በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ብርሃን የመረጡ የሚያገኙት መዳን

ብርሃን የመረጡ የሚያገኙት መዳን

ብርሃን የመረጡ የሚያገኙት መዳን

“እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማን ነው?”​—⁠መዝሙር 27:​1

1. ይሖዋ ሕይወት ሰጭ የሆነ ምን ዝግጅት አድርጓል?

 ይሖዋ የፀሐይ ብርሃን ምንጭ ሲሆን ይህም ብርሃን በምድር ላይ ሕይወት እንዲኖር አስችሏል። (ዘፍጥረት 1:​2, 14) በተጨማሪም የመንፈሳዊ ብርሃን ፈጣሪ ሲሆን ይህም ሞት የሚያስከትለውን የሰይጣን ዓለም ጨለማ ያስወግዳል። (ኢሳይያስ 60:​2፤ 2 ቆሮንቶስ 4:​6፤ ኤፌሶን 5:​8-11፤ 6:​12) ብርሃን የመረጡ ሰዎች እንደ መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማን ነው?” ሊሉ ይችላሉ። (መዝሙር 27:​1) ይሁን አንጂ በኢየሱስ ዘመን እንደሆነው ጨለማን የሚመርጡ የሚጠብቃቸው የቅጣት ፍርድ ብቻ ይሆናል።​—⁠ዮሐንስ 1:​9-11፤ 3:​19-21, 36

2. በጥንት ጊዜ የይሖዋን ብርሃን የናቁ ሰዎች ምን ደርሶባቸዋል? ቃሉን የሰሙትስ ምን አግኝተዋል?

2 በኢሳይያስ ዘመን ከይሖዋ የቃል ኪዳን ሕዝብ መካከል አብዛኛዎቹ ብርሃኑን ንቀው ነበር። ከዚህም የተነሳ ኢሳይያስ የእስራኤል ሰሜናዊ መንግሥት በሕዝብ ደረጃ የሚደርስበትን ጥፋት ተመልክቷል። እንዲሁም በ607 ከዘአበ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ የጠፉ ሲሆን የይሁዳ ነዋሪዎችም በግዞት ተወስደዋል። ይሁን እንጂ የይሖዋን ቃል የሰሙት በዚያን ጊዜ የነበረውን ክህደት ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ጥንካሬ አግኝተዋል። ይሖዋ እርሱን የሚያዳምጡ ሰዎች በ607 ከዘአበ ከደረሰው ጥፋት እንደሚተርፉ ቃል ገብቷል። (ኤርምያስ 21:​8, 9) ዛሬም ብርሃን የምንወድ ሁሉ ጥንት ከደረሰው ብዙ ነገር ልንማር እንችላለን።​—⁠ኤፌሶን 5:​5

በብርሃኑ የሚመላለሱ የሚያገኙት ደስታ

3. ዛሬ ምን ትምክህት ሊኖረን ይችላል? የምንወደው “ጻድቅ ሕዝብ” የትኛው ነው? የዚህ “ሕዝብ” “የጸናች ከተማ” ምንድን ነች?

3 “የጸናች ከተማ አለችን፤ [አምላክ] ለቅጥርና ለምሽግ መድኃኒትን ያኖርባታል። እውነትን የሚጠብቅ ጻድቅ ሕዝብ ይገባ ዘንድ በሮችን ክፈቱ።” (ኢሳይያስ 26:​1, 2) እነዚህ እምነታቸውን በይሖዋ ላይ ያደረጉ ሰዎች በደስታ የሚናገሯቸው ቃላት ናቸው። በኢሳይያስ ዘመን የነበሩ ታማኝ አይሁዳውያን የእውነተኛ ደህንነት ብቸኛ ምንጭ አድርገው የተመለከቱትን የአገራቸው ሰዎች ይከተሏቸው የነበሩትን የሃሰት አማልክት ሳይሆን ይሖዋን ነበር። በዛሬው ጊዜ እኛም ተመሳሳይ የሆነ ትምክህት አለን። ከዚህም በላይ የይሖዋን “ጻድቅ ሕዝብ” ማለትም ‘የአምላክ እስራኤልን’ እንወድዳለን። (ገላትያ 6:​16፤ ማቴዎስ 21:​43) ይሖዋም በታማኝ አኗኗሩ ምክንያት ይህን ሕዝብ ይወድደዋል። ይህ የአምላክ እስራኤል በይሖዋ በረከት “የጸናች ከተማ” ማለትም ድጋፍና ከለላ የሚያገኝበት ከተማ መሰል ድርጅት አግኝቷል።

4. ምን ዓይነት ዝንባሌ ማዳበራችን የተገባ ይሆናል?

4 በዚህች “ከተማ” የሚኖሩ ሰዎች “በአንተ [በይሖዋ] ላይ ታምናለችና በአንተ [በይሖዋ] ለምትደገፍ ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ” የሚለውን በሚገባ ያውቃሉ። ይሖዋ በእርሱ የመደገፍ ዝንባሌ ያላቸውንና ከጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ጋር ተስማምተው የሚሄዱትን ይደግፋቸዋል። ስለዚህ በይሁዳ ይኖሩ የነበሩ ታማኞች የሚከተለውን ኢሳይያስ የሰጠውን ጥብቅ ምክር ተከትለዋል:- “ጌታ እግዚአብሔር [“ያህ ይሖዋ፣” NW ] የዘላለም አምባ ነውና ለዘላለም በእግዚአብሔር ታመኑ።” (ኢሳይያስ 26:​3, 4፤ መዝሙር 9:​10፤ 37:​3፤ ምሳሌ 3:​5) እንዲህ ያለ ዝንባሌ ያላቸው “ያህ ይሖዋን” ብቸኛው አምባቸው እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ከእርሱ ጋር ‘ያልተቋረጠ ሰላም’ [NW ] ይኖራቸዋል።​—⁠ፊልጵስዩስ 1:​2፤ 4:​6, 7

የአምላክ ጠላቶች ይዋረዳሉ

5, 6. (ሀ) የጥንቷ ባቢሎን የተዋረደችው እንዴት ነው? (ለ) “ታላቂቱ ባቢሎን” የተዋረደችው በምን መንገድ ነው?

5 በአምላክ ላይ የሚታመኑ ሰዎች መከራ ቢደርስባቸውስ? መፍራት አይኖርባቸውም። ይሖዋ እንዲህ ያለ ነገር እንዲደርስ ለጊዜው ሊፈቅድ ይችላል። በመጨረሻ ግን ዕረፍት ይሰጣል። መከራ በሚያመጡ ላይ ደግሞ ይፈርድባቸዋል። (2 ተሰሎንቄ 1:​4-7፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:​8-10) ‘ከፍ ስላለ’ ስለ አንድ “ከተማ” አስብ። ኢሳይያስ እንዲህ ይላል:- “በከፍታ የሚኖሩትን ሰዎች [ይሖዋ] ዝቅ ያደርጋል፤ ከፍ ያለችውን ከተማ ያዋርዳል፣ እስከ መሬትም ድረስ ያወርዳታል፣ እስከ አፈርም ድረስ ይጥላታል። እግር፣ የድሀ እግርም የችግረኛም አረጋገጥ፣ ትረግጣታለች።” (ኢሳይያስ 26:​5, 6) እዚህ ላይ የተጠቀሰችው ከፍ ያለች ከተማ ባቢሎን ሳትሆን አትቀርም። ይህቺ ከተማ በእርግጥም የአምላክን ሕዝቦች ጨቁናለች። ታዲያ ባቢሎን ምን ደረሰባት? በ539 ከዘአበ በሜዶንና በፋርስ እጅ ወደቀች። እንዴት ያለ ውርደት ነው!

6 ኢሳይያስ የተናገረው ትንቢት በዘመናችን ከ1919 ጀምሮ ‘በታላቂቱ ባቢሎን’ ላይ የደረሰውን ነገር ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ነው። የይሖዋን ሕዝብ ከመንፈሳዊ ምርኮ ለመልቀቅ በተገደደችበት ዓመት ከፍ ብላ የነበረችው ከተማ በውርደት ወድቃለች። (ራእይ 14:​8) ከዚያ በኋላ የተከናወነውም ነገር ለባሰ ውርደት ዳርጓታል። እነዚህ ጥቂት ቁጥር ያላቸው ክርስቲያኖች ቀድሞ ትጨቁናቸው የነበረችውን ከተማ በእግራቸው ረግጠዋታል። በ1922 በራእይ 8:​7-12 ላይ የተገለጹት መላእክቱ የሚነፏቸውን አራት መለከቶችና በራእይ 9:​1–11:​15 ላይ የተተነበዩትን ሦስት ወዮታዎች በማወጅ በሕዝበ ክርስትና ላይ ስለሚደርሰው መጪ ጥፋት ማስታወቅ ጀመሩ።

“የጻድቃን መንገድ ቅን ናት”

7. ወደ ይሖዋ ብርሃን ዞር የሚሉ ሰዎች ምን መመሪያ ያገኛሉ? ተስፋቸውን የጣሉት በማን ላይ ነው? ከፍ አድርገው የሚመለከቱትስ ነገር ምንድን ነው?

7 ይሖዋ ወደ ብርሃኑ ዞር ለሚሉ ሰዎች መዳንን ያዘጋጀ ሲሆን ቀጥሎ ኢሳይያስ እንደተናገረው መንገዳቸውንም ይመራቸዋል። “የጻድቃን መንገድ ቅን ናት፤ አንተ ቅን የሆንህ የጻድቃንን መንገድ ታቃናለህ። አቤቱ፣ በፍርድህ መንገድ ተስፋ አድርገንሃል፣ ስምህም መታሰቢያህም የነፍሳችን ምኞት ነው።” (ኢሳይያስ 26:​7, 8) ይሖዋ ጻድቅ አምላክ ነው። እርሱን የሚያመልኩም የጽድቅ የአቋም ደረጃዎቹን መጠበቅ ይገባቸዋል። እንደዚህ ካደረጉ ይሖዋ መንገዳቸውን ቀና በማድረግ ይመራቸዋል። እነዚህ ቅን ሰዎች የእርሱን መመሪያ በመከተል በይሖዋ ተስፋ እንደሚያደርጉና ስሙን ማለትም ‘መታሰቢያውን’ ከልባቸው ከፍ አድርገው እንደሚይዙ ያሳያሉ።​—⁠ዘጸአት 3:​15

8. ኢሳይያስ ምሳሌ የሚሆን ምን ዝንባሌ አሳይቷል?

8 ኢሳይያስ ለይሖዋ ስም ከፍ ያለ ግምት ነበረው። ቀጥሎ ከተናገራቸው ቃላት ይህን መገንዘብ ይቻላል:- “ፍርድህን በምድር ባደረግህ ጊዜ በዓለም የሚኖሩ ጽድቅን ይማራሉና ነፍሴ በሌሊት ትናፍቅሃለች፣ መንፈሴም በውስጤ ወደ አንተ ትገሠግሣለች።” (ኢሳይያስ 26:​9) የኢሳይያስ ነፍስ ማለትም ሁለንተናው ይሖዋን ናፍቃለች። ነቢዩ ፀጥ ባለው ሌሊት ወደ ይሖዋ አምላክ ሲጸልይና ውስጣዊ ስሜቱን ሲገልጥ እንዲሁም መመሪያ ለማግኘት ከልብ ሲማጸን በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ይህ ምንኛ ግሩም ምሳሌ ነው! ከዚህም በላይ ኢሳይያስ ይሖዋ ከወሰዳቸው የፍርድ እርምጃዎች ጽድቅን ተምሯል። በዚህም የይሖዋን ፈቃድ ለማወቅ ዘወትር ንቁ የመሆንንና ያለ ማቋረጥ ነቅቶ የመኖርን አስፈላጊነት ያሳስበናል።

አንዳንዶች ጨለማን መረጡ

9, 10. ይሖዋ ታማኝ ላልነበሩት ሕዝቡ በደግነት ምን ነገር አድርጎላቸዋል? ሆኖም ሕዝቡ ምን ምላሽ ሰጡ?

9 ይሖዋ ለይሁዳ ትልቅ ፍቅራዊ ደግነት ቢያሳይም ጥሩ ምላሽ የሰጡት ሁሉም አለመሆናቸው የሚያሳዝን ነው። በተደጋጋሚ አብዛኞቹ ከይሖዋ የእውነት ብርሃን ይልቅ ዓመፀኝነትንና ክህደትን መርጠዋል። ኢሳይያስ እንዲህ ብሏል:- “ለኃጢአተኛ ሞገስ ቢደረግለት ጽድቅን አይማርም፤ በቅኖች ምድር ክፉን ነገር ያደርጋል፣ የእግዚአብሔርንም ግርማ አያይም።”​—⁠ኢሳይያስ 26:​10

10 በኢሳይያስ ዘመን ይሖዋ በተዘረጋች ክንዱ ይሁዳን ከጠላቶቻቸው ቢታደጋቸውም ብዙዎቹ ይህን ሳይገነዘቡ ቀርተዋል። ሰላም በማስፈን በባረካቸው ጊዜ ሕዝቡ አመስጋኝነት አላሳየም። ከዚህ የተነሳ ይሖዋ ‘ሌሎች ጌቶችን’ እንዲያገለግሉ በመተው በ607 ከዘአበ አይሁዶች በግዞት ወደ ባቢሎን እንዲወሰዱ ፈቀደ። (ኢሳይያስ 26:​11-13) የሆነ ሆኖ ውሎ አድሮ የሕዝቡ ቅሬታ ተገቢውን ቅጣት አግኝተው ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰዋል።

11, 12. (ሀ) ይሁዳን በምርኮ የያዙት ሰዎች ምን ይጠብቃቸው ነበር? (ለ) በ1919 የተቀቡ የይሖዋ አገልጋዮችን በምርኮ ይዘው የነበሩት ዕጣቸው ምን ነበር?

11 ይሁዳን የማረከችው አገርስ? ኢሳይያስ በሚከተለው ትንቢት መልሱን ይሰጠናል:- “እነርሱ ሞተዋል፣ በሕይወት አይኖሩም፤ ጠፍተዋል፣ አይነሡም፤ ስለዚህ አንተ ጐብኝተሃቸዋል አጥፍተሃቸውማል፣ መታሰቢያቸውንም ሁሉ ምንምን አድርገሃል።” (ኢሳይያስ 26:​14) አዎን፣ ባቢሎን በ539 ከዘአበ ከወደቀች በኋላ ተስፋዋ ሁሉ አብሮ ተቀብሯል። ከጊዜ በኋላ ከተማዋ ጭራሽ ከሕልውና ውጭ ትሆናለች። ‘ምውት’ ስለምትሆን ግዙፉ ግዛቷ የጥንት ታሪክ ብቻ ሆኖ ይቀራል። በዚህ ዓለም ኃያላን ላይ ተስፋቸውን ለሚጥሉ ሁሉ ይህ እንዴት ያለ ማስጠንቀቂያ ነው!

12 እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት ይሖዋ ቅቡዓን አገልጋዮቹ በ1918 በመንፈሳዊ ምርኮ እንዲወሰዱ በፈቀደና በ1919 ነፃ እንዲወጡ ባደረገ ጊዜም ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ በምርኮ ይዘዋቸው የነበሩት ወገኖች በተለይ ደግሞ የሕዝበ ክርስትና የወደፊት ዕጣ የጨለመ ሆኗል። የይሖዋ ሕዝቦች ግን የተትረፈረፈ በረከት ይጠብቃቸው ነበር።

“ሕዝብን አበዛህ”

13, 14. የይሖዋ ቅቡዓን አገልጋዮች ከ1919 ጀምሮ ምን የተትረፈረፈ በረከት አግኝተዋል?

13 አምላክ የንስሐ መንፈስ ያሳዩትን ቅቡዓን አገልጋዮቹን በ1919 በመባረክ በቁጥር እንዲበዙ አድርጓል። በመጀመሪያ፣ የአምላክ እስራኤልን የመጨረሻ አባላት በመሰብሰቡ ሥራ ላይ ትኩረት የተደረገ ሲሆን ከዚያም “የሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑትን ‘እጅግ ብዙ ሰዎችን’ መሰብሰብ ተጀመረ። (ራእይ 7:​9፤ ዮሐንስ 10:​16) እነዚህ በረከቶች በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ አስቀድመው ተተንብየዋል:- “ሕዝብን አበዛህ፣ አቤቱ፣ ሕዝብን አበዛህ፤ አንተም ተከበርህ፣ የአገሪቱንም ዳርቻ ሁሉ አሰፋህ። አቤቱ፣ በመከራ ጊዜ ፈለጉህ፣ በገሠጽሃቸውም ጊዜ ልመናቸውን ወደ አንተ አፈሰሱ።”​—⁠ኢሳይያስ 26:​15, 16

14 ዛሬ የአምላክ እስራኤል ዳርቻ እስከ ምድር ዳር ድረስ ተስፋፍቷል። ወደ ስድስት ሚልዮን የሚጠጋ ቁጥር ያላቸው እጅግ ብዙ ሰዎች ምሥራቹን የመስበኩን ወሳኝ ሥራ በቅንዓት በመደገፍ ላይ ናቸው። (ማቴዎስ 24:​14) ይህ እንዴት ያለ የይሖዋ በረከት ነው! ለስሙ የሚያመጣው ክብር ምንኛ ከፍ ያለ ነው! ዛሬ ይህ ስም በ235 አገሮች ውስጥ የሚሰማ ሲሆን ይህ አምላክ የሰጠው ተስፋ ድንቅ ፍጻሜ ነው!

15. በ1919 ምን ምሳሌያዊ የሆነ ትንሣኤ ተከናውኗል?

15 የይሁዳ ሰዎች ከባቢሎን ምርኮ ነፃ ለመውጣት የይሖዋ እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር። በራሳቸው ጉልበት ይህን ማድረግ አይችሉም ነበር። (ኢሳይያስ 26:​17, 18) በተመሳሳይም የአምላክ እስራኤል በ1919 ያገኘው ነፃነት የይሖዋ እርዳታ ማረጋገጫ ነው። ያለ እርሱ እርዳታ ነፃነታቸውን ማግኘት አይችሉም ነበር። አስገራሚ የሆነው ነገር ደግሞ ያደረጉትን ለውጥ ኢሳይያስ ከትንሣኤ ጋር ማመሳሰሉ ነው። “ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፣ ሬሳዎችም ይነሣሉ። በምድር የምትኖሩ ሆይ፣ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና፣ ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ ዘምሩም።” (ኢሳይያስ 26:​19፤ ራእይ 11:​7-11) አዎን፣ በሞት እስር የተያዙት ሰዎች በአዲስ መልክ ሥራቸውን ለመጀመር ዳግም የተወለዱ ያህል ይሆናል!

በአደገኛ ጊዜ ጥበቃ ማግኘት

16, 17. (ሀ) በ539 ከዘአበ አይሁዳውያን ባቢሎን በወደቀችበት ወቅት ለመዳን ምን ማድረግ ነበረባቸው? (ለ) ‘ቤት’ የሚለው መግለጫ ዛሬ የሚያመለክተው ምንን ሳይሆን አይቀርም? የሚጠቅሙንስ እንዴት ነው?

16 የይሖዋ አገልጋዮች ሁልጊዜ የእርሱ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል። በቅርቡ ግን በሰይጣን ዓለም ላይ ለመጨረሻ ጊዜ እጁን ይዘረጋል። የይሖዋ አምላኪዎችም ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የእርሱ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። (1 ዮሐንስ 5:​19) ይሖዋ ይህን አደገኛ ጊዜ በማስመልከት እንዲህ በማለት ያስጠነቅቀናል:- “ሕዝቤ ሆይ፣ ና ወደ ቤትህም ግባ፣ ደጅህን በኋላህ ዝጋ፤ ቁጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ። በምድር በሚኖሩት ላይ በበደላቸው ምክንያት ቁጣውን ያመጣባቸው ዘንድ፣ እነሆ፣ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል፤ ምድርም ደምዋን ትገልጣለች፣ ሙታኖችዋንም ከእንግዲህ ወዲህ አትከድንም።” (ኢሳይያስ 26:​20, 21፤ ሶፎንያስ 1:​14) ይህ ማስጠንቀቂያ ባቢሎን በ539 ከዘአበ በምትወድቅበት ጊዜ አይሁዳውያን እንዴት መዳን እንደሚችሉ የሚጠቁም ነበር። ይህን ማስጠንቀቂያ የተቀበሉ ሁሉ ቤታቸው በመቆየት በጎዳና ላይ ካሉት ድል አድራጊ ወታደሮች ራሳቸውን መጠበቅ ይችሉ ነበር።

17 ዛሬ በትንቢቱ ላይ የተጠቀሰው ‘ቤት’ በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች የሚያመለክት እንደሚሆን እሙን ነው። እነዚህ ጉባኤዎች ዛሬም ጭምር ሽማግሌዎች በሚሰጡት ፍቅራዊ እንክብካቤ አማካኝነት ክርስቲያኖች ወንድሞቻቸው መካከል የደህንነት ስሜት ተሰምቷቸው የሚመላለሱባቸውና ጥበቃ የሚያገኙባቸው ቦታዎች ናቸው። (ኢሳይያስ 32:​1, 2፤ ዕብራውያን 10:​24, 25) በተለይ ለመዳን ታዛዥነት አስፈላጊ የሆነበት የዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ከመቅረቡ አንጻር ሲታይ ትክክል ነው።​—⁠ሶፎንያስ 2:​3

18. ይሖዋ በቅርቡ ‘የባሕሩን ዘንዶ’ የሚገድለው እንዴት ነው?

18 ያንን ጊዜ በተመለከተ ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይተነብያል:- “በዚያም ቀን እግዚአብሔር ፈጣኑን እባብ ሌዋታንን ጠማማውንም እባብ ሌዋታንን በጠንካራ በታላቅም በብርቱም ሰይፍ ይቀጣል፣ በባሕርም ውስጥ ያለውን ዘንዶ ይገድላል።” (ኢሳይያስ 27:​1) የዘመናችን “ሌዋታን” ማን ነው? “የቀደመው እባብ” የተባለው ሰይጣንና መንፈሳዊ እስራኤላውያንን ለመዋጋት መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀምበት የእርሱ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ይመስላል። (ራእይ 12:​9, 10, 17፤ 13:​14, 16, 17) ሌዋታን በ1919 በአምላክ ሕዝብ ላይ የነበረውን የበላይነት አጥቷል። በቅርቡም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይወገዳል። (ራእይ 19:​19-21፤ 20:​1-3, 10) በዚህ መንገድ ይሖዋ ‘የባሕሩን ዘንዶ’ ይገድላል። እስከዚያው ድረስ ግን ሌዋታን የይሖዋን ሕዝብ ለማጥቃት የሚሞክረው ማንኛውም ነገር አይከናወንለትም። (ኢሳይያስ 54:​17) ይህን ማረጋገጫ ማግኘት ምንኛ የሚያጽናና ነው!

‘የተወደደ የወይን ቦታ’

19. በዛሬው ጊዜ ቀሪዎቹ ያሉበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

19 ከይሖዋ ያገኘነው ይህ ሁሉ ብርሃን ለመደሰት የሚያበቃ ምክንያት አይደለምን? በእርግጥም ለመደሰት በቂ ምክንያት አለን! ኢሳይያስ የይሖዋ ሕዝቦች የሚያገኙትን ደስታ ውብ በሆነ መንገድ ሲገልጽ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በዚያም ቀን ለተወደደው የወይን ቦታ ተቀኙለት። እኔ እግዚአብሔር ጠባቂው ነኝ፤ ሁልጊዜ አጠጣዋለሁ፤ ማንም እንዳይጐዳው በሌሊትና በቀን እጠብቀዋለሁ።” (ኢሳይያስ 27:​2, 3) ይሖዋ ‘የወይን ቦታውን’ ማለትም የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎችንና በትጋት የሚሠሩትን ተባባሪዎቻቸውን ይንከባከባል። (ዮሐንስ 15:​1-8) በዚህ መንገድ የሚገኘው ውጤት ለስሙ ክብር የሚያመጣ ፍሬ ሲሆን በምድር ላይ ለሚገኙ አገልጋዮቹም ታላቅ ደስታ ያስገኛል።

20. ይሖዋ ክርስቲያን ጉባኤን የሚጠብቀው እንዴት ነው?

20 ይሖዋ በ1918 ቅቡዓን አገልጋዮቹ በመንፈሳዊ ምርኮ እንዲወሰዱ የፈቀደበት ቁጣው በማለፉ ዛሬ ደስ ሊለን ይችላል። ይሖዋ ራሱ እንዲህ ብሏል:- “አልቈጣም፤ እሾህና ኩርንችት በእኔ ላይ ምነው በሰልፍ በነበሩ! በእነርሱ ላይ ተራምጄ በአንድነት ባቃጠልኋቸው ነበር። ወይም ጉልበቴን ይያዝ፣ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ፤ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ።” (ኢሳይያስ 27:​4, 5) ይሖዋ የወይን ቦታው ‘የተወደደውን ወይን’ አትረፍርፎ መስጠቱን ይቀጥል ዘንድ የወይን ቦታውን ሊያበላሹ የሚችሉ እንደ አረም ያሉ ተጽዕኖዎችን ሁሉ ይነቃቅላል በእሳትም ያቃጥላቸዋል። እንግዲያውስ ማንም ሰው የክርስቲያን ጉባኤን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ማድረግ አይኖርበትም! ይልቁንም ሰው ሁሉ የይሖዋን ሞገስና ጥበቃ ለማግኘት በመጣጣር ‘የይሖዋን ጉልበት ሊይዝ ይገባል።’ ይህን በማድረግ ከአምላክ ጋር ሰላም እንፈጥራለን። ይህ ጉዳይ ደግሞ በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሣ ኢሳይያስ ሁለት ጊዜ ጠቅሶታል።​—⁠መዝሙር 85:​1, 2, 8፤ ሮሜ 5:​1

21. ፍሬያማው መሬት ‘በፍሬ’ የተሞላው በምን መንገድ ነው?

21 በረከቱ ይቀጥላል:- “በሚመጣው ዘመን ያዕቆብ ሥር ይሰድዳል፣ እስራኤልም ያብባል ይጨበጭብማል፤ በፍሬያቸውም የዓለሙን ፊት ይሞላሉ።” (ኢሳይያስ 27:​6) ይህ ጥቅስ ከ1919 ጀምሮ ፍጻሜውን ማግኘቱ የይሖዋን ኃይል የሚያረጋግጥ ድንቅ ማስረጃ ነው። ቅቡዓን ክርስቲያኖች መላዋን ምድር ‘በፍሬ’ ማለትም በሚገነባ መንፈሳዊ ምግብ ሞልተዋታል። በዚህ ብልሹ ዓለም ውስጥ የአምላክን ከፍ ያሉ የአቋም ደረጃዎች ደስ ብሏቸው ያከብራሉ። ይሖዋም ጭማሪ በመስጠት እነርሱን መባረኩን ቀጥሏል። ከዚህ የተነሣ ከጎናቸው የተሰለፉት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች በጎች ‘ቀንና ሌሊት ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብ’ ላይ ናቸው። (ራእይ 7:​15) ‘ከፍሬው’ የመካፈልና ይህንን ፍሬ ለሌሎች የማዳረስ ታላቅ መብት እንዳገኘን ፈጽሞ አንዘንጋ!

22. ብርሃኑን የሚቀበሉ ሁሉ ምን በረከት ያገኛሉ?

22 ምድርን ጨለማ፣ አሕዛብንም ድቅድቅ ጨለማ በዋጠበት በዚህ አስጨናቂ በሆነው ዘመን ይሖዋ በሕዝቡ ላይ መንፈሳዊ ብርሃን በማብራቱ አመስጋኞች አይደለንም? (ኢሳይያስ 60:​2፤ ሮሜ 2:​19፤ 13:​12) ይህንን መንፈሳዊ ብርሃን የሚቀበሉ ሁሉ በአሁኑ ጊዜ የአእምሮ ሰላምና ደስታ ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። ይህን ብርሃን የምንወድ ሁሉ ልባችንን ከፍ አድርገን ይሖዋን በማወደስ ከመዝሙራዊው ጋር እንደሚከተለው የምንልበት ጥሩ ምክንያት አለን:- “እግዚአብሔር የሕይወቴ መታመኛዋ ነው፤ የሚያስደነግጠኝ ማን ነው? እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።”​—⁠መዝሙር 27:​1, 14

ታስታውሳለህ?

• የይሖዋን ሕዝብ የሚጨቁኑ የወደፊት ዕጣቸው ምንድን ነው?

• በኢሳይያስ ትንቢት የተገለጸው ጭማሪ ምንድን ነው?

• መቆየት የሚኖርብን በየትኛው ‘ቤት’ ውስጥ ነው? ለምንስ?

• የይሖዋ ሕዝቦች ያሉበት ሁኔታ ለይሖዋ ውዳሴ የሚያስገኘው እንዴት ነው?

[የጥናት እትም]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አዲስ ጽሑፍ

በእነዚህ ሁለት የጥናት ርዕሶች ላይ የተብራሩት አብዛኞቹ ሐሳቦች በ2000/2001 በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ፕሮግራም ላይ በንግግር ቀርበዋል። በንግግሩ መደምደሚያ ላይ የኢሳይያስ ትንቢት​—⁠ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 1 የተባለ አንድ አዲስ ጽሑፍ መውጣቱ ተነግሯል። ይህ 416 ገጽ ያለው መጽሐፍ የኢሳይያስን መጽሐፍ የመጀመሪያ 40 ምዕራፎች ቁጥር በቁጥር የሚያብራራ ነው።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በይሖዋ ‘ጽኑ ከተማ’ ማለት በድርጅቱ ውስጥ እንዲኖሩ የሚፈቀድላቸው ጻድቃን ሰዎች ብቻ ናቸው

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢሳይያስ ‘በሌሊት’ ይሖዋን ፈልጓል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ‘የወይን ቦታውን’ ይንከባከበዋል ፍሬያማም ያደርገዋል