ከሰማይ ወፎች የምናገኘው ትምህርት
“እስቲ . . . በሰማያት የሚበርሩ [ወፎችን] ጠይቅ፤ እነሱም ይነግሩሃል። የይሖዋ እጅ ይህን ማድረጉን፣ ከእነዚህ ሁሉ መካከል የማያውቅ ማን ነው?” —ኢዮብ 12:7, 9
ሦስት ሺህ ከሚበልጡ ዓመታት በፊት የኖረው ኢዮብ የሰማይ ወፎች የአምላክን ሥራዎች በተመለከተ ብዙ የሚያስተምሩን ነገር እንዳለ ተገንዝቦ ነበር። በተጨማሪም ወፎች ያሏቸው ለየት ያሉ ባሕርያት አንድን ነገር በምሳሌያዊና ዘይቤያዊ በሆነ መንገድ ለመግለጽ ተስማሚ እንዲሆኑ ያደርጓቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ወፎች የተገለጹት ነገሮች ሕይወትንና ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና በተመለከተ ጠቃሚ ትምህርት ይሰጡናል። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።
ወንጭፊት ጎጆ የምትሠራበት ቦታ
የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ወንጭፊት የምትባለውን፣ ብዙውን ጊዜ በሕንጻዎች ጣሪያ ሥር ጎጆዋን የምትሠራውን ወፍ በሚገባ ያውቋት ነበር። ከእነዚህ ወፎች አንዳንዶቹ ሰለሞን በገነባው ቤተ መቅደስ ጣሪያ ሥር ጎጇቸውን ሠርተው ነበር። በቤተ መቅደሱ አካባቢ ጎጇቸውን የሚሠሩት እነዚህ ወፎች ይህ ቦታ በየዓመቱ ጫጩቶቻቸውን ያለ ችግር ማሳደግ የሚችሉበት አስተማማኝ ስፍራ ሳይሆንላቸው አልቀረም።
በየስድስት ወሩ ለአንድ ሳምንት ያህል በቤተ መቅደሱ ያገለግል የነበረውና ከቆሬ ልጆች አንዱ የሆነው የመዝሙር 84 ጸሐፊ፣ በቤተ መቅደሱ አካባቢ የሚገኙትን የወፍ ጎጆዎች አስተውሎ ነበር። በይሖዋ ቤት ቋሚ መኖሪያ እንዳገኘችው ወንጭፊት ለመሆን ተመኝቶ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ታላቁ የማደሪያ ድንኳንህ ምንኛ ያማረ ነው! ሁለንተናዬ የይሖዋን ቅጥር ግቢዎች እጅግ ናፈቀ፤ አዎ፣ በጣም ከመጓጓቴ የተነሳ ዛልኩ። . . . ንጉሤና አምላኬ የሆንከው የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣ ታላቁ መሠዊያህ ባለበት አቅራቢያ፣ ወፍ እንኳ በዚያ ቤት ታገኛለች፤ ወንጭፊትም ጫጩቶቿን የምታሳድግበት ጎጆ ለራሷ ትሠራለች።” (መዝሙር 84:1-3) ታዲያ እኛስ ከልጆቻችን ጋር ሆነን ከአምላክ ሕዝቦች ጋር በጉባኤ ለመሰብሰብ እንዲህ ያለ ጉጉት አለን?—መዝሙር 26:8, 12
ራዛ ጊዜዋን ታውቃለች
ነቢዩ ኤርምያስ “በሰማይ የምትበረው ራዛ እንኳ ወቅቷን ታውቃለች” በማለት ጽፏል። ኤርምያስ ራዛዎች ተስፋይቱን ምድር አቋርጠው እንደሚፈልሱ በሚገባ ያውቅ እንደነበር አያጠራጥርም። ከ300,000 በላይ የሚሆኑ ነጭ ራዛዎች በጸደይ ወቅት ከአፍሪካ ተነስተው በዮርዳኖስ ሸለቆ አድርገው ወደ ሰሜናዊ አውሮፓ ሲፈልሱ ታይተዋል። በተፈጥሮ ያገኙት ጊዜ ጠቋሚ ሰዓት በበጋ ወቅት ወደ መራቢያ ስፍራቸው እንዲመለሱ ያነሳሳቸዋል። ከቦታ ወደ ቦታ እንደሚፈልሱ ሌሎች ወፎች ሁሉ ራዛዎችም “የሚመለሱበትን ጊዜ ያከብራሉ።”—ኤርምያስ 8:7
ኮሊንስ አትላስ ኦቭ በርድ ማይግሬሽን የተባለው መጽሐፍ “ፍልሰትን በጣም አስደናቂ የሚያደርገው በደመ ነፍስ የሚደረግ መሆኑ ነው” በማለት ይናገራል። ይሖዋ አምላክ ከቦታ ወደ ቦታ ለሚፈልሱ ወፎች ወቅቶችን መለየት የሚችሉበት ደመ ነፍሳዊ ጥበብ የሰጣቸው ሲሆን ለሰው ልጆች ግን ጊዜያትንና ወቅቶችን እንዲያስተውሉ ችሎታ ሰጥቷቸዋል። (ሉቃስ 12:54-56) ራዛዎች ካላቸው ደመ ነፍሳዊ ጥበብ በተለየ መልኩ የሰው ልጆች በዘመናችን የሚፈጸሙት ክንውኖች ያላቸውን ትርጉም መረዳት እንዲችሉ ስለ አምላክ እውቀት ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። በኤርምያስ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን እንዲህ ያሉትን ምልክቶች ትርጉም አላስተዋሉም ነበር። አምላክ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋን ቃል ንቀዋል፤ ታዲያ ምን ዓይነት ጥበብ ይኖራቸዋል?”—ኤርምያስ 8:9
አሁን የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ በማለት በሚጠራው ጊዜ ውስጥ መሆኑን የሚያሳይ በቂ ማስረጃ አለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) የራዛን ምሳሌ በመከተል ‘ወቅቱን’ ታስተውላለህ?
ንስር ከሩቅ ይመለከታል
ንስር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል፤ በተስፋይቱ ምድር ንስር ሲያንዣብብ መመልከት የተለመደ ነገር ነበር። ንስር ከፍ ባለ ቋጥኝ ላይ ከሚገኘው ጎጆው ሆኖ “የሚበላውን ነገር ይፈልጋል፤ዓይኖቹም እጅግ ሩቅ ወደሆነ ቦታ ይመለከታሉ።” (ኢዮብ 39:27-29) ንስር፣ የማየት ችሎታው በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ 1 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝን ጥንቸል እንኳ ማየት እንደሚችል ይነገርለታል።
ንስር “እጅግ ሩቅ ወደሆነ ቦታ” የመመልከት ችሎታ እንዳለው ሁሉ ይሖዋም የወደፊቱን ጊዜ አሻግሮ መመልከት ይችላል። ስለሆነም ይሖዋ አምላክ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ከመጀመሪያ መጨረሻውን፣ ገና ያልተከናወኑትንም ነገሮች ከረጅም ጊዜ በፊት አስቀድሜ እናገራለሁ።” (ኢሳይያስ 46:10) ይሖዋ የሚሰጠንን ምክር የምንሰማ ከሆነ እሱ ካለው ተወዳዳሪ የሌለው ጥበብና የወደፊቱን ጊዜ የማወቅ ችሎታ ጥቅም ማግኘት እንችላለን።—ኢሳይያስ 48:17, 18
መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ኃይላቸው ይታደሳል። እንደ ንስር በክንፍ ወደ ላይ ይወጣሉ” በማለት በአምላክ የሚታመኑ ሰዎችንም ከንስር ጋር ያመሳስላቸዋል።(ኢሳይያስ 40:31) ንስር በሚበርበት ወቅት ሞቃት አየር ወደ ላይ የሚወጣባቸውን ተርማል በመባል የሚጠሩ መስመሮች በመከተል ከፍ እያለ ይሄዳል። ንስሩ ተርማል ያለበትን መስመር ካገኘ በኋላ እዚያ ቦታ ላይ ሲያንዣብብ አየሩ እየገፋ ወደ ላይ ይዞት ይወጣል። ንስር ወደ ላይ የሚመጥቀውና ረጅም ርቀት በአየር ላይ የሚንሳፈፈው በራሱ ኃይል ብቻ አይደለም። በተመሳሳይም በይሖዋ የሚታመኑ ሰዎች እሱ ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ እንደሚሰጣቸው መጠበቅ ይችላሉ።—2 ቆሮንቶስ 4:7, 8
‘ዶሮ ጫጩቶቿን እንደምትሰበስብ’
ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ የአይሁድን ዋና ከተማ ቆም ብሎ ተመልክቶ ነበር። እንዲህ አለ፦ “ኢየሩሳሌም፣ ኢየሩሳሌም፣ ነቢያትን የምትገድል! ወደ እሷ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግር! ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ እኔም ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግኩ! እናንተ ግን አልፈለጋችሁም።”—ማቴዎስ 23:37
ወፎች በደመ ነፍስ ከሚያከናውኗቸው ነገሮች ዋነኛው ጫጩቶቻቸውን ከአደጋ መጠበቅ ነው። እንደ ዶሮ ያሉ በመሬት ላይ የሚኖሩ ወፎች አደጋ መምጣቱን ለማወቅ በንቃት መከታተል ይጠበቅባቸዋል። ዶሮ፣ ጭልፊት ከላይ እያንዣበበ መሆኑን ካስተዋለች ከፍ ያለ ጩኸት በማሰማት ማስጠንቀቂያ ትሰጣለች፤ ጫጩቶቿም ይህን ሲሰሙ ተሯሩጠው በመምጣት በክንፎቿ ሥር ይሸሸጋሉ። ጫጩቶቹ በእናታቸው ክንፍ ውስጥ ከሚያቃጥል ፀሐይም ሆነ ከከባድ ዝናብ መጠለያ ያገኛሉ። ኢየሱስም በተመሳሳይ ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች መንፈሳዊ መጠለያና ጥበቃ ሊሰጣቸው ፈልጎ ነበር። ዛሬም ኢየሱስ በዕለታዊ ሕይወታችን ከሚያጋጥመን ሸክምና ጭንቀት እረፍት ለማግኘት ወደ እሱ እንድንመጣ ጋብዞናል።—ማቴዎስ 11:28, 29
በእርግጥም ከወፍ ዝርያዎች ብዙ የምንማረው ነገር አለ። ወፎች የሚያደርጓቸውን አንዳንድ ነገሮች ስትመለከት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ወፎች የተጠቀሱትን ምሳሌያዊ አነጋገሮች ለማስታወስ ሞክር። ስለ ወንጭፊት ስታስብ ይሖዋ ለሚመለክበት ቤት አድናቆት ሊኖርህ እንደሚገባ ትዝ ይበልህ። እንደ ንስር ወደ ላይ እንድትወጣ የሚያስችልህ ተስፋ እንዲኖርህ ወደ ይሖዋ ቅረብ። ዶሮ በክንፎቿ ጫጩቶቿን እንደምትከልል ሁሉ አንተም መንፈሳዊ ጥበቃ እንድታገኝ የሚረዳህን እውነት ለማግኘት ወደ ኢየሱስ ተጠጋ። እንዲሁም የራዛን ምሳሌ በማስታወስ የምንኖርበትን ጊዜ ለይተው የሚያሳውቁ በዓለም ላይ የሚፈጸሙ ክንውኖችን ለማስተዋል ንቁ ሁን።