በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ ምን ፈተናዎችን አልፏል?

መጽሐፍ ቅዱስ በተቃዋሚዎች ከመጥፋት ተርፏል

መጽሐፍ ቅዱስ በተቃዋሚዎች ከመጥፋት ተርፏል

ፈተናው፦ ብዙ የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የሚቃወም አቋም ይዘው ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ሥልጣናቸውን በመጠቀም ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይኖራቸው እንዲሁም መጽሐፉን እንዳያሳትሙ ወይም እንዳይተረጉሙ ከልክለዋል። ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት፦

  • በ167 ዓ.ዓ. ገደማ፦ አይሁዳውያን የግሪክን ሃይማኖት እንዲቀበሉ ለማስገደድ ይጥር የነበረው ሰሉሲዳዊው ንጉሥ አንታይከስ ኤፒፋነስ ሁሉም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች እንዲቃጠሉ አዋጅ አውጥቶ ነበር። የታሪክ ምሁር የሆኑት ሃይንሪክ ግሬትስ እንደጻፉት የንጉሡ ባለሥልጣናት “የሕጉን ጥቅልሎች ባገኙበት ቦታ ሁሉ ያቃጥሉ ነበር፤ እንዲሁም ጥቅልሎቹን በማንበብ ብርታትና መጽናኛ ለማግኘት ይሞክሩ የነበሩ ሰዎችን ገድለዋል።”

  • መካከለኛው ዘመን፦ አንዳንድ የካቶሊክ መሪዎች ምዕመናኑ የካቶሊክን ቀኖና ትተው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ነገር በመስበካቸው ስለተበሳጩ በላቲን ከተዘጋጀው የመዝሙር መጽሐፍ በቀር ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ይዘው የተገኙ ሰዎችን መናፍቃን በማለት ይፈርጇቸው ነበር። አንድ የቤተ ክርስቲያን ምክር ቤት “መናፍቃን እንዳሉባቸው የሚጠረጠሩ ቤቶችንና የምድር ቤት ክፍሎችን ሁሉ በመፈተሽ መናፍቃንን በትጋት፣ በታማኝነትና ያለማሰለስ ፈልገው እንዲያመጡ” የሚያዝዝ መመሪያ ለሠራተኞቹ ሰጥቶ ነበር። “መናፍቃን የተገኙባቸው ቤቶች በሙሉ መቃጠል ነበረባቸው።”

የመጽሐፍ ቅዱስ ጠላቶች መጽሐፉን ለማጥፋት ያደረጉት ጥረት ቢሳካላቸው ኖሮ የያዘው መልእክትም ይጠፋ ነበር።

በዊሊያም ቲንደል የተተረጎመው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ እገዳ ተጥሎበት የነበረ ከመሆኑም ባሻገር እንዲቃጠል ተደርጓል፤ በ1536 ደግሞ ቲንደል ራሱ ተገድሏል፤ ሆኖም ይህ መጽሐፍ ቅዱስ እስካሁን ድረስ ሳይጠፋ ቆይቷል

መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ፈተና ያለፈው እንዴት ነው? የንጉሥ አንታይከስ ዘመቻ ያነጣጠረው በእስራኤል ላይ ነበር፤ ሆኖም በወቅቱ የአይሁድ ማኅበረሰብ በሌሎች አገሮች ውስጥም ይኖር ነበር። እንዲያውም አንዳንድ ምሁራን እንደገመቱት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ላይ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት አይሁዳውያን የሚኖሩት ከእስራኤል ውጭ ነበር። አይሁዳውያን በየምኩራቦቻቸው ውስጥ የቅዱሳን መጻሕፍትን ቅጂዎች ያስቀምጡ የነበረ ሲሆን ክርስቲያኖችን ጨምሮ ቀጣዮቹ ትውልዶች ሁሉ የተጠቀሙት በእነዚህ ቅጂዎች ነው።—የሐዋርያት ሥራ 15:21

በመካከለኛው ዘመን የኖሩ ለመጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ስደትን በድፍረት የተቋቋሙ ከመሆኑም ሌላ ቅዱሳን መጻሕፍትን መተርጎማቸውንና መገልበጣቸውን ቀጥለው ነበር። በ15ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ የማተሚያ መሣሪያ ከመፈልሰፉ በፊትም እንኳ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በ33 ቋንቋዎች ተዘጋጅተው ነበር። ከዚያ ወዲህ መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስገርም ፍጥነት መተርጎምና መታተም ጀመረ።

ውጤቱ፦ ኃያል ነገሥታትና የተሳሳተ አካሄድ የተከተሉ ቀሳውስት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት የሞከሩ ቢሆንም በስፋት በመተርጎምና በመሰራጨት ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው መጽሐፍ ሆኗል። መጽሐፉ የአንዳንድ አገሮችን ሕግና ቋንቋ የቀረጸ ከመሆኑም ሌላ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል።