልጵስዩስ 4:​6) ጸሎት ወደ አምላክ እንድንቀርብ የሚያስችለን ወሳኝ መንገድ በመሆኑ የጸሎታችንን ይዘት በተመለከተ ቆም ብለን ማሰባችን ተገቢ ነው። ጸሎታችን በቃላት አመራረጡና ይዘቱ የላቀ መሆን አለበት ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የምናቀርበው ጸሎት ከልባችን የመነጨ መሆን አለበት። የጸሎታችንን ይዘት ማሻሻል የምንችለው እንዴት ነው?

19, 20. ከመጸለያችን በፊት ማሰላሰል ያለብን ለምንድን ነው? ልናሰላስልባቸው የምንችላቸው አንዳንድ ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?

19 ከመጸለያችን በፊት ማሰላሰል እንችላለን። አስቀድመን ማሰላሰላችን በጸሎታችን ልንጠቅሳቸው የፈለግናቸውን ነገሮች በደፈናው ከመግለጽ ይልቅ ለይተን ለመናገር ያስችለናል። በዚህ መንገድ በጣም የተለመዱና በቀላሉ ወደ አእምሯችን የሚመጡ ቃላትን ወይም ሐረጎችን ከመደጋገም እንቆጠባለን። (ምሳሌ 15:​28, 29) ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ላይ በጠቀሳቸው አንዳንድ ነጥቦች ላይ ማሰላሰላችንና ከእኛ ሁኔታ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ማሰባችን ሊጠቅመን ይችላል። (ማቴዎስ 6:​9-13) ለምሳሌ ያህል የይሖዋ ፈቃድ በምድር እንዲሆን እኛ በበኩላችን ምን ድርሻ ማበርከት እንደምንችል ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን። አቅማችን የፈቀደውን ያህል እሱን የማገልገል ፍላጎት እንዳለን ለይሖዋ መግለጽና የሰጠን የአገልግሎት መብት ምንም ይሁን ምን መወጣት እንድንችል እንዲረዳን መጠየቅ እንችል ይሆን? ቁሳዊ ፍላጎቶቻችንን የማሟላቱ ኃላፊነት ጫና ፈጥሮብን ይሆን? ይሖዋ ይቅር እንዲለን የምንፈልገው የትኛውን በደላችንን ነው? በይበልጥ የይቅር ባይነት ባሕርይ ማሳየት የሚኖርብን ለእነማን ነው? ምን ፈተናዎች አጋጥመውናል? በዚህ ረገድ የይሖዋ ጥበቃ በአፋጣኝ እንደሚያስፈልገን ተገንዝበናልን?

20 በተጨማሪም የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ስለምናውቃቸው ሰዎች ማሰብ እንችላለን። (2 ቆሮንቶስ 1:​11) ምስጋና ማቅረብ እንደሚያስፈልገንም መርሳት አይኖርብንም። ቆም ብለን ካሰብንበት ይሖዋ ላሳየን ከፍተኛ ደግነት በየዕለቱ እሱን የምናመሰግንበትና የምናወድስበት ምክንያት አናጣም። (ዘዳግም 8:​10፤ ሉቃስ 10:​21) እንዲህ ማድረጋችን ተጨማሪ ጥቅም ያስገኝልናል፤ ይኸውም በሕይወታችን ውስጥ ይበልጥ አዎንታዊና አመስጋኝ እንድንሆን ይረዳናል።

21. ይሖዋን በጸሎት መቅረብን በተመለከተ የትኞቹን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች ማጥናታችን ይጠቅመናል?

21 በተጨማሪም ጥናት የጸሎታችን ይዘት እንዲሻሻል ሊረዳን ይችላል። በአምላክ ቃል ላይ ተመዝግበው የሚገኙ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ያቀረቧቸው ግሩም ጸሎቶች አሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ከባድ ችግር አጋጥሞን ጭንቀት ካደረብን እንዲሁም ሁኔታው የራሳችንን ወይም የምናፈቅራቸውን ሰዎች ደኅንነት አደጋ ላይ እንደሚጥል ከተሰማን ያዕቆብ ቂመኛ ከሆነው ከወንድሙ ከዔሳው ጋር የሚገናኝበት ጊዜ ሲደርስ ያቀረበውን ጸሎት ማንበብ እንችላለን። (ዘፍጥረት 32:​9-12) ወይም ደግሞ ንጉሥ አሳ አንድ ሚልዮን የሚያህል የኢትዮጵያ ሠራዊት በአምላክ ሕዝብ ላይ ስጋት በፈጠረ ጊዜ ያቀረበውን ጸሎት ማጥናት እንችላለን። (2 ዜና መዋዕል 14:​11, 12) በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ ሊያስከትል የሚችል ችግር ካጋጠመን ኤልያስ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ በበኣል አምላኪዎች ፊት ያቀረበውን ጸሎት መመርመራችን ጠቃሚ ነው። ኢየሩሳሌም የነበረችበትን አሳዛኝ ሁኔታ በተመለከተ ነህምያ ያቀረበው ጸሎትም በዚህ ረገድ ይጠቅመናል። (1 ነገሥት 18:​36, 37፤ ነህምያ 1:​4-11) እንዲህ ዓይነቶቹን ጸሎቶች ማንበብና በዚያም ላይ ማሰላሰል እምነታችንን የሚያጠናክርልን ከመሆኑም በላይ የሚያስጨንቁንን ችግሮች በተሻለ ሁኔታ ለይሖዋ መግለጽ የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ ፍንጭ ይሰጡናል።

22. የ2003 የዓመት ጥቅስ ምንድን ነው? በዓመቱ ውስጥ በየጊዜው ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ እንችላለን?

22 ያዕቆብ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ” ሲል የሰጠውን ምክር ከመከተል የበለጠ ክብርም ሆነ የላቀ ግብ ሊኖር አይችልም። (ያዕቆብ 4:​8) ስለ አምላክ ያለንን እውቀት እያሳደግን በመሄድ፣ ለእሱ ያለንን ፍቅር ከበፊቱ በተሻለ መንገድ ለመግለጽ በመጣርና በጸሎታችን ከእሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት በማጠናከር ወደ እሱ እንቅረብ። በ2003 የዓመቱ ጥቅስ የሆነውን ያዕቆብ 4:​8ን በአእምሯችን ይዘን በእርግጥ ወደ ይሖዋ እየቀረብን ስለመሆናችን ምንጊዜም ራሳችንን እንጠይቅ። “ወደ እናንተም ይቀርባል” ስለሚለው ዓረፍተ ነገርስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋ ‘ወደ እኛ የሚቀርበው’ እንዴት ነው? ይህስ ምን በረከቶች ያስገኝልናል? ይህ ጉዳይ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።

ታስታውሳለህ?

• ወደ ይሖዋ መቅረብ በቁም ነገር ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው?

• ስለ ይሖዋ እውቀት ለመቅሰም ልናወጣቸው የሚገቡ አንዳንድ ግቦች ምንድን ናቸው?

• ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

• በጸሎት አማካኝነት ከይሖዋ ጋር ከበፊቱ የጠበቀ ወዳጅነት መገንባት የምንችለው በምን መንገዶች ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የ2003 የዓመት ጥቅስ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” የሚለው ይሆናል።​—⁠ያዕቆብ 4:8

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳሙኤል እያደገ ሲሄድ ይሖዋን በቅርብ ማወቅ ችሏል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤልያስ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ያቀረበው ጸሎት ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል