በዛሬው ጊዜ ለመለከት ድምፅ ምላሽ መስጠት
ይሖዋ በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ሕዝቡን እየመራና በመንፈሳዊ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እያቀረበ እንደሆነ ሁላችንም እናምናለን። (2 ጢሞ. 3:1) ይሖዋ ለሚሰጠው አመራር ምላሽ መስጠት ግን የእያንዳንዳችን ፋንታ እንደሆነ የታወቀ ነው። ያለንበት ሁኔታ እስራኤላውያን በምድረ በዳ ከነበሩበት ሁኔታ ጋር ሊነጻጸር ይችላል። እስራኤላውያን ለተለያዩ የመለከት ድምፆች ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸው ነበር።
ይሖዋ፣ ወጥ የሆነ ብር ጠፍጥፎ ሁለት መለከቶች እንዲሠራ ሙሴን አዞት ነበር፤ እነዚህ መለከቶች “ማኅበረሰቡን ለመሰብሰብና ሕዝቡ ከሰፈረባቸው ቦታዎች ተነስቶ እንዲሄድ ምልክት ለመስጠት” የሚያገለግሉ ነበሩ። (ዘኁ. 10:2) ሕዝቡ ምን እንደሚጠበቅበት ለመጠቆም ካህናቱ መለከቶቹን በተለያየ መንገድ ይነፉ ነበር። (ዘኁ. 10:3-8) በዛሬው ጊዜም የአምላክ ሕዝቦች በተለያዩ መንገዶች መመሪያ ይሰጣቸዋል። በጥንት ዘመን በመለከት መመሪያ ከሚሰጥበት መንገድ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ በዛሬው ጊዜ መመሪያ የምናገኝባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት። በዘመናችን ያሉ የአምላክ ሕዝቦች በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ጥሪ ይቀርብላቸዋል፤ የተሾሙ የበላይ ተመልካቾች ሥልጠና ይሰጣቸዋል እንዲሁም ለሁሉም ጉባኤዎች በሚተላለፉ ቲኦክራሲያዊ መመሪያዎች ላይ ማሻሻያ ወይም ማስተካከያ ይደረጋል።
ለትላልቅ ስብሰባዎች የሚቀርብ ጥሪ
ይሖዋ “መላው ማኅበረሰብ” በማደሪያ ድንኳኑ በስተ ምሥራቅ ባለው መግቢያ እንዲሰበሰብ ሲፈልግ ካህናቱ ሁለቱንም መለከቶች ይነፉ ነበር። (ዘኁ. 10:3) በማደሪያ ድንኳኑ ዙሪያ በአራት ምድቦች ተከፋፍለው ይሰፍሩ የነበሩት ሁሉም ነገዶች ይህን ድምፅ መስማት ይችላሉ። በመግቢያው አቅራቢያ የሰፈሩት ሰዎች በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ መምጣት ይችሉ ነበር። ራቅ ብለው የሰፈሩት ሌሎቹ ሰዎች ደግሞ ወደ ቦታው ለመድረስ የበለጠ ጊዜና ጥረት ይጠይቅባቸው ይሆናል። በዚያም ሆነ በዚህ፣ ይሖዋ ማኅበረሰቡ በሙሉ እንዲሰበሰብና እሱ ከሚሰጠው መመሪያ እንዲጠቀም ይፈልግ ነበር።
በዛሬው ጊዜ ወደ ማደሪያው ድንኳን ሄደን አንሰበሰብም፤ ሆኖም የአምላክ ሕዝቦች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ እንድንገኝ ጥሪ ይቀርብልናል። ከእነዚህ ስብሰባዎች መካከል የክልል ስብሰባዎችና ሌሎች ልዩ ፕሮግራሞች ይገኙበታል፤ በዚያም በጣም አስፈላጊ ትምህርትና መመሪያ እናገኛለን። በዓለም ዙሪያ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርብላቸው ትምህርት አንድ ዓይነት ነው። በመሆኑም ጥሪውን ተቀብለው በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሁሉ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ካቀፈው ከዚህ ደስተኛ ቡድን ጋር የመሰብሰብ አጋጣሚ ያገኛሉ። አንዳንዶች በስብሰባዎቹ ላይ ለመገኘት ረዘም ያለ ርቀት መጓዝ ያስፈልጋቸዋል። ሆኖም ጥሪውን ተቀብለው በስብሰባው ላይ የሚገኙ ሁሉ ጥረታቸው የሚክስ እንደሆነ ይሰማቸዋል።
እነዚህ ትላልቅ ስብሰባዎች ከሚካሄዱባቸው ቦታዎች በጣም ርቀው ገለልተኛ በሆኑ አካባቢዎች ስለሚኖሩ ወንድሞችና እህቶችስ ምን ማለት ይቻላል? ለዘመናዊ ቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና ብዙዎቹ ፕሮግራሙን መከታተል ችለዋል፤ እንዲያውም በስብሰባው ቦታ ካሉት ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር አብረው የተሰበሰቡ ያህል ሆኖ ተሰምቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በዋናው መሥሪያ ቤት ተወካይ ጉብኝት ወቅት የቤኒን ቅርንጫፍ ቢሮ ፕሮግራሙን በአርሊት፣ ኒጀር ለሚገኙ ወንድሞች አስተላልፎ ነበር፤
አርሊት በሰሃራ በረሃ የምትገኝ ማዕድን የሚወጣባት ትንሽ ከተማ ናት። ስብሰባውን 21 ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች መከታተል ችለዋል። እነዚህ ሰዎች የሚኖሩት በጣም ርቀው ቢሆንም በስብሰባው ላይ ከተገኙት 44,131 ሰዎች ጋር አብረው እንደተሰበሰቡ ተሰምቷቸዋል። አንድ ወንድም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ይህን ፕሮግራም ስላስተላለፋችሁልን ከልብ እናመሰግናችኋለን። ዝግጅቱ፣ ምን ያህል እንደምታስቡልን እንድናስተውል ያደረገን ሌላ አጋጣሚ ነው።”ለተሾሙ የበላይ ተመልካቾች የሚቀርብ ጥሪ
አንዱ መለከት ብቻ በሚነፋበት ጊዜ ወደ መገናኛው ድንኳን እንዲመጡ የሚጠበቅባቸው “የእስራኤል የሺህ አለቆች ብቻ” ነበሩ። (ዘኁ. 10:4) በዚያም ሙሴ መረጃ እና ሥልጠና ይሰጣቸዋል። ይህም በየነገዶቻቸው የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ይረዳቸዋል። አንተ ከእነዚህ አለቆች አንዱ ብትሆን ኖሮ በቦታው ለመገኘትና ከትምህርቱ ተጠቃሚ ለመሆን የምትችለውን ሁሉ አታደርግም ነበር?
በዛሬው ጊዜ ያሉ የጉባኤ ሽማግሌዎች “አለቆች” አይደሉም፤ በአደራ በተሰጣቸው የአምላክ መንጋ ላይ ሥልጣናቸውን ማሳየትም የለባቸውም። (1 ጴጥ. 5:1-3) ያም ሆኖ መንጋውን እንደ እረኛ ሆነው ለመንከባከብ የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ የታወቀ ነው። ስለዚህ ተጨማሪ ሥልጠና እንዲያገኙ ጥሪ ሲቀርብላቸው ለምሳሌ በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት እንዲካፈሉ ሲጋበዙ ግብዣውን በደስታ ይቀበላሉ። በዚህ ሥልጠና ወቅት ሽማግሌዎች የጉባኤ ጉዳዮችን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን የሚያስችል ትምህርት ያገኛሉ። ይህም የእነሱንም ሆነ የሁሉንም የጉባኤው አባላት መንፈሳዊነት ለማጠናከር አስተዋጽኦ ያደርጋል። አንተ በግልህ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ባትካፈልም እንኳ በትምህርት ቤቱ ሥልጠና ካገኙት ወንድሞች ጥቅም እያገኘህ ነው።
ማስተካከያ እንዲደረግ የሚቀርብ ጥሪ
አንዳንድ ጊዜ እስራኤላውያን ካህናት፣ የመለከቱን ድምፅ እያለዋወጡ ይነፉ ነበር። ይህም ይሖዋ፣ መላው ማኅበረሰብ ከሰፈረበት እንዲንቀሳቀስ እንደፈለገ የሚጠቁም ነበር። (ዘኁ. 10:5, 6) ሕዝቡ ከሰፈሩበት የሚንቀሳቀሱት በጣም በተደራጀ መንገድ ነው፤ ሆኖም ይህን ማድረግ ለእያንዳንዱ ግለሰብ ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነገር ነበር። አንዳንዶች ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ አመንትተው ይሆናል። ለምን?
ምናልባትም አንዳንዶች፣ መለከቱ ቶሎ ቶሎ እንዲሁም ባልተጠበቀ ሰዓት እየተነፋ እንደሆነ ተሰምቷቸው ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “እስራኤላውያን ደመናው በማደሪያ ድንኳኑ ላይ እስካለ ድረስ . . . በሰፈሩበት ይቆያሉ” ይላል። ሆኖም “አንዳንድ ጊዜ . . . ደመናው የሚቆየው ከምሽት እስከ ጠዋት ድረስ ብቻ ነበር።” በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ‘ለሁለት ቀን፣ ለአንድ ወር ወይም ረዘም ላለ ጊዜ’ ሊቆይ ይችላል። (ዘኁ. 9:21, 22) ደግሞስ ሕዝቡ ከቦታ ወደ ቦታ የተጓዙት ምን ያህል ጊዜ ነው? ዘኁልቁ 33 እስራኤላውያን የሰፈሩባቸውን 40 ያህል ቦታዎች ይጠቅሳል።
አንዳንድ ጊዜ እስራኤላውያን ጥላ ያለበት ቦታ ላይ ሊሰፍሩ ይችላሉ። “ጭልጥ ያለና የሚያስፈራ” በተባለው “ምድረ በዳ” እንዲህ ያለ ቦታ ላይ መስፈር አስደሳች እንደሚሆን የታወቀ ነው። (ዘዳ. 1:19) በዚህም የተነሳ፣ ከሰፈሩበት ተነስተው ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ምቾታቸውን እንደሚያሳጣቸው የሚሰማቸው ይኖሩ ይሆናል።
ነገዶቹ መንቀሳቀስ ሲጀምሩ ደግሞ አንዳንዶች ተራቸው እስኪደርስ በትዕግሥት መጠበቅ ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። እየተለዋወጠ የሚነፋውን የመለከት ድምፅ ሁሉም ቢሰሙም ሁሉም በአንድ ጊዜ መንቀሳቀስ አይችሉም። ይህ የመለከት ድምፅ በስተ ምሥራቅ የሰፈሩት ነገዶች ማለትም የይሁዳ፣ የይሳኮርና የዛብሎን ነገዶች መንቀሳቀስ እንዲጀምሩ የሚጠቁም ነበር። (ዘኁ. 2:3-7፤ 10:5, 6) እነዚህ ነገዶች ተነስተው ሲጓዙ ካህናቱ ለሁለተኛ ጊዜ የመለከቱን ድምፅ እያለዋወጡ ይነፋሉ፤ ይህም በስተ ደቡብ የሰፈሩት ሦስቱ ነገዶች መንቀሳቀስ እንዲጀምሩ ምልክት የሚሰጥ ነበር። መላው ማኅበረሰብ እስኪነሳ ድረስ ካህናቱ በዚህ መንገድ መለከቱን መንፋታቸውን ይቀጥላሉ።
አንተም አንዳንድ ድርጅታዊ ማስተካከያዎችን መቀበል ከብዶህ ሊሆን ይችላል። በርከት ያሉ ያልተጠበቁ ማስተካከያዎች እንደተደረጉ ይሰማህ ይሆናል። አሊያም ደግሞ አንዳንድ አሠራሮችን ትወዳቸው ስለነበር ማስተካከያ መደረጉ አላስደሰተህ ይሆናል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ከእነዚህ ለውጦች ጋር መላመድ ትዕግሥት ጠይቆብህ ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ የተደረገውን ለውጥ ለመቀበል ጥረት የምናደርግ ከሆነ የአምላክን በረከት የማየት አጋጣሚ እናገኛለን።
በሙሴ ዘመን ይሖዋ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወንዶችን፣ ሴቶችንና ልጆችን በምድረ በዳ መርቷል። እሱ ባይንከባከባቸውና ባይመራቸው ኖሮ በሕይወት መቀጠል አይችሉም ነበር። ዛሬም መንፈሳዊነታችንን ጠብቀን መኖር የቻልነው ይሖዋ ስለሚመራን ነው። እንዲያውም በመንፈሳዊ ጠንካሮች መሆን ችለናል! እንግዲያው ሁላችንም፣ ታማኝ እስራኤላውያን እንዳደረጉት ሁሉ ለመለከቶቹ ድምፅ ምላሽ ለመስጠት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ!