አዲስ የኃይል ምንጭ ማግኘት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
አዲስ የኃይል ምንጭ ማግኘት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
“የነዳጅ ዘይት ጉዳይ ትልቅ ችግር ሆኗል ብለን የምናስብ ከሆነ ከ20 ዓመት በኋላ የሚሆነውን እንጠብቅ። በዚያ ጊዜ የሚኖረው ችግር በጣም ከፍተኛ ይሆናል።”—ጄረሚ ሪፍከን፣ ፋውንዴሽን ኦቭ ኢኮኖሚክ ትሬንድስ፣ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ነሐሴ 2003
የዛሬ 20 ዓመት ገደማ ሕፃኑ ማይካ መኪና መንዳት በሚችልበት ዕድሜ ላይ ይደርሳል። የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ያወጣው ኢንተርናሽናል ኢነርጂ አውትሉክ 2003 የተባለ ሪፖርት እንደገለጸው በዚያ ጊዜ የመላው ዓለም የኃይል ፍጆታ “በ58 በመቶ እንደሚጨምር ይጠበቃል።” ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ስለሚጠበቀው ጭማሪ ሲናገር “በታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የኃይል ፍጆታ እመርታ ይኖራል” ብሏል። በአሁኑ ጊዜ ያሉት የኃይል ምንጮች ይኖራል ተብሎ የሚታሰበውን ይህን የኃይል ፍጆታ ማሟላት ይችላሉ? የሚከተሉትን አሳሳቢ እውነታዎች ተመልከት።
የድንጋይ ከሰል:-
▪ ከከርሰ ምድር ከሚገኙ የነዳጅ ዓይነቶች ሁሉ በብዛቱ የአንደኝነትን ደረጃ የያዘው የድንጋይ ከሰል ሲሆን ለ1,000 ዓመት የሚበቃ ክምችት አለ ተብሎ ይታሰባል። በመላው ዓለም የድንጋይ ከሰልን የሚጠቀሙ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ከዓለም የኤሌክትሪክ ፍጆታ 40 በመቶ የሚሆነውን ያቀርባሉ። ከዓለም የድንጋይ ከሰል ላኪ አገሮች የአንደኝነቱን ቦታ የያዘችው አውስትራሊያ ስትሆን ለዓለም ገበያ ከሚቀርበው የድንጋይ ከሰል ሩብ የሚሆነውን ትሸፍናለች።
ይሁን እንጂ ወርልድ ዎች ኢንስቲትዩት በቅርቡ ያወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲህ ይላል:- “የድንጋይ ከሰልን ያህል ብዙ የካርቦን ጭስ የሚያወጣ ነዳጅ የለም። ከድንጋይ ከሰል የሚወጣው ካርቦን ከነዳጅ ዘይት ከሚወጣው 29 በመቶ፣ ከተፈጥሮ ጋዝ ከሚወጣው ደግሞ 80 በመቶ ይበልጣል። በመላው ዓለም ወደ ከባቢ አየር ከሚገባው ካርቦን 43 በመቶ የሚሆነው የሚወጣው ከድንጋይ ከሰል ሲሆን ይህም 27 ቢሊዮን ኩንታል ይደርሳል ተብሎ ይገመታል።” የድንጋይ ከሰል ሲቃጠል በከባቢ አየር ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት በተጨማሪ በሰው ልጆች ጤና ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል? አንድ ምሳሌ ብቻ ብንጠቅስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቅርቡ ያወጣው ግሎባል ኢንቫይሮመንት አውትሉክ የተባለ ሪፖርት “በቻይና በድንጋይ ከሰል ከሚጠቀሙ የኃይል ማመንጫዎች የሚወጣው ጭስና ጥቃቅን ብናኞች በ11 ትላልቅ ከተሞች የሚኖሩ 50,000 ሰዎች በየዓመቱ ያለ ዕድሜያቸው በሞት እንዲቀጩና 400,000 የሚያክሉ ሰዎች በአስም በሽታ እንዲጠቁ ምክንያት ሆነዋል” ብሏል።
ነዳጅ ዘይት:-
▪ በአሁኑ ጊዜ የመላው ዓለም የነዳጅ ዘይት ዕለታዊ ፍጆታ 75 ሚሊዮን በርሜል ደርሷል። ሁለት ትሪሊዮን በርሜል ይደርሳል ተብሎ ከሚገመተው የጠቅላላው ዓለም የነዳጅ ዘይት ክምችት ውስጥ 900 ቢሊዮን በርሜል የሚያህለው ጥቅም ላይ ውሏል። በአሁኑ የነዳጅ ዘይት ፍጆታ መሠረት የመላው ዓለም አቅርቦት የሚቆየው ለ40 ዓመት ብቻ እንደሆነ ይገመታል።
ይሁን እንጂ በ1998 ኮለን ካምፕቤል እና ዦን ላኸረር የተባሉት ጂኦሎጂስቶች “ከአሥር ዓመት በኋላ በቀላሉ ሊወጡ የሚችሉ የነዳጅ ክምችቶች የሚኖረውን ፍጆታ ማሟላት ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ” ብለው ነበር። እነዚህ የነዳጅ ኢንዱስትሪው ጠበብት እንደሚሉት “ብዙ ሰዎች በከርሰ ምድር ውስጥ ያለውን የነዳጅ ዘይት ክምችት ዛሬ ከየጉድጓዱ እንደልብ ማውጣት እንደሚቻለው እስከ መጨረሻዋ ጠብታ ድረስ አሟጥጦ መጠቀም የሚቻል ይመስላቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን አንድ የነዳጅ ጉድጓድ ወይም አንድ አገር ሊያቀርብ የሚችለው የነዳጅ ዘይት መጠን እያደገ ይሄድና ከነበረው ክምችት ግማሽ ያህሉ ካለቀ በኋላ ቀስ በቀስ እየቀነሰ ሄዶ ወደ ዜሮ ይደርሳል። ስለዚህ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው አንጻር ሲታይ ትልቅ ችግር የሚከሰተው የመላው ዓለም የነዳጅ ክምችት ሙሉ በሙሉ ተሟጥጦ ሲያልቅ ሳይሆን አቅርቦቱ እያሽቆለቆለ በሚሄድበት ጊዜ ነው።”
ታዲያ የነዳጅ ዘይት አቅርቦት ማሽቆልቆል ይጀምራል ተብሎ የሚታሰበው መቼ ነው? የነዳጅ ዘይት ጂኦሎጂስት የሆኑት ጆሰፍ ሪቫ “ይኖራል ተብሎ የታቀደው የነዳጅ ዘይት አቅርቦት ጭማሪ ኢንተርናሽናል ኢነርጂ ኤጀንሲ በ2010 ይደርሳል ብሎ ከሚጠብቀው የመላው ዓለም ፍጆታ በግማሽ ያነሰ ነው” ብለዋል። ኒው ሳይንቲስት እንደሚከተለው በማለት ያስጠነቅቃል:- “ፍጆታው እየጨመረ ባለበት ሁኔታ አቅርቦቱ ከቀነሰ የነዳጅ ዘይት ዋጋ በጣም ከፍ ሊል ወይም ሊዋዥቅ ይችላል። ይህ ደግሞ ምግብና ሌሎች ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችን በማጓጓዙ ሥራ ላይ ችግር ከማስከተሉም በላይ አገሮች ያለውን ነዳጅ ለመቀራመት ሲሻሙ ጦርነት ሊነሳ ይችላል።”
አንዳንድ ተንታኞች የነዳጅ ዘይት አቅርቦት እየተመናመነ መሄዱ አሳሳቢ ችግር እንደሆነ ሲናገሩ ሌሎቹ ደግሞ በነዳጅ ዘይት መጠቀማችንን ካላቆምን ልንወጣ በማንችለው ችግር ውስጥ እንደምንገባ ይናገራሉ። ጀረማያ ክሪደን ኡትኔ ሪደር በተባለው መጽሔት ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ከነዳጅ ዘይት ማለቅ የባሰ ችግር የሚገጥመን ነዳጅ ዘይት ያላለቀ እንደሆነ ብቻ ነው። ነዳጅ ዘይት በማቃጠል የምንፈጥረው ካርቦን ዳይኦክሳይድ የምድራችን ሙቀት እየጨመረ እንዲሄድ ቢያደርግም አሁንም የአካባቢ ደኅንነትና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ውይይት የሚደረግባቸው የተነጣጠሉና የማይገናኙ ነገሮች እንደሆኑ ተደርጎ ነው።” የአውስትራሊያ ብሮድካስቲንግ ኮሚሽን አንድ አገር ብቻ እንኳ ነዳጅ ዘይት በከፍተኛ ሁኔታ መጠቀሙ ምን ዓይነት ውጤት እንዳስከተለ ሲያመለክት “በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙት 26 ሚሊዮን የሚያክሉ ተሽከርካሪዎች ይህች አገር ወደ ከባቢ አየር ከምታስገባውና የምድራችን ሙቀት እንዲጨምር ከሚያደርገው ካርቦን ዳይኦክሳይድ አንድ ሦስተኛውን ያመነጫሉ (በዚህ ብክለት ሳቢያ በየዓመቱ 10,000 ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ)” ብሏል።
የተፈጥሮ ጋዝ:-
▪ ኢንተርናሽናል ኢነርጂ አውትሉክ 2003 የተባለው ሪፖርት እንደገለጸው በሚቀጥሉት 20 ዓመታት “የተፈጥሮ ጋዝ በመላው ዓለም ከፍተኛ እድገት የሚያሳይ ዋነኛ የኃይል ምንጭ ይሆናል።” ከከርሰ ምድር ከሚወጡ ነዳጆች በሙሉ አካባቢን በመበከል ዝቅተኛውን ደረጃ የያዘው የተፈጥሮ ጋዝ ሲሆን በምድራችን ውስጥ በጣም ብዙ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ይገኛል።
ይሁን እንጂ ናቹራል ጋስ ሰፕላይ አሶስዬሽን የተባለ በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኝ ድርጅት እንዲህ ይላል:- “የተፈጥሮ ጋዝ ተቆፍሮ እስኪወጣ ድረስ ምን ያህል ክምችት እንዳለ ሊያውቅ የሚችል ሰው የለም። ሁሉም መላ ምቶች የተለያዩ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት የሚሰጡ ናቸው። . . . ስለዚህ ምን ያህል የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አለ ለሚለው ጥያቄ ቁርጥ ያለና የተረጋገጠ መልስ መስጠት አስቸጋሪ ነው።”
አንደኛውና ዋነኛው የተፈጥሮ ጋዝ ክፍል ሚቴን ሲሆን “ይህ ጋዝ የምድራችንን ሙቀት በመጨመር ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታል። እንዲያውም ሚቴን ሙቀት አምቆ የመያዝ አቅሙ ከካርቦን ዳይኦክሳይድ በ21 እጥፍ ይበልጣል” ሲል ቀደም ብሎ የተገለጸው ድርጅት አመልክቷል። ይሁን እንጂ ይህ የመረጃ ምንጭ ኢንቫይሮመንታል ፕሮቴክሽን ኤጀንሲ እና ጋስ ሪሰርች ኢንስቲትዩት የተባሉት የዩናይትድ ስቴትስ ተቋሞች ያደረጉትን ጥናት በመጥቀስ “ከነዳጅ ዘይትና ከድንጋይ ከሰል የሚወጣውን ጭስ ለመቀነስ ስንል የተፈጥሮ ጋዝ በስፋት መጠቀማችን ሚቴን እንዲጨምር ቢያደርግም ከሌሎቹ ጋዞች ይልቅ ሚቴን የሚያስከትለው ጉዳት በእጅጉ የተሻለ ነው” ብሏል።
አቶሚክ ኢነርጂ:-
▪ አውስትራሊያን ጂኦግራፊክ የተባለው መጽሔት “430 የሚያክሉ የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች መላው ዓለም ከሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል 16 በመቶ የሚሆነውን ያመነጫሉ” በማለት ዘግቧል። ኢንተርናሽናል ኢነርጂ አውትሉክ 2003 የተባለው ሪፖርት አሁን ሥራ ላይ ከዋሉት የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫዎች በተጨማሪ እየተደረገ ስላለው ሁኔታ ሲዘግብ “ከየካቲት 2003 ወዲህ በመላው ዓለም 35 የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫዎች በመገንባት ላይ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል 17ቱ የሚገኙት በመልማት ላይ ባሉት የእስያ አገሮች ነው” ብሏል።
የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫዎች በቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት፣ ቸርኖብል ውስጥ በ1986 የደረሰውን ዓይነት ከፍተኛ እልቂት የማስከተል አደጋ ቢኖራቸውም አሁንም የእነዚህ የኃይል ማመንጫዎች ጥገኛ መሆን አልቀረም። ኒው ሳይንቲስት እንደዘገበው “አሁን በሥራ ላይ የሚገኙት የአሜሪካ የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫዎች በመሰነጣጠቅና በዝገት የተጎዱ ናቸው።” በመጋቢት 2002፣ በኦሃዮ የሚገኘው የዴቪስ ቤስ ኃይል ማመንጫ በውስጡ በተፈጠረ ዝገት ምክንያት “ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር።”
የኃይል አቅርቦት አቅም ውስን መሆኑንና በአሁኑ ጊዜ የምንገለገልባቸው የኃይል ምንጮች የሚያስከትሉትን ችግር ስንመለከት ‘የሰው ልጅ ማቆሚያ የሌለውን የኃይል ጥማቱን ለማርካት ሲል ምድርን ፈጽሞ የሚያበላሽበት ደረጃ ላይ ይደርስ ይሆን?’ የሚል ጥያቄ ይነሳል። ብክለት የማያስከትልና አስተማማኝ የሆነ አማራጭ የኃይል ምንጭ እንደሚያስፈልገን ግልጽ ነው። ይሁንና እነዚህ የኃይል ምንጮች በቀላሉ የሚገኙ ናቸው? አቅማችንስ ይፈቅድልናል?